1914—ዓለምን ያስደነገጠው ዓመት
“ከ1914-18 የተደረገው ታላቅ ጦርነት ያንን ዘመን ከዘመናችን የሚለይ ምልክት ሆኗል። ብዙ ሕይወትን በመደምሰስ ሰዎች የነበራቸውን እምነት በማጥፋት፣ የሰዎችን አስተሳሰብ በመለወጥ ተስፋ የመቁረጥን የማይድን ቁስል ትቶ በማለፍ በሁለት ዘመኖች መካከል በአካላዊም ሆነ በስነ-ልቦና ትልቅ ልዩነትን የፈጠረ ጦርነት ነው።”—ትምክህተኛው ግንብ—1890–1914 ከጦርነቱ በፊት የነበረው የዓለም ገጽታ ባርባራ ቱቸማን እንደጻፈው
“በዚህ ከፍተኛ ሃያኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ወጣት የነበሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ገና በሕይወት ስላሉ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ነገሩ የታሪክ ክፍል ነው።”— በሊን ማክ ዶናልድ የተዘጋጀ፣ 1914 የተሰኘ መጽሐፍ በ1987 የታተመ
ስለ 1914 ለመናገር ለምን ፍላጐት አደረብን? ‘እኔን የሚመለከተኝ የወደፊቱ ጊዜ ነው እንጂ ያለፈው አይደለም’ ብለህ ትናገር ይሆናል። የመሬት ብክለት፣ የቤተሰብ መፈራረስ፣ የወንጀል መጨመር፣ የአእምሮ በሽታና ሥራ አጥነት እንደነዚህ የመሰሉ ችግሮች የሰውን የወደፊት ሕይወት ጨለማ አስመስለውታል። ይሁን እንጂ የ1914ን ትርጉም የሚመራመሩ ብዙ ሰዎች ስለወደፊቱ ጊዜ የተሻለ ይሆናል የሚል ተስፋ ለማድረግ በቂ መሰረት አግኝተዋል።
በ1914 የሰው ዘር “የምጥ ጣር”ተብሎ የተጠራው ሁኔታ እንደደረሰበት መጠበቂያ ግንብ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሲያብራራ ቆይቷል። ይህ አነጋገር ኢየሱስ ክርስቶስ ክፉው የሰው ሥርዓት ከመደምደሙ በፊት ስለሚሆኑት ነገሮች የተናገረው ታላቅ ትንቢት ክፍል ነው።—ማቴዎስ 24:7, 8
በ1914 የተከሰቱትን ታላላቅ ሁኔታዎች እስከዛሬ ድረስ ማስታወስ የሚችሉ ጥቂት ሰዎች አሉ። አምላክ ምድርን ከጥፋት ከማዳኑ በፊት ይህ በእድሜ የገፋ ትውልድ ሞቶ ያልቅ ይሆን? እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አገላለጽ ሞቶ አያልቅም። “እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደቀረበ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ሲል ኢየሱስ ቃል ገብቷል።—ማቴዎስ 24:33, 34
የ1914 ዓመት ለምን በታሪክ ትልቅ ቦታ እንዳለው ለመረዳት እስከ 1914 መካከለኛ ዓመት ድረስ ያለውን ሁኔታ እንመርምር። ከዚያ ዓመት በፊት የነበሩት ንጉሠ ነገሥቶች የሩሲያው ዛር ኒኮላስ፣ የጀርመኑ ኬይሰር ዊልሄል እና የኦስትሪያ-ሀንጋሪው ንጉሠ ነገሥት ፍራንዝ ጆሴፍ ታላላቅ ኃይል ነበራቸው። እነዚህ ሰዎች እያንዳንዳቸው ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተዋጊ ወታደሮችን አሰባስበው ሊይዙና ወደ ጦርነት ማዝመት ይችሉ ነበር። ነገር ግን ቅድመ አያቶቻቸው ቅዱስ ሕብረት የሚል ውል በመፈረም የአንዱን ታላቅ “ክርስቲያን ሕዝብ” ልዩ ልዩ ክፍሎች እንዲገዙ አምላክ የመደበላቸው መሆኑን አስታውቀው ነበር።
እንደ ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ አባባል ይህ ሰነድ “በ19ኛው መቶ ዘመን የአውሮፓውያንን ዲፕሎማሲ አቅጣጫ በኃይል ነክቷል።” የዲሞክራቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ለመቃወምና ነገሥታት ለመግዛት መለኮታዊ መብት አላቸው የሚለውን አባባል ለመደገፍ ተጠቅመውበታል። ኬይሰር ዊልሄል ለዛር ኒኮላስ ሲጽፉ “እኛ ክርስቲያን ነገሥታት ከሰማይ በተሰጠን ኃላፊነት አንድ ቅዱስ ግዴታ አለብን እርሱም [ነገሥታት ለመግዛት መለኮታዊ መብት አላቸው] የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ማስጠበቅ ነው” ብለዋል። ታዲያ የአውሮፓ ነገሥታት በአንድ ዓይነት መንገድ ከአምላክ መንግሥት ጋር ተያይዘው ነበር ማለት ነውን? (ከ1 ቆሮንቶስ 4:8 ጋር አወዳድር) እነዚያን ነገሥታት ስለደገፉት ቤተ ክርስቲያኖችስ ምን ለማለት ይቻላል? ክርስቲያን ነን ባይነታቸው በሐቅ ላይ የተመረኮዘ ነበርን? የነዚህን ጥያቄዎች መልስ 1914ን ተከትለው በመጡት ዓመታት ግልጽ ሆኗል።
በነሐሴ፣ በድንገት ጀመረ
“በ1914 ጸደይና በጋ አውሮፓ ልዩ በሆነ ሰላምና ጸጥታ ትታወቅ ነበር” ሲሉ የእንግሊዙ መሪ ዊንስተን ቸርችል ጽፈዋል። ሕዝቦች ባጠቃላይ ስለወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ተስፋ ነበራቸው። “የ1914ቱ ዓለም በተስፋዎች የተሞላ ዓመት ነበር” ሲሉ ሉዊ ሲንደር አንደኛ የዓለም ጦርነት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ተናግረዋል።
እርግጥ ነው ለብዙ ዓመታት በጀርመንና በእንግሊዝ መካከል ከፍተኛ ተቀናቃኝነት ነበር። ቢሆንም ታሪክ ጸሐፊው ጂ.ፒ.ጎች በስድስት ነገስታት ሥር በተባለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት “በአውሮፓ ውስጥ ግጭት የመነሳቱ ስጋት ከ1911፣ ከ1912 ወይም ከ1913 ይልቅ በ1914 ይበልጥ ቀንሶ ነበር።. . . የሁለቱ ነገሥታት ግንኙነት ለብዙ ዓመታት ከነበረው በጣም ተሽሎ ነበር።” የ1914 የእንግሊዝ አገር የካቢኔ አባል የነበሩት ዊኒስተን ቸርችል “ጀርመን ሰላም መስርታ ከኛ ጐን ያለች ትመስላለች” ብለዋል።
ይሁን እንጂ ሰኔ 28, 1914 የኦስትሪያ-ሀንጋሪ ግዛት አልጋ ወራሽ በሳራዬቮ በመገደላቸው በአድማሱ ላይ ጥቁር ደመና ብቅ አለ። ከአንድ ወር በኋላ ንጉሠ ነገሥት ፍራንዝ ጆሴፍ በሰርቢያ ላይ ጦርነት በማወጅ ይህንን መንግሥት እንዲወር ጦራቸውን አዘዙ። በዚህ ጊዜ ነሐሴ 3, 1914 በሌሊት በኬይሰር ዊልሔልም ትዕዛዝ ብዙ የጀርመን ጦር የቤልጂግ ግዛት በድንገት ወርሮ ወደ ፈረንሳይ አቀና። በማግስቱ እንግሊዝ በጀርመን ላይ ጦርነት አወጀች። ዛር ኒኮላስም በጀርመንና በኦስትሪያ-ሀንጋሪ ላይ ግዙፉን የሩሲያን ሠራዊት ለጦርነት የክተት ትዕዛዝ አወጁ። ቅዱስ ህብረት የአውሮፓን ነገስታት አህጉሯ ከእርስ በርስ እልቂት ወደ ደም መፋሰስ እንዳትገባ ለማቆም አልቻሉም። ነገር ግን ይበልጡን አስደንጋጭ የሆኑ ሁኔታዎች ለመምጣት ጊዜአቸውን ሲጠብቁ ነበር።
እስከ ገና ድረስ ጦርነቱ አበቃን?
የጦርነቱ መጀመር የሰዎችን የወደፊት ብሩህ አመለካከት አላቀዘቀዘውም። እንዲያውም ብዙዎች የተሻለ ዓለም እንደሚፈጠር አምነው ነበር። ብዙ ሕዝቦች ድጋፋቸውን ለመግለጽ በአውሮፓ በሙሉ ይሰበሰቡ ነበር። ኤ.ጄ.ፒ ቴይለር ዘ ስትራግል ፎር ማስተሪይ ኢን ዩሮፕ—1848–1918 (አውሮፓን ለመቆጣጠር የተደረገው ፍትጊያ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “1914 በወታደራዊ ግጭት ደረጃ እንጂ ማንም ሰው ከዛ አስበልጦ አክብዶ የተመለከተው አልነበረም። . . . የማህበራዊ መቅሰፍት ይሆናል ብሎ የገመተ ማንም አልነበረም።” ከዚህ ይልቅ በጥቂት ወራት ውስጥ ይቆማል ብለው ብዙዎች ተንብየው ነበር።
ሆኖም አውሮፓውያን የ1914ን የገና በዓል ከማክበራቸው ከረዥም ጊዜ በፊት ከደቡብ ስዊዘርላንድ 720 ኪ.ሜ እስከ ሰሜን ቤልጂግ የባህር ጠረፍ እስካለው የመከላከያ ምሽግ ድረስ የማይቆም ደም መፋሰስ ተጀምሮ ነበር። ይህም የምዕራብ ጦር ግንባር ተብሎ ይታወቅ ነበር። የጀርመኑ ደራሲ ኸርበርት ሱልዝባክ በግል ማስታወሻ ማህደራቸው ላይ የ1914ን የመጨረሻ ቀን ጠቅሰው መዝግበዋል። በማህደሩ ላይ የተመዘገበው ቃል እንዲህ ይነበባል። “ይህ ኃይለኛ ጦርነት እየቀጠለ ሄደ። በጅምሩ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይቆማል ብላችሁ ያሰባችሁት አሁን መጨረሻ የሌለው ሆኗል” ይላል። በዚህ ጊዜ የአውሮፓ ሌሎች ክፍሎች በሩሲያ፣ በጀርመን፣ በኦስትሪያ-ሀንጋሪና፣ በሰርቢያ ወታደሮች መካከል በሚደረገው የደም መፋሰስ ውጊያ ተጧጡፎ ነበር። ግጭቱ ከአውሮፓ አልፎ በፍጥነት በመሰራጨቱ ጦርነቱ በውቅያኖሶች ላይ እና በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በፓስፊክ ደሴቶች ላይ ተዛምቶ ነበር።
ከአራት ዓመት በኋላ አውሮፓ ወደመች። ጀርመን፣ ሩስያና የኦስትርያ-ሀንጋሪ መንግሥት እያንዳንዳቸው በአንድና በሁለት ሚሊዮን መሐል የሚቆጠሩ ወታደሮችን አጥተዋል። ሩሲያ እንኳን በ1917 በቦልሸቪክ አብዮት ንጉሳዊ አገዛዟን አጥታለች። በአውሮፓ ነገስታቶችና ደጋፊዎቻቸው የነበሩት ካህናት ላይ ምን ያህል ድንጋጤ ወድቆባቸው ይሆን! አሁንም ዘመናዊ ታሪክ ጸሐፊዎች በ1914 የተፈጸመው ሁኔታ ያስደነገጣቸው መሆኑን ይገልፃሉ። ብሩክ-ሼፈርድ ሮያል ሳንሴት በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ “እነዚህ በአብዛኛው በደምና በጋብቻ የተሳሠሩትና ንጉሣዊ አስተዳደርን ጠብቀው ለማቆየት ከቆረጡ ገዥዎች እንዴት ብዙዎቻቸውን ከመኖር ውጪ ባደረጋቸውና በሕይወት የተረፉትንም ደካማ አድርጐ ባስቀረው ጦርነት ራሳቸውን በመክተት ደም መፋሰስን ፈቀዱ” ብለዋል።
የፈረንሳይ ሪፑብሊክ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወታደሮችን አጥታለች። ከጦርነቱ ከብዙ ዓመታት በፊት ተዳክሞ የነበረው የእንግሊዝ ንጉሣዊ አገዛዝም 900,000 ወታደሮችን አጥቷል። በጠቅላላው ከ9 ሚልዮን የሚበልጡ ወታደሮች ሞተዋል። በተጨማሪም 21 ሚልዮን ወታደሮች ቆስለዋል። በጦርነቱ የተገደሉትን ሲቪሎች በሚመለከት ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ ሲገልጽ፦ “በበሽታ፣ በረሃብና ከጦርነቱ ጋር በተያያዙ ሌሎች ምክንያቶች የሞቱት ምን ያህል ሲቪሎች እንደሆኑ የሚያውቅ ሰው የለም። አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች በጦርነቱ የተገደሉት ሲቪሎች ቁጥር ከተገለጹት ወታደሮች ቁጥር አያንስ ይሆናል” ብለው ያምናሉ። በ1819 የተነሳው ተላላፊ በሽታ በምድር በሙሉ የ21,000,000 ሰዎችን ህይወት ቀጥፎአል።
ስር-ነቀል ለውጥ
በዚያ ጊዜ ‘ታላቁ ጦርነት’ ተብሎ ይጠራ ከነበረው ጦርነት ወዲህ ዓለም የቀድሞ ሁኔታዋን ልታገኝ አልቻለችም። ብዙዎቹ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በጦርነቱ በጋለ ስሜት በመካፈላቸው ግራ የተጋቡ ብዙ ከጦርነቱ የተረፉ ሰዎች ለሐይማኖት ጀርባቸውን በመስጠት አምላክ የለሾች ሆነዋል። ሌሎች ደግሞ ቁሳዊ ሐብትና ደስታ አሳዳጅ ሆነዋል። ፕሮፌሰር ሞድርስ ኤክስታይን ራይትስ ኦፍ ስፕሪንግ በተባለው መጽሐፋቸው በ1920 ዎቹ ዓመታት “ሰዎች ከመጠን ያለፈ ራስና ተድላ ወዳዶች ሆነዋል” ብለዋል።
ፕሮፌሰር ኤክስታይን ሲገልጹ “ጦርነቱ የስነ ምግባር ደረጃዎችን አጥፍቷል” ብለዋል። የሐይማኖት፣ የውትድርናና የፖለቲካ መሪዎች በሁለቱም ተዋጊ ወገኖች የሚኖሩት ሰዎች ሕዝቦችን መግደል በስነ ምግባር በኩል ጥሩ እንደሆነ አድርገው እንዲመለከቱ አስተምረዋል። ይህም ይላሉ ኤክስተይን “ከአይሁድና ከክርስትና ሥነምግባር የመጣ ነው ተብሎ በሚታመነው የስነ ምግባር ደረጃ ላይ ከፍተኛ ውድቀት አስከትሎአል” ብለዋል። ጨምረው ሲናገሩም፦ “በምዕራብ ግንባር ዝሙት አዳሪነት በጣም ተስፋፋ በቤት ውስጥም የነበረው የስነ ምግባር መቀነትና ቀበቶ ላላ። ሴተኛ አዳሪነት በፍጥነት ጨመረ።”
በእርግጥ 1914 ብዙ ለውጦችን አስከትሎአል። የተሻለ ዓለም አላስገኘም። ጦርነቱም ብዙ ሰዎች ተስፋ እንዳደረጉት “ጦርነቶችን ሁሉ ወደ ፍፃሜ የሚያመጣው ጦርነት” አልሆነም። ከዚህ ይልቅ ታሪክ ፀሐፊው ባርባራ ቱችማን እንዳሉት “እስከ 1914 ይፈጸማሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት ሕልሞችና ተስፋዎች ቀስ በቀስ ግዙፍ በሆነ ግራ የመጋባት ባህር ውስጥ ሰጠሙ።”
ነገር ግን አንዳንድ የ1914ን መከራ የተመለከቱ ሰዎች በዚያ ዓመት የተከናወነው ሁኔታ ድንገተኛ ነገር አልሆነባቸውም ነበር። በእርግጥ ጦርነቱ ከመፈንዳቱ በፊት “የአሰቃቂ ችግር ዘመን” እንደሚመጣ ጠብቀው ነበር። እነዚህ ሰዎች እነማን ነበሩ? እነርሱስ ሌሎች ያላወቁትን ምን ነገር አውቀው ነበር?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ብሪታኒያ በ1914 የነበራት ብሩሕ ተስፋ
“አንድ መቶ ዓመት ለሚሆን ጊዜ በየቤታችን ዙሪያ ባለው ባህር ላይ አንድም ጠላት አልታየም። . . . በእነዚህ ሰላማዊ የባሕር ዳርቻዎች ላይ አደገኛ ሁኔታ ይፈጠራል ብሎ ማሰብ እንኳን ያስቸግር ነበር። . . . ሎንደን እንደዚያ ጊዜ ደስታና ብልፅግና ያገኘችበት ጊዜ አልነበረም። እንደዚያ ዘመን ብዙ የሚሠሩ ሥራዎች፣ ብዙ የሚታዩና የሚሰሙ ነገሮች የነበሩበት ጊዜ አልነበረም። ሽማግሌዎችም ሆኑ ወጣቶች በ1914 የተመለከቱት ነገር እስከዚያ ድረስ ይታወቅ የነበረው ዘመን ፍጻሜ ይሆናል ብለው አልጠረጠሩም ነበር።”—ቢፎር ዘ ላምፕስ ዌንት አውት፣ በጂኦፍሬይ ማርኩስ