ነፃ፣ ግን ተጠያቂነት ያለበት ሕዝብ
“እውነትን ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል”—ዮሐንስ 8:32
1, 2. (ሀ) ነፃነት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የተሰጠው እንዴት ነው? (ለ) ሙሉ ነፃነት ያለው ማን ብቻ ነው? አብራራ።
ነፃነት። ይህ ቃል ትልቅ ትርጉም ያለው ቃል ነው! የሰው ዘር ለነፃነት ሲል ብዙ ጦርነቶችንና አብዮቶችን፣ እንዲሁም ሕዝባዊ አመፆችን ሲያካሂድ ኖሮአል። ኢንሳይክሎፒድያ አሜሪካና፦ “በስልጣኔ ዕድገት ውስጥ ከነፃነት የበለጠ ከፍተኛ ሚና የተጫወተ ጽንሰ ሐሳብ የለም” ማለቱ አያስደንቅም።
2 ይሁን እንጂ እውነተኛ ነፃነት ያላቸው ሰዎች ምን ያህል ናቸው? ነፃነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚያውቁትስ ስንቶቹ ናቸው? ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች ሙሉ ነፃነት እንዲኖራቸው ከተፈለገ በሚያስቡት፣ በሚናገሩትና በሚያደርጉት ነገር ላይ ምንም ዓይነት ገደብ መደረግ የለበትም። ምን ምርጫ እንዳላቸው ሊያውቁና ከእነዚህ ምርጫዎች የፈለጉትን የመምረጥ ሥልጣን ሊኖራቸው ይገባል።” በዚህ መሠረት ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነ ሰው ይገኛልን? ‘በሚያስቡት፣ በሚናገሩትና በሚያደርጉት ነገር ላይ ምንም ዓይነት ገደብ’ እንደሌለባቸው ሊናገሩ የሚችሉ ሰዎች አሉን? እንደ እውነቱ ከሆነ በመላው ጽንፈ ዓለም ውስጥ ሙሉ ነፃነት ያለው አንድ ብቻ ነው። እርሱም ይሖዋ አምላክ ነው። ፍጹም ነፃነት ያለው እርሱ ብቻ ነው። ምንም ዓይነት ተቃውሞ ቢኖር የፈለገውን ለመምረጥና የመረጠውንም ለመፈጸም የሚችል እርሱ ብቻ ነው። እርሱ ሁሉን ቻይ ነው።—ራእይ 1:8፤ ኢሳይያስ 55:11
3. አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች በነፃነታቸው ለመደሰት ምን ማሟላት የሚኖርባቸው ግዴታ አለ?
3 ተራ የሆኑ ሰዎች ሊኖራቸው የሚችለው ነፃነት አንፃራዊ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ነፃነት ከአንድ ዓይነት ሥልጣን የሚሰጥ ወይም አንድ ሥልጣን የሚሰጠው ዋስትናና ለዚያ ሥልጣን ከመገዛታችን ጋር የተያያዘ ነው። እርግጥ ነው አንድ ሰው በማንኛውም ሁኔታ ነፃ ሊሆን የሚችለው ነፃነት የሰጠውን ሰው ሥልጣን በትክክል ሲገነዘብ ብቻ ነው። ለምሳሌ ያህል “በነፃው ዓለም” ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦች እንደልብ የመንቀሳቀስ፣ የመናገርና የሃይማኖት ነፃነት ስለ አላቸው በጣም ይደሰታሉ። ለእነዚህ ነፃነቶች ዋስትና የሚሰጠው ምንድን ነው? የየአገሩ ሕግ ነው። አንድ ሰው በእነዚህ ነፃነቶች ሊደሰት የሚችለው ሕግ ካከበረ ብቻ ነው። ነፃነቱን አለአግባብ ከተጠቀመበትና ሕግ ካፈረሰ በባለ ሥልጣኖች ይጠየቃል። እስር ቤት በመግባትም ነፃነቱን ሊያጣ ይችላል።—ሮሜ 13:1-4
ተጠያቂነት ያለበት አምላካዊ ነፃነት
4, 5. የይሖዋ አምላኪዎች ምን ዓይነት ነፃነት አግኝተዋል? ለምንስ ነገር ተጠያቂዎች ያደርጋቸዋል?
4 ኢየሱስ በአንደኛው መቶ ዘመን ስለ ነፃነት ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ ለአይሁዶች “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀ መዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሎአል። (ዮሐንስ 8:31, 32) ኢየሱስ ስለ ንግግር ነፃነት ወይም ስለ ሃይማኖት ነፃነት መናገሩ አልነበረም። ብዙ አይሁዶች ይናፍቁት ስለነበረው ከሮም የአገዛዝ ቀንበር ነፃ ስለመውጣት መናገሩ አልነበረም። ኢየሱስ የተናገረው ከሰብአዊ ገዢዎች ሳይሆን ከአጽናፈ ዓለም የበላይ ገዥ ከይሖዋ ስለሚገኘው በጣም ውድ ስለሆነ ነፃነት ነው። ይህም ነፃነት ከአጉል እምነት፣ ከሃይማኖታዊ ድንቁርና ነፃ መውጣትንና ከዚህ የበለጡ ብዙ ነገሮችን ይጨምራል። ይሖዋ የሚሰጠው ነፃነት እውነተኛ ነፃነት ነው። ይህም ነፃነት ለዘላለም ይኖራል።
5 ሐዋርያው ጳውሎስ “[ይሖዋ (አዓት)] መንፈስ ነው፤ የ[ይሖዋ]ም መንፈስ ባለበት በዚያ አርነት አለ” ብሎአል። (2 ቆሮንቶስ 3:17) ይሖዋ የሰው ልጆች “ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብራማ ነፃነት” ደርሰው ከሁሉም በሚበልጠው ትልቅ ነፃነት እንዲደሰቱ ለማድረግ ለብዙ መቶ ዘመናት ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። (ሮሜ 8:21) በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አማካኝነት የተወሰነ ነፃነት ሰጥቶናል። ይህን ነፃነታችንንም አለአግባብ ከተጠቀምንበት ተጠያቂዎች ያደርገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም” ሲል ጽፎአል።—ዕብራውያን 4:13
6-8. (ሀ) አዳምና ሔዋን ምን ዓይነት ነፃነት ነበራቸው? እነዚህ ነፃነቶች እንዳይወሰዱባቸው ምን ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር? (ለ) አዳምና ሔዋን ራሳቸውም ሆኑ ልጆቻቸው ምን ነገር እንዲያጡ አደረጉ?
6 ለይሖዋ ተጠያቂ መሆን የጀመረው የመጀመሪያዎቹ ሰብአዊ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን በሕይወት መኖር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ነው። ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ውድ የሆነ ነፃ ፈቃድ ሰጥቶ ፈጥሮአቸዋል። ይህን ነፃ ፈቃዳቸውን በኃላፊነት እንደሚጠየቁበት አድርገው እስከተጠቀሙበት ድረስ ከፍርሃት፣ ከበሽታ፣ ከሞት ነፃ የመሆን፣ ሰማያዊ አባታቸውን በንፁህ ሕሊና የመቅረብ ነፃነትና የመሳሰሉትን ሌሎች በረከቶች በማግኘት ይደሰቱ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ነፃ ፈቃዳቸውን አለአግባብ በተጠቀሙበት ጊዜ ይህ ሁሉ ተለወጠ።
7 ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን ፈጥሮ በኤደን የአትክልት ቦታ አኖራቸው። ለደስታቸውም ሲል ከአንዷ በስተቀር በአትክልት ቦታው ውስጥ ያሉትን የዛፍ ፍሬዎች ሁሉ እንዲበሉ ፈቀደላቸው። ከእርሱ እንዳይበሉ የከለከላቸው “መልካምንና ክፉውን የምታስታውቀውን ዛፍ” ብቻ ነበር። (ዘፍጥረት 2:16, 17) አዳምና ሔዋን ከተከለከለው ፍሬ ከመብላት በመቆጠብ መልካም የሆነውንና መጥፎ የሆነውን ለመወሰን ሙሉ ነፃነት ያለው ይሖዋ ብቻ እንደሆነ አምነው መቀበላቸውን ለማሳየት ይችሉ ነበር። በኃላፊነት እንደሚጠየቁ ቢሰማቸውና ከተከለከለው ፍሬ ከመብላት ቢቆጠቡ ይሖዋ ሌሎች ነፃነቶቻቸውን ያስከብርላቸው ነበር።
8 የሚያሳዝነው ግን ሔዋን ‘መልካምና ክፉ’ የሆነውን እራሷ ማወቅ እንደሚኖርባት የሚገልጸውን የእባቡን የማታለያ ሐሳብ ሰማች። (ዘፍጥረት 3:1-5) በመጀመሪያ እሷ ከዚያም አዳም ከተከለከለው ፍሬ በሉ። በዚህም ምክንያት ይሖዋ አምላክ በኤደን የአትክልት ቦታ ሊያነጋግራቸው በፈለገ ጊዜ አፍረው ተደበቁ። (ዘፍጥረት 3:8, 9) አሁን በንፁህ ሕሊና ወደ አምላክ የመቅረብ ነፃነት ያጡ ኃጢአተኞች ሆኑ። በዚህም ምክንያት ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው ከበሽታና ከሞት ነፃ የመሆንን መብት አሳጡ። ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ጽፎአል፦ “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ። በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።”—ሮሜ 5:12፤ ዘፍጥረት 3:16, 19
9. በተሰጣቸው መጠነኛ ነፃነት በሚገባ እንደተጠቀሙ የሚታወቁ ሰዎች እነማን ናቸው?
9 ይሁን እንጂ የሰው ዘር አሁንም ነፃ ፈቃድ አለው። አንዳንድ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችም ይህን ነፃነታቸውን ኃላፊነት ባልጎደለው ሁኔታ ይሖዋን ለማገልገል ተጠቅመውበታል። የአንዳንዶቹ ስም ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተጠብቆ ቆይቶናል። እንደ አቤል፣ ሄኖክ፣ ኖህ፣ አብርሃም፣ ይስሃቅና ያዕቆብ (እስራኤል ተብሎ የተጠራው) የነበራቸውን መጠነኛ ነፃነት የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የተጠቀሙበት ምሳሌዎቻችን ናቸው።—ዕብራውያን 11:4-21
የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች ያገኙት ነፃነት
10. ይሖዋ ከተለዩ ሕዝቦቹ ጋር የገባው የቃል ኪዳን ውለታ ምን ነበር?
10 ይሖዋ በሙሴ ዘመን በጊዜው በሚሊዮን ይቆጠሩ የነበሩትን እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ አውጥቶ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ከዚያ በኋላ የእርሱ ልዩ ሕዝቦች ሆኑ። እስራኤላውያን በዚህ ቃል ኪዳን ሥር ሆነው የሚያገለግሉ ካህናትና ኃጢአታቸውንም በምሳሌያዊ ሁኔታ የሚሸፍንላቸው የእንስሳ መስዋዕት የሚያቀርቡበት ሥርዓት ነበራቸው። ስለዚህ ወደ ይሖዋ የመቅረብና እርሱን የማምለክ ነፃነት ነበራቸው። በተጨማሪም ከአጉል እምነትና ከሐሰት አምልኮ ነፃ የሚያደርጋቸው ሕግና ደንብ ነበራቸው። የተስፋይቱን ምድር የመውረስ ተስፋ ነበራቸው። ከጠላቶቻቸው ለሚሰነዘርባቸው ጥቃትም አምላካዊ እርዳታ ማግኘት ይችሉ ነበር። ከይሖዋ ጋር የገቡት ቃል ኪዳን የይሖዋን ሕግ እንዲጠብቁ ይፈልግባቸው ነበር። ይህንንም ውል ለመቀበል ፈቃደኛ መሆናቸውን “[ይሖዋ (አዓት)] ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” በማለት አረጋግጠዋል።—ዘጸአት 19:3-8፤ ዘዳግም 11:22-25
11. የእሥራኤል ብሔር ከይሖዋ ጋር የገባው ቃል ኪዳን የጣለበትን ግዴታ ሳይፈጽም በቀረ ጊዜ ምን ደረሰበት?
11 እስራኤላውያን ከ1,500 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ከይሖዋ ጋር ልዩ ዝምድና ነበራቸው። ይሁን እንጂ በየጊዜው ቃል ኪዳናቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል። በተደጋጋሚ በሐሰት አምልኮ በመታለል ለጣዖት አምልኮና ለአጉል እምነት ባሪያ ሆነዋል። በዚህም ምክንያት አምላክ የጠላቶቻቸው ባሪያዎች እንዲሆኑ ፈቀደ። (መሳፍንት 2:11-19) ቃል ኪዳኑን ከመጠበቅ በሚገኙት በረከቶች ከመደሰት ይልቅ ቃል ኪዳኑን በማፍረሳቸው ምክንያት ይቀጡ ነበር። (ዘዳግም 28:1, 2, 15) ከጊዜ በኋላ ይሖዋ የእስራኤል ሕዝብ በ607 ከዘ.አ.በ የባቢሎናውያን ባሪያ እንዲሆን ፈቀደ።—2 ዜና መዋዕል 36:15-21
12. ከጊዜ በኋላ ስለ ሙሴ የሕግ ቃል ኪዳን ምን ነገር ታወቀ?
12 ይህ ለእነርሱ ከባድ ትምህርት ነበር። ከደረሰባቸው ችግር ሕጉን ማክበር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብ ይገባቸው ነበር። ይሁን እንጂ ከ70 ዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው በተመለሱም ጊዜ ቢሆን የቃል ኪዳኑን ሕግ በትክክል መጠበቅ አልቻሉም። ወደ አገራቸው ከተመለሱ ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ ይሖዋ ለእስራኤላውያን ካህናት እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ግን ከመንገዱ ፈቀቅ ብላችኋል በሕግም ብዙ ሰዎችን አሰናክላችኋል፤ የሌዊንም ቃል ኪዳን አስነውራችኋል” (ሚልክያስ 2:8) ከእስራኤላውያን መካከል በጣም ቅን የነበሩት እንኳን ፍጹም የሆነውን ሕግ ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም አልቻሉም። ሕጉ በረከት ከማምጣት ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “እርግማን” ሆነባቸው። (ገላትያ 3:13) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ፍጹማን ያልሆኑ ታማኝ የሰው ልጆች ለአምላክ ልጆች ወደሚሆን ክብራማ ነፃነት ለማምጣት ከሙሴ ሕግ የበለጠ ነገር ያስፈልግ ነበር።
ክርስቲያኖች ያገኙት የነፃነት ባሕርይ
13. ከጊዜ በኋላ ምን የተሻለ የነፃነት ዝግጅት ተደረገ?
13 ይህ ከሙሴ ሕግ የበለጠው ነገር የኢየሱስ ቤዛዊ መስዋዕት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በ50 እዘአ ገደማ በገላትያ ለሚገኙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጽፎላቸው ነበር። ይሖዋ ከሕጉ ቃል ኪዳን ባርነት እንዴት ነፃ እንዳወጣቸው ከገለጸ በኋላ እንዲህ ብሎአል፦ “በነፃነት ልንኖር ክርስቶስ ነፃነት አወጣን እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ። (ገላትያ 5:1) ኢየሱስ ሰዎችን ነፃ ያወጣቸው በምን መንገድ ነው?
14, 15. ኢየሱስ ያመኑትን አይሁዳውያንም ሆነ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ነፃ ያወጣው እንዴት ባለ አስደናቂ መንገድ ነው?
14 ከኢየሱስ ሞት በኋላ ኢየሱስን እንደ መሲህ አድርገው የተቀበሉና ደቀ መዛሙርቱ የሆኑ አይሁዶች አሮጌውን የሕግ ቃል ኪዳን በተካው አዲስ ቃል ኪዳን ሥር መኖር ጀመሩ። (ኤርምያስ 31:31-34፤ ዕብራውያን 8:7-13) በዚህ ቃል ኪዳን ሥር አይሁዳውያንና በኋላ ከእነርሱ ጋር የተባበሩት አይሁድ ያልሆኑ አማኞች የአምላክ ልዩ ሕዝብ የነበሩትን ሥጋዊ እስራኤላውያንን የሚተካው የአዲሱ መንፈሳዊ ሕዝብ ክፍል ሆኑ። (ሮሜ 9:25, 26፤ ገላትያ 6:16) ኢየሱስ “እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሎ በገባላቸው ቃል መሠረት እውነት ባስገኘላቸው ነፃነት ተደስተዋል። እውነት አይሁድ ክርስቲያኖችን ከሙሴ ሕግ እርግማን ነፃ ከማውጣቱም በተጨማሪ የሃይማኖት መሪዎች ይጭኑባቸው ከነበረው ከባድ ወግ ነፃ አውጥቶአቸዋል። አይሁድ ያልሆኑትንም ክርስቲያኖች በፊት ያመልኩት ከነበረው ጣዖትና አጉል እምነት ነፃ አውጥቶአቸዋል። (ማቴዎስ 15:3, 6፤ 23:4፤ ሥራ 14:11-13፤ 17:16) ከዚህ የበለጠ ነገርም ነበር።
15 ኢየሱስ ነፃ ስለሚያወጣው እውነት በተናገረበት ጊዜ፦ “እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው” ብሎአል። (ዮሐንስ 8:34) አዳምና ሔዋን ኃጢአት በመስራታቸው ምክንያት ሁሉም ሰው ኃጢአተኛና የኃጢአት ባርያ ሆነ። ከኃጢአት ነፃ የሆነው ኢየሱስ ብቻ ነው። አማኞችን ከዚህ ባርነት ነፃ የሚያወጣውም የኢየሱስ መስዋዕት ብቻ ነው። እውነት ነው፣ አሁንም ቢሆን ሰዎች ፍጽምና የጎደላቸውና በተፈጥሮአቸው ምክንያት ኃጢአተኛ ናቸው። ሆኖም አሁን በኢየሱስ መስዋዕት አማካኝነት ከኃጢአታቸው ንስሐ መግባትና ይሖዋ የኃጢአት ይቅርታ እንዲያደርግላቸው መለመን ይችላሉ። ጸሎታቸውም እንደሚሰማላቸው ትምክህት አላቸው። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) አምላክ በኢየሱስ ቤዛዊ መስዋዕት አማካኝነት ስላጸደቃቸው በንፁህ ሕሊና ወደ እርሱ መቅረብ ይችላሉ። (ሮሜ 8:33) በተጨማሪም ቤዛው ከሙታን ተነስተው የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን በር ስለከፈተላቸው እውነት ከሞት ፍርሃት ነፃ አውጥቶአቸዋል።—ማቴዎስ 10:28፤ ዕብራውያን 2:15
16. ክርስቲያናዊ ነፃነት ዓለም ከሚሰጠው ማንኛውም ዓይነት ነፃነት የበለጠ ስፋት ያለው የሆነው እንዴት ነው?
16 ወንዶችና ሴቶች በሰብአዊ አመለካከት በምንም ዓይነት ሁኔታ የሚኖሩ ቢሆኑ ክርስቲያናዊ ነፃነት የሚያገኙበት አስደናቂ መንገድ ተከፍቶላቸዋል። ድሆች፣ እስረኞች፣ ባሪያዎች እንኳ ነፃ መሆን ይችላሉ። በሌላ በኩል ግን ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን መልእክት ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑት የዓለም ታላላቅ ሰዎች አሁንም የአጉል እምነት፣ የኃጢአትና የሞት ፍርሃት ባርያዎች ናቸው። ለዚህ ለምንደሰትበት ነፃነታችን ይሖዋን ማመስገናችንን በፍጹም ማቋረጥ አይኖርብንም። ዓለም የሚያቀርብልን ማንኛውም ነገር ከዚህ ነፃነት ጋር ሊስተካከል አይችልም።
ነፃ፣ ግን ተጠያቂ
17. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያናዊ ነፃነታቸውን ያጡት እንዴት ነበር? (ለ) በሰይጣን ዓለም ውስጥ በሚገኘው የይስሙላ ነፃነት መታለል የማይገባን ለምንድን ነው?
17 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በነፃነታቸው ተደስተዋል። ምንም ዓይነት መሥዋዕትነት ቢጠይቅባቸውም በፍጹም አቋማቸው ጸንተዋል። የሚያሳዝነው ግን አንዳንዶቹ ክርስቲያናዊ ነፃነት የሚያስገኛቸውን በረከቶች በሙሉ ከቀመሱ በኋላ በዓለም ውስጥ ወዳለው ባርነት በመመለስ ክርስቲያናዊ ነፃነታቸውን አቃልለዋል። ይህ ሊሆን የቻለው ለምን ነበር? የብዙዎቹ እምነት በመዳከሙ ምክንያት ‘ከሰሙት ነገር እንደ ተወሰዱ’ አያጠራጥርም። (ዕብራውያን 2:1) ሌሎችም ‘እምነትና በጎ ሕሊናን ጥለው መርከብ አለመሪ እንደሚጠፋ በእምነት ነገር ጠፍተዋል።’ (1 ጢሞቴዎስ 1:19) ምናልባትም ቁሳዊ ሀብት በመፈለግ ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ አኗኗር በመምረጥ ተታልለው ወድቀው ይሆናል። በግል ጥናት ትጉሆች በመሆን፣ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በመተባበር፣ በመጸለይና በሌሎች ክርስቲያናዊ ሥራዎች በመሳተፍ እምነታችንን መጠበቅና መገንባት ምንኛ አስፈላጊ ነው! (2 ጴጥሮስ 1:5-8) ክርስቲያናዊ ነፃነታችንን ማድነቃችንን በፍጹም አናቋርጥ! እውነት ነው፣ አንዳንዶች ከጉባኤ ውጭ ያለውን ልቅነት በመመልከት ከእኛ ከክርስቲያኖች ይልቅ በዓለም ውስጥ ያሉት ነፃነት አላቸው ብለው በማሰብ ሊፈተኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በዓለም ውስጥ ነፃነት መስሎ የሚታየው ብዙውን ጊዜ ከኃላፊነት መሸሽ እንጂ ነፃነት አይደለም። የአምላክ ባሪያዎች ካልሆንን የኃጢአት ባሪያዎች ነን። የኃጢአት ባርነት ደግሞ የሚያስከፍለው ደመወዝ በጣም መራራ ነው።—ሮሜ 6:23፤ ገላትያ 6:7, 8
18-20. (ሀ) አንዳንዶች “የመከራው እንጨት ጠላቶች” የሆኑት እንዴት ነው? (ለ) አንዳንዶች ‘ነፃነታቸውን የክፋት መሸፈኛ’ ያደረጉት እንዴት ነው?
18 በተጨማሪም፣ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሎአል፦ “ብዙዎች ለክርስቶስ [የመከራ እንጨት (አዓት)] ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፣ አሁንም እንኳን እያለቀስሁ እላለሁ።” (ፊልጵስዩስ 3:18) አዎ፣ አንድ ወቅት ክርስቲያኖች የነበሩና በኋላ ግን የእምነት ጠላቶች፣ ምናልባትም ከሐዲዎች የሆኑ ሰዎች አሉ። የእነዚህን ሰዎች መንገድ አለመከተል በጣም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፎአል፦ “አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባርያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነታችሁ ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ።” (1 ጴጥሮስ 2:16) አንድ ግለሰብ ነፃነቱን ለክፋት መሸፈኛ የሚያደርገው እንዴት ነው? ከጉባኤው ጋር እየተባበረ ምናልባት በምሥጢር ከባድ ኃጢአት ይሠራ ይሆናል።
19 ዲዮጥራጢስ ትዝ ይበለን። ዮሐንስ ስለ ዲዮጥራጢስ ሲናገር እንዲህ ብሎአል፦ “ዳሩ ግን ዋናቸው ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም። . . . እርሱ ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም፣ ሊቀበሉአቸውም የሚወዱትን ከልክሎ ከቤተ ክርስቲያን ያወጣቸዋል።” (3 ዮሐንስ 9, 10) ዲዮጥራጢስ ነፃነቱን ለራስ ወዳድነት ምኞቱ መሸፈኛ አድርጎ ተጠቅሞበታል።
20 ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ እንዲህ ሲል ጽፎአል፦ “ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ።” (ይሁዳ 4) እነዚህ ግለሰቦች ከጉባኤው ጋር በሚተባበሩበት ጊዜ በጉባኤው ላይ የምግባረ ብልሹነት ተጽእኖ ያመጡ ነበር። (ይሁዳ 8-10, 16) በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በጴርጋሞንና በትያጥሮን ጉባኤዎች መናፍቅነት፣ የጣዖት አምልኮ እና የሥነ ምግባር ብልሹነት እንደነበረ እናነባለን። (ራእይ 2:14, 15, 20-23) ክርስቲያናዊ ነፃነታቸውን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ተጠቅመውበታል።
21. በክርስቲያናዊ ነፃነታቸው አለአግባብ የሚጠቀሙ ሁሉ ምን ይጠብቃቸዋል?
21 በዚህ መንገድ ክርስቲያናዊ ነፃነታቸውን አለአግባብ የሚጠቀሙ ሁሉ ምን ይጠብቃቸዋል? በእስራኤል ሕዝብ ላይ ምን እንደ ደረሰ አስታውሱ። እስራኤላውያን የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች ነበሩ። ይሁን እንጂ ይሖዋ በመጨረሻ ላይ ጥሎአቸዋል። ለምን? ምክንያቱም እስራኤላውያን ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ዝምድናና፣ ግንኙነት ለክፋት መሸፈኛ አድርገው ተጠቅመውበት ስለነበረ ነው። የአብርሃም ዘሮች ነን እያሉ ቢኩራሩም የአብርሃም ዘር የሆነውንና ይሖዋ የመረጠውን መሲሕ ኢየሱስን ሳይቀበሉ ቀሩ። (ማቴዎስ 23:37-39፤ ዮሐንስ 8:39-47፤ ሥራ 2:36፤ ገላትያ 3:16) ‘የአምላክ እስራኤል’ በአጠቃላይ ተመሳሳይ የሆነ የክህደት መንገድ አይከተልም። (ገላትያ 6:16) ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ወይም ስነ ምግባራዊ እድፍ የሚያመጣ ማንኛውም ግለሰብ ክርስቲያን ተግሳጽ፣ እንዲያውም የቅጣት ፍርድ ይጠብቀዋል። ሁላችንም በክርስቲያናዊ ነፃነታችን እንዴት እንደምንጠቀም እንጠየቃለን።
22. ክርስቲያናዊ ነፃነታቸውን አምላክን ለማገልገል የሚጠቀሙ ሁሉ ምን ዓይነት ደስታ ያገኛሉ?
22 ከዚህ ይልቅ ለአምላክ ባሪያ በመሆን እውነተኛ ነፃነት ማግኘት ምንኛ የተሻለ ነው! እውነተኛ ዋጋ ያለውን ነፃነት የሚሰጠው ይሖዋ ብቻ ነው። የምሳሌ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ።” (ምሳሌ 27:11) ክርስቲያናዊ ነፃነታችንን ለይሖዋ ስም መቀደስ እንጠቀምበት። እንዲህ ካደረግን ሕይወታችን ትርጉም ይኖረዋል፣ ሰማያዊ አባታችንንም እናስደስተዋለን። በመጨረሻም ለአምላክ ልጆች በሚሆን ነፃነት ከሚደሰቱ ሕዝቦች መሐል እንሆናለን።
ልታብራራ ትችላለህን?
◻ ሙሉ በሙሉ ነፃ የሆነ ማን ብቻ ነው?
◻ አዳምና ሔዋን ምን ዓይነት ነፃነት ነበራቸው? ይህንንስ ነፃነታቸውን ያጡት ለምንድን ነው?
◻ እሥራኤላውያን ከይሖዋ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን በጠበቁባቸው ጊዜያት ምን ዓይነት ነፃነት አግኝተው ነበር?
◻ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ክርስቲያናዊ ነፃነታቸውን ያጡት ወይም በነፃነታቸው አለአግባብ የተጠቀሙት እንዴት ነው?
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የሰጠው ነፃነት የሰው ልጅ ሊሰጥ ከሚችለው ነፃነት በጣም የተሻለ ነው