ወደ “ነፃነት አፍቃሪዎች” የወረዳ ስብሰባዎች እንድትመጡ ተጋብዛችኋል
ነፃነት! ያ ቃል እንዴት የሚያስደስት ቃና አለው! በግዞተኛነት ወይም በምርኰኛነት የሚደሰት ማንም የለም። ሊታወሱ ከሚችሉት ከምንጊዜዎቹም ዓመታት ይበልጥ የቅርቦቹ ዓመታት ሰዎች ተስፋ የሚያደርጉበትን የፖለቲካ ነፃነት ለማግኘት ከፍተኛ መረባረብ የተደረገባቸው ዓመታት ናቸው።
ይሁን እንጂ ፖለቲካዊ ነፃነት ሰዎች በጣም የሚፈልጉት ነገር ቢሆንም ከዚያ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነና ደስ የሚል ነፃነት አለ። እሱም የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ “እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀመዛሙርቴ ናችሁ። እውነትንም ታውቃላችሁ። እውነትም አርነት (ነፃነት) ያወጣችኋል” በማለት በተናገረ ጊዜ የተናገረለት ዓይነት ነፃነት ነው። (ዮሐንስ 8:31, 32) ይህም ከሐሰት ሃይማኖታዊ እምነቶች፣ ሰውን ከመፍራት፣ ለኃጢአተኛነት ልማዶች ባሪያ ከመሆንና ከሌሎችም ነገሮች ነፃ መሆን ማለት ነው።
በ1991 የክረምት ወራት መግቢያ ላይ የሚጀምሩት በመላው ዓለም የሚደረጉት “ነፃነት አፍቃሪዎች” የወረዳ ስብሰባዎች አጠቃላይ መልእክትም ይኸው ነፃነት ነው። በአምላክ ሕዝቦች መካከል የመሪነቱን ቦታ በያዙት ላይ የመንግሥት ዕገዳ የተነሳበት በመሆኑ ከታወቀው ከ1919 ጀምሮ ንጹሕ አምልኰአቸውን በሚመለከት እየጨመረ የሚሄድ ነፃነት በማግኘት ሲደሰቱ ቆይተዋል።
የነፃነት ጉዳይ ባለፉት ዓመታትም የአምላክ ሕዝቦች ባደረጓቸው የወረዳ ስብሰባዎች ላይ ጐልቶ መገለጹ ተገቢ ነበር። ለምሳሌ ያህል “የነፃ ሕዝብ ቲኦክራቲካዊ ስብሰባ” እና “የአምላክ ነፃ ልጆች የወረዳ ስብሰባዎች” የሚሉ አጠቃላይ መልዕክት የያዙ የወረዳ ስብሰባዎች ተደርገው ነበር። እንዲሁም “እውነት ነፃ ያወጣችኋል” እና “የአምላክ ልጆች ነፃ ሆነው የሚያገኙት የዘላለም ሕይወት” በመሳሰሉት ጽሑፎች ነፃነት በስፋት ሐሳብ ተሰጥቶበታል።
የይሖዋ አገልጋዮች ያላቸው ከአምላክ የተሰጠ ነፃነት ለራሳቸው ደህንነትና ደስታ ብቻ የተሰጠ አይደለም። ገላትያ 5:13ን ስናነብ “ወንድሞች ሆይ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋል ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያት አይስጥ። ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደባሪያዎች ሁኑ” የሚል ቃል እናገኛለን። “ነፃነት አፍቃሪዎች” የተባለው የወረዳ ስብሰባም የነፃነታችንን ዓላማ እንዲገባን ይረዳናል፣ ውድ ነፃነታችንን አጥብቀን እንድንይዝ ያስችለናል፣ እንዲሁም በተሻለ ሁኔታ እንዴት እንደምንጠቀምበት ያሳየናል።
ስብሰባው ዓርብ ዕለት ጧት በ4:20 የሚጀምር ሲሆን ቀጥሎ ለሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ አእምሮአችንን የሚያዘጋጅ የሙዚቃ ፕሮግራም ይኖራል። የመጀመሪያው ቀን በዮሐንስ 8:32 ላይ የተመሠረተ “ነፃ የሚያወጣንን እውነት ማወቅ” የሚል አጠቃላይ መልዕክት ይኖረዋል። ከሰዓት በፊት የስብሰባው ሊቀ መንበር እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት አንዳንድ ሐሳቦችን አቅርቦ “አምላክ የሰጠን ነፃነታችን ዓላማና አጠቃቀም” የሚለውን የስብሰባውን ዋና መንፈስ የሚያንጸባርቅ ንግግር ይሰጣል። ይህ ንግግር የሚያጐላው አምላክ ባለው ፍጹም (ገደብ የለሽ) ነፃነትና ለእኛ በተሰጠን ገደብ ያለው ነፃነት መካከል ያለውን ልዩነት ነው። በተጨማሪም እኛ ያለንን ነፃነት ከሁሉ በተሻለ ሁኔታ እንድንጠቀምበትም ያበረታታናል። ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው ፕሮግራም የነፃነታችንንና የአገልግሎታችንን የተለያዩ ገጽታዎች የሚመለከት ይሆናል። እውነተኛውን አምልኰ ለማስፋፋት ነፃ የወጡ በሚለው ድራማም ይደመደማል።
የሁለተኛው ቀን አጠቃላይ መልእክት በገላትያ 5:1 ላይ የተመሠረተ ሲሆን “አምላክ በሰጠን ነፃነት መጽናት” የሚል ይሆናል። የጧቱ ፕሮግራም በተለይ የአንድ ቤተሰብ አባሎች አምላክ የሰጣቸውን ነፃነት በቤተሰብ ክልል ውስጥ እንዴት ሊደሰቱበት እንደሚችሉ በተከታታይ ተናጋሪዎች ይብራራል። ለመጠመቅ የተዘጋጁትም ራስን በመወሰንና በመጠመቅ ነፃነት እንዴት እንደሚገኝ የሚሰጠውን ሐሳብ በተለይ የሚያደንቁት ይሆናል። ከሰዓት በኋላ በሚቀርበው ፕሮግራም ከሚጠቃለሉት መካከል ጋብቻ ለደስታ ቁልፍ ስለመሆኑና አለመሆኑ የሚገልጽ ማራኪ ውይይት ይገኝበታል። በተጨማሪም ተከታታይ ተናጋሪዎች ስለ ነፃነት የተለያዩ ገጽታዎች ያብራራሉ። በኋላም የዘላለም ሕይወትን ለማምጣት የአምላክ ዋና ወኪል በሆነው ላይ የሚያተኩር የመዝጊያ ንግግር ይኖራል።
እሁድ በ2 ቆሮንቶስ 3:17 ላይ የተመሠረተ “ነፃነታችንን ከአምላክ መንፈስ ጋር በሚስማማ መንገድ እንጠቀምበት” የሚል አጠቃላይ መልእክት ይኖረዋል። ፕሮግራሙ በማቴዎስ 13:47-50 ላይ በተመዘገበው የኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተመሠረተ የይሖዋ ምሥክሮች እንዴት የሰዎች አጥማጆች እንደሆኑ የሚገልጽ ልዩ ስሜት የሚቀሰቅስ በተከታታይ ተናጋሪዎች የሚሸፈን ይሆናል። ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው የሕዝብ ንግግር “ነፃነት የሚሰፍንበትን የአምላክን አዲስ ዓለም በዕልልታ መቀበል!” የሚል ይሆናል። ቀጥሎም ለወረዳ ስብሰባ አዲስ ገጽታ የሆነ ይከተለዋል፤ ማለትም የዚያ ሳምንት መጠበቂያ ግንብ ትምህርት ባጭሩ ይሸፈናል። ከዚያም ፕሮግራሙ ሁላችንም በጠባያችንና በምሥክርነታችን አምላክ የሰጠንን ነፃነት በጥሩ ሁኔታ በመጠቀም ማደጋችንን እንድንቀጥል በሚያሳስብ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ይዘጋል።
ለነፃነት አፍቃሪዎች በሙሉ በመዝሙራዊው ዳዊት ቃላት “ይሖዋ ቸር እንደሆነ ቅመሱ እዩም” እንላቸዋለን። (መዝሙር 34:8) ወደዚህ ስብሰባ ለመሄድ በምታደርገው ጥረት የማትፈነቅለው ድንጋይ አይኑር። ዓርብ ዕለት ጧት ከሚቀርበው የመክፈቻ ክፍለ ጊዜ ጀምሮ እሁድ ዕለት ከሰዓት በኋላ እስከሚሰጠው የመደምደሚያ ንግግር ድረስ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ለሚያስፈልግህ መንፈሣዊ ምግብ ንቁ ሆነህ ከጤናማ መንፈሳዊ ረሀብ ጋር ብትመጣ እውነትም ደስተኛ ትሆናለህ። (ማቴዎስ 5:3 አዓት) በተጨማሪም “በበረከት የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት አንርሳ። ይህም በስብሰባው ለመገኘት አስቀድመን እንዴት ከልብ እንደምንዘጋጅ፣ ፕሮግራሙ ሲቀርብ እንዴት በትጋት እንደምናዳምጥና ከ“ነፃነት አፍቃሪዎች” የወረዳ ስብሰባችን ጋር በተያያዘ የሚከፈትልንን ማንኛውንም ዓይነት የፈቃደኝነት አገልግሎት እንዴት በትጋት እንደምንፈጽመው ያጠቃልላል።—2 ቆሮንቶስ 9:6