አምላክ የሰጠውን ነፃነት ከሚያፈቅሩ ሕዝቦች ጋር መሰብሰብ
የይሖዋ ምሥክሮች በብዙ መንገዶች ልዩ ሕዝቦች ናቸው። “ንጹሑን ልሣን” የሚናገሩት እነሱ ብቻ ናቸው። (ሶፎንያስ 3:9) ኢየሱስ ክርስቶስ የገለጸው የፍቅር መለያ ምልክት ያላቸውና አንድነት ያላቸው ሕዝቦች እነሱ ብቻ ናቸው። (ዮሐንስ 13:35) በዮሐንስ 8:32 ላይ “እውነትን ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” በሚለው ቃል መሠረት ኢየሱስ የተናገረለትን እውነት ከማወቅ የሚገኝ ነፃነት ያገኙት እነሱ ብቻ ናቸው።
የአምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት እውነት ሆነዋል። በ“ነፃነት አፍቃሪዎች” የወረዳ ስብሰባ ላይ የተገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ ከምንጊዜውም ይበልጥ እነዚህን ቃላት ተገንዝበዋል። የስብሰባው ፕሮግራም የነፃነታቸውን ልዩ ልዩ ገጽታዎች፣ ነፃነታቸውን እንዴት እንደሚጠቀሙበት፣ ከነፃነታቸው ጋር አብሮ የሚመጣውን ኃላፊነትና ነፃ ሕዝቦች በመሆናቸውም ምን ያህል የተባረኩ ሕዝቦች እንደሆኑ አስገንዝቧቸዋል።
እነዚህ ወቅታዊና ተግባራዊ ትምህርቶች የተሰጡባቸው ስብሰባዎች በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ በሚገኙ አገሮች የተጀመረው በዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ፣ በካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ ሰኔ 7, 1991 ነበር። ፕሮግራሙ ከጧቱ በ4 ሰዓት ከ20 በአጭር የሙዚቃ ፕሮግራም በኋላ በመዝሙርና በጸሎት ተከፈተ። የመክፈቻ ንግግሩ በያዕቆብ 1:25 ላይ የተመሠረተ ኃይለኛ መልእክት ያለው ነበር። ይህ ጥቅስ በኢየሩሳሌም መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት “ፍጹሙን የነፃነት ሕግ አተኩሮ የሚመለከትና ይህንኑም ልማዱ የሚያደርግ፣ ከሰማ በኋላ የሚረሳ ሳይሆን በተግባር የሚተረጉመው በሚሠራው ነገር ሁሉ ደስተኛ ይሆናል” በማለት ይነበባል። መልካችንን በመስተዋት አይተን መስተካከል የሚያስፈልገውን እንደምናስተካክል ሁሉ በባሕሪያችንም ምን ለውጥ ማድረግ እንዳለብን ለማወቅ የአምላክን ፍጹም የነፃነት ሕግ አተኩረን መመልከት ያስፈልገናል። ይህን መስታወት ያለማቋረጥ መመልከት አለብን።
ቀጥሎ “ነፃነት አፍቃሪዎች በሙሉ እንኳን ደህና መጣችሁ” የሚለው የሊቀመንበሩ ንግግር ቀረበ። የይሖዋ ምሥክሮች ነፃነት ወዳድ ናቸው፤ ነፃ ሆነው መኖርም ይፈልጋሉ። ተናጋሪው ያለ ሕግ ነፃነት ሊኖር የማይችል መሆኑን የሚገልጹ የሕግ ሊቃውንትን ሐሳብ ጠቀሰ። አዎ ክርስቲያኖችም ነፃ የሆኑት ደስ ያሰኛቸውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ሳይሆን የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ነው። ነፃነታቸውን ሙሉ በሙሉ ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ እንጂ ያለአግባብ ሊጠቀሙበት አይፈልጉም። በተለይ ከ1919 ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች ተጨማሪ ነፃነት አግኝተዋል። ተናጋሪው በስብሰባው ርዕሶችና በክርስቲያናዊ ጽሑፎች ስለ ነፃነት ጎላ ብሎ መገለጹን ዘረዘረ። ሁሉም ተሰብሳቢዎች ከአምላክ ስለተሰጣቸው ነፃነትና ይህንን ነፃነት እንዴት እንደሚጠቀሙበት የበለጠ እንደሚማሩ ገለጸ።
እነዚህ ወቅታዊ አስተያየቶች በማስከተልም በስብሰባው ላይ በመገኘታቸው ከተደሰቱ ነፃነት አፍቃሪዎች ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ ቀርቧል። የጥንት እሥራኤላውያን በዓመት ውስጥ በሚያከብሯቸው ሦስት በዓሎች አንድ ላይ ሲሰበሰቡ በጣም ይደሰቱ እንደነበረ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም በስብሰባዎች ሲገኙ በጣም ይደሰታሉ። ስብሰባዎች መንፈሳዊ መታነጽ የሚገኝባቸውና የደስታ ጊዜዎች እንደሆኑ በርካታ ቃለ ምልልሶች አረጋግጠዋል።
ከዚያም “ከአምላክ የተሰጠን ነፃነት ዓላማውና አጠቃቀሙ” የሚለው የስብሰባውን አጠቃላይ መንፈስ የሚገልጽ ንግግር ቀርቧል። ተሰብሳቢዎች ይሖዋ ከፍተኛው ባለሥልጣንና ሁሉን ቻይ አምላክ ስለሆነ ፍጹም ነፃነት ያለው እሱ ብቻ መሆኑን ከዚህ ንግግር ተምረዋል። ይሁን እንጂ ለስሙና ለፍጡሮቹ ጥቅም ሲል ለቁጣ የዘገየ በመሆን ራሱን ገዝቷል። ይህንንም በማድረግ በነፃነቱ ላይ ገደብ አድርጓል። አስተዋይ ፍጡሮቹ ሁሉ ለይሖዋ የሚገዙና በሱ ፍጥረታዊና ሥነ ምግባራዊ ሕጎች የሚወሰኑ ስለሆኑ ያላቸው ነፃነት አንጻራዊ ነው። ይሖዋ ለደስታቸው የሚበጅ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። በተለይ ግን ነፃነት የሰጣቸው እሱን በማምለክ ክብርና ደስታ እንዲያመጡለት ብሎ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነታቸው በጥሩ ሁኔታ በመጠቀማቸው፣ በጥሩ ጠባያቸውና ለአገልግሎቱ ባላቸው ቅንዓት መልካም ዝና አትርፈዋል።
ዓርብ ከሰዓት በኋላ
የዓርብ ዕለት ከሰዓት በኋላው ፕሮግራም የተከፈተው “ጊዜያችሁ የተያዘው በሞቱ ሥራዎች ነው ወይስ በይሖዋ አገልግሎት?” የሚል የሚያሳስብ ርዕስ ባለው ንግግር ነበር። የሞተ ሥራ ሲባል የሥጋ ሥራን ብቻ ሳይሆን ገንዘብ የሚገኝባቸውንና የመሳሰሉትን በመንፈሳዊ ሙት የሆኑ፣ ከንቱ፣ ፍሬ ቢስ ሥራዎችን ሁሉ ይጨምራል። በዚህ ረገድ መንግሥቱን በሕይወታችን እያስቀደምን እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ በሐቀኝነት ራሳችንን መመርመር ያስፈልገናል።
“የአምላክ አገልጋዮች በመሆን የተሰጠንን ተልእኮ መፈጸም” የሚለው የሚቀጥለው ንግግርም ተመሳሳይ መልእክት ነበረው። ተናጋሪው ክርስቲያኖች በይስሙላ አገልግሎት ወይም የሰዓት ግቦችን በማሟላት ብቻ መርካት እንደሌለባቸው ገለጸ። በሁሉም የክርስቲያናዊ አገልግሎት ገጽታዎች ውጤታማ ለመሆን መፈለግ ይኖርባቸዋል። እነዚህን ቁም ነገሮች የሚያስገነዝቡ ትዕይንቶችና ቃለ ምልልሶች ቀርበዋል። ሁሉም የተቻላቸውን ያህል አገልግሎታቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲፈጽሙ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።
“ነፃ፤ ግን ተጠያቂነት ያለበት ሕዝብ” በሚለው ንግግር ተናጋሪው አጥብቆ የገለጸው የይሖዋ ሕዝቦች እውነት ያመጣላቸውን ነፃነት የሚያፈቅሩ ቢሆንም ከነፃነታቸው ጋር ኃላፊነትም አብሮ የሚመጣ መሆኑንም ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ነፃነታቸውን ሊጠቀሙበት የሚገባው ለመጥፎ ጠባይ ማመካኛ ለማድረግ ሳይሆን ለይሖዋ ክብር መሆን ይኖርበታል። በክርስቲያንነታቸው “ለበላይ ባለሥልጣኖች” ተጠያቂዎች ናቸው። በተጨማሪም ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር መተባበር ይኖርባቸዋል። (ሮሜ 13:1) ከዚህም በላይ ስለ አለባበሳቸው፣ ስለ ጸጉር አበጣጠራቸውና ስለ ጠባያቸው ተጠያቂዎች ናቸው። “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንደምንሰጥ” ፈጽሞ መርሳት የለባቸውም።—ሮሜ 14:12፤ 1 ጴጥሮስ 2:16
ከዚያም በኋላ ክርስቲያኖች ሁሉ “የዓለም ፍጻሜ እየቀረበ ሲመጣ ፍርሃትን ማስወገድ” እንደሚያስፈልጋቸው የሚገልጸው ንግግር ቀጠለ። የሰው ልጅ መጪው ጊዜ ስለሚያመጣው ነገር በፍርሐት ሲዋጥ ክርስቲያኖች ግን አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ደፋር መሆን ያስፈልጋቸዋል። ድፍረት የሚገኘው በይሖዋ ከመተማመን ነው። ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን አምላክን ላለማሳዘን በፈራ መጠን ለፍጡሮች ያለው ፍርሐት ያነሰ ይሆናል። የሚያጽናኑ ጥቅሶችን በቃል ማጥናት አንድ ሰው ደፋር እንዲሆን ሊያበረታው ይችላል። የአምላክ አገልጋዮች በመንፈሳዊ ጠንካራና ደፋር ለመሆን ከመሰል አማኞች ጋር ለመሰብሰብና አብሮ ለመሆን ባላቸው አጋጣሚ ሁሉ በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋቸዋል። እያንዳንዱም ደፋር ለመሆን ጸሎት የሚጫወተውን ሚና ማስታወስ ያስፈልገዋል። ክርስቲያኖች ደፋር ሆነው በመኖር ከይሖዋ አምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ይኖራቸዋል።
የመጀመሪያው ቀን ስብሰባ የተደመደመው “እውነተኛ አምልኮን ለማስፋፋት ነፃ መውጣት” የሚል ርዕስ ባለው በጣም ትምህርት ሰጪ በሆነ ድራማ ነበር። ድራማው አንድ የዘመናችን ቤተሰብ ብዙ መሥዋዕቶችን ከፍለው ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱት ከዕዝራና 7,000 ከሚያክሉት ሰዎች ትምህርት እንዳገኘ ያሳያል። እያንዳንዱ ተሰብሳቢ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ነገሮች እንዲመረምርና የአገልግሎት መብቱን እንዴት ሊጨምር እንደሚችል እንዲያስብ አስችሎታል። ይህ ድራማ በዕድሜ ለገፉትም ሆነ ለወጣቶች የሚጠቅም ትምህርት ነበረው።
ቅዳሜ ጠዋት
ከሙዚቃ ፕሮግራም፣ ከመዝሙር፣ ከጸሎትና በዕለታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ የቅዳሜ ጧት ፕሮግራም ተጀመረ። በመጀመሪያ የቀረበው “በቤተሰብ ክልል ውስጥ ያለ ነፃነትና ኃላፊነት” የሚል ርዕስ የነበረውን በተከታታይ ተናጋሪዎች የቀረበውን ነበር። “አባቶች ይሖዋን ለመምሰል የሚችሉት እንዴት ነው?” በሚለው የመጀመሪያ ክፍል አባቶች ሰማያዊውን አባታችንን ሊመስሉ ስለሚችሉባቸው የተለያዩ መንገዶች ተመክረዋል። በ1 ጢሞቴዎስ 5:8 መሠረት ለቤተሰባቸው እንዲያቀርቡ የሚፈለግባቸው ሥጋዊ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ነገሮችን ጭምር ነው። የቤተሰባቸው መልካም አስተማሪዎች በመሆንና አስፈላጊ ሲሆንም ፍቅራዊ ቅጣትን በመፈጸም ይሖዋን ሊመስሉት ይችላሉ።
የዚህ ተከታታይ ንግግር የሚቀጥለው ክፍል “የሚስት አጋዥነት ሚና” የሚል ነበር። ሚስት በክርስቲያናዊ ቤተሰብ ውስጥ ድጋፍ የመስጠት የተከበረ ቦታ እንዳላት አጥብቆ በመግለጽ ይጀምራል። ይህስ ከእሷ ምን ይጠይቅባታል? ባሏ እሷ ብቻ የምትፈልገውን ነገር እንዲያደርግ ግፊት ሳታደርግ በተገቢ ሁኔታ እንድትገዛለት ይጠይቅባታል። ለባሏና ለልጆቿ ያለባትን ግዴታ በሚገባ ማከናወን ያስፈልጋታል። ቤቷን ንጹሕና ያልተዝረከረከ ጽዱ አድርጋ በመጠበቅ እውነተኛ እርካታ ልታገኝ ትችላለች። ክርስቲያን አገልጋይ በመሆንም በመስክ አገልግሎት የምትካፈልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ሊኖሯት ይችላሉ። ከአንድ ቤተሰብ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ ይህ ምክር ጥበብ ያለው መሆኑን አስገንዝቧል።
ወጣቶችም “የሚያዳምጡና የሚማሩ ልጆች” በተሰኘው ክፍል ትኩረት አግኝተዋል። ወላጆች ልጆቻቸው እንዲያዳምጡና እንዲማሩ በማሠልጠን ለይሖዋ ክብር ያመጣሉ። ለመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና ለራሳቸው ልጆችም ፍቅር ያሳያሉ። ወላጆችና ልጆች ብዙ ጊዜ አብረው ጊዜ ካሳለፉ በመካከላቸው ጠንካራ መተሳሰር ይኖራል። ወላጆች የልጆቻቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ የተዘጋጁ መሆንና የዕውቀት ጥማት እንዲኖራቸው መቀስቀስ አለባቸው። ይህንንም እንዴት ማድረግ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ቃለ ምልልሶች ቀርበዋል።
ቀጥሎ የቀረበው “ይሖዋን ለማገልገል ከማንኛውም ጣጣ ነፃ ሁኑ” የሚል ጥሩ ምክር ነበር። ዓለማዊ ሥራዎችን፣ ጊዜ የሚፈጁ መደበኛ ያልሆኑ ሥራዎችን ዓለማዊ ግቦችን ከማሳደድ ነፃ በመሆን ነው። ኢየሱስና ሐዋርያው ጳውሎስ ራስን በመሠዋት ረገድ መልካም ምሳሌ ትተውልናል። የይሖዋ ሕዝቦች ያልተወሳሰቡና በመንግሥቱ ፍላጎቶች ላይ ያተኮሩ ቀላል ዓይኖች እንዲኖሯቸው ያስፈልጋል። ቁሳዊ ነገሮችን ማግኘትን በተመለከተ አሁን ገዝቶ በኋላ ከመክፈል አሁን ቆጥቦ አጠራቅሞ በኋላ መግዛት ጥበብ ነው። ወጣቶች ስለ ከጾታዊ ግንኙነት ስለሚገኙ ደስታዎችና ስለ ዓለማዊ ሥራዎች በቅዠት ዓለም ከመኖር ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው። ከአንድ አቅኚ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ አንድ ሰው ይሖዋን ለማገልገል ራሱን ነፃ በሚያደርግበት ጊዜ የሚያገኛቸውን በረከቶች ገልጿል።
የቅዳሜ ጠዋት ፕሮግራም የተደመደመው “ራሳችሁን ለአምላክ በመወሰንና በጥምቀት ወደ ነፃነት ግቡ” በሚል ንግግር ነበር። የጥምቀት ዕጩዎቹ የሰው ልጅ ወደ ባርነት የተጣለ ሲሆን ኃያሉ ነፃ አውጪ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሥዋዕቱ አማካኝነት የነፃነትን ጐዳና እንደከፈተ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። ተናጋሪው የአምላክን ፈቃድ ከማድረግ ነፃ መውጣት ምን ነገሮችን እንደሚያጠቃልል ከመግለጹም በላይ የሚጠመቁ ሰዎች የሚያገኙአቸውን ግዴታዎችና በረከቶች ጐላ አድርጎ ገልጿል።
ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ
የቅዳሜ ከሰዓት በኋላው ፕሮግራም የተጀመረው “የማንን ጥቅም ለማስቀደም ትጥራለህ?” በሚል ልብን የሚመረምር ጥያቄ ነበር። ዓለም የሚያንፀባርቀው የዲያብሎስን የራስ ጥቅም የማሳደድ መንፈስ ነው። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስን ራስን መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ መቅዳት አለባቸው። ኢየሱስ የተወልን ምን ዓይነት ምሳሌ ነበር? ሰማያዊ ክብሩን ትቶ ከመምጣቱም በላይ ሰብአዊ ሕይወቱንም ለእኛ ጥቅም ሲል መሥዋዕት አድርጓል። የማንን ጥቅም እየፈለግን መሆናችን ይፋ የሚያወጣው በክርስቲያኖች መካከል በንግድ ወይም በገንዘብ ጉዳዮች ላይ አለመግባባት ሲፈጠር፣ የእርስ በርስ ግጭት ሲያጋጥም ወዘተ ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ነገሮች ክርስቲያናዊ ፍቅርን ይፈትናሉ። ይሁንና አንድ ሰው የሌሎችን ጥቅም ሲያስቀድም መስጠት የሚያስገኛቸውን ከፍተኛ በረከቶች እንደሚያገኝና የይሖዋን ሞገስም እንደሚያተርፍ እርግጠኛ ነው።
ከዚህ በመቀጠልም “መንፈሳዊ ድክመቶችን ማወቅና ማሸነፍ” የሚለው ከላይ ከተሰጠው ንግግር ጋር የሚቀራረብ መልእክት ያለው ንግግር ቀርቧል። ይህ ንግግር የጐላው የመንፈሳዊ ድክመቶችን ምልክቶች ለይቶ የማወቅንና ሰይጣንንና ወጥመዶቹን ለማሸነፍ በመዋጋት በቁርጠኝነት የመነሣትን አስፈላጊነት ነው። የይሖዋ አገልጋዮች ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅርና መጥፎ ለሆነው ነገር ደግሞ ጥላቻን መኮትኮት አለባቸው። ይህም ዘወትር በሚደረግና ዓላማ ባለው የግልና የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ይሖዋን እንዲያውቁት ይጠይቅባቸዋል። ዓመፅንና የጾታ ብልግናን የሚያሞጋግሱ የመዝናኛ ዓይነቶችን በሙሉ ማስወገድ አለባቸው። (ኤፌሶን 5:3-5) የዘወትር ጸሎትና በስብሰባዎች መገኘትም መንፈሳዊ ድክመቶችን በመቋቋሙ ረገድ የተሳካ ውጤት ለማግኘት አስፈላጊ ናቸው።
ምናልባትም በስብሰባው ውስጥ ከተሰጠው ከማንኛውም ንግግር ይበልጥ ብዙ ያወያየው “ጋብቻ ደስታ የሚገኝበት ቁልፍ ነውን?” የሚል ርዕስ የነበረው ንግግር ሳይሆን አልቀረም። በጣም ብዙ ወጣቶች ጋብቻ ለደስታ ቁልፍ እንደሆነ ያስባሉ! ተናጋሪው ግን ባያገቡም ደስተኞች የሆኑ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ታማኝ መንፈሳዊ ፍጡሮችና በጋብቻ ባይተሳሰሩም ብዙ ደስታ ያገኙ ውስን ክርስቲያኖች እንዳሉ ግልጽ አድርጓል። ከዚህም በላይ ፍቺ በጣም መብዛቱ እንደሚጠቁመው ብዙ የተጋቡ ባልና ሚስቶች ደስተኞች አይደሉም። አንድ ሰው ጋብቻ በረከት ሊሆን ቢችልም ለደስታ ቁልፍ ያለመሆኑን ለመገንዘብ ውስን ክርስቲያኖች በሙሉ የሚያገኟቸውን ብዙ በረከቶች ማሰብ ያስፈልጋቸዋል።
ከዚህ በማስከተልም “ክርስቲያናዊ ነፃነት በዘመናችን” የተሰኘው ርዕስ በተከታታይ ተናጋሪዎች ቀረበ። የመጀመሪያው ተናጋሪ “የክርስቲያናዊ ነፃነት ገጽታዎች” በሚል ርዕስ ንግግር አደረገ። እነዚህ የክርስቲያናዊ ነፃነታችን ገጽታዎችም ሥላሴ፣ የሰው ነፍስ አለመሞትና ዘላለማዊ ሥቃይ ከመሳሰሉት የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ነፃ መሆንን ይጨምራሉ። ከኃጢአት የባርነት ግዞት ነፃ መውጣትም አለ። ክርስቲያኖች ፍጽምና የሌላቸው ቢሆኑም እንደ ማጨስ፣ ቁማር፣ ስካርና የጾታ ልክስክስነት ከመሳሰሉት መጥፎ ዐመሎች ነፃ ናቸው። ከተስፋ መቁረጥም ነፃነት አግኝተዋል። ለሌሎች ሰዎች እንዲናገሩ የሚገፋፋቸው የገነት ተስፋ አላቸው።
ተከታዩ ተናጋሪ “እናንተ ራሳችሁ ይህ ዓይነቱን ነፃነት እንደ ውድ ነገር ቆጥራችሁ ትይዙታላችሁን?” የሚለውን ጥያቄ አቀረበ። ከፍተኛ ዋጋ መስጠት ማለት እንደ ውድ ነገር መቁጠር በጥንቃቄ መከባከብ ማለት ነው። ይህን ለማድረግም አንድ የአምላክ አገልጋይ የክርስቲያናዊ ነፃነትን ድንበሮች አልፎ ከመሄድ ፈተና ራሱን መጠበቅ አለበት። የዓለም ነፃነት የኃጢአትና የውዳቂ ስነ ምግባር ባርነት ስለሚያስከትል አታላይና ሐሰት ነው።
በዚህ ተከታታይ ንግግር የመጨረሻው ተናጋሪ የሆነው ወንድም የተናገረው “ነፃነት አፍቃሪዎች በአቋማቸው ይጸናሉ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ነበር። ይህን ለማድረግም ክርስቲያኖች ሰማያዊ ወላጆቻቸው ከሆኑት ከይሖዋና ከሚስት መሰሏ ድርጅቱ ጋር መቀራረብ አለባቸው። የይሖዋ ሕዝቦች የክህደት ፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ የተከተለ ሐሳብ ይዘው የመጡባቸውን ሁሉ ሐፍረት አከናንበው መመለስ አለባቸው። ክርስቲያኖች በአምላካዊ ነፃነት ጸንቶ ለመቆም “በመንፈስ መኖር” አለባቸው።—ገላትያ 5:25
የዕለቱ የመጨረሻ ንግግር በእርግጥ አስደሳች ነበር። ርዕሱ “እስከ ዛሬ ድረስ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጥ ሰው” የሚል ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉም ሠራዊቶች፣ የባሕር ኃይሎች፣ ፓርላማዎች ወይም ምክር ቤቶችና ነገሥታት አንድ ላይ ቢደመሩ ከሚኖራቸው ኃይል የበለጠ ተጽእኖ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ ያሳደረ በመሆኑ ታላቅ ሰው ነው። ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት በሰማይ የሚኖር የአምላክ ልጅ ነበር። ኢየሱስ “እኔን ያየ አብን አይቷል” ብሎ መናገር እስኪችል ድረስ በተናገረው፣ ባስተማረው ትምህርትና ባኗኗሩ ሰማያዊ አባቱን ጥሩ አድርጎ ቀድቷል። (ዮሐንስ 14:9) ኢየሱስ “አምላክ ፍቅር” መሆኑን ግሩም በሆነ መንገድ አሳይቷል። (1 ዮሐንስ 4:8) ተናጋሪው ስለ ኢየሱስ ባሕርያት በሠፊው ከዘረዘረ በኋላ “የኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎቱ” የተሰኘው ተከታታይ ርዕሰ ትምህርቶች ከ1985 ጀምሮ በመጠበቂያ ግንብ ላይ ሲወጣ እንደቆየ ገለጸ። ማህበሩ ለብዙ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የበለጠው ታላቅ ሰው የተሰኘው መጽሐፍ እንደወጣም ገለጸ። መጽሐፉ 133 ምዕራፎችና በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ ሥዕሎች አሉት። በመጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡት ተከታታይ ርዕሰ ትምህርቶች በሙሉ በመጽሐፉ ላይ ወጥተዋል። በመጽሐፉ 448 ገጾች ተጠቃልለዋል። በእርግጥም ይህ የስብሰባ ቀን ያበቃው ከፍተኛ በሆነ መንፈስ ነበር።
እሁድ ጠዋት
በእሁድ ጠዋቱ ስብሰባ ቀደም ብሎ “ምሳሌያዊ ዓሣ አጥማጅ ሆኖ ማገልገል” በሚል ርዕስ በተከታታይ ተናጋሪዎች ቀረበ። “ምሳሌያዊና እውነተኛ ዓሦችን መያዝ” የሚለው ንግግር ለተከታዮቹ ንግግሮች መሠረት ጥሏል። ተናጋሪው ኢየሱስ የዓሣ ማጥመድ ተአምር ከፈጸመ በኋላ ዓሣ አጥማጆች እንዲሆኑ እንደጋበዛቸው ገለጸ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሰዎችን አጥማጆች እንዲሆኑ ለጥቂት ጊዜ ካሰለጠናቸው በኋላ በ33 እዘአ ከዋለው የጴንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ ብዙ ወንዶችና ሴቶችን ደቀመዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ችለዋል። ተከታዩ ተናጋሪ በማቴዎስ 13:47-50 የተመዘገበውን የመረብ ምሳሌ የሚመረምር ነበር። ይህ ተናጋሪ ምሳሌያዊው መረብ ቅቡዓን ክርስቲያኖችንና ሕዝበ ክርስትናን እንደሚጨምር፣ ሕዝበ ክርስትና የተጨመረችው መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎም፣ በማተምና በማሠራጨት በፈጸመችው ሥራ ምክንያት እንደሆነና ሆኖም ግን ይህ ጥረቷ በጣም ብዙ መጥፎ ዓሦችን እንደሰበሰበ አመለከተ። በተለይ ከ1919 ወዲህ የመለያየት ሥራ እንደተካሄደና መጥፎ ዓሦች ሲጣሉ ጥሩዎቹ ግን እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለመለኮታዊ አገልግሎት በመከላከልና በመጠበቅ ወዳገለገሉት በዕቃ የተመሰሉ ጉባኤዎች ተጨምረዋል።
“በዓለም ዙሪያ ባሉት ውኃዎች ውስጥ ሰዎችን እንደ ዓሣ መያዝ” የተሰኘው ሦስተኛው ንግግር ሁሉም ውስን ክርስቲያኖች በዓለም አቀፉ የዓሣ ማጥመድ ሥራ የመካፈል ግዴታ እንዳለባቸው አጥብቆ አሳሰበ። አሁን በዚህ ሥራ ከ200 በላይ በሆኑ አገሮች ከ4,000,000 የሚበልጡ ክርስቲያኖች እየተካፈሉ ሲሆን በቅርብ ዓመታትም በየዓመቱ ከ230,000 የሚበልጡ ሰዎች ሲጠመቁ ቆይተዋል። ሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች የዓሣ ማጥመድ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ በጥብቅ ተመክረዋል። ብዙ የተሳካ ውጤት ያገኙ “ዓሣ አጥማጆችም” ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል።
በዚህ ተከታታይ ንግግር መጨረሻ በሆነውና “በፍጻሜው ዘመን ነቅቶ መኖር” በሚል ርዕስ በቀረበው ንግግር ተናጋሪው የአምላክ ሕዝቦች ነቅተው እንዲኖሩ የሚረዷቸውን ሰባት ነገሮች ዘረዘረ። እነሱም የሐሳብ መበታተንን መዋጋት፣ መጸለይ፣ ስለዚህ ሥርዓት ፍጻሜ የሚገልጸውን ማስጠንቀቂያ ማሰማት፣ ከይሖዋ ድርጅት ጋር መቀራረብ፣ ራስን መመርመር፣ በተፈጸሙት ትንቢቶች ላይ ማሰላሰልና አማኞች ከሆኑበት ጊዜ ይልቅ ዛሬ መዳናቸው የቀረበ መሆኑን ማስታወስ ናቸው።
የጠዋቱ ፕሮግራም የተደመደመው “‘ከጭንቀት ቀን’ የሚያመልጥ ማን ይሆን?” በሚል ንግግር ነበር። ተናጋሪው የኢዩኤል ትንቢት እንዴት በሐዋርያት ዘመን መጠነኛ ፍጻሜ እንደነበረውና አሁንም ተጨማሪ ፍጻሜ ሲያገኝ እንደቆየና ወደፊት በቅርቡ የተሟላ ፍጻሜ እንደሚኖረው ገለጸ።
እሁድ ከሰዓት በኋላ
ከሰዓት በኋላ የቀረበው ፕሮግራም የተጀመረው “የአምላክን አዲስ የነፃነት ዓለም በእልልታ ማወደስ” በሚል የሕዝብ ንግግር ነበር። ይህ ንግግር የስብሰባው ዋና መልእክት የሆነውን ነፃነት የሚያብራራ ነበር። ንግግሩ የአምላክ ቃል ከሐሰት ሃይማኖት፣ ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ ባርነትና ከዘር ጭቆና ነፃነት ስለሚገኝበት አዲስ ዓለም እንደሚተነብይ አመለከተ። ከኃጢአትና ከሞትም ነፃነት ይኖራል። ሕዝቦች በገነት ምድር ላይ ለዘላለም በደስታ መኖር እንዲችሉ ፍጹም ጤንነት ያገኛሉ። በመሆኑም የጽድቅ አፍቃሪዎች “ይሖዋ ሆይ በመጨረሻ ላጐናጸፍከው እውነተኛ ነፃነት እናመሰግንሃለን!” በማለት የአዲሲቱን ዓለም ሠሪ በአድናቆት የሚያመሰግኑበት ብዙ ምክንያት ይኖራቸዋል።
ከሕዝብ ንግግሩ በኋላ የተከተለው በወረዳ ስብሰባዎች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው የሳምንቱ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ውይይት ነው። ከዚያ በኋላ ስብሰባው ቀስቃሽ በሆነና “ነፃነት አፍቃሪዎች ሆይ፣ አሁንም ወደፊት ግፉ” በሚል ምክር አበቃ። ተናጋሪው የስብሰባው ዋና መልእክት የሆነውን የነፃነት ዋና ዋና ነጥቦች ባጭሩ ዘረዘረ። የይሖዋ ሕዝቦች በነፃነታቸው ምክንያት ምን ያህል ደስተኛ ሕዝቦች እንደሆኑ በድጋሚ ካሳሰበና ክርስቲያኖች መሻሻል ያደረጉባቸውን መንገዶች ከዘረዘረ በኋላ ተጨማሪ በረከቶችን ለማግኘት በኅብረት ወደፊት መራመዳቸውን እንዲቀጥሉ በጥብቅ አሳሰባቸው። ንግግሩንም “ይህንንም ስናደርግ ሁላችንም ነፃነት አፍቃሪዎች በመሆን ወደፊት በመራመድ እንድንቀጥል ይሖዋ በረከቱን አያቋርጥብን” በሚሉት ቃላት ደመደመ።
“ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቷልና በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም። ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።”—ሮሜ 8:20, 21
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቼኮስሎቫኪያ ፕራግ በተደረገው ስብሰባ ላይ የተገኘ አንድ ወጣት ልኡክ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
1. በፕራግ ቼኮስሎቫኪያ የጥምቀት ዕጩዎች ወደ መጠመቂያው ቦታ ሲሄዱ።
2. በታሊን ኢስቶኒያ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዷ በመሆን ስትጠመቅ
3. በሳይቤሪያ ኡሶሊ ሲብርስኮይ በስብሰባው ላይ የወጡት አዳዲስ ጽሑፎች ተሰብሳቢዎቹን በጣም አስደስተዋል
4. በፕራግ በተደረገው ስብሰባ “አዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም” በቼክና በስሎቫክ ቋንቋዎች እንደወጣ ማስታወቂያ ሲነገር