በክርስቲያናዊ ነፃነታችሁ በጥበብ ተጠቀሙበት
“እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ሆናችሁ በነፃነት ኑሩ”—1 ጴጥሮስ 2:16
1. አዳም ያጣው ምን ዓይነት ነፃነት ነበር? ይሖዋስ ለሰው ልጆች መልሶ የሚያመጣላቸው ምን ዓይነት ነፃነት ነው?
የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በኤደን የአትክልት ቦታ ኃጢአት በሠሩ ጊዜ ለልጆቻቸው ማስተላለፍ የነበረባቸውን ከኃጢአትና ከጥፋት ነፃ የመሆን ክብራማ ውርሻ አጡ። በዚህም የተነሳ ሁላችንም የጥፋትና የሞት ባሪያዎች ሆነን ተወለድን። ይሁን እንጂ ይሖዋ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ግሩም የሆነ ነፃነት መልሶ የሚያመጣበትን ዝግጅት ማድረጉ በጣም ያስደስታል። ዛሬ፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ‘ከጥፋት ባርነት ነፃ ወጥተው ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብራማ ነፃነት እንዲደርሱ’ በጉጉት ይጠብቃሉ።—ሮሜ 8:19-21
‘ለስብከት የተቀቡ’
2, 3. (ሀ) “የአምላክ ልጆች” እነማን ናቸው? (ለ) ምን ዓይነት አቋም አግኝተዋል? ይህስ ምን ዓይነት ኃላፊነት አስከትሎባቸዋል?
2 እነዚህ “የአምላክ ልጆች” እነማን ናቸው? ከኢየሱስ ጋር በሰማያዊ መንግሥት የሚገዙ በመንፈስ የተቀቡ የኢየሱስ ወንድሞች ናቸው። የመጀመሪያዎቹ “የአምላክ ልጆች” አባላት የታዩት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ነበር። እነርሱም ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነፃ የሚያወጣ እውነት ተቀበሉ። በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምረው ደግሞ ጴጥሮስ “የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ” በማለት ከተናገረለት ክብራማ መብት መካፈል ጀመሩ።—1 ጴጥሮስ 2:9ሀ፤ ዮሐንስ 8:32
3 ‘ለርስቱ የተለየ ወገን’ መሆን በእርግጥም በጣም አስደናቂ በረከት ነው። በዘመናችን ያሉት የአምላክ ልጆች ቀሪዎችም እነርሱ ያገኙትን የመሰለ አቋም ከአምላክ ዘንድ አግኝተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ከፍተኛ የሆነ መብት ኃላፊነትም አስከትሎባቸዋል። ጴጥሮስ እንደሚከተለው በማለት ከእነዚህ ኃላፊነቶች አንዱን ጠቅሷል። “እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት” ተናገሩ።—1 ጴጥሮስ 2:9ለ
4. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ክርስቲያናዊ ነፃነታቸው ያስከተለባቸውን ኃላፊነት የፈጸሙት እንዴት ነው?
4 ቅቡአን ክርስቲያኖች ይህንን የአምላክን ክብር በሰፊው የመናገር ኃላፊነታቸውን ፈጽመዋልን? አዎ፣ ፈጽመዋል። ኢሳይያስ ከ1919 ጀምሮ ስለሚኖሩት ቅቡዓን ትንቢት ሲናገር “የጌታ [የይሖዋ (አዓት)] መንፈስ በእኔ ላይ ነው፣ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ [ይሖዋ (አዓት)] ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፣ ለተማረኩትም ነፃነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል። የተወደደችውን [የይሖዋ (አዓት)] ዓመት አምላካችንም የሚበቀልበትን ቀን እናገር ዘንድ” ብሏል። (ኢሳይያስ 61:1, 2) ዛሬ፣ ቅቡዓን ቀሪዎች ይህ ትንቢት ዋነኛ ፍጻሜውን ያገኘበትን የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ይህን የነፃነት ምሥራች ለሌሎች ሰዎች በቅንአት በማወጅ ላይ ይገኛሉ።—ማቴዎስ 4:23-25፤ ሉቃስ 4:14-21
5, 6. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች በጋለ ስሜት በመስበካቸው ምን ውጤት ተገኝቶአል? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎች የሚደሰቱባቸው ምን መብቶችና ኃላፊነቶች አግኝተዋል?
5 ቅቡዓን ቀሪዎች በጋለ ስሜት በመስበካቸው ምክንያት በእነዚህ በኋለኞቹ ዘመናት የሌሎች በጎች እጅግ ብዙ ሕዝብ በዓለም መድረክ ላይ ሊታይ ችሎአል። እነዚህ ሰዎች ከቅቡዓን ጋር ተባብረው ይሖዋን ለማገልገል ከአሕዛብ ሁሉ ተውጣጥተዋል። እውነት እነሱንም ነፃ አውጥቷቸዋል። (ዘካርያስ 8:23፤ ዮሐንስ 10:16) ልክ እንደ አብርሃም ባላቸው እምነት ምክንያት ጻድቃን ሆነው ተቆጥረዋል። ከይሖዋ አምላክም ጋር የተቀራረበ ዝምድና መሥርተዋል። ጻድቃን ሆነው መቆጠራቸው እንደ ረዓብ ደህንነት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ከአርማጌዶን ጥፋት ይተርፋሉ። (ያዕቆብ 2:23-25፤ ራእይ 16:14, 16) ሆኖም እንደነዚህ ያሉት ከፍተኛ መብቶች ስለ አምላክ ክብር የመናገር ኃላፊነት አስከትለውባቸዋል። ዮሐንስ “በታላቅም ድምፅ እየጮሁ፦ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው” እያሉ ይሖዋን በሕዝብ ፊት ሲያመሰግኑ የተመለከተው በዚህ ምክንያት ነው።—ራእይ 7:9, 10, 14
6 ባለፈው ዓመት ከአራት ሚልዮን በላይ የሚሆኑት የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባሎች ከጥቂት የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቀሪዎች ጋር ሆነው አንድ ቢልዮን የሚያክሉ ሰዓቶች የይሖዋን ክብር በማወጅ ሥራ አሳልፈዋል። ይህም መንፈሳዊ ነፃነታቸውን የሚጠቀሙበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው።
“ንጉሥን አክብሩ”
7, 8. ክርስቲያናዊ ነፃነታችን ዓለማዊ ባለ ሥልጣኖችን በተመለከተ ምን ኃላፊነት ያስከትልብናል? በዚህስ ረገድ እንዴት ያለውን የተሳሳተ ዝንባሌ ማስወገድ ይገባናል?
7 ክርስቲያናዊ ነፃነታችን ሌሎች ኃላፊነቶችንም ያስከትልብናል። ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ በመጻፍ አንዳንዶቹን ኃላፊነቶች አመልክቶአል፦ “ሁሉን አክብሩ ወንድሞችን ውደዱ፣ እግዚአብሔርን ፍሩ፣ ንጉሥን አክብሩ።” (1 ጴጥሮስ 2:17) “ንጉሥን አክብሩ” የሚለው አነጋገር ምን ያመለክታል?
8 “ንጉሥ” ዓለማዊ ገዢዎችን ያመለክታል። በዛሬው ጊዜ ለሥልጣን አልታዘዝም የማለት መንፈስ በዓለም ላይ በጣም ተስፋፍቷል። ይህ ደግሞ በቀላሉ ወደ ክርስቲያኖች ሊዛመት ይችላል። አንድ ክርስቲያን ‘ዓለም በሞላው በክፉው የተያዘ ከሆነ’ “ንጉሥን” ማክበር የሚኖርብኝ ለምንድን ነው ብሎ ሊያስብ ይችላል። (1 ዮሐንስ 5:19) በእነዚህ የዮሐንስ ቃላት መሠረት አመቺ ያልሆኑለትን ሕጎች ላለመታዘዝ ነፃ እንደሆነና ማምለጥ የሚቻል ሆኖ ካገኘው ግብር መክፈል እንደማይኖርበት ሊሰማው ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ኢየሱስ “የቄሣርን ለቄሣር” ክፈሉ ብሎ ከሰጠው ትዕዛዝ ጋር ይጋጫል።—ማቴዎስ 22:21፤ 1 ጴጥሮስ 2:16
9. ለዓለማዊ ባለ ሥልጣኖች የምንታዘዝባቸው ምን ሁለት ጥሩ ምክንያቶች አሉን?
9 ክርስቲያኖች ባለ ሥልጣኖችን የሚታዘዙት አለገደብ ባይሆንም ለባለ ሥልጣኖች ክብር የማሳየትና የመገዛት ግዴታ አለባቸው። (ሥራ 5:29) ለምን? ጴጥሮስ በ1 ጴጥሮስ 2:14, 15 ላይ ገዢዎች “ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና” ብሎ በተናገረ ጊዜ ሦስት ምክንያቶችን አመልክቷል። ባለ ሥልጣኖች የሚያመጡትን ቅጣት መፍራት ባለ ሥልጣኖችን ለማክበር የሚያስችል በቂ ምክንያት ነው። አንድ የይሖዋ ምሥክር ሰው ደብድቦ፣ ሰርቆ ወይም ሌላ ወንጀል ፈጽሞ በመገኘቱ ምክንያት ቢቀጣ ወይም ቢታሰር ምን ያህል የሚያሳፍር ነገር ይሆናል! ተቃዋሚዎቻችን አድራጎቱን ለሰው ሁሉ ለማውራትና ለማሳወቅ ምን ያህል ደስ እንደሚላቸው ገምቱ! በሌላ በኩል ደግሞ ለሕዝባዊ ባለ ሥልጣኖች በመታዘዝ በኩል ጥሩ ዝና ካተረፍን አድሎአዊነት ከሌላቸው ባለ ሥልጣኖች ምስጋና እንቀበላለን። ምሥራቹን የመስበክ ሥራችንን ለማከናወን እንድንችል የበለጠ ነፃነት ሊሰጠን ይችላል። በተጨማሪም ‘በጎ እያደረግን የማያውቁትን ሞኞች ዝም እናሰኛለን።’ (1 ጴጥሮስ 2:15ለ) ለባለ ሥልጣኖች የምንታዘዝበት ሁለተኛው ምክንያት ይህ ነው።—ሮሜ 13:3
10. ዓለማዊ ባለ ሥልጣኖችን የምንታዘዝበት ትልቁ ምክንያት ምንድን ነው?
10 ይሁን እንጂ ባለ ሥልጣኖችን የምንታዘዝበት ሌላ ጠንካራ ምክንያት አለን። ባለ ሥልጣኖቹ ሥልጣናቸው ላይ ሊቆዩ የቻሉት ይሖዋ ስለፈቀደላቸው ነው። ጴጥሮስ እንዳለው የፖለቲካ ገዥዎች በይሖዋ የተላኩ ናቸው። ክርስቲያኖችም እንዲገዙላቸው “የእግዚአብሔር ፈቃድ” ነው። (1 ጴጥሮስ 2:15ሀ) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ “ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በየሥልጣን ቦታቸው የተቀመጡት በአምላክ ነው” ብሎአል። ስለዚህ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነው ሕሊናችን ባለ ሥልጣኖችን እንድንታዘዝ ይገፋፋናል። ራሳችንን ለእነርሱ ለማስገዛት እምቢ ካልን “የእግዚአብሔርን ሥርዓት” እየተቃወምን ነው። (ሮሜ 13:1, 2, 5 [አዓት]) ከመካከላችን የአምላክን ሥርዓት ሊቃወም የሚፈልግ ማን ነው? እንዲህ ማድረግ በክርስቲያናዊ ነፃነት አላግባብ መጠቀም ይሆናል!
“ወንድሞችን ውደዱ”
11, 12. (ሀ) ክርስቲያናዊ ነፃነታችን በእምነት ጓደኞቻችን ረገድ ምን ዓይነት ኃላፊነት ያስከትልብናል? (ለ) በተለይ ፍቅርና አሳቢነት ማሳየት የሚገባን ለእነማን ነው? ለምንስ?
11 በተጨማሪም ጴጥሮስ አንድ ክርስቲያን ‘መላውን የወንድሞች ማኅበር መውደድ’ አለበት ብሎአል። (1 ጴጥሮስ 2:17 [አዓት]) ይህም ሌላው ክርስቲያናዊ ነፃነት የሚያስከትለው ኃላፊነት ነው። ሁላችንም የጉባኤ አባሎች ነን። ጉባኤው ደግሞ የዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ወይም ድርጅት ክፍል ነው። ለዚህ ዓለም አቀፍ ማኅበር ፍቅር ማሳየት ክርስቲያናዊ ነፃነትን በጥበብ መጠቀም ማለት ነው።—ዮሐንስ 15:12, 13
12 ሐዋርያው ጳውሎስ የተለየ ፍቅር ልናሳያቸው ስለሚገቡን ክርስቲያኖች ለይቶ አመልክቶአል። እንዲህ ብሎአል፦ “ለዋኖቻችሁ ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፣ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፣ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፣ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ።” (ዕብራውያን 13:17) በጉባኤ ውስጥ በዋነኝነት ወይም ቅድሚያ በመውሰድ የሚያገለግሉት ሽማግሌዎች ናቸው። እውነት ነው፣ እነዚህ ሰዎች ፍጹሞች አይደሉም። ይሁን እንጂ ሽማግሌዎች የሚመረጡት በአስተዳደር አካል የበላይ ተቆጣጣሪነት ነው። ጥሩ ምሳሌ በመሆንና አሳቢነት በማሳየት ጉባኤውን ይመራሉ። ለነፍሳችን እንዲተጉ ተሹመዋል። እንዴት ያለ ከባድ ኃላፊነት ነው! (ዕብራውያን 13:7) ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹ ጉባኤዎች ግሩም የሆነ የትብብር መንፈስ ያላቸው መሆኑ በጣም ያስደስታል። በእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ ማገልገል ሽማግሌዎችን ያስደስታል። ግለሰቦች ለመተባበር ፈቃደኛ አልሆን ሲሉ በጣም አስቸጋሪ ነው። ቢሆንም ሽማግሌው ሥራውን መስራቱ አይቀርም። ግን የሚሠራው ጳውሎስ እንዳለው “በኃዘን” ይሆናል። በእርግጥ ሽማግሌዎችን ማሳዘን እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው! እኛን መገንባት እንዲችሉ በሥራቸው ደስተኞች እንዲሆኑ እንፈልጋለን።
13. ከሽማግሌዎች ጋር የምንተባበርባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
13 ከሽማግሌዎች ጋር የምንተባበርባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? አንዱ መንገድ በመንግሥት አዳራሽ እድሳትና ጽዳት መርዳት ነው። ሌላው ደግሞ የታመሙትን በመጠየቅና የአካል ችግር ያለባቸውን በመርዳት መተባበር ነው። በተጨማሪም ለሽማግሌዎች ሸክም እንዳንሆን መንፈሳዊ ጥንካሬያችንን መጠበቅ ይኖርብናል። በጣም አስፈላጊ የሆነ የትብብር መስክ ደግሞ በራሳችን አኗኗርም ሆነ ሌሎች የሚፈጽሟቸውን ከባድ ኃጢአቶች ስንመለከት ለሽማግሌዎች በመንገር የጉባኤውን ስነ ምግባራዊም ሆነ መንፈሳዊ ንጽህና መጠበቅ ነው።
14. ሽማግሌዎች የሚወስዱትን እርምጃ በተመለከተ መተባበር የሚኖርብን እንዴት ነው?
14 አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎች የጉባኤውን ንጽህና ለመጠበቅ ሲሉ ንስሐ የማይገቡ ጥፋተኞችን ማስወገድ ያስፈልጋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 5:1-5) ይህም ጉባኤውን ይጠብቀዋል። በተጨማሪም ጥፋተኛውን ሊጠቅመው ይችላል። ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ቅጣት ኃጢአተኛውን ወደ አእምሮው እንዲመለስ ይረዳዋል። ሆኖም የተወገደው ሰው የቅርብ ወዳጃችን ወይም ዘመዳችን ቢሆንስ? የተወገደው ሰው አባታችን ወይም እናታችን ወይም ልጃችን ነው እንበል። ምንም ቢሆን የሽማግሌዎችን እርምጃ እናከብራለንን? እርግጥ፣ ከባድ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የሽማግሌዎችን ውሳኔ አልቀበልም ብሎ በጉባኤው ላይ መጥፎ ተጽእኖ ከሚያሳድረው ሰው ጋር በመንፈሳዊ መተባበራችንን መቀጠል በነፃነታችን አለአግባብ መጠቀም ነው። (2 ዮሐንስ 10, 11) የይሖዋ ሕዝቦች በእነዚህ ዓይነት ጉዳዮች ተባባሪዎች ስለሆኑ የሚመሰገኑ ናቸው። ከዚህም የተነሳ በዚህ የተጨማለቀ ዓለም ውስጥ የይሖዋ ድርጅት ንጹህ ሆኖ ይቀጥላል።—ያዕቆብ 1:27
15. አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ቢፈጽም ምን ማድረግ ይኖርበታል?
15 ነገር ግን ራሳችን ከባድ ኃጢአት ብንሠራስ? ንጉሥ ዳዊት ይሖዋ ስለሚቀበላቸው ሰዎች በገለጸ ጊዜ እንዲህ ብሎአል፦ “ወደ [ይሖዋ (አዓት)] ተራራ ማን ይወጣል? በቅድስናውስ ስፍራ ማን ይቆማል? እጆቹ የነጹ፣ ልቡም ንጹህ የሆነ፣ ነፍሱን ለከንቱ ያላነሳ፣ ለባልንጀራውም በሽንገላ ያልማለ።” (መዝሙር 24:3, 4) በማንኛውም ምክንያት እጆቻችን ንጹህ ልባችንም የጠራ ሆነው ካልተገኙ እርምጃ መውሰድ አለብን። የዘላለም ሕይወታችን አደጋ ላይ ይወድቃል ማለት ነው።
16, 17. አንድ ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ሰው ችግሩን በራሱ ለመፍታት መሞከር የማይኖርበት ለምንድን ነው?
16 አንዳንዶች ከባድ ኃጢአቶችን ደብቀው ለመኖር ተፈትነዋል። ምናልባትም ለይሖዋ ተናዘናል፣ ንስሐ ገብተናል ለሽማግሌዎች መንገር ምን ያስፈልጋል? ብለው ለራሳቸው ምክንያት ያቀርቡ ይሆናል። ሽማግሌዎች በሚወስዱት እርምጃ ጥፋተኛው ሊያፍር ወይም ሊፈራ ይችላል። ይሁን እንጂ ምንም እንኳን ኃጢአታችንን ሊያነፃ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ቢሆንም ለጉባኤው ንጽህና በቅድሚያ ኃላፊነት የተሰጠው ለሽማግሌዎች መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። (መዝሙር 51:2) ሽማግሌዎች “ቅዱሳንን ለማስተካከል” የሚረዱ ፈውሶች ናቸው። (ኤፌሶን 4:12) መንፈሳዊ እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ወደ ሽማግሌዎች አለመሄድ ማለት በምንታመምበት ጊዜ ወደ ሐኪም ቤት አለመሄድ ማለት ነው።
17 አንዳንድ ኃጢአታቸውን ለራሳቸው ብቻ ደብቀው ለማስተካከል የሚሞክሩ ሰዎች ከወራት ወይም ከዓመታት በኋላም ኅሊናቸው በጣም እንደሚያሰቃያቸው ተገንዝበዋል። የከፋ የሚሆነው ደግሞ ከባድ ስህተት ሠርተው ሲደብቁ ለተደጋጋሚ ጊዜ ኃጢአት ውስጥ ይወድቃሉ። በመጨረሻም ነገሩ ወደ ሽማግሌዎች በሚደርስበት ጊዜ የተደጋጋመ ጥፋት ይሆናል። የያዕቆብን ምክር መከተል እንዴት የተሻለ ነው! እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በ[ይሖዋ (አዓት)] ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት።” (ያዕቆብ 5:14) ለመፈወስ የምትችሉበት ጊዜ ከማለፉ በፊት ወደ ሽማግሌዎች ሂዱ። ብዙ ከቆየን በኃጢአት መንገድ እንደነድናለን።—መክብብ 3:3፤ ኢሳይያስ 32:1, 2
የሰውነታችን ቁመናና መዝናኛዎች
18, 19. አንድ ቄስ ስለ ይሖዋ ምስክሮች ጥሩነት የተናገረው ለምን ነበር?
18 ከአምስት ዓመታት በፊት አንድ በኢጣሊያ አገር የሚኖሩ ቄስ በአንድ የሰበካ ጋዜጣ ላይ የይሖዋ ምሥክሮችን በማድነቅ ጽፈዋል።a “የይሖዋ ምስክሮችን እወዳቸዋለሁ። ይህን በግልጽ እናገራለሁ። . . . የማውቃቸው ሁሉ ጥሩ ጠባይ ያላቸው፣ በዝግታና በአሳማኝ ሁኔታ የሚናገሩ ናቸው። እውነት ተቀባይነት ባለው መንገድ መቅረብ እንደሚኖርበት፣ እውነቱን የሚያስታውቁ ሁሉ በግማሽ ልብ የሚሠሩ፣ መጥፎ ጠረን ያላቸው፣ ዝርክርኮችና የተንጨባረሩ መሆን እንደማይገባቸው የምንረዳው መቼ ነው?”
19 እኚህ ቄስ ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ በይሖዋ ምስክሮች አለባበስና አቀራረብ ልባቸው እንደተነካ ግልጽ ነው። ያገኙአቸው የይሖዋ ምስክሮች “ታማኝና ልባም ባሪያ” ባለፉት ዓመታት ስለዚህ ጉዳይ የሰጠውን ምክር የሰሙና የፈጸሙ እንደሆኑ ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 24:45) የሴቶች ልብስ ‘ልከኛና በሚገባ የተደራጀ’ መሆን እንደሚገባው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9) በዚህ ብልሹ ዘመን ውስጥ ይህ ምክር ለወንዶችም የሚያገለግል ነው። የአምላክ መንግሥት ወኪሎች ጥሩ ቁመና ኖሮአቸው ለውጭ ሰዎች መታየታቸው ተገቢ አይደለምን?
20. አንድ ክርስቲያን በማንኛውም ጊዜ ስለ አለባበሱ ጠንቃቃ መሆን የሚኖርበት ለምንድን ነው?
20 አንዳንዶች በስብሰባዎችና በመስክ አገልግሎት በጥሩ ሁኔታ ሁኔታ መልበስ አስፈላጊ እንደሆነ ይስማሙ ይሆናል። በሌሎች ጊዜያት ግን ስለ አለባበሳቸው ግድየለሽ ሊሆኑ የሚችሉ ሊመስላቸው ይችላል። ይሁን እንጂ የአምላክ መንግሥት ወኪሎች መሆናችንን የምናቆምበት ጊዜ ሊኖር ይችላልን? በፍጹም አይኖርም። እርግጥ ነው፣ አለባበሳችን ለወጥ እንዲል የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ሥራ ላይ በምንሆንበት ጊዜ የምንለብሰው ልብስ በዚያው አዳራሽ ውስጥ በስብሰባ ላይ በምንገኝበት ጊዜ ከምንለብሰው የተለየ ይሆናል። በምንዝናናበት ጊዜም የምንለብሰው ልብስ ዘና ያለና ቀለል ያለ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የውጭ ሰዎች በሚያዩን በማንኛውም ጊዜ ሁሉ አለባበሳችን ልከኛና በደንብ የተደራጀ መሆን ይኖርበታል።
21, 22. ጉዳት ከሚያስከትል መዝናኛ የተጠበቅነው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ የሚሰጡንን ምክሮች እንዴት መመልከት ይኖርብናል?
21 ባለፉት በርካታ ዓመታት ልዩ ትኩረት ከተሰጣቸው ነገሮች አንዱ መዝናኛ ነው። የሰው ልጆች በአጠቃላይ፣ በተለይም ወጣቶች መዝናናት ያስፈልጋቸዋል። ቤተሰብ ለሚዝናናበት ጊዜ ፕሮግራም ማውጣት ኃጢአት ወይም ጊዜ ማባከን አይደለም። ኢየሱስ እንኳን ደቀ መዛሙርቱን “ጥቂት እረፉ” ብሎአቸዋል። (ማርቆስ 6:31) ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች መዝናኛቸው ለመንፈሳዊ እድፈት በር የሚከፍት እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። የምንኖረው አብዛኛዎቹ መዝናኛዎች በጾታዊ ብልግና፣ በከባድ አመጽ፣ በጭካኔ ድርጊቶችና በመናፍስትነት ሥራ ላይ በተመሠረቱበት ዓለም ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:3፤ ራእይ 22:15) ታማኝና ልባም ባሪያ እነዚህ መዝናኛዎች ስለሚያስከትሉት ጉዳት ንቁ ስለሆነ ሳያሰልስ አስጠንቅቆናል። እንዲህ ዓይነቱ ማሳሰቢያ ነፃነታችሁን መጋፋት ማለት እንደሆነ ይሰማችኋልን? ወይም የይሖዋ ድርጅት ስለ እነዚህ አደገኛ ሁኔታዎች በማሳሰብ ስለ ዘላለማዊ ደህንነታችሁ የሚያስብ መሆኑን በማሳየቱ አመስጋኞች ናችሁ?—መዝሙር 19:7፤ 119:95
22 ነፃነታችን የመጣው ከይሖዋ አምላክ ቢሆንም በነፃነታችን ስለተጠቀምንበት ሁኔታ በኃላፊነት የምንጠየቅ መሆናችንን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። የሚሰጠንን ጥሩ ምክር ችላ ብለን የተሳሳተ ውሳኔ ብናደርግ በሌላ ሰው ላይ ልናማርር አንችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል፦ “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን።”—ሮሜ 14:12፤ ዕብራውያን 4:13
የአምላክ ልጆችን ነፃነት በጉጉት ተጠባበቁ
23. (ሀ) በነፃነት ረገድ በአሁኑ ጊዜ ምን ዓይነት በረከቶች አግኝተናል? (ለ) ወደ ፊትስ በጉጉት የምንጠብቃቸው ምን በረከቶች አሉ?
23 በእውነትም በጣም የተባረክን ሕዝቦች ነን። ከሐሰት ሃይማኖትና ከአጉል እምነት ነፃ አውጥቶናል። የኢየሱስ ቤዛዊ መስዋዕት ምስጋና ይግባውና ይሖዋን በንጹህ ሕሊና መቅረብ ችለናል። በመንፈሳዊ መንገድ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ወጥተናል። በቅርቡ ‘የእግዚአብሔር ልጆች ይገለጣሉ።’ የኢየሱስ ወንድሞች በሰማያዊ ክብራቸው የይሖዋ ጠላቶች አጥፊዎች ሆነው በአርማጌዶን ለሰዎች ይገለጣሉ። (ሮሜ 8:19፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6-8፤ ራእይ 2:26, 27) ከዚያም እነዚህ የአምላክ ልጆች ከአምላክ ዙፋን ወደ ሰው ልጆች ለሚፈሱት በረከቶች ማስተላለፊያ ሆነው ያገለግላሉ። (ራእይ 22:1-5) በመጨረሻም የእነዚህ የአምላክ ልጆች መገለጥ ታማኝ ለሆኑት የሰው ዘሮች ለአምላክ ልጆች የሚሆነውን ክብራማ ነፃነት የሚያስገኝላቸው በረከት ይሆንላቸዋል። ይህ የሚፈጸምበትን ጊዜ ትናፍቃላችሁን? እንግዲያው ክርስቲያናዊ ነፃነታችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት። አሁኑኑ የአምላክ ባሪያዎች ሆናችሁ ብታገለግሉት በዚህ እጅግ ግሩም በሆነ ነፃነት ለዘላለም ትደሰታላችሁ!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እኚህ ቄስ በኋላ ይህን ምስጋና እንዲያነሱ ስለተገደዱ አንስተዋል።
የክለሳ ሣጥን
◻ ቅቡአንና ሌሎች በጎች ይሖዋን ያከበሩት እንዴት ነው?
◻ ክርስቲያኖች ዓለማዊ ባለ ሥልጣኖችን ማክበር የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
◻ አንድ ክርስቲያን ከሽማግሌዎች ጋር መተባበር የሚችለው በምን መንገዶች ነው?
◻ የይሖዋ ምስክሮች በአለባበስ ረገድ በዓለም ውስጥ ካሉት ሰዎች የሚለዩት ለምንድን ነው?
◻ በመዝናኛዎችስ ረገድ ከምን ዓይነት መዝናኛዎች መራቅ ይኖርብናል?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሽማግሌዎች የተለየ ፍቅርና ትብብር ሊሰጣቸው ይገባል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአንድ ክርስቲያን ልብስ በሚገባ የተደራጀ፣ ልከኛና ከሁኔታው ጋር የሚስማማ መሆን ይገባዋል