የስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱስ ያደረገው የሕልውና ተጋድሎ
በ1559 በአንድ የጥቅምት ቀን 200,000 የሚሆኑ የስፓኝ ካቶሊኮች ሰሜናዊ ከተማ በሆነችው በቫላዶሊድ ተሰበሰቡ። የተሰበሰቡት “ሁለት ሰዎች በሕይወት እንዳሉ በእሳት ተቃጥለው፣ አስሩ ደግሞ ታንቀው” ሲሞቱ ለመመልከት ነበር። እነዚህ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ሰዎች “መናፍቃን” ነበሩ።
የቅጣቱን አፈጻጸም በበላይነት ይመራ የነበረው በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ሆኖ የነበረው ወጣቱ ንጉሥ ፊሊፕ ዳግማዊ ነበር። የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው መካከል አንዱ ምሕረት እንዲደረግለት በተማጸነ ጊዜ ንጉሡ በንዴት፦ “የራሴ ልጅ እንኳ እንደ አንተ ያለ ክፋት ቢፈጽም እኔ ራሴ የሚቃጠልበትን እንጨት ተሸክሜ አመጣ ነበር” በማለት መለሰለት። ይህ አሳዛኝ ሰው የፈጸመው ወንጀል ምን ነበር? ወንጀሉ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቡ ብቻ ነበር።
በዚሁ ጊዜ በሴቪል ክፍለ ሀገር በአንዳሉዥያ ከተማ ኢንኩዊዝሽን የተባለው የካቶሊክ መናፍቃን ምንጠራ ተጧጡፎ ነበር። በዚህ ከተማ በሳን ኢስድሮ ደል ካምፖ ገዳም ውስጥ የሚኖሩ መነኮሳት በዛ ያሉ የስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱሶችን በምስጢር አስመጥተው ነበር። ይህን ያወቁ ሰዎች አሳልፈው ይሰጡአቸው ይሆን? አንዳንዶቹ የሞት አደጋ እንደተደቀነባቸው ሲያውቁ ከአገር ሸሽተው አመለጡ። ሳይሸሹ የቀሩት 40 የሚያክሉ መነኮሳት ግን ከግንድ ጋር ታስረው በእሳት ተቃጠሉ። ከእነርሱ መካከል መጽሐፍ ቅዱሶቹን በድብቅ ወደ አገሪቱ ያስገባው ሰው ይገኛል። በ16ኛው መቶ ዘመን ስፓኝ መጽሐፍ ቅዱስ ለሚያነቡ ሰዎች በጣም አደገኛ አገር ሆና ነበር። ከኢንኩዊዝሽን ፍርድ ለማምለጥ የቻሉት ጥቂቶች ብቻ ነበሩ።
ካመለጡት ሰዎች አንዱ መነኩሴ የነበረው ካስዮዶሮ ደ ሬይና (1520-94) ነበር። እርሱም ወደ ለንደን ሸሽቶ ነበር። ሆኖም እንግሊዝ አገርም ቢሆን በሰላም ለመኖር አልቻለም። ኢንኩዊዝሽን ይህን ሰው ለሚያመጣለት ሰው ሽልማት እንደሚሰጥ ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር። በእንግሊዝ የሚገኘው የስፓኝ አምባሳደር በግድም ይሁን በውድ ወደ ስፓኝ እንዲመለስ የሚያደርገውን ደባ ማቀነባበር ጀመረ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ምንዝርና ግብረ ሰዶም እንደፈጸመ በቀረበበት የሐሰት ክስ ምክንያት እንግሊዝን ለቅቆ እንዲወጣ ተገደደ።
በቁጥር እየበዛ የሄደውን ቤተሰቡን ለማኖር የማይችል ጥቂት ቅርስ ብቻ ይዞ መጀመሪያ በፍራንክፈርት ጥገኝነት አገኘ። ከዚያም የሃይማኖት ጥገኝነት ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ ወደ ፈረንሳይ፣ ሆላንድ እና በመጨረሻም ወደ ስዊዘርላንድ እንዲሄድ አስገደደው። ይሁን እንጂ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ለአንድ አፍታ እንኳን ሥራ አልፈታም። ‘ካልታመምኩ ወይም በጉዞ ላይ ካልሆንኩ በስተቀር ብዕሬ ከእጄ አይለይም ነበር’ ብሎአል። መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ስፓኝ ቋንቋ በመተርጎም ብዙ ዓመት አሳልፎአል። በመጨረሻም የሬይና መጽሐፍ ቅዱስ በ1568 በስዊዘርላንድ አገር በ2,600 ቅጂዎች መታተም ጀምሮ በ1569 አለቀ። የሬይናን ትርጉም ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የአምላክን የተፀውኦ ስም የሚወክሉትን አራቱን የዕብራይስጥ ፊደላት ሲኞር (ጌታ) ብሎ ከመተርጎም ይልቅ ኢዮዋ (ይሖዋ) ማለቱ ነው።
የስፓኝ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አጀማመር
በዚህ ዘመን በአውሮፓ አገሮች የማተሚያ መሣሪያ በመፈልሰፉ ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስ ስርጭት እየተስፋፋ ቢሄድም በእስፓኝ አገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እየጠፋ መጥቶ ነበር። ከዚያ በፊት በነበሩት ዘመናት ግን ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነበር። ለብዙ መቶ ዓመናት በስፓኝ አገር መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት የተሰራጨ መጽሐፍ ነበር። በላቲንና፣ ለጥቂት መቶ ዓመታት ደግሞ በጐቲክ ቋንቋዎች የተጻፉ የእጅ ጽሑፍ መጻሕፍት እንደ ልብ ይገኙ ነበር። አንድ ታሪክ ጸሐፊ በመካከለኛው ዘመን “መጽሐፍ ቅዱስ በስፓኝ አገር የጥሩ ሐሳብ መቀስቀሻና የሥልጣን ምንጭ፣ የእምነትና የመልካም ምግባር መለኪያ በመሆን የሰጠው አገልግሎት ከጀርመንም ሆነ ከእንግሊዝ አገር የበለጠ ጎልቶ የሚታይ ነበር።” የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች፣ መዝሙሮች፣ ሥነ ምግባራዊ ታሪኮችና ተመሳሳይ ሥነ ጽሑፎች በዘመኑ ከፍተኛ ተወዳጅነት ነበራቸው።
የሰለጠኑ የእጅ ጸሐፊዎች በጣም በሚደነቅ ሁኔታ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን አዘጋጅተዋል። አንድ በእጅ የተጻፈ መጽሐፍ ገልብጦ ለመጨረስ 20 ጸሐፊዎችና የአንድ ዓመት ጊዜ ቢያስፈልግም በ15ኛው መቶ ዘመን በስፓኝ አገር የተሠራጩ ብዙ የላቲን መጽሐፍ ቅዱሶችና የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ መጻሕፍት ነበሩ።
ከዚህም በላይ የስፓንኛ ቋንቋ መስፋፋት ሲጀምር መጽሐፍ ቅዱስን በዚሁ ቋንቋ ለመተርጎም ፍላጎት መታየት ጀመረ። በ12ኛው መቶ ዘመን እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ተራው ሕዝብ ይናገርበት በነበረው ሮማንስ የተባለ ጥንታዊ ስፓንኛ ተተርጉሞ ነበር።
በአጭሩ የተቀጨ ንቃት
ይሁን እንጂ ይህ ንቃት ለብዙ ጊዜ አልቆየም። ዋልንደንሳውያን፣ ሎላርዳውያን እና ሁሳይቶች ቅዱሳን ጽሑፎችን እየጠቀሱ ስለ እምነታቸው መከራከር በጀመሩ ጊዜ ፈጣንና ኃይለኛ እርምጃ ተወሰደ። በዚህ ምክንያት የካቶሊክ ባለ ሥልጣኖች መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስን ብዙ ሕዝብ በሚነጋገርባቸው ቋንቋዎች የመተርጎሙ ሥራ ገና ከጅምሩ ተወገዘ።
በ1229 በቱሉስ (ፈረንሳይ) የተደረገው የካቶሊክ ጉባኤ የሚከተለውን ውሳኔ አወጣ፦ “ማንኛውም ተራ ሰው በተራ ቋንቋዎች የተተረጎመ የብሉይ ኪዳንም ሆነ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ይዞ እንዳይገኝ አዘናል። አንዳንድ ሃይማኖተኛ ሰዎች ከፈለጉ የመዝሙርና የጸሎት መጽሐፎችን ሊይዙ ይችላሉ። . . . ከላይ የተጠቀሱት ወደ ሮማንስ ቋንቋ የተተረጎሙ መጻሕፍት ግን በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ሊኖሩአቸው አይገባም።” ከአራት ዓመት በኋላም የአይቤሪያን ምድረ ሰላጤ አብዛኛውን ክፍል ይገዛ የነበረው የአራጎኑ ቀዳማዊ ጀምስ በተራው ሕዝብ ቋንቋ የተተረጎመ መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው በሙሉ በስምንት ቀናት ውስጥ በአካባቢያቸው ለሚገኘው ጳጳስ እንዲያስረክቡና እንዲቃጠል እንዲያደርጉ አዋጅ አወጣ። ይህን ሳያደርግ የቀረ ማንም ሰው፣ ካህንም ሆነ ተራ ሰው በመናፍቅነት ይጠረጠራል።
እነዚህን የመሰሉ እገዳዎች ቢኖሩም እገዳዎቹ ሁልጊዜ የሚከበሩ ስላልነበሩ እስከ መካከለኛው ዘመን የመጨረሻ ክፍል ድረስ በሮማንስ ቋንቋ የተተረጎመ የስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱስ የነበራቸው የስፓኝ ዜጎች ነበሩ። በ1478 የስፓኝ ኢንኩዊዝሽን በንግሥት ኢዛቤላና በንጉሥ ፈርዲናንድ ሲቋቋም ግን ይህ ሁኔታ አከተመ። በ1492 በሳለማንካ ከተማ ብቻ እጅግ ውድ የሆኑ በእጅ የተጻፉ 20 መጽሐፍ ቅዱሶች ተቃጠሉ። ሳይቃጠሉ የቀሩት በሮማንስ ቋንቋ የተጻፉ መጽሐፍ ቅዱሶች በንጉሡ ወይም በማይጠረጠሩ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ታላላቅ ሰዎች የግል ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ብቻ ነበሩ።
ከዚህ በኋላ በነበሩት ሁለት መቶ ዓመታት በስፓኝ አገር ከላቲን ቩልጌት መጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ በይፋ ይሠራጭ የነበረው ኮምፕሉቴንሲያን ፖሊግሎት የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ብቻ ነበር። ይህ በካርዲናል ሲስኔሮስ የበላይ ጠባቂነት የተዘጋጀው የመጀመሪያው በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንጂ ተራ ሰዎች ሊረዱ የሚችሉት ዓይነት አልነበረም። መጽሐፉ የተዘጋጀው በ600 ቅጂዎች ብቻ ሲሆን ጥቅሶቹ በስፓንኛ ቋንቋ ሳይሆን በዕብራይስጥ፣ በአረማይክ፣ በግሪክኛና በላቲን ቋንቋዎች የተጻፉ ስለነበሩ ብዙ ሰዎች ሊረዱ የሚችሉት አልነበረም። ከዚህም በላይ የመጽሐፉ ዋጋ በጣም ውድ ነበር። ሦስት የወርቅ ዱካት (ከአንድ ተራ የቀን ሠራተኛ የስድስት ወር ደሞዝ ጋር የሚመጣጠን ዋጋ ነው) ያወጣ ነበር።
የስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱስ በድብቅ ለመሰራጨት ተገደደ
በ16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ እንደ “ቲንዳል” ያለ ፍራንሲስኪ ዲ ኤንሲናስ የተባለው የስፓኝ ሰው ተነሳ። ይህ የአንድ የመሬት ከበርቴ ልጅ የነበረ ሰው ገና ተማሪ ሳለ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ስፓኝ ቋንቋ መተርጎም ጀመረ። በኋላም ትርጉሙ በኔዘርላንድስ እንዲታተም አደረገ። በ1544 ይህ ትርጉም በስፓኝ አገር እንዲሠራጭ ንጉሣዊ ፈቃድ ለማግኘት በቆራጥነት ተነሳ። በዚያን ጊዜ የስፓኝ ንጉሠ ነገሥት የነበረው ቻርልስ ቀዳማዊ ብራሰልስ ስለነበረ ኤንሲናስም ይህን ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ለዚህ እቅዱ ፈቃድ እንዲሰጠው ንጉሡን ጠየቀ።
በሁለቱ ሰዎች መካከል የተደረገው ውይይት የሚከተለው ነበር፦ “ምን ዓይነት መጽሐፍ ነው?” ሲል ንጉሡ ጠየቀ። ኤንሲናስም “አዲስ ኪዳን ተብሎ የሚጠራው የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ነው” ሲል መለሰለት። ንጉሡም “ደራሲው ማን ነው?” ሲል ደግሞ ጠየቀ። ኤንሲናስም “መንፈስ ቅዱስ ነው” ብሎ መለሰ።
ንጉሡ መጽሐፉ እንዲሰራጭ የሚፈቅደው አንድ ቅድመ ሁኔታ ከተሟላ በኋላ ብቻ እንደሆነ ነገረው። የንጉሡ ንስሐ አባት የሆነው የስፓኝ መነኩሴ ካልተስማማበት ሊፈቀድለት እንደማይችል ገለጸለት። ኤንሲናስ የመነኩሴውን ስምምነት ለማግኘት አልቻለም። እንዲያውም ብዙ ሳይቆይ በኢንኩዊዝሽን ሰዎች ተይዞ ታሠረ። ከሁለት ዓመት በኋላ ከእሥር ቤት ለማምለጥ ቻለ።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ የኤንስናስ ትርጉም ታርሞ በኢጣሊያ አገር በቬኒስ ከተማ ታተመ። ሁሊያን ኤርናንዴዝ ወደ ሴቪል፣ ስፔይን በድብቅ ለማስገባት የሞከረው ይህንን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች እትም ነበር። ይሁን እንጂ ለማስገባት ሲሞክር ስለተያዘ ከሁለት ዓመት ሥቃይና እሥራት በኋላ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር ተገደለ።a
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከ1545-63 በተደረገው የትራንት ጉባኤ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ በተራው ሕዝብ መነጋገሪያ ቋንቋ መተርጎሙን እንደሚያወግዝ በድጋሚ አረጋገጠ። ጉባኤው ከቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ውጭ የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ጨምሮ የተከለከሉ መጻሕፍትን ዝርዝር አውጥቶ ነበር። በስፓኝ ቋንቋ የተጻፉት መጽሐፍ ቅዱሶች በሙሉ ሕገ ወጥ መጻሕፍት ሆኑ ማለት ነው። መጽሐፎቹን ይዞ የተገኘ ሰው ሁሉ የሞት ቅጣት ይፈረድበት ነበር።
የሬይና ትርጉም ከታተመ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከኢንኩዊዝሽን ቅጣት ያመለጠ ሲፕሪያኖ ዲ ቫለሪ የተባለ የቀድሞ መነኩሴ ይህን ትርጉም በድጋሚ አሻሽሎ በ1602 እዘአ በአምስተርዳም እንዲታተም አደረገ። ጥቂት ቅጂዎችም ወደ ስፓኝ ገብተው ነበር። አሁንም ቢሆን የስፓንኛ ቋንቋ የሚናገሩ ፕሮቴስታንቶች በብዛት የሚጠቀሙት በዚህ የሬይና-ቫሌራ መጽሐፍ ቅዱስ የጥንት ወይም የተሻሻሉ እትሞች ነው።
ሰፊ በር ተከፈተ
በመጨረሻም፣ በ1782 የኢንኩዊዝሽን ሸንጎ መጽሐፍ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያንን የታሪክና የሕግ ቀኖናዎች የሚገልጽ ጽሑፍ አብሮ እስከወጣ ድረስ ሊታተም የሚችል መሆኑን የሚደነግግ ሕግ አወጣ። በ1790 የሴጎቪያ ካቶሊካዊ አቡን የነበሩት ፊሊፔ ሲዮ ዲ ሳን ሚጌል የላቲኑን ቩልጌት መሠረት በማድረግ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ስፓኝ ቋንቋ ተረጎሙ። የሚያሳዝነው ግን ዋጋው በጣም ውድ መሆኑ ነበር። በዚያ ጊዜ 1,300 ሪያል በጣም ከፍተኛ ዋጋ ነበር። አንድ የስፓኝ ታሪክ ጸሐፊ “በጣም ቅር የሚያሰኝ” ነው ብለዋል።
ጥቂት ዓመታት ቆይቶ የስፔይን ንጉሥ የነበሩት ፈርናንዶ 7ተኛ የአስቶርጋ አቡን የነበሩት ፌሊክስ ቶረስ ኤሜት የላቲኑን ቩልጌት መሠረት በማድረግ የተሻለ ትርጉም እንዲያዘጋጁ ትእዛዝ አስተላለፉ። ይህ ትርጉም በ1823 ታትሞ ወጣና ከሲዮ ትርጉም በበለጠ ሁኔታ በሰፊው ተሰራጨ። ይሁን እንጂ በመጀመሪያዎቹ የግሪክና የዕብራይስጥ ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ ትርጉም ስላልነበረ ይህም መጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ትርጉም የሆኑ መጽሐፍ ቅዱሶች በሙሉ ያላቸው ጉድለት ነበረው።
ይህ ሁሉ መሻሻል ቢደረግም ቤተ ክርስቲያኒቱና የአገሪቱ ገዥዎች ተራው ሕዝብ ቅዱሳን ጽሑፎችን ማንበብ ይኖርበታል ብለው ገና አላመኑም ነበር። በ1830ዎቹ ዓመታት የብሪታኒያና የውጭ አገሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ተወካይ የሆኑት ጆርጅ ቦሮው መጽሐፍ ቅዱስን በስፓኝ ቋንቋ ለማተም ፈቃድ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ፣ የመንግሥት ሚንስትር ከሆኑት ከመንደሴቤል የተሰጣቸው ምላሽ፦ “ውድ ጌታዬ፣ አሁን እኛ የምንፈልገው መጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን አመጸኞችን የምንደመስስበት ጠመንጃ እና ጥይት ነው። ከሁሉ በላይ የሚያስፈልገን ደግሞ ለወታደሮች የምንከፍለው ገንዘብ ነው” የሚል ነበር። ቦሮው የሉቃስ ወንጌልን ወደ ስፓኝ ጂፕሲዎች ቋንቋ መተርጎማቸውን ቀጥለው ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ጥረታቸው ምክንያት በ1837 ተይዘው ታሠሩ።
በመጨረሻም መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም የተነሳውን ግፊት መቋቋም የማይቻል ሆነ። በ1944 ማለትም የካሲዮ ዲ ሬይና ትርጉም ከተዘጋጀ ከ375 ዓመት በኋላ የስፓኝ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸውን የመጀመሪያ ቋንቋዎች መሠረት በማድረግ የተተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ አሳተመች። ይህ ትርጉም የተዘጋጀው የካቶሊክ ምሁራን በነበሩት በኔካር እና በኮሉንጋ ነበር። በ1947 ደግሞ ቦቨር እና ካንቴራ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አሳተሙ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በስፓኝ ቋንቋ የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መጉረፍ ጀመሩ።
ድሉ ተረጋገጠ
የስፓኝ መጽሐፍ ቅዱስ ሕልውናውን ላለማጣት ብዙ መቶ ዘመናት የቆየ ተጋድሎ ለማድረግ የተገደደ ቢሆንም በመጨረሻ ላይ ድል ለመቀዳጀት ችሎአል። እንደ ሬይና ያሉት ጀግና ተርጓሚዎች የከፈሉት መሥዋዕት ከንቱ ሆኖ አልቀረም። በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ከሚገዙት ሰዎች መካከል መጽሐፍ ቅዱስ መያዝ ክልክል ስለነበረበት ጊዜ ቆም ብለው የሚያስቡ ስንቶች ናቸው?
ዛሬ በስፔይን አገርም ሆነ የስፓኝ ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑ ሌሎች አገሮች ከማንኛውም መጽሐፍ ይበልጥ በብዛት የሚሸጠው መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በርካታ የሆኑ ጥሩ ትርጉሞችም ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል በሁሉም ቦታዎች የአምላክን ስም ሄኦቫ ብሎ የሚጠራው ቬርሲዮን ሞዴርና (ዘመናዊ ትርጉም 1893)፣ አምላክን በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያቬ ብሎ የሚጠራው የፓውሊን የመጽሐፍ ቅዱስ እትም (1964)፣ አምላክን ሄኦቫ ወይም ያቬ ብሎ የማይጠራው ኑዌቫ ቢብልዮ ኤስፓኞላ (አዲሱ የስፓንኛ መጽሐፍ ቅዱስ፣ 1975) እና ጀሆቫ በሚለው ስም የሚጠቀመውና በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የታተመው ትራዱክስዮን ዴል ኑዌቫ ሙንዶ (አዲሲቱ ዓለም ትርጉም፣ 1967) ይገኙበታል።
የይሖዋ ምሥክሮች የስፓኝ ቋንቋ ተናጋሪ ወደ ሆኑ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት እየሄዱ መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት መሥዋዕት ሊከፈልለት የሚገባ የሕይወት መመሪያ ሊሆን የሚገባ መጽሐፍ መሆኑን እንዲገነዘቡ ይረዳሉ። የስፓኝ መጽሐፍ ቅዱስ ከሕልውና ውጭ እንዳይሆን ያደረገው ተጋድሎ ‘የአምላክ ቃል ለዘላለም ጸንቶ የሚኖር መሆኑን የሚያረጋግጥ’ አንድ ማስረጃ ነው።—ኢሳይያስ 40:8
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚያ ዘመን ልዩ ፈቃድ ካልተሰጠ በቀር ምንም ዓይነት መጽሐፍ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አይፈቀድም ነበር። በተጨማሪም ማንኛውም የቤተ መጻሕፍት ሠራተኛ የቅዱስ ቢሮውን (ኢንኩዊዝሽን) ባለ ሥልጣን ፈቃድ ሳያገኝ ማንኛውንም ዓይነት የመጽሐፍ ጭነት ለመፍታት አይችልም ነበር።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኮምፕሉቴንሲያን ፖሊግሎት ታትሞ የወጣ ስለሆነ መመርመር ይቻላል (ገጽ 8ን ተመልከት)
[ምንጭ]
በቢብልዮቲካ ናሲዮናል፣ ማድሪድ፣ ስፔይን ፈቃድ ታትሞ የወጣ