ካስዮዶሮ ዴ ሬይና ለስፓኒሽ መጽሐፍ ቅዱስ ያደረገው ተጋድሎ
በአሥራ ስድስተኛው መቶ ዘመን ስፔይን ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አደገኛ ነበር። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የማትቀበላቸውን እምነቶች ለማጥፋት ኢንኩዊዝሽን እንዲካሄድ አዝዛ ነበር። ሆኖም በደቡባዊ የስፔይን ግዛት ውስጥ የሚገኝ አንድ ወጣት ቅዱሳን ጽሑፎችን ከማንበቡም በተጨማሪ እያንዳንዱ ስፔይናዊ ሊያነባቸው እንዲችል ወደ አገሩ ቋንቋ ለመተርጎም ቁርጥ ውሳኔ አደረገ። ይህ ወጣት ካስዮዶሮ ዴ ሬይና ይባላል።
ሬይና ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍላጎት ያደረበት በስፔይን ከሲቬሌ ወጣ ብሎ በሚገኝ ሳን ኢሲድሮ ዴል ካምፖ በሚባል ገዳም ባሳለፈባቸው ዓመታት ውስጥ ነው። በ1550ዎቹ በዚህ ለየት ያለ ገዳም የሚኖሩ አብዛኞቹ መነኮሳት በገዳሙ ውስጥ የተሰጣቸውን ተግባር ከመፈጸም ይልቅ ቅዱሳን ጽሑፎችን በማንበብ ብዙ ሰዓታት ያሳልፉ ነበር። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አስተሳሰባቸውን ለውጦት ነበር። ስለ ምስሎችና ስለ መንጽሔ የሚናገረውን የካቶሊክ መሠረተ ትምህርት አይቀበሉም ነበር። አመለካከታቸው በአካባቢው መታወቁ ስለማይቀር የስፓኒሽ ኢንኩዊዝሽን እንዳይዛቸው ፈርተው ከአገር ለመኮብለል ወሰኑ። ሬይና ወደ ጄኔቭ ስዊዘርላንድ ሸሽተው ካመለጡት 12 መነኮሳት አንዱ ነበር።
ሬይና ለጥቂት ካመለጠ በኋላ አሳዳጆቹ እንዳያገኙት ሲል ከአንድ የአውሮፓ ከተማ ወደ ሌላ የአውሮፓ ከተማ ይጓዝ ነበር። በ1562 እጅግ የተበሳጩት የኢንኩዊዝሽን አራማጆች የእርሱን ምስል ሠርተው በሲቬሌ ውስጥ ቢያቃጥሉም ይህ ጭካኔ የተሞላበት የማስፈራራት እርምጃ ሬይና ቅዱሳን ጽሑፎችን ከመተርጎም ወደ ኋላ እንዲል አላደረገውም። ምንም እንኳ አሳዳጆቹ እርሱን ይዞ ለሚያመጣ ሰው ሽልማት እንደሚሰጡ በመናገራቸው ምክንያት እያዝ ይሆን የሚል ስጋት ቢያድርበትም ወደ ስፓኒሽ ቋንቋ የመተርጎም ሥራውን አላቋረጠም። “ካልታመምኩ ወይም በጉዞ ላይ ካልሆንኩ በስተቀር . . . ብዕሬ ከእጄ አይለይም” ሲል ተናግሯል።
ሬይና ሥራውን ለማጠናቀቅ አሥር ዓመት ፈጅቶበታል። ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ ያቀፈው ትርጉሙ በ1569 በባዜል ስዊዘርላንድ ታተመ። ይህ ትልቅ የሥራ ውጤት በኩረ ጽሑፉ ከተጻፈባቸው ቋንቋዎች በቀጥታ የተተረጎመ የመጀመሪያው የተሟላ የስፓኒሽ ቋንቋ ትርጉም ነበር። ለብዙ መቶ ዘመናት የላቲን መጽሐፍ ቅዱሶች የነበሩ ቢሆንም ላቲን የታላላቅ ሰዎች ቋንቋ ነበር። ሬይና ማንኛውም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ እንደሚያስፈልገው ያምን ስለ ነበር ይህን ዓላማ ለማሳካት ሲል ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሏል።
በትርጉም ሥራው መግቢያ ላይ የተረጎመበትን ምክንያት ገልጿል። “ቅዱሳን ጽሑፎች በተራው ሕዝብ ቋንቋ እንዳይተረጎሙ መከልከል አምላክን ክፉኛ የሚያሰድብ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሰዎች ደኅንነት አይበጅም። ይህ የሰይጣንና እርሱ የሚቆጣጠራቸው ሰዎች ሥራ እንደሆነ ግልጽ ነው። . . . አምላክ ቃሉን ለሰው ልጆች የሰጠው ሁሉም ሰዎች እንዲረዱትና በዕለታዊ ሕይወታቸው በሥራ ላይ እንዲያውሉት ስለሆነ በየትኛውም ቋንቋ ቢሆን እንዳይተረጎም የሚከለክል ማንኛውም ሰው ጥሩ ዝንባሌ አለው ለማለት አይቻልም።”
ይህ ቃል የስፓኒሽ ኢንኩዊዝሽን መጽሐፍ ቅዱስ “በካስትል ሮማንስ [በስፓኒሽ] ወይም በማንኛውም ተራ ቋንቋ” እንዳይታተም ካገደ ከ18 ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የታተመ ስለሆነ ድፍረት የተሞላበት ቃል ነበር። ሬይና የሰው ፍራቻ ለእውነት የነበረውን ፍቅር እንዲገታበት እንዳልፈቀደ ግልጽ ነው።
ሬይና ሁሉም የስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን በቀላሉ እንዲያገኙ ከፍተኛ ፍላጎት የነበረው ከመሆኑም በተጨማሪ በተቻለ መጠን ከሁሉ የተሻለ ትርጉም ለማዘጋጀት ፈልጎ ነበር። በትርጉሙ መግቢያ ላይ በኩረ ጽሑፉ ከተጻፈባቸው ቋንቋዎች በቀጥታ መተርጎም የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች አብራርቷል። ሬይና በላቲኑ ቩልጌት ጽሑፍ ላይ አንዳንድ ስሕተቶች ገብተውበታል በማለት ገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው የመለኮታዊው ስም መጥፋት ነው።
መለኮታዊው ስም በስፓኒሽ ቋንቋ ትርጉሞች ውስጥ
ሬይና ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በበኩረ ጽሑፉ ላይ እንደሚገኝ ሁሉ በማንኛውም ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ መገኘት እንደሚኖርበት ተገንዝቧል። መለኮታዊውን ስም “አምላክ” ወይም “ጌታ” በሚሉት ማዕረጎች የመተካት ልማድን አልተቀበለም። በትርጉሙ መግቢያ ላይ ይህን ያደረገበትን ምክንያት በግልጽ አብራርቷል።
“(አይሆቫ) የሚለውን ስም ጠብቀን ያቆየነው ያለ በቂ ምክንያቶች አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ የአምላክ ስም በትርጉማችን ውስጥ በሚገኝበት ስፍራ ሁሉ በዕብራይስጡ ጽሑፍ የሚገኝ ሲሆን ይህን ስም ከተውነው ወይም ከለወጥነው ታማኝ ካለመሆናችንም በተጨማሪ አንዳች አታጉድል ወይም አትጨምር የሚለውን የአምላክ ሕግ እንደናቅን እናሳያለን። . . . ይህ [ስሙን የመሰረዝ] ልማድ ዲያብሎስ የጠነሰሰውና የአምላክን ስም እናከብራለን ቢሉም እንኳ ከሌሎች . . . አማልክት ራሱን ለይቶ ለማሳወቅ የሚፈልግበትን ስሙን የአምላክ ሕዝቦች እንዲረሱ በማድረግ ቅዱስ ስሙን ከሸሸጉት ዘመናዊ ረቢዎች የመነጨ አጉል ልማድ ነው።”
ሬይና የአምላክን ስም ከፍ ከፍ ለማድረግ የነበረው የሚያስመሰግን ምኞት ከፍተኛ ጥቅሞችን አስገኝቷል። እስከ ዛሬ ድረስ አብዛኞቹ የካቶሊክም ሆኑ የፕሮቴስታንት የስፓኒሽ ትርጉሞች ስሙን ከዳር እስከ ዳር በመጠቀም ይህን ምሳሌ ተከትለዋል። በተለይ ሬይና ምስጋና ይግባውና ማንኛውም የስፓኒሽ ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አንባብያን አምላክ ከሌሎች አማልክት ራሱን የሚለይበት የግል ስም እንዳለው በቀላሉ ሊያስተውሉ ይችላሉ ማለት ይቻላል።
ሬይና በተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ የአርዕስት ማውጫው ገጽ ላይ የይሖዋ ስም በዕብራይስጥ ተጽፎ የሚገኝ መሆኑ ሊስተዋል ይገባል። ሬይና የአምላክ ቃል ተጠብቆ እንዲቆይና ብዙ ሰዎች ሊያነቡት በሚችሉት ቋንቋ እንዲተረጎም በማድረግ ሕይወቱን ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ተጠቅሞበታል።