ሕይወት—የአምላክ ስጦታ ነው
ልባችን በቀን ሃያ አራት ሰዓት ውድ የሆነውን ደም በሰውነታችን ውስጥ ይረጫል። ተኝተን እያለ ሳንባችን አየር ማስወጣቱንና ማስገባቱን አያቋርጥም። ምግብ ከተመገብን በኋላ ምግቡ በፍጥነት ይፈጫል። ይህ ሁሉ በሰውነታችን ውስጥ የሚካሄደው እኛ በሥራው ጥቂት ወይም ምንም ዓይነት ጥረት ሳናደርግ ነው። እነዚህ በጣም ቀላል አድርገን የምንመለከታቸው ምስጢራዊና በጣም አስደናቂ የሆኑት ሒደቶች ሕይወት ብለን የምንጠራው ስጦታ ክፍል ናቸው። በሌላ በኩልም ሕይወት ተአምር ተብሎ ሊጠራ የሚችል ስጦታ ነው።
የሰውን ልጅ የመፀነስና የመወለድ ሂደት እንመልከት። በመሠረቱ የሰውነት አካል ባእድ ነገሮችን የማይቀበልና የሚያስወግድ ቢሆንም ማሕፀን ግን ይህንን ደንብ ሳይከተል የዳበረውን እንቁላል ይቀበላል። በማደግ ላይ ያለውን ፅንስ እንደ ባእድ አካል አድርጎ ከማስወገድ ይልቅ ሕፃን ሆኖ ለመወለድ ዝግጁ እስኪሆን ድረስ ይመግበዋል፣ ከጉዳትም ይጠብቀዋል። ማህፀን ባእድ አካልን የማስወገድ ባሕርይን በዚህ ጊዜ ባይተው ኖሮ የሰው ልጅ ሊወለድ አይችልም ነበር።
ከዚህም በላይ ሽሉ የአራት ወር እድሜ ብቻ በሆነው ጊዜ አንድ አይነት እድገት በማህፀን ውስጥ ባይከናወን ኖሮ አዲስ የሚወለደው ህፃን ሕይወት አጭር ይሆን ነበር። በዚህ ጊዜ ሽሉ አውራ ጣቱን መጥባትና ከተወለደ በኋላ ከእናቱ ጡቶች ለመመገብ እንዲያስችለው ጡንቻዎቹ እንዲጠነክሩ ማለማመድ ይጀምራል። ይህ አንድ ህፃን ከመወለዱ ከረዥም ጊዜ በፊት ሊከናወን የሚገባው የሕይወትና የሞት ጉዳይ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ ነው።
አንድ ሽል በማህፀን ውስጥ እንዳለ በልቡ ግድግዳ ውስጥ አንድ ቀዳዳ አለው። ይህ ቀዳዳ ልጁ በሚወለድበት ጊዜ ከመቅጽበት ይዘጋል። በተጨማሪም ሽሉ በማህፀን ውስጥ እያለ በሳንባዎቹ ጎን ያልፍ የነበረው ትልቅ የደም ሥር ህፃኑ በሚወለድበት ጊዜ ወዲያውኑ ይሸመቀቃል። ቀጥሎም ደም ከአየር ጋር ሊዋሃድ ወደሚችልበትና ሕፃኑ የመጀመሪያውን አየር ወደሚያስገባበት ወደ ሳንባዎቹ መፍሰስ ይጀምራል።
ይህ ሁሉ የመጀመሪያ ክንውን ብቻ ነው። በሕይወት ዘመን ሁሉ ሕይወትን ጠብቆ ለማቆየት ሲባል እንደነዚህ ያሉ በአስደናቂ ሁኔታ የተቀናበሩ ሥርዓቶች (እንደ የአተነፋፈስ ሥርዓት፣ የደም ዝውውር ሥርዓት፣ የነርቭ አሠራር ሥርዓት እና በሰውነት ውስጥ የሚመነጩ ኬሚካሎች ሥርዓት) በቅልጥፍናና በህብረት ሥራቸውን ያከናውናሉ። በጥንት ዘመን ይኖር የነበረ አንድ ጸሐፊ ስለ አምላክ እንዲህ ብሎ መናገሩ አያስደንቅም፦ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬያለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፣ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።”—መዝሙር 139:14
የእነዚህ ውብ ቃላት ጸሐፊ ሕይወት በቀላሉ ጭፍን በሆነ የዝግመተ ለውጥ እድል ወይም በአጋጣሚ የተገኘ ውጤት ነው ብሎ እንደማያምን ግልጽ ነው። በአጋጣሚ የተገኘን ብንሆን ኖሮ ሕይወታችንን ስለምንጠቀምበት መንገድ ተገቢ የሆነ ግዴታ ወይም ሐላፊነት አይኖርብንም ነበር። ይሁን እንጂ የሕይወታችን አሠራር ራሱ ሕይወት በዓላማና በእቅድ የተዘጋጀ መሆኑን ያሳያል። ዓላማና እቅድ ከኖረ ደግሞ ያንን ዓላማና እቅድ ያወጣ አንድ አካል መኖር ያስፈልገዋል። ንድፍ እንዳለው በግልፅ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሥርዓት እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአልና፣ ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው። ” (ዕብራውያን 3:4) ስለዚህ “እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] እርሱ አምላክ እንደሆነ እወቁ እርሱ ሠራን እኛም አይደለንም” የሚለውን መገንዘባችን እጅግ አስፈላጊ ነው። (መዝሙር 100:3) አዎ፣ ሕይወት በድንገተኛ አጋጣሚ የመጣ ሳይሆን ከአምላክ ከራሱ የተገኘ ስጦታ ነው። —መዝሙር 36:9
ታዲያ ሕይወታችን ከአምላክ የተገኘ ስጦታ ከሆነ ሕይወት ሰጪ በሆነው አምላክ ፊት ምን ግዴታ አለብን? በሕይወታችንስ እንዴት እንድንጠቀምበት ይጠብቅብናል? እነዚህንና ከእነዚህ ጋር የሚዛመዱ ሌሎች ጥያቄዎችን በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታቸዋለን።