‘ዕድገታችሁ በግልጽ ይታይ’
“ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ።”—1 ቆሮንቶስ 13:11
1. ዕድገት አስደናቂ ለሆነው ተፈጥሮ ምስክር የሆነው እንዴት ነው?
ዓሣ ነባሪ በአጉሊ መነፅር ብቻ ሊታይ ከሚችል በጣም ረቂቅ የሆነ እንቁላል ተነስቶ ከመቶ ጫማ (30 ሜትር) በላይ ርዝመትና ከ800 ኩንታል በላይ ክብደት ያለው ፍጡር ወደመሆን ሊያድግ ይችላል። በተመሳሳይም በጣም ጥቃቅን ከሆኑት ዘሮች መካከል ከአንዷ በመነሳት ግዙፉ የሴኮያ ዛፍ ከ300 ጫማ ወይም 90 ሜትር በላይ ርዝመት እስኪኖረው ድረስ ሊያድግ ይችላል። እውነትም ዕድገት ከሕይወት አስደናቂ ነገሮች አንዱ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው እኛ ልንተክልና ልናጠጣ ብንችልም “የሚያሳድገው ግን እግዚአብሔር ነው።”—1 ቆሮንቶስ 3:7
2. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትንቢት የተነገረው ምን ዓይነት ዕድገት ነበር?
2 ይሁን እንጂ ይህንኑ ያህል አስገራሚ የሆነ ሌላ ዓይነት ዕድገትም አለ። እርሱም በነቢዩ ኢሳይያስ “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሽ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ” በማለት በትንቢት የተናገረለት ዕድገት ነው። (ኢሳይያስ 60:22) ይህ ትንቢት የአምላክን ሕዝቦች ዕድገት የሚያመለክት ሲሆን እርሱም በዘመናችን በታላቅ ሁኔታ ፍጻሜውን በመፈጸም ላይ ነው።
3. ይሖዋ የሕዝቡን ሥራ እያፋጠነው እንዳለ የ1991 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት የሚያሳየው እንዴት ነው?
3 የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ የሚገልጸው የ1991 የአገልግሎት ዓመት ሪፖርት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር 4,278,820 ወደሆነ አዲስ ከፍተኛ ቁጥር እንደደረሰና በዓመቱ ውስጥ በጠቅላላው 300,945 ሰዎች እንደተጠመቁ ይገልጻል። ብዙ አዳዲስ ሰዎች ስለመጡ 3,191 አዳዲስ ጉባኤዎችና ብዛት ያላቸው አዳዲስ ክልሎችና ወረዳዎች ተመሥርተዋል። በየቀኑ ከ8 በላይ ጉባኤዎችና በየሁለት ቀኑ አንድ አዲስ ክልል ይመሠረት ነበር ማለት ነው። ምንኛ አስደናቂ እድገት ነው! በግልጽ እንደሚታየው ይሖዋ ነገሮችን እያፋጠናቸውና የሕዝቡንም ጥረት እየባረከ ነው።—መዝሙር 127:1
ራስን መመርመር አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ
4. የወደፊቱን ጊዜ ስንመለከት ምን ጥያቄዎች ሊታሰብባቸው ይገባል?
4 ይህን በረከት ማሰብ ልብን በደስታ የሚያሞቅ ቢሆንም አንዳንድ ኃላፊነቶችንም አስከትሎአል። የእነዚህን ሁሉ አዳዲስ ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎቶች የሚንከባከቡ በቂ ቁጥር ያላቸው የጎለመሱና ፈቃደኛ የሆኑ ግለሰቦች ይኖሩ ይሆን? መጪውን ጊዜ ስንመለከት ዕድገቱና መስፋፋቱ የሚጠይቃቸውን አቅኚዎች፣ ዲያቆናት፣ ሽማግሌዎችና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እንዲሁም ይህን ሥራ ለመደገፍ በዓለም ዙሪያ በቅርንጫፍ ቢሮዎችና በቤቴል ቤቶች የሚያስፈልጉትን የፈቃደኛ ሠራተኞች ቁጥር ስናስብ በጣም ከፍተኛ ነው። ይህን ያህል ታላቅ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከየት ይመጡ ይሆን? መከሩ ታላቅ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ታዲያ ባሁኑ ጊዜ ይህን መከር ለማጨድ ለሚያስፈልጉት ሠራተኞች ሁሉ ክብካቤ ለማድረግ በሚያስችላቸው አቋምና ሁኔታ ላይ ያሉት እነማን ናቸው?—ማቴዎስ 9:37, 38
5. በአንዳንድ አካባቢዎች ፈጣን ዕድገት በመኖሩ ምክንያት ምን ሁኔታዎች ተፈጥረዋል?
5 ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች በአንድ ወይም በሁለት ዲያቆናት በሚታገዝ አንድ ሽማግሌ ብቻ የሚገለገሉ እስከ መቶ የሚደርሱ የመንግሥት አስፋፊዎች ያሏቸው ጉባኤዎች እንዳሉ ሪፖርት ተደርጓል። አንዳንድ ጊዜም አንድ ሽማግሌ በሁለት ጉባኤዎች ውስጥ ያገለግላል። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ብቃት ያላቸው ክርስቲያን አገልጋዮች በጣም ከማነሳቸው የተነሳ ማጥናት የሚፈልጉ አዳዲስ ሰዎች በማቆያ መዝገቦች ላይ እንዲመዘገቡ ግድ ሆኖአል። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ አዳዲስ ጉባኤዎች በከፍተኛ ፍጥነት ስለሚመሠረቱ ሦስት፣ አራት ወይም አምስት ጉባኤዎች በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ለመገልገል ተገደዋል። ምናልባትም እናንተ በአካባቢያችሁ እንዲህ ዓይነት ዕድገት ተመልክታችሁ ይሆናል።
6. ራሳችንን መመርመር ወቅታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
6 ከዚህ በላይ የተዘረዘረው ሁሉ ምን ይነግረናል? ከጊዜው አንፃር ሁላችንም ላለው ሥራ ምላሽ መስጠት እንችል ዘንድ ጊዜያችንንና ንብረታችንን ከሁሉ በተሻለ መንገድ እየተጠቀምንበት መሆንና አለመሆኑን ለማየት ሁኔታዎቻችንን መመርመር እንደሚያስፈልገን ይጠቁመናል። (ኤፌሶን 5:15-17) ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች “ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም” በማለት ጽፎላቸዋል። (ዕብራውያን 5:12) እነዚህ ቃላት እንደሚያመለክቱት ግለሰብ ክርስቲያኖችም ማደግ ያስፈልጋቸዋል። አንድ ሰው ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ከማደግ ይልቅ በመንፈሳዊ ሕፃንነት ላይ የመቆየት አስጊ አደጋም ሊያጋጥመው ይችላል። ከዚህም ጋር በመስማማት ጳውሎስ “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ” በማለት አጥብቆ መክሮናል። (2 ቆሮንቶስ 13:5) ከተጠመቃችሁበት ጊዜ ጀምሮ በመንፈሳዊ እያደጋችሁ መሆን አለመሆኑን ለማየት ራሳችሁን መርምራችኋልን? ወይስ በነበራችሁበት ቆማችኋል? ታዲያ አንድ ሰው ይህ እንዴት ሊታወቀው ይችላል?
“የሕፃን ጠባይ”
7. መንፈሳዊ ዕድገታችን በግልጥ እንዲታይ ምን ማድረግ አለብን?
7 ሐዋርያው ጳውሎስ “ሕፃን በነበርሁ ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር ነበር፣ እንደ ሕፃን አስብ ነበር፣ እንደ ሕፃን እመራመር ነበር፤ ሙሉ ሰው በሆንሁ ጊዜ ግን የሕፃንነቴን ጠባይ ተውሁ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:11 የ1980 ትርጉም) በመንፈሳዊ ዕድገት ረገድ ሁላችንም በአንድ ወቅት በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን እንደ ሕፃናት ነበርን። ይሁን እንጂ ዕድገታችን በግልጽ እንዲታይ ጳውሎስ እንዳለው “የሕፃንነትን ጠባይ” ማስወገድ አለብን። ከእነዚህ የሕፃንነት ጠባዮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
8. በዕብራውያን 5:13, 14 ላይ ባሉት የጳውሎስ ቃላት መሠረት የመንፈሳዊ ሕፃን አንዱ ጠባይ ምንድን ነው?
8 በመጀመሪያ በዕብራውያን 5:13, 14 ላይ የሚገኙትን የጳውሎስን ቃላት አስተውሉ፦ “ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን [ለጎለመሱ አዓት] ሰዎች ነው።” ‘ከጽድቅ ቃሎች ጋር ተዋውቃችኋልን?’ “መልካሙንና ክፉውን ለመለየት” ልትጠቀሙበት እንድትችሉ የአምላክን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን ጥሩ አድርጋችሁ ታውቁታላችሁን? ጳውሎስ የጎለመሱ ሰዎች አዘውትረው “ጠንካራ ምግብ” ስለሚመገቡ መልካሙንና ክፉውን መለየት እንደሚችሉ ተናግሯል። በመሆኑም አንድ ሰው ለጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ ያለው ስሜት ወይም ፍላጎት በመንፈሳዊ ማደጉን ወይም በመንፈሳዊ ሕፃን እንደሆነ መቅረቱን የሚያሳይ ጥሩ ምልክት ነው።
9. የአንድ ሰው የመንፈሳዊ ምግብ ፍላጎት መንፈሳዊ ዕድገቱን የሚገልጽ ምልክት የሆነው እንዴት ነው?
9 እናንተስ መንፈሳዊ የምግብ ፍላጎታችሁ እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና በታላላቅ ስብሰባዎች አማካኝነት ይሖዋ ዘወትር እያቀረበ ያለውን የተትረፈረፈ የመንፈሳዊ ምግብ አቅርቦት የምትመለከቱት እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 65:13) በዓመታዊ የወረዳ ስብሰባዎች ላይ አዳዲስ ጽሑፎች ሲወጡ በጣም እንደምትደሰቱ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ እቤታችሁ ከወሰዳችኋቸው በኋላ ምን ታደርጋላችሁ? የመጠበቂያ ግንብ ወይም የንቁ! መጽሔት አዳዲስ እትሞች ሲደርሷችሁ ምን ታደርጋላችሁ? እነዚህን ጽሑፎች ለማንበብ ጊዜ ትመድባላችሁን ወይስ ዋና ዋና ርዕሶችን ለማየት ያህል ገልበጥ ገልበጥ አድርጋችሁ ካያችኋቸው በኋላ በመጻሕፍት መደርደሪያችሁ ላይ ከሌሎቹ ጋር ትደረድሯቸዋላችሁ? ስለ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ሊቀርቡ ይችላሉ። በሁሉም ስብሰባዎች ላይ አዘውትራችሁ ትገኛላችሁን? ለስብሰባዎቹ ተዘጋጅታችሁ በመሄድ ትሳተፋላችሁን? በግልጽ እንደሚታየው አንዳንዶች ሲዘጋጁ እየሮጡ የመብላት ያህል ገረፍ ገረፍ እያደረጉ የሚያነቡ በመሆናቸው መጥፎ ወደሆነ የመንፈሳዊ ምግብ አመጋገብ ልማድ ላይ ወድቀዋል። ይህ ደግሞ “አቤቱ፣ ሕግህን እንደምን ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው” በማለት ከተናገረው መዝሙራዊ እንዴት የተለየ ነው! በተጨማሪም ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ፣ በታላቁ ጉባኤ ውስጥ እገዛልሃለሁ፣ [አመሰግንሃለሁ አዓት]፣ በብዙ ሕዝብ መካከልም አመሰግንሃለሁ” ብሎአል። (መዝሙር 35:18፤ 119:97) ለመንፈሳዊ ዝግጅቶች ያለን የአድናቆት መጠን የመንፈሳዊ ዕድገታችንን መጠን የሚገልጽ ምልክት መሆኑ ግልጽ ነው።
10. በኤፌሶን 4:14 ላይ ምን የመንፈሳዊ ሕፃን ጠባይ ተገልጿል?
10 ጳውሎስ “እንደ ስህተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም” በማለት ባስጠነቀቀ ጊዜ የመንፈሳዊ ሕፃንን ሌላ ባሕርይ አመልክቷል። (ኤፌሶን 4:14) ልጆች ማንኛውንም ነገር ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት እንዳላቸው ወላጆች በሚገባ ያውቃሉ። በአንድ በኩል ይህ ጠባይ እንዲመራመሩና እንዲማሩ ቀስ በቀስም የጎለመሱ ሰዎች ወደ መሆን እንዲያድጉ ስለሚያስችላቸው ገንቢ ጠባይ ነው። ይሁን እንጂ ትኩረታቸው በመጣው ነገር ሁሉ በቀላሉ ከተወሰደ ይህ ጠባይ አደጋ አለው። ከዚህ የሚከፋው ደግሞ ተሞክሮ ስለሚያንሳቸው ይህ ነገሮችን ሁሉ ለማወቅ የመጓጓት ጠባይ ብዙውን ጊዜ ወደ ከፍተኛ ችግር ይመራቸውና ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ። በመንፈሳዊ ሕፃናት ላይም የሚደርሰው ይኸው ነው።
11. (ሀ) ጳውሎስ “በትምህርት ነፋስ ሁሉ” የሚለውን አባባል ሲጠቀም በአእምሮው የያዘው ምንን ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ ምን ዓይነት ‘ነፋሶች’ ያጋጥሙናል?
11 ይሁንና ጳውሎስ መንፈሳዊ ሕፃናት “በትምህርት ነፋስ ሁሉ” ይፍገመገማሉ ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? እዚህ ላይ “ነፋስ” የሚለው ቃል የተተረጎመው አኔሞስ ከሚለው የግሪክኛ ቃል ሲሆን ይህንንም በሚመለከት የኢንተርናሽናል ክሪቲካል ኮሜንታሪ የተሰኘ መጽሐፍ “ተለዋዋጭነትን ለመግለጽ ተስማሚ ቃል በመሆኑ እንደተመረጠ” ይናገራል። ይህም ቀደም ብለው በተጠቀሱት “በሰዎችም ማታለል” በሚሉት የጳውሎስ ቃላት ተገልጿል። በበኩረ ጽሑፉ ቋንቋ “ማታለል” የሚለው ቃል ለዕጣ ማውጫ የሚያገለግልን መጫወቻ። ያም ማለት በየጊዜው ምንም ጉዳት የሌላቸው የሚመስሉ፣ የሚያስጎመጁ፣ እንዲያውም ጠቃሚ የሚመስሉ አዳዲስ ሐሳቦችና ግቦች ያጋጥሙናል ማለት ነው። የጳውሎስ ቃላት በመጀመሪያ ደረጃ በሥራ ላይ የሚውሉት ከእምነታችን ጋር ለሚዛመዱ ነገሮች፣ ይኸውም ለሃይማኖታዊ አንድነት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን፣ ለማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችና ለመሳሰሉት ነገሮች ነው። (ከ1 ዮሐንስ 4:1 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ምንጊዜም ተለዋዋጭ የሆኑትን የዓለም የየጊዜው ፈሊጦችንና ፋሽኖችን ለሚመለከቱ ጉዳዮችም ይኸውም ለቄንጦች፣ ለመዝናኛዎች፣ ለምግቦች፣ ለጤንነት ወይም ለሰውነት እንቅስቃሴ ልማዶችና ለመሳሰሉትም ሁሉ ይሠራሉ። በመንፈሳዊ ሕፃን የሆነ ሰው ተሞክሮና ጥሩ አስተዋይነት ስለሚጎድለው በእንዲህ ዓይነቶቹ ነገሮች ትኩረቱ በቀላሉ ሊወሰድና መንፈሳዊ ዕድገት ከማድረግና ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቹን ከመፈጸም ወደ ኋላ ይቀራል።—ማቴዎስ 6:22-25
12. በኃላፊነት ረገድ ሕፃናት ከአዋቂዎች የሚለዩት እንዴት ነው?
12 የሕፃናት ሌላው ጠባይ ዘወትር የሌሎች እርዳታና ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው መሆናቸው ነው። ኃላፊነትን አያውቁም ወይም ለኃላፊነት ደንታ የላቸውም። ልጅነት ሁሉም ነገር ደስታና ጨዋታ እንደሆነ ያህል ብቻ የሚታይበት ጊዜ ነው። ጳውሎስ እንደተናገረው ሕፃናት ‘እንደ ልጅ ይናገራሉ፣ እንደ ልጅም ያስባሉ፣ እንደ ልጅም ይመራመራሉ ወይም ምክንያቶችን ይሰጣሉ።’ ሌሎች ለእነርሱ እንክብካቤ የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው አድርገው ያስባሉ። ስለ መንፈሳዊ ሕፃናትም እንዲሁ ሊባል ይቻላል። አንድ አዲስ የሆነ ሰው የመጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሩን ሲሰጥ ወይም መጀመሪያ ወደ መስክ አገልግሎት ለመሄድ ሲነሳ መንፈሳዊ ወላጁ እርሱን ለመርዳት ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ደስ ይለዋል። ይህ አዲስ ሰው በእንዲህ ዓይነቱ እርዳታ ላይ ብቻ ተማምኖ ለራሱ እንክብካቤ የማድረግን ኃላፊነት ለመቀበል የማይችል ሆኖ ቢቀጥል ምን ይሆናል? ግለሰቡ ለራሱ ጥረት እንደማያደርግ በግልጽ ያመለክታል።
13. እያንዳንዱ የራሱን ሸክም መሸከምን መማር ያለበት ለምንድን ነው?
13 በዚህ ረገድ “አንዱ የሌላውን ሸክም መሸከም” ቢኖርበትም “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ይሸከም” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር አስታውሱ። (ገላትያ 6:2, 5) በእርግጥ አንድ ሰው የራሱን ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶች መሸከም እንዲማር ጊዜና ጥረት ይጠይቅበታል፣ ይህም በአንዳንድ ነገሮች ረገድ መስዋዕት ማድረግን ሊጠይቅ ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ ተሳትፎውን ለመጨመር ወይም ለመንፈሳዊ ዕድገትና ኃላፊነት ለመብቃት ምንም ፍላጎት የሌለው ቢሆንና በመዝናኛም ሆነ፣ በሽርሽር ጉዞዎች፣ በአዳዲስ መሣሪያዎች በመጠቀም ወረት ወይም አስፈላጊ ባልሆነ ዓለማዊ ሥራ ፍለጋ ተጠምዶ በሕይወት ደስታዎችና ጨዋታዎች ከልክ በላይ እንዲጠላለፍ ቢፈቅድ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ዳር ቆሞ ተመልካች ብቻ ስለሚሆን ይህ ከባድ ስህተት ይሆንበታል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ” በማለት አጥብቆ አሳስቧል።—ያዕቆብ 1:22፤ 1 ቆሮንቶስ 16:13
14. የመንፈሳዊ ሕፃንን ጠባይ በማሳየት መርካት የሌለብን ለምንድን ነው?
14 አዎን፣ አንድን ሕፃን ከአዋቂ የሚለዩት በቀላሉ የሚታዩ ብዙ ጠባዮች አሉ። ይሁን እንጂ አስፈላጊው ነገር ጳውሎስ እንደተናገረው ቀስ በቀስ የሕፃንነትን ጠባዮች እያስወገድን ማደጋችን ነው። (1 ቆሮንቶስ 13:11፤ 14:20) አለዚያ ግን በመንፈሳዊ አባባል ዕድገታችን ይጎተታል። ይሁንና አንድ ሰው ዕድገት ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? ወደ ጉልምስና ለመድረስ መንፈሳዊ ዕድገት ማድረግ ምንን ይጨምራል?
ዕድገት እንዴት ይገለጣል?
15. በዕድገት ውስጥ መሠረታዊ የሆኑት ሂደቶች ምን ምን ናቸው?
15 ታዲያ በተፈጥሮአዊው ዓለማችን ውስጥ ዕድገት የሚከናወነው እንዴት ነው? “እያንዳንዱ ግለሰብ ሕይወቱ የሚጀምረው ከአንድ ነጠላ ሴል ነው” በማለት ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ ያስረዳል። “ሴሉ ለዕድገቱ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ወስዶ ለዕድገቱ ወደሚያስፈልጉት የመገንቢያ ክፍሎች ይለውጣቸዋል። በዚህም ምክንያት ነጠላው ሴል ከውስጥ ያድጋል። ይህ ሴል ሊበዛና ሌሎች ሴሎችን ለማስገኘት ሊከፋፈል የሚችል ነው። የመገንባቱ፣ የመባዛቱና የመከፋፈሉ ሂደት የዕድገት ክፍል ነው።” ከዚህ የምናገኘው ጠቃሚ ፍሬ ነገር ዕድገት የሚከናወነው ከውስጥ መሆኑን ነው። ተገቢው ገንቢ ምግብ ተወስዶ ከሰውነት ጋር ሲዋሃድና በጥቅም ላይ ሲውል ዕድገት ይገኛል። ይህም አዲስ በተወለደ ሕፃን ላይ በግልጽ ይታያል። እንደምናውቀው አዲስ የተወለደው ሕፃን በተለይ ለእርሱ ተመጣጥኖ የተዘጋጀውን ለዕድገት በሚያስፈልጉት በስብ (በቅባት)ና በፕሮቲን የበለጸገ ወተት ባለማቋረጥ ይወስዳል። ውጤቱስ? ሕፃኑ በመጀመሪያው ዓመት በክብደትና በቁመት የሚያገኘው የዕድገት መጠን በቀሪው የሕይወት ዘመኑ ከሚኖረው ተራ ዕድገት ጋር በፍጹም አይወዳደርም።
16. በብዙዎቹ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ላይ የሚታየው ምን ዓይነት ዕድገት ነው? ይህስ የሚቻለው እንዴት ነው?
16 ከዚህ ተፈጥሮአዊ የዕድገት ሂደት ከመሠረታዊ ነገሮች ወደ ጉልምስና ለመድረስ በምናደርገው መንፈሳዊ መሻሻል ሥራ ላይ ልናውል የምንችላቸው ብዙ ነገሮች እንማራለን። ከሁሉ በፊት ቋሚ የሆነ የመመገቢያ ፕሮግራም ማዘጋጀት ያስፈልጋል። መጽሐፍ ቅዱስን ለመጀመሪያ ጊዜ ማጥናት የጀመራችሁበትን ወቅት መለስ ብላችሁ አስቡ። እንደ አብዛኞቹ ሌሎች ሰዎች ከነበራችሁ ስለ አምላክ ቃል ምንም የምታውቁት ነገር አልነበረም። በኋላ ግን በየሳምንቱ ለትምህርታችሁ እየተዘጋጃችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስላደረጋችሁ በአጭር ጊዜ ውስጥ የቅዱሳን ጽሑፎችን መሠረታዊ ትምህርቶች በሙሉ ለመረዳት ቻላችሁ። ይህም ሁኔታ የአምላክን ቃል አዘውትራችሁ በመመገብ የተገኘ ከፍተኛ ዕድገት እንደነበረ መቀበል ይኖርባችኋል።
17. የዘወትር የመንፈሳዊ ምግብ መመገቢያ ፕሮግራም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
17 ይሁን እንጂ አሁንስ እንዴት ናችሁ? አሁንም የዘወትር የመመገቢያ ፕሮግራማችሁን እየተከተላችሁ ትመገባላችሁን? አንድ ሰው ከተጠመቀ በኋላ መንፈሳዊ አልሚ ምግቦችን ለመውሰድ የዘወትርና ሥርዓትን የተከተለ ጥናት አያስፈልግም ብሎ ፈጽሞ ማሰብ የለበትም። ጢሞቴዎስ የጎለመሰ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች የነበረ ቢሆንም ጳውሎስ “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፣ ይህንም አዘውትር” በማለት አጥብቆ አሳስቦታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) ሁላችንም እንዲህ ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! እናንተም መንፈሳዊ ዕድገታችሁ በግልጥ እንዲታይ ከፈለጋችሁ እንዲህ ዓይነቶቹ ጥረቶች በጣም አስፈላጊ ናቸው።
18. የአንድ ሰው መንፈሳዊ ዕድገት የሚታየው እንዴት ነው?
18 አንድ ሰው ማደጉ እንዲገለጥ ለማድረግ ማወቁ እንዲታይለት ብሎ ወይም ሌሎችን ለማስደነቅ በመሞከር የተለየ ጥረት ማድረግ አይኖርበትም። ኢየሱስ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም” እንዲሁም “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:14፤ 12:34) ልባችንና አእምሮአችን በአምላክ ቃል መልካም ነገሮች ሲሞላ ይህንኑ በምናደርገውም ሆነ በምንናገረው ከመግለጽ ልንቆጠብ አንችልም።
19. መንፈሳዊ ዕድገታችንን በተመለከተ ምን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል? ምን ውጤትንስ በመጠባበቅ?
19 እንግዲያው ጥያቄው፦ ውስጣዊ መንፈሳዊ ዕድገታችሁን ሊያነቃቃ የሚችለውን በመንፈሳዊ የበለፀገ ነገር ለመመገብ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትራችሁ ታጠናላችሁን? በማጥናት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አዘውትራችሁ ትካፈላላችሁን? የሚል ነው። በመንፈሳዊ ዕድገትን ረገድ ተሳትፎ የሌላችሁ ተመልካቾች ብቻ በመሆን አትርኩ። ይሖዋ በሚያቀርበው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ሙሉ በሙሉ እየተጠቀማችሁ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ቁርጥ ያለ አዎንታዊ እርምጃ ውሰዱ። ‘በእግዚአብሔር [በይሖዋ አዓት] ሕግ ደስ የሚላችሁና እርሱንም ቀንና ሌሊት የምታሰላስሉት’ ከሆናችሁ ስለ እናንተም “ስለዚህም እርሱ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ ቅጠሏም እንደማይረግፍ በፈሳሽ ውኃ ዳር እንደተተከለች ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይሳካለታል” ሊባልላችሁ ይችላል። (መዝሙር 1:2, 3) ሆኖም መንፈሳዊ ዕድገት በማድረግ እንደምትቀጥሉ ለማረጋገጥ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? ይህን በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርታችን የምንወያይበት ይሆናል።
ልትመልሱ ትችላላችሁ?
◻ የራሳችንን መንፈሳዊ ዕድገት መመርመራችን ወቅታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ መንፈሳዊ ዕድገት ከመንፈሳዊ የምግብ ፍላጎት ጋር ዝምድና ያለው እንዴት ነው?
◻ “የትምህርት ነፋስ ሁሉ” ማለት ምን ማለት ነው?
◻ እያንዳንዱ የየራሱን ሸክም መሸከም ያለበት ለምንድን ነው?
◻ መንፈሳዊ ዕድገት ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ለማንበብ ጊዜ ትመድባላችሁን?