የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w01 8/1 ገጽ 12-17
  • እድገታችሁ ግልጥ ሆኖ ይታይ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • እድገታችሁ ግልጥ ሆኖ ይታይ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በእምነትና በእውቀት የሚገኝ አንድነት
  • “የመንፈስ ፍሬ” ማፍራት
  • እድገት በማድረግ አምላክን አስከብር
  • እድገትህ በግልጽ እንዲታይ አድርግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ማደግህ በግልጥ ይታይ
    ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ
  • ወጣቶች—እድገታችሁ በግልጽ እንዲታይ አድርጉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • እድገትህ በግልጽ እንዲታይ አድርግ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
w01 8/1 ገጽ 12-17

እድገታችሁ ግልጥ ሆኖ ይታይ

“ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ [“ግልጥ ሆኖ እንዲታይ፣” NW ] ይህን አስብ፣ ይህንም አዘውትር።”​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:15

1. አንድ ፍሬ መብሰሉንና ለመበላት መድረሱን እንዴት ማወቅ ትችላለህ?

እስቲ ብርቱካን፣ ሙዝ፣ ማንጎ ወይም ሌላ የምትወደውን አንድ ፍሬ አስብ። መብሰሉንና ለመበላት መድረሱን ማወቅ ትችላለህ? እንደምታውቅ ጥርጥር የለውም። መዓዛው፣ መልኩና ልስላሴው ብሉኝ ብሉኝ ያሰኛል። ገና ገመጥ ስታደርገው ከፍተኛ እርካታ ይሰማሃል። አቤት ውኃው! አቤት ጣዕሙ! የሚሰጥህ እርካታና ደስታ ልዩ ነው።

2. ጉልምስና ግልጥ ሆኖ የሚታየው እንዴት ነው? እርስ በርስ በሚኖረን ግንኙነት ላይስ ምን አስተዋጽኦ አለው?

2 በዕለት ተዕለት ሕይወት የሚያጋጥም ይህ ዓይነቱ አስደሳች ሁኔታ በሌሎች የሕይወት መስኮች ከሚያጋጥሙ ሁኔታዎች ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንድ ፍሬ መብሰሉ እንደሚታወቅ ሁሉ የአንድ ሰው መንፈሳዊ ጉልምስናም ብዙውን ጊዜ በተለያዩ መንገዶች ይገለጣል። በአንድ ሰው ላይ እንደ ማስተዋልና ጥበብ የመሳሰሉ ባሕርያትን ስንመለከት ግለሰቡ እንደጎለመሰ እንረዳለን። (ኢዮብ 32:7-9) በዝንባሌያቸውና በድርጊታቸው እንደነዚህ ያሉ ባሕርያትን ከሚያንጸባርቁ ሰዎች ጋር መቀራረብና አብሮ መሥራት በእርግጥም የሚያስደስት ነው።​—⁠ምሳሌ 13:20

3. ኢየሱስ በዘመኑ ስለነበሩት ሰዎች የሰጠው መግለጫ ስለ ጉልምስና ምን ይጠቁማል?

3 በሌላው በኩል ደግሞ አንድ ሰው በአካል የጎለመሰ ሊሆንና አነጋገሩና ድርጊቱ ግን በስሜትና በመንፈሳዊ እንዳልጎለመሰ ሊያሳዩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመኑ የነበረውን አስቸጋሪ ትውልድ በማስመልከት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፣ እነርሱም:- ጋኔን አለበት አሉት። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፣ እነርሱም:- እነሆ፣ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፣ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል።” ምንም እንኳ እነዚህ ሰዎች በአካል የጎለመሱ ቢሆኑ ኢየሱስ ምንም ከማያውቁ “ልጆች” ጋር አመሳስሏቸዋል። ጨምሮም “ጥበብም በልጆችዋ [“በሥራዋ፣” NW ] ጸደቀች” በማለት ተናግሯል።​—⁠ማቴዎስ 11:16-19

4. እድገትና ጉልምስና በምን መንገዶች ይገለጣሉ?

4 አንድ ሰው ጉልምስናን ለይቶ የሚያሳውቀው ጥበብ ያለው መሆኑን በሚያከናውነው ሥራና በሚያፈራው ፍሬ ማወቅ እንደሚቻል ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ያሳያሉ። ከዚህ ጋር በመስማማት ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠውን ምክር ልብ በል። ጢሞቴዎስ ሊከታተላቸው የሚገቡ የተለያዩ ነገሮችን ከዘረዘረ በኋላ ጳውሎስ “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ [“ግልጥ ሆኖ እንዲታይ፣” NW ] ይህን አስብ፣ ይህንም አዘውትር” ብሎታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) አዎን፣ አንድ ክርስቲያን ወደ ጉልምስና የሚያደርገው እድገት ‘ይገለጣል’ ወይም ግልጽ ሆኖ ይታያል። ክርስቲያናዊ ጉልምስና ፍንትው ብሎ እንደወጣ ብርሃን ግልጽ ሆኖ የሚታይ እንጂ የተሰወረ ባሕርይ አይደለም። (ማቴዎስ 5:14-16) ስለዚህ እድገትና ጉልምስና የሚገለጥባቸውን ሁለት ዋና ዋና መንገዶች እንመረምራለን። (1) በእውቀት፣ በማስተዋልና በጥበብ በማደግ፤ (2) የመንፈስ ፍሬ በማፍራት።

በእምነትና በእውቀት የሚገኝ አንድነት

5. ጉልምስና እንዴት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል?

5 ብዙ መዝገበ ቃላት ጉልምስና የሚለውን ቃል የተሟላ እድገት፣ ሙሉ ሰው መሆንና ወደ መጨረሻ ወሰን ወይም ወደ አንድ የሚፈለግ ደረጃ መድረስ በማለት ይፈቱታል። ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው አንድ ፍሬ ጠቅላላ የዕድገት ደረጃውን ከጨረሰ በኋላ ተፈላጊውን መልክ፣ ቀለም፣ መዓዛና ጣዕም በሚይዝበት ጊዜ ፍሬው እንደበሰለ ይታወቃል። ስለዚህ ጉልምስና ምርጥነት፣ ምሉዕነት ሌላው ቀርቶ ፍጹምነት ከሚሉት ቃላት ጋር ይመሳሰላል።​—⁠ኢሳይያስ 18:5፤ ማቴዎስ 5:45-48፤ ያዕቆብ 1:4

6, 7. (ሀ) ይሖዋ ሁሉም አገልጋዮቹ ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና እንዲደርሱ እንደሚፈልግ ምን ያሳያል? (ለ) መንፈሳዊ ጉልምስና ከምን ነገር ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው?

6 ይሖዋ አምላክ ሁሉም አገልጋዮቹ ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና እንዲደርሱ ይፈልጋል። ለዚህም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ግሩም ዝግጅት አድርጓል። ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኙ ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት ጽፎላቸዋል:- “እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፣ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፣ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፣ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኰል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም።”​—⁠ኤፌሶን 4:11-14

7 ጳውሎስ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ እንደገለጸው አምላክ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንዲህ ያሉ በርካታ መንፈሳዊ ዝግጅቶች ያደረገበት ምክንያት ሁሉም ‘በእምነትና በእውቀት ወደሚገኝ አንድነት እንዲደርሱ፣’ “ሙሉ ሰው” እንዲሆኑና ‘ወደ ክርስቶስ ልክ እንዲደርሱ’ ነው። በተሳሳቱ አስተሳሰቦችና ትምህርቶች እንደ መንፈሳዊ ሕፃናት ወዲያና ወዲህ ከመንሳፈፍ የምንጠበቀው በዚህ መንገድ ብቻ ነው። ስለሆነም ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና እድገት በማድረግና ‘የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ በሚገኝ አንድነት’ መካከል የተቀራረበ ዝምድና እንዳለ እንመለከታለን። ጳውሎስ ባሰፈረው ምክር ውስጥ ልብ ልንላቸው የሚገቡ በርካታ ነጥቦች አሉ።

8. በእምነትና በትክክለኛ እውቀት ‘አንድነትን’ ለመጠበቅ ምን ያስፈልጋል?

8 በመጀመሪያ ደረጃ፣ “አንድነት” መጠበቅ ስላለበት ጎልማሳ ክርስቲያን በእምነትና በእውቀት ከእምነት ባልንጀሮቹ ጋር የተባበረና ሙሉ በሙሉ የተስማማ መሆን ይኖርበታል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት በተመለከተ የግል አመለካከቱን ወይም አስተሳሰቡን አያራምድም ወይም ግትር ያለ አቋም አይዝም። ከዚያ ይልቅ ይሖዋ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስና ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝት በገለጠው እውነት ላይ ሙሉ በሙሉ ይታመናል። በክርስቲያናዊ ጽሑፎች፣ በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች አማካኝነት ‘በጊዜው’ የሚቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ አዘውትረን በመመገብ በእምነትና በእውቀት ከክርስቲያን ባልደረቦቻችን ጋር የመሠረትነውን “አንድነት” መጠበቅ እንችላለን።​—⁠ማቴዎስ 24:45

9. ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ በተጠቀመበት መሠረት “እምነት” የሚለውን ቃል ትርጉም አብራራ።

9 ሁለተኛ፣ “እምነት” የሚለው ቃል የሚያመለክተው እያንዳንዱ ክርስቲያን የሚያዳብረውን እምነት ሳይሆን አጠቃላዩን የእምነታችንን ‘ስፋት፣ ርዝመት፣ ከፍታና ጥልቀት’ ነው። (ኤፌሶን 3:18፤ 4:5፤ ቆላስይስ 1:23፤ 2:7) አንድ ክርስቲያን ‘ከእምነት’ ከፊሉን ብቻ ቢቀበልና ሌላውን ቢተው ከእምነት ባልደረቦቹ ጋር እንዴት አንድ ሊሆን ይችላል? ይህ ማለት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች ስላወቅን ወይም የእውነትን እውቀት ከላይ ከላይ ወይም ከፊሉን ብቻ ስለተገነዘብን በዚያ መርካት አይገባንም። ከዚያ ይልቅ ይሖዋ ቃሉን በጥልቀት መቆፈር እንችል ዘንድ በድርጅቱ አማካኝነት በሚያቀርብልን በሁሉም ዝግጅቶች የመጠቀም ፍላጎት ሊያድርብን ይገባል። በተቻለን አቅም የአምላክን ፈቃድና ዓላማ በትክክልና ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይገባናል። ይህም ጊዜ ወስዶ መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ማንበብን፣ ማጥናትን፣ የእርሱን እርዳታና መመሪያ ለማግኘት ወደ አምላክ መጸለይን፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘትንና በመንግሥቱ የስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግን ይጨምራል።​—⁠ምሳሌ 2:1-5

10. ኤፌሶን 4:​13 ላይ በተሠራበት መንገድ “እስክንደርስ ድረስ” የሚለው መግለጫ ምን ያመለክታል?

10 ሦስተኛ፣ ጳውሎስ ሦስቱን ግቦች ከጠቀሰ በኋላ “እስክንደርስ ድረስ” የሚል መግለጫ ተጠቅሟል። “እስክንደርስ” የሚለውን መግለጫ በተመለከተ አንድ የመምሪያ መጽሐፍ “ሁሉም በተናጠል ለየብቻው የሚያደርገው ሳይሆን ሁሉም በአንድነት” የሚል ትርጉም ሰጥቶታል። በሌላ አባባል ሁላችንም ከመላው የወንድማማች ማኅበር ጋር አንድ ላይ ሆነን ጎልማሳ ክርስቲያኖች እንድንሆን የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ዚ ኢንተርፕሪተርስ ባይብል የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “አንድ የሰውነት ክፍል ከተቀሩት የሰውነት ክፍሎች ተለይቶ ብቻውን እንደማያድግ ሁሉ ግለሰቦች በተናጠል በሚያደርጉት እድገትም ወደ አንድ መንፈሳዊ የእድገት ደረጃ ላይ መድረስ አይቻልም።” ጳውሎስ እምነታቸውን በጥልቅ መረዳት የሚኖርባቸው “ከቅዱሳን ሁሉ ጋር” እንደሆነ የኤፌሶን ክርስቲያኖችን አሳስቧቸዋል።​—⁠ኤፌሶን 3:18

11. (ሀ) መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ምን ነገርን አያመለክትም? (ለ) እድገት ለማድረግ ምን ያስፈልገናል?

11 መንፈሳዊ እድገት ማድረግ አእምሯችንን በእውቀትና በብዙ ትምህርት መሙላት ማለት እንዳልሆነ ከጳውሎስ ቃላት መገንዘብ ይቻላል። ጎልማሳ ክርስቲያን በችሎታው ሌሎችን ለማስደነቅ አይሞክርም። ከዚያ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 4:18) አዎን፣ ‘እየተጨመረ የሚበራው’ ግለሰቡ ሳይሆን ‘መንገዱ’ ነው። ይሖዋ ለሕዝቡ ከሚሰጣቸው እያደር ከሚገለጠው የአምላክ ቃል እውቀት ጋር እኩል ለመራመድ ያልተቋረጠ ጥረት ብናደርግ በመንፈሳዊ እያደግን እንሄዳለን። እኩል መራመድ ማለት ወደፊት መግፋት ማለት ነው። ይህን ደግሞ ሁላችንም ማድረግ እንችላለን።​—⁠መዝሙር 97:11፤ 119:105

“የመንፈስ ፍሬ” ማፍራት

12. በምናደርገው መንፈሳዊ እድገት የመንፈስ ፍሬዎችን ማፍራት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ‘በእምነትና በትክክለኛ እውቀት ወደሚገኝ አንድነት’ መድረስ አስፈላጊ ቢሆንም በየትኛውም የኑሮ ዘርፍ የአምላክን የመንፈስ ፍሬ ማፍራትም የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። ለምን? ይህ የሆነበት ምክንያት ቀደም ሲል እንደተመለከትነው እድገት ድብቅ ወይም የተሰወረ ሳይሆን ሌሎችን ሊጠቅምና ሊያንጽ የሚችል በገሃድ የሚታይ ባሕርይ ነው። እርግጥ ነው መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የምንጓጓበት ምክንያት እንዲሁ ከላይ ጥሩ ሰው መስለን ለመታየት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ መንፈስ የሚሰጠንን አመራር ተከትለን መንፈሳዊ እድገት ስናደርግ በዝንባሌያችንና በድርጊታችን ከፍተኛ ለውጥ ይታያል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በመንፈስ ተመላለሱ፣ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ” በማለት ተናግሯል።​—⁠ገላትያ 5:16

13. እድገት መኖሩን በግልጽ የሚያሳየው ለውጥ ምንድን ነው?

13 ከዚያም ጳውሎስ ‘የተገለጡ’ በርካታ ‘የሥጋ ሥራዎችን’ መዘርዘሩን ቀጠለ። አንድ ሰው አምላክ የሚፈልግበትን ብቃቶች ከማወቁ በፊት አኗኗሩ የዓለምን መንገዶች የተከተለና “ዝሙት፣ ርኵሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቊጣ፣ አድመኛነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ መግደል፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ ይህንም የሚመስል ነው” በማለት ጳውሎስ ከዘረዘራቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን ይፈጽም የነበረ ሊሆን ይችላል። (ገላትያ 5:19-21) ይሁን እንጂ ግለሰቡ መንፈሳዊ እድገት እያደረገ ሲሄድ እነዚህን ‘የሥጋ ሥራዎች’ እያሸነፈ በእነርሱ ምትክ ‘የመንፈስ ፍሬ’ ማፍራት ይጀምራል። እንዲህ ያለው በሌሎች ዘንድ የሚታይ ለውጥ ግለሰቡ ወደ ክርስቲያናዊ ጉልምስና እድገት እያደረገ እንዳለ በግልጽ ያሳያሉ።​—⁠ገላትያ 5:22

14. ‘የሥጋ ሥራ’ እና “የመንፈስ ፍሬ” የሚሉትን ሁለት መግለጫዎች አብራራ።

14 ‘የሥጋ ሥራ’ እና “የመንፈስ ፍሬ” የሚሉትን መግለጫዎች ልብ ማለት ይኖርብናል። ‘ሥራ’ የአንድ ሰው ተግባር ወይም የአንድ ድርጊት ውጤት ነው። በሌላ አባባል ጳውሎስ የሥጋ ሥራ በማለት በዝርዝር የጻፋቸው ነገሮች አንድ ሰው ሆን ብሎ ወይም በሥጋ ድካም ምክንያት የሚያደርጋቸው ነገሮች ናቸው። (ሮሜ 1:24, 28፤ 7:21-25) በሌላ በኩል ደግሞ “የመንፈስ ፍሬ” የሚለው መግለጫ የተዘረዘሩት ባሕርያት አንድ ሰው በራሱ ጥረት ጠባዩን ወይም ባሕርዩን ማሻሻል እንደሚችል ሳይሆን በአምላክ መንፈስ አማካኝነት የሚገኙ መሆናቸውን ያመለክታል። አንድ ዘር ፍሬ የሚያፈራው ጥሩ እንክብካቤ ሲደረግለት እንደሆነ ሁሉ አንድ ሰው የመንፈስ ፍሬዎችን ማፍራት የሚችለውም መንፈስ ቅዱስ በውስጡ እንደልብ መሥራት ሲችል ነው።​—⁠መዝሙር 1:1-3

15. ለሁሉም “የመንፈስ ፍሬ” ገጽታዎች ትኩረት መስጠቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

15 ጳውሎስ የዘረዘራቸውን አስፈላጊ የሆኑ ባሕርያት ለማመልከት የተጠቀመበት “ፍሬ” የሚለው ቃልም ሌላው ሊመረመር የሚገባው ነው። መንፈሱ ደስ ያለንን ባሕርይ መምረጥ እንችል ዘንድ የተለያዩ ፍሬዎችን አያፈራም። ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃትና ራስን መግዛት በማለት ጳውሎስ የዘረዘራቸው ባሕርያት በጠቅላላ የሚሰጡት ጥቅም እኩል ነው። ሁሉም በአንድ ላይ ሆነው አዲሱን ክርስቲያናዊ ሰው ይፈጥራሉ። (ኤፌሶን 4:24፤ ቆላስይስ 3:10) ስለዚህ ከተፈጥሯችን የተነሳ ከእነዚህ ባሕርያት መካከል አንዳንዶቹ በእኛ ላይ ይበልጥ ቢንጸባረቁም እንኳ ጳውሎስ ለዘረዘራቸው ለሁሉም ባሕርያት ትኩረት መስጠታችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ በማድረግ በመላው አኗኗራችን የክርስቶስን ዓይነት ባሕርያት ይበልጥ ማንጸባረቅ እንችላለን።​—⁠1 ጴጥሮስ 2:12, 21

16. ክርስቲያናዊ ጉልምስናን የምንከታተልበት ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው? ይህን ልናደርግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

16 ክርስቲያናዊ ጉልምስናን የምንከታተልበት ዋነኛ ዓላማ ከፍተኛ እውቀት ለመሰብሰብ ወይም መልካም የሚባሉ ባሕርያትን ለማዳበር ካለን ፍላጎት የተነሳ አለመሆኑን ከጳውሎስ መግለጫ ልንረዳ እንችላለን። የአምላክ መንፈስ በእኛ ላይ በነፃነት እንዲፈስስ ለማድረግ ነው። አስተሳሰባችንና ድርጊታችን የአምላክ መንፈስ ለሚሰጠው አመራር ጥሩ ምላሽ በሰጠ መጠን የዚያኑ ያህል እኛም በመንፈሳዊ የጎለመስን እንሆናለን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ መንፈስ ለሚያሳድረው ተጽእኖ ልባችንንና አእምሯችንን ክፍት ማድረግ አለብን። ይህም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘትና ተሳታፊ መሆንን ያካትታል። መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት፣ በምናደርገው ምርጫና ውሳኔ እንዲመሩን በመፍቀድ የአምላክን ቃል አዘውትረን ማጥናትና ማሰላሰል ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን እድገታችን በሁሉም ዘንድ ግልጥ ሆኖ እንደሚታይ ምንም ጥርጥር የለውም።

እድገት በማድረግ አምላክን አስከብር

17. እድገት ማድረግ የሰማዩ አባታችንን ከማክበር ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

17 የምናደርገው እድገት ግልጥ ሆኖ መታየቱ ውሎ አድሮ ለእኛ ሳይሆን መንፈሳዊ የጉልምስና ደረጃ ላይ እንድንደርስ ለረዳን ለሰማያዊ አባታችን ለይሖዋ ክብርና ውዳሴ ያመጣለታል። ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት ደቀ መዛሙርቱን “ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 15:8) ደቀ መዛሙርቱ በሚያፈሩት የመንፈስ ፍሬም ሆነ በአገልግሎት በሚያገኙት የመንግሥቱ ፍሬ ለይሖዋ ክብር አምጥተዋል።​—⁠ሥራ 11:4, 18፤ 13:48

18. (ሀ) በጊዜያችን ምን አስደሳች የመከር ሥራ እየተከናወነ ነው? (ለ) ይህ መከር ተፈታታኝ የሆኑ ምን ሁኔታዎችን አስከትሏል?

18 በዛሬው ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች በዓለም ዙሪያ በመንፈሳዊ የመከር ሥራ ሲካፈሉ ይሖዋ ይባርካቸዋል። ካለፉት በርካታ ዓመታት ጀምሮ በየዓመቱ 300, 000 የሚያክሉ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች ውሳኔያቸውን በውኃ ጥምቀት ያሳያሉ። ይህ እኛን የሚያስደስት ከመሆኑም በላይ የይሖዋንም ልብ ደስ እንደሚያሰኝ ጥርጥር የለውም። (ምሳሌ 27:11) ይሁን እንጂ በዚህ መንገድ የሚገኘው ደስታና ለይሖዋ የሚቀርበው ውዳሴ ቀጣይ ይሆን ዘንድ እነዚህ አዳዲስ ሰዎች ‘በእርሱ [በክርስቶስ] መመላለስና ሥር ሰድደው በእርሱ መታነጽ’ ይኖርባቸዋል። (ቆላስይስ 2:6, 7) ይህም በአምላክ ሕዝቦች ላይ ሁለት ፈታኝ ሁኔታዎችን ያስከትላል። በአንድ በኩል በቅርቡ የተጠመቅህ ከሆንክ ‘እድገትህ በሰው ሁሉ ዘንድ እንዲገለጥ’ ለማድረግ የቻልከውን ያህል ጥረት ለማድረግ ፈቃደኛ ነህ? በሌላው በኩል ደግሞ በእውነት ቤት ውስጥ የተወሰነ ጊዜ የቆየህ ከሆንክ ኃላፊነቶችን ለመቀበልና የአዲሶችን መንፈሳዊ ደህንነት ለመንከባከብ ፈቃደኛ ነህ? በሁለቱም አቅጣጫ ወደ ጉልምስና እድገት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ነው።​—⁠ፊልጵስዩስ 3:16፤ ዕብራውያን 6:1

19. እድገትህ ግልጥ ሆኖ እንዲታይ ካደረግህ ምን መብትና በረከት ልታገኝ ትችላለህ?

19 እድገታቸው ግልጥ ሆኖ እንዲታይ ጥረት የሚያደርጉ ሁሉ አስደናቂ በረከት ይጠብቃቸዋል። ጳውሎስ እድገት እንዲያደርግ ጢሞቴዎስን ካሳሰበው በኋላ ያሰፈራቸውን የማበረታቻ ቃላት አስታውስ:- “ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፣ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፣ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።” (1 ጢሞቴዎስ 4:16) እድገትህ ግልጥ ሆኖ እንዲታይ ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግህ የአምላክን ስም ታስከብራለህ እንዲሁም የእርሱን በረከት ከሚያገኙት ሰዎች መካከል ልትሆን ትችላለህ።

ታስታውሳለህን?

• መንፈሳዊ ጉልምስና በምን መንገዶች ሊገለጥ ይችላል?

• ጉልምስናን የሚያንጸባርቀው ምን ዓይነት እውቀትና ማስተዋል ነው?

• ‘የመንፈስ ፍሬን’ ማፍራት መንፈሳዊ እድገትን የሚጠቁመው እንዴት ነው?

• ወደ ጉልምስና በምናደርገው እድገት ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታዎችን መቀበል ይኖርብናል?

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መብሰል ወይም ጉልምስና በግልጽ የሚታይ ነገር ነው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከተገለጠው እውነት ጋር እኩል በመራመድ መንፈሳዊ እድገት እናደርጋለን

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጸሎት “የመንፈስ ፍሬ” እንድናፈራ ይረዳናል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ