እድገትህ በግልጽ እንዲታይ አድርግ
“እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን።”—1 ጢሞ. 4:15
1, 2. ስለ ጢሞቴዎስ የልጅነት ሕይወት እንዲሁም በ20 ዓመቱ ገደማ ስለተከሰተው ለውጥ ምን የምናውቀው ነገር አለ?
ጢሞቴዎስ ያደገው የሮም ግዛት በሆነችው በገላትያ (በአሁኗ ቱርክ ውስጥ) ነው። ኢየሱስ ከሞተ ከአሥርተ ዓመታት በኋላ በዚህች ከተማ በርካታ የክርስቲያን ጉባኤዎች ተቋቁመው ነበር። በአንድ ወቅት ላይ ወጣቱ ጢሞቴዎስ፣ እናቱና አያቱ ወደ ክርስትና እምነት ተለውጠው ከእነዚህ ጉባኤዎች ውስጥ በአንዱ ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ ነበር። (2 ጢሞ. 1:5፤ 3:14, 15) ጢሞቴዎስ ባደገበት አካባቢ ክርስቲያን ሆኖ ያሳለፈው የወጣትነት ሕይወት አስደሳች እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም በድንገት ነገሮች መለወጥ ጀመሩ።
2 ይህ ለውጥ የጀመረው ሐዋርያው ጳውሎስ አካባቢውን ለሁለተኛ ጊዜ በጎበኘበት ወቅት ነበር። በዚያን ጊዜ ጢሞቴዎስ በአሥራዎቹ ዕድሜ መገባደጃ አሊያም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አካባቢ የነበረ ይመስላል። ጳውሎስ ምናልባትም ልስጥራን እየጎበኘ እያለ በአካባቢው በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ‘ወንድሞች ስለ ጢሞቴዎስ መልካም ምግባር ሲመሠክሩ’ ሳይሰማ አልቀረም። (ሥራ 16:2) ወጣቱ ጢሞቴዎስ በዚያን ወቅት ከዕድሜው በላይ የጎለመሰ ሰው እንደሆነ አሳይቶ መሆን አለበት። በመሆኑም ጳውሎስና በአካባቢው የነበረው የሽማግሌዎች አካል በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በጢሞቴዎስ ላይ እጃቸውን ከጫኑ በኋላ በጉባኤ ውስጥ ለአንድ ልዩ ሥራ አጩት።—1 ጢሞ. 4:14፤ 2 ጢሞ. 1:6
3. ጢሞቴዎስ ምን ልዩ የሆነ የአገልግሎት መብት አገኘ?
3 ጢሞቴዎስ የሐዋርያው ጳውሎስ የአገልግሎት ጓደኛ እንዲሆን ግብዣ ቀረበለት፤ ይህ በእርግጥ ልዩ የሆነ ግብዣ ነበር! (ሥራ 16:3) ጢሞቴዎስ ምን ያህል ተገርሞና ተደስቶ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም! ይህን ግብዣ መቀበሉ ከጳውሎስ አንዳንድ ጊዜም ከሌሎች ወንድሞች ጋር እየተጓዘ ሐዋርያትንና ሽማግሌዎችን ወክሎ የተለያዩ ተልዕኮዎችን የመወጣት መብት ያስገኝለታል። ጳውሎስና ጢሞቴዎስ የወንድሞች መንፈሳዊነት እንዲጠናከር በእጅጉ ሊረዳ በሚችል የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ላይ ተካፍለዋል። (የሐዋርያት ሥራ 16:4, 5ን አንብብ።) ይህ ደግሞ ጢሞቴዎስ ባደረገው መንፈሳዊ እድገት በብዙ ክርስቲያኖች ዘንድ እንዲታወቅ አድርጎታል። ሐዋርያው ጳውሎስ አሥር ለሚያህሉ ዓመታት ከጢሞቴዎስ ጋር ካገለገለ በኋላ በፊልጵስዩስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች እንዲህ በማለት ጽፎላቸዋል፦ “ስለ እናንተ ጉዳይ ከልብ የሚጨነቅ እንደ [ጢሞቴዎስ] ያለ በጎ አመለካከት ያለው ሌላ ማንም የለኝም። . . . ከአባቱ ጋር እንደሚሠራ ልጅ ምሥራቹን በማስፋፋቱ ሥራ ከእኔ ጋር እንደ ባሪያ በማገልገል ማንነቱን እንዴት እንዳስመሠከረ ታውቃላችሁ።”—ፊልጵ. 2:20-22
4. (ሀ) ጢሞቴዎስ ምን ከባድ ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር? (ለ) ጳውሎስ በ1 ጢሞቴዎስ 4:15 ላይ የተናገረው ሐሳብ ምን ጥያቄዎች ያስነሳል?
4 ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ለጢሞቴዎስ አንድ ከባድ ኃላፊነት ማለትም ሽማግሌዎችንና የጉባኤ አገልጋዮችን የመሾም መብት ሰጥቶት ነበር። (1 ጢሞ. 3:1፤ 5:22) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጢሞቴዎስ እምነት የሚጣልበት ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ሆኗል። ያም ሆኖ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ‘እድገቱ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ’ አሳስቦታል። (1 ጢሞ. 4:15) ይሁንና ጢሞቴዎስ ቀደም ሲል ከፍተኛ እድገት ማድረጉን በግልጽ አሳይቶ አልነበረም? ታዲያ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? እኛስ ጳውሎስ ከሰጠው ምክር ምን ትምህርት እናገኛለን?
መንፈሳዊ ባሕርያት በግልጽ እንዲታዩ ማድረግ
5, 6. የኤፌሶን ጉባኤ መንፈሳዊ ንጽሕናው አደጋ ላይ ወድቆ የነበረው እንዴት ነው? ጢሞቴዎስ ጉባኤውን ከአደጋ መጠበቅ የሚችለው እንዴት ነበር?
5 በ1 ጢሞቴዎስ 4:15 ዙሪያ ያሉትን ሐሳቦች እስቲ እንመርምር። (1 ጢሞቴዎስ 4:11-16ን አንብብ።) ጳውሎስ ይህን ሐሳብ ከመጻፉ በፊት ወደ መቄዶንያ ተጉዞ የነበረ ሲሆን ጢሞቴዎስን ግን በኤፌሶን እንዲቆይ ነግሮት ነበር። ለምን? በዚያች ከተማ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች የሐሰት ትምህርቶችን በማስፋፋት በጉባኤ ውስጥ መከፋፈል ፈጥረው ነበር። በመሆኑም ጢሞቴዎስ የጉባኤውን መንፈሳዊ ንጽሕና መጠበቅ ነበረበት። ታዲያ ይህን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነበር? አንደኛው መንገድ ለሌሎች ጥሩ አርዓያ በመሆን ነው።
6 ጳውሎስ፣ ለጢሞቴዎስ “ታማኞች ለሆኑት በንግግር፣ በምግባር፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና አርዓያ” እንዲሆን ጽፎለታል። አክሎም “እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ በእነዚህ ነገሮች ላይ ያረፈ ይሁን” ብሎታል። (1 ጢሞ. 4:12, 15) ጢሞቴዎስ እድገት ማድረግ የነበረበት ከኃላፊነት ቦታ አንጻር ሳይሆን መንፈሳዊ ባሕርያትን ከማዳበር ጋር በተያያዘ ነበር። ደግሞም እያንዳንዱ ክርስቲያን ማሳየት ያለበት እንዲህ ያለ መንፈሳዊ እድገት ነው።
7. በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሁሉ ምን ይጠበቅባቸዋል?
7 ጢሞቴዎስ በኖረበት ዘመን እንደነበረው ሁሉ ዛሬም በጉባኤ ውስጥ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አሉ። አንዳንዶች ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ሆነው ያገለግላሉ። ሌሎች ደግሞ በአቅኚነት አገልግሎት ተሰማርተዋል። አንዳንዶች ተጓዥ የበላይ ተመልካች፣ ቤቴላውያን ወይም ሚስዮናውያን ሆነው የማገልገል መብት አግኝተዋል። ሽማግሌዎች በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ የማስተማር ኃላፊነት አላቸው። ይሁን እንጂ ሁሉም ክርስቲያኖች ይኸውም ወንዶች፣ ሴቶች እንዲሁም ወጣቶች መንፈሳዊ እድገታቸው በግልጽ እንዲታይ የማድረግ አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል። (ማቴ. 5:16) እንዲያውም ልክ እንደ ጢሞቴዎስ የተለየ የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እድገታቸውን ለሁሉም ሰው በግልጽ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
በንግግር ረገድ አርዓያ መሆን
8. ንግግራችን በአምልኮታችን ላይ ምን ሊያስከትል ይችላል?
8 ጢሞቴዎስ አርዓያ ከሚሆንባቸው መንገዶች አንዱ በአነጋገሩ ነበር። እኛስ ከአነጋገር ጋር በተያያዘ እድገታችን በግልጽ እንዲታይ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ንግግራችን ስለ እኛ ማንነት የሚጠቁመው ብዙ ነገር አለ። ኢየሱስ “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው” ብሎ መናገሩ የተገባ ነው። (ማቴ. 12:34) በተጨማሪም የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ንግግራችን በአምልኮታችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት ተገንዝቦ ነበር። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አንድ ሰው አምልኮቱን እያከናወነ እንዳለ የሚሰማው ቢሆንም እንኳ አንደበቱን የማይገታ ከሆነ ይህ ሰው የገዛ ልቡን እያታለለ ይኖራል፤ የዚህ ሰው አምልኮም ከንቱ ነው።”—ያዕ. 1:26
9. በአነጋገር ረገድ አርዓያ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
9 ንግግራችን በጉባኤ ውስጥ ለሚገኙ ወንድሞች በመንፈሳዊ ምን ያህል እድገት እንዳደረግን ይጠቁማቸዋል። በመሆኑም የጎለመሱ ክርስቲያኖች ወራዳ፣ አሉታዊ፣ ነቀፋ የሞላበት ወይም የሚጎዳ ነገር ከመናገር ይልቅ በንግግራቸው ሌሎችን ለማነጽ፣ ለማበረታታትና ለማጽናናት ይጥራሉ። (ምሳሌ 12:18፤ ኤፌ. 4:29፤ 1 ጢሞ. 6:3-5, 20) የምንከተለውን የሥነ ምግባር አቋም እንዲሁም አምላክ ባወጣቸው የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መመራት የምንፈልገው ለምን እንደሆነ ሁልጊዜ ለሌሎች መናገራችን ለአምላክ ያደርን መሆናችንን ያሳያል። (ሮም 1:15, 16) ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የመናገር ችሎታችንን ጥሩ አድርገን እንደምንጠቀምበት ማስተዋላቸው አይቀርም፤ ይህ ደግሞ የእኛን አርዓያ እንዲከተሉ ሊያነሳሳቸው ይችላል።—ፊልጵ. 4:8, 9
በምግባርና በንጽሕና አርዓያ መሆን
10. መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ግብዝነት የሌለበት እምነት ማዳበራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
10 አንድ ክርስቲያን ጥሩ አርዓያ መሆን የሚጠበቅበት በአነጋገሩ ብቻ አይደለም። የሚናገረው ነገር ትክክል ቢሆንም በተግባር ካልተደገፈ ግብዝ ያደርገዋል። ጳውሎስ የፈሪሳውያንን ግብዝነትም ሆነ ይህ አካሄዳቸው ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ በሚገባ ያውቅ ነበር። በመሆኑም ጢሞቴዎስን እንዲህ ካለው ግብዝነት እንዲርቅ እንዲሁም ያልሆነውን ሆኖ ለመታየት ከመሞከር እንዲቆጠብ በተደጋጋሚ ጊዜ አስጠንቅቆታል። (1 ጢሞ. 1:5፤ 4:1, 2) ይሁንና ጢሞቴዎስ ግብዝ አልነበረም። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው በሁለተኛው ደብዳቤ ላይ “በአንተ ውስጥ ያለውን ምንም ግብዝነት የሌለበት እምነት አስታውሳለሁ” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞ. 1:5) እንደዚያም ሆኖ ጢሞቴዎስ ግብዝ ክርስቲያን አለመሆኑን ለሌሎች በግልጽ ማሳየት ነበረበት። በምግባሩ አርዓያ ሆኖ መገኘት ይጠበቅበት ነበር።
11 ጳውሎስ ቁሳዊ ሀብትን አስመልክቶ ለጢሞቴዎስ ምን ጽፎለታል?
11 ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፋቸው ሁለት ደብዳቤዎች ላይ ምግባርን በሚመለከት ከተለያየ አቅጣጫ ምክር ሰጥቶታል። ለምሳሌ ያህል፣ ጢሞቴዎስ ቁሳዊ ሀብትን ከማሳደድ መቆጠብ ነበረበት። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፎለታል፦ “የገንዘብ ፍቅር የብዙ ዓይነት ጎጂ ነገሮች ሥር ነው፤ አንዳንዶች በዚህ ፍቅር ተጠምደው ከእምነት ጎዳና ስተው ወጥተዋል፤ እንዲሁም ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።” (1 ጢሞ. 6:10) አንድ ሰው ቁሳዊ ሀብትን መውደዱ በመንፈሳዊ ችግር እንዳለበት ይጠቁማል። ከዚህ በተቃራኒ ግን ባላቸው “ምግብ እንዲሁም ልብስና መጠለያ” ረክተው ቀላል ሕይወት የሚመሩ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እድገታቸው በግልጽ ይታያል።—1 ጢሞ. 6:6-8፤ ፊልጵ. 4:11-13
12. በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እድገታችን በግልጽ እንዲታይ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
12 ጳውሎስ ክርስቲያን ሴቶች “በልከኝነትና በማስተዋል ሥርዓታማ በሆነ ልብስ ራሳቸውን [ማስዋባቸው]” ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለጢሞቴዎስ ገልጾለታል። (1 ጢሞ. 2:9) በአለባበስና በአጋጌጥ ምርጫቸው ብሎም በሌሎች የሕይወታቸው ዘርፎች ልከኛ እንዲሁም አስተዋይ የሆኑ ሴቶች ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። (1 ጢሞ. 3:11) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለክርስቲያን ወንዶችም ይሠራል። ጳውሎስ የበላይ ተመልካቾች ‘በልማዶቻቸው ልከኛ እንዲሆኑ፣ ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖራቸውና ሥርዓታማ እንዲሆኑ’ አሳስቧቸዋል። (1 ጢሞ. 3:2) እኛም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እነዚህን ባሕርያት ስናሳይ እድገታችን ለሁሉም ሰው በግልጽ ይታያል።
13. እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ እኛም በንጽሕና ረገድ አርዓያ መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
13 ጢሞቴዎስ በንጽሕና ረገድም አርዓያ መሆን ነበረበት። ጳውሎስ ንጽሕና የሚለውን ቃል የተጠቀመው ምግባር ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱን በተለይም የፆታ ሥነ ምግባርን በተዘዋዋሪ ለማመልከት ነበር። ጢሞቴዎስ በተለይ ከሴቶች ጋር ባለው ግንኙነት ረገድ የማይነቀፍ ምግባር ማሳየት ይጠበቅበት ነበር። ‘አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እህቶች አድርጎ በፍጹም ንጽሕና’ መያዝ ነበረበት። (1 ጢሞ. 4:12፤ 5:2) አንድ ሰው አንድ ዓይነት የሥነ ምግባር ብልግናን ማንም ሳያየው እንደፈጸመ ቢሰማውም እንኳ ድርጊቱ በአምላክ ፊት የተሰወረ አይደለም፤ ይዋል ይደር እንጂ በሰዎችም ዘንድ መታወቁ አይቀርም። በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን የሚሠራቸው መልካም ሥራዎች ተደብቀው ሊቀሩ አይችሉም። (1 ጢሞ. 5:24, 25) በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉም ክርስቲያኖች በምግባርና በንጽሕና ረገድ እድገታቸው በግልጽ እንዲታይ የማድረግ አጋጣሚ አላቸው።
ፍቅርና እምነት አስፈላጊ ነው
14. ቅዱሳን መጻሕፍት እርስ በርስ የመዋደድን አስፈላጊነት ጎላ አድርገው የሚገልጹት እንዴት ነው?
14 የእውነተኛ ክርስትና ዋነኛ መታወቂያው ፍቅር ነው። ኢየሱስ “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። (ዮሐ. 13:35) እንዲህ ያለውን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ ቃል ‘እርስ በርስ በፍቅር’ እንድንቻቻል፣ ‘አንዳችን ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምንራራ እንድንሆን፣ እርስ በርሳችን በነፃ ይቅር እንድንባባል’ እንዲሁም እንግዳ ተቀባይ እንድንሆን ይመክረናል። (ኤፌ. 4:2, 32፤ ዕብ. 13:1, 2) ሐዋርያው ጳውሎስ “በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ” ሲል ጽፏል።—ሮም 12:10
15. ሁሉም ክርስቲያኖች በተለይም ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ፍቅር ማሳየታቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
15 ጢሞቴዎስ የእምነት ባልንጀሮቹን በኃይል ወይም ደግነት በጎደለው መንገድ ቢይዛቸው ኖሮ ይህ ድርጊቱ አስተማሪና የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያከናውነው መልካም ተግባር ጎልቶ እንዳይታይ ያደርግበት ነበር። (1 ቆሮንቶስ 13:1-3ን አንብብ።) በሌላ በኩል ግን ጢሞቴዎስ ለወንድሞቹ ከልብ የመነጨ ፍቅር ማሳየቱ እንዲሁም እነሱን በእንግድነት መቀበሉና ለእነሱ መልካም ማድረጉ መንፈሳዊ እድገቱ ጎልቶ እንዲታይ እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ አርዓያ መሆን ከሚጠበቅበት ባሕርያት መካከል ፍቅርን መጥቀሱ ተገቢ ነበር።
16. ጢሞቴዎስ ጠንካራ እምነት ማሳየት የነበረበት ለምንድን ነው?
16 ጢሞቴዎስ በኤፌሶን በቆየባቸው ጊዜያት እምነቱ ተፈትኖ ነበር። አንዳንዶች ከክርስትና እውነቶች ጋር የሚጋጩ መሠረተ ትምህርቶችን ያስፋፉ ነበር። ሌሎች ደግሞ ‘የፈጠራ ወሬዎችን’ ወይም ለጉባኤው መንፈሳዊነት ምንም የማይፈይዱ እርባና ቢስ ሐሳቦችን ያሰራጩ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 1:3, 4ን አንብብ።) ጳውሎስ እንዲህ ያሉ ግለሰቦችን ‘በትዕቢት የተወጠሩና ምንም የማያስተውሉ ይሁንና ስለ ቃላት ጥያቄ የማንሳትና የመከራከር አባዜ የተጠናወታቸው’ በማለት ገልጿቸዋል። (1 ጢሞ. 6:3, 4) ጢሞቴዎስ ወደ ጉባኤው ሰርገው በገቡት በእነዚህ ጎጂ ሐሳቦች ላይ በማውጠንጠን መንፈሳዊነቱን አደጋ ላይ ይጥል ይሆን? በፍጹም! ምክንያቱም ጳውሎስ ‘መልካሙን የእምነት ተጋድሎ እንዲጋደል’ እንዲሁም “ቅዱስ የሆነውን ነገር ከሚጻረሩ ከንቱ ንግግሮችና በውሸት ‘እውቀት’ ተብለው ከሚጠሩ እርስ በርሳቸው ከሚቃረኑ ሐሳቦች” እንዲርቅ ጢሞቴዎስን አሳስቦት ነበር። (1 ጢሞ. 6:12, 20, 21) ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስ የሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር እንደተከተለ ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ቆሮ. 10:12
17. በዛሬው ጊዜ እምነታችን ሊፈተን የሚችለው እንዴት ነው?
17 የሚገርመው ነገር ጢሞቴዎስ “በኋለኞቹ ዘመናት አንዳንዶች ከመናፍስት ለሚመነጩ አሳሳች ቃሎችና የአጋንንት ትምህርቶች ጆሯቸውን በመስጠት ከእምነት [እንደሚወጡ]” ተነግሮት ነበር። (1 ጢሞ. 4:1) በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ ግለሰቦችን ጨምሮ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች በሙሉ እንደ ጢሞቴዎስ ጠንካራና ጽኑ እምነት መያዛቸው አስፈላጊ ነው። ክህደትን በመቃወም ረገድ ጠንካራ አቋም በመያዝና ቁርጥ ያለ እርምጃ በመውሰድ እድገታችን በግልጽ እንዲታይ ማድረግ ብሎም በእምነት ለሌሎች አርዓያ መሆን እንችላለን።
እድገትህ በግልጽ እንዲታይ ለማድረግ ጥረት አድርግ
18, 19. (ሀ) እድገትህ በሁሉም ሰው ዘንድ በግልጽ እንዲታይ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?
18 የአንድ እውነተኛ ክርስቲያን መንፈሳዊ እድገት ከቁመናው፣ ከተፈጥሮ ችሎታዎቹ ወይም በሌሎች ዘንድ ካለው ክብር ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ከማገልገልም ጋር የተያያዘ ላይሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ እውነተኛ መንፈሳዊ እድገት እንዳደረግን በግልጽ ማሳየት የምንችለው በአስተሳሰብ፣ በንግግርና በምግባር ለይሖዋ ታዛዦች በመሆን ነው። (ሮም 16:19) እርስ በርስ እንድንዋደድና ጠንካራ እምነት እንድናዳብር የተሰጠንን መመሪያ መታዘዝ ይኖርብናል። እድገታችን በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ እንዲታይ፣ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በሰጠው ምክር ላይ እናሰላስል፤ እንዲሁም ትኩረታችን ሙሉ በሙሉ በዚህ ምክር ላይ ያረፈ ይሁን።
19 በመንፈሳዊ እድገት እንዳደረግንና ክርስቲያናዊ ጉልምስና ላይ እንደደረስን በግልጽ ከሚያሳዩት ባሕርያት መካከል አንዱ የአምላክ መንፈስ ቅዱስ ፍሬ ገጽታ የሆነው ደስታ ነው። (ገላ. 5:22, 23) የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ አስቸጋሪ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜም እንኳ እንዴት ደስተኞች መሆን እንደምንችል እንዲሁም ይህን ደስታችንን ጠብቀን መኖር የምንችልበትን መንገድ ያብራራል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ሌሎች ከአነጋገራችን ስለ እኛ ምን ሊረዱ ይችላሉ?
• እድገታችን ከምግባርና ከንጽሕና ጋር በተያያዘ በግልጽ ሊታይ የሚችለው እንዴት ነው?
• ክርስቲያኖች በፍቅርና በእምነት ረገድ አርዓያ መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣቱ ጢሞቴዎስ ከዕድሜው በላይ የጎለመሰ ሰው እንደሆነ አሳይቷል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እድገትህ በሌሎች ዘንድ በግልጽ የሚታይ ነው?