የአፍሪካ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች
ወደ አፍሪካ ቋንቋዎች ከተተረጎሙት የመላው መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የመጀመሪያው የተተረጎመው በግብፅ ነበር። እርሱም የኮፕቲክ ትርጉም በመባል የሚታወቅ ሲሆን የተተረጎመበት ዘመን ከሦስተኛው እስከ አራተኛው መቶ ዘመን እንደነበረ ይታመናል። ከዚያም ሦስት መቶ ዘመናት ቆይቶ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ኢትዮጵያ ቋንቋ ተተረጎመ።
በደቡብ ኢትዮጵያና ከሰሐራ በስተደቡብ ይነገሩ የነበሩት በመቶዎች የሚቆጠሩ ጽሑፍ የሌላቸው ቋንቋዎች ግን ሚሲዮናውያን እስከመጡበት እስከ 19ኛው መቶ ዘመን ድረስ መቆየት ነበረባቸው። በ1857 ሮበርት ማፈት መጽሐፍ ቅዱስን የደቡባዊ አፍሪካ ቋንቋ በሆነው ስዋንኛ ተርጉሞ በጨረሰ ጊዜ አንድ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። ይህም ትርጉም በእጅ በሚሠራ ማተሚያ መሣሪያ በተለያዩ ክፍሎች ታትሞ ወጣ። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በአፍሪካ ውስጥ ለመታተም የመጀመሪያ የሆነው ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ከመሆኑም ሌላ ከዚያ በፊት በጽሑፍ ላይ ባልዋለ አፍሪካዊ ቋንቋ ለመዘጋጀትም የመጀመሪያው ሆኗል። ሞፋት በትርጉሙ ውስጥ መለኮታዊውን ስም የሆቫ በማለት አስገብቶአል። በ1872 የብሪቲሽና የውጭ አገሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ባሳተመው መጽሐፍ ቅዱስ የሆቫ የሚለው ስም በማቴዎስ 4:10 ላይና በማርቆስ 12:29, 30 ላይ ተመዝግበው በሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ላይ ይገኛል።
እስከ 1990 ድረስ መላው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በ119 የአፍሪካ ቋንቋዎች ከመተርጎሙም በላይ በከፊል ደግሞ በሌሎች ተጨማሪ 434 ቋንቋዎች ተተርጉሞአል።