ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ
“እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ።”—ሥራ 10:34, 35
1. አንድ ፕሮፌሰር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚሰማቸው ሲጠየቁ ምን ብለዋል? ምን ለማድረግስ ተስማሙ?
ፕሮፌሰሩ አንድ እሁድ ቀን ከሰዓት በኋላ እቤታቸው ተቀምጠዋል። እንግዳ ይመጣብኛል ብለው አላሰቡም ነበር። አንዲት ክርስቲያን እህታችን ቤታቸውን አንኳኩታ ባነጋገረቻቸው ጊዜ ግን የምትለውን አዳመጧት። ስለ አካባቢያችን መበከልና ስለ ምድር የወደፊት ዕጣ አነጋገረቻቸው። እነዚህ ለፕሮፌሰሩ የሚጥሙ ርዕሰ ጉዳዮች ነበሩ። በውይይቱ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ባስገባች ጊዜ ግን የጥርጣሬ መንፈስ ተነበበባቸው። በዚህ ምክንያት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን አስተያየት እንዳላቸው ጠየቀቻቸው።
“ብልህ የሆኑ ሰዎች የጻፉት ጥሩ መጽሐፍ ነው። ከዚህ በተረፈ ግን መጽሐፍ ቅዱስ በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው መጽሐፍ አይደለም” ሲሉ መለሱላት።
“መጽሐፍ ቅዱስን አንብበውት ያውቃሉ?” ስትል ጠየቀቻቸው።
ፕሮፌሰሩ በጥያቄው ደንገጥ ቢሉም አንብበውት የማያውቁ መሆናቸውን ለማመን ተገድደዋል።
ከዚያም ቀጥላ “ታዲያ አንብበው ስለማያውቁት መጽሐፍ እንዴት እንዲህ እርግጠኛ ሆነው ሊናገሩ ይችላሉ?” ስትል ጠየቀች።
እህታችን ትክክል ነበረች። ፕሮፌሰሩ መጽሐፍ ቅዱስን ለመመርመርና ከዚያ በኋላ አስተያየት ለመስጠት ወሰኑ።
2, 3. መጽሐፍ ቅዱስ ለብዙ ሰዎች የተከደነ መጽሐፍ የሆነባቸው ለምንድን ነው? ይህስ ምን ፈታኝ ሁኔታ ይጋርጥብናል?
2 ይህን የመሰለ አስተያየት የሚሰነዝሩ ብዙ ሰዎች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስን በግላቸው አንብበው የማያውቁ ቢሆኑም ስለ መጽሐፉ አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩ ሰዎች በርካታ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ሊኖራቸው ይችላል። አልፎ ተርፎም ሥነ ጽሑፋዊና ታሪካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ያምኑ ይሆናል። ይሁን እንጂ ለብዙዎቹ የተከደነ መጽሐፍ ነው። አንዳንዶች ‘እኔ መጽሐፍ ቅዱስን የማነብበት ጊዜ የለኝም’ ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ‘ይህን የሚያህል ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ ጥንታዊ መጽሐፍ ለግል ሕይወቴ ምን ዓይነት ፋይዳ ሊኖረው ይችላል?’ ብለው ይጠይቃሉ። እንደነዚህ ያሉት አመለካከቶች በእርግጥ ፈታኝ የሆነ ሁኔታ ይጋርጡብናል። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት[ና] . . . ለትምህርት” የሚጠቅም መሆኑን አጥብቀው ያምናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ታዲያ ሰዎች ቀለማቸው፣ ብሔራቸው ወይም ነገዳቸው ምንም ይሁን ምን መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር እንደሚገባቸው ልናሳምናቸው የምንችለው እንዴት ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ ልንመረምረው የሚገባ መጽሐፍ መሆኑን የሚጠቁሙ አንዳንድ ምክንያቶችን እንመልከት። ይህም በአገልግሎታችን የምናገኛቸውን ሰዎች ለማሳመንና ምናልባትም መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን እንዲመረምሩ ለማነሳሳት የሚያስችለን ነው። ከዚህም በላይ እነዚህን ምክንያቶች መመርመራችን መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም ስለራሱ እንደሚመሠክረው ‘የአምላክ ቃል’ ስለመሆኑ ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን ይሆናል።—ዕብራውያን 4:12
በዓለም ላይ በስፋት በመሠራጨት ረገድ አቻ የሌለው መጽሐፍ
4. መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ ካሉት መጻሕፍት ሁሉ በስርጭቱ አቻ አይገኝለትም ለማለት የሚያስችለን ምንድን ነው?
4 በመጀመሪያ ደረጃ በታሪክ ዘመናት ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በስፋት የተሰራጨና በብዛት የተተረጎመ መጽሐፍ ባለመኖሩ መጽሐፍ ቅዱስን ልንመረምረው ይገባናል። ከ500 ዓመታት በፊት በተንቀሳቃሽ የማተሚያ መሣሪያ ለመታተም የመጀመሪያ የሆነው መጽሐፍ በዮሐንስ ጉተንበርግ መሣሪያ ታተመ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ አራት ቢልዮን የሚያክሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ወይም ከፊል ቅጂዎች እንደታተሙ ይገመታል። እስከ 1996 ድረስ ሙሉው ወይም ከፊሉ መጽሐፍ ቅዱስ በ2,167 ቋንቋዎችና ቀበሌኛዎች ተተርጉሟል።a ከምድር ነዋሪዎች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት መጽሐፍ ቅዱስን ቢያንስ በከፊል በራሳቸው ቋንቋ ሊያነቡ ይችላሉ። ወደዚህ አኃዝ በሚጠጋ መጠን የተሰራጨ ሃይማኖታዊም ሆነ ሌላ መጽሐፍ የለም!
5. መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ዙሪያ ላሉ ሰዎች ሁሉ መድረስ ይገባዋል ብለን ልንጠብቅ የሚገባን ለምንድን ነው?
5 አኃዛዊ መረጃዎቹ ብቻቸውን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን አያረጋግጡም። ይሁን እንጂ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መጽሐፍ ከሆነ በምድር ዙሪያ ላሉ ሰዎች መዳረስ አለበት ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ” ይነግረናል። (ሥራ 10:34, 35) ብሔራዊ ድንበሮች ያልገደቡት፣ የዘርና የጎሳ እንቅፋቶች ያላሸነፉት መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። በእርግጥም ለሁሉ ሰው የሚሆን መጽሐፍ ነው!
ተጠብቆ በመቆየት ረገድ ድንቅ ታሪክ ያስመዘገበ መጽሐፍ
6, 7. ዛሬ የትኞቹም የመጀመሪያ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች አለመገኘታቸው የማያስገርመን ለምንድን ነው? ይህስ ምን ጥያቄ ያስነሣል?
6 መጽሐፍ ቅዱስ ልንመረምረው የሚገባ መጽሐፍ ነው የምንልበት ሌላም ምክንያት አለ። ተፈጥሮአዊና ሰብዓዊ እንቅፋቶችን በድል አድራጊነት ተወጥቷል። የገጠሙትን እጅግ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሸንፎ መትረፉ ከማንኛውም የጥንት ጽሑፍ የተለየ ግምት እንዲሰጠው የሚያደርግ ነው።
7 የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ጽሑፎቻቸውን ያሰፈሩት በፓፒረስ (ፓፒረስ ተብሎ ከሚጠራ የግብጻውያን ተክል የሚሠራ) እና በብራናዎች (ከእንስሳት ቆዳ የሚሠሩ) ላይ ነበር።b (ኢዮብ 8:11) ይሁን እንጂ እነዚህ የጽሕፈት መሣሪያዎች ተፈጥሮአዊ ጠላቶች አሏቸው። ምሁሩ ኦስካር ፓሬት እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል:- “እነዚህ የጽሕፈት መሣሪያዎች በእርጥበት፣ በሻጋታና በብል ሊጠቁ የሚችሉ ናቸው። ወረቀትም ሆነ ቆዳ ለአየርና ለእርጥበት ሲጋለጡ በቀላሉ እንደሚበላሹ ከዕለታዊ ተሞክሮአችን እናውቃለን።” በዚህ ምክንያት የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች በአሁኑ ጊዜ የማይገኙ መሆናቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ከብዙ ዘመናት በፊት ተቀዳደው ጠፍተው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች በተፈጥሮ ጠላቶች ተሸንፈው የጠፉ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ ሊኖር የቻለው እንዴት ነው?
8. ባለፉት መቶ ዘመናት የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች ተጠብቀው የቆዩት እንዴት ነው?
8 የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ከተጻፉ በኋላ ወዲያው የእጅ ጽሑፍ ቅጂዎች መገልበጥ ጀመሩ። እንዲያውም በጥንቷ እስራኤል ሕጉንና ሌሎች የቅዱሳን ጽሑፎችን ክፍሎች መገልበጥ ራሱን የቻለ ሙያ ሆኖ ነበር። ለምሳሌ ያህል ካህኑ ዕዝራ “የሙሴ ሕግ ፈጣን ጸሐፊ ነበር” ተብሏል። (ዕዝራ 7:6, 11፤ ከመዝሙር 45:1 ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ እነዚህ ገልባጮች ያዘጋጁዋቸውም ቅጂዎች ዘላለማዊ ስላልነበሩ በሌሎች የእጅ ግልባጭ ቅጂዎች መተካት ነበረባቸው። ይህ ከአንዱ ቅጂ ወደሌላው የመግለበጥ ሂደት ለበርካታ መቶ ዘመናት ቀጥሏል። የሰው ልጆች ፍጹማን ስላልሆኑ የገልባጮቹ ስህተት የመጽሐፍ ቅዱስን ይዘት ለውጦት ይሆን? ማስረጃው በግልጽ እንደሚያሳየው መልሱ አልለወጠውም የሚል ነው!
9. የማሶሪቶች ምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ገልባጮች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዳደረጉና ትክክለኛ ሐሳብ እንደመዘገቡ የሚያሳየው እንዴት ነው?
9 ገልባጮቹ በሞያቸው የተካኑ ከመሆናቸውም በላይ ለሚገለብጧቸው ቃላት ከፍተኛ አክብሮት ነበራቸው። “ገልባጭ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል መቁጠርንና መመዝገብን ያመለክታል። ገልባጮቹ ምን ያህል በትክክል ይገለብጡ እንደነበር በምሳሌ ለማስረዳት ማሶሪቶች ተብለው ይጠሩ የነበሩትና በስድስተኛውና በአሥረኛው መቶ ዘመን እዘአ መካከል ይኖሩ የነበሩት ገልባጮች ምን ያደርጉ እንደነበር እንመልከት። ቶማስ ሃርትዌል ሆርን የተባሉት ምሁር ማሶሪቶችን በሚመለከት እንዲህ ብለዋል:- “እያንዳንዱ [የዕብራይስጥ] ሆሄ በመላው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ምን ያህል ጊዜ እንደሚገኝ” ይቆጥሩ ነበር። ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስበው! እነዚህ ራሳቸውን ለሙያቸው መሥዋዕት ያደረጉ ገልባጮች አንዷን ፊደል እንኳ እንዳያልፉ ሲሉ የገለበጧቸውን ቃሎች ብቻ ሳይሆን ፊደሎች ጭምር ይቆጥሩ ነበር። የሚገርመው አንድ ተመራማሪ እንዳሉት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን 815,140 ቃላት አንድ በአንድ ይከታተሉ ነበር! ይህን የመሰለው ትጋት የተሞላበት ጥረታቸው ቅጂዎቹ ከፍተኛ የሆነ ጥራት እንዲኖራቸው አድርጓል።
10. ዛሬ ላሉት ትርጉሞች መነሻ ሆነው ያገለገሉት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ጽሑፎች የመጀመሪያዎቹን ጸሐፊዎች ቃላት በትክክል እንደያዙ የሚያረጋግጥ ምን አሳማኝ ማስረጃ አለ?
10 እንዲያውም ለዛሬዎቹ ትርጉሞች መነሻ ሆነው ያገለገሉት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ጽሑፎች የመጀመሪያዎቹን ጸሐፊዎች ቃላት በታማኝነት የያዙ እንደሆኑ የሚያረጋግጡ አሳማኝ ማስረጃዎች አሉ። በአሁኑ ጊዜ የሚገኙትን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በሙሉ ወይም በከፊል የያዙ ወደ 6,000 ያህል የሚገመቱ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችና 5,000 የሚያክሉ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች እስከዛሬ ድረስ ተጠብቀው መትረፋቸው ለዚህ ማስረጃ ይሆነናል። ምሁራኑ ዛሬ የሚገኙትን ጥንታዊ ጽሑፎች በጥንቃቄ በማነጻጸር ባደረጉት ግምገማ ገልባጮቹ የሠሯቸውን ስህተቶች ለመለየትና የመጀመሪያው ንባብ የትኛው እንደነበር ለማስተዋል ችለዋል። ምሁሩ ዊልያም ኤች ግሪን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በተመለከተ ሲናገሩ “የዚህን ያህል ትክክል የሆኑ ጥንታዊ ጽሑፎች የሉም ቢባል ማጋነን አይሆንም” ለማለት ችለዋል። የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችም የዚያኑ ያክል አስተማማኝ ናቸው።
11. በ1 ጴጥሮስ 1:24, 25 መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቆ ሊቆይ የቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?
11 የመጀመሪያዎቹን ጽሑፎች የተኩትና ውድ መልእክቶችን የያዙት የእጅ ግልባጭ ቅጂዎች ባይኖሩ ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ በቀላሉ በጠፋ ነበር! የተረፈበት ምክንያቱ አንድ ነው፤ ይኸውም ቃሉን የጠበቀውና ተንከባክቦ ያቆየው ይሖዋ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ በ1 ጴጥሮስ 1:24, 25 ላይ እንደሚናገረው “ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል።”
ሕያዋን በሆኑ የሰው ልጅ ቋንቋዎች ተተረጎመ
12. መጽሐፍ ቅዱስ ባለፉት መቶ ዘመናት ከአንዱ ቅጂ ወደሌላው ሲገለባበጥ ከመቆየቱም ሌላ ምን ተጨማሪ እንቅፋቶች ገጥመውት ነበር?
12 መጽሐፍ ቅዱስ ለበርካታ መቶ ዘመናት ሲገለበጥ ቆይቶ እስከ ዛሬ ተጠብቆ መቆየቱ ራሱ ቀላል ነገር ባይሆንም ሌላም ከባድ እንቅፋት ለመወጣት ተገዷል። በዘመኑ ወደሚነገሩ ሌሎች ቋንቋዎች መተርጎም ነበረበት። መጽሐፍ ቅዱስ የሁሉንም ሕዝቦች ልብ እንዲነካ ከተፈለገ በገዛ ቋንቋቸው ሊያናግራቸው ይገባ ነበር። ይሁን እንጂ ከ1,100 ምዕራፎችና ከ31,000 ቁጥሮች በላይ ያሉትን መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም ቀላል ሥራ አይደለም። ቢሆንም ባለፉት መቶ ዘመናት ለዚህ ሥራ ከፍተኛ ፍቅር ያደረባቸው ተርጓሚዎች የማይታለፉ የሚመስሉ እንቅፋቶች ቢጋረጡባቸውም ፈተናውን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ ሆነው ተገኝተዋል።
13, 14. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚው ሮበርት ሞፋት በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ አፍሪካ ውስጥ ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ገጥሞት ነበር? (ለ) የጽዋና ቋንቋ ተናጋሪዎች በቋንቋቸው የተዘጋጀውን የሉቃስ ወንጌል ሲያገኙ ምን ምላሽ ሰጡ?
13 ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ በአፍሪካ ቋንቋዎች የተተረጎመበትን ሁኔታ እንመልከት። በ1800 በመላዋ አፍሪካ ፊደል የነበራቸው ቋንቋዎች ከአንድ ደርዘን አይበልጡም ነበር። ሌሎቹ በመቶ የሚቆጠሩ ቋንቋዎች በአፍ የሚነገሩ እንጂ ጽሑፍ ያላቸው አልነበሩም። የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የነበረው ሮበርት ሞፋት የገጠመው እንቅፋት ይህ ነበር። ሞፋት በ1821 በ25 ዓመት ዕድሜው በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩት የጽዋና ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል የሚስዮን ጣቢያ አቋቋመ። ምንም ዓይነት ጽሑፍ ያልነበረውን ይህን ቋንቋ ለመማር ሲል ከሕዝቡ ጋር ተደባልቆ መኖር ጀመረ። ሞፋት ተስፋ ሳይቆርጥ ጥረቱን በመቀጠሉ ያለ ቋንቋ መመሪያ መጽሐፍና መዝገበ ቃላት እርዳታ ቋንቋውን ከመቻሉም በላይ የአጻጻፍ ስልት ፈጥሮ አንዳንድ የጽዋና ተወላጆች ይህን ፊደል እንዲማሩ አድርጓል። ሞፋት ከጽዋና ተወላጆች ጋር ለስምንት ዓመታት ከቆየ በኋላ በ1829 የሉቃስን ወንጌል ተርጉሞ ጨረሰ። በኋላም የሚከተለውን ተናግሯል:- “የቅዱስ ሉቃስን ወንጌል ቅጂ ለማግኘት በመቶ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተጉዘው የመጡ ሰዎች አውቃለሁ። . . . ‘ተዉ መጽሐፋችሁን በእንባችሁ አርሳችሁ ታበላሻላችሁ’ ብዬ እስክከለክላቸው ድረስ የደስታና የአመስጋኝነት ሲቃ እየተናነቃቸው መጽሐፋቸውን አቅፈው ያለቀሱ ብዙ ሰዎች አይቻለሁ።” ሞፋት በርከት ያሉ ሰዎች የሉቃስን ወንጌል ይዘው ሲያነቡ ተመልክቶ በእጃቸው ያለው ምን እንደሆነ ለማወቅ ስለጠየቀ አንድ አፍሪካዊ ሰውም ተናግሯል። “የአምላክ ቃል ነው” አሉት። ሰውዬው “ይናገራል?” ሲል ጠየቀ “አዎን፣ ለልብ ይናገራል” ሲሉ መለሱለት።
14 ሞፋትን የመሰሉ ለተሰማሩበት ዓላማ ራሳቸውን መሥዋዕት ያደረጉ ተርጓሚዎች ለበርካታ አፍሪካውያን በጽሑፍ ሐሳብ ለሐሳብ የመለዋወጥ አጋጣሚ ከፍተዋል። ይሁን እንጂ ተርጓሚዎቹ ከዚህ ይበልጥ በጣም ውድ የሆነ ነገር ለአፍሪካውያኑ ሰጥተዋል። እርሱም በገዛ ቋንቋቸው የተተረጎመ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ከዚህም በላይ ሞፋት ለጽዋናዎች መለኮታዊውን ስም አስተዋውቋል። በመላው ትርጉሙ ውስጥ በዚህ ስም ተጠቅሟል።c በዚህም ምክንያት ጽዋናዎች መጽሐፍ ቅዱስን “የይሖዋ አፍ” ሲሉ ጠርተውታል።—መዝሙር 83:18
15. ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው ነው የምንለው ለምንድን ነው?
15 በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የነበሩ ሌሎች ተርጓሚዎችም ተመሳሳይ እንቅፋቶች ገጥመዋቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ሲሉ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠዋል። እስቲ አስበው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በጥንቶቹ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቋንቋዎች ብቻ ተወስኖ ቢቀር ኖሮ እነዚህ ቋንቋዎች ከጊዜ በኋላ በብዙሐኑ ዘንድ የተረሱና በብዙዎቹ የምድር ክፍሎች የማይታወቁ መሆናቸው ስለማይቀር ከረጅም ዘመን በፊት “የሞተ” መጽሐፍ ይሆን ነበር። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት በተለየ መልኩ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች በቋንቋቸው “ሊናገር” የሚችል በመሆኑ ሕያው መጽሐፍ ነው። ከዚህ የተነሣ መልእክቱ ‘በሚያምኑት ላይ የሚሠራ’ ሆኗል። (1 ተሰሎንቄ 2:13) ዘ ጀሩሳሌም ባይብል እነዚህን ቃላት “በምታምኑት በእናንተ ዘንድ አሁንም ሕያው ኃይል ነው” በማለት አስቀምጧቸዋል።
እምነት የሚጣልበት
16, 17. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት ነው ለመባል እንዲበቃ ምን ማስረጃ ሊኖር ይገባል? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የነበረውን የሙሴን ሐቀኝነት የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ስጥ።
16 አንዳንዶች ‘መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ እምነት ሊጣልበት የሚችል መጽሐፍ ነውን?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ‘የሚጠቅሳቸው ሰዎች በእርግጥ በሕይወት የኖሩ፣ የሚጠራቸው ቦታዎች እውነትም የነበሩና የሚተርካቸው ክንውኖች በእርግጥ የተፈጸሙ ናቸውን?’ እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ ነው እንዲባል ጠንቃቃና ሐቀኛ በሆኑ ጸሐፊዎች የተጻፈ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሊኖር ይገባል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ተገቢ ወደሚሆንበት ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ያመጣናል:- መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛና እምነት የሚጣልበት መሆኑን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ አለ።
17 ሐቀኛ የሆኑ ታሪክ ጸሐፊዎች መዝግበው የሚያቆዩት ድሎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ሽንፈቶቻቸውን፣ ጠንካራ ጎኖቻቸውን ብቻ ሳይሆን ድክመቶቻቸውን ጭምር ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እንዲህ የመሰለ የሐቀኝነት ባሕርይ አሳይተዋል። ለምሳሌ ያህል የሙሴን ግልጽነት ተመልከት። በግልጽነት ከዘገባቸው ነገሮች መካከል የእስራኤል መሪ ለመሆን እንደማይበቃ ምክንያት አድርጎ ያቀረበው አንደበተ ርቱዕ አለመሆኑ (ዘጸአት 4:10)፣ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ያስከለከው ከባድ ጥፋት (ዘኁልቁ 20:9-12፤ 27:12-14)፣ የወርቅ ጥጃ ምስል በመሥራት ከዓመፀኞቹ እስራኤላውያን ጋር የተባበረው የወንድሙ የአሮን ጥፋት (ዘጸአት 32:1-6)፣ የእህቱ የሚርያም ዓመፅና የደረሰባት አሳፋሪ ቅጣት (ዘኁልቁ 12:1-3, 10)፣ የወንድሙ ልጆች ዮናዳብና አብዩድ ያሳዩት የንቀት ዝንባሌ (ዘሌዋውያን 10:1, 2) እንዲሁም የአምላክ ሕዝቦች በተደጋጋሚ ጊዜያት ማማረራቸውና ማጉረምረማቸው ይገኙበታል። (ዘጸአት 14:11, 12፤ ዘኁልቁ 14:1-10) እንዲህ ያለው ግልጽነትና ሐቀኛነት ያልተለየው ዘገባ ጸሐፊዎቹ ስለ እውነት ይጨነቁና ይጠበቡ የነበሩ ሰዎች መሆናቸውን አያመለክትምን? የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የሚወዷቸውን ሰዎች፣ የገዛ ራሳቸውን ሕዝቦችና ራሳቸውን ሳይቀር የሚያስነቅፉ ክንውኖች ለመጻፍ ፈቃደኞች መሆናቸው በጽሑፎቻቸው እንድንታመን በቂ ምክንያት አይሆነንምን?
18. የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በጽሑፍ ያሰፈሯቸው ነገሮች እምነት የሚጣልባቸው መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው?
18 በተጨማሪም ጸሐፊዎቹ ያሰፈሩት ነገር እርስ በርሱ የሚስማማ መሆኑ ጽሑፎቻቸው አስተማማኝ እንደሆነ ያረጋግጣል። ከ1,600 በሚበልጡ ዓመታት ርዝመት ውስጥ የጻፉ 40 የሚያክሉ ጸሐፊዎች በጥቃቅን ዝርዝር ጉዳዮች ሳይቀር አንዳቸው ከሌላው ጋር የሚደጋገፍ ነገር መጻፋቸው እጅግ የሚያስገርም ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ስምምነት እርስ በርሳቸው ተመካክረው ያደረጉት እስኪመስል ድረስ ሆን ተብሎ በጥንቃቄ የተቀናበረ አይደለም። በአንጻሩ ግን በተለያዩት ዝርዝሮች መካከል ያለው ስምምነት ሆነ ተብሎ በዕቅድ የተደረገ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በአብዛኛው ስምምነቱ እንዲሁ የተከሰተ እንደነበር ግልጽ ነው።
19. ኢየሱስ ስለመያዙ የሚገልጹት የወንጌል ዘገባዎች ታስቦበት የተቀነባበረ እንዳልሆነ በግልጽ በሚታይ መንገድ ስምምነታቸው የተንጸባረቀው እንዴት ነው?
19 ይህን ጉዳይ በምሳሌ ለማስረዳት ያህል ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት የተከናወነ አንድ ሁኔታ ተመልከት። አራቱም የወንጌል ጸሐፊዎች ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ሰይፉን መዝዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ ጆሮ መቁረጡን ጽፈዋል። ኢየሱስ ‘ጆሮውን ዳስሶ እንደፈወሰለት’ የሚነግረን ሉቃስ ብቻ ነው። (ሉቃስ 22:51) ይሁን እንጂ እኛስ ብንሆን ‘የተወደደው ሐኪም’ ተብሎ ከተጠራው ጸሐፊ የምንጠብቀው ከዚህ የተለየ ይሆናልን? (ቆላስይስ 4:14) በዚያ ከነበሩት ደቀ መዛሙርት በሙሉ ሰይፉን የተጠቀመው ጴጥሮስ መሆኑን የሚገልጽን የዮሐንስ ዘገባ ነው፤ ከጴጥሮስ የችኩልነት ባሕርይ አንጻር ይህን ማለቱ ምንም አያስገርምም። (ዮሐንስ 18:10፤ ከማቴዎስ 16:22, 23 እንዲሁም ከዮሐንስ 21:7, 8 ጋር አወዳድር።) ዮሐንስ “የባሪያውም ስም ማልኮስ ነበር” ሲል እምብዛም ጠቀሜታ ያለው የማይመስል ተጨማሪ ነገር ዘግቧል። ዮሐንስ ብቻ የሰውዬውን ስም የጻፈው ለምንድን ነው? በዮሐንስ ዘገባ ውስጥ ብቻ እንደ ዋዛ የተጠቀሰ አንድ አነስተኛ ሐቅ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሆነናል። ዮሐንስ “በሊቀ ካህናቱ ዘንድ የታወቀ” ሰው ነበር። በተጨማሪም የሊቀ ካህናቱ ቤተሰብና አገልጋዮች የሚያውቁት ሰው ሲሆን እርሱም ያውቃቸው ነበር።d (ዮሐንስ 18:10, 15, 16) ስለዚህ ዮሐንስ ጉዳት የደረሰበትን ሰው በስም መጥቀሱና ከሰውዬው ጋር የማይተዋወቁት ሌሎቹ ጸሐፊዎች በስም አለመጥቀሳቸው እንግዳ ነገር አይደለም። በእነዚህ ሁሉ ዝርዝር ጉዳዮች መካከል ያለው ተመሳሳይነት አስገራሚ ነው፤ ይሁንና እርስ በርስ በመመካከር የተደረገ እንዳልነበር ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የዚህ ዓይነት በርካታ ምሳሌዎችን ማግኘት ይቻላል።
20. ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ነገር ማወቅ ያስፈልጋቸዋል?
20 ታዲያ እምነታችንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መጣል እንችላለን? አዎን፣ በእርግጥ እንችላለን! የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሐቀኛነትና መጽሐፉ የያዛቸው ዘገባዎች ያላቸው ስምምነት እውነተኛ መጽሐፍ መሆኑን በግልጽ ይመሰክራል። ቅን ልብ ያላቸው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ‘የእውነት አምላክ የሆነው የይሖዋ’ ቃል በመሆኑ እምነት ሊጣልበት የሚችል መጽሐፍ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። (መዝሙር 31:5) በሚቀጥለው ርዕስ እንደምናየው መጽሐፍ ቅዱስ ለሁሉም ሰዎች የሚሆን መጽሐፍ ነው የምንልባቸው ተጨማሪ ምክንያቶች አሉ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት ባወጡት አኃዝ ላይ የተመሠረተ።
b ጳውሎስ በሮም ለሁለተኛ ጊዜ ታሥሮ በነበረበት ወቅት ጢሞቴዎስ “መጻሕፍቱን ይልቁንም በብራና የተጻፉትን” እንዲያመጣለት ጠይቆት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 4:13) ጳውሎስ በእሥር ቤት ሳለ ማጥናት ይችል ዘንድ እንዲያመጣለት የጠየቀው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ክፍል ሳይሆን አይቀርም። “ይልቁንም በብራና የተጻፉትን” የሚለው መግለጫ በፓፒረስም በብራናም የተጻፉ ጥቅልሎች እንደነበሩ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።
c ሞፋት በ1838 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ትርጉም አጠናቀቀ። በ1857 ደግሞ ካረዳቱ ጋር ሆኖ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ተርጉሞ ጨርሷል።
d ዮሐንስ ከሊቀ ካህናቱና ከቤተሰቡ ጋር ያለው ትውውቅ በዘገባው ውስጥ ወደ ኋላም ተገልጾ ይገኛል። ሌላው የሊቀ ካህናቱ ባርያ ጴጥሮስን የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነው በማለት በከሰሰው ጊዜ ዮሐንስ ይህ ባርያ “ጴጥሮስ ጆሮውን የቆረጠው ዘመድ” መሆኑን ገልጿል።—ዮሐንስ 18:26
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ ከማንኛውም መጽሐፍ ይበልጥ በቀላሉ ሊገኝ የሚችል መሆን አለበት ብለን መጠበቅ የሚገባን ለምንድን ነው?
◻ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ሳይዛባ እስከ ዛሬ ድረስ በትክክል ተጠብቆ እንደቆየ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
◻ መጽሐፍ ቅዱስን የተረጎሙ ሰዎች ምን እንቅፋቶች ገጥመዋቸው ነበር?
◻ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች እምነት የሚጣልባቸው መሆናቸውን የሚያሳየው ምንድን ነው?