በመንፈስ መሪነት የሚከናወን የሚሲዮናዊ ሥራ አፈጻጸም
“እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ።”—1 ቆሮንቶስ 11:1
1. ኢየሱስ ተከታዮቹ ሊኮርጁት የሚገባ የላቀ ምሳሌ የሰጠባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? (ፊልጵስዩስ 2:5-9)
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በጣም ታላቅ የሆነ ምሳሌነት ትቶላቸዋል! ሰማያዊ ክብሩን ትቶ በኃጢአተኛ ሰዎች መካከል ለመኖር ወደ ምድር የመጣው በደስታ ነበር። ለሰው ልጆች መዳን፣ በይበልጥ ደግሞ ለሰማያዊ አባቱ ስም መቀደስ ሲል ከፍተኛ ሥቃይ ለመቀበል ፈቃደኛ ነበር። (ዮሐንስ 3:16፤ 17:4) ኢየሱስ የሞት ፍርድ ሊቀበል ቀርቦ ሳለ “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ” በማለት በድፍረት ተናግሯል።—ዮሐንስ 18:37
2. ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እሱ የጀመረውን ሥራ እንዲቀጥሉ ሊያዛቸው የቻለው ለምን ነበር?
2 ኢየሱስ ከመሞቱ አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱ ለመንግሥቱ እውነት ምስክርነት የመስጠቱን ሥራ ለመቀጠል እንዲችሉ በጣም ጥሩ ማሠልጠኛ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 10:5-23፤ ሉቃስ 10:1-16) በመሆኑም ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለውን ትዕዛዝ ሊሰጣቸው ችሎአል።—ማቴዎስ 28:19, 20
3. ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ የተስፋፋው እንዴት ነበር? ሆኖም በይበልጥ ያተኮረው በየትኞቹ አካባቢዎች ነበር?
3 ከዚያ በኋላ በነበሩት ሦስት ተኩል ዓመታት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን ትዕዛዝ ፈጽመዋል። ሆኖም ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራቸው በአይሁዳውያን፣ ወደ ይሁዲነት በተለወጡና በተገረዙ ሳምራውያን መካከል ብቻ ተወስኖ ነበር። ከዚያም በ36 እዘአ የምሥራቹ ቆርኔሌዎስ ለተባለ ያልተገረዘ ሰውና ለቤተሰቡ እንዲሰበክ አምላክ አዘዘ። በመጪው አሥር ዓመት ሌሎች አሕዛብም ወደ ጉባኤው መጡ። ይሁን እንጂ አብዛኛው ሥራ በምሥራቃዊው የሜዲቴራኒያን አካባቢ ብቻ የተወሰነ ይመስል ነበር።—ሥራ 10:24, 44-48፤ 11:19-21
4. ከ47-48 እዘአ አካባቢ ምን ታላቅ ነገር ተፈጸመ?
4 ክርስቲያኖች ራቅ ባሉ አካባቢዎችም ከአይሁድና ከአሕዛብ መካከል ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው ወይም የሚቀሰቅሳቸው አንድ ነገር ያስፈልግ ነበር። ስለዚህ ከ47-48 እዘአ ገደማ ላይ የሶርያ አንጾኪያ ጉባኤ ሽማግሌዎች “በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ” የሚል መለኮታዊ መልእክት ተቀበሉ። (ሥራ 13:2) በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ይጠራ የነበረው ሳውል በተባለው የቀድሞ ስሙ እንደነበረ አስተውሉ። በርናባስ ከጳውሎስ በፊት መጠቀሱንም አስተውሉ። ይህ የሆነው በዚያን ጊዜ በርናባስ ከጳውሎስ ብልጫ እንዳለው ተደርጎ ይታይ ስለነበረ ሳይሆን አይቀርም።
5. የጳውሎስና የበርናባስ ሚሲዮናዊ ጉዞ ታሪክ በዛሬው ጊዜ ላሉት ክርስቲያኖች ትልቅ ጥቅም ያለው ለምንድን ነው?
5 ስለ ጳውሎስና በርናባስ የሚስዮናዊነት ጉዞ የሚገልጸው ዝርዝር ታሪክ ለይሖዋ ምሥክሮች፣ በተለይም አምላክን ለማገልገል ከትውልድ ቦታቸው ርቀው ወደ ውጭ አገር ለሄዱ ሚስዮናውያንና አቅኚዎች ታላቅ ማበረታቻ ይሰጣቸዋል። በተጨማሪም ሥራ ምዕራፍ 13 እና 14ን መከለስ ሌሎች ክርስቲያኖችም ጳውሎስንና በርናባስን እንዲመስሉና ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ያላቸውን ድርሻ ከፍ እንዲያደርጉ እንደሚገፋፋቸው ጥርጥር የለውም።
የቆጵሮስ ደሴት
6. ሚስዮናውያኑ በቆጵሮስ ምን ጥሩ ምሳሌ አሳይተዋል?
6 ሚስዮናውያኑ ያላንዳች መዘግየት የሶርያ ወደብ ከነበረችው ከሴሌውቅያ ወደ ቆጵሮስ ደሴት በመርከብ ሄዱ። በሳላሚስ ካረፉ በኋላ ወዲያው “በአይሁድ ምኩራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ።” የክርስቶስን ምሳሌነት በመከተላቸው በዚያች ከተማ ተደላድለው ከተቀመጡ በኋላ የደሴቷ ነዋሪዎች ወደ እነርሱ እንዲመጡ በመጠባበቅ አልረኩም። በዚህ ፈንታ “ደሴቲቱንም ሁሉ . . . ዞረው” ሰበኩ። ቆጵሮስ ትልቅ ደሴት ስለነበረችና እነርሱም በቆጵሮስ ዙሪያ ያደረጉት ጉዞ በሚበዛው የደሴቷ ክፍል ብዙ የእግር መንገድ አስኪዷቸው ሊሆን ስለሚችል ብዙ የእግር ጉዞ እንዲያደርጉና በተለያዩ ቦታዎች እንዲያርፉ ጠይቆባቸው እንደነበረ አያጠራጥርም።—ሥራ 13:5, 6
7. (ሀ) በጳፉ ምን ከፍተኛ ሁኔታ ተፈጸመ? (ለ) ይህ ታሪክ ምን አመለካከት እንዲኖረን ያበረታታናል?
7 ሁለቱ ሰዎች በዚያች ደሴት ያደረጉትን ቆይታ ሊጨርሱ ሲሉ በጳፉ ከተማ ግሩም ተሞክሮ በማግኘት ተባርከዋል።ሰርግዮስ ጳውሎስ የሚባል የከተማዋ ገዢ መልእክታቸውን ሰምቶ “አማኝ ሆነ።” (ሥራ 13:7, 12) ጳውሎስ ከዚያ በኋላ በጻፈው መልእክቱ “ወንድሞች ሆይ፣ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፣ ኃያላን የሆኑ ብዙዎች፣ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም” በማለት ጽፎአል። (1 ቆሮንቶስ 1:26) ሰርግዮስ ጳውሎስ ምሥራቹን ከተቀበሉት ኃያላን አንዱ ነበር። ይህ ተሞክሮ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ በተለይም ሚሲዮናውያን በ1 ጢሞቴዎስ 2:1-4 ላይ በተመከርነው መሠረት ለመንግሥት ባለሥልጣኖች ስለመመስከር ይሆናል የሚል ዝንባሌ እንዲኖራቸው የሚያበረታታ ነው። ባለ ሥልጣኖች ለአምላክ አገልጋዮች ትልቅ እርዳታ የሰጡባቸው ጊዜያት አሉ።—ነህምያ 2:4-8
8. (ሀ) ከዚህ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ ሚስዮናውያን መካከል ምን የተለወጠ ዝምድና ይታያል? (ለ) በርናባስ ጥሩ ምሳሌ የሆነው በምን መንገድ ነው?
8 በይሖዋ መንፈስ መሪነት ሰርግዮስ ጳውሎስን ወደ ክርስትና በመለወጥ ረገድ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተው ጳውሎስ ነበር። (ሥራ 13:8-12) በተጨማሪም ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ጳውሎስ የመሪነቱን ቦታ የያዘ ይመስላል። (ሥራ 13:7ን ከሥራ 13:15, 16, 43 ጋር አወዳድሩ) ይህም ጳውሎስ ወደ ክርስትና በገባበት ጊዜ ከተቀበለው መለኮታዊ ተልእኮ ጋር የሚስማማ ነበር። (ሥራ 9:15) ምናልባት ይህ ሁኔታ የበርናባስን ትሕትና ፈትኖት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በርናባስ ይህን ለውጥ እንደ ውርደት በመመልከት ፈንታ “የመጽናናት ልጅ” የሚል ትርጉም ካለው ስሙ ጋር ተስማምቶ በመኖር ጳውሎስን በሚስዮናዊ ጉዞው ሁሉና በኋላም አንዳንድ አይሁድ ክርስቲያኖች ባልተገረዙ አሕዛብ ዘንድ ያደረጉትን አገልግሎት በነቀፉ ጊዜ ጳውሎስን በታማኝነት ሳይደግፈው አልቀረም። (ሥራ 15:1, 2) ይህም በሚስዮናውያን ቤትና በቤቴል ቤቶች የሚሠሩትን ጨምሮ ለሁላችንም የሚጠቅም በጣም ጥሩ ምሳሌ ነው። ምንጊዜም ቲኦክራቲካዊ ማስተካከያዎች ሲደረጉ በፈቃደኝነት መቀበልና በመካከላችን በአመራር ቦታ ላይ ለተሾሙት ሙሉ ድጋፋችንን መስጠት አለብን።—ዕብራውያን 13:17
የትንሹ እስያ አምባ ምድር
9. ጳውሎስና በርናባስ ወደ ጵስዲያ አንጾኪያ ለመሄድ ፈቃደኛ ከመሆናቸው ምን ትምህርት እናገኛለን?
9 ጳውሎስና በርናባስ በመርከብ ከቆጵሮስ ተነስተው ወደ ሰሜናዊው የእስያ አህጉር ተጓዙ። ሚስዮናውያኑ ባልታወቀ ምክንያት በባሕር ዳርቻው ሳይቆዩ የጵስድያ ወደምትሆን አንጾኪያ 180 ኪሎ ሜትር የሚያህል ረዥምና አደገኛ ጉዞ አደረጉ። የጵስድያ አንጾኪያ ደግሞ የምትገኘው በትንሹ እስያ ማዕከላዊ አምባ ምድር ነበር። እዚህች ከተማ ለመድረስ በከፍተኛ ተራራማ መንገድ አልፎ 1,100 ሜትር ከባሕር ወለል በላይ ወደ ሆነ ሜዳ መውረድ ያስፈልግ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ጄ. ኤስ. ሀውሰን እንደሚከተለው ይላሉ፦ “አምባ ምድሩን በስተ ደቡብ ከሚገኘው የባሕር ዳርቻ ላይ ካለው ሜዳ በሚለየው ተራራ ላይ የነበሩ ሕዝቦች የነበራቸው ሕገ ወጥና የውንብድና ልማድ በጥንት ታሪኮች በሙሉ የታወቀ ነበር።” በተጨማሪም ሚስዮናውያኑ ከተፈጥሮ ኃይሎች አደጋ ያጋጥማቸው ነበር። ሀውሰን በመጨመር “በግዙፍ ኮረብታዎች ሥር የሚፈተለኩ ወይም በጠባብ ገደሎች ላይ የሚንዶለዶሉ ወንዞች ካሉበት ከጵስድያ ተራራማ መሬት የበለጠ በጎርፍ የሚታወቅ ሌላ አውራጃ በትንሹ እስያ ውስጥ የለም” ይላሉ። እነዚህ ዝርዝር መግለጫዎች ሚስዮናውያኑ የምሥራቹን ለማዳረስ ሲሉ በፈቃደኝነት ቆርጠው የተነሱበትን የጉዞ ዓይነት በዓይነ ሕሊናችን እንድናይ ይረዱናል። (2 ቆሮንቶስ 11:26) በአሁኑ ጊዜም በተመሳሳይ ብዙ የይሖዋ አገልጋዮች ሰዎች ወዳሉበት ደርሰው የምሥራቹን ለማካፈል ሲሉ ሁሉንም ዓይነት መሰናክሎች በቆራጥነት ይጋፈጣሉ።
10, 11. (ሀ) ጳውሎስ ከአድማጮቹ ጋር የሚስማማበትን የውይይት መሥመር የተከተለው እንዴት ነበር? (ለ) ብዙ አይሁድ መሲሑ ሥቃይ መቀበሉን ሲሰሙ ሳይገረሙ የማይቀሩት ለምንድን ነው? (ሐ) ኢየሱስ ለአድማጮቹ ያቀረበው ምን ዓይነት መዳን ነበር?
10 በጵስዲያ አንጾኪያ የአይሁድ ምኩራብ ስለነበረ ሚስዮናውያኑ ከአምላክ ቃል ጋር ይበልጥ ትውውቅ ያላቸው ሰዎች ምሥራቹን የመቀበል አጋጣሚ እንዲያገኙ ብለው በመጀመሪያ የሄዱት ወደ ምኩራቡ ነበር። እዚያም ጳውሎስ እንዲናገር ሲጋበዝ ቆመና በጣም ግሩም የሆነ የሕዝብ ንግግር አቀረበ። ጳውሎስ በንግግሩ ሁሉ አድማጮቹ ከነበሩት አይሁድና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ጋር በሚስማሙበት ነጥብ ላይ አተኩሮ ነበር። (ሥራ 13:13-16, 26) ጳውሎስ ከንግግሩ መግቢያ በኋላ ይሖዋ አባቶቻቸውን እንደመረጠና ከግብፅ ነፃ እንዳወጣቸው፣ እንዲሁም በተስፋይቱ ምድር የነበሩትን ነዋሪዎች እንዲያሸንፉ እንዴት እንደረዳቸው ለአድማጮቹ ለማስታወስ ገናናውን የአይሁድ ታሪክ ተረከላቸው። ከዚያም ጳውሎስ ይሖዋ ለዳዊት ያደረጋቸውን ነገሮችና የገባለትን ቃል ኪዳን ጎላ አድርጎ ገለጸ። አይሁድ በመጀመሪያው መቶ ዘመን አዳኝና የዘላለም መሪ የሚሆን የዳዊት ዘር አምላክ እንዲያስነሳላቸው ይጠብቁ ስለነበረ ጳውሎስ በንግግሩ ያነሳው ጉዳይ በጣም የሚያሳስባቸው ጉዳይ ነበር። ጳውሎስ እዚህ ደረጃ ላይ እንደደረሰ በድፍረት “ከዚህም ሰው [ከዳዊት] ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእሥራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ” በማለት አስታወቀ።—ሥራ 13:17-23
11 ይሁን እንጂ ብዙ አይሁድ ይጠብቁት የነበረው አዳኝ ከሮማ ግዛት ነፃ የሚያወጣቸውና የአይሁድን ሕዝብ ከሌሎች ሁሉ በላይ የሚያደርግ ወታደራዊ ጀግና ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ መሲሑ በራሳቸው የሃይማኖት መሪዎች ለመገደል አልፎ እንደተሰጠ ሲናገር ሲሰሙ እጅግ እንደተገረሙ አያጠራጥርም። ጳውሎስ በድፍረት “እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሳው” በማለት ተናገረ። ወደ ንግግሩ መጨረሻም አስደናቂ የሆነ ደህንነት ሊያገኙ እንደሚችሉ ለአድማጮቹ ገለጸላቸው። “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፣ በእርሱ በኩል የኃጢአት ሥርየት እንዲነገርላችሁ፣ በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን” አላቸው። አድማጮቹ ይህን አስደናቂ የመዳን ዝግጅት እንደሚንቁ አምላክ አስቀድሞ በትንቢት ከተናገረላቸው ብዙዎች መካከል እንዳይመደቡ አጥብቆ በማስገንዘብ ንግግሩን ደመደመ።—ሥራ 13:30-41
12. ከጳውሎስ ንግግር ምን ውጤት ተገኘ? ይህስ እኛን እንዴት ሊያበረታታን ይገባል?
12 እንዴት ያለ ግሩም በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ ንግግር ነበር! አድማጮቹ ንግግሩን እንዴት ተቀበሉ? “ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው።” (ሥራ 13:43) በዛሬው ጊዜ ላለነው ለእኛ ምንኛ የሚያበረታታ ተሞክሮ ነው! እኛም እንደዚሁ በሕዝባዊ አገልግሎታችንም ይሁን በጉባኤ ስብሰባዎቻችን ሐሳብና ንግግር በምንሰጥበት ጊዜ እውነትን ተደማጭነት ሊኖረው በሚችል መንገድ ለማቅረብ የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።—1 ጢሞቴዎስ 4:13-16
13. ሚስዮናውያኑ የጵስዲያ አንጾኪያን ለመልቀቅ የተገደዱት ለምን ነበር? ስለ አዳዲሶቹ ደቀ መዛሙርት ምን ጥያቄ ይነሳል?
13 በጵስዲያ አንጾኪያ የነበሩት ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች ይህን የምሥራች ለራሳቸው ብቻ ይዘው ዝም ሊሉ አልቻሉም ነበር። ለሌሎች በመናገራቸውም “በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ።” ብዙም ሳይቆይ መልእክቱ ከከተማዋም አልፎ ተሰራጨ። እንዲያውም “የእግዚአብሔርም [የይሖዋም አዓት] ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ።” (ሥራ 13:44, 49) መጥፎ ቅንዓት ያደረባቸው አይሁዶች ይህን ሐቅ በደስታ ከመቀበል ይልቅ ሚስዮናውያኑን ከከተማዋ እንዲወጡ አስደረጉ። (ሥራ 13:45, 50) ይህ ሁኔታ አዲሶቹን ደቀ መዛሙርት እንዴት ነካቸው? ተስፋ ቆርጠው እምነታቸውን ተዉን?
14. ተቃዋሚዎች ሚስዮናውያኑ የጀመሩትን ሥራ ሊደመስሱት ያልቻሉት ለምንድን ነው? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?
14 አልተዉም፣ ምክንያቱም ሥራው የአምላክ እንጂ የሰው አልነበረም። በተጨማሪም ሚስዮናውያኑ ትንሣኤ ባገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ጽኑ እምነት እንዲኖራቸው አድርገው ነበር። በዚህም ምክንያት አዳዲሶቹ ደቀ መዛሙርት እንደ መሪያቸው አድርገው የተመለከቱትን ክርስቶስን እንጂ ሚስዮናውያኑን እንዳልነበረ ግልጽ ነው። በመሆኑም “ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።” (ሥራ 13:52) ይህም በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ሚስዮናውያንና ደቀ መዛሙርት አድራጊዎች በጣም የሚያበረታታ ነው! እኛ የበኩላችንን በትሕትናና በቅንዓት ካደረግን ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎታችንን ይባርኩልናል።—1 ቆሮንቶስ 3:9
ኢቆንዮን፣ ልስጥራንና ደርቤን
15. ሚስዮናውያኑ በኢቆንዮን ምን የአሠራር ሥርዓት ተከተሉ? ምንስ ውጤት ተገኘ?
15 አሁን ጳውሎስና በርናባስ 140 ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ደቡባዊ ምሥራቅ ተጉዘው ወደ ኢቆንዮን ደረሱ። ስደት ይደርስብናል ብለው በመፍራት እዚህም በአንጾኪያ ያደረጉትን ከማድረግ አላመነቱም። በውጤቱም “ብዙ አይሁዳውያንና ግሪኮች” እንዳመኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሥራ 14:1 የ1980 ትርጉም) የምሥራቹን ያልተቀበሉት አይሁድ አሁንም እንደገና ተቃውሞ አነሳሱ። ሚስዮናውያን ግን ጸንተው አዳዲሶቹን ደቀ መዛሙርት እየረዱ በኢቆንዮን ረዘም ያለ ጊዜ አሳለፉ። ከዚያም አይሁዳውያን ተቃዋሚዎቻቸው በድንጋይ ሊወግሩአቸው እንዳሰቡ በሰሙ ጊዜ ጳውሎስና በርናባስ በጥበብ ወደሚቀጥለው ክልል ማለትም “ልስጥራንና ደርቤን ወደሚባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተማዎች በእነርሱም ዙሪያ ወዳለው አገር” ሸሹ።—ሥራ 14:2-6
16, 17. (ሀ) ጳውሎስ በልስጥራን ምን ሆነ? (ለ) አምላክ ለሐዋርያው ጳውሎስ ያደረገለት ነገር አንድን የልስጥራን ወጣት የነካው እንዴት ነው?
16 በዚህ አዲስና ተሠርቶበት የማያውቅ ክልል ውስጥ ያለፍርሐት “ወንጌልን ይሰብኩ ነበር።” (ሥራ 14:7) የጵስዲያ አንጾኪያና የኢቆንዮን አይሁድ ይህን ሲሰሙ ወደ ልስጥራን መጡና ጳውሎስን እንዲወግሩት ሕዝቡን አባበሉ። ጳውሎስ የሚያመልጥበት ጊዜ ስላልነበረው ተቃዋሚዎቹ ሞቷል ብለው እስኪያምኑ ድረስ በድንጋይ ተወገረ። ከከተማዋም ወደ ውጭ ጎተቱት።—ሥራ 14:19
17 ይህ በአዲሶቹ ደቀ መዛሙርት ላይ ያስከተለባቸውን ሐዘንና ጭንቀት ልትገምቱ ትችላላችሁን? ግን በጣም የሚያስገርም ነገር ሆነ። ደቀ መዛሙርት ጳውሎስን ከበውት ሳሉ ተነስቶ ቆመ! ጢሞቴዎስ የሚባለው ወጣት ልጅ ከእነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት መካከል ይኑር አይኑር መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። እርግጥ ነው፣ አምላክ ለጳውሎስ ያደረገለትን ነገር ሳያውቅና በጨቅላ አእምሮው ላይ ጥልቅ ስሜት ሳያሳድርበት እንዳልቀረ ጥርጥር የለውም። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈለት በሁለተኛው ደብዳቤ ላይ “አንተ ግን ትምህርቴን፣ አካሄዴን፣ . . . በአንጾኪያና በኢቆንዮን በልስጥራንም የሆነብኝን የታገሥሁትንም ስደት ታውቃለህ፤ ጌታም ከሁሉ አዳነኝ” ብሎ ጽፎለታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:10, 11) ጳውሎስ ከተወገረበት ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ ልስጥራን ተመልሶ ሲመጣ ወጣቱ ጢሞቴዎስ “በልስጥራንና በኢቆንዮን ያሉ ወንድሞች ሁሉ የመሰከሩለት” ምሳሌ የሚሆን ክርስቲያን መሆኑን ተገነዘበ። (ሥራ 16:1, 2) ስለዚህ ጳውሎስ የጉዞ ጓደኛው እንዲሆን መረጠው። ይህም ጢሞቴዎስን በመንፈሳዊ አቋሙ እንዲያድግ ረድቶታል። ከጊዜ በኋላም የተለያዩ ጉባኤዎችን እንዲጎበኝ በጳውሎስ ለመላክ ብቁ ሆኖ ነበር። (ፊልጵስዩስ 2:19, 20፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:3) ዛሬም እንደዚሁ ቀናተኛ የአምላክ አገልጋዮች አብዛኞቻቸው እንደ ጢሞቴዎስ ጠቃሚ የአምላክ አገልጋዮች ሆነው ለሚያድጉ ትንንሽ ልጆች ግሩም ምሳሌዎች ሆነዋል።
18. (ሀ) ሚስዮናውያኑ በደርቤን ምን ሆኑ? (ለ) ምንስ ዓይነት አጋጣሚ አገኙ? እነርሱ ግን ምን ማድረግን መረጡ?
18 ጳውሎስ በልስጥራን ከሞት ከተረፈ በኋላ በማግሥቱ ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ሄደ። በዚህ ጉዞ ላይ ተቃዋሚዎች አልተከተሉትም ነበር። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ‘እጅግ ደቀ መዛሙርትን አደረጉ’ ይላል። (ሥራ 14:20, 21) ጳውሎስና በርናባስ በደርቤን ጉባኤ ካቋቋሙ በኋላ አንድ ውሳኔ ማድረግ አስፈለጋቸው። ከደርቤን ወደ ጠርሴስ የሚወስድ በሮማውያን የተሠራ መንገድ ነበረ። ከጠርሴስ ወደ ሶርያ አንጾኪያ ለመመለስ በጣም ቅርብ ነበር። ምናልባትም ይህ መንገድ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ከሁሉ የተሻለ ምቹ መንገድ ሳይሆን አይቀርምና ሚስዮናውያኑ አሁን ዕረፍት ማድረግ እንደሚገባቸው አስበው ይሆናል። ነገር ግን ጳውሎስና በርናባስ ጌታቸውን በመምሰል ዕረፍት በማድረግ ፈንታ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ስብከታቸውን መቀጠል መሆኑን ተገነዘቡ።—ማርቆስ 6:31-34
የአምላክን ሥራ ሙሉ በሙሉ መፈጸም
19, 20. (ሀ) ይሖዋ ሚስዮናውያኑ ወደ ልስጥራን፣ ኢቆንዮንና አንጾኪያ መመለሳቸውን የባረከው እንዴት ነበር? (ለ) ይህስ በዛሬው ጊዜ ላሉት የይሖዋ ሕዝቦች ምን ትምህርት ይሰጣቸዋል?
19 ሚስዮናውያኑ ወደ አገራቸው ለመመለስ አቋራጭ መንገድ በመፈለግ ፈንታ በድፍረት እንደገና ተመልሰው ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቆ የነበረባቸውን ከተሞች ጎበኙ። ታዲያ ይሖዋ ለአዳዲስ በጎች ያሳዩትን ይህን ከራስ ወዳድነት የራቀ አሳቢነት ባርኮላቸዋልን? አዎ፣ በእርግጥ ባርኮላቸዋል። ምክንያቱም ታሪኩ “የደቀ መዛሙርትን ልብ ለማጽናትና በሃይማኖታቸው ጸንተው እንዲኖሩ ለመምከር” እንደቻሉ ይነግረናል። ለእነዚያ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” ብለው መናገራቸው ተገቢ ነበር። (ሥራ 14:21, 22) በተጨማሪም ጳውሎስና በርናባስ እነዚህ ደቀ መዛሙርት በአምላክ መንግሥት ተባባሪ ወራሾች ለመሆን የተጠሩ መሆናቸውንም አስታወሷቸው። ዛሬም እኛ ለአዳዲስ ደቀ መዛሙርት ተመሳሳይ ማበረታቻ መስጠት ይኖርብናል። ጳውሎስና በርናባስ በሰበኩት በዚህ የእግዚአብሔር መንግሥት አገዛዝ ሥር የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ዘወትር እንዲያስቡ በማድረግ የሚደርስባቸውን መከራ ሁሉ እንዲታገሡ ልናበረታታቸው እንችላለን።
20 ጳውሎስና በርናባስ እያንዳንዱን ከተማ ለቀው ከመውጣታቸው በፊት የየአካባቢው ጉባኤ በጥሩ ሁኔታ የተደራጀ እንዲሆን ይረዱ ነበር። ብቃት ያላቸውን ሰዎች እያሠለጠኑ አመራሩን እንዲወስዱ ይሾሙ ነበር። (ሥራ 14:23) ይህም ተጨማሪ መስፋፋት እንዲኖር እንደረዳ ጥርጥር የለውም። ዛሬም በተመሳሳይ ሚስዮናውያንና ሌሎች ተሞክሮ የሌላቸውን ወንድሞች ኃላፊነት ለመሸከም እስኪበቁ ድረስ መሻሻል እንዲያደርጉ ከረዱአቸው በኋላ አንዳንድ ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ለማገልገል ወደ ሌላ ቦታ በመዛወር መልካም ሥራቸውን ይቀጥላሉ።
21, 22. (ሀ) ጳውሎስና በርናባስ የሚስዮናዊነት ጉዞአቸውን ሲጨርሱ ምን ሆነ? (ለ) ይህስ ምን ጥያቄዎችን ያስነሳል?
21 ሚስዮናውያኑ በመጨረሻ ወደ ሶርያ አንጾኪያ ሲመለሱ ጥልቅ ደስታ ሊሰማቸው ችሎአል። በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስ የታሪክ መዝገብ አምላክ አደራ የሰጣቸውን “ሥራ [ሙሉ በሙሉ አዓት]” እንደፈጸሙ ይናገራል። (ሥራ 14:26) ተሞክሮአቸውን ሲናገሩ “ወንድሞችን ሁሉ እጅግ ደስ እንዳሰኙአቸው” መረዳት ይቻላል። (ሥራ 15:3) ጳውሎስና በርናባስ ወደፊትስ ምን ያደርጉ ይሆን? ባለፈው የሥራ ውጤታቸው ብቻ በመርካት ተጨማሪ ጥረት ሳያደርጉ ተደላድለው ይቀመጡ ይሆን? በፍጹም አይቀመጡም። በግርዘት ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማግኘት በኢየሩሳሌም ያለውን የአስተዳደር አካል ከጎበኙ በኋላ ሁለቱም እንደገና የሚስዮናዊነት ጉዞአቸውን ቀጠሉ። በዚህ ጊዜ ግን አንድ ላይ ሳይሆን ለየብቻ በተለያዩ አቅጣጫዎች ነበር። በርናባስ ዮሐንስ ማርቆስን ይዞ ወደ ቆጵሮስ ሲሄድ ጳውሎስ ደግሞ ሲላስን አዲስ የሥራ ባልደረባው አድርጎ በሶርያና በኪልቅያ በኩል ተጓዘ። (ሥራ 15:39-41) ወጣቱን ጢሞቴዎስን የመረጠውና ይዞት የሄደው በዚህ ጉዞው ነበር።
22 መጽሐፍ ቅዱስ የበርናባስን የሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞ ውጤት አይገልጽም። ጳውሎስ ግን ጉዞውን ወደ አውሮፓ በመቀጠል ወደ አዳዲስ ክልሎች ሄዶ ቢያንስ በአምስት ከተሞች ማለትም በፊልጵስዩስ፣ በቤርያ፣ በተሰሎንቄ፣ በቆሮንቶስና በኤፌሶን ጉባኤዎችን መሥርቷል። ለጳውሎስ ከፍተኛ የሥራ ውጤት ያስገኘለት ቁልፍ ምን ነበር? ይህ ደንብ በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያን ደቀ መዛሙርት አድራጊዎች ተመሳሳይ ውጤት ሊያስገኝ ይችላልን?
ታስታውሳላችሁን?
◻ ኢየሱስ ከሁሉ ይበልጥ ሊመስሉት የሚገባ ምሳሌ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ በርናባስ ጥሩ ምሳሌ የነበረው በምን መንገድ ነበር?
◻ ጳውሎስ በጵስዲያ አንጾኪያ ካደረገው ንግግር ምን እንማራለን?
◻ ጳውሎስና በርናባስ ምድብ ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ የፈጸሙት እንዴት ነበር?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሐዋርያው ጳውሎስ በስደት መጽናት በወጣቱ ጢሞቴዎስ አእምሮ ላይ ዘላቂ ውጤት አስከትሏል