በርናባስ “የመጽናናት ልጅ”
አንድ ጓደኛህ ለመጨረሻ ጊዜ ያጽናናህ መቼ ነው? አንተስ እንዲያው በቅርቡ የምታስታውሰው ያጽናናኸው ሰው አለ? ሁላችንም ማጽናኛ የምንፈልግበት ጊዜ አለ። ሰዎች በፍቅር ተነሳስተው ሲያጽናኑን እንዴት እናደንቃቸዋለን! ማጽናናት ሰዎችን ለማዳመጥ፣ ችግራቸውን ለመረዳትና ለመርዳት ጊዜን መዋጀት ይጠይቃል። ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ነህን?
“ደግ ሰውና መንፈስ ቅዱስ እምነትም የሞላበት” በርናባስ ሌሎችን ለማጽናናት ፈቃደኛ በመሆን ረገድ ግሩም አርአያ ነው። (ሥራ 11:24) በርናባስ እንዲህ ዓይነት ሰው ነበር ልንል የምንችለው ለምንድን ነው? እንዲህ ዓይነቱንስ ስም ሊያገኝ የቻለው ምን ዓይነት መልካም ተግባር ቢያከናውን ነው?
ለጋስ የሆነ ረዳት
ትክክለኛ ስሙ ዮሴፍ ሲሆን ሐዋርያት ከባህሪው ጋር የሚስማማ በርናባስ የሚል የቅጽል ስም አወጡለት። ይህ ስም “የመጽናናት ልጅ” የሚል ትርጉም አለው።a (ሥራ 4:36) በወቅቱ የክርስቲያን ጉባኤ ገና መቋቋሙ ነበር። በርናባስ ቀደም ሲል ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ እንደነበር አንዳንዶች ይገምታሉ። (ሉቃስ 10:1, 2) ያም ሆነ ይህ በርናባስ ጥሩ ባህርያት የነበሩት ሰው ነበር።
በ33 እዘአ ከጰንጠቆስጤ በኋላ፣ የቆጵሮስ ሰው የነበረው ሌዋዊው በርናባስ በራሱ ፍላጎት መሬቱን ሸጠና ገንዘቡን ለሐዋርያት ሰጣቸው። ይህንን ያደረገው ለምን ነበር? በሐዋርያት ሥራ ላይ ያለው ዘገባ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ከነበሩት ክርስቲያኖች መሃል “ማናቸውም እንደሚፈልግ መጠን ለእያንዳንዱ ያካፍሉት ነበር” በማለት ይነግረናል። በርናባስ እርዳታ እንደሚያስፈልግ በግልጽ ተገንዝቦ ስለነበር በደግነት ተነሳስቶ በጉዳዩ ላይ አንድ ነገር አደረገ። (ሥራ 4:34-37) በርናባስ ጥሩ ኑሮ የነበረው ሊሆን ቢችልም የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም ሲል ቁሳዊ ሀብቱንም ሆነ ራሱን ለማቅረብ ወደ ኋላ አላለም።b ኤፍ ኤፍ ብሩስ የተባሉ ሃይማኖታዊ ምሁር እንደተገነዘቡት “በርናባስ ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸው ሰዎችም ሆኑ ማበረታቻ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት የሚችለውን ያህል ከማበረታታት ወደ ኋላ አይልም ነበር።” ይህንን ሁኔታ እሱ ለሁለተኛ ጊዜ ከተጠቀሰበት ታሪክ በግልጽ ማየት ይቻላል።
በ36 እዘአ አሁን ወደ ክርስትና የተለወጠው የጠርሴሱ ሳውል (በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ የተባለው) በኢየሩሳሌም ያሉትን ክርስቲያኖች ሊያነጋግራቸው ቢፈልግም እንኳ “ሁሉም ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ ስላላመኑ ፈሩት።” ሳውል ወደ እነሱ የመጣው ጉባኤውን ለማጥፋት የሆነ ተንኮል አስቦ ሳይሆን በእርግጥም ለውጥ አድርጎ መሆኑን ጉባኤው እንዲያምነው ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? “በርናባስ ግን ወስዶ ወደ ሐዋርያት አገባው።”—ሥራ 9:26, 27፤ ገላትያ 1:13, 18, 19
በርናባስ ሳውልን እንዴት ሊያምነው እንደቻለ ምንም የተገለጸ ነገር የለም። “የመጽናናት ልጅ” የሆነው በርናባስ ሳውልን አዳምጦ ተስፋ ከሌለው ከሚመስል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲወጣ በመርዳት ከወጣለት ቅጽል ስም ጋር የሚስማማ ነገር አድርጓል። ከዚህ በኋላ ሳውል ወደ ትውልድ ቀዬው ወደ ጠርሴስ ተመለሰ። በእነዚህ ሁለት ሰዎች መሀልም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወዳጅነት ተመሠረተ። ይህ ወዳጅነት ከዚያ በኋላ ለነበሩት ዓመታት ጥሩ ውጤት አምጥቷል።—ሥራ 9:30
በአንጾኪያ
በ45 እዘአ ገደማ በሶርያ አንጾኪያ ያልተጠበቀ ውጤት እንደተገኘ ማለትም ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች አማኞች እየሆኑ እንዳሉ የሚገልጽ ወሬ ወደ ኢየሩሳሌም ደርሶ ነበር። ጉባኤው ያለውን ሁኔታ እንዲመረምርና ሥራውን እንዲያደራጅ በርናባስን በፍጥነት ላከው። ከዚህ የተሻለ ጥበብ ያለበት እርምጃ ሊወስዱ አይችሉም ነበር። ሉቃስ እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “እርሱም መጥቶ የእግዚአብሔርን ጸጋ ባየ ጊዜ ደስ አለው፤ ሁሉንም በልባቸው ፈቃድ በጌታ ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው ደግ ሰውና መንፈስ ቅዱስ እምነትም የሞላበት ነበርና። ብዙ ሕዝብ ወደ ጌታ ተጨመሩ።”—ሥራ 11:22-24
በርናባስ ያደረገው ይህን ብቻ አልነበረም። ሃይማኖታዊ ምሁር የሆኑት ጁሴፔ ሬቺዮቴ እንዲህ ብለዋል:- “በርናባስ ተግባራዊ መፍትሔ የሚያፈልቅ ሰው ነበር። ይህ ተስፋ ሰጭ ሁኔታ ለጥሩ ፍሬ እንዲበቃ አንድ ነገር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደበትም። ስለዚህ የሚያስፈልገው ዋና ነገር ለመከሩ ሥራ የሚሆኑ ሠራተኞች ነበሩ።” በርናባስ የቆጵሮስ ሰው ስለሆነ ከአሕዛብ ጋር መነጋገር ለእሱ አዲስ አልነበረም። በተለይ ለአረማውያን በመስበክ ረገድ ጥሩ ችሎታ እንዳለው ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በዚህ የሚያስደስትና የሚያበረታታ ሥራ ሌሎችም እንዲሳተፉ ፍላጎት ነበረው።
በርናባስ ሳውልን አስታወሰ። በርናባስ ቀድሞ አሳዳጅ የነበረው ሳውል ‘በአሕዛብ ፊት የክርስቶስን ስም እንዲሸከም የተመረጠ ዕቃ’ እንደሚሆን ለሐናንያ ስለ ተገለጠለት ራእይ የተገነዘበ ይመስላል። (ሥራ 9:15) ስለዚህ በርናባስ ሳውልን ፈልጎ ሊያገኘው ወደ ጠርሴስ ጉዞ ጀመረ። እዚያ ለመድረስ ወደ 200 ኪሎ ሜትር መጓዝ ነበረበት። የአገልግሎት ጓደኛሞች ሆነው በሠሩበት ጊዜ “በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፣ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ።”—ሥራ 11:25, 26
በንጉሥ ቀላውዴዎስ ዘመነ መንግሥት በሮማ ግዛት የተለያዩ ክፍሎች ታላቅ ረሀብ ሆነ። የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ የነበረው ጆሴፈስ እንደዘገበው በኢየሩሳሌም “ብዙ ሰዎች በምግብ እጥረት አልቀዋል።” ስለዚህም በአንጾኪያ ያሉ ደቀ መዛሙርት “እያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ፤ እንዲህም ደግሞ አደረጉ፣ በበርናባስና በሳውልም እጅ ወደ ሽማግሌዎቹ ሰደዱት።” በርናባስና ሳውል ተልእኳቸውን ሙሉ በሙሉ ከፈጸሙ በኋላ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስን ይዘው ወደ አንጾኪያ ተመለሱ። በአንጾኪያ በሚገኘው ጉባኤ ነቢያትና መምህራን ከነበሩት መካከል ይቆጠሩ ነበር።—ሥራ 11:29, 30፤ 12:25፤ 13:1
ልዩ ሚስዮናዊ ምድብ
በዚህ ጊዜ አንድ ልዩ ነገር ተከሰተ። “እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ:- በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ።” እስቲ አስበው! የይሖዋ መንፈስ ሁለቱም ልዩ ተልእኮ እንዲሰጣቸው አዘዘ። “እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ።” በርናባስ ሐዋርያ ወይም የተላከ ተብሎም ሊጠራ ይችላል።—ሥራ 13:2, 4፤ 14:14
በቆጵሮስ ሲያልፉ የሮማ ግዛት የሆነችው የዚህች ደሴት ገዢ የሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ወደ ክርስትና እንዲለወጥ ካደረጉ በኋላ በትንሿ እስያ ጠረፍ ወደምትገኘው ጴርጌን ሲጓዙ ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ ትቷቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። (ሥራ 13:13) በርናባስ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ጥሩ ተሞክሮ ያለው የአገልግሎት ጓደኛ በመሆኑ የመሪነት ቦታ ያለው ይመስላል። ከዚህ በኋላ ግን ሳውል (አሁን ጳውሎስ በሚል የሚታወቀው) የመሪነቱን ቦታ ያዘ። (ከሥራ 13:7, 13, 16፤ 15:2 ጋር አወዳድር።) በርናባስ በዚህ የጳውሎስ እድገት ተቀይሞ ይሆን? በፍጹም፣ ይሖዋ የአገልግሎት ጓደኛውንም ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተጠቀመበት እንዳለ ይህ የጎለመሰ ክርስቲያን በትህትና ተቀብሎ ነበር። ይሖዋ በእነሱ ተጠቅሞ ገና ሌሎች ክልሎች ምሥራቹን እንዲሰሙ ይፈልግ ነበር።
ጳውሎስና በርናባስ በጲስድያ ካለችው አንጾኪያ ከመባረራቸው በፊት የአገሬው ነዋሪ በሙሉ የአምላክን ቃል የሰማ ሲሆን፤ ብዙዎችም መልእክቱን ተቀብለዋል። (ሥራ 13:43, 48-52) በኢቆንዮንም ‘ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ብዙዎች አመኑ።’ ይህ ጳውሎስና በርናባስን ‘ምልክትና ድንቅ በእጃቸው ይደረግ ዘንድ እየሰጠ ለጸጋው ቃል ስለ መሰከረው ስለ ጌታ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት ለመቀመጥ’ አነሳስቷቸዋል። በድንጋይ ሊወግሯቸው እንዳደሙ ሲሰሙ ከኢቆንዮን በመሸሽ በልስጥራን፣ በደርቤንና በሊቃኦንያ ሥራቸውን ቀጠሉ። በርናባስና ጳውሎስ በልስጥራን ለሕይወት አስጊ የሆነ ተሞክሮ ቢያጋጥማቸውም “የደቀ መዛሙርቱን ልብ እያጸኑ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩና:- ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል እያሉ” ሥራቸውን ቀጥለዋል።—ሥራ 14:1-7, 19-22
እነዚህ ሁለት ታታሪ ሰባኪዎች ለፍርሃት ቦታ አልሰጡም። ከዚህ ይልቅ አዳዲሶቹን ክርስቲያኖች ለማነጽ በተለይም በአዲሶቹ ጉባኤዎች ውስጥ የመሪነቱን ቦታ ለመያዝ ብቃት ያላቸውን ወንዶች ለመርዳት ቀደም ሲል ከፍተኛ ተቃውሞ ስላጋጠማቸው ትተውት ወደወጡት ቦታ ተመልሰዋል።
ግርዘትን በተመለከተ የተነሳ ክርክር
በርናባስ በ33 እዘአ የጰንጠቆስጤ በዓል ከተከበረ ከ16 ዓመት ገደማ በኋላ የግርዘት ጉዳይን በተመለከተ አንድ ታላቅ ለውጥ ባስከተለ ታሪካዊ ሁኔታ ውስጥ ተካፍሏል። “አንዳንዶችም ከይሁዳ [ወደ ሶሪያ አንጾኪያ] ወረዱና:- እንደ ሙሴ ሥርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር።” በርናባስና ጳውሎስ ነገሩ እንዲህ እንዳልሆነ ከተሞክሮ ያውቁ ስለነበር በጉዳዩ ላይ ተከራከሩ። ስልጣናቸውን ከማሳየት ይልቅ ይህ ጥያቄ ለጠቅላላው የወንድማማች ማኅበር እንደሚጠቅም ተገነዘቡ። ስለዚህ ጥያቄውን በኢየሩሳሌም የሚገኘው የአስተዳደር አካል እንዲመለከተው አስተላለፉት። ከዚያም የተላከው መልስ ክርክሩ እንዲቋጭ አድርጓል። በኋላም ጳውሎስና በርናባስ “ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሳቸውን ከሰጡት ከምንወዳቸው” ተብለው ከተጠሩት ውሳኔውን ወደ አንጾኪያ እንዲያስተላልፉ ከተላኩት ወንድሞች ጋር ነበሩ። ከአስተዳደር አካል የተላከው ደብዳቤ ለጉባኤው ከተነበበና ንግግር ከተሰጠ በኋላ የጉባኤው አባላት ‘በምክሩና በማበረታቻው ደስ አላቸው።’—ሥራ 15:1, 2, 4, 25-32
“መከፋፋት ሆነ”
ስለ በርናባስ ብዙ መልካም ጎኖች ስናነብ የእሱን ምሳሌ መከተል ከባድ እንደሆነ አድርገን እናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ “የመጽናናት ልጅ” የሆነው በርናባስ እንደ እኛው ፍጽምና የሌለው ሰው ነበር። እሱና ጳውሎስ ሁለተኛ የሚስዮናዊ ጉዞ በማድረግ ጉባኤዎችን ለመጎብኘት በዝግጅት ላይ ሳሉ አለመግባባት ተፈጠረ። በርናባስ ያጎቱን ልጅ ማርቆስ የተባለው ዮሐንስን ይዞ ለመሄድ ወሰነ፤ ይሁን እንጂ ጳውሎስ ማርቆስ በመጀመሪያ የሚስዮናዊ ጉዞ ወቅት ትቷቸው ስለተመለሰ እሱን ይዞ መሄድ አግባብ አልመሰለውም። “እርስ በርሳቸው እስኪለያዩ ድረስ መከፋፋት ሆነ፣ በርናባስም ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ።” ‘ጳውሎስ ግን ሲላስን መርጦ’ በሌላ አቅጣጫ ሄደ።—ሥራ 15:36-40
እንዴት የሚያሳዝን ነው! ሆኖም ይህ ግጭት ስለ በርናባስ ባህርይ ግልጽ የሚያደርግልን ነገር አለ። አንድ ምሁር እንዳሉት “ይህ ታሪክ በርናባስ ማርቆስን አምኖ ለሁለተኛ ጊዜ ከእርሱ ጋር ለመሄድና የመጣውን ለመቀበል ዝግጁ እንደነበረ የሚያሳይ የበርናባስ መልካም ባሕርይ ሕያው መግለጫ ነው።” እኚሁ ጸሐፊ “በርናባስ በእሱ ላይ እምነት መጣሉ ማርቆስ በራሱ ላይ ያለው ትምክህት እንዲገነባና እንደገና ቃሉን ለመፈጸም እንዲነሳሳ ረድቶታል” በማለት ሐሳብ ሰጥተዋል። በርናባስ በማርቆስ ላይ የጣለው እምነት ከጊዜ በኋላ ውጤቱ ሙሉ በሙሉ ስለተረጋገጠ ጳውሎስ ራሱ ለክርስቲያናዊ አገልግሎት የማርቆስን ጠቃሚነት ተገንዝቧል።—2 ጢሞቴዎስ 4:11፤ ከቆላስይስ 4:10 ጋር አወዳድር።
የበርናባስ ምሳሌ ያዘኑትን ሰዎች ጊዜ ወስደን እንድናዳምጣቸው፣ ችግራቸውን እንድንረዳላቸውና እንድናበረታታቸው፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ቁሳዊ እርዳታ እንድናደርግላቸው ሊገፋፋን ይችላል። ወንድሞቹን ለመርዳት በየዋህነትና በድፍረት ያሳየው ፈቃደኝነት ጥሩ ውጤት ማስገኘቱን ማንበብ በራሱ የሚያጽናና ነው። በዘመናችንም እንደ በርናባስ ዓይነት ሰዎች በጉባኤዎቻችን ማግኘታችን እንዴት ያለ በረከት ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንድን ሰው “የ—ልጅ” ብሎ መጥራት የታወቀ ባህሪውን ለማጉላት ያገለግል ነበር። (ዘዳግም 3:18 የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የአንድን ሰው ባህርይ ለመግለጽ በቅጽል ስም መጥራት የተለመደ ነበር። (ከማርቆስ 3:17 ጋር አወዳድር።) እንዲህ ዓይነቱ ቅጽል ስም በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታወቅበትን ባህርይ የሚወክል ነበር።
b አንዳንዶች የሙሴ ሕግ የሚደነግገውን መሠረት በማድረግ በርናባስ ሌዋዊ ሆኖ ሳለ እንዴት የራሱ መሬት ሊኖረው ቻለ በማለት ይጠይቃሉ። (ዘኁልቁ 18:20) ይሁን እንጂ መሬቱ የሚገኘው በፍልስጤም ይሁን በቆጵሮስ ግልጽ እንዳልሆነ መታወስ አለበት። በተጨማሪም በርናባስ በኢየሩሳሌም አካባቢ በውርስ ያገኘው የመቃብር ቦታም ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ በርናባስ ሌሎችን ለመርዳት ሲል መሬቱን ሸጧል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በርናባስ ‘ደግ፣ መንፈስ ቅዱስና እምነት የሞላበት ሰው’ ነበር