የአንባብያን ጥያቄዎች
የይሖዋ ምሥክሮች የልደት በዓልን የማያከብሩት ይህ ልማድ በጥንት ዘመን ሃይማኖታዊ ትርጉም ስለነበረው ነውን?
የልደት በዓልን የማክበር ልማድ የመጣው ከባዕድ አምልኮና ከሐሰት ሃይማኖት ነው። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ልማድ የሚርቁበት ምክንያት ይህ ብቻ አይደለም።
በአንድ ወቅት ሃይማኖታዊ ባሕርይ የነበራቸው ልማዶች ባሁኑ ጊዜ በብዙ ቦታዎች ሃይማኖታዊ ትርጉም የላቸውም። ለምሳሌ ያህል የጋብቻ ቀለበት በአንድ ወቅት ሃይማኖታዊ ትርጉም ነበረው፤ ዛሬ ግን በአብዛኞቹ አካባቢዎች ሃይማኖታዊ ትርጉም የለውም። በእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ረገድ በአጠቃላይ ልዩነት የሚያመጣው ልማዱ አሁንም ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ቁርኝት ያለው መሆን አለመሆኑ ነው።—በጥር 15, 1972 እና በጥቅምት 15, 1991 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ የወጡትን “የአንባብያን ጥያቄዎች” ተመልከት።
የልደት በዓልን የማክበር ልማድ የመጣው ከአጉል እምነትና ከሐሰት ሃይማኖት መሆኑን በርካታ የምርምር ጽሑፎች ይገልጻሉ። ዘ ኢንሳይክሎፒድያ አሜሪካና “የጥንቱ የግብፅ፣ የግሪክ፣ የሮማና የፋርስ ዓለም የአማልክትን፣ የነገሥታትንና የመኳንንትን የልደት በዓሎች ያከብር ነበር” በማለት ገልጿል። በአንፃሩ ደግሞ “እሥራኤሎች የወንዶች ዜጎቻቸውን ዕድሜ መዝግበው ይይዙ ነበር እንጂ የልደት ቀኖቻቸውን ድግስ ደግሰው ያከብሩ እንደነበረ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም።”—የ1991 እትም
ሌሎች የምርምር ጽሑፎችም የልደት በዓልን አመጣጥ በሚመለከት ሰፋ ያለ ዝርዝር በመስጠት ‘ለልደት በዓል ድግስ መደገስ የተጀመረው በአውሮፓ ሲሆን ከበርካታ ዓመታት በፊት ነው። ሰዎች በጥሩና በመጥፎ መናፍስት ያምኑ ነበር። ሁሉም ሰው እነዚህ መናፍስት የልደት በዓል በሚከበርለት ሰው ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ተብሎ ይፈራ ስለነበር በዚህ ቀን በወዳጆችና በዘመዶች ተከብቦ ይውል ነበር። ስለዚህ የልደት በዓል መከበር የተጀመረው አንድን ሰው ከክፉ ለመጠበቅና መጪው ዓመት መልካም እንዲሆንለት ለማድረግ ታስቦ ነበር’ ይላሉ።—በርዝደይ ፓርቲስ አራውንድ ዘ ወርልድ፣ 1967
በተጨማሪም ይህ መጽሐፍ በልደት በዓል ላይ የሚፈጸሙ የብዙ ልማዶችን አመጣጥ ያብራራል። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ብሏል፦ “[ሻማ የሚበራበት] ምክንያት ጧፍ ወይም ሻማ ምትሐታዊ ባሕርይ አለው ብለው ያምኑ ከነበሩት ከጥንት ግሪኮችና ሮማውያን የመጣ ነው። ግሪኮችና ሮማውያን ጸሎታቸውና መልካም ምኞታቸው በሻማዎቹ ነበልባል ተሸካሚነት ወደ አማልክት ያርጋሉ ብለው ያምኑ ስለነበር ሻማዎችን ያበሩ ነበር። አማልክቱም ጸሎታቸውን ተቀብለው በረከቶቻቸውን እንደሚልኩላቸው ተስፋ ያደርጉ ነበር።”
ይሁን እንጂ የልደት በዓልን ማክበር ሃይማኖታዊ ትርጉም የነበረውና አሁንም ያለው ይሁንም አይሁን በዚህ ጥያቄ ረገድ ሊታሰብበት የሚገባ ሌላ ጉዳይም አለ። የጎለመሱ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ማንኛውንም ጥቆማ በቸልታ አይመለከቱም።
የአምላክ የጥንት አገልጋዮች የሰዎችን ዕድሜ ለማስላት እንዲያስችላቸው ግለሰቦች የተወለዱበትን ጊዜ ይመዘግቡ ነበር። “ኖኅም የአምስት መቶ ዓመት ሰው ነበረ፤ ኖኅም ሴምን፣ ካምን ያፌትንም ወለደ” የሚል እናነባለን።—ዘፍጥረት 5:32፤ 7:11፤ 11:10-26
የአምላክ ሕዝቦች ልጅ ሲወለድላቸው እንደ ታላቅ ደስታና በረከት ይቆጥሩ ነበር። (ሉቃስ 1:57, 58፤ 2:9-14፤ ዮሐንስ 16:21) ሆኖም ለልደቱ ቀን መታሰቢያ አያደርጉም ነበር። ሌሎች ዓመታዊ በዓሎችን ያከብሩ የነበሩ ቢሆንም የልደት በዓልን ግን አያከብሩም ነበር። (ዮሐንስ 10:22, 23) የእሥራኤል ልማዶችና ባሕሎች የተሰኘ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “አይሁዳውያን የልደት በዓልን ያከብሩ እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ሆነ በታልሙድ ወይም የኋላ ዘመን ሊቃውንት በጻፏቸው ጽሑፎች ውስጥ ስላልተጠቀሰ ይህ ልማድ ከሌሎች አሕዛብ ልማድ የተወሰደ ነበር። እንዲያውም ከጥንቶቹ ግብፃውያን የተወሰደ ልማድ ነበር።”
ልማዱ ከግብፃውያን የመጣ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተተረከ አንድ የልደት በዓል አከባበር ለመረዳት ይቻላል። ይህን በዓል እውነተኛ አምላኪዎች አላከበሩትም ነበር። ዮሴፍ በግብፃውያን እስር ቤት በነበረበት ጊዜ ግብፅን ይገዛ የነበረው የፈርዖን ልደት በዓል ነበር። በበዓሉ የተገኙ አንዳንድ አረማውያን በግብዣው ተደስተው ይሆናል። ሆኖም በዚህ በዓል ላይ የፈርዖን የእንጀራ አበዛዎች አለቃ ራስ ተቆርጧል።—ዘፍጥረት 40:1-22
የታላቁ ሄሮድስ ልጅ በነበረው በሄሮድስ አንጢጳስ የልደት በዓል አከባበር ላይም ከፈርዖን ጋር ተመሳሳይ የሆነ አስከፊ ድርጊት ተፈጽሟል። ይህ የልደት በዓል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ንፁሕ የሆነ ተራ ድግስ እንደሆነ ተደርጎ አይደለም። እንዲያውም ለዮሐንስ መጥምቁ ራስ መቆረጥ ምክንያት ሆኗል። ያን ጊዜም “ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው በድኑን ወሰዱና ቀበሩት፣ መጥተውም ለኢየሱስ አወሩለት። ኢየሱስም በሰማ ጊዜ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ ፈቀቅ አለ።” (ማቴዎስ 14:6-13) የልደት በዓል አከባበር ኢየሱስንና ደቀ መዛሙርቱን ያስደስታቸው የነበረ ይመስልሃል?
የይሖዋ ምሥክሮች የልደት በዓልን የማክበር ልማድ ከየት እንደመጣ ስለሚያውቁና ከዚህም ይበልጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥሩ ልማድ እንደሆነ ተደርጎ ስላልተገለጸ ከዚህ ልማድ የሚርቁበት በቂ ምክንያት አላቸው። በዓመቱ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ የደስታ ግብዣ ሊያደርጉ ስለሚችሉ ይህን ዓለማዊ በዓል መከተል አያስፈልጋቸውም። ስጦታ የሚሰጡትም በግዴታ ወይም በልደት በዓል አስገዳጅነት አይደለም። ስጦታቸው ከለጋስነትና ከእውነተኛ ፍቅር የሚመነጭና በማንኛውም ጊዜ የሚደረግ በፈቃደኛነት ላይ የተመሠረተ ልግስና ነው።—ምሳሌ 17:8፤ መክብብ 2:24፤ ሉቃስ 6:38፤ ሥራ 9:36, 39፤ 1 ቆሮንቶስ 16:2, 3