የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 10/15 ገጽ 30-31
  • የአንባብያን ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንባብያን ጥያቄዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአንባብያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • የልደት ቀን
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • የይሖዋ ምሥክሮች ልደት የማያከብሩት ለምንድን ነው?
    ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች
  • ሁሉም ዓይነት ግብዣ አምላክን ያስደስተዋል?
    ከታላቁ አስተማሪ ተማር
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 10/15 ገጽ 30-31

የአንባብያን ጥያቄዎች

ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች የጋብቻ ቀናቸውን በየዓመቱ ያከብራሉ። የልደት ቀንም ቢሆን አንድ ሰው የተወለደበትን ቀን በየዓመቱ የሚያከብርበት በዓል ነው። ታዲያ የጋብቻ ቀናችንን ካከበርን የልደት ቀናችንን የማናከብረው ለምንድን ነው?

ግልጹን ለመናገር አንድ ክርስቲያን ሁለቱንም ቢሆን ማክበሩ አስፈላጊ አይደለም። ይሁን እንጂ እንዲህ ሲባል ሁለቱም አንድ ዓይነት ትርጉም አላቸው ወይም ለልደት ቀን በዓልም ሆነ ለጋብቻ ቀን በዓል አንድ ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል ማለት አይደለም።

“ዓመት በዓል” ‘በየዓመቱ የሚከበር አንድ ዓይነት ድርጊት የተፈጸመበት ቀን’ ስለሆነ ሁለቱም ዓመት በዓሎች ናቸው። ማንኛውም ክንውን፣ ለምሳሌ ያህል የመኪና አደጋ የደረሰባችሁ ቀን፣ የጨረቃ ግርዶሽ የታየበት ቀን፣ ከቤተሰባችሁ ጋር ሽርሽር የሄዳችሁበት ቀን፣ ወዘተ በየዓመቱ ሊታሰብ ይችላል። ክርስቲያኖች እያንዳንዱን “ዓመት በዓል” እንደማያከብሩ ወይም ቀኑን ለማስታወስ ግብዣ እንደማያደርጉ ግልጽ ነው። አንድ ሰው የማንኛውንም ድርጊት የተለያዩ ገጽታዎች ከተመለከተ በኋላ ምን ማድረግ ተገቢ እንደሚሆን መወሰን አለበት።

ለምሳሌ ያህል አምላክ በ1513 ከዘአበ መልአኩ ግብጽ ውስጥ የእስራኤላውያንን ቤቶች ያለፈበትንና ከዚህም የተነሳ ሕዝቦቹ ነጻ የወጡበትን ቀን በየዓመቱ እንዲያከብሩ እስራኤላውያንን በግልጽ አዟል። (ዘጸአት 12:​14) የአምላክን መመሪያ በመታዘዝ ኢየሱስን ጨምሮ አይሁዳውያን ይህን ቀን በየዓመቱ ያከበሩ ቢሆንም በትልቅ ግብዣ ወይም ስጦታ በመሰጣጣት አላከበሩትም። በተጨማሪም አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱ በድጋሚ ለአምላክ የተወሰነበትን ቀን ዓመት በዓል አድርገው ያከብሩ ነበር። ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ታሪካዊ ክንውን እንዲያከብሩ ባያዝም ኢየሱስ ይህን እንዳልነቀፈባቸው ዮሐንስ 10:​22, 23 ያመለክታል። በመጨረሻም ክርስቲያኖች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ልዩ ስብሰባ ያደርጋሉ። ይህንንም የሚያደርጉት በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ግልጽ ትእዛዝ በማክበር ነው።​—⁠ሉቃስ 22:​19, 20

የጋብቻ ቀን ማክበርን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? በአንዳንድ አገሮች ባልና ሚስቶች አምላክ ወዳስጀመረው ዝግጅት ማለትም ወደ ትዳር ዓለም የገቡበትን ቀን ማሰባቸው የተለመደ ነገር ነው። (ዘፍጥረት 2:​18–24፤ ማቴዎስ 19:​4–6) መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻን አሉታዊ በሆነ መንገድ እንደማይገልጸው የታወቀ ነው። ኢየሱስ በጋብቻ ድግስ ላይ ከመገኘቱም በላይ ወቅቱ አስደሳች እንዲሆን አስተዋጽኦ አበርክቷል።​—⁠ዮሐንስ 2:​1–11

ስለዚህ አንድ ባልና ሚስት በየዓመቱ የተጋቡበትን ቀን ቢያስቡና የተለየ ጊዜ መድበው የሠርጋቸውን ቀን ደስታ መለስ ብለው ቢያስታውሱ ወይም ትዳራቸውን የተሳካ ለማድረግ የጋራ ጥረታቸውን ለመቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ቢያድሱ ምንም ስህተት አይኖረውም። ይህን አስደሳች ቀን ሁለቱ ብቻቸውን ሆነው ለማሰብ ወይም ጥቂት ዘመዶቻቸውንና የቅርብ ወዳጆቻቸውን ለመጨመር ቢወስኑ ይህ የእነሱ ምርጫ ነው። ይሁን እንጂ ወቅቱ ትልቅና ልቅ የሆነ ግብዣ ለማድረግ ሰበብ ወይም ምክንያት መሆን አይኖርበትም። በዚህ ወቅት ክርስቲያኖች በሕይወታቸው በሙሉ በሚመሩባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመመላለስ ይፈልጋሉ። ስለዚህ አንድ ሰው የጋብቻ ቀኑን ማክበር አለማክበሩ የግሉ ጉዳይ ነው።​—⁠ሮሜ 13:​13, 14

የልደት ቀንን ማክበርስ? ቀኑን ማክበር ተገቢ እንደሆነ የሚጠቁም ማስረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለንን?

በዚህ መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይታወቁ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች የልደት ቀናቸውን ያከብሩ ነበር። ብዙዎቹ ዕለታዊ የሰማይ መና (እንግሊዝኛ) በተባለ ለየቀኑ የተመደበ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በሚገኝበት አነስተኛ መጽሐፍ ውስጥ የሌሎች ወንድሞችንና እህቶችን የልደት ቀን መዝግበው ይይዙ ነበር። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የእምነት ባልደረቦቻቸው የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የልደት ቀን ለማስታወስ በቀኑ አንጻር ትናንሽ ፎቶግራፎችን ይለጥፉ ነበር። በተጨማሪም በየካቲት 15, 1909 መጠበቂያ ግንብ ላይ በፍሎሪዳ፣ ጃክሰንቪል በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ወንድም ራስል ወደ መድረክ እንዲወጣ መጠራቱ ሪፖርት ተደርጓል። የተጠራው ለምን ነበር? ለልደት ቀኑ ስጦታ እንዲሆን በጥቂት ሣጥኖች ባሕረ-ሎሚ፣ አናናስና ብርቱካን እንደተላከለት ሊነገረው ነበር። ከዚህ የቀድሞው ጊዜ ምን ይመስል እንደነበረ ለመገንዘብ እንችላለን። በተጨማሪም በዚህ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ታኅሣሥ 25ን የኢየሱስ የልደት ቀን ነው ብለው ያከብሩ ነበር። እንዲያውም ብሩክሊን በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት የገና በዓል የእራት ግብዣ ይደረግ ነበር።

ከዚያ ጊዜ ወዲህ የአምላክ ሕዝቦች ብዙ መንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸው የታወቀ ነው። በ1920ዎቹ ዓመታት የተገኘው ተጨማሪ የእውነት ብርሃን ቀጥሎ ያሉትን ነገሮች እንዲያስተውሉ አስችሏቸዋል:-

ኢየሱስ ከአረማውያን ሃይማኖት ጋር ግንኙነት ባለው ቀን በታኅሣሥ 25 አልተወለደም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዘው ኢየሱስ የሞተበትን ቀን እንድናከብር እንጂ ኢየሱስም ሆነ ማንኛውም ሌላ ሰው የተወለደበትን ቀን አይደለም። ኢየሱስ የሞተበትን ቀን ማሰብ ከመክብብ 7:​1 ጋር እንዲሁም ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው አንድ ታማኝ ሰው በሕይወት ዘመኑ ያከናወነው ነገር እንጂ የተወለደበት ቀን ካለመሆኑ ጋር ይስማማል። መጽሐፍ ቅዱስ አንድም ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የልደት ቀኑን እንዳከበረ እንደማይገልጽና የመዘገባቸው የልደት ቀን ክብረ በዓሎችም አረማውያን ያከበሩዋቸው ከመሆኑም በላይ ከጭካኔ ድርጊቶች ጋር ያያይዛቸዋል። እስቲ የእነዚያን የልደት ቀን ክብረ በዓሎች ሥረ መሠረት ቀረብ ብለን እንመልከት።

በመጀመሪያ ተጠቅሶ የምናገኘው በዮሴፍ ዘመን ስለነበረው የፈርዖን የልደት ቀን ነው። (ዘፍጥረት 40:​20–23) በዚህ ረገድ የሐስቲንግስ ኢንሳይክለፒዲያ ኦቭ ሪሊጅን ኤንድ ኤቲክስ የልደት ቀኖች በሚለው ርዕስ ስር እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “የልደት ቀን የማክበር ልማድ ላይ ላዩን ሲታይ ጊዜውን ከማስታወስ ጋር፣ በይዘቱ ደግሞ ከአንዳንድ ኋላ ቀር ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ጋር የተያያዘ ነው።” በመጨረሻም ኢንሳይክለፒዲያው የጥንታዊ ግብጽ ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ሰር ጄ ጋርድነር ዊልኪንሰን የጻፉትን ጠቅሶ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እያንዳንዱ ግብጻዊ ለተወለደበት ቀን ይቅርና ለተወለደባት ሰዓት እንኳ ሳይቀር ከፍተኛ ግምት ይሰጥ ነበር። በፋርስ አገር እንደሚደረገው ሁሉ እያንዳንዱ ግለሰብ የልደት ቀኑን የሚያከብረው በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታወቁትን መዝናኛዎች በሙሉ አዘጋጅቶና ጣፋጭ የድግስ ምግቦች በገፍ አቅርቦ ባልንጀሮቹን በመጋበዝ በታላቅ ፈንጠዝያ ሳይሆን አይቀርም።”

ሌላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው የሄሮድስ የልደት ቀን በዓል ሲሆን በዚያም ቀን የዮሐንስ አንገት ተቆርጧል። (ማቴዎስ 14:​6–10) ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክለፒዲያ (የ1979 እትም) ይህን ሐሳብ ያቀርባል:- “በቅድመ ሔለናውያን ዘመን የነበሩ ግሪኮች የአማልክትንና የታዋቂ ሰዎችን የልደት ቀኖች ያከብሩ ነበር። ጄኔትሊያ የሚለው የግሪክኛ ቃል እነዚህን በዓላት የሚያመለክት ሲሆን ጄኔሲያ የሚለው ደግሞ አንድ በሕይወት የሌለ እውቅ ግለሰብ የተወለደበትን ቀን ለማክበር የሚደረግን በዓል ያመለክታል። በ2 መቃባውያን 6:​7 ላይ የአንቲዮከስ 4ኛ ወርኃዊ ጄኔትሊያ ተጠቅሶ የምናገኝ ሲሆን በዚያም ወቅት አይሁዳውያን ‘ከመሥዋዕቶቹ እንዲካፈሉ’ ተገድደው ነበር። . . . ሄሮድስ የልደት ቀኑን ያከበረው የሔለናውያንን ልማድ በመከተል ነበር። በቅድመ ሔለናውያን ዘመን እስራኤል ውስጥ የልደት ቀን ይከበር እንደነበር የሚያሳይ አንድም ማስረጃ የለም።”

እርግጥ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች የእያንዳንዱን ልማድ ወይም ባሕል አመጣጥና በጥንት ጊዜ ሊኖረው በሚችለው ሃይማኖታዊ ትስስር ረገድ ከልክ በላይ አይጨነቁም፤ ሆኖም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ ከጉዳዩ ጋር ዝምድና ያላቸውን ፍንጮች ችላ የማለት ዝንባሌ የላቸውም። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የልደት ቀን በዓሎች አረማውያን ብቻ ያከበሩዋቸው እንደሆኑና በዓሎቹም የጭካኔ ድርጊት የተፈጸመባቸው መሆኑን ያካትታል። ቅዱሳን ጽሑፎች የልደት ቀን በዓሎችን አሉታዊ በሆነ መንገድ የሚገልጿቸው ሲሆን እውነተኛ ክርስቲያኖች ደግሞ ይህን ሐቅ አቅልለው አይመለከቱትም።

ስለዚህ ክርስቲያኖች የጋብቻ ቀናቸውን ለማክበር ቢመርጡ ይህ የግል ውሳኔያቸው ነው። የልደት ቀኖችን ማክበር ግን ተገቢ የማይሆንባቸው አጥጋቢ ምክንያቶች አሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ