የመሲሑ ተስፋ፣ እርግጠኛ ተስፋ ነውን?
ራሱን ሙሴ ብሎ ይጠራ ነበር። እውነተኛ ስሙ ግን በታሪክ ብቻ የሚታወስ ሆኖአል። በአምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ አይሁድ ሲጠባበቁ የቆዩት መሲሕ እርሱ መሆኑን ለማሳመን በቀርጤስ ደሴት በሙሉ ተጉዟል። የአይሁድ ጭቁንነት፣ ግዞተኛነትና ምርኮኛነት ፈጥኖ እንደሚያበቃ ነገራቸው። እነርሱም አመኑት። ነፃ ይወጣሉ የተባለበት ቀን ሲደርስ አይሁድ “ሙሴን” ተከትለው የሜድቴራኒያንን ባሕር ቁልቁል ወደሚመለከት አፋፍ ወጡ። ባሕሩ የሚከፈልላቸው ራሳቸውን ወደ ባሕሩ በመወርወር ብቻ እንደሆነ ነገራቸው። ብዙዎቹ ታዘዙትና ራሳቸውን ወደ ባሕሩ ወረወሩ። ባሕሩ ግን አልተከፈለም። ብዙዎቹ ሰጠሙ፣ አንዳንዶቹ በመርከበኞችና በዓሣ አጥማጆች እርዳታ ሕይወታቸው ተረፈ። ከዚያ በኋላ ግን ሙሴ የደረሰበት አልተገኘም። ይህ መሲሕ ጠፍቶ ቀረ።
መሲሕ ምንድን ነው? “አዳኝ”፣ “የሚቤዥ”፣ እና “መሪ” የሚሉት ቃላት ወደ አእምሮ ሊመጡ ይችላሉ። ብዙ ሰዎች መሲሕ ተከታዮቹን ከጭቆና ወደ ነፃነት እንደሚያወጣ ቃል የሚገባ፣ በውስጣቸውም ተስፋና እምነት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ሰው ነው ብለው ያስባሉ። የሰው ታሪክ በአብዛኛው የጭቆና ታሪክ በመሆኑ ባለፉት መቶ ዓመታት ሁሉ ብዙ እንዲህ ዓይነት መሲሖች መነሳታቸው የሚያስደንቅ አይደለም። (ከመክብብ 8:9 ጋር አወዳድር።) እነዚህ መሲሖች ግን ራሱን መሲሕ ብሎ እንደሰየመው እንደ ቀርጤሱ ሙሴ ወደ ነፃነት በመምራት ፈንታ ብዙ ጊዜ ወደ ተስፋ መቁረጥና ወደ ጥፋት መርተዋል።
ከፍተኛ ከበሬታ ይሰጣቸው የነበሩት ራቢ አኪባ ቤን ጆሴፍ በ132 እዘአ ሳይመን ባር ኮክባን ሲቀበሉ “ይህ ንጉሡ መሲሕ ነው!” ብለው ነበር። ባርኮክባ ኃይለኛ ሠራዊት የነበረው ኃያል ሰው ነበር። ብዙ አይሁዶች ከሮማ የዓለም ኃያል መንግሥት ይደርስባቸው የነበረው የረዥም ዘመን ጭቆና እንዲያከትም የሚያደርግ ሰው አሁን ገና መጣ ብለው አስበው ነበር። ባር ኮክባ ግን ነፃ ሳያወጣቸው ቀረ። እንዲያውም በእርሱ ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአገሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ።
በ12ኛው መቶ ዘመን ሌላ አይሁዳዊ “መሲሕ” ብቅ ያለ ሲሆን በዚህ ጊዜ ግን ብቅ ያለው በየመን ነበር። እርሱንም የየመኑ ካሊፍ ወይም ገዢ መሲሕ ለመሆኑ ምልክት እንዲያሳይ በጠየቀው ጊዜ ምልክት እንዲሆን ካሊፉ ራሱን አስቆርጦ እንዲያስገድለውና ቅጽበታዊ ትንሣኤው ምልክት እንደሚሆን ነገረው። ካሊፉም በእቅዱ ተስማማና ራሱን አስቆረጠው። ይህም የየመኑ መሲሕ ፍጻሜ ሆነ። በዚሁ መቶ ዘመን ዴቪድ አልሮይ የሚባል ሰው በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ አይሁዳውያን በመላእክት ክንፎች እየበረሩ ወደ ቅድስቲቱ ምድር ተከትለውት እንዲሄዱ ነግሯቸው ነበር። ብዙ ሰዎችም እርሱ መሲሕ ነው ብለው አምነው ነበር። የባግዳድ አይሁዶች በሌቦች የሚዘረፉትን ቤቶቻቸውን ዞር ብለው ሳይመለከቱ በቤቶቻቸው ጣሪያ ላይ ሆነው በትዕግስት ይጠባበቁ ነበር።
ሳባቲ ዜቪ ደግሞ በ17ኛው መቶ ዘመን በሰምርኔስ ተነስቶ ነበር። እርሱም በመላው አውሮፓ ለነበሩ አይሁዶች መሲሕነቱን አወጀ። ክርስቲያኖችም ጭምር አዳምጠውት ነበር። ዜቪ ተከታዮቹ ያለ ገደብ ኃጢአት በማድረግ ነፃነት እንዲያገኙ ነገራቸው። የቅርብ ተከታዮቹ ጭፈራ፣ ራቁትነት፣ ምንዝርና በቅርብ ዘመዶቻቸው ላይ ዝሙት ከፈጸሙ በኋላ ራሳቸውን በግርፋት፣ ራቁታቸውን በበረዶና በጤዛ ላይ በመንከባለልና በቀዝቃዛ ጉድጓድ ውስጥ እስከ አንገታቸው ድረስ በመቅበር ይቀጡ ነበር። ዜቪ ወደ ቱርክ በሄደ ጊዜ ተያዘና እስላም እንዲሆን አለበለዚያ ግን እንደሚገደል ተነገረውና ሰለመ። በእርሱ ካመኑት ተከታዮቹ መካከል ብዙዎቹ ተበታተኑ። ሆኖም ዜቪ ከዚያ በኋላ በነበሩት ሁለት መቶ ዘመናት በአንዳንድ ሰዎች መሲሕ ተብሎ ሲጠራ ቆይቶአል።
ሕዝበ ክርስትናም የራሷን መሲሖች ፈጥራለች። በ12ኛው መቶ ዘመን ታንኬልም የተባለ ሰው የደጋፊዎቹን ሠራዊት አደራጅቶ የአንትዌርፕን ከተማ ወረረ። ይህ መሲሕ ራሱን አምላክ ብሎ ሰየመ። ገላውን የታጠበበትን ውኃ እንኳን ተከታዮቹ እንደ ፀበል እንዲጠጡት ይሸጥላቸው ነበር። ሌላው ክርስቲያን መሲሕ ደግሞ በ16ኛው መቶ ዘመን በጀርመን አገር የተነሳው ቶማስ ሙንትዘር ነበር። ይህ ሰው የአርማጌዶን ጦርነት ነው ብሎ ለተከታዮቹ በመንገር በአካባቢው የሲቪል ባለ ሥልጣኖች ላይ ዓመፅ እንዲነሳ አደረገ። የጠላቶቹን የመድፍ ጥይቶች በእጆቹ ለመያዝ እንደሚችል ተናግሮ ነበር። በዚህ ፈንታ ግን ሰዎቹ ተጨፈጨፉ። እርሱም ራሱን ተቆረጠ። ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ብዙ ሌሎች እንዲህ ዓይነት መሲሖች ተነስተዋል።
ሌሎች ሃይማኖቶችም የየራሳቸው መሲሖች ነበሯቸው። እስልምና የፍትሕ ዘመን ያመጣል የሚል ተስፋ የጣለበት ማህዲ ወይም በትክክል የተመራው ሰው የተባለ መሲሕ ነበረው። በሂንዱይዝም ውስጥ አንዳንድ ሰዎች አቫታሮች ወይም ሥጋ የለበሱ አማልክት እንደሆኑ ተናግረዋል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ እንደሚገልጸው “እንደ ቡድሂዝም ያለ መሲሕ አልባ ሃይማኖትም እንኳን ማሃያና የሚባሉ ቡድኖች ለወደፊቱ ታማኞቹን ወደ ገነት የሚያስገባ ቡድሃ ማትሬየ ከሰማያዊው መኖሪያው ይወርዳል ብለው እንዲያምኑ አድርጎአል።”
የ20ኛው መቶ ዘመን መሲሖች
በዚህ በእኛ መቶ ዘመን የእውነተኛ መሲሕ አስፈላጊነት ከምንጊዜውም ይበልጥ አጣዳፊ ሆኗል። በመሆኑም ብዙዎች መሲሕ ነን ብለው መምጣታቸው አያስደንቅም። በ1920ዎቹ፣ በ30ዎቹና በ40ዎቹ ዓመታት አፍሪካዊት አገር በሆነችው በኮንጎ ሲሞን ኪምባንጉና የእርሱ ወራሽ የሆነው አንድር “ኢየሱስ” ማትስዋ መሲሖች ናቸው የሚል ተቀባይነት አግኝተው ነበር። እነርሱም ሞቱ። ተከታዮቻቸው ግን እንደሚመለሱና የአፍሪካን የሺህ ዓመት ዘመን እንደሚያመጡ ተስፋ ያደርጋሉ።
በተጨማሪም በዚህ መቶ ዘመን በኒው ጊኒና በማሌኔሺያ “የጭነት አምልኮቶች” ተነስተዋል። የዚህ እምነት ተከታዮች ሙታንም እንኳን በሚነሱበት ዘመን ሀብታሞች በሚያደርጓቸውና የደስታ ዘመን በሚያመጡላቸው መሲሕ መሰል ነጮች የሚነዳ መርከብ ወይም አይሮፕላን ይመጣል ብለው ይጠባበቃሉ።
በኢንዱስትሪ የበለጸጉት አገሮችም የራሳቸው መሲሖች ነበሯቸው። አንዳንዶቹ ተከታዮቹ በሆኑ ቤተሰቦች አማካኝነት ዓለምን የማንፃት ዓላማ እንደነበረውና ራሱን የኢየሱስ ክርስቶስ ወራሽ እንዳደረገው እንደ ሱን ሚዩን ሙን የሃይማኖት መሪዎች ናቸው። ፖለቲካዊ መሪዎችም የመሲሕነትን ቦታ ለመያዝ የሞከሩ ሲሆን በዚህ ረገድ አስፈሪ ምሳሌ የሚሆነው ስለ ሺህ ዓመት ግዛት ታላቅ ንግግር ያደረገው አዶልፍ ሂትለር ነው።
ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎችና ድርጅቶችም መሲሐዊ ክብርና ማዕረግ ተሰጥቶአቸዋል። ለምሳሌ ያህል ዘ ኢንሳይክሎፒድያ ብሪታኒካ የማርክሲዝም ሌኒንዝም ፖለቲካዊ ንድፈ ሐሳብ መሲሐዊ ቅላጼ ወይም ባሕርይ እንዳለው ይገልጻል። ለዓለም ሰላም ብቸኛ ተስፋ እንደሆነ ሠፊ ተቀባይነት ያገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በብዙዎች አእምሮ የመሲሕነት ቦታ የተሰጠው ይመስላል።
እርግጠኛ ተስፋ ነውን?
ይህ አጭር አጠቃላይ መግለጫ የመሲሐዊ እንቅስቃሴዎች ታሪክ በአብዛኛው የከንቱ ስሜት፣ ያልተፈጸሙና ያለቦታቸው ያረፉ ተስፋዎችና ምኞቶች ታሪክ ብቻ እንደሆነ በጣም ግልጽ ያደርጋል። እንግዲያውስ በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በመሲሕ ለማመን ተጠራጣሪዎች መሆናቸው አያስደንቅም።
የሆነ ሆኖ መሲሐዊውን ተስፋ ፈጽመን ከመሰረዛችን በፊት የዚህ ተስፋ ምንጭ ምን እንደሆነ አስቀድመን ማወቅ ይኖርብናል። በመሠረቱ “መሲሕ” የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ነው። የዕብራይስጡ ቃል ማሺያክ ወይም “የተቀባው” ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ነገሥታትና ካህናት የሚሾሙት አንዳንድ ጊዜ ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ራሳቸው ላይ በማፍሰስ በሚከናወን ሥርዓተ ቅብዓት ነበር። ስለዚህ ማሺያክ የሚለው ስያሜ ለእነዚህ ነገሥታት ወይም ካህናት በትክክል ያገለግል ነበር። ያለምንም ሥርዓተ ቅብዓት ለልዩ ሥልጣን የተቀቡ ወይም የተሾሙ ሰዎችም ነበሩ። ሙሴ የአምላክ ነቢይና ወኪል ሆኖ ተመርጦ ስለነበረ በዕብራውያን 11:24-26 ላይ “ክርስቶስ” ወይም “የተቀባው” ተብሎ ተጠርቷል።
መሲሕ ለሚለው ቃል የተሰጠው “የተቀባው” የሚል ፍቺ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሲሖችን እስከ አሁን ካነሳናቸው የሐሰት መሲሖች ይለያቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሲሖች ራሳቸውን የሾሙ ወይም ደግሞ በሚወዷቸው ብዙሐን ተከታዮቻቸው የተመረጡ አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ የእነርሱ ሹመት የመጣው ከላይ፣ ከራሱ ከይሖዋ አምላክ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ብዙ መሲሖች የሚናገር ሲሆን ለአንደኛው መሲሕ ግን ከሌሎቹ ሁሉ የበለጠ ቦታ ይሰጠዋል። (መዝሙር 45:7) ይህ መሲሕ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ ማዕከላዊ ቦታ የያዘ ሲሆን ለሚበዙት መንፈስ አዳሽ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች መፈጸም ቁልፍ ነው። ይህ መሲሕ ዛሬ እኛን ከሚያጋጥሙን ችግሮች ጋር ይዋጋል።
የሰው ልጆች አዳኝ
የመጽሐፍ ቅዱስ መሲሕ የሰው ልጆችን ችግሮች ከሥር መሠረታቸው ይነቅላል። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የነበሩት አዳምና ሔዋን በዓመፀኛው መንፈሳዊ ፍጡር በሰይጣን አነሳሽነት በፈጣሪያቸው ላይ ባመፁ ጊዜ የአምላክን የመግዛት መብት መቀማታቸው ነበር። ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ራሳቸው ለራሳቸው መወሰን ፈለጉ። ይህን በማድረጋቸውም ከይሖዋ ፍቅራዊ ጥበቃ የሠፈነበት አስተዳደር ወጡና ሰብአዊው ቤተሰብ ራስን በራስ ወደ መግዛት ትርምስና መከራ፣ አለፍጽምናና ሞት እንዲወድቅ አደረጉ።—ሮሜ 5:12
ይሖዋ አምላክ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ጨለማ ሰፍኖ በነበረበት በዚህ ዘመን ይህን የተስፋ ጭላንጭል መስጠቱ ታላቅ ፍቅራዊ ድርጊት ነው። አምላክ በዓመፀኞቹ ሰዎች ላይ በፈረደበት ጊዜ ዘሮቻቸው አዳኝ እንደሚያገኙ ትንቢት ተናገረ። “ዘር” ተብሎ የተጠራው ይህ አዳኝ ሰይጣን በኤደን ያደረገውን መጥፎ ሥራ ሁሉ ይሽራል። ዘሩ “እባቡን” ሰይጣንን ከመኖር ውጭ ለማድረግ ራሱን ቀጥቅጦ ይደመስሰዋል።—ዘፍጥረት 3:14, 15
አይሁዶች ከጥንት ዘመን ጀምሮ ይህ ትንቢት መሲሑን የሚመለከት እንደሆነ ተረድተው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ላይ በብዛት ይጠቀሙባቸው በነበሩት የቅዱሳን ጽሑፎች ማብራሪያ የሆኑ አያሌ ታርጉሞች ላይ ይህ ትንቢት “ንጉሥ በሚሆነው መሲሕ ዘመን” እንደሚፈጸም ተገልጾአል።
ስለዚህ የእምነት ሰዎች ከመጀመሪያ ጀምሮ በዚህ በሚመጣው ዘር ወይም አዳኝ ተስፋ መደሰታቸው አያስደንቅም። ይሖዋ አምላክ ለአብርሃም ይህ ዘር በእርሱ የትውልድ መሥመር እንደሚመጣና በእርሱም የአብርሃም የራሱ ዘሮች ብቻ ሳይሆኑ “የምድር አሕዛብ ሁሉ” ራሳቸውን እንደሚባርኩ በነገረው ጊዜ ምን እንደተሰማው ገምት።—ዘፍጥረት 22:17, 18
መሲሑና መንግሥት
ቆይተው የተነገሩ ትንቢቶች ይህን ተስፋ ከጥሩ መንግሥት ወይም መስተዳድር ጋር አዛምደውታል። በዘፍጥረት 49:10 (የ1980 ትርጉም) ላይ የአብርሃም ዘር ስለነበረው ስለ ይሁዳ “‘ሴሎ’ ተብሎ የሚጠራው ሕዝቦች ሁሉ የሚታዘዙለትና ለዘላለም የሚነግሠው እስኪመጣ ድረስ በትረ መንግሥት (የገዢነት ሥልጣን) ከይሁዳ እጅ አይወጣም” ተብሎ ነበር። በግልጽ እንደሚታየው “ሴሎ” የሚመጣው ለመግዛት ነው። የሚገዛውም አይሁድን ብቻ ሳይሆን “ሕዝቦችን” ነው። (ከዳንኤል 7:13, 14 ጋር አወዳድሩት) ጥንታውያን አይሁዶች ሴሎ መሲሕ መሆኑን አውቀው ነበር። እንዲያውም አንዳንድ የአይሁድ ታርጉሞች “ሴሎ” የሚለውን ቃል “መሲሕ” ወይም “ንጉሡ መሲሕ” በሚል ቃል ተክተው ነበር።
በመንፈስ መሪነት የተጻፈው የትንቢት ብርሃን ማብራቱን በቀጠለ መጠን ስለ መሲሑ አገዛዝ ይበልጥ እየታወቀ መጣ። (ምሳሌ 4:18) በ2 ሳሙኤል 7:12-16 ላይ የይሁዳ ዘር ለሆነው ለንጉሥ ዳዊት ይህ ዘር የሚመጣው ከእርሱ የዘር ሐረግ እንደሆነ ተነገረው። በተጨማሪም ይህ ዘር የተለየ ንጉሥ መሆን ነበረበት። ዙፋኑ ወይም አገዛዙ ለዘላለም የሚጸና መሆን ነበረበት! ኢሳይያስ 9:6, 7 “እነሆ ሕፃን ተወልዶልናል! ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል! እርሱም መሪ ይሆናል፤ . . . ለንጉሣዊ ሥልጣኑ ወሰን የለውም፣ መንግሥቱ ዘላለማዊ ሰላም የሰፈነበት ይሆናል፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም እውነትና ፍትሕ የሰፈነበት መንግሥት በዳዊት ዙፋን ላይ ተመሥርቶ እንዲጸና ያደርገዋል፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ይህን ለማድረግ ወስኖአል”(1980 ትርጉም) በማለት ይህን ሐሳብ ይደግፋል።
እንዲህ ያለ መንግሥት ይኖራል ብለህ ልትገምት ትችላለህን? ሰላምን የሚያስከብርና ለዘላለም የሚገዛ ትክክለኛ ፈራጅና ጻድቅ መሪ ይሆናል። ይህስ በታሪክ ውስጥ ከታዩት የሐሰት መሲሖች አሳዛኝ መፈራረቅ ምንኛ የተለየ ነው! የመጽሐፍ ቅዱሱ መሲሕ ከንቱ ሐሳብ የወለደው፣ ራሱን የሾመ መሪ ሳይሆን የዓለምን ሁኔታዎች ለመለወጥ የሚያስፈልገው ኃይልና ሥልጣን ያለው የዓለም መሪ ነው።
ይህ ተስፋ በመከራ ለተዋጠው ዘመናችን በጣም ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። የሰው ልጅ ከአሁኑ ጊዜ የበለጠ እንዲህ ዓይነት ተስፋ ባስፈለገው አሳዛኝ ሁኔታ ሥር ወድቆ አያውቅም። ይሁን እንጂ በሐሰት ተስፋዎች በቀላሉ ልንጠመድ ስለምንችል እያንዳንዳችን፦ የናዝሬቱ ኢየሱስ ብዙዎች እንደሚያምኑበት በትንቢት የተነገረለት መሲሕ ነበርን? የሚለውን ጥያቄ በጥንቃቄ መመርመራችን በጣም አስፈላጊ ነው። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ይህን ጥያቄ የሚመለከት ይሆናል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኘው ሥዕል ምንጭ]
የብሩክሊኑ መሲሕ
እስራኤል ውስጥ በቅርቡ ሥዕላዊ መግለጫዎች፣ የንግድ ማስታወቂያ ሰሌዳዎችና በመብራት የሚሠሩ የማስታወቂያ ጽሑፎች “ለመሲሑ መምጣት ተዘጋጁ” የሚል ማስታወቂያ በሠፊው አስተጋብተዋል። ይህ 400,000 ዶላር የፈጀ የማስታወቂያ ዘመቻ የተደረገው በእንግሊዝኛ ሉባቪቸርስ ተብለው በሚጠሩት የሐሲዳውያን አይሁዶች አክራሪ ኑፋቄ ነበር። ይህ 250,000 አባሎች ያሉት ቡድን በብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚኖሩት ታላቁ ራቢ ሜናኺም መንድል እስክኔርሰን መሲሕ ናቸው ብሎ ያምናል። ለምን? እስክኔርሰን መሲሕ በዚህ ትውልድ ዘመን ይመጣል ብለው ያስተምራሉ። በኒውስዊክ መጽሔት መሠረት የሉባቪቸር ባለ ሥልጣኖች በ90 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙት ራቢ መሲሑ ሳይመጣ አይሞቱም ብለው ያምናሉ። ይህ ሃይማኖታዊ ቡድን በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት እያንዳንዱ ትውልድ መሲሕ ለመሆን ብቃት ያለው ቢያንስ አንድ ሰው ሲያስገኝ ቆይቶአል ብሎ ያስተምራል። እስከኔርሰን እንዲህ ዓይነት ሰው ማለት መሲሕ ለመሆን ብቃት ያላቸው እንደሆኑ ተከታዮቻቸው ያምናሉ። የእርሳቸው ተተኪ የሚሆነውን ሰው ግን ገና አልሾሙም። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ አይሁዶች መሲሕነታቸውን አይቀበሉም ይላል ኒውስዊክ። ኒውስዴይ በተሰኘው ጋዜጣ መሠረት ተፎካካሪያቸው የሆኑት የ96 ዓመቱ ራቢ ኤሊኤዘር ሻክ “ሐሰተኛ መሲሕ” ብለዋቸዋል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ]
ብዙ ሰዎች የቀርጤሱ ሙሴ መሲሕ ነው ብለው ማመናቸው ሕይወታቸውን እንዲያጡ አድርጎአቸዋል