የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 11/1 ገጽ 4-7
  • ኃጢአት የሌለበት ዓለም እንዴት ይገኛል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኃጢአት የሌለበት ዓለም እንዴት ይገኛል?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኃጢአት ምንድን ነው?
  • የኃጢአት ምንጭ
  • ሰዎች ኃጢአትን ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት
  • ከኃጢአት ነፃ መውጣት
  • ኃጢአት የማይኖርበት ጊዜ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ‘በክቡር ደም’ ተዋጅተናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • ኃጢአት
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 11/1 ገጽ 4-7

ኃጢአት የሌለበት ዓለም እንዴት ይገኛል?

በአንድ የክረምት ማለዳ ላይ እርዳታ ለማግኘት የሚጣራ ድምፅ በቶኪዮ ውስጥ ይገኙ የነበሩትን ሰላማዊ ጎረቤቶች ጸጥታ በጠበጠው። ጋዜጣ አዳይ የነበረችውን ሴት እያሳደዱ በተደጋጋሚ በጩቤ ሲወጓት ከአምስት እስከ አሥር ደቂቃ ለሚያህል ጊዜ ታሰማው የነበረውን የሚያሳዝን ድምፅ የሰሙ ብዙ ሰዎች ሰምተዋል። ምን እየተደረገ እንዳለ ለማወቅ የሞከረ አንድም ሰው አልነበረም። እሷም ብዙ ደም ስለፈሰሳት ሞተች። “ልክ ጩኸቷን እንደሰሙ ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ሁኔታውን ለፖሊስ ሪፖርት ቢያደርግ ኖሮ ሕይወቷ ሊተርፍ ይችል ነበር” ሲል አንድ መርማሪ ፖሊስ ተናገረ።

ምንም እንኳን እየሞተች የነበረችውን ሴት የሰሟት ሰዎች እሷን በቸልታ ከማለፍ የበለጠ ምንም ነገር ባያደርጉም ከበደለኝነት ስሜት ነፃ እንደሆኑ ሊናገሩ ይችላሉን? ጩኸቷን ሰምቶ የነበረ አንድ ሰው “ስለ ግድያው ከሰማሁ በኋላ ዐርብ ዕለት ቀኑን ሙሉ ሕሊናዬ ሲያሰቃየኝ ዋለ” በማለት ተናገረ። ይህም በእርግጥ ኃጢአት ምን ይሆን? ብለን እንድናስብ ያደርገናል።

ኃጢአት ምንድን ነው?

በቶኪዮ ጃፓን ውስጥ የሆሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የነበሩ ጡረታ የወጡ ሂዴኦ ኦዳጊሪ የተባሉ ሰው ኃጢአተኝነትን የመገንዘብን ሁኔታ አስመልክተው በአሳሂ ሺምቡን ጋዜጣ ላይ “በሕፃናት ላይ እንዳለው መጥፎ የሆነ ራስን ብቻ የመውደድ ሁኔታ፣ አሳፋሪ ቅናት፣ ድብቅ እንደሆነ ክህደት ያሉ ግልጽ የሆኑ ኃጢአትን የመገንዘብ ትዝታዎቼን ላጠፋቸው አልቻልኩም። ይህ ሐሳብ በአእምሮዬ ውስጥ የተቀረጸውና ገና በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ ነበር፤ እስካሁንም ያሠቃየኛል” ብለው ተናግረዋል። እንዲህ ያሉ ስሜቶች ተሰምተውህ ያውቃሉን? ስህተት እንደሆነ እያወቅህ አንድ ነገር ብታደርግ አንተን የሚወቅስህ አንድ ውስጣዊ ድምፅ አለህን? ምናልባት ምንም ወንጀል አልተፈጸመ ይሆናል፤ ነገር ግን አንድ ደስ የማይል ስሜት አእምሮህ ውስጥ እየተጉላላ ጭንቀት ያሳድርብሃል። እንዲህ ከሆነ ሕሊና የሚባል ነገር በውስጥህ እየሠራ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም ይህንን ቀጥሎ ባለው ጥቅስ ውስጥ ይገልጸዋል፦ “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፣ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳን ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፤ እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፣ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።” (ሮሜ 2:14, 15) አዎን፣ አብዛኞቹ ሰዎች እንደ ዝሙት፣ ስርቆትና ውሸት ያሉትን ድርጊቶች ሲፈጽሙ በተፈጥሯቸው የመረበሽ ስሜት ይሰማቸዋል። ሕሊናቸው ኃጢአት መሥራታቸውን እየመሠከረባቸው ነው።

ይሁን እንጂ የሕሊና ድምፅ በተደጋጋሚ ቸል ሲባል አስተማማኝ ጠባቂ ሆኖ ማገልገሉን ያቆማል። በድንና የረከሰ ይሆናል። (ቲቶ 1:15) መጥፎ ለሆነው ነገር ቶሎ የሚሰማን ስሜት ይጠፋል። እንዲያውም በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች ኃጢአትን በሚመለከት ሕሊናቸው ሞቷል።

የኃጢአት መለኪያ ሕሊና ብቻ ነው ወይስ እንደ ኃጢአት ተደርጎ መቆጠር ያለበት ምን እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን የሚያገለግል ትክክለኛ የአቋም መመዘኛ አለ? ከ3,000 ዓመታት በፊት አምላክ ለተመረጡት ሕዝቦቹ ሕግ ሰጥቷቸው ነበር፤ በዚህም ሕግ አማካኝነት “ኃጢአት ምንነቱ” ታወቀ። (ሮሜ 7:13, የ1980 ትርጉም) በፊት ተቀባይነት የነበረው አኗኗር እንኳን ኃጢአት መሆኑ ተገለጸ። የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች የነበሩት እስራኤላውያን ኃጢአተኞች ሆነው ተጋለጡ፤ በመሆኑም በኩነኔ ሥር ነበሩ።

ሕሊናችን የሚያስገነዝበንና የሙሴ ሕግ ለይቶ የመዘገባቸው ኃጢአቶች ምንድን ናቸው? እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም ኃጢአት የሚለው ቃል ፈጣሪን በተመለከተ አንድ ነገር ማጉደል ማለት ነው። ከእርሱ ጠቅላላ ባሕርያት፣ የአቋም ደረጃ፣ መንገድና ፈቃድ ጋር የማይስማማ ማንኛውም ነገር ኃጢአት ነው። እሱ ያቋቋመውን ደረጃ ያጎደለ ማንኛውም ፍጥረት በሕይወት መኖሩን እንዲቀጥል ሊፈቀድለት አይችልም። ስለዚህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ልዩ ሕግ አዋቂ የነበረው ሰው ዕብራውያን ክርስቲያኖችን፦ “ወንድሞች ሆይ፣ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (ዕብራውያን 3:12) አዎን፣ በፈጣሪ አለማመን ትልቅ ኃጢአት ይሆንብናል። በዚህ መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ኃጢአት በተለምዶ እንደ ኃጢአት ተደርጎ ከሚቆጠረው ነገር የሰፋ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” ብሎ እስከመናገር ይደርሳል።—ሮሜ 3:23

የኃጢአት ምንጭ

ይህ ማለት ሰው የተፈጠረው ኃጢአተኛ ሆኖ ነው ማለት ነው? አይደለም፤ የሰው ሕይወት አመንጪ የሆነው ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያውን ሰው የሠራው ፍጹም ፍጡር አድርጎ ነበር። (ዘፍጥረት 1:26, 27፤ ዘዳግም 32:4) ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹ ሰብአውያን ባልና ሚስት አምላክ የከለከለውን አንድ ነገር ጥሰው “መልካምና ክፉውን ከሚያስታውቀው ዛፍ” ሲበሉ ጎደሎዎች ሆኑ። (ዘፍጥረት 2:17) ፍጹም ሆነው ቢፈጠሩም እንኳን ለአባታቸው ፍጹም ታዛዥነትን በማጉደላቸው ኃጢአተኞች ሆኑ፤ በዚህም ምክንያት እንዲሞቱ ተረገሙ።

ይህ የጥንት ታሪክ ዛሬ ካለው ኃጢአት ጋር ምን ግንኙነት አለው? መጽሐፍ ቅዱስ “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” ሲል ያብራራል። (ሮሜ 5:12) ማንም ከማንም ሳይለይ ሁላችንም በውርሻ ምክንያት ኃጢአተኞች ነን፤ በዚህም ምክንያት ከሞት እርግማን ሥር ነን።—መክብብ 7:20

ሰዎች ኃጢአትን ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት

አዳም ኃጢአትን ለዝርያዎቹ አስተላልፏል፤ ይሁን እንጂ ከአምላክ የሚገኘውንም ሕሊናን አስተላልፎአል። ኃጢአት ጭንቀት እንዲሰማን ሊያደርግ ይችላል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሰዎች እንዲህ ያሉትን ስሜቶች ለማስታገስ የተለያዩ ዘዴዎችን ፈጥረዋል። ይሁን እንጂ በእርግጥ ጥሩ ውጤት የሚሰጡ ናቸውን?

በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ ዓለም ያሉ ሰዎች የአቋም ደረጃቸውን በመለዋወጥ ወይም የኃጢአትን መኖር ራሱ በመካድ ኃጢአት ያመጣቸውን ጉዳቶች ለመቋቋም ሞክረዋል። (1 ጢሞቴዎስ 4:1, 2) የሰው ልጅ የኃጢአተኝነት ሁኔታ ትኩሳት ከያዘው በሽተኛ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ኃጢአት ያንን የበሽታ ምልክት ካስከተለው ቫይረስ ጋር ሲወዳደር የተረበሸው ሕሊና ደግሞ ከሚያስጨንቀው ትኩሳት ጋር የሚወዳደር ነው። የሙቀት መለኪያውን መስበሩ በሽተኛው ከፍተኛ ትኩሳት ያለው የመሆኑን ሐቅ አይለውጠውም። በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ብዙዎች እንዳደረጉት የሥነ ምግባር ደረጃዎችን አሽቀንጥሮ መጣልና የራስን ሕሊና ምስክርነት ችላ ማለት ኃጢአትን ራሱን ለመፋቅ ምንም አይረዳም።

አንድ ሰው ትኩሳቱን ለማስታገስ በሰውነቱ ላይ በረዶ ያደርግ ይሆናል። ይህም የሕሊናን ውጋት ለማስታገስ ሲባል በሺንቶ የማንጻት ሥነ ሥርዓቶች ካንገት በላይ የሆኑ ነገሮችን እንደማድረግ ያህል ነው። በረዶው ትኩሳት የያዘውን በሽተኛ ለጊዜው ትኩሳቱን ያቀዘቅዝለት ይሆናል፤ ነገር ግን የትኩሳቱን መንሥኤ አያስወግደውም። በኤርምያስ ዘመን የነበሩት ካህናትና ነቢያትም በጊዜው ለነበሩት እስራኤላውያን ተመሳሳይ የሆነ ፈውስ ለማድረግ ሞክረው ነበር። “ሁሉም ነገር ደህና ነው፣ ሁሉም ነገር ደህና ነው” እያሉ የሕዝቡን የመንፈሳዊና የሞራል ቁስሎች “በጥቂቱ” ፈውሰው ነበር። (ኤርምያስ 6:14፤ 8:11 አሜሪካን ትራንስሌሽን) ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችና “ሁሉም ነገር ደህና ነው” እያሉ ማዜም የአምላክን ሕዝብ የሞራል ስብራት አይጠግንም፤ የማንጻት ሥርዓቶችም ዛሬ ያለውን የሕዝቡን የሥነ ምግባር ትምህርት አይለውጡትም።

ትኩሳት የያዘው ሰው የትኩሳት መቀነሻ መድኃኒት በመውሰድ ትኩሳቱን ማብረድ ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ቫይረሱ አሁንም ቢሆን በሰውነቱ ውስጥ ነው። ኮንፊዩሺያኖች ክፋትን በትምህርት ለማጥፋት የሚያደርጉት ሙከራም ከዚህ ያልተለየ ነው። ሊ ላይ ላዩን ሰዎች ከክፋት እንዲመለሱ ይረዳ ይሆናል፤ ነገር ግን ሊን በተግባር ላይ ማዋል ኃጢአተኛው ባሕርይ እንዳይወጣ አግዶ ይይዛል እንጂ የክፋት ድርጊቶች ዋና ምንጭ የሆነውን ሰውየው አብሮት የተወለደበትን የኃጢአት ዝንባሌ አያስወግድም።—ዘፍጥረት 8:21

ቡድሂስቶች አንድ ሰው ከኃጢአት ዝንባሌዎች የሚነፃበት አድርገው የሚያስተምሩት ኒርቫና ስለመግባት የሚናገረው ትምህርትስ? የኒርቫና ሁኔታ ትርጉም “ማጥፋት” ማለት ሲሆን ሊገለጽ የማይችል የስሜቶችና የፍላጎቶች ሁሉ ማጥፊያ ተደርጎ ይገመታል። አንዳንዶች የግለሰቡ ሕይወት የሚቋረጥበት ሁኔታ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። ይህስ ትኩሳት የያዘውን በሽተኛ ፋታ ለማግኘት መሞት እንዳለበት የመንገር ያህል አይሆንምን? ከዚህም በተጨማሪ በኒርቫና ሁኔታ ውስጥ መገኘት በጣም ከባድና የማይቻል ነው ተብሎ ይታሰባል። ይህ ትምህርት የተረበሸ ሕሊና ያለን ሰው ሊረዳ ይችላልን?

ከኃጢአት ነፃ መውጣት

ሕይወትንና የኃጢአት ዝንባሌዎችን የሚመለከቱ የሰው ፍልስፍናዎች ግፋ ቢል ሊያደርጉ የሚችሉት ነገር የአንድን ሰው ሕሊና ማረጋጋት ብቻ እንደሆነ ግልጽ ነው። የኃጢአተኝነትን ሁኔታ አያስወግዱም። (1 ጢሞቴዎስ 6:20) ይህንን የኃጢአተኝነት ሁኔታ ለማስወገድ የሚቻልበት መንገድ አለን? በቅርብ ምሥራቅ ውስጥ የተጻፈ የጥንት መጽሐፍ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከኃጢአት ነፃነት የምንወጣበትን ቁልፍ የሆነ ነገር እናገኛለን። “ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች። . . . እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፣ የምድርን በረከት ትበላላችሁ።” (ኢሳይያስ 1:18, 19) እዚህ ላይ ይሖዋ እየተናገረ ያለው የተመረጡ ሕዝቦቹ ቢሆኑም ለእሱ ሊኖራቸው የሚገባውን ንጹሕ አቋም አጉድለው ለነበሩት እስራኤላውያን ነበር። ለሰው ልጆችም ሁሉ የሚሠራው መሠረታዊ ሥርዓት ይኸው ነው። አንድ ሰው ኃጢአቱ እንዲነጻለትና እንዲታጠብለት የሚያደርግበት ቁልፍ የሆነ ነገር ነው። የፈጣሪን ቃል ለመስማት ፈቃደኝነትን ማሳየት ነው።

የሰው ልጆችን ኃጢአት ማጠብን በተመለከተ የአምላክ ቃል ምን ይነግረናል? መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ሰው ምክንያት ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች እንደሆኑ ሁሉ ለአምላክ ፍጹም ታዛዥነት ባሳየ ሌላ ሰው በኩል ደግሞ ታዛዥ የሆኑት የሰው ዘሮች ከመከራ ነፃ እንደሚወጡ ይናገራል። (ሮሜ 5:18, 19) እንዴት? “ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶልናልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።” (ሮሜ 5:8) ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያው አዳም ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት ከነበረበት ሁኔታ ጋር በሚስተካከል መንገድ ሰው ሆኖ በመወለዱ የሰውን ልጆች ኃጢአት ለማስወገድ ቻለ። (ኢሳይያስ 53:12፤ ዮሐንስ 1:14፤ 1 ጴጥሮስ 2:24) ኢየሱስ እንደ ወንጀለኛ ሆኖ በመከራ እንጨት ላይ በመሞቱ የሰውን ዘር ከኃጢአትና ከሞት እስራት አስፈትቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች “ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና። . . . ኃጢአትም በሞት እንደ ነገሠ፣ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በጽድቅ ምክንያት ለዘላለም ሕይወት ይነግሥ ዘንድ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ” በማለት ገልጾላቸዋል።—ሮሜ 5:6, 21

ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ በመሞት በአዳም ተዛንፎ የነበረውን ሚዛን ማስተካከሉ የ“ቤዛው” ዝግጅት ተብሎ ይጠራል። (ማቴዎስ 20:28) ትኩሳት የሚያስከትለውን ቫይረስ ከሚያዳክመው መድኃኒት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። የኢየሱስን የቤዛ ዋጋ በሰው ልጆች ላይ እንዲሠራ በማድረግ በኃጢአት ምክንያት በሰው ልጆች ላይ የመጣው ደካማነት፣ ሞት ራሱ እንኳን ሊፈወስ ይችላል። ይህ የመፈወስ ሂደት በመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ ውስጥ “በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፣ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ” በማለት በምሳሌያዊ ሁኔታ ተገልጿል። (ራእይ 22:2) ምሳሌያዊው የሕይወት ውኃ ቅጠሎቻቸው በሙሉ ለሰው ዘር መፈወሻ በሚሆኑት ዛፎች መካከል ሲፈስ እስቲ አስበው! እነዚህ በመለኮታዊ አነሳሽነት የተገለጹ ምልክቶች አምላክ የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት በማድረግ የሰውን ዘር ወደ ፍጽምና መልሶ ለማምጣት ያለውን ዝግጅት ይወክላሉ።

የራእይ መጽሐፍ ትንቢታዊ ራእዮች በቅርቡ እውን ይሆናሉ። (ራእይ 22:6, 7) ከዚያም የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ዋጋ ሙሉ በሙሉ በሰው ልጆች ላይ ሲሠራ ቅን ልብ ያላቸው ሁሉ ፍጹማን በመሆን “ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት” ይደርሳሉ። (ሮሜ 8:21) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መፈጸማቸው ይህ ክብራማ ነፃነት ቅርብ እንደሆነ ያመለክታል። (ራእይ 6:1-8) በቅርቡ አምላክ የክፋትን ዓለም ያስወግድና ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት በማግኘት ይደሰታሉ። (ዮሐንስ 3:16) ያ ዓለም በእርግጥም ኃጢአት የሌለበት ዓለም ይሆናል!

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት እዚህ ላይ እንደሚታየው ያሉ ቤተሰቦችን ዘላለማዊ ደስታ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ