የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 7/15 ገጽ 4-7
  • ኃጢአት የማይኖርበት ጊዜ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኃጢአት የማይኖርበት ጊዜ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሰው የተፈጠረው ያለ ኃጢአት ነው
  • የኃጢአት አጀማመር
  • ሕሊና ‘ይከሳል’ ወይም ‘ያመካኛል’
  • ከኃጢአት ነፃ መሆን​—⁠እንዴት?
  • የክርስቶስ ቤዛ ለእኛ ምን ሊያደርግልን እንደሚችል
  • የክርስቶስ ቤዛ የአምላክ የመዳን መንገድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ኃጢአት የሌለበት ዓለም እንዴት ይገኛል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ይሖዋ “በብዙ ሰዎች ምትክ . . . ቤዛ” አዘጋጀ
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
  • ኢየሱስ ያድናል—እንዴት?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 7/15 ገጽ 4-7

ኃጢአት የማይኖርበት ጊዜ

“ስንወለድ ጀምሮ ኃጢአተኞች ነን?” በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንደ ጀመረ አካባቢ ይህ ጥያቄ ግራ አጋብቶት ነበር። በሂንዱ እምነት ውስጥ ተወልዶ ያደገ በመሆኑ የተወረሰ ኃጢአት የሚለው ሐሳብ ለእርሱ ፈጽሞ እንግዳ ነገር ነበር። ይሁን እንጂ በእርግጥ ኃጢአት የሚወረስ ከሆነ እውነታውን አለመቀበል ወይም ችላ ማለት ምንም ዋጋ እንደ ሌለው አሰበ። አንድ ሰው ለዚህ ዓይነቱ ጥያቄ መልስ ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው?

ኃጢአት የሚወረስ ከሆነ መጀመሪያ አለው ማለት ነው። የመጀመሪያው ሰው ክፉ ሆኖ ተፈጥሮ ከዚያ በኋላ የክፋት ባሕርያትን ለልጆቹ አስተላልፎ ነውን? ወይስ ጉድለቱ ብቅ ያለው ከጊዜ በኋላ ነው? ኃጢአት በትክክል የጀመረው መቼ ነው? በሌላው በኩል ደግሞ ኃጢአት ውጫዊ፣ ክፉ ሐሳብ ወይም ክፉ መሠረታዊ ሥርዓት ከሆነ ከኃጢአት ነፃ እንሆናለን ብለን ተስፋ ማድረግ እንችላለንን?

እንደ ሂንዱ እምነት ከሆነ ሥቃይና ክፋት ከሰው ጋር አብረው የተፈጠሩ ነገሮች ናቸው። “ሥቃይ [ወይም ክፋት] ልክ ሥር እንደ ሰደደ የቁርጥማት በሽታ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይዘዋወራል እንጂ ሙሉ በሙሉ ሊወገድ አይችልም” በማለት አንድ ህንዳዊ ምሁር ይገልጻሉ። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ክፋት በዓለም ላይ ያሉ የሰው ዘሮች ክፍል ሆኖ ቆይቷል። ኃጢአት ከሰው ልጅ የታሪክ መዝገብ ቀደም ብሎ የነበረ ከሆነ የኃጢአትን አጀማመር ሊናገር የሚችል አስተማማኝ የሆነ መልስ ከሰው በላይ ከሆነ ምንጭ መገኘት ይኖርበታል። መልሱን መስጠት ያለበት አምላክ ነው።​—⁠መዝሙር 36:​9

ሰው የተፈጠረው ያለ ኃጢአት ነው

የሰውን አፈጣጠር አስመልክቶ ቬዳ በተባሉት የሂንዱ ቅዱሳን መጻሕፍት የተሰጡት ማብራሪያዎች ምሳሌያዊ እንደሆኑ የሂንዱ ፈላስፋ ኒኪክሂላናንዳ አምነው ተናግረዋል። በተመሳሳይም አብዛኞቹ የምሥራቅ ሃይማኖቶች ፍጥረትን በሚመለከት የሚሰጡት ማብራሪያ አፈ ታሪክ ከመሆን አያልፍም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያውን ሰው አፈጣጠር በሚመለከት የሚናገረውን ዘገባ ለማመን የሚያበቁ አሳማኝና ሳይንሳዊ ምክንያቶች አሉ።a የመጀመሪያው ምዕራፍ “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ይላል።​—⁠ዘፍጥረት 1:​27

“በእግዚአብሔር መልክ” መፈጠር ማለት ምን ማለት ነው? በአጭር አነጋገር ሰው ከእንስሳት የሚለይባቸውን እንደ ፍትሕ፣ ጥበብና ፍቅር የመሰሉ አምላካዊ ባሕርያት ኖሮት በአምላክ አምሳያ ተሠርቷል ማለት ነው። (ከቆላስይስ 3:​9, 10 ጋር አወዳድር።) እነዚህ ባሕርያት ጥሩ የሆነውን ወይም መጥፎ የሆነውን ነገር መርጦ የማድረግ ችሎታ ስለሚሰጡት የመምረጥ ነፃነት እንዲኖረው አድርገውታል። የመጀመሪያው ሰው ኃጢአት አልነበረበትም፤ ሲጠፈርም በሕይወቱ ውስጥ ክፋትም ሆነ ሥቃይ አልነበረም።

ይሖዋ አምላክ አዳም ለተባለው ሰው የሚከተለውን ትእዛዝ ሰጠው:- “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።” (ዘፍጥረት 2:​16, 17) አዳምና ሚስቱ ሔዋን መታዘዝን በመምረጥ ለፈጣሪያቸው ውዳሴና ክብር በማምጣት ከኃጢአት ነፃ ሆነው መኖር ይችሉ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ታዛዥ ያለመሆን ድርጊት አምላክ ያወጣቸውን ፍጹም የአቋም ደረጃዎች ማሟላት እንደማይችሉ ስለሚያመለክት ፍጹማን ያልሆኑ ኃጢአተኞች ያደርጋቸዋል።

አዳምና ሔዋን መለኮት ሆነው አልተፈጠሩም። ይሁን እንጂ መጠነኛ የሆነ መለኮታዊ ባሕርያትና የሥነ ምግባር ውሳኔዎችን የማድረግ ችሎታ ነበራቸው። የአምላክ ፍጥረት በመሆናቸው ኃጢአት የሌለባቸው ወይም ፍጹማን ነበሩ። (ዘፍጥረት 1:​31፤ ዘዳግም 32:​4) የእነርሱ ወደ ሕልውና መምጣት ከእነርሱ መፈጠር በፊት በአምላክና በአጽናፈ ዓለማት መካከል ለረዥም ዘመናት ተጠብቆ የኖረውን አንድነት አላናጋም። ታዲያ ኃጢአት የጀመረው እንዴት ነው?

የኃጢአት አጀማመር

ኃጢአት ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያለው በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ነው። ከምድርና ከሰው መፈጠር በፊት አምላክ የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ፍጥረታት ማለትም መላእክትን ፈጥሮ ነበር። (ኢዮብ 1:​6፤ 2:​1፤ 38:​4-7፤ ቆላስይስ 1:​15-17) ከእነዚህ መላእክት መካከል አንዱ በነበረው ውበትና እውቀት ታበየ። (ከሕዝቅኤል 28:​13-15 ጋር አወዳድር።) አምላክ አዳምና ሔዋን ልጅ እንዲወልዱ ከሰጠው መመሪያ መላዋ ምድር ጻድቅ በሆኑና አምላክን በሚያመልኩ ሰዎች እንደምትሞላ ይህ መልአክ አስቀድሞ ለመገንዘብ ችሎ ነበር። (ዘፍጥረት 1:​27, 28) ይህ መንፈሳዊ ፍጡር የእነርሱን አምልኮ ለማግኘት በእጅጉ ቋመጠ። (ማቴዎስ 4:​9, 10) ይህን ምኞት ማብሰልሰሉ የተሳሳተ እርምጃ እንዲወስድ አደረገው።​—⁠ያዕቆብ 1:​14, 15

ክፉው መልአክ በአንድ እባብ አማካኝነት ሔዋንን በማነጋገር አምላክ መልካሙንና ክፉዉን ከሚያስታውቀው ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ በመከልከል ሊኖራት የሚገባውን እውቀት እንደከለከላት ተናገረ። (ዘፍጥረት 3:​1-5) እንዲህ ያለው ንግግር ጥላቻ ያዘለ ውሸት ማለትም ኃጢአት ነበር። ይህን ውሸት በመናገር መልአኩ ራሱን ኃጢአተኛ አደረገ። በዚህም ምክንያት ዲያብሎስ ማለትም ስም አጥፊና ሰይጣን ማለትም የአምላክ ተቃዋሚ ሆነ።​—⁠ራእይ 12:​9

ሰይጣን በማግባባት የሰነዘረው ሐሳብ በሔዋን ላይ ጎጂ ተጽዕኖ አሳድሯል። ፈታኙ በተናገራቸው ቃላት ላይ እምነት በመጣሏ ተታለለችና ከተከለከለው ዛፍ ፍሬ ወስዳ በላች። ባሏ አዳምም ፍሬውን ከእርሷ ጋር በላ፤ በዚህ መንገድ ሁለቱም ኃጢአተኞች ሆኑ። (ዘፍጥረት 3:​6፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:​14) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አምላክን ላለመታዘዝ በመምረጣቸው የፍጽምናን ደረጃ በመሳት ራሳቸውን ኃጢአተኞች አደረጉ።

የአዳምና የሔዋን ዘሮችስ? መጽሐፍ ቅዱስ “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” በማለት ያብራራል። (ሮሜ 5:​12) የዘር ውርስ ሕግ በዚያው ጊዜ ሥራውን ጀመረ። አዳም የሌለውን ነገር ለልጆቹ ማስተላለፍ አልቻለም። (ኢዮብ 14:​4) የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ልጆች በወለዱበት ጊዜ ፍጽምናቸውን ያጡ ኃጢአተኞች ነበሩ። በዚህም የተነሳ አንድም ሰው ሳይቀር ሁላችንም ኃጢአት ወረስን። (መዝሙር 51:​5፤ ሮሜ 3:​23) ስለሆነም ኃጢአት ክፋትንና ሥቃይን ከማምጣት ባሻገር የፈየደው ምንም ነገር አልነበረም። ከዚህም በላይ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት” በመሆኑ ሁላችንም እናረጃለን እንዲሁም እንሞታለን።​—⁠ሮሜ 6:​23

ሕሊና ‘ይከሳል’ ወይም ‘ያመካኛል’

በተጨማሪም ኃጢአት በመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ላይ ያስከተለውን የባሕርይ ለውጥ ልብ በል። ከፊል አካላቸውን ሸፈኑና ራሳቸውን ከአምላክ ለመደበቅ ሞከሩ። (ዘፍጥረት 3:​7, 8) ስለዚህም ኃጢአት የጥፋተኝነት፣ የስጋትና የሃፍረት ስሜት እንዲከናነቡ አደረገ። በዛሬው ጊዜ ያለው የሰው ዘርም እነዚህን ስሜቶች ጠንቅቆ ያውቃቸዋል።

ለተቸገረ ሰው ደግነት ከማሳየት ወደኋላ በማለቱ ምክንያት የመረበሽ ስሜት የማይሰማው ወይም መነገር የማይገባውን ቃል በመናገሩ የጸጸት ስሜት የማያድርበት የትኛው ሰው ነው? (ያዕቆብ 4:​17) እንዲህ ያለ የሚቆረቁር ስሜት የሚያድርብን ለምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በልባችን ውስጥ ሕግ ተጽፏል’ በማለት ያብራራል። ሕሊናችን እስካልደነዘዘ ድረስ ያንን ሕግ መጣስ በውስጣችን የስሜት መረበሽ እንዲፈጥር ማድረጉ የማይቀር ነው። ስለዚህም ‘የሚከሰን’ ወይም ‘የሚያመካኘው’ ያ የሕሊና ድምፅ ነው። (ሮሜ 2:​15፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:​2፤ ቲቶ 1:​15) ተገነዘብነውም አልተገነዘብነውም በውስጣችን የጥፋተኝነት ስሜት ማለትም ኃጢአት አለ!

ጳውሎስ የኃጢአት ዝንባሌ እንደነበረው አሳምሮ ያውቅ ነበር። “እንግዲያስ መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ” በማለት የእምነት ቃሉን ሰጥቷል። “በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።” በዚህም የተነሳ ጳውሎስ “ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?” በማለት ጠይቋል።​—⁠ሮሜ 7:​21-24

ከኃጢአት ነፃ መሆን​—⁠እንዴት?

“በሂንዱ ባህል መሠረት ነፃ መውጣት” ይላሉ አንድ ምሁር “ድግግሞሽ ከሆነው ከመወለድና ከመሞት ነፃ መሆን ማለት ነው።” በተመሳሳይም ቡዲሂዝም እንደ መፍትሄ አድርጎ ውጫዊ እውነታን የመርሳት ሁኔታን ማለትም ኒርቫናን ይጠቅሳል። ሂንዱኢዝም ኃጢአት ስለ መውረስ የሚናገረውን ጽንሰ ሐሳብ ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ ከሕልውና ማምለጥን ብቻ የሚመለከት ተስፋ ይሰጣል።

በሌላው በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገርለት ነፃነት የኃጢአተኝነትን ዝንባሌ ሙሉ በሙሉ በማስወገድ የሚገኝ ነፃነት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ከኃጢአት እንዴት ሊድን እንደሚችል ጥያቄ ካቀረበ በኋላ “በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” በማለት ወዲያው መልሱን ይሰጣል። (ሮሜ 7:​25) አዎን፣ መዳን የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከአምላክ ነው።

የማቴዎስ ወንጌል እንደሚገልጸው “የሰው ልጅ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ለመስጠት’ መጥቶ ነበር። (ማቴዎስ 20:​28) ጳውሎስ በ1 ጢሞቴዎስ 2:​6 (NW) ላይ ኢየሱስ “ለሁሉም ተመጣጣኝ የሆነ ቤዛ ሰጠ” በማለት ጽፏል። “ቤዛ” የሚለው ቃል ምርኮኞችን ለማስፈታት የሚከፈልን ዋጋ ያመለክታል። ተመጣጣኝ ቤዛ የሚለው አነጋገር የተከፈለው ዋጋ በፍትህ አንፃር ሲታይ ዝንፍ ሳይል ሚዛኑን የጠበቀ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ይሁን እንጂ የአንድ ሰው ሞት “ለሁሉም ተመጣጣኝ ቤዛ” እንደሆነ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችለው እንዴት ነው?

አዳም ሁሉንም የሰው ዘር እኛንም ጭምር ለኃጢአትና ለሞት አሳልፎ ሸጦናል። የከፈለው ዋጋ ወይም ቅጣት ፍጹም የሆነውን የራሱን ሰብዓዊ ሕይወት ነው። ይህንን ለመሸፈን ሌላ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወት ማለትም ተመጣጣኝ ቤዛ መከፈል ነበረበት። (ዘጸአት 21:​23፤ ዘዳግም 19:​21፤ ሮሜ 5:​18, 19) ፍጹም ያልሆነ ማንም ሰው ይህን ቤዛ መክፈል እስካልቻለ ድረስ አምላክ ተወዳዳሪ በሌለው ጥበቡ ከዚህ ችግር መውጫ መንገድ አዘጋጀ። (መዝሙር 49:​6, 7) ሰማይ ይኖር የነበረውን የአንድያ ልጁን ፍጹም ሕይወት ምድር ትኖር በነበረው ድንግል ማኅፀን ውስጥ በማዘዋወር ፍጹም ሰው ሆኖ እንዲወለድ አደረገ።​—⁠ሉቃስ 1:​30-38፤ ዮሐንስ 3:​16-18

የሰውን ዘር ለመቤዠት የሚያስችለውን ውጥን ወደ ድምድማቱ ለማድረስ ኢየሱስ ምድር በነበረበት ዘመን ሁሉ ፍጹም የታማኝነት አቋም ማስመዝገብ ነበረበት። ይህንንም አድርጓል። ከዚያም መሥዋዕታዊ ሞት ሞተ። በዚህ መንገድ ኢየሱስ የሰው ዘርን ለማዳን የራሱን ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ መክፈል በቂ እንደሆነ አረጋግጧል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 5:​14፤ 1 ጴጥሮስ 1:​18, 19

የክርስቶስ ቤዛ ለእኛ ምን ሊያደርግልን እንደሚችል

የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አሁንም እንኳን ሊጠቅመን ይችላል። በቤዛው ላይ እምነት በማሳደር በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ልንይዝና በይሖዋ ፍቅርና እቅፍ ውስጥ ልንገባ እንችላለን። (ሥራ 10:​43፤ ሮሜ 3:​21-24) ፈጽመነው በነበረው ኃጢአት ምክንያት በጥፋተኝነት ስሜት ከመዋጥ ይልቅ ቤዛውን መሠረት በማድረግ አምላክን በነፃነት ቀርበን ይቅርታ ልንጠይቀው እንችላለን።​—⁠ኢሳይያስ 1:​18፤ ኤፌሶን 1:​7፤ 1 ዮሐንስ 2:​1, 2

በቅርብ ጊዜ ቤዛው፣ ኃጢአት በሰው ዘር ላይ ያደረሰው ሕመም ሙሉ በሙሉ እንዲፈወስ ያደርጋል። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ ክፍል የሆነው መጽሐፍ ከአምላክ ዙፋን ስለሚወጣ “የሕይወት ውኃ ወንዝ” ማብራሪያ ይሰጣል። በወንዙ ግራና ቀኝ “ለሕዝብ መፈወሻ” የሚሆን ቅጠል ያለባቸው የዛፍ ፍሬዎች አሉ። (ራእይ 22:​1, 2) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት በማድረግ የሰው ዘሮችን ከኃጢአትና ከሞት ለዘላለም ነፃ ለማድረግ ያወጣውን አስደናቂ ዝግጅት እዚህ ላይ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ እየገለጸ ነው።

የራእይ መጽሐፍ ትንቢታዊ ራእይ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፍጻሜውን ያገኛል። (ራእይ 22:​6, 7) ከዚያም ቅን ልቦና ያላቸው ሰዎች ሁሉ “ከጥፋት ባርነት ነፃነት” አግኝተው ፍጹም ሆነው ይኖራሉ። (ሮሜ 8:​20, 21) ታዲያ ይህ ስለ ይሖዋና ቤዛ ስለሆነው ታማኝ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ እንድንማር አያንቀሳቅሰንም?​—⁠ዮሐንስ 17:​3

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው መጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ሕይወት እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አዳም በሰው ዘሮች ላይ ኃጢአትና ሞት አመጣ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ ያወጣል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ