ተወቃሹ ይሖዋ አይደለም
“አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ ይሖዋ ለሚፈሩት ይራራል፤ አፈጣጠራችንን አሳምሮ ያውቃልና፣ አፈር እንደሆንን ያስታውሳል።—መዝሙር 103:13, 14 አዓት
1, 2. አብርሃም ማን ነበር? የወንድሙ ልጅ ሎጥ በክፉዋ የሰዶም ከተማ ሊኖር የቻለው እንዴት ነበር?
በስህተታችን ምክንያት ለሚያጋጥመን መከራ ይሖዋ በኃላፊነት አይጠየቅም። በዚህ ረገድ 3,900 ከሚያክሉ ዓመታት በፊት የደረሰውን ሁኔታ እንመልከት። የአምላክ ወዳጅ አብርሃምና (አብራምና) የወንድሙ ልጅ ሎጥ በጣም ባለጠጎች ሆነው ነበር። (ያዕቆብ 2:23) እንዲያውም ንብረታቸውና ከብታቸው በጣም ብዙ ከመሆኑ የተነሣ ‘አንድ ላይ ለመኖር ምድር አልበቃቸውም።’ ከዚህም በላይ በሁለቱ ሰዎች መንጎች ጠባቂዎች መካከል ጠብ ተነስቶ ነበር። (ዘፍጥረት 13:5-7) ስለዚህ ጉዳይ ምን መደረግ ነበረበት?
2 ጠቡን ለማቆም ሁለቱ እንዲለያዩ አብርሃም ሐሳብ አቀረበ። ሎጥንም የሚፈልገውን ቦታ እንዲመርጥ ቅድሚያ ሰጠው። በዕድሜ አብርሃም የሚበልጥ በመሆኑ የወንድሙ ልጅ የተሻለውን አካባቢ እንዲመርጥ ለአብርሃም ዕድል ሊሰጠው ይገባ የነበረ ቢሆንም ሎጥ ለራሱ ምርጥ የሆነውን ስፍራ ይኸውም በታችኛው ዮርዳኖስ አውራጃ ያለውን ለምለም ሜዳ ሁሉ መረጠ። በአካባቢው ከነበሩት ከተሞች በሥነ ምግባር የተበላሹት ሰዶምና ገሞራ ቢሆኑም ከውጭ ሲታዩ ግን የሚያሳስት መልክ ነበራቸው። በመጨረሻም ሎጥና ቤተሰቡ ወደ ሰዶም ገቡ፤ ይህም በመንፈሳዊ አደጋ ላይ ጣላቸው። በተጨማሪም ንጉሥ ኮሎዶጎምርና ተባባሪዎቹ የሰዶምን ገዢ ባሸነፉት ጊዜ ሎጥና ቤተሰቡ ተማርከው ተወሰዱ። አብርሃም ከእርሱ ሰዎች ጋር ሆኖ ከምርኮ ቢያድናቸውም ሎጥና ቤተሰቡ ወደዚያው ወደ ሰዶም ተመለሱ።—ዘፍጥረት 13:8-13፤ 14:4-16
3, 4. አምላክ ሰዶምንና ገሞራን ባጠፋ ጊዜ ሎጥና የቤተሰቡ አባሎች ምን ደረሰባቸው?
3 በሰዶምና ገሞራ ብልሹ የፆታ ድርጊትና የሥነ ምግባር ወራዳነት ምክንያት ይሖዋ እነዚህን ከተሞች ሊያጠፋቸው ወሰነ። እርሱም ለሎጥ ምሕረት በማሳየት ከሚስቱና ከሁለቱ ሴት ልጆቹ ጋር ከሰዶም እንዲያወጡት ሁለት መላእክትን ልኮ ነበር። ወደ ኋላቸው መመልከት አልነበረባቸውም፤ የሎጥ ሚስት ግን ምናልባት ወደ ኋላ የተወቻቸውን ቁሳዊ ንብረቶች በመመኘት ሊሆን ይችላል ወደ ኋላዋ ተመለከተች። በዚህን ጊዜ የጨው ሐውልት ሆነች።—ዘፍጥረት 19:1-26
4 ሎጥና ሁለቱ ሴት ልጆቹ ምንኛ ጉዳት ደረሰባቸው! ልጆቹ ሊያገቧቸው የነበሩትን ወንዶች ትተው መሄድ ነበረባቸው። አሁን ሎጥ ሚስቱንና ቁሳዊ ሀብቱን አጣ። እንዲያውም በመጨረሻው ከሴት ልጆቹ ጋር በዋሻ እስከመኖር ድረስ ደርሷል። (ዘፍጥረት 19:30-38) ለእርሱ ጥሩ መስሎት የነበረው ነገር ተቃራኒውን አመጣበት። በግልጽ እንደሚታየው አንዳንድ ከባድ ስህተቶችን ቢሠራም የኋላ ኋላ “ጻድቁ ሎጥ” ተብሎ ተጠርቷል። (2 ጴጥሮስ 2:7, 8) በእርግጥም ሎጥ ለሠራቸው ስህተቶች ይሖዋ ተወቃሽ አልነበረም።
“ስህተትን—ማን ያስተውላታል?”
5. ዳዊት ስለ ስህተትና ስለ ትዕቢተኝነት የተሰማው እንዴት ነበር?
5 ሁላችንም ፍጽምና የሌለንና ኃጢአተኞች በመሆናችን ስህተት እንሠራለን። (ሮሜ 5:12፤ ያዕቆብ 3:2) እኛም እንደ ሎጥ በውጭ ጥሩ መስለው በሚታዩ ነገሮች ልንታለልና በማመዛዘን ችሎታችን ልንሳሳት እንችላለን። ስለዚህ መዝሙራዊው ዳዊት “ስህተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ። የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፣ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ” በማለት ለምኗል። (መዝሙር 19:12, 13) ዳዊት ሳይታወቀው ኃጢአት ሊሠራ እንደሚችል አውቆ ነበር። ስለዚህ ከራሱም እንኳን ሊሰወሩ ከሚችሉ በደሎች ምሕረት እንዲደረግለት ለምኗል። ፍጹም ያልሆነው ሥጋው የተሳሳተ መንገድ እንዲይዝ ገፋፍቶት ከባድ ስህተቶች በሠራ ጊዜ የይሖዋን እርዳታ እጅግ አድርጎ ይፈልግ ነበር። በድፍረት ከሚፈጸሙ ድርጊቶች አምላክ እንዲያግደው ይፈልግ ነበር። ዳዊት ድፍረት ወይም ትዕቢት ዋነኛ ጠባዩ እንዲሆን አልፈለገም። ከዚህ ይልቅ ለይሖዋ አምላክ በማደር በኩል አቋሙ ፍጹም እንዲሆን ፈልጎ ነበር።
6. ከመዝሙር 103:10-14 ምን ማጽናኛ ሊገኝ ይችላል?
6 እኛም በዘመናችን የይሖዋ ውስን አገልጋዮች እንደ መሆናችን መጠን ፍጽምና የሌለን ስለሆንን ስህተት እንሠራለን። ለምሳሌ ያህል እኛም እንደ ሎጥ በመኖሪያ ቦታችን ረገድ መጥፎ ምርጫ ልናደርግ እንችላለን። ምናልባት ለአምላክ የምናቀርበውን ቅዱስ አገልግሎት ለማስፋት የሚያስችል አጋጣሚ ይመጣልንና ሳንቀበል እንቀር ይሆናል። ይሖዋ እንደዚህ ያሉትን ስህተቶች ቢመለከትም ወደ ጽድቅ የሚያዘነብል ልብ ያላቸውን ሰዎች ያውቃል። ከባድ ስህተት ብንሠራም እንኳን ተጸጽተን ንስሐ የምንገባ ከሆነ ይሖዋ ምሕረትና እርዳታ ይሰጣል፣ እኛን እንደ አምላካዊ ሰዎች አድርጎ መመልከቱንም ይቀጥላል። “እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፣ እንደ በደላችንም አልከፈለንም” በማለት ዳዊት ተናግሯል። “ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ ይሖዋ ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ ይሖዋ ለሚፈሩት ይራራል፤ አፈጣጠራችንን አሳምሮ ያውቃልና፣ አፈር እንደሆንን ያስታውሳል።” (መዝሙር 103:10-14) መሐሪው ሰማያዊ አባታችን ለስህተታችን ማካካሻ እንድናደርግ ያስችለን ይሆናል፣ ወይም ለእርሱ ምስጋና የምናቀርበውን ቅዱስ አገልግሎታችንን ለማስፋት ሌላ አጋጣሚ ይሰጠን ይሆናል።
በአምላክ የማመካኘት ስህተት
7. መከራ የሚደርስብን ለምንድን ነው?
7 ነገሮች ሳይሳኩ ሲቀሩ የደረሰውን ነገር በአንድ ሰው ወይም ነገር ላይ ማላከክ ሰብአዊ ዝንባሌ ነው። አንዳንዶች በአምላክም ላይ ሳይቀር ያመካኛሉ። ይሖዋ አምላክ ግን እንዲህ ዓይነት መከራዎችን በሰዎች ላይ አያመጣም። እርሱ ጥሩ ይሠራል እንጂ ጎጂ ነገር አያደርግም። እንዲያውም “እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣል፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባል”! (ማቴዎስ 5:45) መከራ የሚደርስብን ዋና ምክንያት በስግብግብነት እየተመራ በሚሠራና በሰይጣን ዲያብሎስ ኃይል በተያዘ ዓለም ውስጥ ስለምንኖር ነው።—1 ዮሐንስ 5:19
8. አዳም ነገሮች ሳይሳኩለት ሲቀሩ ምን አደረገ?
8 የገዛ ስህተታችን በራሳችን ላይ ለሚያመጣብን ችግር ይሖዋ አምላክን መውቀስ ጥበብ የጎደለውና አደገኛ ነው። እንዲህ ማድረግ ሕይወታችንንም እንኳን ሊያሳጣን ይችላል። የመጀመሪያው ሰው አዳም ለተቀበላቸው መልካም ነገሮች ሁሉ አምላክን ማመስገን ይገባው ነበር። አዎን፣ አዳም ራሱን ሕይወትን በማግኘቱና በኤደን ገነቱ መናፈሻ ዓይነት ቤት ለሚደሰትባቸው በረከቶች ለይሖዋ በጥልቅ አመስጋኝ መሆን ነበረበት። (ዘፍጥረት 2:7-9) አዳም ይሖዋን ባለመታዘዙና የተከለከለችውን ፍሬ በመብላቱ ምክንያት ነገሮች ሳይሳኩ ሲቀሩ አዳም ያደረገው ምን ነበር? አዳም “ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ” ብሎ በአምላክ ላይ ያለውን ቅሬታ ገለጸ። (ዘፍጥረት 2:15-17፤ 3:1-12) በእርግጥም አዳም እንዳደረገው ይሖዋን መውቀስ አይገባንም።
9. (ሀ) ጥበብ በጎደለው አድራጎታችን ምክንያት ችግር ቢደርስብን መጽናኛ ልናገኝ የምንችለው ከየት ነው? (ለ) በምሳሌ 19:3 መሠረት አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው ላይ ችግር ሲያመጡ ምን ያደርጋሉ?
9 ድርጊታችን ጥበብ የጎደለው በመሆኑ ምክንያት ችግሮች ቢያጋጥሙን ይሖዋ ድካማችንን እኛ ራሳችን ለመረዳት ከምንችለው የበለጠ እንደሚረዳልንና ፍጹም ለእርሱ ያደርን ከሆንን ከችግራችን እንደሚያድነን በማወቃችን መጽናኛ ልናገኝ እንችላለን። በራሳችን ላይ ለምናመጣቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎችና ችግሮች የምንቀበለውን መለኮታዊ እርዳታ ማድነቅ እንጂ ማማረር አይገባንም። ይህን በሚመለከት ጥበብ የተሞላበት ምሳሌ “የሰው ስንፍና [ሞኝነት አዓት] መንገዱን ታጣምምበታለች፣ ልቡም በይሖዋ ላይ ይቆጣል” ይላል። (ምሳሌ 19:3) አንድ ሌላ ትርጉም “አንዳንድ ሰዎች በገዛ ራሳቸው የድንቁርና ድርጊት ምክንያት ራሳቸውን ያጠፉና ጌታን ያማርራሉ” ይላል። (ቱደይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን) አንድ ሌላ ትርጉም ደግሞ “የሰው ድንቁርና ጉዳዮቹን ያመሰቃቅልበትና በይሖዋ ላይ ይቆጣል” ይላል።—ባይንግተን
10. የአዳም ሞኝነት ‘መንገዱን ያጣመመበት’ እንዴት ነበር?
10 ይህ ምሳሌ በሚገልጸው መሠረታዊ ደንብ መሠረት አዳም የራስ ወዳድነት ድርጊት በመፈጸሙ የሞኝነት አስተሳሰቡ ‘መንገዱን አጣሞበታል።’ ልቡ ከይሖዋ አምላክ ዘወር ብሎ በራሱ የስስትና በራስ የመመራት መንገድ ሄዶአል። አዎን፣ አዳም በፈጣሪው እስከ ማመካኘትና ራሱን የልዑሉ ጠላት እስከማድረግ ድረስ በመድረስ እንዲህ ዓይነት ምስጋና ቢስ ሆነ! የአዳም ኃጢአት የራሱና የቤተሰቡ መንገድ እንዲጣመም አድርጎታል። ይህስ ምንኛ ማስጠንቀቂያ የሚሆን ነው! ደስ የማይል ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ይሖዋን ማማረር የሚቀናቸው ሰዎች ራሳቸውን እንደሚከተለው እያሉ ቢጠይቁ መልካም ነው፦ ላገኘኋቸው መልካም ነገሮች አምላክን አመሰግነዋለሁን? ከፍጥረቶቹ እንደ አንዱ ሆኘ ሕይወት በማግኘቴ አመስጋኝ ነኝን? በራሴ ላይ መከራ ያመጣብኝ የራሴ ስህተት ሊሆን ይችል ይሆን? በመንፈስ የተጻፈ ቃሉ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘውን አመራሩን በመከተሌ ምክንያት የይሖዋን ሞገስ ወይም እርዳታ ለማግኘት ብቁ ነኝን?
የአምላክ አገልጋዮችንም እንኳን የሚያጋጥም አደጋ
11. አምላክን በተመለከተ የመጀመሪያው መቶ ዘመን የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ጥፋታቸው ምን ነበር?
11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የነበሩ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች አምላክን እናገለግላለን ይሉ የነበሩ ቢሆንም የእውነት ቃሉን ችላ ብለው በራሳቸው ማስተዋል ይደገፉ ነበር። (ማቴዎስ 15:8, 9) ኢየሱስ ክርስቶስ የተሳሳተ አስተሳሰባቸውን ስላጋለጠባቸው ገደሉት። በኋላም በደቀ መዛሙርቱ ላይ ታላቅ ቁጣ አሳዩ። (ሥራ 7:54-60) የእነዚያ ሰዎች መንገድ በጣም የተጣመመ ከመሆኑ የተነሳ በይሖዋ በራሱ ላይም እንኳን ተቆጥተው ነበር።—ከሥራ 5:34, 38, 39 ጋር አወዳድር።
12. ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር የተቀራረቡ አንዳንድ ሰዎችም እንኳን ችግሮቻቸውን በአምላክ ላይ ለማሳበብ እንደሚሞክሩ የሚያሳይ ምን ምሳሌ አለ?
12 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎችም ላጋጠሟቸው ችግሮች አምላክን ተጠያቂ ለማድረግ በመሞከር በውስጣቸው አደገኛ አስተሳሰብ አሳድረዋል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ጉባኤ ውስጥ የተሾሙት ሽማግሌዎች ለአንዲት ያገባች ወጣት ሴት ከአንድ ዓለማዊ ወንድ ጋር መቀራረቧን እንድትተው ጥብቅ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በደግነት መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አገኙት። አንድ ጊዜ ሲያወያዩዋት ከዚህ ሰው ጋር ባለማቋረጥ መቀራረቧ ያመጣባትን ፈተና እንድትቋቋም አምላክ ስላልረዳት ጥፋተኛ አደረገችው። እንዲያውም በአምላክ ላይ ተናዳ እንደነበረች ተናግራለች! ከእርስዋ ጋር ምክንያት በማቅረብ የተደረገ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይትና እርስዋን ለመርዳት የተደረገ ተደጋጋሚ ጥረት ምንም ፋይዳ ሳያስገኝ ቀረና የብልግና አካሄዷ የኋላ ኋላ ከክርስቲያን ጉባኤ እንድትወገድ አድርጎአታል።
13. የማጉረምረም ጠባይን ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው?
13 የማጉረምረም መንፈስ አንድን ሰው ይሖዋን ጥፋተኛ ለማድረግ እንዲሞክር ሊገፋፋው ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ወደነበረው ጉባኤ ሾልከው የገቡ አንዳንድ “ኃጢአተኞች” ይኸው የማጉረምረም መንፈስ ነበራቸው። በዚህም ላይ ሌላ ዓይነት መንፈሳዊነትን የሚያበላሽ አስተሳሰብ ነበራቸው። ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ እንዳለው እነዚህ ሰዎች “የአምላካችንን ፀጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ።” ይሁዳ በተጨማሪም “እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸውም የሚያጉረመርሙ ናቸው” ብሏል። (ይሁዳ 3, 4, 16) ለይሖዋ በታማኝነት የሚቆሙ አገልጋዮቹ በመጨረሻው በአምላክ ላይ እምነት እስከ ማጣትና ከእርሱ ጋር ያላቸውን ዝምድና በአደጋ ላይ እስከ መጣል የሚያደርስ የማጉረምረም ጠባይ ሳይሆን አድናቂ መንፈስ እንዲኖራቸው ይጸልያሉ። ይህም አስተዋይነት ነው።
14. አንድ ሰው ክርስቲያን ወንድሙ ቢጎዳው እንዴት ሊሰማው ይችላል? ይሁን እንጂ ይህ ተገቢ አካሄድ የማይሆነው ለምንድን ነው?
14 ይህ በአንተ ላይ እንደማይደርስ ታስብ ይሆናል። ሆኖም በራሳችን ወይም በሌሎች ስህተት ምክንያት ነገሮች ሲበላሹ በመጨረሻው አምላክን እንድናማርር ሊያደርጉን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው መሰል አማኝ በሚናገረው ወይም በሚያደርገው ነገር ስሜቱ ይጎዳ ይሆናል። የተጎዳው ግለሰብ (ምናልባትም አምላክን ለብዙ ዓመታት በታማኝነት ያገለገለ ሰው ሊሆን ይችላል) ‘ያ የጎዳኝ ሰው በጉባኤው ውስጥ ካለ ወደ ስብሰባ አልሄድም’ ይል ይሆናል። አንድ ግለሰብ በልቡ ‘ነገሮች እንዲህ የሚቀጥሉ ከሆነ የጉባኤው አባል መሆን አልፈልግም’ እስከ ማለት ድረስ በጣም ይበሳጭ ይሆናል። ነገር ግን አንድ ክርስቲያን ይህ ዝንባሌ ሊኖረው ይገባልን? ፍጹም ያልሆነ ሰው ቢጎዳው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ባላቸውና በታማኝነት ቆመው በማገልገል ላይ ያሉ ሰዎች ያሉበትን መላውን ጉባኤ ለምን ይጨምራል? አንድ ራሱን ለይሖዋ የወሰነ ማንኛውም ሰው የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ለማቆምና በአምላክ ላይ ንዴቱን ለመወጣት ለምን ይሞክራል? በአንድ ሰው ምክንያት ወይም በሁኔታዎች ግፊት ከይሖዋ ጋር የነበረንን ዝምድና ለምን እንተዋለን? በማናቸውም ምክንያት ይሖዋ አምላክን ማምለክን መተው በእርግጥ ሞኝነትና ኃጢአት ነው።—ያዕቆብ 4:17
15, 16. ዲዮጥራጢስ ጥፋተኛ የሆነው በምንድን ነው? ጋይዮስ ግን አቋሙ እንዴት ነበር?
15 ሰው ወዳድ የነበረው ክርስቲያኑ ጋይዮስ በነበረበት ጉባኤ ውስጥ አንተም እንደነበርክ አድርገህ አስብ። ጋይዮስ ለጉብኝት ለሄዱ መሰል አምላኪዎችና ያውም ለማያውቃቸው ሰዎች የእንግድነት አቀባበል በማድረጉ “የታመነ ሥራ” ይሠራ ነበር! ነገር ግን ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው በዚያው ጉባኤ ውስጥ ዲዮጥራጢስ የሚባል ትዕቢተኛ ሰው ነበር። ከኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አንዱ ከነበረው ከዮሐንስ ዘንድ ምንም ነገር በአክብሮት አይቀበልም ነበር። እንዲያውም ዲዮጥራጢስ ስለ ዮሐንስ ክፉ ቃል ለፍልፏል። ሐዋርያው “ይህም ሳይበቃው እርሱ [ዲዮጥራጢስ] ራሱ ወንድሞችን አይቀበልም፣ ሊቀበሏቸው የሚወዱትን ከልክሎ ከቤተ ክርስቲያን ያወጣቸዋል” ብሏል።—3 ዮሐንስ 1, 5-10
16 ዮሐንስ ወደዚያ ጉባኤ ቢመጣ ዲዮጥራጢስ የሚያደርገውን ሊያሳስብ አስቦ ነበር። እስከዚያው ድረስ በዚያ ጉባኤ የነበሩት ጋይዮስና ሌሎች እንግዳ ተቀባይ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ስሜት አሳዩ? ከእነርሱ ማናቸውም ‘ዲዮጥራጢስ በዚህ ጉባኤ እስካለ ድረስ የጉባኤው አባል መሆን አልፈልግም። በስብሰባዎች አልገኝም’ እንዳሉ የሚጠቁም ምንም ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ የለም። ጋይዮስና ሌሎች እርሱን መሰሎች ጸንተው እንደቆሙ አያጠራጥርም። መለኮታዊውን ፈቃድ ከማድረግ ምንም ነገር እንዲያቆማቸው አልፈቀዱም። በይሖዋ ላይ እንዳልተቆጡም ጥርጥር የለውም። በእርግጥም ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት ቢተዉና ለዚህም በአምላክ ላይ ቢያሳብቡ በጣም ይደሰት ለነበረው ለሰይጣን ዲያብሎስ የተንኮል ብልሃቶች አልተሸነፉም።—ኤፌሶን 6:10-18
በይሖዋ ላይ ፈጽሞ አትቆጡ!
17. አንድ ግለሰብ ወይም ሁኔታ ስሜታችንን ቢጎዳ ወይም ቢያስከፋን ምን ማድረግ ይገባናል?
17 በአንድ ጉባኤ ውስጥ አንድ ግለሰብ ወይም ሁኔታ አንድን የአምላክ አገልጋይ ቢጎዳውም የተጎዳው ሰው ከአምላክ ሕዝቦች ጋር የነበረውን መቀራረብ ቢያቆም በእርግጥ መንገዱን እያጣመመ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰው የማስተዋል ኃይሉን በተገቢ መንገድ እየተጠቀመበት አይደለም። (ዕብራውያን 5:14) ስለዚህ ፍጹም አቋም ጠባቂ በመሆን ማንኛውንም መከራ ለመቀበል ቁረጥ። ለይሖዋ አምላክ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስና ለክርስቲያን ጉባኤ ዘወትር በታማኝነት ቁም። (ዕብራውያን 10:24, 25) ወደ ዘላለማዊ ሕይወት የሚመራው እውነት በሌላ በየትም ቦታ አይገኝም።
18. ምንም እንኳን መለኮታዊውን አሠራር ሁልጊዜ መረዳት ባንችልም ይሖዋ አምላክን በተመለከተ ስለምን ነገር እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?
18 በተጨማሪም ይሖዋ ማንንም ሰው በክፉ ነገሮች በጭራሽ እንደማይፈትን አስታውስ። (ያዕቆብ 1:13) ራሱ የፍቅር አብነት የሆነው አምላክ የሚሠራው ጥሩ ነገር ብቻ ነው፤ በተለይም ለሚያፈቅሩት ሰዎች። (1 ዮሐንስ 4:8) የይሖዋን አሠራር ሁልጊዜ መረዳት ባንችልም ይሖዋ አምላክ ለአገልጋዮቹ ከሁሉ የተሻለውን እንደሚያደርግ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ጴጥሮስ “እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” በማለት እንደተናገረው ነው። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) አዎን፣ ይሖዋ በእርግጥ ለሕዝቡ ያስባል።—መዝሙር 94:14
19, 20. አንዳንድ ጊዜ ችግሮቻችን ቢያስተክዙንም እንኳን ምን ማድረግ አለብን?
19 ስለዚህ ምንም ነገር ወይም ማንም ሰው እንዲያሰናክልህ አትፍቀድለት። መዝሙራዊው “ሕግህን ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው፤ እንቅፋትም የለባቸውም” በማለት ሁኔታውን በሚገባ ገልጾታል። (መዝሙር 119:165) ሁላችንም ችግር ያጋጥመናል። እነዚህም ችግሮች አንዳንድ ጊዜ እንድንተክዝና ተስፋ እንድንቆርጥ ሊያደርጉን ይችላሉ። ቢሆንም ግን በልብህ ምሬት እንዲያድግ አትፍቀድ፣ በተለይ ደግሞ በይሖዋ ላይ። (ምሳሌ 4:23) በእርሱ እርዳታና ቅዱስ ጽሑፉን መሠረት በማድረግ ችግሮቹን ለማቃለል የምትችል ሲሆን የማይቃለሉትን ደግሞ ችለህ ልትታገላቸው ትችላለህ።—ማቴዎስ 18:15-17፤ ኤፌሶን 4:26, 27
20 የገዛ ስሜትህ የሞኝነት እርምጃ በመውሰድ መንገድህን እንዲያጣምምብህ አትፍቀድለት። ስትናገርና አንድ ነገር ስታደርግ የአምላክን ልብ በሚያስደስት መንገድ ይሁን። (ምሳሌ 27:11) ይሖዋ ከአገልጋዮቹ እንደ አንዱ አድርጎ እንደሚያስብልህና ከሕዝቡ ጋር በሕይወት መንገድ ላይ እንድትቆይ የሚያስፈልግህን ማስተዋል እንደሚሰጥህ በማወቅ በልባዊ ጸሎት ጠይቀው። (ምሳሌ 3:5, 6) ከሁሉ በላይ ግን በአምላክ ላይ አትቆጣ። ነገሮች ሲበላሹ ወይም አልሳካ ሲሉ ተወቃሹ ይሖዋ እንዳልሆነ ምንጊዜም ትዝ ይበልህ።
እንዴት ትመልሳላችሁ?
◻ ሎጥ የሠራው ስህተት ምን ነበር? አምላክ ግን እንዴት ተመልክቶታል?
◻ ዳዊት ስለ ስህተትና ትዕቢተኝነት የተሰማው እንዴት ነበር?
◻ ነገሮች አልሳካ ሲሉ አምላክን ማማረር የሌለብን ለምንድን ነው?
◻በይሖዋ ላይ እንዳንቆጣ ምን ሊረዳን ይችላል?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሎጥ ከአብርሃም ሲለይ በመኖሪያ ቦታ ረገድ መጥፎ ምርጫ አድርጓል