አምላክ የሚያስበልጠው እነማንን ነው?
ሁላችንም በጓደኞቻችን ዘንድ መወደድን እንፈልጋለን። ለአንድ ክርስቲያን ግን ከሁሉ የበለጠ ፍላጎቱ በአምላክ ዘንድ ጥሩ ግምት ማግኘት ነው። ስለ ይሖዋ አምላክ በመዝሙር 84:11 ላይ “ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም” ይላል። ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ የሰማይ መላእክት “በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን” በማለት የደስታ መዝሙር አሰምተዋል።—ሉቃስ 2:14 እንደ 1980 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም
ታዲያ አምላክ የበለጠ ግምት የሚሰጠው ለእነማን ነው? የአምላክ የአቋም መመዘኛ ደንቦች ከሰው የመመዘኛ ደንቦች ጋር አንድ ዓይነት ናቸውን? ባለፈው ርዕሰ ትምህርት እንደተገለጸው የአምላክ መመዘኛ ደንቦች ከሰው የመመዘኛ ደንቦች ጋር አንድ ዓይነት እንዳልሆኑ እንረዳለን። እንዲያውም ክርስቲያኖች ‘አምላክን እንዲመስሉ’ ስለተመከሩ እያንዳንዳችን ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን ልንጠይቅ እንችላለን፦ የማስበልጠው አምላክ ከፍ አድርጎ የሚመለከታቸውን ሰዎች ነው ወይስ ሰዎችን በምገመግምበት ጊዜ ዓለማዊ የአቋም መመዘኛዎችን ወደ መከተል አዘነብላለሁ? (ኤፌሶን 5:1) በይሖዋ ዘንድ ሞገስንና ጥሩ ግምትን እንዲሁም ተቀባይነትን ለማግኘት ከፈለግን ነገሮችን እርሱ በሚመለከትበት መንገድ ለማየት መጠንቀቅ አለብን።
የአምላክ ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች
‘እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያደላም’ አለ ሐዋርያው ጴጥሮስ “ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ በእርግጥ አስተዋልሁ።” በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ አምላክ “አምላክ የምድርን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ” በማለት መስክሯል። (ሥራ 10:34, 35፤ 17:26) ስለዚህ ሁሉም ሰዎች ምንም ዓይነት አካላዊ ሁኔታ ቢኖራቸውም በአምላክ ፊት እኩል ናቸው ብሎ መደምደም ምክንያታዊ መሆን ነው። ይህም በመሆኑ አንድ ክርስቲያን አንድ ሰው ከአንድ የተወሰነ አካባቢ ስለመጣ ወይም አንድ ዓይነት የቆዳ ቀለም ስላለው ወይም የአንድ ዘር አባል ስለሆነ ብቻ ከሌሎች አስበልጦ ቢመለከተው ወይም ቢያከብር ተገቢ አይሆንም። በዚህ ፈንታ ምንም አድልዎ እንዳላሳየ ጠላቶቹም እንኳን ሳይቀሩ የመሰከሩለትን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ቢከተል መልካም ነው።—ማቴዎስ 22:16
“ስኪን-ዲፕ” የሚለው የእንግሊዝኛ አባባል [“ላይ ላዩን” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም ጥልቀቱ ከቆዳ የማያልፍ ማለት ነው] አንዳንድ ጊዜ ላይ ላዩን የሆነ ወይም ቁም ነገር የሌለውን ነገር ለመግለጽ ያገለግላል። የቆዳ ቀለምም ልክ እንደዚሁ ነው፤ ጥልቀት የሌለው ላይ ላዩን የሆነ ነገር ነው። የአንድ ሰው የቆዳ ቀለም በምንም መንገድ የሰውየውን ጠባይ ወይም ውስጣዊ ባሕርዩን አያንጸባርቅም። ጓደኞች እንዲሆኑን የምንመርጣቸው ወይም አብረናቸው የምንመገበው ወይም የምንጨብጣቸው ሰዎች በተለይ በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት መሆን እንደሌለበት ጥርጥር የለውም። እስከ አሁን ከተጻፉት የፍቅር ቅኔዎች ሁሉ በጣም ውብ የሆኑ ቅኔዎች የተናገረችው ልጃገረድ ስለ ራሷ “እኔ ጥቁር ነኝ፤ ነገር ግን ውብ ነኝ . . . ፀሐይ መልኬን አክስሎታልና” ብላለች። (መኃልየ መኃልይ 1:5, 6) የአንድ ሰው ዘርም ሆነ የቆዳ ቀለም የተለየ አድልዎን ለማሳየት መሠረት አይሆንም። ከሁሉ የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ነገር አንድ ሰው አምላክን የሚወድና ጽድቅን የሚያደርግ መሆን አለመሆኑ ነው።
አምላክ ስለ ቁሳዊ ሀብት እንዴት ይሰማዋል? አምላክ ከሁሉም አብልጦ የሚወደውና ከፍተኛ ግምት የሰጠው ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። ሆኖም ኢየሱስ በምድር ሳለ “ራሱን የሚያስጠጋበት” አልነበረውም። (ማቴዎስ 8:20) የመሬት፣ የቤት፣ የእርሻ፣ የፍራፍሬ ዛፎች፣ ወይም የእንስሳት ሀብት አልነበረውም። ያም ሆኖ ይሖዋ ለኢየሱስ ክብር ሰጥቷል፣ እንዲሁም በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከአምላክ ከራሱ በቀር ከማንኛቸውም ፍጥረቶች የሚበልጥ ሥልጣን በመስጠት ከፍ አድርጎታል።—ፊልጵስዩስ 2:9
ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ መወደድን ያገኘው በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ሀብታም ስለሆነ ሳይሆን በመልካም ሥራ ሀብታም ስለሆነ ነው። (ከ1 ጢሞቴዎስ 6:17, 18 ጋር አወዳድር።) ተከታዮቹን “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሰርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ” በማለት አጥብቆ መክሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:19, 20) ስለዚህ ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም ቁሳዊ ነገሮች ሀብታሞች ለሆኑት ሰዎች ከፍ ያለ ግምት አይሰጡም፤ እንዲያውም ዓለማዊ ንብረቶችን መሠረት በማድረግ ምንም ልዩነት አያደርጉም። ክርስቲያኖች የሚመለከቱት በቁሳዊ ረገድ ሀብታምም ይሁኑ ድሆች በአምላክ ዘንድ ሀብታሞች መሆናቸውን ብቻ ነው። “እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች” እንደመረጠ ምንጊዜም አትዘንጉ። (ያዕቆብ 2:5) የአምላክን አመለካከት ከያዝክ በቁሳዊ ሀብታሞች የሆኑትን ሰዎች በማስበለጥና እነርሱንም ለማስደሰት በሚደረገው የተለመደ ተግባር አትጠመድም።
ትምህርትንም በተመለከተ አምላክ ዕውቀትንና ጥበብን እንድንፈልግ እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የበለጠው ታላቅ አስተማሪ መሆኑን እንድንገነዘብ አጥብቆ እንደሚያሳስበን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። (ምሳሌ 4:7፤ ማቴዎስ 7:29፤ ዮሐንስ 7:46) ይሁን እንጂ በአምላክ ዘንድ የተሻለ ግምት የሚያሰጠን ዓለማዊ ጥበብ ወይም ዕውቀት አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ ጳውሎስ “እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች . . . አልተጠሩም። ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ” በማለት ይነግረናል።—1 ቆሮንቶስ 1:26, 27
አምላክ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርት የተካኑ ሰዎችን ሳይሆን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የእውነትን “ንጹህ ልሳን” በደንብ የተማሩትን ሰዎች አስበልጦ ይመለከታል። (ሶፎንያስ 3:9) እንዲያውም ይሖዋ ራሱ በአሁኑ ጊዜ እስከ ሩቅ የምድር ማዕዘን ድረስ በሚደርስ የትምህርት ፕሮግራም አማካኝነት ሕዝቡን እያስተማራቸው ነው። በነቢዩ ኢሳይያስ እንደተተነበየው ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሕዝቦች “ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን” በማለት ምላሽ እየሰጡ ነው። ስለዚህ ክርስቲያኖች ለዓለማዊ ትምህርት ክብር በመስጠት ፈንታ በቃላቸውም ሆነ በድርጊታቸው “ከእግዚአብሔር [ከይሖዋ አዓት] የተማሩ” መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ሰዎችን ይፈልጋሉ። እንዲህ በማድረጋቸውም አምላክ የሚሰጠውን ‘ብዙ ሰላም’ ያገኛሉ።—ኢሳይያስ 2:3፤ 54:13
በአምላክ ዘንድ ጥሩ ግምት ለማግኘት እንችላለን
አዎን፣ አምላክ ሌሎችን አስበልጦ ለማየት የሚመዝንባቸው ደንቦች ከሰው የመመዘኛ ደንቦች በጣም የተለዩ ናቸው። ሆኖም በእርሱ ፊት ጥሩ ግምት ለማግኘት ከፈለግን በመንገዶቹ ለመመራት መጣር አለብን። ይህም በራስ ወዳድነትና ምክንያተ ቢስ የሆነ ጥላቻ ባለባቸው በሰው የአቋም መመዘኛ ደንቦች ሳንመራ ሌሎችን በአምላክ አመለካከት ማየትን መማር አለብን ማለት ነው። ይህን ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው?
ይሖዋ አምላክ የሰውን ልብ ስለሚመረምር ፍቅር፣ ጥሩነት፣ ደግነትና ትዕግስት የመሳሰሉትን ባሕሪያት የሚያሳዩ ሰዎችን አስበልጦ ይመለከታል። እኛም እንዲሁ ማድረግ አለብን። (1 ሳሙኤል 16:7፤ ገላትያ 5:22, 23) የአንድን ሰው የቆዳ ቀለሙን ወይም የጎሳ መደቡን ሳይሆን በሰብአዊ አቅማችን የምንችለውን ያህል የሰውየውን ውስጣዊ ባሕርይ ማየት ያስፈልገናል። በቁሳዊ ነገር ሀብታሞች የሆኑ ሰዎችን ጓደኝነት በመፈለግ ፈንታ አምላክ ስለ ሀብት ያለውን አመለካከት በመያዝ ‘በበጎ ሥራ ባለጠጎች [ለመሆንና] ልንረዳና ልናካፍል የተዘጋጀን’ ለመሆን ብንጣጣር መልካም ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:18) በአምላክ ዘንድ ጥሩ ግምት ለማግኘት የእውነትን ንጹሕ ልሳን በሚገባ የተማርን በመሆን ስለ አምላክና ስለ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ ዕውቀት መፈለጋችንን መቀጠል አለብን። (ዮሐንስ 17:3, 17) እንዲህ ብናደርግ እኛም አምላክ ከፍ ያለ ግምት ከሚሰጣቸው መካከል እንሆናለን።