የበለጠ ግምት የምትሰጠው ለምን ዓይነት ሰዎች ነው?
“ሚስት እፈልጋለሁ። መልኳ ቀይና ቀጠን ያለች፣ በከፍተኛ ትምህርት የተመረቀች መሆን አለባት፤ የድሕረ ምረቃ ትምህርት ያላት ብትሆን ይመረጣል። ሀብት ካላቸው ጥሩ ቤተሰብ የመጣች መሆን አለባት። ከጎሳዬ ብትሆን ይመረጣል።”
ከላይ እንደተገለጸው የሚነበበው በሕንድ አገር ጋዜጣ ላይ ልታዩት እንደምትችሉት ያለ የተለመደ የጋብቻ ማስታወቂያ ነው። ተመሳሳይ ማስታወቂያዎችን በሌሎች የዓለም ክፍሎችም አይታችሁ ይሆናል። በሕንድ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የጋብቻው ማስታወቂያ የሚወጣው በሚያገባው ወንድ ወላጆች አማካኝነት ነው። ለማስታወቂያው የሚሰጠው ምላሽ ሳሪ በመባል የሚታወቀውን ብሩሕ ቀይ ቀለም ያለው የሕንድ ሴቶች ረዥም ቀሚስ የለበሰችና ብዙ የወርቅ ጌጣጌጥ ያደረገች ልጃገረድን ፎቶግራፍ የሚጨምር ሊሆን ይችላል። የልጁ ቤተሰብ ከወደዳት ለጋብቻው ድርድር ይጀመራል።
ሰዎች በአብዛኛው ከፍ አድርገው የሚመለከቷቸው የአቋም መመዘኛዎች
በሕንድ አገር ቀይ ሚስት መፈለግ በጣም የተለመደ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት ዝቅተኛ የሚባሉት የሒንዱ ኅብረተሰብ ክፍሎች ቀለማቸው ጥቁር ነው የሚል ሥር የሰደደ እምነት ስላለ ነው። በቅርቡ በሕንድ ቴሌቪዢን ላይ የቀረበ አንድ ፕሮግራም አንዷ ቀይ ሌላዋ ደግሞ ጥቁር ስለሆኑ ሁለት ልጃገረዶች አንድ ጭውውት አቅርቦ ነበር። ቀዩዋ ልጃገረድ ጨካኝና ጋጠ ወጥ ስትሆን ጥቁሯ ግን ደግና ጨዋ ናት። ሁኔታው በአስማታዊ መንገድ ተገለባበጠና ቀይዋ ልጃገረድ ቅጣት እንዲሆናት ወደ ጥቁርነት ስትለወጥ ጥቁሯ ልጃገረድ ግን ቀይ ሆነች። በግልጽ እንደሚታየው የጭውውቱ ፍሬ ነገር ውሎ አድሮ አሸናፊው ጥሩ ባሕርይ ቢሆንም ተፈላጊው ግን ቀይ መልክ መሆኑን ለመግለጽ ነበር።
ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነት የዘረኝነት ስሜቶች አንድ ሰው ከሚገነዘበው በላይ በጣም ሥር የሰደዱ ናቸው። ለምሳሌ ያህል አንድ እስያዊ ሰው አንድን ምዕራባዊ አገር ቢጎበኝ በቆዳው ቀለም ወይም በዓይኑ ቅርጽ ምክንያት አድልዎ እንደተደረገበት ቅሬታ ያሰማ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ይረብሹታል፣ አድልዎ እንደተደረገበትም ይሰማዋል። ወደ ትውልድ አገሩ ሲመለስ ግን የተለየ ጎሣ ያላቸውን ሰዎች እሱ በውጭ አገር ሳለ በታየበት መንገድ በአድልዎ ይመለከት ይሆናል። በአሁኑ ጊዜም እንኳን የቆዳ ቀለምና የጎሣ መደብ ሰዎች ለአንድ ሰው ለሚሰጡት ግምት ከፍተኛ ቦታ አላቸው።
“ሁሉም ለገንዘብ ይገዛል” በማለት የጥንቱ ንጉሥ ሰሎሞን ጽፏል። (መክብብ 10:19) ይህ ምንኛ እውነት ነው! ሀብት ባለሀብቶቹ ሰዎች የሚታዩበትን ሁኔታ ይነካል። ሀብቱ የመጣበት መንገድ እምብዛም አይጠየቅም። ሰውየው የከበረው በጥረቱ ነው? በጠንቃቃ አያያዝ ነው? ወይስ በማጭበርበር? ምንም ልዩነት አያመጣም። ሀብቱ በመጥፎ ሁኔታ የተገኘ ሆነም አልሆነ ብዙ ሰዎች ባለሀብቱን በቁልምጫ እንዲያሞግሱት ያደርጋል።
ከፍተኛ ትምህርትም በዚህ የፉክክር ዓለም ውስጥ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ሆኗል። አንድ ልጅ እንደተወለደ ወላጆቹ ለማስተማሪያ የሚሆን ብዙ ገንዘብ ማጠራቀም ይጀምራሉ። ሁለት ወይም ሦስት ዓመት ሲሆነው ለወደፊቱ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ለማስጨበጥ ለሚደረገው ረዥም ጉዞ እንደ መጀመሪያ እርምጃ አድርገው በጥሩ የሕፃናት ማሳደጊያ ትምህርት ቤት ወይም በጥሩ መዋዕለ ሕፃናት ስለማስገባት ይጨነቃሉ። አንዳንድ ሰዎች አንድ ዓይነት በማዕረጉ ከፍተኛ የሆነ ዲፕሎማ ባለቤት መሆን በሌሎች መመረጥንና መከበርን ያስገኛል ብለው የሚያስቡ ይመስላል።
አዎን፣ የቆዳ ቀለም፣ ትምህርት፣ ገንዘብና የጎሣ መደብ ብዙ ሰዎች አንድን ሰው የሚመዝኑባቸው፣ አልፎ ተርፎም አስቀድመው የሚፈርዱባቸው የአቋም መለኪያ ደንቦች ሆነዋል። ማንን መውደድ ወይም ማንን ከመውደድ መቆጠብ እንዳለባቸው የሚወስኑት ነገሮች እነዚህ ናቸው። አንተስ? የምታደላው ለማን ነው? ገንዘብ፣ ቀይ መልክ፣ ወይም ከፍተኛ ትምህርት ያለውን ሰው የበለጠ ሞገስና ክብር እንደሚገባው አድርገህ ትመለከታለህን? ከሆነ ለዚህ ስሜትህ መሠረት የሆኑትን ነገሮች በጥሞና ልታስብባቸው ይገባሃል።
ጥሩ የአቋም መመዘኛ ናቸውን?
የሂንዱ ዓለም የተሰኘ መጽሐፍ እንደሚከተለው ይገልጻል፦ “አንድን ብራህሚን [የሂንዱ ካህን] የሚገድል ማንኛውም የዝቅተኞቹ ኅብረተሰባዊ ክፍሎች አባል የሆነ ሰው እስኪሞት ድረስ ሊደበደብና ንብረቱም ሊወረስ ይችላል፣ ነፍሱም ለዘላለም ልትኮነን ትችላለች። ብራህሚኑ ሌላ ሰው ቢገድል ግን በገንዘብ ይቀጣል እንጂ ፈጽሞ የሞት ቅጣት አይደርስበትም።” መጽሐፉ የሚናገረው ስለ ጥንታዊ ዘመን ቢሆንም ዛሬስ ሁኔታው እንዴት ነው? አግባብ የሌለው የዘር ጥላቻና በማኅበረሰቦች መካከል የሚፈጠር ውጥረት በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመንም እንኳን የደም ጎርፍ እንዲጎርፍ አድርጓል። ይህም በሕንድ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ምክንያት የተነሳው ማቆሚያ የሌለው ጥላቻና ዓመጽ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ያለው አግባብ የሌለው የዘር ጥላቻ፣ በባልቲክስ ያለው ምክንያተ ቢስ የብሔረተኝነት ጥላቻና ሌሎችም ብዙ ተመሳሳይ ነገሮች የተነሱት አንዱ በተፈጥሮው ከሌላው የበላይ እንደሆነ አድርጎ በማሰቡ ምክንያት ነው። በዘር ወይም በብሔር ምክንያት የሚደረገው ማዳላት ጥሩና ሰላማዊ ፍሬ አለማስገኘቱ የተረጋገጠ ነው።
ስለ ሀብትስ ምን ሊባል ይቻላል? ብዙ ሰዎች በሐቀኝነት በርትተው በመሥራታቸው ሀብታሞች እንደሆኑ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ወንጀል መሥራትን ሥራቸው ባደረጉ ሰዎች፣ በጥቁር ገበያ ነጋዴዎች፣ በአደንዛዥ መድኃኒት ነጋዴዎች፣ በሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ሻጮችና በሌሎችም ከልክ ያለፈ ብዙ ሀብት ተከማችቷል። እውነት ነው፣ ከእነዚህ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች መካከል አንዳንዶቹ ለበጎ አድራጎት ተቋሞች ችሮታዎችን ይለግሳሉ፣ ወይም ድሆችን ለመርዳት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ይደግፋሉ። የሆነ ሆኖ የወንጀለኝነት ድርጊታቸው የወንጀላቸው ሰለባ በሆኑት ሰዎች ላይ ከልክ ያለፈ ሥቃይና ጉስቁልና አስከትሏል። ጉቦ የሚበሉና ማጭበርበር በሞላባቸው የንግድ ሥራዎች የሚካፈሉ መለስተኛ ወንጀለኞች እንኳን ምርቶቻቸው ወይም ግልጋሎታቸው መናኛ ሲሆንና እንደተጠበቀው ሳይሆን ሲቀር በሰዎች ላይ ብስጭትን፣ ጉዳትንና ሞትን አስከትለዋል። በእርግጥም ሀብታም መሆን በራሱ ለሰዎች ጥሩ ግምት ለመስጠት መሠረት አይሆንም።
ስለ ትምህርትስ ምን ሊባል ይቻላል? ከአንድ ሰው ስም ጋር ብዙ ዲግሪዎችና ማዕረጎች ቢደረደሩ ሐቀኛና ቅን ለመሆኑ ዋስትና ነውን? በተለየ አክብሮት መታየት አለበት ማለት ነውን? በእርግጥ ትምህርት የአንድን ሰው የአስተሳሰብ አድማስ ያሰፋል፤ ትምህርታቸውንም ሌሎችን ለመጥቀም የተጠቀሙበት ብዙ ሰዎች ክብርና አድናቆት የሚገባቸው ናቸው። ይሁን እንጂ ታሪክ በተማሩት የኅብረተሰብ ክፍሎች ተራው ሕዝብ እንደተበዘበዘና እንደተጨቆነ በሚያሳዩ ምሳሌዎች የተሞላ ነው። በአሁኑ ጊዜ በኮሌጅ ወይም በዩኒቨርሲቲ መድረኮች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ነገር አስቡ። የኮሌጅ ወይም የዩኒቨርሲቲ ግቢዎች አደንዛዥ መድኃኒቶችን ያለአግባብ በመጠቀምና በፆታ ግንኙነት ምክንያት በሚተላለፉ በሽታዎች በሚመጣ ችግር ተወርረዋል፤ ብዙ ተማሪዎችም ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ወይም ወደ ኮሌጆች የሚገቡት ገንዘብ፣ ሥልጣንና ዝና ለማሳደድ ብቻ ነው። የአንድ ሰው የትምህርት ደረጃ ብቻውን የእውነተኛ ባሕሪው አስተማማኝ መለኪያ ነው ለማለት ያዳግታል።
የቆዳ ቀለም፣ የትምህርት ደረጃ፣ ገንዘብ፣ የመጣበት ጎሳ፣ ወይም የመሳሰሉ ምክንያቶች የአንድን ሰው ማንነት ለመገምገም የሚያስችሉ ትክክለኛ መሠረቶች አይደሉም። ክርስቲያኖች በሌሎች ዘንድ ተወዳጅነትንና አክብሮትን ለማግኘት ሲሉ እንዲህ በመሰሉ ጉዳዮች መጠላለፍ የለባቸውም። ታዲያ አንድን ሰው ሊያሳስበው የሚገባው ምን መሆን ይኖርበታል? አንድ ክርስቲያን ሊመራባቸው የሚገቡት የአቋም ደረጃዎች ምን መሆን ይኖርባቸዋል?