ይሖዋን ማገልገል ያመጣልኝ ደስታ
ጆርጅ ብሩምሌይ እንደተናገረው
የንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ወጣት ፖሊስ ዕጩ መኮንኖች ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከሆኑት አንዱ የይሖዋ ምስክር ሚስዮናዊ መሆኔን እንደሚያውቅ ለብቻዬ ሲነግረኝ ለእጩ መኮንኖቹ የሬድዮ ትምህርት ሰጥቼ ገና መጨረሴ ነበር። “መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናኛለህ?” ብሎ በጉጉት ጠየቀኝ።
ሥራችን በኢትዮጵያ ታግዶ ስለነበር ባለሥልጣኖቹ ስለ እኔ አውቀው ቢሆን ኖሮ እንደ ሌሎቹ ምስክሮች እኔም ከአገሪቱ እባረር ነበር። ተማሪው መጽሐፍ ቅዱስን ከልቡ ለማጥናት የሚፈልግ ይሆን ወይስ እኔን ለማጥመድ በመንግሥት የተላከ ሰላይ ነው የሚል ሐሳብ መጣብኝ። ሦስት ልጆች የማሳድግ የቤተሰብ ራስ እንደመሆኔ መጠን ሥራዬን ማጣቴና አገሪቱን ለቅቆ መሄዱ እንዲሁም እዚያ ካፈራኋቸው ወዳጆቼ የመለየቱ ሐሳብ አስፈራኝ።
‘የሆነስ ሆነና የሚያስተዳድራቸው ቤተሰብ ያሉት አሜሪካዊ ከአገሩና ከዘመዶቹ ተለይቶ በምሥራቅ አፍሪቃ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ ለመኖር ሊመርጥ የቻለው እንዴት ነው?’ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። እንድገልጽላችሁ ፍቀዱልኝ።
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አደግሁ
በ1920ዎቹ ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ አባቴ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ኮንትራት ገባና የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የተሰኙትን መጻሕፍት አገኘ። አባቴ ማንበብ ይወድ ስለነበር በጉጉት መጽሐፎቹን አነበባቸው። እሁድ እሁድ የሚጋብዛቸውን እንግዶች በሚያጫውትበት ጊዜ ለማየት እንደሚቻለው በጣም የቀልደኛነትና የተጨዋችነት ጠባይ ያለው ነበር። በቆዳ የተሸፈነና በፊት ለፊቱና በጎኑ ላይ በወርቅማ ፊደላት “መጽሐፍ ቅዱስ” የሚል ጽሑፍ ያለበት ውብ መጽሐፍ ነበረው። ጭውውቱን “እንግዲህ ዛሬ እሁድ ነው፣ ጥቂት ጥቅሶችን ልታነብልን ትችላለህ?” በማለት ይጀምር ነበር።
የሚመጣው እንግዳ ሁሉ ለማንበብ ምን ጊዜም ይስማማ ነበር፣ ነገር ግን መጽሐፉን በገለጠ ጊዜ ምንም ያልተጻፈባቸው ገጾች ሆነው ያገኛቸው ነበር! ሰውየው ይገረም ነበር። ያን ጊዜ አባቴ ሰባኪዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እንደማያውቁ ይናገርና አንድ መጽሐፍ ቅዱስ አንስቶ ዘፍጥረት 2:7ን ያነብ ነበር። እዚህ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጀመሪያው ሰው አፈጣጠር በመግለጽ “ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ” ይላል።—ዘፍጥረት 2:7 የ1879 እትም
አባቴ ሰው ነፍስ ያለው ሳይሆን ራሱ ነፍስ እንደሆነ፣ የኃጢአት ደመወዝ ሞት መሆኑንና አንድ ሰው ሲሞት ምንም እንደማይሰማው ፈጽሞ በድን እንደሚሆን ይገልጽ ነበር። (መክብብ 9:5, 10፤ ሕዝቅኤል 18:4፤ ሮሜ 6:23) በደንብ ማንበብ ከመጀመሬ በፊትም እንኳን ዘፍጥረት 2:7ን በቃሌ አጥንቼው ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በማወቅና ለሌሎች በማካፈል ስለሚገኘው እውነተኛ ደስታ የነበሩኝ የመጀመሪያ ትዝታዎች እነዚህ ነበሩ።
በዚያን ጊዜ በቤታችን መጠበቂያ ግንብ መጽሔትን እናገኝ ስለነበር መላው ቤተሰብ ይህን መንፈሳዊ ምግብ በማግኘት መደሰት ጀመረ። የእናቴ እናት ከእኛ ጋር ትኖር ነበርና በቤተሰባችን ውስጥ የመጀመሪያዋ የምሥራቹ አስፋፊ ሆነች። በምንኖርበት በካርቦንዴል ኢሊኖይ ጉባኤ አልነበረም፣ ይሁን እንጂ መደበኛ ያልሆኑ ስብሰባዎች ይደረጉ ነበር። እናታችን አምስታችንንም ልጆች ከከተማው በአንዱ ዳር ወደነበረ በዕድሜ የገፉ ሴቶች የመጠበቂያ ግንብ ጥናቱን ይመሩበት ወደነበረው ቦታ ትወስደን ነበር። እኛም በመስክ አገልግሎቱ መሳተፍ ጀመርን።
ከሬድዮ ሥራ ወደ እሥር ቤት
በ1937 ገና በ17 ዓመቴ አገባሁ። ሬድዮ በመጠገን መተዳደሪያ ለማግኘት ሞከርኩ፤ ይህን ሙያም አስተምር ነበር። ፔጊ የምትባል ሴት ልጅና ሃንክ የሚባል ወንድ ልጅ ከተወለዱልኝ በኋላ ጋብቻዬ አከተመ። ፍቺው በራሴ ጥፋት የመጣ ነበር፤ አኗኗሬ ክርስቲያናዊ አልነበረም። ሁለቱን ታላላቅ ልጆቼን ለማሳደግ አለመቻሌ የዕድሜ ልክ የልብ ጸጸት ሆኖብኛል።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጣና ስለ ብዙ ነገሮች እንዳስብ አደረገኝ። ወታደራዊ ቡድኖች የመቶ አለቃ እንድሆንና ለምልምል ወታደሮች የሬድዮ ትምህርት እንዳስተምር ሐሳብ አቅርበውልኝ ነበር፤ እኔ ግን ይሖዋ ስለ ጦርነት ያለው አመለካከት አሳሰበኝና በየቀኑ መጸለይ እንድጀምር አነሳሳኝ። የመጠበቂያ ግንብ ኮንትራቴ አብቅቶ ነበርና ሉሴል ሃውርስ ኮንትራቴ ማለቁን የሚገልጸው ማስታወቂያ ደረሳትና ልትጠይቀኝ መጣች። የሉሴል አባት የሆነው ፔሪ ሃውርስና ከትልቁ ቤተሰቧ አብዛኞቹ ከ1930ዎቹ ጀምሮ ምስክሮች የሆኑ ነበሩ። ሉሴልና እኔ ተዋደድንና ታህሣስ 1943 ተጋባን።
በ1944 ተጠመቅሁና አቅኚ በመሆን ከሚስቴ ጋር በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ። ወዲያውም ለውትድርና ተጠራሁና ምልመላውን አልቀበልም አልኩ። በዚህም የተነሳ በኢል ሬኖ ኦክላሆማ ፌዴራል የጠባይ ማረሚያ የሦስት ዓመት እሥራት ተፈረደብኝ። ለይሖዋ ሲባል መከራ መቀበል አስደሳች ነበር። በየጠዋቱ ከእንቅልፌ ነቅቼ የት እንዳለሁና ለምን እንደታሠርኩ ስገነዘብ ትልቅ እርካታ ይሰማኝና ይሖዋን አመሰግን ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ከ25 ዓመት ዕድሜ በላይ የነበርነው በባለ ሥልጣኖቹ ፊት ለጥያቄ መቅረብ ጀመርን። የካቲት 1946 ተፈታሁ።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት
ከሉሴል ጋር ስንገናኝ ኦክላሆማ ውስጥ ዋግንር በምትባል ትንሽ ከተማ በአቅኚነት ታገለግል ነበር። መኪና ስላልነበረን የትም ቦታ በእግር እየሄድን ከተማውን እናዳርስ ነበር። በኋላ በኦክላሆማ ውስጥ ዌዋካ ወደሚባል ቦታ ተዛወርን። ወዲያውም በአቅራቢያው ሬድዮ ጣቢያ ሥራ አገኘሁና በዜና ሥርጭት ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። በቀን ውስጥ ስድስት ሰዓት መሥራትና የአቅኚነት ሰዓት መመለስ ቀላል አልነበረም፤ ሆኖም ይሖዋን በማገልገል በነበረን መብት ተደሰትን። በ1947 በሎስ አንጀለስ ተደርጎ የነበረው ስብሰባ ሊደርስ ሲል አንዲት አሮጌ መኪና ለመግዛት ቻልን። ስብሰባው ላይ እንዳለን በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ሚስዮናዊ ሥልጠና ለማግኘት ማመልከቻ ስለማቅረብ ማሰብ ጀመርን።
ይህ ትልቅ እርምጃ እንደሆነ ስለተገነዘብን ዩናይትድ ስቴትስን ለመልቀቅ በችኮላ ለመወሰን አልፈለግንም ነበር። ልጆቼን በማጣቴ ገና እየተጨነቅሁ ስለነበር አንድ ጊዜ እንደገና የልጆቼ አሳዳጊ የመሆን መብት ፍርድ ቤት እንዲሰጠን ሞክረን ነበር። በቀድሞው አኗኗሬ ምክንያትና ባጋጠመኝ እሥራት ምክንያት ልጆቼን የማሳደግ መብት ለመቀበል ያደረግሁት ሙከራ ከንቱ ሆኖ ቀረ። ስለዚህ ሚስዮናዊ ለመሆን ሙከራ ለማድረግ ወሰንን። ለ12ኛው የጊልያድ ትምህርት ተጋበዝን።
ከትምህርት ቤቱ በ1949 ተመረቅንና መጀመሪያ በቴኔሲ ጉባኤዎችን እንድንጎበኝ ተመደብን። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተጓዥነት ሥራ ሦስት ዓመት ካሳለፍን በኋላ ከስብከቱ ሥራ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ለማስተማር ፈቃደኞች መሆናችንን የሚጠይቅ ደብዳቤ ከመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት ቢሮ ደረሰን። የኢትዮጵያ መንግሥት ሚስዮናውያን ከሚፈልግባቸው ነገሮች አንዱ ማስተማር ነበር። እኛም በነገሩ ተስማማንና በ1952 የበጋ ወራት ወደ ኢትዮጵያ ሄድን።
ኢትዮጵያ ስንደርስ ጧት ጧት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን እናስተምርና ከሰዓት በኋላ ደግሞ ነፃ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንመራ ነበር። ወዲያው ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ በጣም ብዙ ሰዎች መምጣት ስለጀመሩ በየቀኑ ሦስት ወይም አራት ሰዓት መጽሐፍ ቅዱስን እናስተምር ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ከሚማሩት አንዳንዶቹ ፖሊሶች ነበሩ፣ ሌሎቹ ደግሞ ከሌሎች ሚስዮናዊ ትምህርት ቤቶችና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ትምህርት ቤቶች የሚመጡ መምህራን ወይም ዲያቆናት ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ በያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ክፍል ውስጥ 20 ወይም ከዚያ የሚበልጡ ይገኙ ነበር። ከተማሪዎቹ ብዙዎቹ የሐሰት ሃይማኖትን ትተው ይሖዋን ማገልገል ጀምረው ነበር። በደስታ እንፈነድቅ ነበር። አሁንም እንደገና በየጧቱ ስነቃ ለይሖዋ ምስጋና አቀርብ ነበር።
ልጅ ወልዶ በእገዳ ሥር ማገልገል
በ1954 ወላጆች ለመሆን በመንገድ ላይ መሆናችንን ተረዳን፤ ስለዚህ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመልሰን ለመሄድ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት መወሰን ነበረብን። በእርግጥ በኢትዮጵያ መቆየታችን ሰብአዊ ሥራ በማግኘቴ ላይ የተመካ ነበር። በንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ የሬድዮ ጣቢያ የቴክኒሻንነት ሥራ አገኘሁ። ስለዚህ እዚያው ቆየን።
መስከረም 8, 1954 ሴት ልጃችን ጁዲት ተወለደች። ለንጉሠ ነገሥቱ ስለምሠራ የሥራ ዋስትና ያለኝ መስሎኝ ነበር፤ ነገር ግን ከሁለት ዓመት በኋላ ይህን ሥራ አጣሁ። ይሁን እንጂ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በፖሊስ መምሪያው ባለ ሁለት መሥመር ሬድዮኖችን የመጠገን ሥራን ለአንድ የወጣት ወንዶች ቡድን እንዳስተምር በከፍተኛ ደመወዝ ተቀጠርኩ። በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ ፊሊፕና ሌስል የተባሉት ወንዶች ልጆቻችን ተወለዱ።
በመሃሉ በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ያለን ነፃነት በመለወጥ ላይ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት የይሖዋ ምስክሮችን ሚስዮናውያን በሙሉ ካገር እንዲያስወጣ አግባባች። ማኅበሩ በመከረኝ መሠረት ቪዛዬን ከሚስዮናዊነት ሥራ ወደ መንግሥት ሥራ አስቀየርኩ። የሚስዮናዊነት ሥራችን ታገደ፣ እኛም ጥንቁቆችና ልባሞች መሆን አስፈለገን። ሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች አላቋረጡም ነበር፤ ቢሆንም የምንሰበሰበው ትናንሽ የጥናት ቡድኖች በመሆን ነበር።
ፖሊሶች ምስክሮች እንደሆኑ የጠረጠሯቸውን የብዙ ሰዎችን ቤት ይፈትሹ ነበር። ይሁን እንጂ እነርሱ ሳያውቁት ይሖዋን የሚያገለግል አንድ የፖሊስ መቶ አለቃ ፍተሻው መቼ እንደሚደረግ ሁልጊዜ ይነግረን ነበር። በመሆኑም በእነዚያ ዓመታት ውስጥ ምንም ጽሑፍ አልተወረሰብንም ነበር። እሁድ እሁድ በከተማው ዳርቻ ወዳሉ ምግብ ቤቶች እየሄድን ከቤት ውጭ ለመብላት በሚያገለግሉ የመናፈሻ ጠረጴዛዎች ዙሪያ የመጠበቂያ ግንብ ጥናታችንን እናደርግ ነበር።
ለፖሊስ እጩ መኮንኖች ሬድዮ ሳስተምር በነበርኩበት ወቅት በመጀመሪያው ላይ የጠቀስኩት ተማሪ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳስጠናው የጠየቀኝ በዚህ ጊዜ ነበር። ለማጥናት ከልብ የሚፈልግ እንደሆነ ስለተሰማኝ ጥናቱን ጀመርን። ሁለት ጊዜ ካጠናን በኋላ ከእርሱ ጋር ሌላ ሁለተኛ ተማሪ መጣ፣ ሦስተኛም ቀጠለ። ከእኔ ጋር እንደሚያጠኑ ለማንም እንዳይነግሩ አስጠነቀቅኋቸው፣ ደግሞም ለማንም አልነገሩም።
በ1958 መለኮታዊው ፈቃድ በተባለው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ በኒው ዮርክ ያንኪ ስቴድየምና ፖሎ ግራውንድስ ላይ ይደረግ ነበር። በመሀሉ ፔጊና ሀንክ እንዲሁም የሠፊው ቤተሰቤ ብዙ አባሎች በትጋት የሚያገለግሉ ምስክሮች ሆነው ነበር። በስብሰባው ላይ ለመገኘት በመቻሌ ምንኛ ተደሰትኩ! ከሁለቱ የመጀመሪያ ልጆቼና ከሌሎቹ የቤተሰቤ አባሎች ጋር ለመገናኘት በመቻሌ ብቻ ሳይሆን በስብሰባው የመጨረሻ ቀን ከሩብ ሚልዮን በላይ የሆኑ ብዙ ሕዝብ ተሰብስበው በማየቴ ስሜቴ በደስታ ተነካ።
በተከታዩ ዓመት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ናታን ኤች ኖር ሊጎበኘን ወደ ኢትዮጵያ መጣ። በእገዳው ሥር ሥራውን ለመቀጠል ጥሩ ጥሩ ሐሳቦች ሰጠን። እንዲሁም ቤተሰባችን በነበረው መንፈሳዊ ሁኔታ ተደስቶ ነበር። ልጆቻችን እንዲጸልዩ እንደምናስተምራቸው ገለጽኩለት። ጁዲት ጸሎቷን ስታቀርብ ለመስማት ይፈልግ እንደሆነ ጠየቅሁት። እሱም እሺ አለና ከጸሎቱ በኋላ “በጣም ጥሩ ነው ጁዲት” አላት። ከዚያም በምግብ ሰዓት ወንድም ኖር ጸሎት እንዲያደርግልን ጠየቅሁትና ሲጨርስ ጁዲት “በጣም ጥሩ ነው ወንድም ኖር!” አለችው።
ልጆቻችንን በዩናይትድ ስቴትስ አሳደግን
ከፖሊስ መምሪያው ጋር የነበረኝ ኮንትራት በ1959 አበቃ። መቆየት ፈልገን ነበር፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ኮንትራቱን ለማሳደስ አልፈቀደልኝም። ታዲያ የት ልንሄድ እንችል ይሆን? ወንድሞች በጣም ወደሚያስፈልጉባቸው ሌሎች አገሮች ለመሄድ ብሞክርም አልተቻለም። እያዘንን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስን። እዚያም ስንደርስ ከቤተሰብ ጋር እንደገና በመገናኘታችን ተደሰትን፤ አምስቱም ልጆቼ እርስ በርሳቸው ተዋወቁና ገና እንደተያዩ ተዋደዱ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በጣም ይቀራረባሉ።
መኖሪያችንን የሬዲዮ ቴክኒሻንነት ሥራ ባገኘሁበት በዊሺታ ካንሳስ አደረግን። ሉሴል የቤት ውስጥ ሥራዎችን ታከናውን ነበር፣ ልጆችም ለቤት ቅርብ በሆነ ትምህርት ቤት ይማሩ ነበር። በየሰኞ ምሽቱ ለቤተሰቦቼ የመጠበቂያ ግንብ ጥናትን ስመራ ሁልጊዜ ስሜት የሚቀሰቅስና አስደሳች ለማድረግ እጥር ነበር። በትምህርት ቤት ችግር አጋጥሟቸው እንደሆነ በየቀኑ እንከታተል ነበር።
ልጆቹ በቲኦክራቲካዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መካፈል ሲጀምሩ ይህ ማሠልጠኛ ለትምህርት ቤት ጥናታቸውም ረዳቸው። ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በመስክ አገልግሎት አሠለጠንናቸው። በሰዎች ቤት በር ላይ ጽሑፎችን ማበርከት ለምደው ነበር፣ በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይም ከእኛ ጋር ይገኙ ነበር።
አንዱ ሌላው ያለውን ነገር ባንድ ጊዜ ሊያገኝ እንደማይችል ለልጆቹ በማስረዳት ስለ ሕይወት መሠረታዊ ነገሮችንም ለማስተማር ሞክረናል። ለምሳሌ ያህል ሁልጊዜ ለሁሉም የሚሆን ስጦታ ባንድ ጊዜ ሊገኝ አይችልም ነበር። “ወንድምህ ወይም እህትህ አሻንጉሊት ቢሰጠውና ላንተ ወይም ላንቺ ግን ባይገኝ ማጉረምረም ተገቢ ነውን?” በማለት ከእነርሱ ጋር ምክንያት እያቀረብን እንነጋገር ነበር። በእርግጥ በሌሎች ጊዜያት ሌሎቹ ልጆች ደግሞ ሌላ ስጦታ ይቀበሉ ስለነበር ችላ የተባለ ልጅ አልነበረም። ምንጊዜም ሁሉንም ልጆች እናፈቅራቸው ስለነበር ከሁለቱ ልጆች አብልጠን ለአንዱ ልጅ አድልዎ አናደርግም ነበር።
አንዳንድ ጊዜ የእኛ ልጆች እንዲያደርጉ ያልተፈቀደላቸውን ነገር ሌሎች ልጆች ግን እንዲያደርጉ ይፈቀድላቸው ነበር። “እገሌ ያደርገዋል፣ እኛስ ለምን አናደርገውም?” ሲሉ በተደጋጋሚ እሰማ ነበር። ለማስረዳት እሞክራለሁ፣ አንዳንድ ጊዜ ግን መልሱ “እናንተ የዚያ ቤተሰብ ልጆች አይደላችሁም፤ የብሩምሌይ ቤተሰብ ናችሁ። እኛ ደግሞ የተለዩ ደንቦች አሉን” የሚል ብቻ መሆን ነበረበት።
በፔሩ ማገልገል
ከኢትዮጵያ ከተመለስን ጀምሮ ሉሴልና እኔ እንደገና በሚስዮናዊነቱ ሥራ ለመካፈል እንናፍቅ ነበር። በመጨረሻ በ1972 በደቡብ አሜሪካ ወደሚገኘው ወደ ፔሩ ለመሄድ አጋጣሚ አገኘን። በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልላቸው ሳሉ ልጆቻችንን ለማሳደግ ከፔሩ የተሻለ ቦታ ልናገኝ አንችልም ነበር። እነርሱም ከሚስዮናውያን፣ ከልዩ አቅኚዎችና በፔሩ ለማገልገል ከመጡ ከሌሎች ጋር የነበራቸው መቀራረብ የመንግሥቱን ጥቅሞች ከልባቸው የሚያስቀድሙ ሰዎች ምን ያህል ደስተኞች እንደሆኑ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። ፊሊፕ ይህን ቅርርቦሽ ገንቢ የሆነ የእኩያ ግፊት ነው ብሎታል።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ካንሳስ ያሉ የቀድሞ ወዳጆቻችን እኛ በመንግሥቱ አገልግሎት አግኝተነው የነበረውን መልካም ውጤት ሰምተው ወደ ፔሩ መጡና ከእኛ ጋር መኖር ጀመሩ። ቤታችንን የሚስዮናዊ ዓይነት ቤት አድርጌ አደራጀሁት። ሁላችንም በመስክ አገልግሎቱ ለመካፈል እንችል ዘንድ እያንዳንዳችን ለቤት ውስጥ ሥራ እንደለደል ነበር። በየቀኑ ጧት በማዕድ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅስ እንወያይ ነበር። ለሁላችንም አስደሳች ጊዜ ነበር። አሁንም እንደገና በየጧቱ ከእንቅልፌ ስነቃና የትና ለምን እዚያ እንዳለሁ ስገነዘብ ለይሖዋ ጥልቅ ምስጋና አቀርብ ነበር።
ከጊዜ በኋላ ጁዲት አገባችና ወደ ስቴትስ ተመለሱ። እዚያም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ቀጠለች። ፊሊፕ ከሦስት ዓመት የልዩ አቅኚነት አገልግሎት በኋላ በብሩክሊን ኒው ዮርክ ለቤቴል አገልግሎት አመለከተና ተቀባይነት አገኘ። በመጨረሻም ሌስልም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለሰ። ሁሉም ተለይተውን ሲሄዱ ካደረግንላቸው ነገር ሁሉ የበለጠው ወደ ፔሩ ይዘናቸው መምጣታችን መሆኑን ደስታና የመለየት ኀዘን በተቀላቀለበት ስሜት ይነግሩን ነበር።
የፔሩ ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ ሲሄድ እኛም ፔሩን ትተን መሄድ እንዳለብን ተገነዘብን። በ1978 ወደ ዊሺታ ስንመለስ የስፓንኛ ተናጋሪ ምስክሮች ቡድን አገኘን። ከእነርሱ ጋር እንድንቆይና እንድንረዳቸው ጠየቁንና እኛም በደስታ አደረግነው። ጉባኤ ተቋቋመና ወዲያው ከዚያ በፊት እንዳገለገልንባቸው ጉባኤዎች ለእኛ የተወደደ ጉባኤ ሆነ።
ኢኳዶር ተጠራች
በከፊል ሽባ የሚያደርግ የደም መርጋት በሽታ ቢያጋጥመኝም ሉሴልና እኔ እንደገና በሌላ አገር ለማገልገል እንችል ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርግ ነበር። በ1984 አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በኢኳዶር ስላለው ዕድገትና ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንደሚያስፈልጉ ነገረን። በሽባነቴ ምክንያት በመስክ አገልግሎቱ ልሠራ የምችለው በጣም ጥቂት መሆኑን ጠቀስኩለት፤ እርሱ ግን የ65 ዓመት ዕድሜ ያለኝ ግማሽ ጎኔ ሽባ የሆነ ሽማግሌ ብሆንም እንኳን ጠቃሚ ልሆን እንደምችል አረጋገጠልኝ።
እርሱ ከሄደ በኋላ ወደ ኢኳዶር ለመሄድ ስለመቻላችን ስንነጋገር ሌሊቱን በሙሉ ልንተኛ አልቻልንም። ሉሴል እንደኔው ለመሄድ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራት። ስለዚህ የተባይ ማጥፊያ አነስተኛ ንግዳችንን ለመሸጥ ማስታወቂያ አወጣንና በሁለት ሳምንት ውስጥ ሸጥነው። ቤታችንን በአሥር ቀን ውስጥ ሸጥነው። ስለዚህ በእርጅና ዘመናችን ከሁሉ የበለጠ ደስታችን ወደሆነው በውጭ አገር ሚስዮናዊነት አገልግሎት ተመለስን።
ኩዊቶ በሚባል ሥፍራ መኖር ጀመርን፤ የመስክ አገልግሎትም አስደሳች ነበር። በየቀኑም አዳዲስ ተሞክሮ ወይም አጋጣሚ ያስገኝልን ነበር። ይሁን እንጂ በ1987 እኔ የአንጀት ካንሰር እንዳለብኝ በሐኪም ተነገረኝ፤ አስቸኳይ ቀዶ ህክምና ያስፈልገኝ ነበር። ለቀዶ ህክምናውም ወደ ዊሽታ ተመለስን፤ ቀዶ ህክምናውም የተሳካ ሆነ። እንደገና ካንሰር ሲገኝብኝ ወደ ኩዊቶ ከተመለስን ገና ሁለት ዓመታችን ነበር፤ ስለዚህ ለዘለቄታው ወደ ስቴትስ መመለስ ግዴታ ሆነብን። አሁን እየኖርን ባለንበት በሰሜን ካሮላይና መኖር ጀመርን።
በብዙ ነገር ሙሉ የሆነና የሚያረካ ሕይወት
በሕይወት የመቀጠል ሁኔታዬ አስተማማኝ አይደለም። በ1989 ትልቁ አንጀቴ በቀዶ ህክምና ተቆርጦ መውጣት ነበረበት። ቢሆንም በሽማግሌነት እያገለገልኩና እቤቴ ድረስ ከሚመጡ ሰዎች ጋር አያሌ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እየመራሁ ነው። በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ቃል በቃል የእውነትን ዘሮች በመዝራት፣ ውኃ በማጠጣት ወይም በመኮትኮት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ረድተናል። ይህም ምንም ያህል ጊዜ ቢደጋገምም ምን ጊዜም ትዝታው የማይደበዝዝ ነው።
በተጨማሪም ልጆቼ በሙሉ ይሖዋን ሲያገለግሉ በማየቴ ከፍተኛ ደስታ አለኝ። ፔጊ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ፖል ሞስኬ ከተባለው ባሏ ጋር በተጓዥ አገልጋይነት ሥራ ለ30 ዓመታት አብራው ሠርታለች። ፊሊፕና ሚስቱ ኤልሳቤጥ ከጁዲት ጋር ሆነው በኒው ዮርክ በልዩ ጊዜ አገልግሎት ቀጥለዋል። ሃንክና ሌስልም ከትዳር ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ምስክሮች ናቸው፤ ከ80 የሚበልጡ ዘመዶቻችንን ጨምሮ አራቱ ወንድሞቼና እህቶቼ ከነቤተሰቦቻቸው ሁሉም ይሖዋን እያገለገሉ ነው። ሉሴልም ወደ 50 ዓመት በሚጠጋው የትዳር ዘመናችን ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ የምታሳይ ክርስቲያን ሚስት ሆና ቆይታለች። በቅርብ ዓመታት እየተበላሸ የሄደውን ሰውነቴን በመንከባከብ ረገድ ለመርዳት ደስ የማይሉ ብዙ ሥራዎችን ያለማጉረምረም ስታከናውን ቆይታለች።
በእርግጥም ሕይወቴ ደስታ የተሞላበት ሆኖአል። ቃላት ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ አስደሳች ነበር። ይሖዋን ማገልገል በጣም አስደሳች ከመሆኑ የተነሳ በዚህች ምድር ላይ ለዘላለም እንዳመልከው ልባዊ ምኞቴ ነው። “እኔ ግን ለኃይልህ እቀኛለሁ፤ በምሕረትህም ማልዶ ደስ ይለኛል፤ በመከራዬ ቀን መጠጊያዬና አምባዬ ሆነኸኛልና” የሚሉትን የመዝሙር 59:16ን ቃላት ሁልጊዜ አስታውሳቸዋለሁ።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጆርጅ ብሩምሌይ ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ጋር
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጆርጅ ብሩምሌይና ሚስቱ ሉሴል