ይሖዋ በበረሐ እሥር ቤት ውስጥ ደግፎ አቁሞኛል
አይዛያ ምንዌ እንደተናገረው
ፍርድ ቤት አልቀረብኩም፤ የሠራሁትም ወንጀል አልነበረም። ሆኖም በሚለበልበው በአፍሪካ የሰሃራ በረሐ ውስጥ በሚገኝና ከባድ ሥራ በግዳጅ በሚሠራበት እሥር ቤት ውስጥ ተጣልኩ። ከሁሉ የሚብሰው ደግሞ ከወዳጆቼ መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ የት እንዳለሁ አያውቁም ነበር። ይህ የሆነው ከስምንት ዓመታት በፊት በ1984 የበጋ ወራት ነበር። እንዲህ ባለው አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዴት እንደወደቅሁ ልግለጽላችሁ።
በ1958 ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ ታላቅ ወንድሜ የይሖዋ ምሥክር ሆነ። አባቴና እናቴ ግን የምንኖርበትን አካባቢ ማለትም በናይጄሪያ አገር በአቢያ ግዛት የሚገኙትን የጎሣ አማልክት ያመልኩ ነበር።
በ1968 የቢያፍራ ጦር ሠራዊት አባል ሆንኩ። በጦር ሜዳ ላይ እንዳለሁ የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው የገለልተኝነት አቋም ትዝ አለኝና አምላክ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። ከጦርነቱ እንድተርፍ ከፈቀደ ከምሥክሮቹ እንደ አንዱ እንደምሆን ቃል ገባሁ።
ጦርነቱ ካለቀ በኋላ የገባሁትን ቃል ለመፈጸም አፋጣኝ እርምጃ ወሰድኩ። በሐምሌ ወር 1970 ተጠመቅሁና አቅኚ ሆኜ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ። ከጊዜ በኋላ በክርስቲያን ጉባዔ ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ ተሾምኩ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ሕጋዊ ዕውቅና ባላገኘበት የጎረቤት አገር በሚሲዮናዊነት እንዳገለግል የሚጋብዝ ደብዳቤ ከናይጀሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ደረሰኝ። ግብዣውን ተቀበልኩና በጥር ወር 1975 የይለፍ ወረቀቴን ይዤ ጉዞዬን ጀመርኩ።
እሥራት
በ1978 በአገሪቱ የሚኖሩትን ምሥክሮች ተዘዋውሬ እንድጎበኝ ተመደብኩ። የምሥክሮቹ ቁጥር ብዙ ስላልነበረ ጉባዔዎችንና ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ለመጎብኘት ብዙ መጓዝ ነበረብኝ። ብዙ ጊዜ በፖሊስ የፍተሻ ጣቢያዎች እጠየቅ ነበር። ሁለት ጊዜ ለአራት ቀናት ያህል ታስሬ ስለ ሥራችን ምርመራ ተደርጎብኛል።
ከዚያም በሰኔ ወር 1984 ወደ መስክ አገልግሎት ለመሰማራት ተዘጋጅተን በነበርንበት እሁድ ቀን ከእኛ ጋር ይግባባ የነበረ አንድ መኮንን ፖሊሶች የይሖዋ ምሥክሮችን ለማሠር እንደሚፈልጉ ነገረን። ከአንድ ሳምንት በኋላ ከቶጎ የመጣው ጃግሊ ኮፊቪና እኔ ታሠርን። ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰድንና በከተማው የሚኖሩትን የይሖዋ ምሥክሮችን ሁሉ ስም እንድንሰጥ ተጠየቅን። “ስማቸውን ካልሰጣችሁን አንፈታችሁም” አሉ።
እኔም “ፖሊሶች እናንተ ናችሁ። የምትፈልጉአቸውን ሰዎች ፈልጎ ማግኘት የእናንተ ሥራ ነው። እኔ የእናንተ ወኪል አይደለሁም” ስል መለስኩላቸው። 30 ደቂቃ ለሚያክል ጊዜ ከተከራከርን በኋላ እንደበድባችኋለን ብለው አስፈራሩን። ያም ሆኖ የክርስቲያን ወንድሞቻችንን ስም አልሰጠናቸውም። ከዚያ በኋላ ብዛት ያላቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መጻሕፍቴን በርብረው ለመውሰድ ወሰኑ።
በማረፊያ ቤት በቆየሁበት ጊዜ
ጃግሊና እኔ መጽሐፎቹን ተሸክመን ወደ ፖሊስ ጣቢያው ከተመለስን በኋላ አውርደን አስቀመጥናቸው። መጽሐፎቹን በምናወርድበት ጊዜ ከትልቁ መጽሐፍ ቅዱሴ ውስጥ አንድ ወረቀት ወደቀ። በአገሩ ውስጥ ያሉት ክርስቲያን ሽማግሌዎች ስም የተጻፈበት የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም ነበር። ቶሎ ብዬ ያዝኩትና ጨረማምቼ ኪሴ ውስጥ ጨመርኩት። ይሁን እንጂ አንደኛው ፖሊስ አይቶኝ ኖሮ መልሼ እንድሰጠው አዘዘኝ። በጣም አዘንኩ።
ወረቀቱ እኔና ጃግሊ መጽሐፎቹን አምጥተን በምናስቀምጥበት ክፍል ውስጥ በሚገኝ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ መጽሐፍ ተሸክሜ ወደ ክፍሉ ስገባ ወደ ጠረጴዛው ሄድኩና ወረቀቱን አንስቼ ኪሴ ውስጥ ጨመርኩት። ከዚያ በኋላ መጸዳጃ ቤት መሄድ እንደምፈልግ ነገርኳቸው። በፖሊስ ታጅቤ ወደ መጸዳጃ ቤት ሄድኩ። መጸዳጃ ቤት ገብቼ በሩን ከዘጋሁ በኋላ ወረቀቱን ቀዳድጄ በመጸዳጃው ቤቱ ጉድጓድ ውስጥ ከጨመርኩ በኋላ ውኃ ለቀቅኩበት።
ፖሊሶቹ የሆነውን ባወቁ ጊዜ በጣም ተናደዱ። ይሁን እንጂ አለቆቻቸው ቢያውቁ ቸልተኛ ሆናችሁ ወረቀቱን እንዲያጠፋ አድርጋችኋል ተብለው እንደሚወነጀሉ ስለፈሩ ዝም አሉ። ለ17 ቀናት በእስራት ካቆዩን በኋላ ወደሌላ ቦታ ስለምትወሰዱ ዕቃችሁን ያዙ ተባልን። በፕላስቲክ ከረጢት ውስጥ ጥቂት ልብሶች ያዝን። በተጨማሪም እኔ ሊጠይቀኝ የመጣ አንድ ሰው ደብቆ ያስገባልኝን መጽሐፍ ቅዱስ ከከረጢቱ ሥር አስቀመጥኩ።
ለምሥክሮቹ ወደሌላ ቦታ እንደምንወስድና የት እንደሚወስዱን ግን እንደማናውቅ ለማሳወቅ ችለን ነበር። በሚቀጥለው ቀን ማለዳ ማለትም ሐምሌ 4 ቀን 1984 መርማሪው ፖሊስ ቀሰቀሰን። ልብሶቹን ከቀረጢቱ አውጥተን በክንዳችን እንድንይዝ በመጠየቅ ፈተሸን። ይሁን እንጂ የመጨረሻውን ሸሚዝ ላወጣ ስል ልብሶቹን መልሰህ ክተታቸው አለኝ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱሴ ሳይገኝ ቀረ።
የበረሐው እሥር ቤት
ፖሊሶች ወደ አይሮፕላን ማረፊያ በመኪና ወሰዱንና በአንድ የወታደሮች አይሮፕላን ላይ ተሳፈርን። ከጥቂት ሰዓቶች በኋላ 2,000 የሚያክሉ ሰዎች ወደሚኖሩበት ትንሽ ከተማ ደረስን። በከተማው አጠገብ እስር ቤት አለ። ይህ ከተማ በጣም ከሚቀርበው ከተማ 650 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ ነበር። ከአይሮፕላኑ ወደ እስር ቤቱ ተወሰድንና ለወህኒ ቤቱ አዛዥ ተሰጠን። ቤተሰቦቻችንም ሆኑ ወዳጆቻችን የት እንደተወሰድን አያውቁም ነበር።
የተወሰድንበት ከተማ በሰሐራ በረሐ ውስጥ የሚገኝ አነስተኛ ለም ቦታ ነበር። ቁጥቋጦዎች፣ ጥቂት ዛፎችና በፀሐይ ከደረቀ ጭቃ የተሠሩ ቤቶች ይታዩበታል። አንድ ሜትር ወይም አንድ ሜትር ተኩል ያህል ብቻ በመቆፈር ውኃ ማግኘት ይቻላል። ይሁን እንጂ በዚያ የሚኖር አንድ የ31 ዓመት ሰው በዕድሜው ዝናብ ሲዘንብ ያየው አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ነገረን። አካባቢው እጅግ በጣም ይሞቃል። በእስር ቤቱ ውስጥ የሚገኝ የሙቀት መለኪያ 60 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የመዘገበበት ጊዜ እንደነበረ አንድ እስረኛ ነገረን። በጣም ኃይለኛ የሆነ ነፋስ እየነፈሰ ቆዳ የሚቆጠቁጥና ዓይን የሚያሳምም አሸዋ ያለማቋረጥ ይረጫል።
እዚህ የመጣ ማንኛውም ሰው የአገሪቱን የመጨረሻ አሰቃቂ ቅጣት ለመቀበል የተዘጋጀ መሆኑን መገንዘብ አያቅተውም። እሥር ቤቱ ከነፋስና ከፀሐይ መጠነኛ ከለላ በሚሰጥ ከፍ ያለ አጥር ተከቦአል። ይሁን እንጂ እስረኞቹ እንዳያመልጡ ለመከላከል ምንም ዓይነት አጥር አያስፈልግም። ምክንያቱም የት መሄድ ይቻላል? ከዚህች ከተማ ውጭ ለማምለጥ የሚፈልግ ሰው የሚጠለልበት አንድም ዛፍ እንኳን አይገኝም።
ወደ እሥር ቤቱ ከመግባታችን በፊት የወህኒ ቤቱ አዛዥ ፈተሸን። ያለንን ዕቃ በሙሉ ከከረጢታችን እንድናወጣ ጠየቀን። ሸሚዞቻችንን አንድ በአንድ ማውጣት ጀመርኩ። መጽሐፍ ቅዱሱን የሸፈነው ሸሚዝ ብቻ ሲቀር ከውስጥ ያለውን ሸሚዝ ለማሳየት ከረጢቱን ወደ እርሱ ከፍ አደረግኩና “እንድንይዝ የፈቀዱልን ይህን ብቻ ነው” አልኩት። በፍተሻው ረካና ወደ ውስጥ እንድንገባ ነገረን። ከመጽሐፍ ቅዱስ በስተቀር ምንም ዓይነት ሌላ ጽሑፍ አልነበረንም።
የእሥር ቤት ኑሮ
በጠቅላላ 34 የሚያክሉ እስረኞች ነበሩ። በአገሩ ከሚገኙት ወንጀለኞች በሙሉ በጣም አደገኛና ክፉ የሆኑት የሚገኙት በዚህ እስር ቤት ነበር። ብዙዎቹ ነፍሰ ገዳዮችና ሊታረሙ የማይችሉ ናቸው የተባሉ ነበሩ። ሁላችንም የምንተኛው ክፍት በሆነ መታጠቢያ ቤት በተከፈለ ሁለት ሠፊ ክፍል ውስጥ ነው። በመታጠቢያ ቤቱ እንደ መጸዳጃ ቤት የሚያገለግል ክፍት በርሜል አለ። ይህ በርሜል በየጠዋቱ በእስረኞች የሚደፋ ቢሆንም በበረሐው የሚገኙ ዝንቦች በሙሉ ከዚህ በርሜል ቅዝቃዜና ቆሻሻ ሊደሰቱ የመጡ ይመስል ነበር።
የሚሰጠን ምግብ ማሽላ ብቻ ነበር። ማሽላው በእስረኛው ከተፈጨ በኋላ ተቀቅሎ በየእስረኞቹ መኝታ ላይ እየተሰፈረ ይቀመጥልናል። ምግቡ አይከደንም። ከሥራ ስንመለስ በተቀቀለው ማሽላ ላይ በመቶ የሚቆጠሩ ዝንቦች ሠፍረው እናገኛለን። የምግብ ሣህኑን ስናነሳ ዝንቦቹ እየተመሙ ይሸሻሉ። በመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት ምንም ነገር አልበላንም። በሶስተኛው ቀን ግን ዝንቦቹን ካባረርንና ከላይ የደረቀውን ገፍፈን ካነሳን በኋላ መብላት ጀመርን። ይሖዋ ጤንነታችንን እንዲጠብቅልን ጸለይን።
አሮጌውን የእሥር ቤት አጥር እያፈረስን አዲስ አጥር እንሠራ ነበር። ሥራው በጣም ከባድ ነበር። ጠዋት ከ12 ሁለት ሰዓት ጀምረን እስከ ቀትር ድረስ አለአንዳች እረፍት ስንሠራ ከቆየን በኋላ ጥቂት ነገር በልተን እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት እንሠራ ነበር። የዕረፍት ቀን የለንም። ሙቀቱ ብቻ ሳይሆን በክረምቱ ወራት ብርዱ ያሠቃየን ነበር። ጨካኞቹ ዘበኞችም ያሠቃዩን ነበር።
መንፈሳዊ ጥንካሬአችንን ለመጠበቅ የተደረገ ጥረት
እኔና ጃግሊ ተደብቀን መጽሐፍ ቅዱስ እናነብ ነበር። ከምንባቡ ስለተማርናቸው ነገሮች አብረን እንነጋገራለን። መጽሐፍ ቅዱሳችን እንዳይወሰድብንና ሌላም ቅጣት እንዳይደርስብን ስለምንፈራ በግልጽ ለማንበብ አንችልም ነበር። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የጀመርኩለት እስረኛ ኩራዝ ስለነበረው ለእኔም ከመብራቱ ያካፍለኛል። ሌሊት በሰባትና በስምንት ሰዓት ገደማ ተነስቼ እስከ አሥራ አንድ ሰዓት ገደማ አነባለሁ። በዚህ መንገድ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብቤ ለመጨረስ ቻልኩ።
ለሌሎች እስረኞችም ሰበክን። አንድ እስረኛ ለወህኒ ቤቱ ኃላፊ ምን እያደረግን እንዳለን ነገረው። የእስር ቤቱ ኃላፊ ግን ባልጠበቅነው ሁኔታ የነበረውን የንቁ! መጽሔት ሰጠው። እስረኛው ደግሞ ለእኛ አሳልፎ ሰጠን። ይህን መጽሔት ደጋግሜ አነበብኩት። ማንበባችንና መስበካችን በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነን እንድንቆይ ረድቶናል።
ከወንድሞቻችን ጋር በደብዳቤ ተገናኘን
ደብዳቤ ለመጻፍም ሆነ ለመላክ አይፈቀድልንም። ይሁን እንጂ የተግባባነው አንድ ሰው እንደሚረዳን ነገረን። እዚህ እስር ቤት ከገባን ከስድስት ሳምንት በኋላ ነሐሴ 20 ቀን አንድ ደብዳቤ ለናይጄሪያ ኤምባሲ፣ አንድ ሌላ ደብዳቤ ደግሞ ወዳጆቼ ለሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ተደብቄ ጻፍኩ። ደብዳቤዎቹን አሸዋ ውስጥ ከቀበርኩ በኋላ ምልክት እንዲሆን አንድ ትልቅ ድንጋይ ጫንኩበት። በኋላም ወዳጃችን የሆነው ሰው መጥቶ አሸዋውን ቆፍሮ አውጥቶ ወሰዳቸው።
ሳምንታት አለፉ። ምንም ነገር አልሰማሁም። በኋላ ግን ደብዳቤዎቹ ባይደርሱ ነው በማለት ተስፋ ቆረጥሁ። ይሁን እንጂ ደብዳቤዎቹ ደርሰው ስለነበረ ምሥክር ባልንጀሮቻችን እኛን ለማስፈታት ትግሉን ተያይዘውት ነበር። ጉዳዩ ለናይጀሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደርሶ ስለነበረ የታሰርኩበትን አገር መንግሥት ለምን እንዲህ ባለው ወህኒ ቤት እንዳሰረኝ ጥያቄ አቀረበ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ህዳር 15 ቀን 1984 ጠዋት የጽዳት ሥራ እንድንሠራ ተወሰድን። ዘበኞቹ ወደ አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወሰዱኝና ጉድጓዱ ቢዘጋም ለብዙ ሳምንታት ሰዎች ሲጸዳዱበት የቆዩትን መጸዳጃ ቤት እንዳጸዳ አዘዙኝ። መጸዳጃ ቤቱ በዓይነ ምድር የተሞላ ነበር። ከእጆቼ በስተቀር ምንም ዓይነት መሣሪያ አልነበረኝም። ይህን ዓይነቱን የሚቀፍ ሥራ እንዴት እንደምሠራ በማሰብ ላይ እንዳለሁ የእስር ቤቱ ኃላፊ መጥቶ የአካባቢው አስተዳዳሪ ሊያነጋግረኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ።
እንደደረስኩ አስተዳዳሪው ስላጋጠመኝ ችግር ከአገሩ ፕሬዘዳንት ጋር እንደተነጋገረና ፕሬዘዳንቱም ስለሁኔታዬ እንደሰሙ ነገረኝ። በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ስም ዝርዝር ብሰጥ ወዲያው እንደምፈታና በማግስቱ በሚመጣው አይሮፕላን ልሄድ እንደምችል ገልጸውለታል። እኔም በድጋሚ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚፈልጉ ከሆነ እነርሱን ፈልጎ ማግኘቱ የፖሊስ ሥራ እንደሆነ ነገርኩት። አስተዳዳሪው ይህን የቀረበልኝን አማራጭ በጥሞና እንዳስብበት ነገረኝ። በጉዳዩ እንዳስብበት አራት ወይም አምስት ቀን ሰጠኝ። ከዚያ በኋላ ለመሄድ እንደምችል ተነገረኝና ዘበኞች አጅበውኝ ወደ ወህኒ ቤት ተመለስኩ። ወደ መጸዳጃ ቤቱ እንድመለስ ስላልተደረግኩ በጣም አመሰገንኩ።
ከአምስት ቀን በኋላ የአውራጃው አስተዳዳሪ አስጠራኝና ምን እንደወሰንኩ ጠየቀኝ። በወህኒ ቤታቸው እንድታሠር የተደረግኩት ስለ እውነተኛው አምላክ ስለ መሰከርኩ ብቻ እንደሆነና ምንም ሌላ ወንጀል እንዳልሠራሁ ነገርኩት። ሕጋዊ የይለፍ ወረቀትና የመኖሪያ ፈቃድ እንዳለኝ ነገርኩት። ያሉኝ ሰነዶች በሙሉ ትክክለኛ እንደሆኑና ወደ ማንኛውም ከተማ በምሄድበት ጊዜ ሁሉ ምንም የሚጎድለኝ ነገር አለመኖሩን ፖሊሶች ዘንድ ቀርቤ እንደማረጋግጥ ገለጽኩለት። ምንም ዓይነት የሠራሁት ወንጀል ከሌለ “የምቀጣው ለምንድን ነው? በአገሩ እንድኖር የማይፈለግ ከሆነ ለምን ከአገር እንድወጣ አይደረግም? እንዲህ ባለው ቦታ የምጣለው ለምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅኩት።
ለ15 ደቂቃ ያህል ተናገርኩ። ንግግሬን ከጨረስኩ በኋላ የተናገርኩትን ሁሉ በጽሑፍ እንዳሰፍርና ጽሑፉም ለፕሬዘዳንቱ እንደሚላክ ተነገረኝ። ወረቀት ተሰጠኝና አራት ገጽ ደብዳቤ ጻፍኩ።
በመጨረሻ ተለቀቅኩ
ከታሰርኩ ሰባት ወር እስኪሆነኝ ድረስ ማለትም እስከ ጥር 1985 ድረስ ስለ ጉዳዩ ምንም የሰማሁት ነገር አልነበረም። በዚህ ጊዜ ግን የእስር ቤቱ ኃላፊ መጥቶ ለናይጀሪያ ኤምባሲ ደብዳቤ ጽፌ እንደሆነ ጠየቀኝ። “አዎ ጽፌአለሁ” ስል መለስኩለት።
“ለምን ጻፍክ? ለምንስ አልነገርከኝም?” ሲል ጠየቀኝ።
ጉዳዩ እርሱን የማይመለከት እንደሆነ ነገርኩት። ቢሆንም እርሱ እኔን ለማሳሰር ያደረገው ነገር ስላልነበረ ስለእርሱ ምንም ዓይነት መጥፎ ነገር እንዳልጻፍኩ አረጋገጥኩለት። “እናቴ እንኳን የት እንዳለሁ አታውቅም” አልኩት። ከዚያም ደብዳቤውን እንዴት እንደላክሁ ለማወቅ ፈለገ። እኔ ግን አልነገርኩትም።
በሚቀጥለው ቀን ዘበኞቹ አንድ ላንድ ሮቨር መኪና አዘጋጅተው እኔና ጃግሊ ወደሌላ ቦታ እንደምንወሰድ ነገሩን። ከእስር ቤቱ ካወጡን በኋላ ልብሳችንን በሙሉ አውልቀው ፈተሹን። መጽሐፍ ቅዱሴን ካገኙ እንደሚወስዱብኝ አውቄ ስለነበረ መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናው ለነበረው ሰው ቀደም ሲል ሰጥቼው ነበር። ይህ ሰው በሚፈታበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክር እንደሚሆን ነግሮናል። እንደተናገረው የይሖዋ ምሥክር እንዲሆን እንጸልያለን።
ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከአገሩ እንድወጣ ተደረግኩና ወደ ናይጀሪያ ተመለስኩ። በየካቲት ወር 1985 የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አገልግሎቴን ጀመርኩ። ከ1990 ጀምሮ በናይጀሪያ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገለግላለሁ። ጃግሊ በኮት ዲቩዋር በታማኝነት በማገልገል ላይ ይገኛል።
ከዚህ ተሞክሮ ይሖዋ በጣም ከባድ የሆነ ተጽእኖ በሚያጋጥምበት ጊዜ እንኳን ደግፎ ሊያቆመን እንደሚችል ለማወቅ ችዬአለሁ። የይሖዋ እጅ በእሥር ቤት በነበርንበት ጊዜ ሁሉ በተደጋጋሚ ከጥቃት ሲከላከልልን ተመልክቼአለሁ። መፈታታችንም ይሖዋ አገልጋዮቹ የት እንዳሉና ምን ዓይነት መከራ ደርሶባቸው እንዳለ ብቻ ሳይሆን እንዴት ከፈተና እንደሚያወጣቸው ጭምር እንደሚያውቅ አስገንዝቦኛል። — 2 ጴጥሮስ 2:9