ከእስር ቤት አምልጬ እውነትን አገኘሁ
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስጀምር ከእስር ቤት ያመለጥኩ ወንጀለኛ ነበርኩ። ብዙም ሳይቆይ መዋሸት አቁሜ እንዴት እውነትን መናገር እንደምጀምር የሚፈትን ሁኔታ ከፊቴ ተደቀነ።
ኅዳር 1974 ዩ ኤስ ኤ ኖርዝ ካሮላይና ውስጥ በሚገኘው የፔንደር ግዛት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀረብኩ። ክሶቹ በመሣሪያ አስፈራርቶ መዝረፍ፣ አደገኛ በሆነ መሣሪያ በሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸምና በሰዓት ከ56 ኪሎ ሜትር በላይ በሆነ ፍጥነት ማሽከርከር በማይቻልበት ክልል ውስጥ በሰዓት 144 ኪሎ ሜትር ማሽከርከርን ያጠቃልላሉ። በሚቀጥለው ወር በሁሉም ክሶች ወንጀለኛ መሆኔ ተረጋገጠና በኖርዝ ካሮላይና ማረሚያ ቤት 30 ዓመት እንድታሰር ተፈረደብኝ። በዚህ ጊዜ ገና 22 ዓመቴ ነበር።
ያደግሁት ኒው ጀርሲ በምትገኘው ኒውአርክ ከተማ ነበር። ምንም እንኳ አባቴ የፖሊስ መኮንን ቢሆንም ሁልጊዜ ወላጆቼን አስቸግራቸው ነበር። ጊዜዬን ያሳለፍኩት በጠባይ ማረሚያዎችና በወጣት ጥፋተኛ መቅጫ ቦታዎች ነው። እንዲያውም አንድ ጊዜ አባቴ በሚሠራበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ታስሬ ነበር። የዚያን ዕለት ምሽት አባቴ የገረፈኝን መቼም ቢሆን አልረሳውም! ግርፋቱ ማንኛውንም በአሥራዎቹ እድሜ የሚገኝ ወጣት የሚለውጥ ነበር ለማለት ያስደፍራል፤ እኔ ግን አልተለወ ጥኩም።
ከቤት ጠፍቼ ከአንዱ ጓደኛዬ ጋር አለበለዚያም በየጎዳናው አድር ነበር። በመጨረሻም እንደገና ታሰርኩ። አባቴ እንድፈታ ባይፈልግም እናቴ አስፈታችኝ። ከእኔ ሌላ አምስት ልጆች ያሏቸው ወላጆቼ ውትድርና ሳይሻለው አይቀርም የሚል መደምደሚያ ላይ ደረሱ።
የሠራዊቱ አባል ሆንኩ፤ ለሠራዊቱ የሚሰጡት የተለያዩ የልምምድ ፕሮግራሞች ለጥቂት ጊዜ በጠባዬ ላይ ለውጥ አምጥተው ነበር። በኋላ ግን የሄሮይን ሱሰኛ በመሆን የአደንዛዥ ዕፆች ምርኮኛ ሆንኩ። ኖርዝ ካሮላይና ውስጥ በምትገኘው ፎርት ብራግ እንድሠራ ተመደብኩ፤ ብዙም ሳይቆይ እኔና ጓደኞቼ ሱሳችንን ለማርካት የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማግኘት ከከተማ ወደ ከተማ እየተዟዟርን መስረቅ ጀመርን። ስለ ፈጸምነው ዝርፊያ የሚገልጹ ዘገባዎች በጋዜጦችና በቴሌቪዥን ይቀርቡ ነበር።
ብዙም ሳይቆይ ባለሥልጣኖች ያዙኝና መግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው የ30 ዓመት እስራት ተፈረደብኝ። በእስር ቤት ለብዙ ዓመታት ሕጎችንና ደንቦችን እጋፋ ነበር፤ በኋላ ግን ራሴን ከመጉዳት በስተቀር ፋይዳ እንደሌለው ተገነዘብኩ። ስለዚህ እስራቱ ቀለል እንደሚልልኝና በአመክሮ እንደምፈታ ተስፋ በማድረግ ሕጎችን ለመታዘዝ ጥረት ማድረግ ጀመርኩ።
በእስር ቤት አሥር ዓመት ካሳለፍኩ በኋላ እስራቱ ቀለል ተደረገልኝ፤ እንዲሁም ብዙም ሳይቆይ ለሥራ ወደ ውጪ መውጣት እንድችል ተፈቀደልኝ። ያለምንም ጠባቂ ጠዋት ከእስር ቤት ወጥቼ ማታ መመለስ እችል ነበር። አንድ ቀን ከሥራ በኋላ ቶሎ ሳልመለስ ቀረሁ፤ በዚህ የተነሳ ወደ ውጪ እንዳልወጣ ተከለከልኩ። በዚህ ጊዜም ቢሆን ብዙም አይጫኑኝም ነበር።
በእስር ቤት 11 ዓመታት ካሳለፍኩ በኋላ በአመክሮ የመፈታቴ አጋጣሚ እጅግም ተስፋ የሚጣልበት አልነበረም። በነሐሴ ወር 1985 አንድ ሞቃት ጠዋት ከእስር ቤት ውጪ ሳለሁ ማንም ሳያየኝ ማምለጥ የምችልበት አጋጣሚ ተከፈተልኝ። በፊት አብሮኝ ታስሮ ወደ ነበረ አንድ ጓደኛዬ ቤት መንገዴን አቀናሁ። አንድ ቀን አድሬ ልብሴን ከለዋወጥኩ በኋላ 400 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ዋሽንግተን ዲ ሲ ከተማ በመኪና ወሰደኝ።
ወደ እስር ቤት ፈጽሞ ላለመመለስ ወሰንኩ፤ ይህ እንዲሆን ደግሞ ሌላ ምንም ዓይነት የወንጀል ድርጊት ከመፈጸም መታቀብ ነበረብኝ። መጀመሪያ ላይ ያገኘሁትን የቀን ሥራ እሠራ ነበር። ከዚያም በአንድ የኤሌክትሪክ ኩባንያ ውስጥ ተቀጠርኩ። ከጊዜ በኋላ ዴሪክ ማጄት በሚል ሌላ ስም የልደት ሰርተፍኬት አወጣሁ። አሁን ማንነቴን በተመለከተ ማንኛውም ነገር ማለትም ስሜ፣ የተወለድኩበት ቦታ፣ የሕይወት ታሪኬ፣ ቤተሰቤ የውሸት ነበር። አንድም ሰው እስካላወቀ ድረስ አደጋ እንደማይደርስብኝ ተሰምቶኝ ነበር። በዚህ ዓይነት መንገድ በዋሽንግተን ዲ ሲ እና በአካባቢዋ ሦስት ዓመት አሳለፍኩ።
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት
አንድ ቀን ምሽት ንጹህና ሥርዓታማ አለባበስ ያላቸው ሁለት ወጣቶች ወደምኖርበት አፓርታማ መጡ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ነገሩኝና ተመልሰው እንደሚመጡ ቃል ገብተው አንድ መጽሐፍ ትተውልኝ ሄዱ። ቢሆንም ወደ ሌላ አፓርታማ ስለተዘዋወርኩ ከዚያ በኋላ ፈጽሞ አላየኋቸውም። አንድ ቀን ጠዋት ቡና ለመጠጣት ከሥራ በፊት አንድ ቦታ ጎራ ብዬ ሳለ ከሁለት ሴቶች ጋር ተገናኘሁና መጠበቂያ ግንብ የተባለውን መጽሔት እፈልግ እንደሆነ ጠየቁኝ። አንድ መጽሔት ወሰድኩ፤ እነዚህ ሴቶች ከዚያን ቀን ወዲህ ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት እየመጡ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግሩኝ ነበር።
ምንም እንኳ ውይይቱ ሁልጊዜ አጭር የነበረ ቢሆንም እነዚህ ሴቶች የሚናገሩት ነገር ስሜቴን ማርኮት ስለነበር በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ከእነርሱ ጋር ማለትም ከሲንቲያ እና ከጃኔት ጋር የምገናኝበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቅ ነበር። ከጊዜ በኋላ ማልደው በመነሳት ጠዋት ሲሰብኩ ከነበሩ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተዋወቅሁ። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረግ አንድ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዙኝ። ስጋት አድሮብኝ የነበረ ቢሆንም ግብዣውን ተቀበልኩ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዱሳን ጽሑፎች ሊገባ በሚችል ሁኔታ ሲብራሩ የሰማሁት የዚያን ዕለት ከሰዓት በኋላ ተቀምጬ ንግግሩን ባዳመጥኩበት ጊዜ ነበር። በመጠበቂያ ግንብ አማካኝነት የሚደረገውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመከታተል እዚያው ቆየሁ፤ ጥያቄዎቹን በመመለስም ተሳትፎ ማድረግ እንደምችል ተገነዘብኩ። ለመጀመሪያ ጊዜ ሐሳብ ከመስጠቴም በተጨማሪ ከስብሰባው በኋላ ከአንዱ የጉባኤ ሽማግሌ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ተስማማሁ።
ብዙም ሳልቆይ በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እያደግሁ መጣሁ። ከሁሉ በላይ ደግሞ እየተማርኩት ያለሁትን እውነት አደንቅ ነበር። ያለ ሐሳብና ያለ ጭንቀት እኖርበት የነበረው ጊዜ አከተመ። አሁን ጓደኞቼ ለሆኑት ለእነዚህ ሰዎች ውሸት በመናገሬ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኝ ጀመር። አንድም ሰው ስለ እኔ እውነቱን እስካላወቀ ድረስ እንዲሁ መዝለቅ እችላለሁ ብዬ በማሰብ ጥናቴን ቀጠልኩ። ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚዬ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ስለመካፈል ያነጋግረኝ ጀመር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መላ ካልፈጠርኩ በስተቀር በአገልግሎት ወይም በመሰል እንቅስቃሴዎች መካፈል ፈጽሞ የማይቻል እንደሆነ ያስገነዘበኝ አንድ ነገር ተከሰተ። ለመኪናዬ ነዳጅ እየቀዳሁ ሳለ አንድ ሰው ከበስተጀርባዬ መጣና በኋላዬ በኩል እጆቼን ያዘኝ። ፍርሃት ዋጠኝ! በመጨረሻ ባለ ሥልጣኖች ያዙኝ ብዬ አሰብኩ። የቀድሞው የእስር ቤት ጓደኛዬ እንደሆነ ሳውቅ እንዴት ያለ እፎይታ ተሰማኝ! እንዳመለጥኩ ስላላወቀ ደጋግሞ በእውነተኛ ስሜ ይጠራኝ ነበር፤ ያልጠየቀኝ ጥያቄ አልነበረም።
ካመለጥኩ ቀን ጀምሮ እንዲህ ያለ ፍርሃት ተሰምቶኝ አያውቅም። ነገር ግን ይህ ያጋጠመኝ ነገር ቆም ብዬ እንዳስብ አደረገኝ። ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ ሳገለግል እውነተኛ ማንነቴን የሚያውቅ አንድ ሰው ከቤት ቢወጣስ? እኔ ውሸት እየተናገርኩ እንዴት በይሖዋ አገልግሎት ለመካፈልና እውነትን ለመናገር እችላለሁ? ምን ማድረግ አለብኝ? እንዲሁ ውሸት እየተናገርኩ በመኖር ጥናቴን ልግፋበት ወይስ ጥናቴን አቁሜ ወደ ሌላ ቦታ ልዘዋወር? ሁኔታው በጣም ግራ የሚያጋባ ስለሆነ ለጥቂት ጊዜ ከሌሎች ገለል ብዬ ማሰብ ነበረብኝ።
ውሳኔ ማድረግ
ወደ አንድ ቦታ ተጓዝኩ። ረጅሙ ሰላማዊ ጉዞ ልክ እንዳሰብኩት ራሴን ዘና ለማድረግ፣ ለማሰብና ምን ማድረግ እንዳለብኝ ለመወሰን እንዲረዳኝ ይሖዋን ለመጠየቅ አስችሎኛል። ወደ ዋሽንግተን ዲ ሲ ለመመለስ ጉዞዬን እስከተያያዝኩበት ጊዜ ድረስ ምንም አልወሰንኩም ነበር። በመንገድ ላይ እያለሁ መዋሸት አቁሜ እውነቱን ብቻ መናገር አለብኝ የሚል ውሳኔ ላይ ደረስኩ። ቢሆንም በተግባር መተርጎሙ ከውሳኔው ይበልጥ የሚከብድ ነበር። ሲንቲያን በደንብ ስለማውቃት ምሥጢር እንደማታወጣ እምነት በመጣል ነገርኳት። በይሖዋ ፊት ነገሮችን ማስተካከል እንደሚኖርብኝ ገለጸችልኝ። የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንዳነጋግር አሳሰበችኝ።
ትክክል እንደሆነች ስለማውቅ በሐሳቧ ተስማማሁ። ቢሆንም በሕጉ ረገድ ምን ማድረግ እንዳለብኝ እርግጠኛ ስላልነበርኩ በአካባቢው ለሚኖር አንድ ጠበቃ ደወልኩና ያለሁበትን ሁኔታ ነገርኩት። የኖርዝ ካሮላይናን ግዛት ደንቦች የሚያውቀው በዚያ የሚኖር ጠበቃ በመሆኑ በኖርዝ ካሮላይና ከሚገኝ ጠበቃ ጋር እንድገናኝ መከረኝ። ስለዚህ ከአንድ ጠበቃ ጋር ለመነጋገር ወደ ደቡብ ተጓዝኩ።
ኖርዝ ካሮላይና ወደምትገኘው ሮሊ ከተማ ስደርስ ከዋናዎቹ አውራ ጎዳናዎች በአንዱ ወደሚገኘው ወደ እስር ቤቱ ተጓዝኩ። መኪናዬን አቆምኩና ተቀምጬ ረጅሙን የሽቦ አጥር፣ በመጠበቂያ ማማ ላይ የተቀመጡትን የታጠቁ ዘቦችና አጥሩ ውስጥ ወዲያና ወዲህ የሚሉትን እስረኞች ዝም ብዬ ተመለከትሁ። ለ11 ረጅም ዓመታት እኔም እንዲህ ያለ እስረኛ ነበርኩ! የአሁኑ ውሳኔዬ ቀላል አልነበረም።
ያም ሆነ ይህ የስልክ ማውጫ መጽሐፍ አነሳሁና የአንድ ጠበቃ ስልክ መረጥኩ። ስልክ ደወልኩና ለመጀመሪያው ጠበቃ ነግሬው የነበረውን ነገር ለዚህኛውም ነገርኩት። ብዙ ጥያቄ አልጠየቀኝም። ክፍያው ስንት እንደሆነና ቀጠሮ ለማመቻቸት እንዲችል ዝግጁ ስሆን መደወል እንዳለብኝ ብቻ ነገረኝ። ወደ ዋሽንግተን ዲ ሲ ስመለስ በቀጥታ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚዬ ቤት ሄድኩ።
አስጠኚዬ፣ ሚስቱና ሴት ልጃቸው ልክ እንደ ቤተሰቤ ነበሩ። ስለዚህ ቤታቸው በሄድኩበት ምሽት እንዴት ብዬ እንደምናገር ተቸግሬ ነበር። ነገር ግን ከነገርኳቸው በኋላ ቀለል አለኝ። ያለ ምንም ማጋነን በጣም ደንግጠው ነበር። ቢሆንም መለስ ሲልላቸው ችግሬን በእኔ ቦታ ሆነው በመረዳት ከጎኔ ቆመው ደግፈውኛል።
ቀጥሎ ማድረግ ያስፈለገኝ ነገር ለጠበቃው የሚከፈል ገንዘብ ማግኘትና መቼ ወደ እስር ቤት መመለስ እንዳለብኝ መወሰን ነው። መጋቢት 1, 1989 ማለትም ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ለመመለስ ወሰንኩ። ነፃነት የማገኝባቸውን የመጨረሻ ቀናት ሥራ አቁሜ በደስታ ለማሳለፍ ብፈልግም ለጠበቃው የምከፍለው ገንዘብ ያስፈልገኝ ስለነበር ይህን ማድረግ አልቻልኩም።
ቀደም ሲል ከእስር ቤት ኮብልዬ ወጥቼ አሁን ለመመለስ ገንዘብ እያጠራቀምኩ መሆኔ ሁኔታው በጣም አስገረመኝ። አንዳንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር ትቶ ወደ ሌላ ቦታ የመሄድ ሐሳብ ወደ አእምሮዬ ይመጣብኝ ነበር። ቢሆንም ወዲያውኑ መጋቢት 1 ደረሰ። አስጠኚዬና መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስጠናቸው ሰዎች መካከል አንዱ አብረውኝ ወደ ሮሊ ሄዱ። ወደ ጠበቃው ቢሮ ሄድንና ለእስር ያበቁኝን ክሶች፣ ለምን ያህል ጊዜ እንድታሰር እንደተፈረደብኝና ለምን ወደ እስር ቤቱ ለመመለስ እንደፈለግሁ ተነጋገርን። ከዚያም ጠበቃው ወዴት እንደምወሰድ መረጃ ለማግኘት ወደ ዳኛው ቢሮ ደወለ። ዳኛው ወዲያውኑ ወደ እስር ቤት ሊመልሱኝ እንደሚችሉ አውቆ ነበር።
ወዲያውኑ ወደ እስር ቤት እመለሳለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ከጠበቃው ጋር ተነጋግረን በሚቀጥለው ቀን እመለሳለሁ ብዬ አስቤ ነበር። ነገር ግን በተወሰነው ውሳኔ መሠረት አራታችንም በጸጥታ ወደ እስር ቤቱ አመራን። ‘በሕልሜ ነው ወይስ በእውኔ?’ ብዬ ራሴን እንደጠየቅሁ አስታውሳለሁ። ቀጥሎ በዋናው በር ላይ መቆማችንና ጠበቃው ስለማንነቴ ለዘቡ ሲነገረው መስማቴን አውቃለሁ።
ወደ እስር ቤት መመለስ
በሮቹ ሲከፈቱ የምሰናበትበት ጊዜ እንደደረሰ ተረዳሁ። ከጠበቃዬ ጋር ተጨባበጥን። ከዚያም ከአስጠኚዬና እንደኔው መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያጠናው ሰው ጋር ተቃቀፍን። እንደገባሁ እጄን በሰንሰለት ታሠርኩና የለበስኳቸው ልብሶች በእስር ቤት የደንብ ልብስ ወደሚለወጡበት ቦታ ታጅቤ ተወሰድኩ። የእስር ቤት ቁጥር ተሰጠኝ፤ ቁጥሩ 210 52–OS ሲሆን የቀድሞ ቁጥሬ ነበር።
እስር ቤቱ አነስተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ስለነበር ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግበት ቦታ ተወሰድኩ። እንድይዝ የተፈቀደልኝ መጽሐፍ ቅዱሴንና በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ብቻ ነበር። ባለፉት ዓመታት አውቃቸው ከነበሩት እስረኞች ጋር ተቀላቀልኩ። ተይዤ የመጣሁ መስሏቸው ነበር፤ ነገር ግን የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ስለፈለግሁ በራሴ ፍቃድ ተመልሼ እንደመጣሁ ስነግራቸው ሁሉም እንዲህ ያለ የቂልነት ተግባር ሰምተው እንደማያውቁ ተናገሩ።
አስጠኚዬ ከነገረኝ የመጨረሻ ነገሮች አንዱ “ጥናትህን አታቁም” የሚል ነበር። ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜዬን መጽሐፍ ቅዱስንና ለዘላለም መኖር መጽሐፌን በማንበብ እንዲሁም ምን እንደደረሰብኝ ለሚያውቁ እኖርበት በነበረው ቦታ ለሚገኙ ጓደኞቼ ደብዳቤ በመጻፍ አሳልፍ ነበር። ደብዳቤ ከጻፍኩላቸው የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ዤሮምና ባለቤቱ ኧርሊን ይገኙበታል። ደብዳቤዬ አጭር ነበር፤ ጥቂት የምስጋና ቃላቶችንና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አብሬ ስላሳለፍኩት ጊዜ ምን እንደሚሰማኝ የሚገልጽ ሐሳብ የያዘ ነበር።
ብዙም ሳይቆይ ዤሮም ደብዳቤ ጻፈልኝና በይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ ላይ በሚያቀርበው ንግግር ላይ በጻፍኩት ደብዳቤ መጠቀም ይችል እንደሆነ ፈቃድ ጠየቀኝ። ምን እንደሚያስከትል የማውቀው ነገር ባይኖርም በነገሩ ተስማማሁ። ስለ እኔ የቀድሞ ታሪክ የሚያውቁ የይሖዋ ምሥክሮች ጥቂት ነበሩ። ስለዚህ ዤሮም ደብዳቤዬን ካነበበና እውነተኛ ስሜ ብራያን ኢ ጋርነር መሆኑን ካስተዋወቀ በኋላ “የሐሰት ስሙ ዴሪክ ማጄት ነው!” በማለት ሲናገር ብዙዎች በጣም ተደንቀው ነበር። ከዚያም እኔም በተራዬ ያልጠበቅሁት ነገር ሲከሰት በማየቴ በጣም ተደነቅሁ። ስብሰባዎችን እካፈልበት ከነበረው ፔትዎርዝ ጉባኤ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጉባኤዎችም ከሚገኙ ወንድሞችና እህቶችም የማበረታቻ ደብዳቤዎች ይጎርፉልኝ ጀመር።
ብዙም ሳይቆይ ከሴንትራል እስር ቤት በኖርዝ ካሮላይና ሊሊንግተን ከተማ ውስጥ ወደሚገኘው ቀለል ያለ ቅጣት ወዳለበት እስር ቤት ተዘዋወርኩ። እንደደረስኩ ስለ ሃይማኖታዊ ፕሮግራሞች ማጠያየቅ ጀመርኩ። የይሖዋ ምሥክሮች ሁልጊዜ ረቡዕ ማታ ማታ በእስር ቤቱ የትምህርት ቤት ክፍሎች ውስጥ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ሳውቅ ተደሰትኩ። ለእኔ ብቻ ሳይሆን በዚህ እስር ቤት ውስጥ ለሚገኝ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመማር ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው የሚሳዩትን ፍቅር፣ የሚሰጡትን ድጋፍና ለመርዳት የሚያደርጉትን ጥረት ፈጽሞ አልረሳውም። ቀድሞ አጠና እንደነበር ሲያውቁ በእስር ቤቱ ውስጥ የሚደረጉትን ስብሰባዎች ከሚመሩት ሽማግሌዎች አንዱ ወዲያውኑ ካቆምኩበት ጀምሮ ያስጠናኝ ጀመር።
ለአመክሮ መቅረብ
ብዙ ወራት ከተቆጠሩ በኋላ በአመክሮ ከሚፈታው ቦርድ ጋር እንደምገናኝ ተነገረኝ። ምንም እንኳ አምልጬ የነበረና ገና በቅርቡ የተመለስኩ ቢሆንም በአመክሮው ቦርድ ፊት ቀርቤ እንድጠየቅ ወይም ሌላው ቢቀር ጉዳዬን መርምረውት እንደነበር ማሳወቅ እንዳለባቸው ሕጉ ያዝዝ ነበር። በቅርቡ ለአመክሮ እንደምቀርብ ለጓደኞቼ አሳወቅኋቸው። አሁንም እንደገና ደብዳቤዎች ይጎርፉ ጀመር። የሚመጡት ግን ለእኔ ሳይሆን ለአመክሮ ቦርዱ ነበር።
ጉዳዬ እንደገና በአመክሮ ቦርዱ እንደሚታይ ጥቅምት 1989 ተነገረኝ። በጣም ፈነደቅሁ። ቢሆንም የቦርዱ አባላት መምጣት በሚገባቸው ቀን ከመቅረታቸውም በተጨማሪ የሚመጡበት ቀን ወሬው ጠፋ። በጣም ሐዘን ቢሰማኝም ወደ ይሖዋ ከመጸለይ ግን አልቦዘንኩም። ጥቂት ሳምንታት እንዳለፉ የአመክሮ ቦርዱ አባላት በእስር ቤቱ እንደሚገኙና በመጀመሪያ እኔ እንደምጠራ ለእኔና ለሌሎች ሁለት ሰዎች ኅዳር 8 ቀን ተነገረን።
ወደ ቢሮው ስገባ በወረቀት የተሞሉ ሁለት ዶሴዎችን ተመለከትኩ። አንዱ ከ1974 ወዲህ ያለውን መረጃ የያዘ የእኔ ፋይል ነው። ሌላኛው ግን ምን እንደያዘ እርግጠኛ አልነበርኩም ነበር። የእኔን ጉዳይ በተመለከተ አንዳንድ ነገሮችን ከተወያየን በኋላ አንደኛው የአመክሮ ቦርዱ አባል ሌላኛውን ዶሴ ከፈተው። በውስጡ ስለ እኔ የተጻፉ ብዙ ደብዳቤዎች ነበሩበት። ከእስር ቤት ካመለጥኩ በኋላ ከእነዚህ ሁሉ ሰዎች ጋር እንዴት እንደተዋወቅሁ ኮሚቴው ለማወቅ ፈልጎ ነበር። ስለዚህ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያሳለፍኩትን ተሞክሮ በአጭሩ ነገርኳቸው። ከዚያም ውጪ እንድቆይ ጠየቁኝ።
ነፃነትና አዲስ ሕይወት
ወደ ውስጥ ተጠርቼ ስገባ “ባስቸኳይ በገደብ ይፈታ” የሚለውን ውሳኔ ቦርዱ እንዳጸደቀው ተነገረኝ። ልቤ በደስታ ዘለለ። ዘጠኝ ወር ብቻ ከታሰርኩ በኋላ ተለቀቅሁ! አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለማጠናቀቅ የተወሰነ ጊዜ ወስዶ ስለነበረ ኅዳር 22, 1989 ከእስር ቤት ወጣሁ፤ በዚህ ጊዜ ግን መሮጥ አላስፈለገኝም ነበር።
ከተለቀቅሁ ዓመት ሳይሞላኝ ጥቅምት 27, 1990 ራሴን ለይሖዋ አምላክ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። በአሁኑ ጊዜ ዲያቆን ሆኜ ዋሽንግተን ዲ ሲ ከተማ ውስጥ ይሖዋን በደስታ እያገለገልኩ ነው። ሰኔ 27, 1992 እኔና ሲንቲያ አዳምስ በጋብቻ ተሳሰርን።
እንዲህ ያለው በፍቅር የተሳሰረ ዓለም አቀፍ ድርጅት አባል እንድሆን የረዱኝን ይሖዋን፣ ባለቤቴንና ቤተሰቧን እንዲሁም ሁሉንም ወንድሞችና እህቶች አመሰግናቸዋለሁ።— ብራያን ኢ ጋርነር እንደተናገረው።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
11 ረጅም ዓመታት ያሳለፍኩበት እስር ቤት
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከሲንቲያ ጋር