ዓመፀኛ ሰው ነበርኩ
ጊዜው ግንቦት 1, 1947 ሲሆን ቦታው ሲሲሊ ውስጥ ነው። ሴቶችንና ሕፃናትን ጨምሮ 3,000 የሚሆኑ ሰዎች ዓመታዊውን የሠራተኞች ቀን ለማክበር በአንድ ተራራ አጠገብ በሚያልፍ መንገድ ዳር ተሰብስበው ነበር። በአቅራቢያቸው ካሉት ኮረብታዎች በስተጀርባ የሚመጣውን አደጋ አላወቁም ነበር። ምናልባት ከዚያ በኋላ ስለተከሰተው አሳዛኝ ሁኔታ አንብባችሁ ወይም በፊልም ተመልክታችሁ ይሆናል። በዚያ ሥፍራ የደረሰው እልቂት የፖርቴላ ዴላ ዢኔስትራ እልቂት በመባል የሚታወቅ ሲሆን ለ11 ሰዎች መሞትና ለ56 ሰዎች መቁሰል ምክንያት ሆኗል።
በዚህ አሳዛኝ ድርጊት ውስጥ የተካፈልኩ ባልሆንም እንኳ ለዚህ ድርጊት ተጠያቂ የሆነው ተገንጣይ ቡድን አባል ነበርኩ። የዚህ ቡድን መሪ ከነበረው ከሳልቫቶሬ ጁሊያኖ ጋር በሞንቴሌፕሬ መንደር አብረን ነው ያደግነው። በአንድ ዓመት ብቻ ነበር የሚበልጠኝ። በ1942 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የ19 ዓመት ወጣት ሳለሁ በጦር ሠራዊቱ ውስጥ እንዳገለግል ጥሪ ቀረበልኝ። በዚያው ዓመት ትንሽ ቀደም ብሎ ከቪታ ሞቲዚ ጋር ተዋደድንና ተጋባን። ከጊዜ በኋላም ሦስት ወንዶች ልጆች ወለድን፤ የመጀመሪያው የተወለደው በ1943 ነው።
ዓመፀኛ የሆንኩበት ምክንያት
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ባበቃበት ዓመት በ1945 የሲሲሊ ነፃ አውጪ ግንባር ፈቃደኛ ሠራዊት (ኢ ቪ አይ ኤስ) ምዕራባዊ ዕዝ አባል ሆንኩ። ይህ ዕዝ የሲሲሊ ነፃ አውጪ ንቅናቄ (ኤም አይ ኤስ) ተብሎ የሚጠራው ተገንጣይ የፖለቲካ ፓርቲ የጦር ዕዝ ነበር። የኢ ቪ አይ ኤስ እና የኤም አይ ኤስ ሹማምንት በወቅቱ እየታደነ የነበረውን ሳልቫቶሬ ጁሊያኖን የእኛ ዕዝ አዛዥ አድርገው ሾመውት ነበር።
እኔና ሳልቫቶሬ ለደሴታችን ሲሲሊና ለሕዝባችን ባለን ፍቅር አንድ ሆነን ነበር። ይፈጸም በነበረው ግፍ በጣም እንበሳጭ ነበር። ስለዚህ የጁሊያኖ ቡድን ሲሲሊን የዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ 49ኛ ክፍለ ሀገር አድርጎ ለመቀላቀል የነበረውን ዓላማ ተቀበልኩት። ይህ ሊሆን እንደሚችል አድርጎ ለማመን የሚያስችል ምክንያት ነበርን? አዎን፣ ነበር፤ የኤም አይ ኤስ ባለ ሥልጣናት ከዋሽንግተን ዲ ሲ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸውና የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ሃሪ ኤስ ትሩማን ይህን ዓላማ እንደሚደግፉት አረጋግጠውልን ነበር።
ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ
እኔ የነበርኩበት ቡድን ዋነኛ ሥራ ታዋቂ ሰዎችን አፍኖ በመውሰድ ገንዘብ መጠየቅ ነበር። በዚህ መንገድ ለሚያስፈልጉን ቁሳቁሶች መግዣ የሚሆን ገንዘብ እናገኝ ነበር። “እንግዶቻችን” ብለን የምንጠራቸው አፍነን የምንወስዳቸው ሰዎች ምንም ጉዳት ደርሶባቸው አያውቅም። ስንለቃቸው እነሱን ለማስለቀቅ የተከፈለውን ገንዘብ መልሰው ማግኘት የሚችሉበት ደረሰኝ እንሰጣቸው ነበር። እኛ ድል ከተቀዳጀን በኋላ ደረሰኙን በማሳየት ገንዘባቸውን መልሰው መውሰድ እንደሚችሉ እንነግራቸው ነበር።
ወደ 20 በሚጠጉ የአፈና ድርጊቶችና በጦር ኃይል በተደራጀው በካራቢንዬሪ ብሔራዊ የፖሊስ ኃይል ሠፈር ላይ በጦር መሣሪያዎች በተሰነዘሩ ጥቃቶች ተሳትፌ ነበር። ይሁን እንጂ አንድም ሰው ገድዬ የማላውቅ መሆኔ በጣም ያስደስተኛል። ተገንጣይ ቡድናችን ይሰነዝረው የነበረው ጥቃት በፖርቴላ ዴላ ዢኔስትራ መንደር በተወሰደው ጥበብ የጎደለው እርምጃ ተደመደመ። እርምጃው የተቀነባበረው አሥራ ሁለት ገደማ በሚሆኑ የጁሊያኖ ቡድን አባላት ሲሆን የኮሙኒስት ፓርቲውን በመቃወም የተወሰደ እርምጃ ነበር።
ምንም እንኳ ጎረቤቶቻችንንና ደጋፊዎቻችንን ጨምሮ ተራ ሰዎች የተገደሉት ሆን ተብሎ ባይሆንም ይደግፉን የነበሩና የእኛን ጥበቃ እንደሚያገኙ ይሰማቸው የነበሩ ሰዎች እንደ ከዳናቸው ሆኖ ተሰማቸው። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የጁሊያኖን ሕገ ወጥ ቡድን አባላት የማደኑ ተግባር ያለምንም ፋታ ቀጠለ። ለፖሊስ ጥቆማዎች ከተካሄዱ በኋላ ብዙዎቹ ጓደኞቼ ተያዙ። መጋቢት 19, 1950 በቁጥጥር ስር ዋልኩና ታሰርኩ። በዚያው ዓመት የበጋ ወራት ጁሊያኖ ተገደለ።
እስራትና ፍርድ
በፓሌርሞ ወኅኒ ቤት ታስሬ ችሎት ፊት የምቀርብበትን ጊዜ እየተጠባበቅኩ በነበረበት ወቅት ከወጣቷ ሚስቴና ከሦስቱ ወንዶች ልጆቼ በመለያየቴ በጣም አዝኜ ነበር። ሆኖም ትክክል መስሎ ለተሰማኝ ነገር ለመጋደል የነበረኝ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ተስፋ እንዳልቆርጥ ረድቶኛል። ለጊዜ ማሳለፊያ ስል ማንበብ ጀመርኩ። አንድ መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ፍላጎት ቀሰቀሰብኝ። መጽሐፉ በ19ኛው መቶ ዘመን በፖለቲካ ምክንያት የታሰረው ሲልቪዮ ፔሊኮ የተባለ ጣሊያናዊ የሕይወት ታሪክ ነበር።
ፔሊኮ እስር ቤት ውስጥ ሳለ መዝገበ ቃላትና መጽሐፍ ቅዱስ ከእጁ እንደማይለይ ጽፏል። ምንም እንኳ እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ የሮማ ካቶሊኮች ብንሆንም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ነገር ሰምቼ አላውቅም ነበር። ስለዚህ አንድ ቅጂ ለማግኘት ለባለ ሥልጣናቱ ጥያቄ አቀረብኩ። መጽሐፍ ቅዱስ ማስገባት ክልክል እንደሆነ ቢነገረኝም የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ ወንጌሎች ተሰጡኝ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የተሟላ መጽሐፍ ቅዱስ አገኘሁ፤ ይህን መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ቅርስ አድርጌ እስካሁን ድረስ አስቀምጬዋለሁ።
በመጨረሻ በ1951 በሮም አቅራቢያ በምትገኘው በቪተርቦ፣ የተያዝኩበት ወንጀል በችሎት ፊት መታየት ጀመረ። ጉዳዩ 13 ወራት ከፈጀ በኋላ ሁለት የዕድሜ ልክ እሥራት ፍርዶችን ጨምሮ 302 ዓመት ተበየነብኝ! ይህ ማለት እስክሞት ድረስ ከእሥር ቤት አልወጣም ማለት ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን መማር
ወደ ፓሌርሞ ወኅኒ ቤት ስመለስ የጁሊያኖ የአክስት ልጅ የሆነ አንድ የቡድናችን አባል ወደ ታሰረበት ቦታ ተዛወርኩ። የተያዘው እኔ ከመያዜ ከሦስት ዓመት በፊት ነበር። ቀደም ሲል እስር ቤት ውስጥ ከስዊዘርላንድ የመጣ አንድ የይሖዋ ምሥክር አግኝቶት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን ግሩም ተስፋዎች ነግሮት ነበር። ይህ ምሥክር የተያዘው በዚያው በፓሌርሞ ከሚኖር ሌላ ምሥክር ጋር የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ምክንያት ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ይህ ምሥክር የተያዘው በቀሳውስት ቆስቋሽነት እንደሆነ በኋላ ሰማሁ።
ሕገ ወጥ በሆኑ እንቅስቃሴዎች እካፈል የነበረ ቢሆንም እንኳ በአምላክና በቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች አምን ነበር። ስለዚህ ቅዱሳን ተብለው ለሚጠሩት አምልኮታዊ ክብር መስጠት ቅዱስ ጽሑፋዊ እንዳልሆነና ከአሥሩ ትእዛዛት መካከል አንዱ ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን የሚከለክል መሆኑን ስረዳ በጣም ደነገጥኩ። (ዘጸአት 20:3, 4) የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ኮንትራት ገባሁ፤ እነዚህ መጽሔቶች በጣም ጠቃሚ ሆነው አግኝቼአቸዋለሁ። የማነበው ሁሉ ባይገባኝም ብዙ ባነበብኩ ቁጥር ከወኅኒ ቤቱ ሳይሆን ከሐሰት ሃይማኖት እስራትና ከመንፈሳዊ እውርነት ማምለጥ እንዳለብኝ ይበልጥ ተሰማኝ።
አምላክን ለማስደሰት ከፈለግኩ አሮጌውን ሰውነት አስወግጄ የዋህ የሆነውን የክርስቶስ ኢየሱስ ዓይነት አዲስ ሰውነት መልበስ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። (ኤፌሶን 4:20–24) ቀስ በቀስ ለውጥ ማድረግ ጀመርኩ። ሆኖም አብረውኝ ታስረው ለነበሩ ሰዎች አንዳንድ ነገሮችን ማድረግ የጀመርኩት ወዲያውኑ ነበር ማለት ይቻላል፤ በተጨማሪም እየተማርኩት ስለነበረው አስደናቂ ነገር ልነግራቸው እሞክር ነበር። በዚህ መንገድ ከ1953 ወዲህ ያለው ጊዜ አስደሳች ሆነልኝ። ሆኖም እንቅፋቶችም ነበሩ።
ከቄሱ የደረሰብኝ ተቃውሞ
መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ከተኮናተርኩ ከስድስት ወራት በኋላ ኮንትራቱ ተስተጓጎለ። ለእስረኞች የሚመጡትን ደብዳቤዎች ወደሚመረምረው ሰው ሄድኩና ሁኔታውን አስረዳሁት። መጽሔቶቹ እንዳይደርሱኝ ያገደው የእስር ቤቱ ቄስ መሆኑን ነገረኝ።
ቄሱን ማነጋገር እንድችል ጥያቄ አቀረብኩ። በውይይታችን ወቅት ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀምን አስመልክቶ እንደ ዘጸአት 20:3, 4 እና ኢሳይያስ 44:14–17 ያሉትን ጥቅሶች ጨምሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘሁትን ጥቂት እውቀት ገለጽኩለት። በተጨማሪም በማቴዎስ 23:8, 9 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን “በምድር ላይ ማንንም:- አባት ብላችሁ አትጥሩ” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት አሳየሁት። ቄሱ በዚህ በመናደዱ አንተ መሃይም ስለሆንክ መጽሐፍ ቅዱስ ሊገባህ አይችልም አለኝ።
ባሕርዬን መለወጥ ጀምሬ የነበረ መሆኑ በጀኝ እንጂ ምን አደርግ እንደነበረ አላውቅም። በረጋ መንፈስ “አዎን፣ ልክ ነው፤ መሃይም ነኝ። ሆኖም አንተ የተማርክ ብትሆንም እንኳ እኔን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማስተማር ምንም ያደረግከው ነገር የለም” አልኩት። ቄሱ የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች ለማግኘት መጀመሪያ የካቶሊክ ሃይማኖትን ለመተው ለፍትሕ ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረብ እንዳለብኝ ነገረኝ። ያለኝን ወዲያውኑ ባደርግም ጥያቄዬ ተቀባይነት አላገኘም ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንዱ ሆኜ መመዝገብ ቻልኩና መጽሔቶቹን እንደገና ማግኘት ቻልኩ። ሆኖም ይህ ብዙ ድካም ጠይቆብኛል።
በወኅኒ ቤት ውስጥ የመንግሥት አዳራሽ
ገንዘብ አግኝቼ ለቤተሰቦቼ መላክ እችል ዘንድ የእስር ቤቱ ዲሬክተር ሥራ እንዲሰጠኝ በተደጋጋሚ ስጠይቀው ቆየሁ። ሁልጊዜ ስጠይቀው ለአንተ ሥራ ከሰጠሁ ለሌሎቹም መስጠት አለብኝ፤ ይህ ደግሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነው ይለኝ ነበር። ሆኖም ነሐሴ 5, 1955 ጠዋት ላይ ዲሬክተሩ አንድ የምሥራች ነገረኝ፤ በእስር ቤቱ ውስጥ ጸሐፊ ሆኜ እንድሠራ ተፈቀደልኝ።
ሥራዬ የእስር ቤቱን ዲሬክተር አክብሮት ስላተረፈልኝ የመጋዘን ክፍሉን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚካሄድባቸው ስብሰባዎች ለማድረግ እንድጠቀምበት ፈቀደልኝ። በመሆኑም በ1956፣ መጋዘኑን የይሖዋ ምሥክሮች የመሰብሰቢያ ቦታዎች በሚጠሩበት ስያሜ መሠረት እንደ መንግሥት አዳራሽ አድርገን መጠቀም እንድንችል የተጣሉ የፋይል ማስቀመጫ ቁም ሳጥኖችን ጣውላዎች በመጠቀም አግዳሚ ወንበሮች ሠራሁ። በየሳምንቱ እሁድ ከሌሎች እሥረኞች ጋር እሰበሰብ የነበረ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ለማድረግ የምንሰበሰበው ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር 25 ይደርስ ነበር።
ከጊዜ በኋላ ቄሱ ስለማካሂደው ስብሰባ ሲሰማ በጣም ተቆጣ። በዚህም የተነሳ በ1957 የበጋ ወራት ከፓሌርሞ ወጥቼ በኤልባ ደሴት ወደሚገኘው የፖርቶ አትሱሮ እስር ቤት ተዛወርኩ። ይህ ቦታ መጥፎ ስም ያተረፈ ነው።
እስር ቤት ውስጥ ተጠመቅኩ
እዚያ እንደደረስኩ ለ18 ቀናት ለብቻዬ ታሰርኩ። መጽሐፍ ቅዱሴን እንኳ ሳይቀር ተነጥቄ ነበር። ይህ ከሆነ በኋላ የካቶሊክ ሃይማኖትን ለመተው እንዲፈቀድልኝ ለፍትህ ሚኒስቴር በድጋሚ ጻፍኩ። ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት በሮም የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እርዳታ ጠይቄ ነበር። ከአሥር ወራት በኋላ ለረጅም ጊዜ ስጠብቀው የቆየሁትን መልስ አገኘሁ። የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያደረግኩትን የሃይማኖት ለውጥ ተቀበለው! ይህ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሔቶችና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በቀላሉ እንዳገኝ የሚያስችል ብቻ ሳይሆን አንድ የይሖዋ ምሥክር በየጊዜው እየመጣ ጉብኝት እንዲያደርግልኝ ፈቃድ የሚሰጥ ነበር።
በኢጣሊያ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የሚሠራው ጁዜፔ ሮማኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጎበኘኝ ደስታዬ ወሰን አልነበረውም። በእስር ቤቱ ባለ ሥልጣናት ፈቃድ በመጨረሻ ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት ማሳየት የምችልበት ዝግጅት ተደረገ። ጥቅምት 4, 1958 የእስር ቤቱ ዲሬክተር፣ የዲሲፕሊን ሹሙና ሌሎች ባለ ሥልጣናት በተገኙበት ወንድም ሮማኖ እኔንና አንድ ሌላ እስረኛን የእስር ቤቱን አትክልት ውኃ ለማጠጣት በሚያገለግል አንድ ትልቅ ገንዳ ውስጥ አጠመቀን።
ምንም እንኳ ሁልጊዜ ከሌሎች እስረኞች ጋር መጠበቂያ ግንብ ማጥናት እችል የነበረ ቢሆንም ዓመታዊው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል የሚከበረው ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በመሆኑ ይህን በዓል በእስር ቤት ክፍሌ ውስጥ ብቻዬን ማክበር ነበረብኝ። ከመሰል ምሥክሮች ጋር እንደተሰበሰብኩ አድርጌ በማሰብ ዓይኔን ጨፍኜ እጸልያለሁ።
በእስር ቤት ውስጥ ደቀ መዛሙርት ማድረግ
በ1968 በፔዘሮ አውራጃ ወደሚገኘው ወደ ፎሶምብሮኔ እስር ቤት ተዛወርኩ። በዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለሌሎች በመንገር ጥሩ ውጤቶች አግኝቻለሁ። በእስር ቤቱ ክሊኒክ ውስጥ እሠራ ስለነበር ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በቀላሉ አገኝ ነበር። በተለይ ኤማንዌሌ አልታቪላ የተባለ አንድ እስረኛ ያደረገውን እድገት መመልከቱ የሚያስደስት ነበር። ለሁለት ወራት ካጠና በኋላ በሥራ 19:19 ላይ ያለውን ምክር ሥራ ላይ ማዋል እንዳለበት በመገንዘቡ የአስማት መጽሐፉን አስወገደ። ከጊዜ በኋላ ኤማንዌሌ የይሖዋ ምሥክር ሆነ።
በቀጣዩ ዓመት ከኔፕልስ የባሕር ዳርቻ ባሻገር በፕሮቺዳ ደሴት ወደሚገኘው እስር ቤት ተዛወርኩ። አሁንም ጥሩ ምግባር በማሳየቴ በክሊኒክ ውስጥ እንድሠራ ተደረገ። በዚያም ማሪዮ ሞሬኖ የተባለ ሥርአተ ቅባት የፈጸመ አንድ ካቶሊክ እስረኛ አገኘሁ። እሱም በሒሳብ ክፍል ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ይሠራ ነበር።
አንድ ቀን ምሽት ማሪዮ የሚነበብ ነገር እንድሰጠው ጠየቀኝና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለውን መጽሐፍ ሰጠሁት።a የሚያነበው ነገር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ወዲያው በመገንዘብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረ። በቀን ሦስት ፓኬት ሲጋራ ያጨስ የነበረው ማሪዮ ይህን ልማዱን እርግፍ አድርጎ ተወ። በተጨማሪም በእስር ቤት ውስጥ በሚያከናውነው የሒሳብ ሥራ ሳይቀር ሐቀኛ መሆን እንዳለበት ተገነዘበ። ለእጮኛውም መሰከረላትና እሷም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ተቀበለች። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እዚያው እስር ቤት ውስጥ ተጋቡ። በ1975 ኔፕልስ ውስጥ በተካሄደ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የማሪዮ ሚስት ተጠመቀች። ባልዋ በዚያው ቀን እስር ቤት ውስጥ መጠመቁን ስትሰማ ደስታዋ እጥፍ ድርብ ሆነ!
ወደ ፕሮቺዳ እየመጡ ከሚጠይቁኝ ምሥክሮች ጋር በየሳምንቱ መጫወት እንድችል ተፈቀደልኝ። በተጨማሪም ሊጠይቁኝ የሚመጡትን ምሥክሮች በጠያቂዎች ክፍል ውስጥ በሚገባ ለማስተናገድ ምግብ ማዘጋጀት እንድችል ተፈቀደልኝ። በአንድ ጊዜ እስከ አሥር የሚደርሱ ሰዎች ሊገኙ ይችላሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጉብኝት በሚያደርጉበት ጊዜ የሚያሳዩትን የስላይድ ፊልም እንዲያሳዩኝ ይፈቀድልኝ ነበር። በአንድ ወቅት 14 ምሥክሮች ሊጠይቁኝ በመጡ ጊዜ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት የመምራት መብት አግኝቻለሁ። ባለሥልጣናቱ ሙሉ በሙሉ እምነታቸውን ጥለውብኝ ነበር። በተወሰኑ ቀኖች አመሻሹ ላይ ከአንዱ የእስረኞች ክፍል ወደ ሌላው ክፍል እየሄድኩ እሰብክ ነበር።
በተለያዩ ወኅኒ ቤቶች 24 ዓመታት ካሳለፍኩ በኋላ በ1974 አንድ ዳኛ መጥቶ አነጋገረኝና ምሕረት እንዲደረግልኝ ማመልከቻ እንዳስገባ አበረታታኝ። እንደዚያ ማድረጉ በፖርቴላ ዴላ ዢኔስትራ በተካሄደው ጭፍጨፋ ተካፍያለሁ ብሎ ማመን ስለሚሆን ትክክል መስሎ አልታየኝም፤ ምክንያቱም እኔ በዚህ ጭፍጨፋ ፈጽሞ እጄ የለበትም።
እጅግ የተደሰትኩባቸው ወቅቶች
በ1975 ለተወሰነ ጊዜ ከእስር ቤት ወጥቶ መመለስ የሚቻልበት አዲስ ሕግ ወጣ። በዚህም ምክንያት በኔፕልስ ከተማ በይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የመገኘት አጋጣሚ አገኘሁ። ከዚያ በፊት ካየኋቸው ይበልጥ በርካታ የሆኑ ክርስቲያን ወንድሞችንና እህቶችን ያገኘሁባቸውን አምስት የማይረሱ ቀኖች አሳለፍኩ።
ልዩ ደስታ የፈጠረልኝ ነገር ከብዙ ዓመታት በኋላ ከቤተሰቤ ጋር እንደገና መገናኘት መቻሌ ነበር። ሚስቴ ቪታ ለእኔ ታማኝ ሆና የቆየች ሲሆን ልጆቼ ደግሞ በ20ዎቹና በ30ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ላይ ነበሩ።
ለበርካታ ጊዜያት ከእስር ቤት እየወጣሁ በተመለስኩበት በቀጣዩ ዓመት ከእስር ቤት እንድለቀቅ ማመልከቻ እንዳስገባ ሐሳብ ቀረበልኝ። የአመክሮ ጉዳዮችን የሚከታተለው ባለ ሥልጣን ስለ እኔ በጻፈው ሪፖርት ላይ ማመልከቻዬ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሐሳብ አቀረበ። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “በአሁኑ ጊዜ ማኒኖ የጁሊያኖን ትእዛዝ ያስፈጽም ከነበረው ደም የተጠማ ወጣት ጋር ሲነፃፀር ፈጽሞ ተለውጧል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፤ እሱ ነበር ብሎ ለመናገር በሚያስቸግር ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተለውጦ ሌላ ሰው ሆኗል።”
ከጊዜ በኋላ የእስር ቤቱ ባለ ሥልጣናት ምሕረት እንዲደረግልኝ ጥያቄ አቀረቡ። በመጨረሻም ምሕረት ተደረገልኝና ታኅሣሥ 28, 1978 ከእስር ቤት ተለቀቅኩ። ከ28 ዓመት በላይ በእስር ካሳለፉ በኋላ ነፃ ሰው መሆን ምንኛ የሚያስደስት ነው!
ፍትሕ የሚገኝበት ብቸኛው ተስፋ
በሳልቫቶሬ ጁሊያኖ ትእዛዝ ሥር ሆኜ በአፈና ድርጊት በመካፈል ለቤተሰቤና ለአገሬ ሰዎች እውነተኛ ነፃነት ያጎናጽፋል ብዬ ላመንኩበት ነገር ስዋጋ ነበር። ሆኖም ሰዎች ምንም ያህል በቅን ልቦና ቢነሳሱ በወጣትነት ዘመኔ አጥብቄ እፈልገው የነበረውን ፍትሕ ሊያመጡ እንደማይችሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምሬአለሁ። ከአድልዎ በመገላገል በእጅጉ የምንሻውን እፎይታ ሊያስገኝልን የሚችለው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንድገነዘብ ስላደረገኝ አመስጋኝ ነኝ።—ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ ራእይ 21:3, 4
እንዲህ ዓይነቱ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በባሕርዬ ላይ ያመጣውን ለውጥ ብዙ ጋዜጦች ዘግበውታል። ለምሳሌ ያህል ፔዜ ሴራ የተባለው ጋዜጣ የእስር ቤቱ ተቆጣጣሪ የተናገረውን በመጥቀስ እንዲህ ብሏል:- “ሁሉም እስረኞች እንደ ፍራንክ ቢሆኑ ኖሮ እስር ቤቶች አይኖሩም ነበር፤ ምግባሩ እንከን አይወጣለትም፤ ከማንም ጋር ተጣልቶ አያውቅም፤ አንድም ቀን ተወቅሶ አያውቅም።” አቬኒሬ የተባለ ሌላ ጋዜጣ ደግሞ እንዲህ ብሏል:- “ጥሩ ምሳሌ የሚሆን እስረኛ ነው፤ ፈጽሞ የተለየ ነው። ያደረገው ለውጥ ከሚጠበቀው በላይ ነው። ለኢንስቲትዩቶቹና ለእስር ቤቱ ሹሞች አክብሮት ያለው ሲሆን መንፈሳዊነቱ ወደር አይገኝለትም።”
የሚክስ ሕይወት
ከ1984 ጀምሮ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌና የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በሚጠሩበት መጠሪያ መሠረት አቅኚ ሆኜ በማገልገል ላይ ነኝ። በ1990 ከ15 ዓመታት በፊት የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ያካፈልኩት አንድ የእስር ቤት ጠባቂ ስልክ ደወለልኝና እሱና ቤተሰቡ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ነገረኝ።
ሆኖም ከሁሉ ይበልጥ ያስደሰተኝ ነገር የተከናወነው ሐምሌ 1995 ላይ ነበር። በዚያ ዓመት ውዷ ሚስቴ ቪታ በመጠመቋ ደስታዬ እጥፍ ድርብ ሆነ። ከብዙ ዓመታት በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ተቀበለች። በአሁኑ ጊዜ የእኔን እምነት የማይከተሉት ሦስት ልጆቼም ምናልባት አንድ ቀን ከአምላክ ቃል የተማርኩትን ነገር ይቀበሉ ይሆናል።
ሌሎች ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንዲማሩ በመርዳት ያገኘኋቸው ተሞክሮዎች ያስገኙልኝ ደስታ ወደር የለውም። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውን እውቀት ማግኘትና ይህን እውቀት ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ማካፈል መቻል ምንኛ የሚክስ ነው!—ዮሐንስ 17:3—ፍራንክ ማኒኖ እንደተናገረው
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሲሲሊ በአንድ ተራራ አጠገብ የሚገኘው ጭፍጨፋው የተካሄደበት ሥፍራ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1942 ስንጋባ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለእስር ቤት ጠባቂዎቹ እነግራቸው ነበር
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ጋር