“ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የነበረኝን አመለካከት እንድቀይር አድርጋችሁኛል”
አንድ ፖላንዳዊ የእስር ቤት ባለ ሥልጣን በጥቅምት 15, 1998 እትማችን ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ያከናወኑትን ሥራ አስመልክቶ የወጣውን ዘገባ ከተመለከቱ በኋላ ከላይ እንዳለው ብለው ነበር። “እንደ ድንጋይ የጠጠረ ልብ የነበራቸው ሰዎች ሲለወጡ” የሚለው ይህ ርዕስ የይሖዋ ምሥክሮች በፖላንድ ቮዉፍ ወህኒ ቤት ላሉ እስረኞች በመስበክ ያገኙትን ጥሩ ውጤት አስፍሯል።
ከላይ የተጠቀሰው መጠበቂያ ግንብ ለሕዝብ ይፋ ከመሆኑ በፊት መጽሔቱን ለእስረኞች ለማዳረስ ሲባል መስከረም 13, 1998 በቮዉፍ ወህኒ ቤት ለየት ያለ ስብሰባ ተደርጎ ነበር። በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ከተጋበዙት ሰዎች መካከል በአካባቢው ያሉ ምሥክሮች፣ የተጠመቁና ፍላጎት ያላቸው ሌሎች እስረኞች እንዲሁም በርካታ የወህኒ ቤቱ ባለ ሥልጣኖች ይገኙበታል። ተሰብሳቢዎቹ ከሰጧቸው አስተያየቶች አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው።
ከአምስት ዓመት በፊት እስር ቤቱ ውስጥ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር የሆነው የርዚ:- “በአቅራቢያችን ባሉት ጉባኤዎች የሚገኙ ወንድሞች እኛን ለመርዳት ምን ያህል ጥረት እንዳደረጉ ማንበብ በመቻሌ በጣም ተደስቻለሁ” ብሏል። አክሎም “ራሴን ለማሻሻል የማደርገውን ትግል እቀጥልበታለሁ። ይሖዋም እንዴት ሲቀርጸኝ እንደነበር መገንዘብ ችያለሁ።”
ዝዳሽዋፍ የተባለ ሌላ እስረኛ ደግሞ በእስር ቤቱ የሚካሄደውን የምሥክርነት ሥራ አስመልክቶ እንደዚህ ብሏል:- “በአሁኑ ወቅት አራት እስረኞች ለጥምቀት እየተዘጋጁ ሲሆን ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎችም በአዳራሻችን በምናደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘታቸውን ቀጥለዋል። ይህ ጽሑፍ በዚህ መስክ ለተጨማሪ ሥራ ይበልጥ እንድንቀሳቀስ የሚያደርግ ነው።” ዝዳሽዋፍ ገና 19 ዓመታት የሚቀሩት እስረኛ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ይህ እንዴት ያለ አዎንታዊ አመለካከት ነው!
አንድ የእስር ቤቱ ባለ ሥልጣን ስለ ቮዉፍ ወህኒ ቤት የወጣውን ጽሑፍ ካነበቡ በኋላ እንዲህ ብለዋል:- “ይህ ለእኛ ትልቅ ክብር ነው። ይህን ወህኒ ቤት በሚመለከት በዓለም ዙሪያ በ130 ቋንቋዎች እንደዚህ ያለ አዎንታዊ ሪፖርት ይቀርባል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ደስ ትሉኛላችሁ፤ እስረኞቹን ለመርዳት የምታደርጉትንም ጥረት በጣም አደንቃለሁ።” ሌላ ባለ ሥልጣን ደግሞ እንዲህ በማለት አክለው ተናግረዋል:- “ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የነበረኝን አመለካከት እንድቀይር አድርጋችሁኛል። ከዚህ በፊት ሃይማኖታዊ አክራሪዎች እንደሆናችሁ አድርጌ ነበር የምመለከታችሁ። አሁን ግን በመሠረታዊ ሥርዓት የምትመሩ ሰዎች መሆናችሁን ማየት ችያለሁ።”
የቮዉፍ እስር ቤት ዲሬክተር የሆኑት ማሬክ ጋዮስ ፈገግ በማለት እንደዚህ ብለዋል:- “መጀመሪያ ላይ ምንም ነገር ማከናወን እንደማትችሉ ሆኖ ተሰምቶን ነበር። እንዲሁ ለእስረኞች መጽሐፍ ቅዱሳዊ የተሐድሶ ትምህርት የመስጠት ፍላጎት ያለው ሃይማኖት አድርገን ነበር ያየናችሁ። ነገር ግን የመጀመሪያ እንቅስቃሴያችሁ ያስገኘውን ውጤት ስንመለከት ከእናንተ ጋር ተባብረን ለመሥራት ወሰንን። ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ያለመታከት ስትመጡ ቆይታችኋል። እስከ አሁን ያደረጋችሁትን ነገር በጣም አደንቃለሁ።”
በቮዉፍ እስር ቤት የሚገኙ ሌሎች ሰዎችስ ጽሑፉን እንዴት ነበር የተቀበሉት? እስረኞቹ ጽሑፉን ለማግኘት የሚያቀርቡት ጥያቄ ከፍተኛ ስለነበር እዚያ የሚገኙት ምሥክሮች የነበራቸውን መጽሔት ጨረሱ። የእስር ቤቱ ባለ ሥልጣኖችም ተጨማሪ 40 ቅጂዎችን ለራሳቸው በመጠየቅ ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል። ይህን ከፍተኛ መጠን ያለውን ፍላጎት ለማሟላት በአካባቢው የሚገኙት ጉባኤዎች በእስር ቤት ላሉ ወንድሞች ተጨማሪ 100 ቅጂዎችን ልከውላቸዋል። በእስር ቤቱ በሚደረገው ስብሰባ ላይ የሚገኙት ሰዎች ቁጥርም ጨምሯል።
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በቅርብ ተባብረው የሠሩት ፒዮት ሆዱውን የተባሉ የእስር ቤት ባለ ሥልጣን እንደዚህ ብለዋል:- “ይህ ርዕስ ወህኒ ቤቱ ውስጥ ባሉ ማስታወቂያ መለጠፊያ መስታወቶች ሁሉ እንዲቀመጥ ወስነናል። እስከ አሁን ከእናንተ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ያልጀመሩ እስረኞች ሁሉ ያነቡታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።”
የምሥክሮቹ መልካም ምሳሌነትና ለመስበክ የሚያደርጉት ከፍተኛ ጥረት ጥሩ ፍሬ ማፍራቱን ቀጥሏል። እድገት አድርገው ከተጠመቁት 15 እስረኞች በተጨማሪ 2 የእስር ቤቱ ባለ ሥልጣኖች ሕይወታቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሲሆን አንድ ሌላ የእስር ቤቱ ባለሥልጣን ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። በእርግጥም፣ በቮዉፍ እስር ቤት የሚሰብኩት ወንድሞች ላገኙት ጥሩ ውጤት ሁሉ ይሖዋ አምላክን ያመሰግናሉ።—ከ1 ቆሮንቶስ 3:6, 7 ጋር አወዳድር።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በእስር ቤቱ የትምህርት መስጫ አዳራሽ በተካሄደው የመጽሔት ማስተዋወቂያ ፕሮግራም ላይ የተገኙ ሦስት ምሥክሮችና አንድ እስረኛ