መፍትሔ ይሆናል የተባለው ነገር ራሱ የችግሩ አካል ይሆን?
“እስረኞችን ሰብዓዊ ክብራቸውን በመግፈፍና ሞራላቸውን በማላሸቅ የተሻሉ ሰዎች ሆነው እንዲወጡ ማድረግ ይቻላል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።”—ዘ አትላንታ ኮንስቲትዩሽን ላይ የወጣ ርዕሰ አንቀጽ።
አብዛኛውን ጊዜ እስር ቤቶች ከጊዜያዊ መቆጣጠሪያነት ያለፈ ግልጋሎት ሲሰጡ አይታይም። አንድ እስረኛ በሚለቀቅበት ጊዜ በእርግጥ ከፈጸመው ወንጀል ጋር የሚመጣጠን ካሳ ከፍሏል ለማለት ይቻላል?a የወንጀሉ ሰለባ ስለሆኑት ወይም ስለ ዘመዶቻቸው ምን ለማለት ይቻላል? ሪታ የ16 ዓመት ልጅዋን የገደለው ሰው ለሦስት ዓመት ብቻ ታስሮ በተለቀቀ ጊዜ “እኔ ልጄን በነፍስ ግድያ ያጣሁ ሴት ነኝ። እስቲ ፍረዱኝ። ይህ ለእኔ ምን ማለት እንደሆነ መገመት ትችላላችሁ?” ስትል ብሶቷን አሰምታለች። በሪታ ላይ የደረሰው ሁኔታ እንደሚያሳየው ብዙውን ጊዜ ፍርድ ቤቶች ችሎቱን ከዘጉና ጉዳዩ ከዜና ገጾች ላይ ከጠፋ ከረጅም ጊዜ በኋላም እንኳ ሐዘኑ የሚያስከትለው የስሜት ቁስል በቀላሉ አይሽርም።
ይህ ጉዳይ ሕይወታቸው በወንጀል ድርጊቶች የተነካ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሰው የሚያሳስብ ነው። ከወኅኒ የወጡ እስረኞች ከብረት አጥር በስተጀርባ ባሳለፉት ሕይወት ለውጥ ማድረጋቸው አሊያም ይበልጥ መደንደናቸው በአእምሮ ሰላምህ ላይ አልፎ ተርፎም በደህንነትህ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
የወንጀለኞች ትምህርት ቤት
የእስር ቤት ሥርዓት ሁልጊዜ የወንጀለኞችን ባሕርይ ሙሉ በሙሉ ይለውጣል ማለት አይቻልም። ጂል ስሞሎው ታይም በተሰኘው መጽሔት ላይ “ብዙውን ጊዜ አንድ እስረኛ ለራሱ ያለውን ግምት መልሶ እንዲገነባ ከማድረግ ይልቅ ሌላ የእስረኛ ክፍል ለመገንባት ብዙ ገንዘብ ማፍሰስ ለባሰና ይበልጥ አስከፊ ለሆነ የወንጀል ድርጊት በር ከመክፈት ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም” ሲሉ ጽፈዋል። ከብረት አጥር በስተጀርባ 14 ዓመታት ያሳለፈው ፒተርb በዚህ አባባል ይስማማል። “አብረውኝ የታሰሩት አብዛኞቹ የሕግ ታራሚዎች መጀመሪያ ላይ ቀላል ወንጀሎችን ፈጽመው የታሰሩ ነበሩ። በኋላ ግን ከዘረፋና ከማጭበርበር ጋር ወደተያያዙ የወንጀል ድርጊቶች ተሸጋገሩ። በመጨረሻም ደረጃቸውን ይበልጥ በማሻሻል በሌሎች ሰዎች ላይ ከባድ ወንጀሎችን መፈጸም ጀመሩ” ይላል። “እስር ቤቶች ለእነሱ የሙያ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤቶች ናቸው። የወንጀል ድርጊቶችን ይበልጥ ተክነው ይወጣሉ።”
ምንም እንኳ እስር ቤቶች ወንጀለኞችን ለተወሰነ ጊዜ ከኅብረተሰቡ የሚያርቋቸው ቢሆንም ወንጀልን ለዘለቄታው በመከላከል ረገድ ግን ብዙም የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ያለ አይመስልም። ብዙውን ጊዜ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ባለበት መሃል ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ወንዶች ልጆችና ወጣቶች እስር ቤት መግባት ትልቅ ሰው ወደመሆን ደረጃ የመሸጋገር ምልክት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። እንዲህ ዓይነቶቹ ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ ልማደኛ ወንጀለኞች ይሆናሉ። “እስር ቤት ፈጽሞ አይለውጥህም” ይላል አብዛኛውን የሕይወት ዘመኑን በተደጋጋሚ ጊዜያት ወደ እስር ቤት በመግባት ያሳለፈው ላሪ። “እነዚህ ሰዎች ከእስር ቤት ከወጡም በኋላ እንደገና ያንኑ ድርጊት ሲፈጽሙ ይገኛሉ።”
ይህ ሁኔታ በዩናይትድ ስቴትስ በተካሄደው ጥናት መሠረት በየጊዜው ከሚፈጸሙት ከባድ ወንጀሎች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት 5 በመቶ ገደማ በሚሆኑት ወንጀለኞች ብቻ የሚፈጸሙት ለምን እንደሆነ ግልጽ ሊያደርግልን ይችላል። “እስረኞች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ምንም ዓይነት ጠቃሚ ነገር ከሌለ” ይላል ታይም መጽሔት፣ “ከእስር ሲወጡ የሚጠቀሙባቸውን . . . ወንጀል ለመፈጸም የሚያስችሉ በርካታ የረቀቁ ዘዴዎች ከማጥናት በተጨማሪ ቁጭ ብለው ቂም ሲቋጥሩ ይውላሉ።”
ይህ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ያለ ችግር አይደለም። በግሪክ ወታደራዊ እስር ቤት በሕክምና ሙያ የሚያገለግሉት ጆን ቫቲስ “ወኅኒ ቤቶቻችን አደገኛ፣ ጠበኛና ጨካኝ የሆኑ ሰዎችን በማፍራት ረገድ ተዋጥቶላቸዋል። አብዛኞቹ የሕግ ታራሚዎች ከእስር ሲለቀቁ ኅብረተሰቡን መበቀል ይፈልጋሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
በኅብረተሰቡ ላይ የሚያስከትለው ወጪ
እስር ቤቶች የሚያስከትሉት ቀውስ የአንተንም ኪስ መዳበሱ አይቀርም። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ግብር ከፋዮች ለእያንዳንዱ እስረኛ በዓመት 21, 000 ዶላር ገደማ እንደሚያወጡ ይገመታል። ከ60 ዓመት በላይ የሆናቸው እሥረኞች ደግሞ የዚህን ሦስት እጥፍ ያህል የሚሆን ወጪ ሊያስከትሉ ይችላሉ። በብዙ አገሮች በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች የተነሳ ሕዝቡ በቅጣት ሥርዓቱ ላይ ያለው እምነት እየተዳከመ መጥቷል። የእስር ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ የሚለቀቁ ወንጀለኞችና ሕግ ነክ የሆኑ ሥርዓቶችን በረቀቀ መንገድ በሚጠቀም ጠበቃ አማካኝነት ሙሉ በሙሉ ከእስራት ነፃ የሚሆኑ ሕግ ተላላፊዎች ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል። ብዙውን ጊዜ የወንጀል ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ዳግመኛ ሊፈጸምባቸው ከሚችለው ጥቃት በቂ ጥበቃ እንዳገኙ ሆኖ የማይሰማቸው ከመሆኑም በላይ በሕጋዊ አሠራር ሂደቱ ውስጥ እምብዛም ተደማጭነት ላያገኙ ይችላሉ።
አሳሳቢ ሁኔታዎች እየጨመሩ መጥተዋል
ከዚህ ርዕስ ጋር ተያይዞ በወጣው ሳጥን ላይ ለተገለጹት ዓይነት ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እስረኞችን በማጋለጥ ሕዝቡ በእስር ቤቶች አሠራር ላይ እምነት እንዲኖረው ማድረግ አይቻልም። ተገቢ ያልሆነ ድርጊት የሚፈጸምባቸው እስረኞች ይለወጣሉ ብሎ መጠበቅ የማይመስል ነገር ነው። በተጨማሪም በእስር ቤቶች ውስጥ ተጥለው የሚገኙ የአናሳ ወገኖች አባላት ቁጥር ከልክ ያለፈ መሆኑ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖችን እያሳሰበ ይገኛል። ይህ እንዲሁ በአጋጣሚ የተከሰተ ነገር ነው ወይስ የዘር መድልዎ ውጤት የሚል ጥያቄ ያነሳሉ።
በ1998 የወጣው የአሶስዬትድ ፕሬስ ዘገባ እስር ቤት ሳለን የኬሚካል ሙከራ ለማካሄድ መሣሪያ አድርገው የተጠቀሙብን በመሆኑ ካሳ ሊከፈለን ይገባል የሚል ጥያቄ ያቀረቡትን በፔንሲልቬንያ ዩ ኤስ ኤ የሆምስበርግ የቀድሞ እስረኞች ጉዳይ አንስቶ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ወንጀለኞችን እርስ በርስ በሰንሰለት አቆራኝቶ የማሠራት ልማድ በድጋሚ ብቅ ማለቱን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሚከተለውን ዘገባ አውጥቷል:- “በሰንሰለት አንድ ላይ ተቆራኝተው የሚሠሩ ወንጀለኞች ብዙውን ጊዜ በጠራራ ፀሐይ ከ10-12 ሰዓት ያህል የሚሠሩ ሲሆን ትንሽ ተንፈስ የሚሉት ውኃ ለመጠጣት በሚኖራቸው አነስተኛ ጊዜና ለአንድ ሰዓት ያህል በሚቆየው የምሳ ዕረፍት ብቻ ነው። . . . በእንዲህ ዓይነት ሥራ ላይ የተሰማሩ የሕግ ታራሚዎች ሊጸዳዱ የሚችሉት ከአንድ ጊዜያዊ ከለላ ጀርባ በሚቀመጥ ፖፖ አማካኝነት ብቻ ነው። ፖፖውን የሚጠቀሙት እርስ በርስ እንደተቆራኙ ነው። ይህ ፖፖ በማይኖርበት ጊዜ ደግሞ ሰው እያያቸው ሜዳ ላይ ለመጸዳዳት ይገደዳሉ።” እርግጥ ሁሉም እስር ቤቶች እንዲህ ዓይነት አሠራር ይጠቀማሉ ማለት አይደለም። ያም ሆነ ይህ ግን እንዲህ ያለ ኢሰብዓዊ ድርጊት እስረኞቹም ሆነ ቅጣቱን የሚያስፈጽሙት ሰዎች ርኅራኄ የለሾች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
የማኅበረሰቡ ጥቅሞች ተጠብቀዋልን?
አብዛኞቹ ማኅበረሰቦች አደገኛ ወንጀለኞች ከብረት አጥር ጀርባ ሲከረቸሙ ደህንነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ እንደሚሰማቸው የታወቀ ነው። ሌሎች ማኅበረሰቦች ደግሞ እስር ቤቶች እንዲኖሩ የሚፈልጉባቸው ሌሎች ምክንያቶች አሉ። ኩማ በተሰኘች አንዲት አነስተኛ የአውስትራሊያ ከተማ የሚገኝ እስር ቤት በተዘጋ ጊዜ ሰዎች ተቃውሞ አሰምተዋል። ለምን? ምክንያቱም የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ለሚማስነው ማኅበረሰብ እስር ቤቱ የሥራ ዕድል ፈጥሮ ስለነበረ ነው።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳንድ መንግሥታት ወጪን ለመቀነስ በሚል ወኅኒ ቤቶችን ለግል ድርጅቶች ሸጠዋል። ረዥም ዓመታት የተበየነባቸው በርካታ እስረኞችን ማግኘት እንደ ጥሩ ገበያ ተደርጎ መቆጠሩ የሚያሳዝን ነው። ይህ ሁኔታ ፍትሐዊ እርምጃን ከንግድ ጋር ለተያያዘ ዓላማ ማዋል የሚቻልበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል የሚያሳይ ነው።
ይሁንና እስር ቤቶች ወንጀለኞች ለውጥ እንዲያደርጉ ሊረዱ ይችላሉን? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ አሁንም ምላሽ የሚያሻው ሆኖ እናገኘዋለን። ብዙውን ጊዜ መልሱ አሉታዊ ቢሆንም አንዳንድ የሕግ ታራሚዎች ለውጥ ለማድረግ የሚያስችል እርዳታ እንዳገኙ ስታውቅ ልትገረም ትችላለህ። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ እስቲ እንመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እስረኞችን የጠቀስነው በተባዕታይ ፆታ ቢሆንም የተገለጹት መሠረታዊ ሥርዓቶች ለወንድም ሆነ ለሴት የሕግ ታራሚዎች የሚሠሩ ናቸው።
b በዚህ ርዕስ ውስጥ ያሉት አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።
[በገጽ 6 እና 7 ሣጥን/ሥዕል]
ከብረት አጥሮች ጀርባ ያለው ሁኔታ ሲቃኝ
መጨናነቅ:- በብሪታንያ የሚገኙ እስር ቤቶች በከፍተኛ ሁኔታ በእስረኞች የተጨናነቁ ሲሆን ይህም የሚያስደንቅ አይደለም! ከሕዝቡ ብዛት አንጻር ሲታይ በዚህች አገር ያለው እስረኛ ቁጥር በምዕራብ አውሮፓ ካሉት አገሮች በሙሉ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የያዘ ሲሆን ከ100, 000 ሕዝብ መካከል 125 እስረኞች ይገኛሉ። በብራዚል የሳኦ ፓውሎ ትልቁ እስር ቤት 500 ለሚሆኑ እስረኞች የተሠራ ቢሆንም በዚህ እስር ቤት ውስጥ 6, 000 እስረኞች ታጉረዋል። በሩስያ ለ28 እስረኞች በተሠሩ ክፍሎች ውስጥ ከ90 እስከ 110 እስረኞች ታጉረው ይገኛሉ። ችግሩ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ እስረኞች በፈረቃ ለመተኛት ተገድደዋል። በእስያ ውስጥ በምትገኝ አንዲት አገር 13 ወይም 14 የሚሆኑ እስረኞች 3 ካሬ ሜትር ስፋት ባላት ክፍል ውስጥ ይታጨቁ ነበር። በምዕራብ አውስትራሊያ ደግሞ ባለ ሥልጣናት የቦታ ጥበት ያስከተለውን ችግር ለማቃለል ሲሉ ትልልቅ የዕቃ መጫኛ ኮንቴይነሮችን የእስረኞች ክፍል አድርገው ተጠቅመውባቸዋል።
ዓመፅ:- በጀርመን እስር ቤቶች ውስጥ ያሉ ጨካኝ እስረኞች “ሕገወጥ ከሆነ የአልኮልና ሱስ የሚያስይዙ መድኃኒቶች ንግድ፣ ከጾታና በወለድ ከማበደር ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች እርስ በርስ በሚቀናቀኑ ቡድኖች መካከል በሚፈጠር ግጭት” ሳቢያ ይገድላሉ እንዲሁም ያሰቃያሉ ሲል የጀርመን የዜና መጽሔት የሆነው ዴር ሽፒገል ዘግቧል። በጎሳዎች መካከል ያለ ውጥረት ብዙውን ጊዜ በእስር ቤት ውስጥ ዓመፅ እንዲቀጣጠል ያደርጋል። “የ72 አገር ተወላጅ የሆኑ እስረኞች ይገኛሉ” ይላል ዴር ሽፒገል። “ወደ ዓመፅ የሚያመሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች መፈጠራቸው አይቀሬ ነው።” በደቡብ አሜሪካ በሚገኝ አንድ እስር ቤት ውስጥ በየወሩ በአማካይ 12 እስረኞች እንደሚገደሉ ባለ ሥልጣናት ተናግረዋል። እስረኞቹ ግን ቁጥሩ በእጥፍ እንደሚበልጥ ተናግረዋል ሲል የለንደኑ ፋይናንሻል ታይምስ ዘግቧል።
ወሲባዊ በደል:- ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “ከብረት አጥሮች ጀርባ የሚፈጸም የግዳጅ ወሲብ ያስከተለው ቀውስ” በሚል ርዕስ ሥር መረጃን መሠረት በማድረግ በተሰጠ ግምታዊ አስተያየት መሠረት በዩናይትድ ስቴትስ “በሚገኙ እስር ቤቶች በየዓመቱ ከ290, 000 የሚልቁ ወንዶች ወሲባዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል” ሲል አትቷል። ዘገባው “ይህ ዘግናኝ ወሲባዊ ጥቃት በአብዛኛው አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ የሚፈጸም ክስተት ሆኖ ይቀጥላል” በማለት አክሎ ገልጿል። አንድ ድርጅት በሰጠው ግምታዊ አስተያየት መሠረት በዩናይትድ ስቴትስ እስር ቤቶች ውስጥ በየቀኑ ወደ 60, 000 የሚጠጉ ወሲባዊ የኃይል ድርጊቶች ይፈጸማሉ።
ጤናና የንጽሕና አጠባበቅ:- በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች በእስረኞች መካከል በከፍተኛ ደረጃ እየተዛመቱ መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል። በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ እስር ቤቶች ውስጥ የሕክምና፣ የንጽሕና አጠባበቅና የአመጋገብ ሥርዓት ችላ መባል ዓለም አቀፋዊ ትኩረት እንዳገኘ ሁሉ በሩስያና በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በሚገኙ እስረኞች መካከል እየተዛመተ ያለው የሳንባ ነቀርሳ በሽታም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እየሳበ መጥቷል።
[ሥዕል]
በብራዚል ሳኦ ፓውሎ ውስጥ የሚገኝ በእስረኞች የተጨናነቀ እስር ቤት
[ምንጭ]
AP Photo/Dario Lopez-Mills
[በገጽ 4 እና 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ የሚገኘው ከፍተኛ ቁጥጥር የሚካሄድበት የላ ሳንቴ እስር ቤት
[ምንጭ]
AP Photo/Francois Mori
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኒካራጉዋ፣ ማናጓ ውስጥ የሚገኙ ሴት እስረኞች
[ምንጭ]
AP Photo/Javier Galeano