የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 5/1 ገጽ 2-31
  • “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ”
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ገና በልጅነት የተደረገ ምርጫ
  • ወደ ሲንጋፖር
  • የሻንግሀይ ምድቤ
  • ሆንግ ኮንግና ከዚያም በርማ
  • ወደ አውስትራሊያ ተመለስኩ
  • ወደ መጀመሪያው መመለስ
  • የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ያገኘሁት የዕድሜ ልክ ደስታ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ከወጣትነት ጀምሮ ይሖዋ መታመኛዬ ነው
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነትና እንክብካቤ አይቻለሁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 5/1 ገጽ 2-31

“እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ”

ዊልፍሬድ ጆን እንደተናገረው

የጦር መሣሪያ የታጠቁ የበርማ ወታደራዊ ዘቦች ከወንዙ ግራና ቀኝ እየሮጡ መጡብን። ሳንጃቸውን መዘውና ሽጉጦቻቸውን አቀባብለው እስከወገባቸው ድረስ በሚደርሰው ውኃ እየዋኙ ተሻግረው በአውራ ጎዳናው ድልድይ ላይ ደረሱብንና ከበቡን።

እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ በጣም ፈራን። ነገሩ ምን ይሆን? ቋንቋቸው ባይገባንም እኛን ሊይዙ እንደመጡ ገባን። ወገባችንን በፎጣ ሸብ አደረጉንና ያላንዳች ውጣ ውረድ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱንና እንግሊዝኛ በሚናገር የፖሊስ አዛዥ አስመረመሩን።

ጊዜው 1941 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሚካሄድበት ጊዜ ነበርና ድልድይ አፍራሾች መስለናቸው ነበር። አዛዡ እስኪረካ ድረስ ስለ ክርስቲያናዊ የስብከት ሥራችን ካስረዳነው በኋላ በተያዝንበት ቦታ ሳንገደል መትረፋችን ራሱ እድለኞች መሆናችንን ነገረን። በድልድይ አፍራሽነት ከተጠረጠሩ ሰዎች የሚበዙት የተገደሉ ሲሆን ለምን ተገደሉ ብሎ ማንም እንዳልጠየቀ ነገረን። ይሖዋን አመሰገንንና ለወደፊቱ በድልድዩ አካባቢ እንዳናልፍ የነገረንን የአዛዡን ምክር ተቀብለን ወጣን።

በበርማ (አሁን ማያንማር) እንዲህ ባለ ሁኔታ ላይ ልወድቅ የቻልኩት እንዴት ነው? ምክንያቱን ልግለጽላችሁ፤ ስለራሴ አስተዳደግም ጥቂት ልንገራችሁ።

ገና በልጅነት የተደረገ ምርጫ

በ1917 በዌልስ ተወለድኩና በ6 ዓመቴ ከወላጆቼና ከትንሽ ወንድሜ ጋር በኒው ዚላንድ ወደሚገኘው ወዳደግሁበት ያባቴ የከብት ርቢ ጣቢያ ተዛወርኩ። አንድ ቀን አባቴ ከአንድ የአሮጌ መጻሕፍት መደብር የገዛውን የአሮጌ መጻሕፍት ጥቅል ይዞ መጣ። በጥቅሉም ውስጥ በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀው ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ የተሰጠው መጽሐፍ ሁለት ጥራዞች ይገኙበት ነበር። እነዚህ መጻሕፍት የእናቴ ተወዳጅ ንብረቶች ሆኑና እርሷም የጢሞቴዎስ እናት እንደነበረችው እንደ ኤውንቄ ወጣትነቴን የይሖዋን የመንግሥት ፍላጎቶች ለማስቀደም እንድጠቀምበት ፍላጎት አሳደረችብኝ።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 1:5

በ1937 ሁለት ምርጫዎች አጋጠሙኝ። እነርሱም፦ የአባቴን የከብት እርባታ ጣቢያ መረከብ ወይም የአምላክ ነቢይ የነበረው ኢሳይያስ እንዳደረገው ለይሖዋ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” ማለት ነበሩ። (ኢሳይያስ 6:8) ወጣት፣ ሙሉ ጤነኛና ከሌሎች ኃላፊነቶች ነፃ የሆንኩ ነበርኩ። የእርሻን ኑሮ ቀምሼዋለሁ፤ እወደውም ነበር። ነገር ግን በሙሉ ጊዜ አገልጋይነት ወይም በአቅኚነት ምንም ተሞክሮ አልነበረኝም። ታዲያ የትኛውን ልምረጥ? በከብት እርባታ ጣቢያው ላይ መሥራትን ወይስ በአቅኚነት ማገልገልን?

ከአውስትራሊያው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የተላኩ ተናጋሪዎች የመጽናናት ምንጭ ነበሩ። በኒው ዚላንድ ያለውን አካባቢያችንን ጎብኝተው ስለነበር አፍላ ወጣትነቴን አምላክን ለማገልገል እንድጠቀምበት አጥብቀው መከሩኝ። ጉዳዩን ከወላጆቼ ጋር ተወያየሁበትና የአምላክን ፈቃድ ማስቀደም ጥበብ መሆኑን ተስማሙበት። በተጨማሪም ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል”ያለውን ቃል አሰላሰልኩበት።​—⁠ማቴዎስ 6:33

ምርጫዬን አደረግሁ! በዚያን ጊዜ በኒው ዚላንድ የይሖዋ ምስክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ስላልነበረ በአውስትራሊያው የሲድኒ ቅርንጫፍ እንዳገለግል ተጋበዝኩ። ስለዚህ በ1937 የይሖዋ አምላክ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ለመሆን በመርከብ ወደ አውስትራሊያ ሄድኩ።

‘ምን ዓይነት የሥራ ምድብ ይደርሰኝ ይሆን?’ ብዬ አሰብኩ። ሆኖም የፈለገው ዓይነት የሥራ ምድብ ቢሰጠኝ ምን ልዩነት ያመጣል? ለይሖዋ ‘እነሆኝ፣ በፈለግከው መንገድ ተጠቀምብኝ’ እንዳልኩት ያህል ነበር። ለሁለት ዓመት ያህል በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምስክሮች በአገልግሎታቸው ላይ ለቤት ባለቤቶች በክር የተቀዱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን ለማሰማት ይጠቀሙበት የነበረውን የሸክላ ማጫወቻ በማዘጋጀት አገለግል ነበር። ይሁን እንጂ በቅርንጫፉ የሚሰጠኝ ዋና ሥልጠና ለሥነ ጽሑፍ ግምጃ ቤት ሥራ ነበር።

ወደ ሲንጋፖር

በ1939 ወደ ሩቅ ምሥራቅ እንድሄድና ከዚያም በሲንጋፖር ባለው የማኅበሩ ግምጃ ቤት እንዳገለግል ተመደብኩ። ግምጃ ቤቱ በእስያ ላሉት ብዙ አገሮች ከአውስትራሊያ፣ ከብሪታንያና ከዩናይትድ ስቴትስ የሚላኩ ጽሑፎችን ለመቀበልና ለመጫን በማዕከልነት የሚያገለግል ነበር።

ሲንጋፖር የምሥራቁ ዓለምና የአውሮፓ ባሕሎች የተቀላቀሉባት ብዙ ቋንቋ የሚነገርባት ከተማ ነበረች። ዋናው መግባቢያ የማላይ ቋንቋ ስለነበር ከውጭ አገር የመጣነው ሰዎች ከቤት ወደ ቤት ለመስበክ እንችል ዘንድ ቋንቋውን መማር ነበረብን። በዚያን ጊዜ የምስክርነት መስጫ ካርዶች የሚባሉት በብዙ ቋንቋዎች ነበሩን። እነዚህ ካርዶች በአጭሩ የቀረበ የመንግሥቱ መልእክት የታተመባቸው ነበሩ።

ለመጀመሪያ ጊዜ በማላይ ቋንቋ የተዘጋጀውን የምስክርነት መስጫ ካርድ በቃሌ አጠናሁና ቀስ በቀስም በዚያ ቋንቋ ያለኝን የቃላት እውቀት እያሳደግሁ ሄድኩ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በሌሎች ብዙ ቋንቋዎችም ይዘን እንሄድ ነበር። ለምሳሌ ያህል ለህንዶች በቤንጋሊ፣ በጉጀራቲ፣ በሂንዲ፣ በማላያላም፣ በታሚልና በኡርዱ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች ነበሩን። ብዙ ቋንቋ ካላቸው ሕዝቦች ጋር መገናኘት ለእኔ አዲስ ተሞክሮ ነበር።

መስከረም 1939 በአውሮፓ ጦርነት መታወጁን የገለጸውን አስፈሪ ማስታወቂያ እስካሁን አስታውሰዋለሁ። ‘ጦርነቱ ተባብሶ ወደ ሩቅ ምሥራቅም ይዛመት ይሆን’ ብለን አሳሰበን። ጦርነቱ የአርማጌዶን ዋዜማ መስሎኝ በተገቢ ሰዓት ላይ ሊመጣ ነው ብዬ አስቤ ነበር! በወጣትነቴ ሙሉ በሙሉና ተገቢ በሆነ መንገድ እየተጠቀምኩበት በመሆኔ እርካታ ይሰማኝ ነበር።

በግምጃ ቤቱ ከነበረኝ ሥራ ጋር በጉባኤ ስብሰባዎችና በመስክ አገልግሎት ሙሉ ተሳትፎ ነበረኝ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እመራና አንዳንዶቹን ምላሽ ሰጥተው ለውኃ ጥምቀት ይደርሱ ነበር። በአቅራቢያው ወደሚገኘው የባሕር ዳርቻ ይወሰዱና በሲንጋፖር ወደብ ባለው ለብ ያለ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ ይጠመቁ ነበር። ለሰው ሳናሰማ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የጥሪ ወረቀት በማሠራጨት ትልቅ ስብሰባ ለማድረግም ወሰንን። በዚያን ጊዜ ከአርማጌዶን በፊት የመጨረሻው ትልቅ ስብሰባ ይሆናል ብለን ባሰብነው ስብሰባ ላይ 25 ሰዎች ሲገኙ በጣም ተደስተን ነበር።

በማኅበሩ ቅርንጫፎች መካከል ግንኙነት የማድረጉን ሂደት ጦርነቱ በጣም ገድቦት ነበር። ለምሳሌ ያህል የሲንጋፖሩ ግምጃ ቤታችን ተለይቶ ላልተገለጸ የሥራ ምድብ የተላኩ ሦስት ጀርመናውያን አቅኚዎች ስሙ ባልተገለጸ መርከብ እግረ መንገዳቸውን ሲንጋፖር እንደሚደርሱ የሚገልጽ አጭር ማስታወቂያ ደርሶት ነበር። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ መጡና ከእኛ ጋር ለአሥር ሰዓት ያህል በጣም አስደሳች ጊዜ አሳለፉ። ለመነጋገር የቋንቋ ችግር ቢኖርብንም ምድብ አድራሻቸው ሻንግሀይ መሆኑን ለመረዳት ቻልን።

የሻንግሀይ ምድቤ

ከአንድ ዓመት በኋላ እኔም በሻንግሀይ እንዳገለግል ተመደብኩ። የተሰጠኝ አድራሻ የፖስታ ሣጥን ቁጥር ብቻ እንጂ የጎዳና ስም አልነበረበትም። ፖስታ ቤቱ በመስቀለኛ ጥያቄ በደንብ ከመረመረኝ በኋላ ማንነቴን በበቂ ሁኔታ ስላሳወቅሁ የማኅበሩ መኖሪያ አድራሻ ሰጡኝ። ይሁን እንጂ በመኖሪያ ቤቱ ያገኘሁት ቻይናዊ ነዋሪ ቅርንጫፉ ቦታ እንደለወጠና በቀላሉ ላገኝበት የምችለው አድራሻ እንደሌለው ነገረኝ።

‘አሁን እንግዲህ ምን ላድርግ?’ ብዬ አሰብኩ። አመራር እንዳገኝ ድምፅ ሳላሰማ ጸሎት አቀረብኩ። ቀና ብዬ ስመለከት ቁመናቸው ከሌሎቹ ሰዎች የቁመት አወራረድ ረዘም ብሎ የሚታይና መልካቸውም ለየት ያለ ሦስት ሰዎች አየሁ። በሲንጋፖር ጥቂት ሰዓቶችን ያሳለፉትን ሦስት ጀርመናውያን ይመስሉ ነበር። ፈጠን ብዬም በመንገዳቸው ላይ ድቅን አልኩ።

“አንዴ ይቅርታ” አልኩኝ በደስታ ስሜት እየተንተባተብኩ። ቆሙና ከእግር እስከ ራሴ እየተመለከቱ በጥርጣሬ አተኩረው አዩኝ። “ሲንጋፖር። የይሖዋ ምስክሮች። አስታወሳችሁኝ?” ብዬ ጠየቅሁ።

ከጥቂት ቆይታ በኋላ “ያ! ያ! ያ! [በጀርመንኛ አዎ! አዎ! አዎ! ማለት ነው]” አሉና ተቃቀፍን፣ የደስታ እንባ በጉንጬ ላይ ወረደ። በሚልዮን ከሚቆጠሩ ሰዎች ውስጥ በዚያ ሰዓት እነዚህ ሦስት ሰዎች እንዴት በዚያ ሊያልፉ ቻሉ? ብቻ “ይሖዋ አመሰግንሃለሁ” አልኩኝ። በሻንግሀይ የነበርነው ምስክሮች ሦስት ቻይናውያን ቤተሰቦች፣ ሦስቱ ጀርመናውያንና እኔ ብቻ ነበርን።

ሆንግ ኮንግና ከዚያም በርማ

በሻንግሀይ ለጥቂት ወራት ካገለገልኩ በኋላ በሆንግ ኮንግ እንዳገለግል ተመደብኩ። ከአውስትራሊያ ይመጣል የተባለው አቅኚ ሳይመጣ በመቅረቱ በሆንግ ኮንጉ የብሪታንያ ቅኝ ግዛት የነበርኩት ምስክር እኔ ብቻ ነበርኩ። ለይሖዋ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” ያልኩ መሆኔን ለራሴ በድጋሚ ማስታወስ ነበረብኝ።

ሥራዬ በአብዛኛው እንግሊዝኛ በሚናገሩ ቻይናውያን ላይ ያተኮረ ነበር። ሆኖም በቻይናውያን መኖሪያ ቤቶች የውጭ በራፍ ላይ የሚመደቡት ሠራተኞች የሚናገሩት ቻይንኛ ቋንቋ ብቻ ስለሆነ ከበር አላሳልፍ እያሉ ችግር ያጋጥመኝ ነበር። ስለዚህ ብዙው ሕዝብ በሚነጋገርባቸው ሁለት የቻይንኛ ያነጋገር ዘዴዎች ጥቂት ቻይንኛ ተማርኩ። ብልሃቱም ሠራ! ዘበኞቹን ቀርቤ የሥራ ካርዴን አሳያቸውና ጥቂት የቻይንኛ ቃላት እየሰባበርኩ እናገራለሁ። አብዛኛውን ጊዜ ወደ ቤት ያስገቡኛል።

አንድ ጊዜ አንድን ትምህርት ቤት ስጎበኝ ከትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ጋር ለመነጋገር ባደረግሁት ሙከራ ከላይ በጠቀስኩት አሠራር ተጠቅሜ ነበር። በመተላለፊያው ላይ አንዲት የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ መምህር አገኘችኝ። በአንዳንድ የመማሪያ ክፍሎች በኩል አልፋ ስትሄድ ተከተልኳት። ለልጆቹ የአክብሮት ሰላምታ አጸፋውን መለስኩና ከርዕሰ መምህሩ ጋር ለመተዋወቅ ተዘጋጀሁ። መምህሯ በሩን አንኳኳችና ከፍታ ከኋላዬ ስትቆም እኔን በማስቀደም እንድገባ ምልክት ሰጠችኝ። ከማስገረምም አልፎ ያስቆጣኝ ነገር እንደዚያ በትሕትና ተሽቆጥቁጣ የወሰደችኝ ለካስ ሽንት ቤት ኖሯል! ምናልባት የተናገርኩት ቻይንኛ ቋንቋ ሳያግባባን ቀርቶ ይሆናል ብዬ አሰብኩኝ፤ ርዕሰ መምህሩ በኋላ እንደነገሩኝ ከሆነ የቧንቧና የፍሳሽ ተቆጣጣሪ መስያት ኖሯል።

ከአራት ወር ሥራ በኋላ በስብከት ሥራችን ላይ እገዳ እንደተደረገና መስበኬን መተው እንዳለብኝ ወይም ከአገር መውጣት እንዳለብኝ በሆንግ ኮንጉ ፖሊስ በኩል ተነገረኝ። በሌላ ቦታ በስብከት የመቀጠል አጋጣሚ ክፍት በመሆኑ ከአገር መውጣቱን መረጥኩ። በሆንግ ኮንግ እያለሁ 462 መጻሕፍትን አበርክቼና ሌሎች ሁለት ሰዎች በስብከቱ ሥራ እንዲካፈሉ ለመርዳት ችዬ ነበር።

ከሆንግ ኮንግ በኋላ በርማ ተመደብኩ። እዚያም በአቅኚነት እሠራና በራንጉን ከተማ (አሁን ያንጉን) በግምጃ ቤት ሥራ አግዝ ነበር። በጣም አስደሳች ከሆኑት ተሞክሮዎች አንዱ ከራንጉን እስከ ማንዳሌይ እና ከዚያም አልፎ በቻይና ድንበር ላይ እስከምትገኘው የላሺዮ ከተማ ድረስ በዋናው መንገድ ላይ ተበታትነው በሚገኙት ከተሞችና ገጠሮች መስበክ ነበር። አቅኚው ጓደኛዬና እኔ እንግሊዝኛ ተናጋሪ በሆኑት አካባቢዎች ላይ በማተኮር ኮንሶሌሽን [በአሁኑ ጊዜ ንቁ!] ለተሰኘው መጽሔት በመቶ የሚቆጠሩ ኮንትራቶች አገኘን። ከራንጉን ወደ ማንዳሌይ የሚወስደው ይህ ዋና መንገድ የበርማ መንገድ በመባል የሚታወቅ ሲሆን የአሜሪካ ጦር ስንቅና ትጥቅ ወደ ቻይና የሚላኩበት መንገድ ነበር።

እስከ ቁርጭምጭሚት የሚደርስ አቧራ ባለበት ቦታ በእግር መጓዛችን ብዙውን ጊዜ እግራችንን እንድንታጠብ ያስገድደን ነበር። በመጀመሪያ ላይ ወደገለጽኩት በድልድዩ ሥር ባለው ወንዝ እንደ ድልድይ አፍራሾች ተቆጥረን ወደ መያዝ ያደረሰን ይህ ነበር። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወታደራዊ እንቅስቃሴና ሕመም ወደ ራንግጎን እንድንመለስ አስገደደን። የጦርነቱ መፋፋም ወደ አውስትራሊያ እንድመለስ እስካስገደደኝ እስከ 1943 ድረስ በርማ ውስጥ ለመቆየት ቻልኩ።

ወደ አውስትራሊያ ተመለስኩ

በመሃሉ የይሖዋ ምስክሮች እንቅስቃሴ በአውስትራሊያ ታግዶ ነበር። ይሁን እንጂ እገዳው ወዲያው ተነሳና ከዚያ በኋላም በቅርንጫፍ ቢሮው እንድሠራ እንደገና ተጠራሁ። በኋላም በ1947 በአውስትራሊያው የማኅበሩ ቅርንጫፍ ትሠራ የነበረችውን ቤቲ ሞስን አገባሁ። የቤቲ አባትና እናት አቅኚዎች ነበሩ፤ ልጆቻቸውን ቤቲንና ታላቅ ወንድሟን ቢልን አቅኚነትን ቋሚ ሥራቸው እንዲያደርጉ ያበረታቷቸው ነበር። ቤቲ አቅኚነትን የጀመረችው ትምህርቷን ባጠናቀቀችበት ቀን በ14 ዓመትዋ ነበር። ቤቲም ለይሖዋ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” እንዳለች ስለሚቆጠር ሁለታችንም አንድ ላይ ብዙ እንሠራለን ብዬ ገመትኩ።

ከተጋባን ከአንድ ዓመት በኋላ የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤዎችን እንድጎበኝ በክልል የበላይ ተመልካችነት እንድሠራ ተመደብኩ። በአውስትራሊያ ገለልተኛ ሥፍራዎች መሥራት በእርግጥም ተፈታታኝ ነገር ነበር። በወንዞች ላይ የሚያጋጥመን ድንገት ደራሽ ውኃ በተለይም የሚያዳልጥ የአፈር መንገድ ባለባቸው መንገዶች ላይ አዘውትሮ የጉዞ ችግር ይፈጥርብን ነበር። የበጋው ሙቀት እስከ 43 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ከፍ ይል ነበር። በሸራ ድንኳኖች ስንኖር የሚያቃጥለው የበጋው ወራት ሙቀትና የክረምቱ ወራት ቅዝቃዜ ከአቅማችን በላይ መስሎ እስኪሰማን ድረስ ከመጠን ያለፈ ነበር።

በአውስትራሊያ ሁለት ወረዳዎች ብቻ በነበሩበት ጊዜ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ማገልገል ደስ ይል ነበር። ዶናልድ ማክላን አንዱን ወረዳ ሲያገለግል እኔ ደግሞ ሌላውን አገለግል ነበር። ከዚያም ወረዳዎችን እንለዋወጥ ነበር። ባንድ ወቅት እናገለግልባቸው በነበሩት ሥፍራዎች ዛሬ ስላሉት ጉባኤዎች ማንበብ በስሜት የሚያስፈነድቅ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዘሮች አብበው ፍሬ እንደሰጡ ጥርጥር የለውም።

ወደ መጀመሪያው መመለስ

የጊልያድ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት ወደ ኒው ዮርክ ከተዛወረ በኋላ በ1961 በመጀመሪያው የትምህርት ክፍለ ጊዜ የመካፈል መብት አግኝቼ ነበር። ወደ ትምህርት ቤቱ እንድገባ ከዚያም በፊት ተጋብዤ ነበረ፤ ቢሆንም በጤንነት ምክንያት ግብዣውን ልቀበል አልቻልኩም ነበር። በአሥር ወሩ ትምህርት መጨረሻ ላይ ኒው ዚላንድን በምድብ ቦታነት እንድቀበል ተጋበዝኩ።

ስለዚህ ከጥር 1962 ጀምሮ ቤቲና እኔ ከታችኞቹ አገሮች አንዷ በሆነችው በዚህች በኒው ዚላንድ እንገኛለን። ይህች ምድር ብዙውን ጊዜ የፓሲፊክ ዕንቁ በመባል ትታወቃለች። የዚህ አጠራር ትርጉምም በጣም ውብ ከሆኑት የፓሲፊክ አገሮች አንዷ ነች ማለት ነው። ከቲኦክራቲካዊ ሥራ አንፃር በዚህ አገር በክልል የበላይ ተመልካችነቱም ሆነ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራው ማገልገል አስደሳች ሆኖልኛል። ከሚያዝያ 1979 ጀምሮ ላለፉት 14 ዓመታት በኒው ዚላንዱ ቅርንጫፍ ቢሮ ስንሠራ ቆይተናል።

አሁን ቤቲና እኔ ሁለታችንም በ70ዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የምንገኝ ሲሆን ሁለታችንም ባንድነት በመንግሥቱ አገልግሎት ከጀመርን ጀምሮ ያለማቋረጥ 116 ዓመት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት አሳልፈናል። ቤቲ አገልግሎት የጀመረችው ጥር 1933 ሲሆን እኔ ደግሞ ሚያዝያ 1937 ነበር። መንፈሳዊ ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን እኛ ወጣት ሳለን ያደረግነውን ነገር ማለትም “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን የመክብብ 12:1 ምክር በሥራ ላይ እያዋሉት በመመልከታችን ደስታችን ብዙ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘው የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክና ደቀ መዛሙርት በማድረግ መላ ሕይወትን ማሳለፍ እንዴት ያለ መብት ነው! (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) አምላክ ላቀረበልን ጥሪ በጥንት ዘመን የነበረው ነቢዩ ኢሳይያስ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” በማለት እንደሰጠው ያለ ምላሽ በመስጠታችን በጣም ደስተኞች ነን።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ