ከወጣትነት ጀምሮ ይሖዋ መታመኛዬ ነው
በባሲል ትሳቶስ እንደ ተነገረው
ዓመቱ 1920 ነበር፤ ቦታው፣ በግሪክ አገር በውቧ የፔሎፖኒሶስ ልሳነ ምድር የሚገኙት የአካዲያ ኮረብታዎች ነው። ዓለምን እየጠራረገ በነበረው አስፈሪው የኅዳር በሽታ በጠና ታምሜ በአልጋ ላይ ወድቄ ነበር።
የቤተ ክርስቲያን ደወል በጮኸ ቁጥር የበሽታው ሰለባ የሆነን የአንድ ሰው መሞት እንደሚያስታውቅ እገነዘብ ነበር። ቀጥሎ የእኔ ተራ ይሆንን? እንደ አጋጣሚ ሆነና እኔ ዳንኩኝ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ግን አለቁ። በዚያን ጊዜ ዕድሜዬ ስምንት ዓመት ብቻ ቢሆንም እንኳ ይህ አስፈሪ የሕይወት ተሞክሮ አሁንም በአዕምሮዬ ውስጥ ሕያው ሥዕል ሆኖ ይታየኛል።
በልጅነቴ የነበሩኝ መንፈሳዊ ፍላጐቶች
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አያቴ ሞተ። አስታውሳለሁ፣ ከቀብሩ ሥነ ስርዓት በኋላ እናቴ፣ እኅቴና እኔ ወደ ነበርንበት የቤታችን ሠገነት መጣች። ከኀዘናችን እኛን ለማጽናናት በመሞከር በዝግታ:- “መቼም ልጆች፤ ሁላችንም ማርጀት እና መሞት ይጠብቀናል” አለችን።
ምንም እንኳ አነጋገሯ ለዘብ ያለ ቢሆንም የተናገረቻቸው ቃላት ግን እኔን አሳሰቡኝ። ‘እንዴት የሚያሳዝን ነገር ነው!’ ‘ምንኛ ተገቢ ያልሆነ ነገር ነው!’ በማለት አሰብኩ። ነገር ግን እናታችን በማከል “ጌታ ደግሞ ሲመጣ ሙታንን ያስነሣል እንዲሁም ከዚያ በኋላ አንሞትም!” ስትል የሁለታችንም ፊት ፈካ። ይህ በእርግጥም የሚያጽናና ነበር!
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ አስደሳች ጊዜ መቼ ሊመጣ እንደሚችል ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አደረብኝ። ብዙ ሰዎችን ጠየቅሁ፤ ነገር ግን ሊነግረኝ የሚችል ቀርቶ በጉዳዩ ላይ ለመወያየት እንኳ ማንም ፍላጐት ያለው አይመስልም ነበር።
ዕድሜዬ 12 ዓመት ገደማ ሲሆን አንድ ቀን አባቴ አሜሪካ ይኖር ከነበረው ወንድሙ መጽሐፍ ደረሰው። በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመ “ዘ ሃርፕ ኦቭ ጐድ ” የሚል ርዕስ ያለው ነበር። የአርዕስት ማውጫውን ስመለከት “የጌታችን መምጣት” የሚል ርዕስ ሳይ በጣም ተደሰትኩ። በታላቅ ጉጉት አነበብኩት፤ ነገር ግን የሚመለስበት ዓመት ባለመጠቀሱ ወሽመጤ ተቆረጠ። ይሁን እንጂ መጽሐፉ ጊዜው በጣም ሩቅ እንዳልሆነ ይጠቁማል።
ወዲያው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባሁና በጥናት ተጠመድሁ። አልፎ አልፎ ግን አሜሪካ የነበረው አጐቴ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎችን ይልክልኝ ነበር፤ እነርሱንም ማንበብ ያስደስተኝ ነበር። እሁድ እሁድ የሰንበት ትምህርት ቤት እሄድ ነበር። እዚያም ጳጳሱ ብዙ ጊዜ እየመጡ ያነጋግሩን ነበር።
አንድ እሁድ ዕለት ጳጳሱ በጣም ተሸብረው “ጐብኚዎች ከተማችንን በመናፍቃን ጽሑፎች ሞልተዋታል” አሉ። ከዚያም አንድ የመጠበቂያ ግንብ ቅጅ አነሱና እንዲህ በማለት ጮሁ:- “ከእናንተ መካከል ማናችሁም የዚህ ዓይነት ጽሑፍ እቤታችሁ ካገኛችሁ ወደ ቤተ ክርስቲያን አምጡት እኔ አቃጥለዋለሁ።”
የድምፅ ቃናቸው በይበልጥም ደግሞ የነበራቸው የበቀል ስሜት ረበሸኝ። ስለሆነም ያቀረቡትን ጥያቄ ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆንኩም። ይሁን እንጂ አጐቴ ሁለተኛ የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎችን እንዳይልክልኝ በደብዳቤ ነገርኩት። በክርስቶስ መመለስ ጉዳይ ላይ ግን ማብሰልሰሉን ቀጠልኩበት።
መንፈሳዊ ፍላጎቴ እያደገ ሄደ
የክረምት ዕረፍት ወራት ሲደርስ ልብሶቼን ለማዘጋጀት ሻንጣዬን አወጣሁ። በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የታተሙ ሦስት ቡክሌቶች ከስሩ ተቀምጠው ነበር። ከዚያ በፊት ልብ አላልኳቸውም ነበር። አንደኛው ሙታን የት ናቸው? የሚል ነበር።
‘ይህ አስደሳች ይመስላል’ ብዬ አሰብኩ። ምንም እንኳ የጳጳሱን ማስጠንቀቂያ ባስታውስም በውስጣቸው ይኖራሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ስሕተቶች ለማግኘት ቡክሌቶቹን በደንብ ለማንበብ ወሰንኩ። እርሳስ ያዝኩኝና በጥንቃቄ መፈለግ ጀመርኩ። በቡክሌቶቹ ውስጥ ያለው ሁሉም ነገር ምክንያታዊ ይመስላል እንዲሁም አንባቢው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዲያመሳክር እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር በጥቅስ የተደገፈ መሆኑ አስገረመኝ።
እኛ መጽሐፍ ቅዱስ ስላልነበረን ግን የተጠቀሱት ጥቅሶች ከጸሐፊው ዓላማ ጋር እንዲስማሙ አለቦታቸው የተጠቀሱ ይሆናሉ ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ አጐቴን አንድ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲልክልኝ ጠየቅሁት። እርሱም ሳይዘገይ ላከልኝ። ከዳር እስከ ዳር ሁለት ጊዜ አነበብኩት፤ ልረዳው ያልቻልኩት ብዙ ነገር ቢኖርም እንኳ በዳንኤል እና በራእይ መጻሕፍት ተማረክሁ። የተነበዩአቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ ለማወቅ ፈለግሁ። በአቅራቢያዬ ሊረዳኝ የሚችል ግን ማንም አልነበረም።
በ1929 ትምህርቴን እንደጨረስኩ አሜሪካ ያለው አጐቴ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎችን እንደገና ላከልኝ። የበለጠ እነርሱን ማንበብ እያስደሰተኝ ሲመጣ ዘወትር እንዲልክልኝ ጠየቅሁት። ከጽሑፎቹ ስለወደፊቱ ተስፋ የተማርኩትንም ለሌሎች ሰዎች መናገር ጀመርኩ። ያን ጊዜ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ መጣ።
በበርማ ያደረግሁት መንፈሳዊ እድገት
የእናቴ ወንድሞች ወደ በርማ (የዛሬዋ ማየንማር) ሄደው ነበር፤ እነርሱ ጋር ብሄድ የአስተሳሰብ አድማሴ እንደሚሰፋ እና ምናልባትም የንግድ ሥራ አጋጣሚ ላገኝ እንደምችል በማሰብ ወደዚያ እንድሄድ ቤተሰቡ ወሰነ። የሩቅ ምስራቅ አካባቢ ይማርከኝ ስለነበረ ወደዚያ የመሄዱ ተስፋ አስደሰተኝ። በበርማም ከአጐቴ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች ይደርሱኝ ነበር፤ ነገር ግን የይሖዋ ምስክሮችን ማለትም በዚያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው የሚጠሩትን በግል አግኝቼአቸው አላውቅም ነበር።
አንድ ቀን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የራእይ መጽሐፍ ስለሚያብራራ ላይት የተባለ ባለ ሁለት ጥራዝ መጽሐፍ ማስታወቂያ ሳነብ በደስታ ተዋጥኩ። ከዚህም በተጨማሪ በበርማ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ቦምቤሌ በሚገኘው የሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ስር እንደሚካሄድ ተረዳሁ፤ ወዲያውኑ ላይት የተባሉትን መጻሕፍት ለማግኘት እና በሕንድ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ወደ በርማ ተልከው እንዲሰብኩ ለመጠየቅ ደብዳቤ ጻፍኩ።
መጽሐፎቹ ሳይዘገዩ በፖስታ ደረሱኝ፤ እንዲሁም ከሳምንት ገደማ በኋላ በበርማ የሚገኙ የሀገሩ ተወላጅ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መጥተው ጠየቁኝ። እኔ እኖርበት በነበረው በበርማ ዋና ከተማ በራንጉን (ዛሬ ያናን በምትባለው) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ትንሽ ቡድን መኖሩን ሳውቅ በጣም ተደሰትኩ። በዘወትር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራማቸው ላይ እንድገኝ እንዲሁም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ስብከት እንድካፈል ጋበዙኝ። በመጀመሪያ ትንሽ አመነታ ነበር። ወዲያው ግን ያገኘሁትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ለቡድሂስቶች፣ ለሂንዱዎችና ለእስላሞች እንደዚሁም በስም ብቻ ክርስቲያኖች ነን ለሚሉትም ማካፈሌ ያስደስተኝ ጀመር።
ከዚያም የሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ኤዋርት ፍራንሲስ እና ራንዳል ሆፕሌ የተባሉ ሁለት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች (አቅኚዎች) ወደ ራንጉን ላከ። ሁለቱም የመጡት ከእንግሊዝ ሲሆን በሕንድ ለጥቂት ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። እነርሱም በከፍተኛ ሁኔታ አበረታቱኝ ከዚያም በ1934 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በማሳየት ተጠመቅሁ።
ደፋር ምስክር
ውሎ አድሮ የሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ተጨማሪ አቅኚዎችን ወደ በርማ ላከ። ከእነርሱ መካከል ሁለቱ ክላውድ ጉድማን እና ራን ቲፒን ወደ ባቡር ጣቢያ በመሄድ የባቡር ጣቢያ ሃላፊውን ሲድኒ ኩትን አነጋገሩት። መጻሕፍትን ወሰደ፣ በሙሉ አነበባቸው እና በማንዳሌይ ለምትገኘው ባለ ትዳር እህቱ ለዴዚ ዴ ሱዛ መጻፍ ጀመረ። እርሷም ጭምር መጻሕፍቱን አስደሳች ሆነው አገኘቻቸው እና ተጨማሪ መጻሕፍትን ጠየቀች።
ካቶሊክ ሆና የቆየችው ዴዚ በጣም ደፋር ነበረች። ወደ ጎረቤቶችዋ እየሄደች የምትማራቸውን ነገሮች ትነግራቸው ነበር። ቤተ ክርስቲያን መምጣት ለምን እንዳቆመች ሊጠይቃት ለመጣውም የደብር አለቃ የመቃጠያ ሲኦል አለ እያለ እርሱ እንደሚያስተምረው ያሉ ትምህርቶችን መጽሐፍ ቅዱስ እንደማይደግፍ አሳየችው።
በመጨረሻም እንዲህ ሲል ጠየቃት:- “ይህንን ሁሉ ዓመት ስለ መቃጠያ ሲኦል ሲነገራቸው ቆይቶ አሁን እንዲህ ዓይነት ቦታ የለም ብዬ እንዴት ልነግራቸው እችላለሁ? እንዲህ ከሆነ ማንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመምጣት አይፈልግም።”
ዴዚ እንዲህ ስትል መለሰችለት:- “ሐቀኛ ክርስቲያን ከሆኑ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን እውነቱን ያስተምሯቸዋል።” በመቀጠልም “እርስዎ የማይነግሯቸው ከሆነ እኔ እነግራቸዋለሁ” አለችው። ልክ እንዳለችውም አደረገች።
ዲክ እና ዴዚ እንዲሁም ሁለቱም ትልልቅ ልጆቻቸው የተጠመቁት በራንጉን ከእኔ ጋር አንድ ላይ ነበር። ከሦስት ዓመት በኋላ በ1937 ሁለተኛዋን ሴት ልጃቸውን ፌሊስን አገባሁ።
ወደ ሕንድ ሸሽተን አመለጥን
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጃፓን ኃይሎች በርማን ወረሯትና ራንጉን በየካቲት 8, 1942 ተያዘች። የውጭ ዜጋ የሆኑ ሲቪሎች በፍጥነት ወደ ሕንድ እንዲወጡ ይገደዱ ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ በጫካ አቋርጠው ለመውጣት ሞክረው ነበር። ነገር ግን ብዙዎቹ በመንገድ ላይ ሞቱ። ለማስወጣት ኃላፊነት የነበረውን መኮንን በግል አውቀው ስለነበር ከራንጉን ወደ ካልካታ ከሚሄዱት የመጨረሻ የዕቃ መጫኛ ጀልባዎች በአንዱ የመሄጃ ቲኬት ማግኘት ችዬ ነበር። በዚያ ጥድፊያ ቤታችንንና ብዙውን ንብረታችንን ጥለን መሄዳችን ለሁላችንም የሚያሳዝን አጋጣሚ ነበር። በርማ ከ1942 እስከ 1945 ድረስ በጃፓኖች እጅ ተይዛ ነበር።
ሕንድ ስንደርስ ገንዘባችን ትንሽ ቀርቶ ነበር፤ ሥራ ማግኘትም ቀላል አልነበረም። ይህም እምነታችንን የሚፈትን ነገር አስከተለ። ከአንድ እንግሊዛዊ መኮንን ጋር ተገናኘንና ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝ ነገር ግን በውጊያ የማያሳትፍ ሥራ አለን አለኝ። ሆኖም ሥራው የወታደራዊው መዋቅር አካል ነበር። የቀረበልኝን ሥራ በይሖዋ እርዳታ በመተው ንጹሕ ክርስቲያናዊ ሕሊናዬን ልጠብቅ ችያለሁ። (ኢሳይያስ 2:2–4) በሌሎች መንገዶችም የአፍቃሪውን የይሖዋን እጆች አይተናል።
በሕንድ ዋና ከተማ በኒው ዴልሂ መኖር ጀመርን። በዚህ ከተማ መኖሪያ ቤት ማግኘት በጣም ከባድ ነው። የሆነ ሆኖ በከተማዋ መሃል ሰፊ አፓርተማ አገኘን። መግቢያው ለብቻ የሆነ ሰፊ የመዝናኛ ክፍል ነበረው፤ ይህም ክፍል ለሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ለዴልሂ የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤ እንደ መንግሥት አዳራሽ ሆኖ አገልግሏል። ይሁን እንጂ በ1941 በሕንድ ውስጥ በሁሉም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበሩ ጽሑፎች ላይ እገዳ ስለተደረገ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማግኘት አልቻልንም ነበር።
እገዳው እንዴት ተነሳ?
በ1943 አንድ እሁድ በዴልሂ ቤተ ክርስቲያኖች ቅዳሴ የተካፈሉት ሁሉ በ13 የተለያዩ ቤተ ክርስቲያን ቄሶች የተፈረመ ጽሑፍ ተሰጣቸው። “የዴልሂ ነዋሪዎች ከይሖዋ ምስክሮች ተጠንቀቁ” በማለት የሚያስጠነቅቅ ነበር። ክሱ በሕንድ የታገድነው በፖለቲካ ምክንያት እንደሆነ የሚገልጽ ነበር።
ከቦምቤ የቅርንጫፍ ቢሮ ፈቃድ አገኘንና ቄሶቹን ያጋለጠ በራሪ ጽሑፍ በፍጥነት አሳትመን አሰራጨን። እኔ መሪ የበላይ ተመልካች ስለነበርኩ ስሜ እና አድራሻዬ በጠንካራ ቃላት ከሰፈረው ጽሑፍ በታች ይገኝ ነበር። ወዲያው ማርግሪት ሆፍማንና እኔ የጽሑፉን ቅጂዎች ስናሰራጭ ፖሊሶች አገኙንና ተይዘን ታሰርን፤ ይሁን እንጂ ወዲያው በዋስ ተለቀቅን።
ከጊዜ በኋላ ማርግሬት ስታገለግል በሕንድ የተወካዮች ምክር ቤት የታወቁትን ሚኒስትር የሰር ስሬቫስታቫን ቤት አንኳኳች። ሰር ስሬቫስታቫ በጥሩ መንፈስ ተቀበሏት። በውይይታቸውም ወቅት ጽሑፎቻችን በሕንድ የታገዱት ያለ አግባብ መሆኑን ነገረቻቸው። በዚያው ቀን ማርግሬት በፓርላማ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ከማድራስ ክፍለ ግዛት ወደ ከተማ የመጡ የፓርላማ አባል አገኘች። እርሷም በጽሑፎቻችን ላይ የተደረገው እገዳ አግባብነት እንደሌለው ጠቀሰችላቸውና ጉዳዩን በመጪው ስብሰባ ላይ እንደሚያነሱት ቃል ገቡላት።
በዚያን ወቅት እኔ በአካባቢው በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ በፊዚዮቴራፒ የሕክምና ሙያ እሠራ ነበር። ሰር ስሬቫስታቫ በሕመም ይሠቃዩ ስለነበር ሆስፒታሉ የፊዚዮቴራፒ ሕክምና ሊረዳቸው እንደሚችል በማሰብ እኔ እንዳያቸው ላከኝ። ሰር ስሬቫስታቫ ተግባቢ ሰው ሆነው አገኘኋቸውና ስንጫወት በመሃል ሚስ ሖፍማንና እኔ ከእስር ቤት በዋስ እንደ ተለቀቅን ጠቀስኩላቸው። የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንም በፖለቲካ ስም የታገዱት በቄሶች ግፊት እንጂ ፈጽሞ ከፖለቲካ ነፃ መሆናችንን አስረዳኋቸው። በመቀጠልም የቅርንጫፍ ቢሮአችን ተወካይ ኤድዊን ስኪነር አቋማችንን ለማስረዳት ጠይቆ ተቀባይነት እንዳላገኘም ነገርኳቸው።
ከአንድ ሁለት ቀን በኋላም ሰር ስሬቫስታቫ “ሚስተር ጄንኮዝ [ለሥራችን እንቅፋት የነበረው የመንግሥት ባለ ሥልጣን] ከጥቂት ቀናት በኋላ ጡረታ ይወጣልና በእርሱ ስፍራ ሰር ፍራንሲስ ሙዴ ይተካል። ሚስተር ስኪነር እንዲመጣ ንገረውና እኔ ከሰር ፍራንሲስ ጋር አስተዋውቀዋለሁ” አሉኝ።
አስቀድመው ቃል ገብተው እንደነበረው ሰር ስሬቫስታቫ የሚገናኙበትን ቀን አመቻችተው ነበር። በዚያም ወቅት ሰር ፍራንሲስ ሙዴ ለወንድም ስኪነር “ምንም ነገር ቃል ልገባልህ አልችልም ነገር ግን በነገሩ አስብበታለሁ” አሉት። ፓርላማው በጥቂት ቀናት ውስጥ ይከፈት ስለነበረ ወንድም ስኪነር ውጤቱን ይጠባበቅ ነበር። ከማድረስ የመጡት የፓርላማው አባል ቃላቸውን በመጠበቅ ተነሡና “የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ጽሑፎች በፖለቲካ ምክንያት ታግደዋል የሚባለው እውነት ነውን?” ሲሉ ጠየቁ።
ሰር ፍራንሲስ ሙዴ በበኩላቸው “አይደለም፤ እገዳው የተጣለው ለጥንቃቄ ሲባል ነው። አሁን ግን መንግሥት እገዳው እንዲሻር ወስኗል” ሲሉ መለሱ።
ይህንን ዜና ስንሰማ ለእኛ እንዴት ያለ አስደሳች ወቅት ነበር! ከሳምንት ጊዜ በኋላ የቦምቤ ቅርንጫፍ ቢሮ እገዳው እንዳበቃ የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰው።
በጦርነት ወደ ደቀቀችው በርማ መመለስ
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የብሪታንያ አገዛዝ ወደ በርማ ተመለሰና ከጥቂት ወራት በኋላ 10 ምስክሮች ሆነን ወደ ራንጉን ተመልሰን ሄድን። በዚያ የቀሩትን ጥቂት የአካባቢው ምስክሮች እንደገና ለማየት በመቻላችን ተደሰትን። አገሪቷ በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ ነበረች። ኤሌክትሪክንና የሕዝብ መጓጓዣዎችን ጨምሮ የሕዝብ አገልግሎቶች ተቋርጠው ነበር። ስለዚህ አንድ ጂፕ መኪና ከወታደሮቹ ገዛንና ከተመለስን በኋላ ወዳደራጀናቸው ስብሰባዎች የሚመጡትን ሰዎች ለማጓጓዝ በሚገባ ተጠቀምንባት።
አንድ ፍላጐት ያሳየ ሰው መሬት ሰጠንና በአካባቢው ባሉ ደግ ሰዎች ትብብር መጠነኛ ስፋት ያለው የመንግሥት አዳራሽ ሠራን። አዳራሹ በጠንካራ የቀርከሃ ምሰሶ እና ግድግዳው አንድ ላይ በተጣበቁ ቀርከሃዎች እንዲሁም ጣሪያው ከሣር የተሠራ ነበር። በሚያዝያ 1947 በዚያን ጊዜ የማኅበሩ ፕሬዘዳንት የነበረው ናታን ኤች ኖር እና ጸሐፊው ሚልተን ጂ ሄንሼል ራንጉንን ሲጎበኙ በዚህ አዳራሽ ንግግር አደረጉ። በዚያን ወቅት በበርማ 19 ምስክሮች ነበርን። የወንድም ኖር የሕዝብ ንግግር በኒው ኤክሴልሲየር የቲያትር አዳራሽ ሲሰጥ ግን 287 ተገኝተው ነበር።
በአውስትራሊያ ውስጥ መኖር ጀመርን
በጥር 4, 1948 በርማ ከታላቋ ብሪታንያ ነፃነቷን ስላገኘች አብዛኛዎቹ አውሮፓውያን አገሪቷን ለቅቆ መውጣቱን የተሻለ እንደሆነ ገምተው ነበር። ፊሊስ እና እኔ በጸሎት ካሰብንበት በኋላ ሴት ልጃችንን ይዘን ወደ አውስትራሊያ ለመሄድ ወሰንን። የምዕራብ አውስትራሊያ ዋና ከተማ በሆነችው ፐርዝ በተባለች ከተማ መኖር ጀመርን።
እንደገና በርማን ለቀን በመሄዳችን በተለይ አሁን ሁለተኛ ስለማንመለስ በጣም የሚያሳዝን ወቅት ነበር። አልፎ አልፎ እዚያ ካሉ ወዳጆቻችን ስለ ሁኔታው እንሰማ ስለነበረ የመንግሥቱ ሥራ በአገሪቱ ውስጥ በትጋት እየተካሄደ መሆኑን በማወቃችን ደስተኞች ነበርን።
ከ1978 ጀምሮ ለአራት ዓመታት በአውስትራሊያ ታላላቅ ከተሞች የሚገኙትን ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑ ጉባኤዎችን በሙሉ በማገልገል መብት ስንደሰት ቆይተናል። የዚህች ትልቅ አገር ስፋት ከምዕራባዊ ጫፍ እስከ ምሥራቅ ጫፍ ድረስ ከ4,200 ኪሎ ሜትር በላይ ስለሆነ ረጅም ርቀት ያለው ጉዞ ነበር። ከአንዱ ክፍለ ግዛት ወደ ሌላው መዘዋወሩ የሚያስከትለው ከፍተኛ የአየር ለውጥ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ጤንነታችን እየቀነሰ እንዲሄድ አስተዋጽኦ አደረገ። ስለዚህ ወደ ፐርዝ ተመለስንና በዚያ ከሚገኙት 44 ጉባኤዎች መካከል በአንዱ ሽማግሌ ሆኜ ማገልገል ቀጠልኩ።
ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ዓይኖቼ እየደከሙ መጡና ማንበብ አስቸጋሪ ሆነ። ይሁንና የጤና ችግር ቢኖርብንም ልባችን ግን ገና ወጣት ነው። ይሖዋን የሚፈልጉ ሁሉ የጽድቅ ፀሐዩን ሲያወጣ የሚያዩበትን አስደሳች ቀን ሁለታችንም በልበ ሙሉነት እየጠበቅን ነው:- “ፈውስም በክንፎቿ ውስጥ ይሆናል፤ እናንተም ትወጣላችሁ፣ እንደ ሰባም እምቦሳ ትፈነጫላችሁ።” — ሚልክያስ 4:2a
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የሕይወት ታሪኩ ተጽፎ በሚጠናቀቅበት ጊዜ በታህሣሥ 13, 1992 ወንድም ትሳቶስ በሞት አንቀላፋ።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1947 ቤተሰቤ ከወንድም ሄንሼል እና ኖር ጋር በበርማ (ማያንማር )
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባሲል ትሳቶስ እና ሚስቱ ፊሊስ በአውስትራሊያ