ወደፊት የሚሆነውን ለማወቅ የሚደረግ ጥረት
“ከሦስት ቀናት በኋላ የሚፈጸሙትን ነገሮች አስቀድሞ ለማወቅ የቻለ ሰው ለብዙ ሺህ ዓመታት ሐብታም ይሆናል” ይላል አንድ የቻይናውያን ምሳሌ።
ሰዎች የነገው ዕለት ምን ይዞ እንደሚመጣ ለማወቅ ይፈልጋሉ። ብዙዎች እንዲህ ዓይነቱን አስተማማኝ መረጃ ለማግኘት ቢችሉ በጣም ብዙ ብር በደስታ ይከፍሉ ነበር። ወደፊት ስለሚሆነው ነገር አስተማማኝ ትንበያ ለማግኘት ይፈልጋሉ። ከአየር ሁኔታ ትንበያዎችና ከኢኮኖሚ አቅጣጫ ጠቋሚዎች ለማየት እንደሚቻለው ከፊታችን ስላሉት ሁኔታዎች ለማወቅ ፍላጎት አለን። ከዚህም በላይ ደግሞ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚኖረን አስተማማኝ እውቀት ዕቅድ ለማውጣትና ሕይወታችንን ለማስተካከል ያስችለናል።
ብዙዎች የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደያዘ ለማወቅ ያላቸው ምኞት ሟርተኞችን፣ ደብተራዎችን፣ ኮከብ ቆጣሪዎችንና ጠንቋዮችን እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል። የመጻሕፍትና የመጽሔት መሸጫ መደብሮች ስለወደፊቱ ጊዜ ይናገራሉ በሚባልላቸው ጥንታዊና ዘመናዊ ጽሑፎች ተሞልተዋል። ይሁን እንጂ እንደዚህ ዓይነቶቹ ትንቢቶች ብዙዎች ይጠራጠሯቸዋል። ሮማዊው የሃገር መሪ ካቶ ‘ሁለት ትንቢት ተናጋሪዎች ሲገናኙ ሳይሳሳቁ አይቀሩም ብዬ እገምታለሁ’ ብሏል።
በእርግጥ ብዙ ዓይነት ትንበያዎች አሉ። በ1972 ክለብ ኦቭ ሮም በመባል የሚታወቅ አንድ የምሁራንና የንግድ ሰዎች ቡድን መተኪያ የሌላቸው የምድር ሀብቶች በቅርቡ እንደሚሟጠጡ የሚተነብይ አንድ ጥናት አውጥቶ ነበር። ምድር በ1981 ወርቅ አልባ፣ በ1985 ሜርኩሪ፣ በ1990 ዚንክ፣ በ1992 ነዳጅ አልባ ትሆናለች የሚሉትንና የመሳሰሉትን ተንብዮ ነበር። አሁን እነዚህ ትንበያዎች እንዳልተፈጸሙ እንመለከታለን።
ብዙ ትንበያዎች በሃይማኖታዊ አመለካከቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል የሳክሰን ጳጳስ የነበሩት ዉልፍስታን በ11ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ገደማ ዴንማርኮች እንግሊዝን መውረራቸው የዓለም መጨረሻ መቅረቡን የሚያሳይ ምልክት ነው ብለው አምነው ነበር። በ1525 ቶማስ ሙንትሰር መላእክት ማጭድ ሲስሉ በራእይ ስላየና ይህም ታላቅ መከር የሚሰበሰብበት ጊዜ ይሆናል ብሎ ስላሰበ የጀርመን ገበሬዎችን ለዓመፅ አነሳስቷል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እነዚህ ትንበያዎች የተሳሳቱ ነበሩ።
እንደምታውቀው መጽሐፍ ቅዱስ ስለወደፊቱ ሁኔታ ብዙ የሚናገራቸው ነገሮች አሉ። ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ትንቢቶቹን የጻፉት በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደሆነ ይናገራሉ። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጴጥሮስ “በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” ብሏል። — 2 ጴጥሮስ 1:20, 21
መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ከሚናገራቸው ነገሮች መካከል ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማያዊ መንግሥት ሥልጣን ላይ መገኘቱን የሚመለከተውን ትውልድ ለይተው የሚያሳውቁ የተለያዩ ክስተቶች እንደ ሚመጡ የሚገልጸው ይገኝበታል። ታይቶ የማይታወቅ ጦርነት፣ ረሐብ፣ የምድር መንቀጥቀጥና የሥነ ምግባር አውታሮች መበጣጠስ መጽሐፍ ቅዱስ “የመጨረሻ ቀኖች” ብሎ ለሚጠራቸው መለያ ምልክት ይሆናሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5፤ ማቴዎስ 24:3–14, 34) በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የአሁኑ የነገሮች ሥርዓት መወገድ የሰው ዘሮች መጨረሻ የሌላቸው በረከቶችን በሚያገኙበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለሚኖራቸው ደስታ መንገድ የሚጠርግ ይሆናል። — 2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1–4
እንደዚህ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንዴት ትመለከታቸዋለህ? እንደ ብዙዎቹ ሌሎች ትንበያዎች ሁሉ እንዲያው ግምታዊ ሐሳቦች ብቻ ናቸውን? ባለፉት ዘመናት ስለተፈጸሙት ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ የተናገራቸው ነገሮች አስተማማኝ መሆናቸውንና አለመሆናቸውን ካወቅን ገና ያልተፈጸሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አስተማማኝ መሆናቸውን ፈትነን ለማረጋገጥ እንችላለን። በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹን እንመረምራለን።
[ምንጭ]
Courtesy National Weather Srvice