ይሖዋን የምታገለግለው ለምንድን ነው?
“የይሖዋ ቀን ደርሷል! ‘ታላቁ መከራ’ ቅርብ ነው፤ አምላክን ካላገለገልክ ታላቁን መከራ በሕይወት ልታልፍ አትችልም።” አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ቢነግርህ ኖሮ ምን ዓይነት እርምጃ ትወስድ ነበር? — ሶፎንያስ 2:2, 3፤ ማቴዎስ 24:21
እርግጥ ነው የይሖዋን ቀን በአእምሮአችን መያዝ ይኖርብናል፤ በቅርብ ጊዜ ከሚመጣው ታላቅ መከራ በሕይወት መትረፍ አምላክን በታማኝነት በማገልገላችን ላይ የተመካ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች ለይሖዋ አምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንድናቀርብ የሚያደርጉን ዋና ምክንያቶች መሆን ይኖርባቸዋልን? አንተ ይሖዋን የምታገለግለው ለምንድን ነው?
በትክክለኛ ዓላማ ተነሳስቶ የማገልገል አስፈላጊነት
አንድ ሰው በትክክለኛ ዓላማ ተነሳስቶ አምላክን የማያገለግል ከሆነ ይመጣሉ ብሎ ተስፋ ያደረጋቸው ነገሮች በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ሳይመጡ ቢቀሩ አምላክን ማገልገሉን ሊተው ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በ1843 ወይም በ1844 ውስጥ ይመለሳል ብለው ጠብቀው ነበር። ተስፋቸው ሳይፈጸም እነዚያ ቀኖች አለፉ። በዚህ ረገድ የባይብል ኤግዛሚነር አሳታሚ በነበረውና በኋላም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጀመሪያ ፕሬዘዳንት ከነበረው ከቻርልስ ቴዝ ራስል ጋር ትውውቅ በነበረው በጆርጅ ስቶርዝ የተጻፈው ሐሳብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነው። በመስከረም 1846 ስቶርዝ ባይብል ኤግዛሚነር በተባለው በራሪ ጽሑፍ ላይ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:-
“አምላክን የማገልገል ግዴታ ቀኑ በመግፋቱ ላይ ብቻ የተመሠረተ አይደለም። . . . የ1846 እና የ1847 ዓመታት የጌታ ሁለተኛ መምጣት ሳይፈጸምባቸው ካለፉ (ደግሞም ሊያልፉ ይችላሉ) ሰዎች የሚወስዱት እርምጃ ከገመትነው በላይ የከፋ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በፊት በተሞክሮ የታየው ሁኔታ ይህን አረጋግጧል። በ1843 እና በ1844 የደረሰውን ሁኔታ ማለቴ ነው። በዚያን ጊዜ በነበረው አስተሳሰብ የጌታ መምጫ ጊዜ ነው በሚለው ጩኸት ‘አምላክን ለማገልገል ተነሳስተው’ ከነበሩት መካከል አብዛኞቹ አሁን የት አሉ? የገደል ማሚቶውም የት አሉ!!! እያለ ያስተጋባል። ክርስቲያን ነኝ ባይነቱን አክብሮ የተገኘው ግፋ ቢል ከአሥር አንዱ ብቻ ነው። ለምን እንደዚያ ሆነ? በተሳሳተ ዓላማ ተነሳስተው ስለ ነበረ ነው። ስሜታቸውን የማረከውና የቀሰቀሰው ዋናው ነገር ራስ ወዳድነታቸው ነበር። ታሞ በሞት አፋፍ ላይ እንዳለ ወይም በባሕር ማዕበል ውስጥ እንደሚገኝ አድርጎ ራሱን እንደሚመለከት ኃጢአተኛ ሆነው ነበር። መ ሞቱ የማይቀር ከሆነ ክርስቲያን ይሆናል። አደጋው እንደሚቀርለት ካወቀ ግን እንደ ቀድሞው ግዴለሽ ይሆን ነበር።”
በትክክለኛ ዓላማ ተነሳስቶ ማገልገል
ራስ ወዳድነትና እንዳልጠፋ የሚል ፍርሃት አንዳንዶች የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ለነገሩ ያህል አንዳንድ ነገሮችን እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል። ሌሎች ደግሞ በገነት ውስጥ የመኖሩ ተስፋ ይስባቸውና ለዚህ ሲሉ ብቻ አምላክን ያገለግሉ ይሆናል። ሆኖም መጀመሪያውኑ እዲህ ባሉት ግፊቶች ተነሳስተው የሚያገለግሉ ሰዎች የይሖዋ ቀንና ታላቁ መከራ በጣም ቅርብ እንዳልሆኑ ቢያስቡ ኖሮ አምላክን በቅንአት ወደ ማገልገል ላያዘነብሉ ይችሉ ነበር።
እርግጥ ነው በአምላክ ተስፋዎችና አስቀድመው በተነገሩት በረከቶች መደሰት ራስ ወዳድነት አይደለም። አምላክ የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች በመሆን ከፊታችን በተዘረጉልን ተስፋዎች እንድንደሰት ይፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በተስፋ ደስ ይበላችሁ” ብሏል። አክሎም “በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ” አለ። (ሮሜ 12:12) ጸሎት የታከለበት “የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] ደስታ” ችግሮችን እንድንቋቋምና የአምላክ ተስፋዎች የሚፈጸሙበትን ጊዜ በትዕግሥት እንድንጠብቅ ይረዳናል። (ነህምያ 8:10) እስከዚያው ድረስ ይሖዋን የምናገለግልበት ብዙ ምክንያቶች አሉን። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
ግዴታና መብት
ይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዢ እንደመሆኑ መጠን ለእሱ ብቻ የተወሰነ አምልኮ እንድንሰጠው ይፈልጋል፤ ደግሞም ይገባዋል። (ዘጸአት 20:4, 5) ስለዚህ ታላቁ መከራ ነገም ይጀምር፣ የሚቀጥለው ዓመት ወይም ከዚያ በኋላ እያንዳንዱ ክርስቲያን በአምላክ ፊት እኩል ግዴታ አለበት። አንድ ክርስቲያን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ሁኔታ ይሖዋን የማገልገል ግዴታ አለበት። ይህንንም የሚያደርገው አምላክን በሙሉ ልቡ፣ ነፍሱ፣ አእምሮውና ኃይሉ ስለሚወድ መሆን አለበት። (ማርቆስ 12:30) አንዳንድ የጥንት ክርስቲያኖች የይሖዋ ቀን እንደደረሰ አድርገው አስበው ነበር። ሆኖም ተስፋቸው በዚያን ጊዜ አልተፈጸመም፤ ስለሆነም ያን ሁኔታ ሳያዩ ሞተዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:1–5፤ 2 ተሰሎንቄ 2:1–5) ይሁን እንጂ እነዚያ የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮች እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ከነበሩ በመጨረሻው ለሰማያዊ ሕይወት ትንሣኤ አግኝተዋል ማለት ነው። — ራእይ 2:10
የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች እሱን በታማኝነት ማገልገል ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም የእሱን ፈቃድ የማድረጉን ግዴታ ራሳቸው ፈቅደው ተቀብለዋል። እስቲ አስበው! እንደ ቅዱሳን መላእክት ሁሉ እኛም የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ገዢ ፈቃድ ለማድረግ እንችላለን። (መዝሙር 103:20, 21) ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን መብት ከፍ አድርጎ ስለተመለከተው “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:34) እኛም ይኸው ዓይነት መንፈስ ካለን የይሖዋን ምስጋና በቅንዓት ለሰው ሁሉ እናስታውቃለን፤ እንዲሁም በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለተገለጹት የእሱ ዓላማዎች ለሌሎች እንናገራለን። በዚህ መንገድ እኛም ሌሎችን በመንፈሳዊ የመርዳት መብት እናገኛለን። እንግዲያው የይሖዋ ቀን መቼም ይጀምር መቼ ለእሱ ባለን ፍቅር ተገፋፍተን የአምላክን ፈቃድ ማድረግ በጣም ግሩም መብት ነው።
አመስጋኝነት አምላክን እንድናገለግል ይገፋፋናል
በተጨማሪም አምላክ የልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት በማቅረብ ላሳየው ፍቅር ያለን አመስጋኝነት ይሖዋን እንድናገለግል ሊገፋፋን ይገባል። በአንድ ወቅት በኃጢአት ምክንያት ከይሖዋ አምላክ ርቀን ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሏል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን [የሰው ልጆችን ዓለም] እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐንስ 3:16) ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ እንደጻፈው በዚህ ረገድ ቀዳሚውን እርምጃ የወሰደው ይሖዋ ነው። “ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።” (ሮሜ 5:8) ለዚህ የአምላክ የፍቅር መግለጫ ያለን አመስጋኝነት በሙሉ ልባችን እሱን እንድናገለግል ሊገፋፋን ይገባል።
ይሖዋ ለሚሠጠን መንፈሳዊና ቁሳዊ ምግብ ያለን አድናቆት እሱን በታማኝነት የምናገለግልበትን ተጨማሪ ምክንያት ይሰጠናል። የአምላክ ቃል አስተማማኝ መሪ ነው፤ ለመንገዳችንም ብርሃን ነው። “በታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት የሚቀርቡልን ጽሑፎች አኗኗራችንን ከመለኮታዊው ፈቃድ ጋር እንድናስማማ ይረዱናል። (ማቴዎስ 24:45–47፤ መዝሙር 119:105) አስቀድመን መንግሥቱን ስለምንፈልግ ይሖዋም በቁሳዊ በኩል የሚያስፈልገንን ነገር ያቀርብልናል። (ማቴዎስ 6:25– 34) ለእነዚህ ነገሮች ያለህን አድናቆት እያሳየህ ነውን?
አምላክ ከሐሰት ሃይማኖት እንድንላቀቅ ለሰጠን ነፃነት ያለን አመስጋኝነት ይሖዋን በታማኝነት የምናገለግልበትን ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ይሰጠናል። ሃይማኖታዊ ጋለ ሞታ የሆነችው ታላቂቱ ባቢሎን “በብዙ ውኃዎች ላይ ተቀምጣለች”። እነዚህም ውኃዎች “ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም ናቸው።” (ራእይ 17:1, 15) ነገር ግን ሃይማኖታዊ አመራርና ቁጥጥር በማድረግ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ አትቀመጥም። ለምሳሌ ያህል የሰው ነፍስ አትሞትም የሚለውን ሐሰት የሆነ ሃይማኖታዊ ትምህርት አይቀበሉም። ሰው “ሕያው ነፍስ” ሆኖ እንደተፈጠረ፣ ‘ሙታን አንዳች እንደማያውቁ’ እንዲሁም ወደፊት ትንሣኤ እንደሚኖር ያውቃሉ። (ዘፍጥረት 2:7 የ1879 ትርጉም ፤ መክብብ 9:5, 10፤ ሥራ 24:15) ስለዚህ ሙታን ይጎዱናል ብለው አይፈሩም ወይም አያመልኳቸውም። ለእንዲህ ዓይነቱ መንፈሳዊ ነፃነት ያለህ አመስጋኝነት ክህደት ወደ አንተ እንዳይመጣ እንድትከላከልና ንጹህ ከሆነው የይሖዋ አምልኮ ጋር እንድትጣበቅ አድርጎሃልን? — ዮሐንስ 8:32
ይሖዋ በየዕለቱ ለሚሰጠን ድጋፍ ያለን አድናቆት ከእሱ ጎን በታማኝነት በመቆም እሱን ለማገልገል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ከፍ ሊያደርገው ይገባል። መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ብሏል:- “ሸክማችንን በየቀኑ የሚያቀልልንና እኛን የሚያድን እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አምላክ የተመሰገነ ይሁን።” (መዝሙር 68:19 የ1980 ትርጉም ) በሌላም ቦታ ላይ “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ግን ተቀበለኝ” ብሏል። (መዝሙር 27:10) አዎ፣ ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ ያለ ሰው እንደ ጭንቀትና መከራ የመሳሰሉትን ምሳሌያዊ ሸክሞቹን በአምላክ ላይ ሊጥል ይችላል። እሱን በታማኝነት በማገልገል ምንጊዜም ቢሆን ለማይቋረጠው የይሖዋ ድጋፍ አድናቆትህን እያሳየህ ነውን? — መዝሙር 145:14
ይሖዋንና ንግሥናውን ከፍ ከፍ አድርግ
ይሖዋን ከፍ ከፍ ለማድረግ ያለን ምኞትም እርሱን እንድናገለግለው ሊገፋፋን ይገባል። ሰማያዊ ፍጥረታት በሚከተሉት ቃላት አምላክን ከፍ ከፍ አድርገዋል:- “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል።” (ራእይ 4:11) ንጉሥ ዳዊት እንደሚከተለው በማለት አምላክን ከፍ ከፍ አድርጓል:- “አቤቱ፣ . . . አምላክ [ይሖዋ አዓት] ሆይ፣ . . . ታላቅነትና ኃይል፣ ክብርም፣ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፣ መንግሥት የአንተ ነው፣ . . . ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፣ አንተም ሁሉን ትገዛለህ፤ . . . አምላካችን ሆይ፣ እንገዛልሃለን፣ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን።” (1 ዜና መዋዕል 29:10–13) የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ተስፋዎቹ የሚፈጸሙበትን ጊዜ እየጠበቅን በቃልና በድርጊት እሱን ከፍ ከፍ ለማድረግ መገፋፋት አይገባንምን? — 1 ቆሮንቶስ 10:31
ስለ አምላክ መንግሥት ለመናገር ያለን ከውስጥ የሚሰማን ኃይለኛ ግፊትም ይሖዋን እንድናገለግል የሚያነሳሳንን ሌላ ነገር ይጨምርልናል። ይህ ተገቢ የሆነ ውስጣዊ ግፊት በሚከተሉት የመዝሙራዊው ቃላት በሚገባ ተገልጸዋል:- “አቤቱ፣ ሥራህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፣ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል። የመንግሥትህን ክብር ይናገራሉ፣ ኃይልህንም ይነጋገራሉ፣ ለሰው ልጆች ኃይልህን የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቁ ዘንድ። መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፣ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው።” (መዝሙር 145:10–13) የመንግሥቱን መልእክት በየቦታው ማሳወቁ የክርስቲያኖች ተልዕኮና በአሁኑ ጊዜ በአስፈላጊነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ትልቅ ሥራ ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ይሖዋን በሰው ፊት ከፍ ከፍ ለማድረግና ስለ መንግሥቱ ለሌሎች ለመናገር እንደ እሳት የሚያቃጥል ስሜት አለህን?
የይሖዋ ስም መቀደስና የሉዓላዊነቱ መረጋገጥ ለእኛ በጣም አስፈላጊ ነገር ከመሆኑ የተነሳ እርሱን በታማኝነት የማገልገል ፍላጎት ሊያሳድርብን ይገባል። የይሖዋ ስም እንዲቀደስና ሉዓላዊነቱ እንዲረጋገጥ እንጸልይ ይሆናል። (ማቴዎስ 6:9) በክርስቲያናዊ አገልግሎት ዘወትር በመሳተፍና እንደዚህ ስላሉት እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች የሚናገረውን እውነት በማሰራጨት ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ ድርጊት ለመፈጸም እንችላለን። — ሕዝቅኤል 36:23፤ 39:7
ደስታና እርካታ
ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል የእሱን ልብ ደስ በማሰኘትና ዲያብሎስ ውሸታም መሆኑን በማረጋገጥ እርካታ እናገኛለን። ምንም እንኳን ሰይጣን ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ነው በማለት በሐሰት ቢናገርም በፍቅር ተነሳስተን ለይሖዋ በታማኝነት በመቆም የምናቀርበው አገልግሎት የዚህ ተሳዳቢ ክርክር ሐሰት መሆኑን ያረጋግጣል። (ኢዮብ 1:8–12) ይህም በምሳሌ 27:11 ላይ እንደሚከተለው በማለት የተነገረውን ሐሳብ በማድረግ እንድንገፋበት ጥሩ ምክንያት ይሰጠናል:- “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ።” ከዚህም በላይ ሰይጣን በፊታችን ያስቀመጣቸው ብዙ ጋሬጣዎች እያሉ ከይሖዋ ጎን በታማኝነት በመቆም ስናገለግለው የአቋም ጽናታችን የእምነት ጓደኞቻችንን ያጠነክራቸዋል። — ፊልጵስዩስ 1:12–14
መንፈሳዊውን መከር በመሰብሰቡ ሥራ ተካፋይ ስንሆን የምናገኘው ደስታና እርካታም ይሖዋን በታማኝነት እንድናገለግል ሊያነሳሳን ይገባል። ኢየሱስ ሰዎችን በተለይ በመንፈሳዊ በመርዳት ደስታ አግኝቷል። ማቴዎስ 9:35–38 እንደሚከተለው ይላል:- “ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፣ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፣ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፣ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር። ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፣ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን:- መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት አላቸው።” የመከሩ ሥራ እኛ ከጠበቅነው በላይ ከቆየ ሌሎችን በመንፈሳዊ በመርዳት ደስታና እርካታ የምናገኝበት የበለጠ አጋጣሚ ይሰጠናል። ይህም ከእኛ የሚጠበቅብንን የጎረቤት ፍቅር የምናሳይበት መንገድ ነው። — ማቴዎስ 22:39
አምላክን የምታገለግለው ለምንድን ነው?
ይሖዋን በታማኝነት እንድናገለግለው ከሚያስገድዱን ብዙ ምክንያቶች ውስጥ ጥቂቶቹን ብቻ ተመልክተናል። እያንዳንዳችን ለአምላክ መልስ ስለምንሰጥ እሱን የምናገለግልባቸውን የግል ምክንያቶቻችንን በጸሎት ብናስብባቸው ጥሩ ነው። (ሮሜ 14:12፤ ዕብራውያን 4:13) በራስ ወዳድነት ብቻ ተገፋፍተው ማገልገላቸውን የሚቀጥሉ የመለኮታዊውን ሞገስ ደስታ አያገኙም።
በቅድሚያ የሚያሳስበን ነገር የአምላክ ስም መቀደስ ከሆነና ከራስ ወዳድነት ሐሳቦች ነፃ በሆኑ ግፊቶች ተነሳስተን ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እየሰጠን ከሆነ ምን ልንጠብቅ እንችላለን? ይሖዋ እኛንና አገልግሎታችንን ይባርካል! (ምሳሌ 10:22) በተጨማሪም ይሖዋን በታማኝነት ስላገለገልን የዘላለም ሕይወት እናገኛለን።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
SIX SERMONS, by George Storrs (1855)
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጃፓን በሺዎች የሚቆጠሩ ይሖዋን ያገለግላሉ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኮትዲቩዋር ይሖዋን ማገልገል