የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 ሚያዝያ ገጽ 2-7
  • “የምታገለግሉትን . . . ምረጡ”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “የምታገለግሉትን . . . ምረጡ”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኢየሱስ ይሖዋን ለማገልገል የመረጠው ለምንድን ነው?
  • ይሖዋ አምልኳችን የሚገባው ለምንድን ነው?
  • ይሖዋን ለማገልገል የምንመርጠው ለምንድን ነው?
  • ይሖዋን ማገልገልህን ቀጥል
  • የማታውቋቸው ነገሮች እንዳሉ አምናችሁ በመቀበል ልካችሁን እንደምታውቁ አሳዩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • በይሖዋ እንደምንታመን የሚያሳዩ ውሳኔዎች
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2023
  • ይሖዋ “ሕያው አምላክ” እንደሆነ አስታውስ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
  • ይሖዋ “የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2024
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 ሚያዝያ ገጽ 2-7

የጥናት ርዕስ 14

መዝሙር 8 ይሖዋ መጠጊያችን ነው

“የምታገለግሉትን . . . ምረጡ”

“እኔና ቤተሰቤ . . . ይሖዋን እናገለግላለን።”—ኢያሱ 24:15

ዓላማ

ይህ ርዕስ ይሖዋን ለማገልገል የመረጥንባቸውን ምክንያቶች ያስታውሰናል።

1. እውነተኛ ደስታ ማግኘት ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ? (ኢሳይያስ 48:17, 18)

የሰማዩ አባታችን በጣም ይወደናል፤ እንዲሁም አሁንም ሆነ ወደፊት አስደሳች ሕይወት እንድንመራ ይፈልጋል። (መክ. 3:12, 13) አምላካችን ሲፈጥረን አንዳንድ አስደናቂ ችሎታዎችን የሰጠን ቢሆንም ራሳችንን በተሳካ ሁኔታ የመምራት ወይም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በራሳችን የመወሰን ችሎታ አልሰጠንም። (መክ. 8:9፤ ኤር. 10:23) እውነተኛ ደስታ ማግኘት የምንችለው እሱን ስናገለግለውና በመሥፈርቶቹ ስንመራ ብቻ እንደሆነ ያውቃል።—ኢሳይያስ 48:17, 18⁠ን አንብብ።

2. ሰይጣን ምን ብለን እንድናምን ይፈልጋል? ይሖዋስ ለዚህ የሐሰት ክስ ምላሽ ለመስጠት ሲል ምን አደረገ?

2 ሰይጣን ደስተኛ ለመሆን ይሖዋ እንደማያስፈልገን እንዲሁም ሰዎች በተሳካ ሁኔታ ራሳቸውን መምራት እንደሚችሉ እንድናምን ይፈልጋል። (ዘፍ. 3:4, 5) ይሖዋ ለዚህ የሐሰት ክስ ምላሽ ለመስጠት ሲል ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ ያህል ራሳቸውን በራሳቸው እንዲመሩ ፈቀደላቸው። የሰዎች አገዛዝ ያስከተለውን መራራ ውጤት ለማየት ብዙ ጥረት አይጠይቅም። በሌላ በኩል ደግሞ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን በማገልገላቸው አርኪ ሕይወት መምራት የቻሉ በርካታ ወንዶችና ሴቶችን ታሪክ ይዟል። ከእነሱ መካከል ዋነኛው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ ይሖዋን ለማገልገል የመረጠው ለምን እንደሆነ እንመልከት። ከዚያም የሰማዩ አባታችን አምልኳችን የሚገባው ለምን እንደሆነ እናያለን። በመጨረሻም፣ ይሖዋን ለማገልገል እንድንመርጥ የሚያነሳሱንን አንዳንድ ምክንያቶች እንከልሳለን።

ኢየሱስ ይሖዋን ለማገልገል የመረጠው ለምንድን ነው?

3. ኢየሱስ ምን ፈተና ቀርቦለት ነበር? እሱስ ምን ምርጫ አደረገ?

3 ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ማንን እንደሚያገለግል መምረጥ ነበረበት። ኢየሱስ ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ ሰይጣን ፈትኖት ነበር፤ አንድ ጊዜ ተደፍቶ ካመለከው የዓለምን መንግሥታት በሙሉ እንደሚሰጠው ነገረው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ! ‘ይሖዋ አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’ ተብሎ ተጽፏልና።” (ማቴ. 4:8-10) ኢየሱስ ይህን ምርጫ ያደረገው ለምንድን ነው? አንዳንዶቹን ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።

4-5. ኢየሱስ ይሖዋን ለማገልገል እንዲመርጥ ያነሳሱት አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

4 ኢየሱስ ይሖዋን ለማገልገል የመረጠበት ዋነኛው ምክንያት ፍቅር ነው፤ ኢየሱስ ለአባቱ ጥልቅና የማይናወጥ ፍቅር አለው። (ዮሐ. 14:31) በተጨማሪም ኢየሱስ ይሖዋን የሚያገለግለው እንዲህ ማድረግ ተገቢ ስለሆነ ነው። (ዮሐ. 8:28, 29፤ ራእይ 4:11) ይሖዋ የሕይወት ምንጭ እንዲሁም እምነት የሚጣልበትና ለጋስ አምላክ እንደሆነ ያውቃል። (መዝ. 33:4፤ 36:9፤ ያዕ. 1:17) ይሖዋ የነገረው ነገር ሁሉ እውነት ነው፤ እንዲሁም ያለውን ነገር ሁሉ ያገኘው ከእሱ ነው። (ዮሐ. 1:14) በአንጻሩ ግን ሰይጣን የሞት መንስኤ ነው። ስግብግብ፣ ራስ ወዳድና ውሸታም ነው። (ዮሐ. 8:44) ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ስለሚያውቅ እንደ ሰይጣን በይሖዋ ላይ የማመፅ ሐሳብ እንኳ ወደ አእምሮው መጥቶ አያውቅም።—ፊልጵ. 2:5-8

5 ኢየሱስ ይሖዋን ለማገልገል የመረጠበት ሌላው ምክንያት በታማኝነት የሚያቀርበው አገልግሎት የሚያስገኘውን ውጤት አሻግሮ በመመልከቱ ነው። (ዕብ. 12:2) ታማኝነቱን ከጠበቀ የአባቱን ስም እንደሚያስቀድስ እንዲሁም ዲያብሎስ ያስከተለውን መከራ በሙሉ እንደሚያስወግድ ያውቅ ነበር።

ይሖዋ አምልኳችን የሚገባው ለምንድን ነው?

6-7. በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ይሖዋን የማያገለግሉት ለምንድን ነው? ይሁንና ይሖዋ አምልኳችን የሚገባው ለምንድን ነው?

6 በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ስለ ይሖዋ ማራኪ ባሕርያት እንዲሁም ለእነሱ ስላደረገላቸው ነገር ስለማያውቁ እሱን አያገለግሉም። ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴንስ የሰበከላቸው ሰዎች ሁኔታም ተመሳሳይ ነበር።—ሥራ 17:19, 20, 30, 34

7 ጳውሎስ “ሕይወትንና እስትንፋስንም ሆነ ማንኛውንም ነገር ለሰው ሁሉ የሚሰጠው” እውነተኛው አምላክ እንደሆነ ለአድማጮቹ አብራራላቸው። አክሎም “ሕይወት ያገኘነው፣ የምንንቀሳቀሰውና የምንኖረው በእሱ ነው” አላቸው። አምላክ ፈጣሪ ነው፤ “የሰውን ወገኖች በሙሉ ከአንድ ሰው” ፈጥሯል፤ በመሆኑም አምልኳችን ይገባዋል።—ሥራ 17:25, 26, 28

8. ይሖዋ ፈጽሞ የማያደርገው ነገር ምንድን ነው? አብራራ።

8 ይሖዋ ፈጣሪና የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እንደመሆኑ መጠን ሰዎች እንዲያገለግሉት ማስገደድ ይችል ነበር። ሆኖም ይሖዋ ፈጽሞ እንዲህ አያደርግም። ከዚህ ይልቅ እሱ መኖሩን እንዲሁም እያንዳንዳችንን በጣም እንደሚወደን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ሰጥቶናል። በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ለዘላለም ወዳጆቹ ሆነው እንዲኖሩ ይፈልጋል። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ለዚህም ሲባል ይሖዋ ሌሎችን ስለ ዓላማዎቹ እንድናስተምር እንዲሁም ለሰው ልጆች ስላዘጋጀው በረከት እንድንናገር አሠልጥኖናል። (ማቴ. 10:11-13፤ 28:19, 20) በጉባኤ አደራጅቶናል፤ የሚንከባከቡን አፍቃሪ የበላይ ተመልካቾችም ሰጥቶናል።—ሥራ 20:28

9. የይሖዋ ፍቅር የታየው እንዴት ነው?

9 ይሖዋ የእሱን መኖር መቀበል የማይፈልጉ ሰዎችን የሚይዝበት መንገድ ታላቅ ፍቅሩን ያሳያል። እስቲ አስበው፦ በታሪክ ዘመናት ሁሉ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ ራሳቸው ባወጡት መሥፈርት ለመመራት መርጠዋል። ያም ቢሆን ይሖዋ በሕይወት ለመቀጠልና ለመደሰት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በደግነት ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 5:44, 45፤ ሥራ 14:16, 17) ከወዳጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በፍቅር የመኖር፣ ልጆች የመውለድ እንዲሁም የሥራቸውን ውጤት የማጣጣም ችሎታ ሰጥቷቸዋል። (መዝ. 127:3፤ መክ. 2:24) የሰማዩ አባታችን ሁሉንም ሰዎች እንደሚወድ ማስረጃው በግልጽ ያሳያል። (ዘፀ. 34:6) ከዚህ በመቀጠል ይሖዋን ለማገልገል የምንመርጥባቸውን አንዳንድ ምክንያቶች ለማስታወስና እሱም በምላሹ የሚሰጠንን አንዳንድ በረከቶች ለማየት እንሞክራለን።

ይሖዋን ለማገልገል የምንመርጠው ለምንድን ነው?

10. (ሀ) ይሖዋን የምናገለግልበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? (ማቴዎስ 22:37) (ለ) የይሖዋ ትዕግሥት ምን ጥቅም አስገኝቶልሃል? (መዝሙር 103:13, 14)

10 እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ይሖዋን የምናገለግልበት ዋነኛ ምክንያት እሱን በጣም ስለምንወደው ነው። (ማቴዎስ 22:37⁠ን አንብብ።) ስለ ይሖዋ ባሕርያት ስንማር ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ እንነሳሳለን። ይሖዋ የሚያሳየንን ትዕግሥት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እስራኤላውያን ባመፁበት ወቅት “እባካችሁ፣ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ” በማለት ተማጽኗቸዋል። (ኤር. 18:11) ይሖዋ ፍጽምና እንደሚጎድለንና አፈር እንደሆንን ያስታውሳል። (መዝሙር 103:13, 14⁠ን አንብብ።) በይሖዋ ትዕግሥትና በሌሎቹ ማራኪ ባሕርያቱ ላይ ስታሰላስል እሱን ለዘላለም ለማገልገል አትነሳሳም?

11. የሰማዩ አባታችንን ለማገልገል እንድንመርጥ የሚያነሳሱን ሌሎች ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

11 ይሖዋን ለማገልገል የሚያነሳሳን ሌላው ምክንያት እንዲህ ማድረግ ተገቢ ስለሆነ ነው። (ማቴ. 4:10) በተጨማሪም በታማኝነት የምናቀርበው አገልግሎት ምን ውጤት እንደሚያስገኝ እናውቃለን። ታማኝነታችንን ስንጠብቅ የይሖዋ ስም እንዲቀደስ አስተዋጽኦ እናበረክታለን፤ ዲያብሎስ ውሸታም መሆኑን እናረጋግጣለን፤ እንዲሁም የአባታችንን ልብ እናስደስታለን። ከዚህም ሌላ፣ በዛሬው ጊዜ ይሖዋን ለማገልገል ከመረጥን እሱን ለዘላለም የማገልገል አጋጣሚ ይከፈትልናል።—ዮሐ. 17:3

12-13. ከጄንና ከፓም ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?

12 ገና ልጆች ብንሆንም እንኳ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ማዳበር እንችላለን፤ ይህ ፍቅር ደግሞ ዕድሜያችን ሲጨምር እያደገ ይሄዳል። ጄን እና ፓምa የተባሉ ሁለት እህትማማቾችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምሩ ጄን 11 ዓመቷ፣ ፓም ደግሞ 10 ዓመቷ ነበር። ወላጆቻቸው የማጥናት ፍላጎት ባይኖራቸውም ጄንና ፓም በየሳምንቱ ከቤተሰባቸው ጋር ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸውን እስከቀጠሉ ድረስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንዲያጠኑ ተፈቀደላቸው። ጄን እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያስተማሩኝ ነገር እኩዮቼ ዕፅ እንድወስድና የሥነ ምግባር ብልግና እንድፈጽም የሚያሳድሩብኝን ተጽዕኖ ለመቋቋም ረድቶኛል።”

13 በአሥራዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ ሲደርሱ ሁለቱም አስፋፊዎች ሆኑ። ከጊዜ በኋላም በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን እየተንከባከቡ በአቅኚነት ማገልገል ጀመሩ። ጄን ባለፉት ዓመታት ይሖዋ ስላደረገላቸው ነገር ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ወዳጆቹን በታማኝነት እንደሚንከባከባቸው እንዲሁም 2 ጢሞቴዎስ 2:19 እንደሚለው ‘ይሖዋ የእሱ የሆኑትን እንደሚያውቅ’ በራሴ ሕይወት ተመልክቻለሁ።” በእርግጥም ይሖዋ እሱን ለመውደድና ለማገልገል የሚመርጡ ሰዎችን ይንከባከባቸዋል!

14. ንግግራችንና ድርጊታችን የይሖዋ ስም ከነቀፋ ነፃ እንዲሆን አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

14 የይሖዋ ስም ከተሰነዘረበት ነቀፋ ሁሉ ነፃ እንዲሆን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንፈልጋለን። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ደግ፣ ለጋስና ይቅር ባይ የሆነ አንድ የቅርብ ጓደኛ አለህ እንበል። አንድ ቀን ግን የሆነ ሰው ጓደኛህ ጨካኝና ውሸታም እንደሆነ ሲናገር ብትሰማ ምን ታደርጋለህ? ለጓደኛህ ጥብቅና ትቆምለታለህ። በተመሳሳይም ሰይጣንና በእሱ ተጽዕኖ ሥር ያሉ ሰዎች ስለ ይሖዋ ውሸት በማስፋፋት ስሙን ሲያጠፉ ስለ እሱ እውነቱን በመናገር ለስሙ ጥብቅና እንቆማለን። (መዝ. 34:1፤ ኢሳ. 43:10) ይሖዋን በሙሉ ነፍሳችን ማገልገል እንደምንፈልግ በንግግራችንም ሆነ በድርጊታችን እናሳያለን።

1. አንዲት ሴት ትልቅ ስብሰባ በሚደረግበት አዳራሽ ደጅ ላይ ተቃውሞ የሚያሰሙ ከሃዲዎችን ትመለከታለች። 2.በኋላም ሴትየዋ የጋሪ ምሥክርነት እየሰጡ ካሉ ባልና ሚስት ጋር ትነጋገራለች።

ለይሖዋ ስም ጥብቅና ትቆማለህ? (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)b


15. ሐዋርያው ጳውሎስ በግቦቹ ላይ ማስተካከያ በማድረጉ የተጠቀመው እንዴት ነው? (ፊልጵስዩስ 3:7, 8)

15 ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ለማገልገል ወይም ለእሱ የምናቀርበውን አገልግሎት ለማሳደግ ስንል በግቦቻችን ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ፈቃደኞች ነን። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቶስን ለመከተልና ይሖዋን ለማገልገል ሲል በማኅበረሰቡ ውስጥ የነበረውን ትልቅ ቦታ ለመተው ፈቃደኛ ሆኗል። (ገላ. 1:14) በዚህም የተነሳ አርኪ ሕይወት መምራት እንዲሁም ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመግዛት አጋጣሚ ማግኘት ችሏል። ይሖዋን ለማገልገል ባደረገው ውሳኔ ፈጽሞ አልተቆጨም፤ እኛም ብንሆን አንቆጭም።—ፊልጵስዩስ 3:7, 8⁠ን አንብብ።

16. ከጁልያ ተሞክሮ ምን እንማራለን? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

16 በሕይወታችን ውስጥ ለይሖዋ አገልግሎት ቅድሚያ ከሰጠን አሁንም ሆነ ወደፊት አርኪ ሕይወት መምራት እንችላለን። ጁልያ የተባለችን እህት ተሞክሮ እንመልከት። ጁልያ ከልጅነቷ አንስቶ የቤተ ክርስቲያን ዘማሪ ነበረች። በጣም ጎበዝ ስለነበረች የኦፔራ ዘፋኝ ለመሆን ሥልጠና መውሰድ ጀመረች። ብዙም ሳይቆይ ጁልያ ዝና ያተረፈች ከመሆኑም ሌላ ስመ ጥር በሆኑ የሙዚቃ አዳራሾች ውስጥ ትዘፍን ነበር። በአንድ ታዋቂ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ውስጥ እየተማረች ሳለ አብሯት የሚማር አንድ ሰው ስለ አምላክ ያወያያት ጀመር፤ የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነም ነገራት። ከዚያም ጁልያ በሳምንት ሁለት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ውሎ አድሮ በሙዚቃ ሙያዋ ከመቀጠል ይልቅ በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት ለመምራት ወሰነች። ይህን ውሳኔ ማድረግ ለእሷ ቀላል አልነበረም። እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ሰዎች ‘ተሰጥኦሽን እያባከንሽው ነው’ ብለውኝ ነበር። እኔ ግን በመላው ሕይወቴ ይሖዋን ለማገልገል ፈልጌ ነበር።” ታዲያ ከ30 ዓመት በፊት ስላደረገችው ስለዚህ ውሳኔ አሁን ላይ ምን ይሰማታል? እንዲህ ብላለች፦ “የአእምሮ ሰላም አለኝ። እንዲሁም ይሖዋ ወደፊት የልቤን ፍላጎት በሙሉ እንደሚያሟላልኝ እተማመናለሁ።”—መዝ. 145:16

ሥዕሎች፦ ጁልያ ያደረገችውን ምርጫ የሚያሳይ ትወና። 1. መድረክ ላይ ቆማ በአድማጮች ፊት ስትዘፍን። 2. በጉባኤ ስብሰባ ላይ ከባለቤቷ ጋር ስትዘምር።

ለይሖዋ አገልግሎት ቅድሚያ ከሰጠን ከሁሉ ይበልጥ አርኪ የሆነ ሕይወት መምራት እንችላለን (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)c


ይሖዋን ማገልገልህን ቀጥል

17. የምንኖረው መጨረሻው በጣም በቀረበበት ጊዜ ላይ መሆኑ ይሖዋን ለማገልገል ለመረጡና እስካሁን ላልመረጡ ሰዎች ምን ትርጉም አለው?

17 የምንኖረው መጨረሻው በጣም በቀረበበት ጊዜ ላይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ምክንያቱም ‘ለጥቂት ጊዜ ነው’ እንጂ ‘የሚመጣው እሱ ይመጣል፤ ደግሞም አይዘገይም።’” (ዕብ. 10:37) ይህ ምን ትርጉም አለው? በአንድ በኩል፣ በአሁኑ ወቅት ይሖዋን እያገለገሉ ያልሆኑ ሰዎች እሱን ለማገልገል መምረጥ የሚችሉበት ጊዜ አጭር ነው፤ ስለዚህ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለባቸው። (1 ቆሮ. 7:29) በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋን ለማገልገል መርጠን ከሆነ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም ቢኖርብንም ፈተናዎቹ የሚቆዩት “ለጥቂት ጊዜ” ብቻ እንደሆነ እናውቃለን።

18. ኢየሱስና ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይፈልጋሉ?

18 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ያበረታታቸው እሱን መከተል እንዲጀምሩ ብቻ ሳይሆን ያለማቋረጥ እንዲከተሉት ጭምር ነው። (ማቴ. 16:24) እንግዲያው ይሖዋን ለዓመታት ስናገለግል ቆይተን ከሆነ እሱን ማገልገላችንን ላለማቆም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እሱን ለማገልገል ካደረግነው ውሳኔ ጋር ተስማምተን ለመኖር ብርቱ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። እንዲህ ማድረግ ቀላል ላይሆን ቢችልም በአሁኑ ጊዜም እንኳ ብዙ በረከትና እርካታ ያስገኝልናል!—መዝ. 35:27

19. ከጂን ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?

19 አንዳንዶች ይሖዋን ማገልገል ብዙ መሥዋዕትነት እንደሚጠይቅ ይሰማቸዋል። ወጣት ከሆንክ፣ ይሖዋን በማገልገልህ የቀረብህ ነገር እንዳለ ይሰማሃል? ጂን የተባለ ወጣት ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክር መሆኔ ነፃነቴን እንዳሳጣኝ ተሰምቶኝ ነበር። ብዙዎቹ ጓደኞቼ ጭፈራ ቤት በመሄድ፣ የፍቅር ጓደኛ በመያዝ ወይም ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸውን የቪዲዮ ጌሞች በመጫወት ሲዝናኑ እኔ ግን በስብሰባና በአገልግሎት ጊዜዬን ለማሳለፍ እንደተገደድኩ ተሰማኝ።” ታዲያ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በጂን ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደረበት? እንዲህ ብሏል፦ “ሁለት ዓይነት ሕይወት መምራት ጀመርኩ። መጀመሪያ ላይ ይህ አስደሳች ሆኖልኝ ነበር። ሆኖም ዘላቂ ደስታ አላስገኘልኝም። ችላ ስላልኳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ማሰብ ጀመርኩ። ከዚያም በሙሉ ልቤ ይሖዋን ለማገልገል ወሰንኩ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ይሖዋ ጸሎቶቼን በሙሉ እንደመለሰልኝ ይሰማኛል።”

20. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

20 አንድ መዝሙራዊ እንዲህ ሲል ለይሖዋ ዘምሯል፦ “በቅጥር ግቢዎችህ ይኖር ዘንድ የመረጥከውና ያቀረብከው ሰው ደስተኛ ነው።” (መዝ. 65:4) እንግዲያው እንደ ኢያሱ ዓይነት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፦ “እኔና ቤተሰቤ . . . ይሖዋን እናገለግላለን።”—ኢያሱ 24:15

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ኢየሱስ ይሖዋን ለማገልገል የመረጠው ለምንድን ነው?

  • ይሖዋ አምልኳችን የሚገባው ለምንድን ነው?

  • ይሖዋን ለማገልገል የመረጥከው ለምንድን ነው?

መዝሙር 28 የይሖዋ ወዳጅ መሆን

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት ሴት ትልቅ ስብሰባ ከሚደረግበት አዳራሽ ውጭ ተቃዋሚዎቻችን የሚናገሩትን ነገር ከሰማች በኋላ ወደ አንድ የጽሑፍ ጋሪ ቀርባ እውነትን ትሰማለች።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ ጁልያ በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ሕይወት ለመምራት ስትል ያደረገችውን ምርጫ የሚያሳይ ትወና።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ