ከዓለም ጋር ባላችሁ ግንኙነት ረገድ በጥበብ ተመላለሱ
“ዘመኑን እየዋጃችሁ፣ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ።”—ቆላስይስ 4:5
1. የጥንት ክርስቲያኖች ምን ነገሮች ያጋጥሟቸው ነበር? ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ ለነበረው ጉባኤ ምን ምክር ሰጠ?
በሮም ግዛት ውስጥ ባሉት ከተሞች ውስጥ ይኖሩ የነበሩት የጥንት ክርስቲያኖች የጣዖት አምልኮ፣ የሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ደስታ እንዲሁም የአረማውያን ወግና ልማድ ዘወትር ያጋጥማቸው ነበር። በማዕከላዊ ምዕራብ በትንሿ እስያ በምትገኘው በቆላስይስ ከተማ ይኖሩ የነበሩት ክርስቲያኖች የእናት አምላክ አምልኮና የፍርግያ ተወላጆች መናፍስታዊ ድርጊት፣ የግሪክ መጤዎች አረማዊ ፍልስፍናና ይሁዳ በተባለው የሮም ቀኝ ግዛት ውስጥ ይኖሩ የነበሩት አይሁዶች የይሁዲነት እምነት ያጋጥማቸው እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። እንደዚህ በመሰሉት “በውጭ ባሉት” ሰዎች ዘንድ ‘በጥበብ መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉ’ ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቲያን ጉባኤን መክሯል።—ቆላስይስ 4:5
2. በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ በጥበብ መመላለስ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
2 ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች ተመሳሳይ የሆኑና እንዲያውም ከዚያ የከፋ መጥፎ ድርጊቶች ያጋጥሟቸዋል። ስለዚህ እነሱም ከእውነተኛው ክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ካሉት ሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ በጥበብ መመላለስ ያስፈልጋቸዋል። በሃይማኖታዊና በፖለቲካዊ ድርጅቶች እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ይቃወማሉ። ከእነዚህ አንዳንዶቹ የሚቃወሙት በቀጥታ በማጥቃት ወይም በአሽሙር እየተናገሩ የይሖዋ ምሥክሮችን መልካም ስም ለማጉደፍ በመሞከርና በእነሱ ላይ መሠረተ ቢስ ጥላቻን በመቀስቀስ ነው። የጥንት ክርስቲያኖች እንደ አንድ አክራሪና እንዲሁም አደገኛ የሆኑ “ኑፋቄ” ያላግባብ ይታዩ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም የይሖዋ ምሥክሮች የጥላቻና ካለማወቅ ለሚሰነዘሩ ነቀፋዎች ኢላማ ናቸው።—የሐዋርያት ሥራ 24:14፤ 1 ጴጥሮስ 4:4
መሠረተ ቢስ ጥላቻን ማርገብ
3, 4. (ሀ) እውነተኛ ክርስቲያኖች መቼም ቢሆን ዓለም የማይወዳቸው ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ ምን ለማድረግ መሞከር ይኖርብናል? (ለ) አንዲት ደራሲ በናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ስለነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው ጽፈዋል?
3 እውነተኛ ክርስቲያኖች ሐዋርያው ዮሐንስ በጻፈው መሠረት ይህ ‘በክፉው የተያዘው’ ዓለም ይወደናል ብለው አይጠብቁም። (1 ዮሐንስ 5:19) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች አሳምነው ወደ ይሖዋና ወደ ንፁህ አምልኮው ለማምጣት እንዲጥሩ ያበረታታል። ይህንን የምናደርገው በቀጥታ በመመስከርና በጸባያችን ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦“ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፣ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፣ በሚጐበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።”—1 ጴጥሮስ 2:12
4 ሲልቪያ ሳልቨሰን የተባሉት አንዲት ደራሲ ፎር ጊቭ— በት ዱ ኖት ፎርጌት በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በአንድ የናዚ የማጎሪያ ካምፕ አብረዋቸው ታስረው ስለነበሩት ሴት ምሥክሮች እንዲህ ብለዋል፦ “ኬትና ማርጋሬታ የሚባሉትና ሌሎች ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በጣም ረድተውኛል፤ በእምነታቸው ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ በሆኑ ጉዳዮች ረድተውኛል። ለቁስላችን የሚሆን ንጹህ ጨርቅ መጀመሪያ የሰጡን እነሱ ናቸው።. . . በአጭሩ ለእኛ መልካም በሚመኙልንና የወዳጅነት ስሜታቸው በድርጊታቸው በሚያሳዩን ሰዎች መካከል ነበርን።” “በውጭ ካሉት ሰዎች” የተሰጠ እንዴት ያለ ግሩም ምስክርነት ነው!
5, 6. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ ክርስቶስ ምን ሥራ እንዲከናወን በማድረግ ላይ ነው? ምንስ መዘንጋት አይኖርብንም? (ለ) በዓለም ላሉት ሰዎች ምን ዝንባሌ ማሳየት ይኖርብናል? ለምንስ?
5 በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ በጥበብ በመመላለስ ሰዎች በእኛ ላይ ያላቸው ተገቢ ያልሆነ ጥላቻ ለማርገብ ብዙ አስተዋጽኦ ልናደርግ እንችላለን። እውነት ነው፤ እየገዛ ያለው ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እረኛም በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ” ሰዎችን እየለየ ባለበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። (ማቴዎስ 25:32) ይሁን እንጂ ዳኛው ክርስቶስ መሆኑን ፈጽሞ አትዘንጉ፤ እነማን “በጎች” እነማን “ፍየሎች” የሚወስነው እሱ ነው።— ዮሐንስ 5:22
6 ይህም የይሖዋ ድርጅት ክፍል ላልሆኑት ሰዎች ያለንን አመለካከት ሊነካው ይገባል። ስለ እነሱ ስናስብ የሚታየን ዓለማዊ መሆናቸው ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ቢሆንም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ” የወደደው የሰው ዘር የዓለም ክፍል ናቸው። (ዮሐንስ 3:16) አለቦታችን ገብተን ሰዎች ፍየሎች ናችው ብለን ከመፍረድ ይልቅ በጎች ሊሆኑ ይችላሉ ብለን ማሰብ የተሻለ ነው። በአንድ ወቅት የዓመፅ እርምጃ እስከመውሰድ የሚያደርስ ከፍተኛ የእውነት ተቃውሞ የነበራቸው ሰዎች አሁን ራሳቸውን የወሰኑ ምሥክሮች ሆነዋል። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ በቀጥታ የተደረገላቸው ምሥክርነት ከመቀበላቸው በፊት ወደ እውነት ሊማረኩ የቻሉት በተደረገላቸው የደግነት ሥራ ነው። ለምሳሌ ያህል በገጽ 18 ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።
በቅንዓት የሚሰብኩ እንጂ ወራሪ ኃይል አይደሉም
7. የሮማው ጳጳስ ምን ትችት ሰነዘሩ? ነገር ግን ምን ጥያቄ ልንጠይቅ እንችላለን?
7 ፖፕ ጆን ፖል ሁለተኛ የሌላ ሃይማኖት ቡድኖችን በጠቅላላ ተችተው ነበር፣ በተለይ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮችን ሲተቹ እንዲህ አሉ፦ “አንዳንዶች ተከታዮችን ለማፍራት በሚያሳዩት ከወረራ ያላነሰ ቅንዓት፤ ይኸውም ከቤት ቤት በመሄድ ወይም መንገደኛውን በመንገድ ዳር እያስቆሙ በማነጋገር የሚያደርጉት መሯሯጥ የሐዋርያዊውንና የሚስዮናዊነትን የጋለ ስሜት ለመኮረጅ የተደረገ የአስመሳይ ድርጊት ነው።” የእኛ የምስክርነት ሥራ “የሐዋርያዊውንና የሚስዮናዊነትን የጋለ ስሜት ለመኮረጅ የተደረገ የአስመሳይ ድርጊት” ከሆነ ታዲያ እውነተኛው የወንጌላዊነት ቅንዓት ያለው የት ነው? በካቶሊክ ወይም በፕሮቴስታንት ወይም ደግሞ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ላይ እንደማይገኝ የተረጋገጠ ነው።
8. ከቤት ወደ ቤት የምናደርገውን አገልግሎት እንዴት ማከናወን ይኖርብናል? ምን ውጤትስ ተስፋ በማድረግ?
8 ሆኖም ወረራ ያካሄዱብናል የሚለው ክስ ሐሰት መሆኑን ለማሳየት ሰዎችን በምንቀርብበት ጊዜ ሁሉ ደግ፣ ሰው አክባሪዎችና ትሑቶች መሆን ይኖርብናል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ፦“ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ሥራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 3:13) ሐዋርያው ጳውሎስም ‘የማንጨነቅ እንድንሆን’ በጥሞና መክሮናል። (ቲቶ 3፡2) ለምሳሌ ያህል የምንመሰክርለትን ሰው እምነት በቀጥታ ከማውገዝ ይልቅ የሚሰጠውን ወይም የምትሰጠውን ሐሳብ ለመስማት ለምን ልባዊ ፍላጎት አናሳይም? ከዚያም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን የምሥራች ለሰውዬው ንገሩት። ሌላ እምነት ያላቸውን ሰዎች ቀና በሆነ መንገድ በመቅረብና ተገቢ አክብሮት በማሳየት በተሻለ ሁኔታ ለመስማት ዝግጁዎች እንዲሆኑና ምናልባትም የመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት ዋጋማነት እንዲገነዘቡት እንረዳቸዋልን። በዚህም የተነሳ እንዳንዶች ‘እግዚአብሔርን ማክበር ሊጀምሩ’ ይችሉ ይሆናል።—1 ጴጥ. 2:12
9. ሐዋርያው ጳውሎስ (ሀ) በቆላስይስ 4፡5 (ለ) ቆላስይስ 4፡6 ላይ የሰጠውን ምክር እንዴት በሥራ ላይ ማዋል እንችላለን?
9 ሐዋርያው ጳውሎስ “ዘመኑን እየዋጃችሁ፣ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ” ሲል መክሯል። (ቆላስይስ 4:5 አዓት) ጄ ቢ ላይትፉት ዘመኑን እየዋጃቹ የሚለውን አባባል በማብራራት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የአምላክን ዓላማ የሚያስፋፉ ነገር ሳትናገሩ እና ሳታደርጉ ምንም አጋጣሚ አይለፋችሁ።” (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን) አዎ፣ በቃልም ሆነ በተግባር ለመመስከር አመቺ የሆነው ጊዜ ዝግጁዎች መሆን አለበት። እንዲህ ዓይነቱ ጥበብ ቤታቸው ሄዶ ለማነጋገር አመቺ የሆነውን ጊዜ መምረጥንም ይጨምራል። መልእክታችን ተቀባይነት ካላገኘ ይህ ሊሆን የቻለው ሰዎች መልእክቱን ስላላደነቁት ነው ወይም አመቺ ባልሆን ሰዓት ሄደን ስላነጋገርናቸው ነው? በተጨማሪም ጳውሎስ “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደ ተቀመመ፣ በጸጋ ይሁን” ሲል ጽፏል። (ቆላስይስ 4:6) ይህም ቀደም ብሎ መዘጋጀትንና ለጎረቤት እውነተኛ ፍቅርን መያዝን ይጠይቃል። የመንግሥቱን መልእክት ምንጊዜም በጸጋ እናቅረብ።
ሰው አክባሪዎችና “ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ”
10. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ በቀርጤስ ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች ምን ምክር ሰጠ? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች የጳውሎስን ምክር በመከተል ረገድ ምሳሌ የሆኑት እንዴት ነው?
10 ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለንን አቋም ማላላት አንችልም። በሌላ በኩል ክርስቲያናዊ አቋም በማይነኩ ጉዳዮች ላይ አላስፈላጊ ክርክር ማንሳት አንፈልግም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “[በቀርጤስ ያሉ ክርስቲያኖች] ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ፣ ማንንም የማይሰድቡ፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ አሳስባቸው።” (ቲቶ 3:1, 2) የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ኢ ኤፍ ስኮት ይህን ሃሳብ በተመለከተ እንዲህ ብለው ጽፈዋል፦ “ክርስቲያኖች ባለሥልጣንን ማክበር ብቻ ሳይሆን ለመልካም ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ መሆን አለባቸው። ይህም. . . ማለት ክርስቲያኖች አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሰዎችን ለመርዳት ቀድመው ከሚደርሱት ሰዎች መካከል መሆን ይኖርባቸዋል። ብዙ ጊዜ እሳት አደጋ የሚደርስበት እንዲሁም የተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚከሰቱበትና ጥሩ የሆኑ ዜጎች ሁሉ ጎረቤቶቻቸውን ለመርዳት የሚሯሯጡበት ጊዜ ይኖር ይሆናል።” በዓለም ዙሪያ አደጋዎች የደረሱባቸውና የእርዳታ የተግባር ከሚያከናውኑት መካከል የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑባቸው ጊዜያት አሉ። የይሖዋ ምሥክሮች የረዱት ወንድሞቻቸውን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰዎችንም ጭምር ነው።
11, 12. (ሀ) ክርስቲያኖች ለባለ ሥልጣኖች ምን ፀባይ ማሳየት ይኖርባቸዋል? (ለ) የመንግሥት አዳራሾችን መሥራትን በተመለከተ ለባለ ሥልጣኖች መገዛት ምን ማድረግን ይጨምራል?
11 ጳውሎስ ለቲቶ በጻፈው ደብዳቤ ውስጥ የሚገኘው ይኸው ሐሳብ ለባለ ሥልጣኖች አክብሮት የማሳየትን አስፈላጊነት አጥብቆ ይገልጻል። በገለልተኛ አቋማቸው ምክንያት በዳኛ ፊት የሚቀርቡ ወጣት ክርስቲያኖች በተለይም በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ በጥበብ ለመመላለስ አስተዋይ መሆን ይኖርባቸዋል። በአለባበሳቸው፣ በአቀራረባቸውና እንደዚህ ያሉትን ባለሥልጣናት በሚያነጋግሩበት ጊዜ የይሖዋን ሕዝቦች ስም ከፍ ሊያደርጉ ወይም ሊያዋርዱ ይችላሉ። ‘ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት’ እና የመከላከያ ሐሳባቸውን ጥልቅ አክብሮት በተሞላበት መልኩ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ሮም 13:1-7፤ 1 ጴጥሮስ 2:17፤ 3:15
12 “ባለሥልጣኖች” የሚለው አባባል በአካባቢው ያሉትን የመንግሥት ባለሥልጣኖች ይጨምራል። በአሁኑ ጊዜ ብዙ የመንግሥት አዳራሾች እየተሠሩ ስለሆነ በአካባቢው ከሚገኙት ባለሥልጣናት ጋር መገናኘት የማይቀር ነገር ነው። ሽማግሌዎች ብዙውን ጊዜ በወሬ ብቻ የሚጠሉን ባለሥልጣኖች ያጋጥሟቸዋል። ነገር ግን የጉባኤ ተወካዮች ከባለሥልጣናት ጋር ጥሩ ግንኙነት ሲመሠርቱና የከተማውን ፕላን ከሚቆጣጠረው መሥሪያ ቤት ጋር ሲተባበሩ ይህ ጥላቻ ሊወገድ የሚችል ሆኖ ተገኝቷል። ብዙውን ጊዜ ስለ ይሖዋ ምሥክሮችና ስለ መልእክታቸው ጥቂት ብቻ ያውቁ ለነበሩት ወይም ምንም ለማያውቁት ጥሩ ምሥክርነት ተሰጥቷል።
‘ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ’
13, 14. ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች ምን ምክር ሰጥቶ ነበር? እኛስ ይህን ምክር በውጭ ካሉት ሰዎች ጋር ባሉን ግንኙነቶች በሥራ ላይ ልናውለው የምንችለው እንዴት ነው?
13 ጳውሎስ በአረመኔዋ ሮም ይኖሩ ለነበሩት ክርስቲያኖች የሚከተለውን ምክር ሰጥቶ ነበር፦ “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቊጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፣ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።”—ሮም 12:17-21
14 እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን በውጭ ካሉ ሰዎች ጋር በምናደርጋቸው ግንኙነቶች ተቃዋሚዎች ማጋጠማቸው የማይቀር ነገር ነው። ተቃውሞውን በደግነት ድርጊት ለማሸነፍ መጣር የጥበብ መንገድ እንደሆነ ጳውሎስ ከላይ ባለው ምንባብ ላይ ገልጿል። ይህ የደግነት አድራጎት እንደ እሳት ፍም በመሆን ጥላቻውን ሊያከስመውና ለይሖዋ ሕዝቦች የደግነት ዝንባሌ እንዲኖር ሊያደርግ ይችላል፤ አልፎ ተርፎም ለምሥራቹ ፍላጎቱ እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ክፉው ነገር በመልካም ተሸነፈ ማለት ነው።
15. ክርስቲያኖች በውጭ ካሉት ሰዎች ጋር በጥበብ ለመመላለስ መጠንቀቅ የሚኖርባቸው በተለይ መቼ ነው?
15 አንደኛው የትዳር ጓደኛ እውነትን ባልተቀበለበት ቤት ውስጥ በተለይ በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ በጥበብ መመላለስ በጣም አስፈላጊ ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መጠበቅ የተሻሉ ባሎችን፣ የተሻሉ ሚስቶችን፣ የተሻሉ አባቶችን፣ የተሻሉ እናቶችን እንዲሁም ይበልጥ ታዛዥ የሆኑና በትምህርት ቤት ይበልጥ ጠንክረው የሚያጠኑ ልጆችን ያስገኛል። የማያምነው ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚያምነው ሰው ላይ ያላቸውን መልካም ውጤት ለማየት መቻል ይኖርበታል። በዚህ መንገድ አንዳንዶች ራሳቸውን በወሰኑ የቤተሰብ አባላት ‘ፀባይ ምክንያት ያለ ቃል ሊማረኩ ይችሉ ይሆናል።’ —1 ጴጥሮስ 3:1, 2
‘ለሰው ሁሉ መልካም ማድረግ’
16, 17. (ሀ) አምላክ በምን መሥዋዕቶች ይደሰታል? (ለ) ለወንድሞቻችን እንዲሁም በውጭ ላሉት ሰዎች “መልካም” ማድረግ የሚኖርብን እንዴት ነው?
16 ለጎረቤታችን ልናደርግለት የምንችለው ከሁሉ የሚበልጠው መልካም ነገር የሕይወትን መልዕክት ማድረስና በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከይሖዋ ጋር የሚታረቅበትን መንገድ ማስተማር ነው። (ሮም 5:8-11) ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምሥጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፣ በእርሱ [በክርስቶስ] እናቅርብለት።” (ዕብራውያን 13:15) ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና።” (ዕብራውያን 13:16) ለሕዝብ ከምናደርገው ስብከት በተጨማሪ “መልካም ማድረግን” መዘንጋት የለብንም። ይህም አምላክን ደስ ከሚያሰኘው ሊነጠል የማይችል አንደኛው ክፍል ነው።
17 እርግጥ ነው፣ ስሜታዊ፣ መንፈሳዊ፣ አካላዊ ወይም ቁሳዊ ችግር ላለባቸው ወንድሞቻችን መልካም እናደርጋለን። ጳውሎስ “እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ።” (ገላትያ 6:10፤ ያዕቆብ 2:15, 16) ሆኖም “ለሰው ሁሉ. . . መልካም እናድርግ” የሚሉትን ቃላት መዘንጋት አይኖርብንም። ለዘመድ፣ ለጎረቤት፣ ወይም ለሥራ ባልደረባ በደግነት አንድ ጥሩ ነገር ብናደርግለት በእኛ ላይ ያደረበትን መሠረተ ቢስ ጥላቻ ለማስወገድና የሰውዬውን ልብ ለእውነት እንዲከፈት በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሊያበረክት ይችላል።
18. (ሀ) ከምን አደጋ መራቅ ይኖርብናል? (ለ) ክርስቲያናዊ ጥሩነታችን ለሕዝብ ለምናደርገው የምሥክርነት ሥራ እንደ ድጋፍ አድርገን ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?
18 ለዚህ ሲባል ግን በውጭ ያሉትን ሰዎች የቅርብ ወዳጆቻችን ማድረግ አያስፈልገንም። እንዲህ ዓይነቱ ወዳጅነት ከፍተኛ አደጋ አለው። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ከዓለም ጋር ወዳጆች ለመሆን ዓላማ የለንም። (ያዕቆብ 4:4) ሆኖም ክርስቲያናዊ ጥሩነታችን ለስብከታችን ድጋፍ ሊሆነው ይችላል። በአንዳንድ አገሮች ሰዎችን እቤታቸው ማነጋገር ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። አንዳንድ የአፓርታማ ሕንፃዎች በመሣሪያ ስለሚጠበቁ ከነዋሪዎቹ ጋር ለመገናኘት አንችልም። በበለጸጉ አገሮች ስልክ አንዱ የመመስከሪያ መንገድ ነው። በአብዛኞቹ አገሮች ደግሞ መንገድ ላይ መመስከር ይቻላል። ነገር ግን በሁሉም አገሮች ቢሆን ሞቅ ያለ ስሜት ማሳየት፣ ትሑት፣ ደግና አሳቢ መሆን ሰዎች በእኛ ላይ ያላቸውን ጥላቻ ለማስወገድና ግሩም ምሥክርነት ለመስጠት አጋጣሚዎችን ይከፍታል።
የተቃዋሚዎችን አፍ ማዘጋት
19. (ሀ) ዋናው ዓላማችን ሰዎችን ማስደሰት ስላልሆነ ምን ልንጠብቅ እንችላለን? (ለ) የዳንኤል ምሳሌ ለመከተልና የጴጥሮስን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል መጣር የሚኖርብን እንዴት ነው?
19 የይሖዋ ምሥክሮች ዋና ዓላማ ሰዎችን ማስደሰት አይደለም፣ እንዲሁም ሰውን አይፈሩም። (ምሳሌ 29:25፤ ኤፌሶን 6:6) ምንም እንኳ በወቅቱ ግብር በመክፈልና ጥሩ ዜጎች በመሆን ምሳሌ ለመሆን ጥረት ቢያደርጉም ተቃዋሚዎች ስማቸውን እንደሚያክፋፉና እንደሚያንቋሽሻቸው አሳምረው ያውቃሉ። (1 ጴጥሮስ 3:16) ይህንን በማወቃቸው ጠላቶቹ በእሱ ላይ የሚከተለውን ያሉበትን ዳንኤልን ለመምሰል ይጥራሉ፦ “ከአምላኩ ሕግ በቀር በዚህ በዳንኤል ላይ ሌላ ሰበብ አናገኝበትም አሉ።” (ዳንኤል 6:5) ሰዎችን ለማስደሰት ስንል በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ያለንን አቋም በፍጹም አናላላም። በሌላ በኩል ሰማዕት ለመሆን ፍላጎት አድሮብን የምናደርገው ነገር የለም። ሰላማውያን ሆነን ለመኖርና ቀጥሎ ያለውን ሐዋርያዊ ምክር ለመከተል እንጥራለን፦ “በጎ እያደረጋችሁ፣ የማያውቁትን ሞኞች ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና።”— (1 ጴጥሮስ 2:15)
20. (ሀ) ስለ ምን ነገር ጥርጥር የለንም? ኢየሱስ ምን ማበረታቻ ሰጥቶናል? (ለ) በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ በጥበብ መመላለሳችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
20 የያዝነው ከዓለም የተለየ አቋም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚስማማ ምንም ጥርጥር የለንም። ይህንን አቋም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ታሪክም የሚደግፈው ነው። “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” በሚሉት የኢየሱስ ቃላት እንበረታታለን። (ዮሐንስ 16:33) ምንም ነገር አንፈራም። “በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው? ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፣ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፣ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት [በጥልቅ አክብሮት አዓት] ይሁን።” (1 ጴጥሮስ 3:13-15) እንዲህ ስናደርግ በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ በጥበብ መመላለሳችንን እንቀጥላለን።
ለክለሳ ያህል
□ የይሖዋ ምሥክሮች በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ በጥበብ መመላለስ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
□ እውነተኛ ክርስቲያኖች ዓለም መቼም ቢሆን ይወደናል ብለን ተስፋ ለማድረግ የማይችሉት ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ ምን ለማድረግ መሞከር ይኖርባቸዋል?
□ ለዓለም ሰዎች ያለን ዝንባሌ ምን መሆን ይኖርበታል? ለምንስ?
□ ለወንድሞቻችን ብቻ ሳይሆን በውጭ ላሉት ሰዎችም ጭምር “መልካም ማድረግ” የሚኖርብን ለምንድን ነው?
□ በውጭ ባሉት ሰዎች ዘንድ በጥበብ መመላለሳችን ለሕዝብ በምናደርገው የምሥክርነት ሥራ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኘው ሥዕል]
በስተግራ፦ በፈረንሳይ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከጎርፍ ማጥለቅለቅ በኋላ ጎረቤቶቻቸውን ሲረዱ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኘው ሥዕል]
የክርስቲያኖች የደግነት ሥራ መሠረተ ቢስ ጥላቻን ለማስወገድ ብዙ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል
[በገጽ 23 ላይ የሚገኘው ሥዕል]
ክርስቲያኖች “ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ” መሆን አለባቸው