የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
የባቡር ጉዞን እጅግ የሚያፈቅር አንድ ወጣት እውነትን አወቀ
አንድ ሰው ልቡ ወደ ጽድቅ ካዘነበለ ይሖዋ አምላክ ክርስቶስ ኢየሱስንና ሰማያዊ መላዕክቶቹን በመጠቀም እንዲህ ዓይነቱ በግ መሰል ሰው ውሎ አድሮ የመንግሥቱን ምሥራች እንዲያገኝ እንደሚያደርግ አያጠራጥርም። ከጊዜ በኋላ ይህ ሰው የኢየሱስን ሞገስ አግኝቶ በቀኙ ሊቆም ሊመጣ ይችላል። (ማቴዎስ 25:31–33) ይህ ሁኔታ በኦስትሪያ በሚገኝ ለየት ባለ መንገድ እውነትን ባወቀ የባቡር ጉዞን እጅግ በሚያፈቀር አንድ ወጣት ላይ ተፈጽሟል።
ይህ ወጣት እጅግ የሚደሰትበት የጊዜ ማሳለፊያው በባቡር ጣቢያው አስተዳደር ፈቃድ ከባቡር ነጂው ጎን ተቀምጦ መጓዝ ነበር። ወደ ቤቱ ሲመለስ እንደገና ማየት እንዲችል እያንዳንዱን ጉዞ በቪዲዮ ካሜራው ይቀርጸው ነበር። ከቪየና ወደ ሳልስበርግ በሄደበት ወቅት የባቡር ነጂው ከይሖዋ ምስክሮች አንዱ ነበር። የባቡር ጉዞን እጅግ ለሚያፈቅረው ለዚህ ወጣት ስለ መንግሥቱ ለማነጋገር አጋጣሚውን ተጠቀመበት። በመጀመሪያ የባቡር ነጂው ስለ አምላክና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መናገሩ ወጣቱን አስገርሞት ነበር፤ በጉዞው ወቅት ግን የባቡር ነጂው በሚነግረው ነገር ላይ ሳይሆን በሚያየው ነገር ላይ ይበልጥ አተኮረ።
ወደ ቤት ሲመለስ የባቡር ጉዞን እጅግ የሚያፈቅረው ይህ ወጣት በዚህ ጉዞ በጣም ተደስቶ ስለነበር የቪዲዮ ቅጂውን አንዴ ሳይሆን አሥር ጊዜ ተመለከተው። ድምፁንም ቀድቶት ስለነበር ምስክሩ የነገረውን ነገር ደጋግሞ ሰማው። ቪዲዮውን ደጋግሞ ባየ ቁጥር ከተነገረው ነገር ጋር በደንብ ተዋወቀ። ነገሩን አሰበበት፤ በመጨረሻም ከመጽሐፍ ቅዱስ ለቀረበው ግሩም የሆነ ትምህርት ጉጉት አደረበት። የበለጠ ለማወቅ ፈለገ።
የባቡር ነጂውን ስም አስታወሰ፤ በቪየና ውስጥ በሆነ ቦታ እንደሚኖርም ያውቅ ነበር። ስለዚህ ወደ ፖስታ ቤት ሄደና በስልክ ማውጫው ላይ በዚያ ስም የሰፈሩትን የስልክ ቁጥሮች አንድ በአንድ መደወል ጀመረ። ስልኩን ለሚያነሱት ሰዎች “የባቡር ነጂ ነዎትን?” የሚል ጥያቄ ያቀርብላቸው ነበር። አይደለሁም የሚል መልስ ከሰጡት ሌላውን ቁጥር ይደውል ነበር። በመጨረሻ የባቡር ነጂውን አገኘው። የሆነውን ነገር ተረከለትና በቪድዮው የሰማውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት እንደተደሰተበት ገለጸለት።
ምስክሩ ወጣቱ በሚኖርበት አካባቢ የሚኖር አንድ ሰው እንዲያነጋግረው በቅርንጫፍ ቢሮ በኩል ሁኔታዎችን አመቻቸ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዚያ አካባቢ በሚገኘው ጉባኤ የባቡር ነጂ የሆነ ሌላ ምስክር ይገኝ ነበር። ይህ ሁለተኛው የባቡር ነጂ የባቡር ጉዞን እጅግ የሚያፈቅረውን ወጣት አነጋገረውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ። በ1991 የበጋ ወራት ወጣቱ ተጠመቀ።
ልብን ሁሉ የሚመረምረው ይሖዋ ይህ ሰው ለጽድቅ ልባዊ የሆነ ፍቅር እንዳለው አይቶ መሆን አለበት። ስለዚህም ለየት ባለ መንገድ ቢሆንም እንኳን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያገኝ አስችሎታል። — 1 ዜና መዋዕል 28:9፤ ዮሐንስ 10:27
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Courtesy of the Austrian Railways