አስተማማኝ ጥበቃ ማግኘት ይቻላልን?
ደራሲው ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን በአንድ ወቅት “ደካማ ሰዎች በዕድል ያምናሉ። . . . የሥነ ምግባርና የአእምሮ ጥንካሬ ያላቸው ሰዎች ግን ምክንያትና ውጤት ባላቸው ዝምድና ያምናሉ” ብለዋል። አዎ፣ ምትሀታዊ ኃይል አላቸው በሚባሉ ጌጦችና ጥሩ ዕድል ያስገኛሉ ተብሎ በሚታመንባቸው ክታቦች የሚያምን ሰው ሕይወቱን የማይታዩ ኃይሎች እንዲቆጣጠሩ ይፈቅዳል፤ ምክንያታዊ አስተሳሰብን አሽቀንጥሮ ጥሎ ለጭፍንና ለአጉል እምነት ያጐበድዳል።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ሰው እንደዚህ ከመሰለው ፍርሃት ሊያላቅቀው ይችላል። ምትሀታዊ ኃይል አላቸው የሚባሉ ጌጦችም ሆኑ ክታቦች ደካማና ኃይል የሌላቸው መሆናቸውን ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን የሚያሳየው እንዴት ነው? ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንደሚለው:- “ምትሀታዊ ኃይል አላቸው የሚባሉ ጌጦች ኃይላቸውን የሚያገኙት [ከሌሎች ኃይሎች በተጨማሪ] ከተፈጥሮ ኃይሎች ጋር ካላቸው ግንኙነት ነው ተብሎ ይታሰባል።” እነዚህ ኃይሎች ‘የሙታን መናፍስት’ ወይም ‘የዕድል ኃይል’ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም” በማለት ይነግረናል። (መክብብ 9:5) ስለሆነም ሊጠቅሙ ወይም ሊጐዱ የሚችሉ የሙታን መናፍስት የሉም። እንዲሁም አንዳች ነገር ሊያደርግልህ የሚችል ዕድል የሚባል የማይታይ ኃይል የለም።
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አምላክ እሱን የተዉትን፣ ቅዱሱንም ተራራውን የረሱትን፣ ‘የአጋጣሚና የዕድል አማልክቶቻቸውን የሚያመልኩትን’ አውግዟቸዋል። እነዚህ የዕድል አምላኪዎች ጥበቃ ከማግኘት ይልቅ ለጥፋት ተዳርገዋል። ይሖዋ አምላክም “ዕድላችሁን ለሰይፍ አደርገዋለሁ” ብሏቸዋል። — ኢሳይያስ 65:11, 12 1980 ትርጉም
የጥንቷ ባቢሎን ብሔርም የአስማት ጥበቦችን በማስፋፋት ምሥጢራዊ ኃይሎች በሚሰጡት ጥበቃ ተማምና ነበር። ይሁን እንጂ ባቢሎን ከፍተኛ ጥፋት አጋጥሟታል። ኢሳይያስ “ከአስማቶችሽና ከመተቶችሽ ብዛት ጋር ቀጥዪ። ከእነርሱ እርዳታ ታገኚ ይሆናል . . . ግን አታገኚም! አታላይነትሽ ቢበዛም ደካማ ሆነሻል” በማለት ተገዳድሯታል። (ኢሳይያስ 47:12, 13 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ) ከጊዜ በኋላ ያ መንግሥት እንዳልነበረ ሆነ። በአጋንንታዊ ጥበብ ላይ እምነት መጣል ከንቱ መሆኑ ተረጋገጠ። በተመሳሳይም ምትሀታዊ ኃይል አላቸው የሚባሉ ጌጦች፣ ክታቦችና ሌሎች የሚያዙ ነገሮች ሊረዱህ ወይም ሊጠብቁህ አይችሉም።
የጣዖት አምልኮ
ቢሆንም አንዳንድ ሰዎች ዛጐል፣ የጥንቸል እግር ወይም ሃይማኖታዊ ጌጥ ማንጠልጠል ምንም ክፋት የለውም ብለው ያስቡ ይሆናል። ምንም ጉዳት የማያመጡ ጥቃቅን ጌጣጌጦች አይደሉምን? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ከሆነ አይደሉም። አስማት የተደረገባቸው ዕቃዎች ሁሉ ጉዳት የሚያስከትሉ እንደሆኑ ይገልጻል።
ምትሀታዊ ኃይል እንዳለው በሚታመንበት ጌጥ መጠቀም የጣዖት አምልኮ ዘርፍ ስለሆነ በአምላክ ቃል ውስጥ በግልጽ ተወግዟል። (ዘጸአት 20:4, 5) እውነት ነው አንድ ሰው ምትሀታዊ ኃይል እንዳለው የሚታመንበትን ጌጥ ወይም ሌላ ነገር እያመለከ እንዳለ ሆኖ ላይሰማው ይችላል። ነገር ግን እነዚህን ነገሮች መያዝ ለአስማታዊ ኃይል አክብሮት የተሞላበት ፍርሃት በማሳየት የአምልኮ ዝንባሌ መያዝ አይሆንበትምን? እነዚህን ጌጦች መሳለምና አምልኮታዊ ክብር መስጠት የተለመደ አይደለምን? ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ዮሐንስ 5:21 ላይ ክርስቲያኖችን “ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ” በማለት ይመክራል። ታዲያ ይህ ምክር ምትሀታዊ ኃይል አላቸው የሚባሉትን ጌጦችና ክታቦች አይጨምርምን?
አስማታዊ ጥበብ የሚያመጣው ወጥመድ
ብዙ ሰዎች ምትሀታዊ ኃይል አላቸው በሚባሉ ጌጦች አማካኝነት በአስማታዊ ጥበብ ወጥመድ ውስጥ ወድቀዋል። እውነት ነው አንዳንዶች ስለሚያምኑበት ሳይሆን የአካባቢው ባሕል ስለሆነ ብቻ ዛጐል ወይም ጨሌ ወይም የተደገመበት ጠበል ያስቀምጡ ይሆናል። ከአንዲት ዝሙት አዳሪ ሴት ጋር መዳራት በኤድስ ወደመለከፍ ሊያመራ እንደሚችል ሁሉ ከአስማታዊ ጥበብ ጋር መቀራረብም አጥፊ ውድቀት ሊያስከትል ይችላል። አምላክ እስራኤላውያንን ከአስማት፣ ከምዋርትና ከጥንቆላ እንዲርቁ ያዘዘው ጥሩ ምክንያት ስለነበረው ነው። “ይህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል። — ዘዳግም 18:10–14
እንዲህ ያለ ጥብቅ እገዳ የተደረገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ከእነዚህ ልማዶች በስተጀርባ ያሉት ኃይሎች የሙታን መናፍስት ወይም የዕድል ኃይል ሳይሆኑ ሰይጣን ዲያብሎስና አጋንንቱ ናቸው።a ምትሀታዊ ኃይል እንዳላቸው በሚታመንባቸው ጌጦች መጠቀም ደግሞ ከአጋንንት አምልኮ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። ቫይንስ ኤክስፖዚቶሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ እንደሚከተለው ብሏል:- “የጥንቆላ ወይም የምዋርት ድርጊት በሚፈጸምበት ጊዜ የሚሰጠው ዕፅ ቀላልም ይሁን ከባድ አብዛኛውን ጊዜ ምትሀታዊ ኃይል እንዲኖረው ከተደገመበት በኋላ ከተለያዩ ክታቦችና ጌጦች ጋር ይሰጣል።”
ስለዚህ ምትሀታዊ ኃይል እንዳለው የሚታመንበት ክታብ ወይም ጌጥ ያለው ሰው ከመናፍስታዊ ድርጊት ጋር ይካፈላል ማለት ነው። ራሱን “የዚህ ዓለም አምላክ” በሆነው በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ስር ማድረጉና ራሱን ለክፉ ነገር ማጋለጡ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውንም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት እንድናስወግድ የሚያዘን ጥሩ ምክንያት ስላለው ነው። — ገላትያ 5:19–21
ከአጉል እምነት መላቀቅ
ይሁን እንጂ ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ እንደታዘበው:- “ሰዎች እርስ በርሳቸው እስከተፈራሩና ስለወደፊቱም ጊዜ ጥርጣሬ እስካላቸው ድረስ አጉል እምነቶች በሰዎች ሕይወት ውስጥ ቦታ ማግኘታቸው ላይቀር ይችላል።” ነገር ግን የይሖዋ ምስክሮች ብዙ ሰዎችን ጐጂ ከሆኑ አጉል እምነቶች እንዲላቀቁ እየረዷቸው ነው። አንዲት በደቡብ አፍሪካ የምትኖር ባለትዳር ሴት እንዲህ አለች:- “ክፉ መናፍስት ያስቸግሩኝ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ እንዲጠብቁኝ በማሰብ ሙቲ በሚባሉ ነገሮች ቤቴን ሞልቼ ነበር።” ከአስማታዊ ጥበብ ጋር መጫወት የሚያስከትለውን አደጋ እንድታስተውል የይሖዋ ምስክሮች ረዷት። በዚህስ ምክንያት ምን አደረገች? “ከአጋንንታዊ ድርጊቶች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ንብረቶች በሙሉ አውጥቼ ጣልኳቸው” አለች። “ጤናዬ ተሻሻለልኝ። ይሖዋን ለማገልገል ሕይወቴን ወስኜ ተጠመቅሁ።” አሁን ከአጉል እምነትና ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ተላቅቃለች።
በተጨማሪም በሽተኞችን ለማዳን ከሚጠቀምበት ጥበብ ጋር መናፍስታዊ ድርጊቶችን ያቀላቅል የነበረውን ናይጄሪያዊ የአገር ባሕል ሐኪምም ሁኔታ እንመልከት። የይሖዋ ምስክሮች ሊያነጋግሩት ወደ ቤቱ ሲሄዱ እያስፈራራና እየተራገመ ቤቱ እንዳይደርሱ በማድረግ ያባርራቸው ነበር። አንድ ጊዜ ልዩ የሆነ ፈሳሽ አዘጋጅቶ ከደገመበት በኋላ በምስክሩ ፊት ላይ ረጨው! “በሰባት ቀን ውስጥ ትሞታለህ!” ብሎ ጮኸ። ከሰባት ቀን በኋላ ምስክሩ ተመልሶ ሄደ። ባለመድኃኒቱም አንድ ዓይነት መንፈስ ያየ መስሎት ከቤቱ ተንደርድሮ ወጣ። አሁን አስማቱ ከንቱ መሆኑ ስለተጋለጠበት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ። ከጊዜ በኋላም ራሱ ምስክር ሆነ።
አንተም ከፍርሃትና ከአጉል እምነት እስራት ነፃ መሆን ትችላለህ። ይህን ለማድረግ ቀላል እንደማይሆን እሙን ነው። ምናልባት ምትሀታዊ ኃይል አላቸው በሚባሉ ጌጦችና ክታቦች መጠቀም በሚዘወተርበት አካባቢ አድገህ ይሆናል። በጥንቷ ኤፌሶን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟቸው ነበር። መናፍስታዊነት በጣም በተስፋፋበት ባሕል ውስጥ ይኖሩ ነበር። የአምላክን ቃል እውነት ካወቁ በኋላ ምን አደረጉ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ።” — ሥራ 19:19
የአምላክን ጥበቃ ማግኘት
ከአጋንንታዊ ጥበብ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች ከነርዝራዣቸው ካስወገድክ የሚጠብቅህ ታጣለህን? አታጣም። ከዚህ ይልቅ “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።” (መዝሙር 46:1) በተለይ የአምላክ ጥበቃ የሚታየው ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት በሚያጠፋበት ጊዜ ይሆናል። “ይሖዋ ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን እንዴት እንደሚያድንና በደለኞችንም ለፍርድ ቀን እንዴት እንደሚጠብቅ ያውቃል።” — 2 ጴጥሮስ 2:9 አዓት ፤ ከመዝሙር 37:40 ጋር አወዳድር።
ይህ እስኪሆን ድረስ ‘ሁላችንንም ጊዜና አጋጣሚ ያገኘናል።’ (መክብብ 9:11) አምላክ አገልጋዮቹ ከማንኛውም ችግር ተጠብቀው “ደልቷቸው” እንደሚኖሩ ወይም ማንኛውም ዓይነት አካላዊ ጉዳት እንደማይደርስባቸው ተስፋ አልሰጠም። ይሁን እንጂ መንፈሳዊነታችንንና ከእሱ ጋር የመሠረትነውን የተቀራረበ ዝምድና ለመጠበቅ ቃል ገብቷል። (መዝሙር 91:1–9) እንዴት? በመጀመሪያ ደረጃ ሰይጣን ከሚያመጣቸው የሚያበላሹ ተጽእኖዎች የሚጠብቁንና የሚጠቅሙንን ሕጐችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ሰጥቶናል። (ኢሳይያስ 48:17) ስለ ይሖዋ መንገዶች በመማራችን ‘ጥንቃቄ ይጠብቀናል፣ ማስተዋልም ይጋርደናል።’ ለምሳሌ ያህል ፍሬቢስ ከሆኑ ወይም ከጐጂ ድርጊቶች እንጠበቃለን። — ምሳሌ 2:11
አምላክ እኛን የሚጠብቅበት ሌላው መንገድ በመከራ ወቅት “ከወትሮው ለየት ያለ ኃይል” በመስጠት ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:7 አዓት) አንድ ክርስቲያን ሁኔታዎቹ አስጊ ሆነውበት ሲፈራ “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም” ልቡንና የማሰብ ኃይሉን እንዲጠብቅለት ያደርጋል። (ፊልጵስዩስ 4:7) አዎን፣ ክርስቲያኑ “የዲያብሎስን ሽንገላ” ተቃውሞ መጽናት የሚያስችለው የተሟላ ትጥቅ አለው። — ኤፌሶን 6:11–13
እንደዚህ ዓይነቱን ጥበቃ እንዴት ማግኘት ትችላለህ? ስለ ይሖዋና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መማር ጀምር። (ዮሐንስ 17:3) በዚህ ረገድ የይሖዋ ምስክሮች ሊረዱህ ይችላሉ። ከይሖዋ ጋር ሞቅ ያለ የተቀራረበ ዝምድና እያዳበርክ ስትሄድ ደግነት የተሞላውን የእሱን ጥበቃ መቅመስ ትጀምራለህ። አምላክ በመዝሙር 91:14 ላይ እንደዚህ ይላል:- “በእኔ ተማምኗልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም አውቋልና እጋርደዋለሁ።”
ለአምላክ ከልብህ ታማኝ ከሆንክ ከጊዜ በኋላ በመጪው አዲስ ዓለም የዘላለም ሕይወት እንድታገኝ በማድረግ ይባርክሃል። ይሖዋ በዚያ ጊዜ ለሚኖሩት የሚከተለውን ዋስትና ሰጥቷቸዋል:- “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሯልና . . . የሚያስፈራውም የለም።” (ሚክያስ 4:4) ከዚያ በኋላ በሽታና ሞት አይኖሩም። (ራእይ 21:4) አሁንም እንኳ ቢሆን ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና ካዳበርክ መጠነኛ ጥበቃ ታገኛለህ። አንተም ልክ እንደ መዝሙራዊው እንደሚከተለው ለማለት ትችላለህ:- “ረዳቴ ሰማይንና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።” — መዝሙር 121:2
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “የሙታን መናፍስት — ሊጠቅሙህ ወይም ሊጐዱህ ይችላሉን? በሕይወትስ አሉን? ” የተባለውን በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብና ትራክት ማኅበር የታተመውን ብሮሹር ተመልከት።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኤፌሶን የነበሩ ክርስቲያኖች ከአስማታዊ ጥበቦች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ማንኛቸውንም ነገሮች አስወግደዋል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር ፍርሃት አይኖርም