መልካም ዕድል ያስገኛሉ ተብለው የሚደረጉ ክታቦች ከጉዳት ሊጠብቁህ ይችላሉን?
አንዳንድ ብራዚላውያን መስተዋት መሰል ዶቃ በኪሳቸው ይይዛሉ። አሜሪካዊ አትሌት መልካም ዕድል የሚያመጣ ሳንቲም ይይዛል። በአየርላንድ አንዳንድ ቤተሰቦች ከራስጌያቸው የቅዱስ ብርጂድን መስቀል ይሰቅላሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህን በመሰሉት መልካም ዕድል ያስገኛሉ በሚባሉ ክታቦችና ጌጦች ይጠቀማሉ።a እነዚህን ክታቦች ማድረጋቸው ከክፉ ነገር እንደሚከላከልላቸውና መልካም ዕድል እንደሚያስገኝላቸው ያምናሉ።
ለምሳሌ ያህል ብራዚልን እንመልከት። ቬዥ የተባለ መጽሔት እንደገለጸው ብዙ ብራዚላውያን “ጥሩ ዕድል እንዲሁም የአካልና የአእምሮ ብርታት ያስገኛሉ ተብሎ የሚታመንባቸውን ከአለት ስባሪና ከከበረ ድንጋይ የሚሠሩ ጠጠሮችን ይይዛሉ።” በዚህ አገር የሚኖሩ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ከአስማትና ምትሀት የሚመነጩ ኃይሎችን እንዳያስቀይሙ በመፍራት ሃይማኖታዊ ምስሎችን ወይም ጥቅሶችን በቤታቸው ግድግዳ ላይ ይሰቅላሉ። አንዳንዶች እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ክታብ አድርገው በመጠቀም መዝሙር 91 ላይ ገልጠው በጠረጴዛ ላይ ያስቀምጡታል።
በአፍሪካ ደቡባዊ ክፍልም ሙቲ የሚባለውን ባሕላዊ መድኃኒት በፈዋሽነቱ ብቻ ሳይሆን ከመጥፎ ዕድል ይጠብቀናል በሚል እምነት ይጠቀሙበታል። ሕመም፣ ሞት፣ የኤኮኖሚ ችግርና የፍቅር አለመሳካት የሚደርሰው ጠላቶች በሚጥሉት አስማት ወይም የሞቱ አባቶችን እንደሚገባ ካለመለማመን እንደሆነ ያስባሉ። ሙቲ አብዛኛውን ጊዜ የሚገኘው ከዕፅዋት፣ ከዛፎች ወይም ከእንስሳት አካል መድኃኒት ከሚቀምም የገጠር መድኃኒተኛ ነው። የሚያስገርመው ግን ሙቲ በገጠሩ አካባቢ ብቻ ሳይወሰን በደቡብ አፍሪካ ከተሞች መስፋፋቱ ነው። በሙቲ ከሚታመኑ ሰዎች መካከል የንግድ ሰዎችና የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ይገኛሉ።
መልካም ዕድል ለማግኘት የሚደረገው ጥረት በአውሮፓ አገሮችም የተለመደ ነው። ስተዲስ ኢን ፎልላይፍ ፕሬዘንትድ ቱ ኢሚር ኤስቲን ኢቫንስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በአየርላንድ በፈረስ ኮቴ ላይ የሚገጠመውን ብረት በመኖሪያ ቤታቸው ወይም በሰርቪስ ክፍሎች በር ላይ ወይም ከበሩ ከፍ ተደርጎ የማይሰቀልበት ደብር ወይም ከተማ በጣም ጥቂት ነው።” በተጨማሪም በዚህ አገር መልካም ዕድል ለማምጣት ሲባል ከተገመደ እንግጫ የተሠራ መስቀል ከአልጋ በላይ ወይም በበር ላይ ማንጠልጠል በጣም የተለመደ ነው። ስለ ጉዳዩ የታዘቡ ሰዎች እንደሚናገሩት ብዙ የአየርላንድ ተወላጆች እንደነዚህ ላሉት አጉል እምነቶች ከፍተኛ ግምት አይሰጡም። ሆኖም በቸልታ የሚመለከቷቸው ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው።
ጥበቃ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት
እንደነዚህ ዓይነቶቹ አጉል እምነቶች ተቀባይነት የሚያገኙት ለምንድን ነው? መሠረታዊ የሆነውን የሰዎች የደኅንነት ፍላጎት ለማሟላት ማገልገላቸው ነው። መንገድ ላይ ወጥተው ይቅርና በገዛ ቤታቸው ሆነው ምንም አደጋ እንደማይደርስባቸው የሚሰማቸው ሰዎች ምን ያህል ናቸው? በዚህ ሥጋት ላይ ኑሮ የማሸነፍና ልጆችን የማሳደግ ውጥረት ይጨመርበታል። አዎ፤ የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ “የመከራ ጊዜ” ብሎ በሚጠራው ወቅት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ስለዚህ ሰዎች ጠንካራ የሆነ ጥበቃ የማግኘት ፍላጎት ያላቸው መሆኑ እንግዳ ነገር አይደለም።
ይህ ደግሞ በተለይ ጎልቶ የሚታየው የተለያየ ዓይነት የመናፍስትነት ሥራዎችና ጥንቆላ በተስፋፋባቸው ባሕሎች ነው። ከሙታን መናፍስት ይመጣል ተብሎ ለሚታሰበው ጥቃት ወይም ለጠላት እርግማን እንዳይጋለጡ ያላቸው ፍላጎት ምትሀታዊ ኃይል አላቸው ተብለው በሚታሰቡ ጌጦች ወይም ክታቦች እንዲታመኑ ያደርጋቸዋል። ያም ሆነ ይህ ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒድያ “ብዙ ሰዎች ያልተረጋጋ ኑሮ እንዲኖሩ የሚያስገድዳቸው ፍርሃት አላቸው። አጉል እምነቶች የደኅንነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ ፍርሃታቸውን እንዲያሸንፉ ይረዷቸዋል። የፈለጉትን እንደሚያገኙና ችግር እንደሚወገድላቸው ያረጋግጡላቸዋል” ብሏል።
ምትሀታዊ ኃይል አላቸው ተብሎ የሚታመኑ ጌጦችና ክታቦች ያላቸው ኃይል አጠራጣሪ ነው
በዓለም በሙሉ ምትሀታዊ ኃይል አላቸው ተብሎ የሚታመኑ ጌጦችንና ክታቦችን በተለያየ መልክና ቅርፅ ሠርቶ ማድረግ፣ ማንጠልጠል፣ መስቀልና መያዝ በጣም የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ በሰው እጅ የተሠራ ክታብ እውነተኛ ጥበቃ ያስገኛል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነውን? ብዙ ሰዎች የሚጠቀሙባቸው ክታቦች በፋብሪካ የሚመረቱ የንግድ ውጤቶች ናቸው። በፋብሪካ የተመረተ ነገር የጥንቆላ ኃይል ይኖረዋል ብሎ ማመን ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ጋር አይቃረንምን? በገጠር መድኃኒተኛ የሚቀመም መድኃኒትም ቢሆን ተራ የሆኑ ሥራ ሥሮች፣ የዕፅዋት ቅጠሎችና እነዚህን የመሰሉ ነገሮች ቅልቅል ከመሆን አያልፍም። እንደዚህ ዓይነቱ ቅይጥ በምን መንገድ የጥንቆላ ባሕርይ ይኖረዋል? ከዚህም በተጨማሪ ክታቦችን የሚጠቀሙ ሰዎች ከማይጠቀሙ ሰዎች የበለጠ ዕድሜና ደስታ እንዳገኙ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ? የዚህ ዓይነቶቹን የጥንቆላ ክታቦች የሚሠሩት ሰዎችስ በበሽታና በሞት አይጠቁምን?
በአጉል እምነት ላይ ተመሥርቶ ምትሀታዊ ኃይል አላቸው ተብለው በሚታመኑ ጌጦችና ክታቦች መጠቀም ሰዎች እውነተኛ ጥበቃ እንዲያገኙና ሕይወታቸውን እንዲቆጣጠሩ ከማስቻል ይልቅ ዕድላቸው ሁሉንም ነገር እንዲያስተካክልላቸው በመጠበቅ ችግራቸውን ፊት ለፊት እንዳይቋቋሙ ያደርጋቸዋል። ምትሀታዊ ኃይል ባላቸው ጌጦች መተማመን ተጠቃሚው ሰው የሐሰት ደኅንነት እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል። በአልኮል መጠጥ የደነዘዘ ሰው የተፈጥሮ ስሜቶቹና ችሎታዎቹ በመጠጡ እንዳልተጎዳ ሊሰማው ይችላል። ነገር ግን መኪና ለመንዳት ቢሞክር በራሱና በሌሎች ላይ አደጋ እንደሚያመጣ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም አንድ ምትሀታዊ ኃይል አላቸው ተብለው በሚታመንባቸው ጌጦች የሚታመን ሰው ራሱን ይጎዳል። ከማንኛውም አደጋ እንደተጠበቀ በማሰብ አደጋ የሚያስከትሉ የሞኝነት ምርጫዎችንና ጥበብ የጎደላቸውን ውሳኔዎች ወደ ማድረግ ሊያዘነብል ይችላል።
ምትሀታዊ ኃይል አላቸው ተብሎ በሚታመንባቸው ጌጦች መታመን በጌጦቹ ከሚጠቀሙት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የተሰወሩ ሌሎች ከባድ አደጋዎችን ያመጣል። እነዚህ አደጋዎች ምንድን ናቸው? ራሳችንንስ ከጉዳት የምንጠብቅበት መንገድ ይኖራልን? የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ ያተኩራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮሊጄት ዲክሽነሪ “አምዩሌት” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል “አድራጊውን ከክፉ ነገር የሚጠብቅ የጥንቆላ ድግምት ወይም ምስል የተቀረጸበት ጌጥ” በማለት ይገልጸዋል።