ታስታውሳለህን?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በጥንቃቄ አንብበሃልን? አንብበህ ከነበረ የሚከተሉትን ነጥቦች ለማስታወስ ትችላለህ:-
▫ በዛሬው ጊዜ በአንድ ጉባኤ ውስጥ ለታመሙና ለአረጋውያን ምን ተግባራዊ እርዳታ መስጠት ይቻላል?
በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ቁሳዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መበለቶች ስም ዝርዝር ይወሰድ ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 5:9, 10) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ሽማግሌዎች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡትን የታመሙና አረጋውያን ስም ዝርዝር መያዝ ያስፈልጋቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ቅድሚያ ወስዶ የመንከባከቡ ኃላፊነት ለሽማግሌዎች ብቻ መተው የለበትም። እንደዚህ ላሉት አስፈላጊ ነገሮች ሁሉም የጉባኤው አባላት ንቁዎች መሆን አለባቸው። (1 ጢሞቴዎስ 5:4–8) — 8/15 ገጽ 28–29
▫ መጽሐፍ ቅዱስ ዮናስ በአንድ የባሕር እንስሳ እንደተዋጠ የሚናገረው ታሪክ የማይታመን ነውን?
አይደለም። ስፐርም ሁዌል፣ ነጭ ትልቅ ዓሣ ነባሪ ወይም ሁዌል ሻርክ የተባለው የዓሣ ነባሪ ዓይነት ሰው ሊውጡ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ የዮናስ ታሪክ እውነት መሆኑን ኢየሱስ ራሱ አረጋግጧል። (ማቴዎስ 12:39, 40) — 8/15 ገጽ 32
▫ መልካም ዕድል ያስገኛሉ ተብለው የሚደረጉ ክታቦችና ጌጦች ምን ጉዳት ያስከትላሉ?
እነዚህ ነገሮች ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በማሰብ ችሎታቸው ተጠቅመው እንዳይቋቋሟቸው ከማድረጋቸውም በላይ ለምንም ነገር መፍትሔው ዕድል ብቻ ነው ወደሚለው እምነት ይመራቸዋል። ተጠቃሚውም በስሕተት ከማንኛውም አደጋ የተጠበቀ እንደሆነ ይሰማዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በምትሀታዊ ጌጦች ወይም መልካም ዕድል ያስገኛሉ ተብሎ በሚታመንባቸው ክታቦች የሚያምን ሰው ሕይወቱን የማይታዩ አጋንንታዊ ኃይሎች እንዲቆጣጠሩት ይፈቅዳል። — 9/1 ገጽ 4
▫ ጋብቻ ዘላቂ እንዲሆን የሚያደርጉት አራት ነገሮች ምንድን ናቸው?
እነዚህ ነገሮች ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆን፣ ይቅርታ የመጠየቅ ችሎታ፣ የማያቋርጥ ስሜታዊ ድጋፍ ለመስጠት መቻል እና በፍቅር ስሜት የመደባበስ ፍላጎት ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 13:4–8፤ ኤፌሶን 5:33፤ ያዕቆብ 1:19) — 9/1 ገጽ 20
▫ ይሖዋ መከራ ለሚያጋጥማቸው ጽናት ከሚሰጥባቸው መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?
ይሖዋ ይህን የሚያደርገው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመዘገቡት የጽናት ምሳሌዎች አማካኝነት ነው። (ሮሜ 15:4) እነዚህን ስናነብ እንድንጸና ማበረታቻ እናገኛለን። እንዲሁም እንዴት መጽናት እንደምንችል ብዙ እንማራለን። — 9/15 ገጽ 11–12
▫ ለአምላክ ያደሩ መሆን ምንድን ነው?
ለአምላክ ያደሩ መሆን እሱን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ለማድረግ በሚገፋፋ መንገድ ራስን ለይሖዋ ሳይቆጥቡ ማቅረብን ያመለክታል። አምላክን ከልባችን ስለምናፈቅረው በአስቸጋሪ መከራ ሥር ብንወድቅም ይህን እናደርጋለን። — 9/15 ገጽ 15
▫ የአምላክን ምሕረት እንዴት ልንመለከተው ይገባል?
የአምላክን ምሕረት በፍጹም አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ልንሆንና ካለብን አለፍጽምና ጋር በመታገል ለአምላክ ምህረት ያለንን አድናቆት ማሳየት ይገባናል። (1 ቆሮንቶስ 9:27) በዚህ መንገድ በአስቸጋሪ ወቅትም እንኳ ቢሆን ትክክለኛ የሆነውን ነገር የማድረግ እውነተኛ ምኞት እንዳለን እናሳያለን። — 10/1 ገጽ 23
▫ ጳውሎስ ትዕግሥትን ፍቅር ከሚገለጽባቸው መንገዶች የመጀመሪያው አድርጎ መጻፉ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
ትዕግሥትና እርስበርስ መቻቻል ካልኖረ ክርስቲያናዊ ባልንጀርነት ሊኖር አይችልም ተብሏል። ይህ የሆነበትም ምክንያት ፍጹም ስላልሆንንና አለፍጽምናችንና ድክመታችን ሌሎችን ስለሚፈትን ነው። ስለዚህ በወንድሞች መካከል ፍቅር እንዲሰፍን ከተፈለገ ትዕግሥት መኖሩ በጣም አስፈላጊ ነው። — 10/15 ገጽ 21
▫ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በአምላክ ስም ተጠቅመው ነበርን?
በአምላክ ስም ለመጠቀማቸው ማስረጃዎቹ ይመሰክራሉ። ኢየሱስ “ስምህ ይቀደስ” ብለው ለአምላክ እንዲጸልዩ ተከታዮቹን አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:9) በአገልግሎቱ መጨረሻ ላይ “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው” በማለት ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:6) ከዚህም በተጨማሪ በሴፕቱጀንት የጥንት ቅጂዎች በአራቱ የዕብራይስጥ ፊደላት የተጻፈው የአምላክ ስም ይገኛል። — 11/1 ገጽ 30
▫ ስሕተት ስንሠራ የምናደርገው ነገር ሕይወታችንን ሊነካው እንደሚችል የሚያሳዩት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
ንጉሥ ሳኦል በእልኸኝነት ምክር አልቀበልም አለ፣ በስሕተቶቹ ላይ ስህተት ጨማመረባቸው። በመጨረሻም የአምላክን ሞገስ አጥቶ ለመሞት በቃ። (1 ሳሙኤል 15:17–29) በሌላ በኩል ደግሞ ዳዊት ስሕተትና ኃጢአት ቢሠራም ንስሐ በመግባት የተሰጠውን እርማት ተቀብሎ ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ ኖሯል። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ስሕተታችንን ማመናችን ከአምላክ ጋር የገባነውን ዝምድና በጥሩ ሁኔታ ይዘን እንድንቀጥልና የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ እንደሚረዱን ያሳያሉ። (መዝሙር 32:1–5) — 11/15 ገጽ 29–30
▫ በተፈጥሮ አደጋዎች ወይም በሌሎች ችግሮች መከራ ሲገጥማቸው ይሖዋ ለሕዝቦቹ የሚደርስላቸውና የሚረዳቸው እንዴት ነው?
ይሖዋ የሚረዳው ተአምራዊ በሆነ መንገድ የተፈጥሮ ኃይሎችን አቅጣጫ በማስቀየር ወይም በሌላ ከፍተኛ ኃይል በመጠቀም ሳይሆን ብዙ ሰዎች ለመረዳት አዳጋች በሆነባቸው ሌላ ኃይል ማለትም በፍቅር ይጠቀማል። አዎን፣ ይሖዋ ሕዝቦቹን በእውነት ይወዳቸዋል። ስለዚህም እንደ ተአምር ሊቆጠር በሚችል መንገድ የሚያስፈልጋቸውን ለማድረግ የሚያስችል እጅግ በጣም ጠንካራ የሆነ ፍቅር እንዲኖራቸው አድርጓል። (1 ዮሐንስ 4:10–12, 21) — 12/1 ገጽ 10