የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 11/15 ገጽ 28-30
  • ስሕተትህን ማመን ያለብህ ለምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ስሕተትህን ማመን ያለብህ ለምንድን ነው?
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለተስፋ መቁረጥ ምክንያት ሊሆን አይገባውም
  • ትሕትና በጣም አስፈላጊ ጠባይ ነው
  • ስሕተቶቻቸውን አምነዋል
  • ስሕተቶቻችንን ለማረም አንድ ነገር ማድረግ
  • አንድ ሽማግሌ ስሕተት በሚሠራበት ጊዜ
  • አንድን ስሕተት ለማመን አትዘግይ
  • ስሕተትህን በማመንህ ደስ ይበልህ
  • ስህተት ስሠራ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • ስህተትን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መመልከት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
  • ይቅርታ መጠየቅ—እርቅ ለመፍጠር የሚያስችል ቁልፍ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • ከስህተታችሁ ተማሩ
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2017
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 11/15 ገጽ 28-30

ስሕተትህን ማመን ያለብህ ለምንድን ነው?

በወታደራዊ ታሪክ ውስጥ ከደረሱት እንግዳ ነገሮች አንዱ ነበር። ትጥቅ የሌላት የሰላም ልኡክ አንዴ ከተነሡ የማይመለሱትን 400 ወታደሮች የተሰደቡበትን ለመበቀል ከሚያደርጉት ቆራጥ ጉዞ እንዲመለሱ አደረገቻቸው። የአንዲትን ደፋር ሴት ልመና በመስማት የእነዚህ ሰዎች መሪ የተነሣበትን ተልእኮ ሰረዘው።

መሪው ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ዳዊት ነበር። አምላክን ለማስደሰት ስለፈለገ አቢጋኤል የተባለችውን ሴት አደመጣት። በባልዋ በናባል ላይ የበቀል እርምጃ መውሰድ ወደ ደም ዕዳ ውስጥ መግባት ማለት እንደሆነ በዘዴ በነገረችው ጊዜ ዳዊት እንዲህ አለ:- “ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። ወደ ደም እንዳልሄድ፣ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፣ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ።” አምላክ አቢጋኤልን ተጠቅሞ ከከባድ ስሕተት እንዲርቅ ስለረዳው ዳዊት አምላኩን በጣም አመሰገነ። — 1 ሳሙኤል 25:​9–35

በመዝሙር ላይ ዳዊት “ስሕተትን ማን ያስተውላታል?” በማለት ጠይቋል። (መዝሙር 19:​12) እኛም እንደ ዳዊት አንድ ሰው ስሕተታችንን ለይቶ ካላሳየን ላንጠነቀቅ እንችላለን። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ደስ የማይሉ ውጤቶችን ስናይ ተሳስተን፣ ጥበብ የጎደለው ወይም ደግነት የጎደለው ነገር አድርገን እንደነበረ ለመገንዘብ እንገደዳለን።

ለተስፋ መቁረጥ ምክንያት ሊሆን አይገባውም

ሁላችንም ስሕተት የምንሠራ ብንሆንም ይህ ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም። ኤድዋርድ ጆን ፌልፕስ የተባሉ ዲፕሎማት “ስሕተት የማይሠራ ሰው ምንም ነገር የማይሠራ ሰው ነው” በማለት የታዘቡትን ተናግረዋል። እንዲሁም ክርስቲያኑ ደቀ መዝሙር ያዕቆብ “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለን” በማለት ተናግሯል። (ያዕቆብ 3:​2) አንድ ሕፃን ልጅ ሳይወድቅ በእግሩ መሄድን ሊማር ይችላልን? አይችልም። ከዚህ ይልቅ ከሚሠራቸው ስሕተቶች ይማራል፤ ሚዛኑን መጠበቅ እስኪችል ድረስም እንዲህ ማድረጉን ይቀጥላል።

ሚዛኑን የጠበቀ ሕይወት ለመምራት እንድንችል እኛም ከራሳችንና ከሌሎች ስሕተቶች መማር ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስ ከእኛ ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ተሞክሮዎችን ስለሚተርክልን እነርሱ የሠሩትን የሚመስል ስሕተት ከመሥራት እንድንርቅ ሊረዳን ይችላል። ታዲያ ከእነርሱ ስሕተት ምን ልንማር እንችላለን?

ትሕትና በጣም አስፈላጊ ጠባይ ነው

ልናውቀው የሚገባ አንድ ነገር ቢኖር አምላክ ስሕተት የሚሠሩትን ሁሉ የሚያወግዝ አለመሆኑን ከዚህ ይልቅ ስሕተታቸውን ለማስተካከል እምቢተኞች በሆኑት ላይ የሚፈርድ መሆኑን ነው። የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሳኦል አማሌቃውያንን እንዲያጠፋ ይሖዋ የሰጠውን መመሪያ አልታዘዘም ነበር። ነቢዩ ሳሙኤል ስሕተቱን በነገረው ጊዜ ግን ሳኦል በመጀመሪያ ስሕተቱን ቀላል አድርጎ ለማሳየት ሞከረ፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ ስሕተቱን በሌሎች ላይ ለማላከክ ሞከረ። ይበልጥ ያሳሰበው ነገር ስሕተቱን ማስተካከሉ ሳይሆን በሰዎቹ ፊት መዋረዱ ብቻ ነበረ። ስለዚህም ‘ይሖዋ ንጉሥ እንዳይሆን ሰረዘው።’ — 1 ሳሙኤል 15:​20–23, 30

ከሳኦል ቀጥሎ የነገሠው ዳዊት ከባድ ስሕተት ቢሠራም ይቅርታ ሊያገኝ የቻለው የተሰጠውን ምክርና ተግሣጽ በትሕትና ስለተቀበለ ነው። የዳዊት ትሕትና የአቢጋኤልን ምክር እንዲሰማ አድርጎታል። ወታደሮቹ ለውጊያ ዝግጁ ነበሩ። ሆኖም ዳዊት በችኮላ ውሳኔ እንዳደረገ በወታደሮቹ ፊት አምኖ ተቀበለ። በሕይወቱ ሁሉ እንደዚህ ያለው ትሕትና ይቅርታ እንዲጠይቅና እርምጃዎቹን እንዲያስተካክል ዳዊትን ረድቶታል።

ትሕትና የይሖዋ አገልጋዮች ሳያስቡት የተናገሩትንም እንዲያስተካክሉ ይገፋፋቸዋል። በሳንሄድሪን ጳውሎስ ተከሶ ሸንጎ ፊት በቀረበ ጊዜ ሊቀ ካህኑ በጥፊ እንዲመቱት አዘዘ። ሐዋርያውም ወዲያውኑ “አንተ በኖራ የተለሰነ ግድግዳ፣ እግዚአብሔር አንተን ይመታ ዘንድ አለው” በማለት አጸፋውን መለሰ። (ሥራ 23:​3) ጳውሎስ ምናልባት ዓይኑ በደንብ አጥርቶ ስለማያይለት አጠገቡ የቆሙት “የእግዚአብሔርን ሊቀ ካህናት ትሳደባለህን?” ብለው እስከጠየቁት ድረስ ማንን ያነጋግር እንደነበር አልገባውም ነበር። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ወዲያውኑ ስሕተቱን አመነና “ወንድሞች ሆይ፣ ሊቀ ካህናት መሆኑን ባላውቅ ነው፤ በሕዝብህ አለቃ ላይ ክፉ ቃል አትናገር ተብሎ ተጽፎአልና” በማለት መልስ ሰጣቸው። (ሥራ 23:​4, 5፤ ዘጸአት 22:​28) አዎን፣ ጳውሎስ ስሕተቱን በትሕትና አምኗል።

ስሕተቶቻቸውን አምነዋል

መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንዶች የተሳሳተውን የአስተሳሰብ መንገዳቸውን እንደለወጡ ያሳያል። ለምሳሌ መዝሙራዊውን አሳፍ ውሰድ። ክፉ ሰዎች የተሳካላቸው ስለመሰለው “በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ” በማለት ተናገረ። ነገር ግን አሳፍ ወደ ይሖዋ ቤት ከሄደና የንጹሕ አምልኮን ጥቅም ካሰላሰለ በኋላ ወደ አእምሮው ተመልሷል። ከዚህም በላይ በመዝሙር 73 ላይ ስሕተቱን አምኗል።

ዮናስም እንዲሁ የተሳሳተ አስተሳሰብ አመለካከቱን እንዲያጨልምበት ፈቅዶ ነበር። በነነዌ ከሰበከ በኋላ ከከተማይቱ ሰዎች መዳን ይልቅ የራሱ ትክክለኛነት ስለመረጋገጡ ብቻ ተጨንቆ ነበር። ንስሐ ቢገቡም ይሖዋ የነነዌን ሰዎች ባለመቅጣቱ ዮናስ ቅር ስለተሰኘ አምላክ አረመው። ዮናስ አመለካከቱ የተሳሳተ እንደነበረ አስተዋለ። እንዲህ ለማለት የምንችለውም በስሙ የተመዘገበው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ስሕተቱን በሐቀኝነት ማመኑን ስለሚገልጽልን ነው። — ዮናስ 3:​10 እስከ 4:​11

ኢዮብ የተባለው ሰው በስሕተት ሰይጣን ዲያብሎስ ሳይሆን ይሖዋ አምላክ መከራውን እንዳመጣበት አድርጎ ስላሰበ መከራው ሊደርስበት ይገባ እንዳልነበረ ለመከራከር ሞክሮ ነበር። የአምላክ አገልጋዮች ቢፈተኑ ታማኝ ደጋፊ ሆነው በአምላክ ጎን ይቆማሉን? የሚለውን ታላቅ ግድድር አላወቀም ነበር። (ኢዮብ 1:​9–12) በመጀመሪያ ኤሊሁ ከዚያም ይሖዋ ስሕተቱን እንዲገነዘብ ኢዮብን ከረዱት በኋላ “እኔ የማላስተውለውን . . . ነገር ተናግሬአለሁ። ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እጸጸታለሁ” በማለት ስሕተቱን አምኗል። — ኢዮብ 42:⁠3, 6

ስሕተትን ማመን ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ይዘን እንድንቀጥል ይረዳናል። ከላይ የተመለከትናቸው ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ስሕተታችንን እስካመንን ድረስና የተሳሳተውን አስተሳሰባችንን፣ ሳናስብ የተናገርነውን ወይም ቸኩለን ያደረግነውን ነገር ለማስተካከል የምንችለውን ያህል ካደረግን ስሕተት ስለ ሠራን ብቻ አይኮንነንም። ይህንን እውቀት እንዴት ልንሠራበት እንችላለን?

ስሕተቶቻችንን ለማረም አንድ ነገር ማድረግ

በትሕትና ስሕተትን ማመንና ስሕተቱን ለማረም አንድ ነገር ማድረግ የቤተሰብን ማሠሪያ ሊያጠነክረው ይችላል። ለምሳሌ አንድ ወላጅ ከድካም የተነሣ ወይም በአንድ ነገር ስለ ተበሳጨ ልጁን ኃይለኛ ቃል በመናገር ገሥጾት ይሆናል። ይህንን ስሕተት ለማረም እምቢተኛ መሆን መጥፎ ውጤቶች ሊያስከትል ይችላል። ይህም በመሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ “እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” በማለት ጽፏል። — ኤፌሶን 6:​4

ጳውሎስ የተባለ አንድ ወጣት “ከልኩ እንዳለፈ ከተሰማው አባቴ ሁልጊዜ ይቅርታ ይጠይቅ ነበር። እንደዚህ ማድረጉ እንዳከብረው አድርጎኛል” በማለት ትዝታውን ተናግሯል። በአንድ የተወሰነ ሁኔታ ሥር ይቅርታ መጠየቅ ማስፈለጉ በግል የሚወሰን ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ የሚጠየቁትን ይቅርታዎች ለወደፊቱ ተመሳሳይ ስሕተቶች እንዳይደገሙ የሚያደርጉ ጥረቶች ሊከተሏቸው ይገባል።

አንድ ባል ወይም ሚስት ጭንቀት የሚፈጥር ስሕተት ቢፈጽሙ ምን ማድረግ ያስፈልጋል? ፍቅራዊ ዝምድናቸው እንዲቀጥል ሊረዳቸው የሚችለው በግልጽ ስሕተትን ማመን፣ ልባዊ ይቅርታ መጠየቅና የይቅር ባይነት መንፈስ መያዛቸው ነው። (ኤፌሶን 5:​33፤ ቆላስይስ 3:​13) በ50ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ውስጥ የሚገኘውና በጣም ቁጡ የሆነው ካሱስ የተባለው የስፔይን ተወላጅ ሚስቱን አልቤናን ይቅርታ መጠየቅ አይከብደውም። “አንዳችን ሌላውን ስናስቀይም ይቅርታ መጠየቅ ልማዳችን ነው። ይህን ማድረጋችንም በፍቅር እርስ በርሳችን ተቻችለን እንድንኖር ረድቶናል” በማለት ሚስቱ ተናግራለች።

አንድ ሽማግሌ ስሕተት በሚሠራበት ጊዜ

ስሕተትን ማመንና በቅን ልብ ይቅርታ መጠየቅ ክርስቲያን ሽማግሌዎችንም ቢሆን ተባብረው እንዲሠሩና ‘አንዳቸው ሌላውን እንዲያከብረው’ በማድረግ ይረዳቸዋል። (ሮሜ 12:​10) አንድ ሽማግሌ በጉባኤ ውስጥ ያለውን ሥልጣን ያቃልልብኝ ይሆናል በሚል ፍርሃት ስሕተቱን ለማመን ያመነታ ይሆናል። ይሁን እንጂ ስሕተቱን ለመሸፋፈን፣ ችላ ለማለት ወይም አቅልሎ ለማየት መሞከር ሌሎች ይበልጥ በእርሱ የበላይ ጥበቃ ላይ እንዳይተማመኑ ሊያደርጋቸው ይችላል። ሳያስበው ስለ ተናገረው ነገር በትሕትና ይቅርታ የሚጠይቅ የጎለመሰ ወንድም የሌሎችን አክብሮት ሊያተርፍ ይችላል።

በስፔይን የሚገኝ ፈርናንዶ የሚባል ሽማግሌ አንድ የክልል የበላይ ተመልካች ብዙ ሽማግሌዎች የተገኙበትን ስብሰባ ሲመራ ጉባኤ እንዴት ሊመራ እንደሚገባ ትክክለኛ ያልሆነ ነገር የተናገረበትን ወቅት ያስታውሳል። የተናገረውን ነገር አክብሮት በተሞላበት መንገድ አንድ ወንድም ሲያርመው የክልል የበላይ ተመልካቹ ተሳሳቶ እንደነበረ ወዲያውኑ አመነ። ፈርናንዶ እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “በእነዚያ ሁሉ ሽማግሌዎች ፊት ስሕተቱን ሲያምን መመልከቴ ልቤን በጣም ነካው። በዚያ ወቅት ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ ከበፊቱ የበለጠ አከበርኩት። የእሱ ምሳሌ እኔም የራሴን ድክመቶች ማመኑ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስተማረኝ።”

አንድን ስሕተት ለማመን አትዘግይ

ይቅርታ በሚጠየቅበት ጊዜ በአድራጎቱ ይበልጥ የሚደነቀው በተለይ ወዲያውኑ ሲደረግ ነው። እንዲያውም የሚሻለው ስሕተታችንን ወዲያውኑ ብናምን ነው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- ጥቅምት 31, 1992 ፓፓ ጳውሎስ ዮሐንስ ሁለተኛ ከ360 ዓመት በፊት ጋሊሊዮ መሬት የጽንፈ ዓለም ማዕከል አይደለችም ብሎ ስለተናገረ የተወሰደበት የኢንኩዚሽን ቅጣት “በስሕተት” የተደረገ ነበረ በማለት አምነዋል። ይሁን እንጂ አንድን የይቅርታ ጥያቄ ለዚህን ያህል ረጅም ጊዜ ማቆየቱ ዋጋውን ዝቅ ያደርገ⁠ዋል።

በግለሰቦች ዝምድና ረገድም እንደዚሁ ነው። ወዲያውኑ ይቅርታ መጠየቅ ደግነት በጎደለው አነጋገር ወይም ድርጊት የተጎዳን ሰው ሊፈውሰው ይችላል። ኢየሱስ ሰላም መፍጠሩን እንዳናዘገየው አሳስቦናል። እንዲህ አለ:- “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፣ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፣ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፣ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፣ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።” (ማቴዎስ 5:​23, 24) አብዛኛውን ጊዜ ሰላማዊ ግንኙነቶች እንዳይደፈርሱ ለማድረግ የሚፈለገው ነገሮችን በተሳሳተ መንገድ አድርገን እንደነበረ መግለጽና ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ነው። ብዙ በቆየን መጠን ይህን ማድረጉ እየከበደን ይመጣል።

ስሕተትህን በማመንህ ደስ ይበልህ

የሳኦልና የዳዊት ምሳሌ እንደሚያሳየው ስሕተቶቻችንን በተመለከተ የምናደርገው ነገር ሕይወታችንን ሊነካው ይችላል። ሳኦል በእልኸኝነት ምክር አልቀበልም አለና ስሕተቶቹን አባባሳቸው፤ በመጨረሻም የአምላክን ሞገስ አጥቶ ለመሞት በቃ። ዳዊት ስሕተቶችና ኃጢአቶች ቢሠራም ንስሐ በመግባት እርማት ስለተቀበለ ለይሖዋ የታመነ ሆኖ ቀጠለ። (ከመዝሙር 32:​3–5 ጋር አወዳድር።) የእኛስ ምኞት እንደዚህ አይደለምን?

አንድን ስሕተት ከማመንና ከማቃናት ወይም ንስሐ ከመግባት የሚገኘው ትልቁ ሽልማት በአምላክ ይቅር እንደተባልን ማወቃችን ነው። “ኃጢአቱ የተከደነችለት ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው። እግዚአብሔር በደልን የማይቆጥርበት . . . ሰው ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው” በማለት ዳዊት ተናግሯል። (መዝሙር 32:​1, 2) እንግዲያው ስሕተትን ማመን ምንኛ ጥበብ የተሞላበት እርምጃ ነው!

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሕፃን ልጅ ሳይወድቅ በእግሩ መሄድን ሊማር ይችላልን?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ