የተስፋይቱ ምድር ገጽታዎች
ገለዓድ የደፋር ሰዎች ምድር
እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው ከጥቂት ጊዜ በፊት ሙሴ እንዲህ ሲል አጥብቆ መከራቸው:- “ቆራጥነትና ድፍረት ይኑራችሁ፤ . . . አምላካችሁ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሆናል።” — ዘዳግም 31:6 የ1980 ትርጉም
የሙሴ ጥብቅ ማሳሰቢያ የሮቤልንና የጋድን ነገዶች እንዲሁም የምናሴን ነገድ እኩሌታ የሚጨምር ነበር። እነዚህ ነገዶች “የገለዓድ ምድር ለእንስሶች የተመቸ ስፍራ እንደነበረ” ስላዩ የገለዓድ ምድር መኖሪያ ሆኖ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቀረቡ። — ዘኁልቁ 32:1–40
ገለዓድ በሌላኛው የተስፋይቱ ምድር ጐን፣ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚገኝ ቦታ ነው። ምሥራቃዊውን ክፍል በሙሉ ይኸውም ከሙት ባሕር ሰሜናዊ ጫፍ እስከ ገሊላ ባሕር ድረስ ያለውን አካባቢ ያጠቃልላል። ይህ አካባቢ ከዮርዳኖስ ሸለቆ ተነስቶ ውኃ በብዛት እስከሚገኝባቸው አምባዎችና ክብ ኮረብታዎች ይደርሳል። ስለዚህ ገለዓድ ለእህል ምርትና ለከብቶች ግጦሽ በጣም ተስማሚ የሆነ ምድር ነው። ከላይ ያለው ሥዕል የገለዓድ አንዱ ክፍል ምን ይመስል እንደነበረ ፍንጭ ይሰጥሃል። ይሁን እንጂ አንፃራዊ ደስታ የሰፈነበት ይህ ሥፍራ ከድፍረት ጋር የተዛመደው ለምንድን ነው?
በገለዓድ ለመኖር የመረጡት ነገዶች በዚህ አካባቢ ለመኖር የመረጡት ከፍርሃት የተነሳ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። እነዚህ ነገዶች በተስፋይቱ ምድር ከነበሩት ጠላቶች ጋር ለመዋጋት ሲሉ ዮርዳኖስን ለመሻገር ተስማምተው እንደ ነበር አስታውስ። ከዚያም በኋላ ወደ ገለዓድ ለመመለስ ተጨማሪ ድፍረት አስፈልጓቸዋል። ለምን? በደቡብ ምሥራቅ ከሚገኙት አሞናውያንና በሰሜን ከሚገኙት ሶርያውያን ለሚመጣው ጥቃት የተጋለጠ የጠረፍ አካባቢ ስለነበረ ነው። ደግሞም ጥቃት ደርሶባቸው ነበር። — ኢያሱ 22:9፤ መሳፍንት 10:7, 8፤ 1 ሳሙኤል 11:1፤ 2 ነገሥት 8:28፤ 9:14፤ 10:32, 33
እነዚህ ጥቃቶች ድፍረት የሚጠይቁ ልዩ ወቅቶች ነበሩ። ለምሳሌ አሞናውያን የገለዓድን ሰዎች እንዲያስጨንቋቸው ይሖዋ ከፈቀደላቸው በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ተጸጸቱ። የአባቱ ስም ገለዓድ ተብሎ የሚጠራ አንድ “ጽኑዕ ኃያል” ሰው እንዲመራቸው ጠየቁ። ይህ ጽኑዕ ወይም ደፋር ሰው ዮፍታሔ ነበር። ይህ ሰው ባደረገው መሐላ ከፍተኛ ዝና አትርፏል። ይህ መሐላ ደፋር ቢሆንም የአምላክን መመሪያና እርዳታ ለማግኘት የሚፈልግ ሰው መሆኑን አሳይቷል። ዮፍታሔ አምላክ ጨቋኞቹን አሞናውያን እንዲያሸንፍ ካስቻለው እሱን ለመቀበል ከቤቱ የሚወጣው የመጀመሪያ ሰው ለአምላክ ‘የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ ይቀርባል’ ብሎ ተሳለ።a ይህ ‘መሥዋዕት የሚሆነው ሰው’ በኋላ በአምላክ ቤተ መቅደስ ለማገልገል የሄደችው የዮፍታሔ አንድያ ልጅ ሆነች። አዎ፣ ዮፍታሔና ሴት ልጁ ለየት ባለ መንገድ ቢሆንም ድፍረት አሳይተዋል። — መሳፍንት 11:1, 4–40
በተጨማሪም የዚህን ያህል በስፋት ያልታወቀ ድርጊት በሳኦል ዘመን ተከናውኗል። የሁኔታውን መነሻ በአእምሮህ መሳል እንድትችል ሳኦል በነገሠበት ጊዜ አሞናውያን በዮርዳኖስ ኮረብታዎች አቋርጦ በሚወርደውና በክረምት ጊዜ በሚሞላው ደረቅ ወንዝ አካባቢ ይኖሩ ነበር ተብሎ የሚታሰቡትን የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ቀኝ ዓይን ለማውጣት ቃጥተው እንደነበረ አስታውስ። ሳኦል የኢያቢስ ሰዎችን ለማጠናከር የጦር ሠራዊቱን በፍጥነት ሰበሰበ። (1 ሳሙኤል 11:1–11) ይህን መንደርደሪያ በአእምሮአችን ይዘን ወደ ሳኦል የግዛት ዘመን ማብቂያ እናቅናና ምን ዓይነት ድፍረት እንደታየ እንመልከት።
ሳኦልና ሶስቱ ወንዶች ልጆቹ ከፍልስጥኤማውያን ጋር በተደረገው ውጊያ እንደሞቱ ታስታውስ ይሆናል። ጠላቶቹ የሳኦልን ራስ ቆረጡና በድል አድራጊነት የሳኦልንና የልጆቹን ሬሳዎች በቤትሳን ቅጥር ላይ አንጠለጠሉአቸው። (1 ሳሙኤል 31:1–10፤ በቀኝ በኩል፣ በቁፋሮ የተገኘውን የቤትሳንን ጉብታ ተመልከት።) ወሬው በዮርዳኖስ ማዶ በገለዓድ ኮረብታዎች ወደሚገኙት የኢያቢስ ሰዎች ደረሰ። ገለዓዳውያን የእሥራኤልን ንጉሥ ድል ለመምታት በቻሉት በጣም ኃያል የሆኑ ጠላቶች ላይ ምን ማድረግ ይችላሉ?
ካርታውን እየተመለከትክ ተከታተል። “ጀግኖች ሰዎች ሁሉ ተነስተው ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ፣ የሳኦልንም ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ከቤትሳን ቅጥር ላይ አወረዱ፤ ወደ ኢያቢስም መጡ፣ በዚያም አቃጠሉት።” (1 ሳሙኤል 31:12) አዎ፣ ጠንካራ በሆነው የጠላት ምሽግ ላይ በሌሊት ድንገተኛ አደጋ ጣሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ለምን ጀግኖች ወይም ደፋሮች ብሎ እንደሚጠራቸው መረዳት ትችላለህ።
ከጊዜ በኋላ አሥር ነገዶች ተገንጥለው ሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት አቋቋሙ። የዚህ መንግሥት ግዛት ገለዓድን ያጠቃልላል። በዙሪያቸው ያሉት ሕዝቦች፣ በመጀመሪያ ሶርያውያን ቀጥሎም አሦራውያን በዮርዳኖስ ምሥራቃዊ ክፍል የሚገኘውን ክልል አንዳንድ ቦታዎች መቆጣጠር ጀመሩ። ስለዚህ የገለዓድ ሰዎች የቀደሙት ዘመናት ደፋሮች ሆነው ቢኖሩም በበለጸገ የጠረፍ ክልል በመኖራቸው መሥዋዕትነት ከፍለዋል። — 1 ነገሥት 22:1–3፤ 2 ነገሥት 15:29
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ታሪክ ላይ የተደረገ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት ዮፍታሔ ልጁን ሰውቷል የሚባለው ትክክል አለመሆኑን አረጋግጧል። በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2, ገጽ 27–28 ተመልከት።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የገሊላ ባሕር
ቤትሳን
ሬማት ዘገለዓድ
ኢያቢስ
ገለዓድ
ዮርዳኖስ ወንዝ
ሙት ባሕር
[ምንጭ]
Based on a map copyrighted by Pictorial Archive (Near Eastern History) Est. and Survey of Israel.
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.