ሥላሴ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነውን?
“የካቶሊክ እምነት ይህ ነው፣ ሥላሴ የሆነን አንድ አምላክና ሥላሴዎችን በአንድነት እናመልካለን . . . ስለዚህ አብ እግዚአብሔር ነው፣ ወልድ እግዚአብሔር ነው፣ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው። ይሁንና ሦስት አምላኮች ሳይሆኑ አንድ አምላክ ነው። ”
የሕዝበ ክርስትና ዋነኛ መሠረታዊ ትምህርት የሆነውን ሥላሴን የአትናቴዎስ እምነት በእነዚህ ቃላት ይገልጸዋል።a የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል ከሆንክ ይኸውም ካቶሊክ ወይም ፕሮቴስታንት ከሆንክ ይህ ልታምንበት የሚገባ ዋናው አስፈላጊ ትምህርት እንደሆነ ተነግሮህ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን መሠረተ ትምህርቱን ልታብራራ ትችላለህን? በሕዝበ ክርስትና ውስጥ አዋቂ ናቸው የሚባሉት እንኳ ሥላሴን መረዳት አለመቻላቸውን አምነዋል።
ታዲያ ለምን ያምኑበታል? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን መሠረተ ትምህርት ስለሚያስተምር ነውን? ሟቹ የአንግሊካን ጳጳስ ጆን ሮቢንሰን በብዙ ቅጂ በተሸጠው ኦነስት ቱ ጎድ (ከአምላክ እውነቱን አለመሸሸግ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ለዚህ ጥያቄ አመራማሪ የሆነ መልስ ሰጥተዋል። እንዲህ ሲሉ ጽፈው ነበር:-
“ስለ ኢየሱስ የተጋነነ አመለካከት ያለው ስብከትና ትምህርት በሰፊው ይሰጣል። ይህ ግን ከአዲስ ኪዳን በማስረጃ ሊረጋገጥ አይችልም። ኢየሱስ እግዚአብሔር ነበር፤ ይህም ስለሆነ ኢየሱስና እግዚአብሔር የሚሉት መጠሪያዎች በተወራራሽነት ይሠራሉ ይላል። ነገር ግን ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም የትም ቦታ አይገኝም። አዲስ ኪዳን ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቃል ነበር ይላል፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ ነበር ይላል፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ይላል፤ ነገር ግን ኢየሱስ እግዚአብሔር ነበር አይልም።”
ጆን ሮቢንሰን በአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበራቸው አቋም አወዛጋቢ ነበር። የሆነው ሆኖ “በአዲስ ኪዳን” ውስጥ “ኢየሱስ እግዚአብሔር ነበር” የሚል የትም ቦታ አናገኝም በማለታቸው ትክክል ነበሩን?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አንዳንዶች ይህንን ጥያቄ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” በሚሉት ዮሐንስ ወንጌሉን በከፈተባቸው ቃላት ይመልሱ ይሆናል። (ዮሐንስ 1:1) ታዲያ የአንግሊካኑ ጳጳስ ከተናገሩት ጋር አይጻረርምን? በእርግጥ አይጻረርም። ያለ ጥርጥር ጆን ሮቢንሰን እንደሚያውቁት አንዳንድ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ኪንግ ጀምስ ቨርሽን ጥቅሱን በዚህ መንገድ መተርጐሙን አይስማሙበትም። ለምን? ምክንያቱም በጥንቱ የግሪክኛ ጽሑፍ “ቃልም እግዚአብሔር ነበር” በሚለው አገላለጽ “እግዚአብሔር” የሚለውን ለማመልከት የገባው የግሪክኛ ቃል [በእንግሊዝኛው “ዘ” የሚለው] የተወሰነ መስተዓምር የለውም። ከዚያ ቀደም ብሎ ባለው “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” በሚለው አገላለጽ ላይ “እግዚአብሔር” የሚለውን የሚወክለው ቃል የተወሰነ መስተዓምር አለው። ይህም ሁለቱ ቃላት አንድ ዓይነት ትርጉም እንደሌላቸው ግልጽ ያደርገዋል።
ይህም በመሆኑ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ሐሳቡን ይበልጥ ግልጽ ሊያደርገው የሚችለውን ቅጽል በትርጉማቸው ውስጥ አስገብተዋል። ለምሳሌ አንዳንዶቹ ይህንን ጥቅስ “ቃልም መለኮታዊ ነበር” በማለት ተርጉመውታል። (አን አሜሪካን ትራንስሌሽን ስከንፊልድ ) ሞፋት የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሲተረጉም “ሎጎስም [ቃልም] መለኮታዊ ነበር” ይላል። ይሁን እንጂ “መለኮታዊ” የሚለው ቃል እዚህ ቦታ ላይ ለመግባት ከሁሉ የተሻለው ትርጉም እንዳልሆነ በመናገር ጆን ሮቢንሰንና የብሪታንያው የሥነ ጽሑፍ ተንታኝ ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን ዮሐንስ አጥብቆ ሊገልጽ የፈለገው ይህንን ቢሆን ኖሮ “መለኮታዊ” ለሚለው ቃል ቲኦስ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ሊጠቀም ይችል እንደነበር ጠቁመዋል። የአዲሲቱ ዓለም ትርጉምም “አምላክ [God]” ነበር የሚለው ቃል የተወሰነ መስተዓምር እንደሌለው በመረዳትና እንዲሁም በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱትን ትርጉሙን ይበልጥ ግልጽ የሚያደረጉትን ነጥቦች በመጨመር በእንግሊዝኛው ያልተወሰነ መስተዓምር ተጠቅሟል:- “ቃልም አምላክ (a god) ነበር”።
ኒው ኢንግሊሽ ባይብል የተባለ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ፕሮጄክት ዴሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ሲ ኤች ዶድ በዚህ አስተሳሰብ ላይ ያላቸውን አስተያየት ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል:- “‘የተሻለ ትርጉም የሚሆነው ቃልም አምላክ (a god) ነበር ’ የሚለው ነው። ቃል በቃል የተደረገ ትርጉም እንደመሆኑ የተሳሳተ ሊሆን አይችልም። ” ይሁን እንጂ ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ይህንን ጥቅስ በዚህ መንገድ አልተረጎመውም። ከዚያ ይልቅ ዮሐንስ 1:1ን እንዲህ እናነባለን:- “ነገሮች ሁሉ ሲጀምሩ ቃል አስቀድሞ ነበር። ቃል ከእግዚአብሔር ጋር ይኖር ነበር፤ እግዚአብሔር የሆነውንም ሁሉ ቃል እንዲሁ ነበር።” የትርጉም ኮሚቴው ቀለል ያለውን ትርጉም ለምን አልመረጠም? ፕሮፌሰር ዶድ ሲመልሱ እንዲህ ብለዋል:- “ተቀባይነት ያጣበት ምክንያት በወቅቱ ዮሐንስ ከነበረው አስተሳሰብ እንዲሁም ከመላው የክርስቲያን አስተሳሰብ ጋር ስለሚቃረን ነው።” — ቴክኒካል ፔፐርስ ፎር ዘ ባይብል ትራንስሌተር፤ ጥራዝ 28፣ ጥር 1977
ግልጽ የሆነው የቅዱሳን ጽሑፎች ሐሳብ
ኢየሱስ አምላክ [god] ነው፤ ሁሉን ከፈጠረው አምላክ [God] ጋር ግን አንድ አይደለም የሚለው ሐሳብ ከሐዋርያው ዮሐንስ እንዲሁም ከመላው ክርስቲያን አስተሳሰብ ጋር ተጻራሪ ነው ለማለት እንችላለንን? እስቲ ስለ ኢየሱስና ስለ አምላክ የሚናገሩትን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንመርምርና የአትናቴዎስ እምነት ከመቀመሩ በፊት የነበሩ ተንታኞች በጥቅሶቹ ላይ የሰጡትን አስተያየት እናያለን።
“ እኔና አብ አንድ ነን” — ዮሐንስ 10:30
ኖቫሽያን (ከ200–258 እዘአ የነበረ) በዚህ ላይ ያለውን አስተያየት ሲሰጥ እንዲህ ብሏል:- “‘ አንድ’ ነገር [b] ስለሆነ ያለው መናፍቃን ‘ አንድ’ አካል ብሎ እንዳልተናገረ ይረዱ። አንድ የሚለው ቃል በግዑዝ ፆታ ስለገባ የአካል አንድነትን ሳይሆን ያለውን የጋራ ስምምነት የሚያመለክት ነው። . . . ከዚህም በተጨማሪ አንድ ማለቱ ያለውን ስምምነት የፍርድ ተመሳሳይነት እንዲሁም የፍቅር ትስስሩን የሚያሳይ ሲሆን በምክንያታዊነት ስንረዳውም አብና ወልድ በስምምነት በፍቅርም በመውደድም አንድ ናቸው።” — ትሪቲስ ኮንስርነንግ ዘ ትሪኒቲ፣ ምዕራፍ 27
“ ከእኔ አብ ይበልጣል” — ዮሐንስ 14:28
ኢረንየስ (ከ130–200 እዘአ የኖረ) እንዲህ ብሏል:- “በእርሱ [በክርስቶስ] አማካኝነት አብ ከሁሉም ነገር የበላይ እንደሆነ እንማራለን። ምክንያቱም ‘ከእኔ አብ ይበልጣል’ ብሏል። ስለዚህ አብ በእውቀት የላቀ ለመሆኑ ጌታችን አሳውቋል።” — አጌይንስት ሄረሲስ። (ፀረ መናፍቅነት )፣ ጥራዝ 2፣ ምዕራፍ 28.8
“ የዘላለም ሕይወትም ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው።” — ዮሐንስ 17:3 1980 ትርጉም
የአሌክሳንድሪያው ክሊመንት (ከ150–215 ገደማ እዘአ የኖረ) “የዘላማዊ ነገሮች ሰጪ የሆነውን ዘላለማዊ አምላክ ማወቅና ከሁሉ በፊት የነበረውንና ከፍተኛውን እንዲሁም አንዱንና ጥሩውን አምላክ በእውቀትና በጥበብ ማግኘት። . . . እውነተኛውን ሕይወት ለመኖር የፈለገ ሁሉ በመጀመሪያ ‘ወልድ ካልገለጠለት በቀር’ ሊታወቅ የማይችለውን እንዲያውቅ ተመክሯል። (ማቴዎስ 11:27) ከዚያ ቀጥሎ ማወቅ ያለበት ከእርሱ በኋላ ያለውን አዳኝ ታላቅነት ነው። — ሁ ኢዝ ዘ ሪች ማን ዛት ሻል ቢ ሴቭድ? (የሚድነው ሀብታም ማን ነው?) ክፍል 7, 8
“ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።” — ኤፌሶን 4:6
ኢረንየስ እንዲህ ብሏል:- “እንግዲያው አንድ አምላክ አብ ከሁሉ በላይ የሆነና በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉም የሚኖር ነው ብሏል። በእርግጥም አብ ከሁሉም በላይ ነው፤ እንዲሁም የክርስቶስ ራስ ነው።” — አጌይነስት ሄረሲስ፣ ጥራዝ 5፣ ምዕራፍ 18. 2
እነዚህ የጥንት ጸሐፊዎች እነዚህን ጥቅሶች አብ ከማንኛውም ነገርና ኢየሱስን ጨምሮ ከሁሉም በላይ ያለ የመጨረሻው ከፍተኛ አካል መሆኑን እንደሚያስረዱ በግልጽ ተረድተዋቸዋል። የሰጧቸው አስተያየቶች በሥላሴ ያምኑ እንደነበር ምንም ፍንጭ አይሰጡም።
መንፈስ ቅዱስ እውነትን ሁሉ ይገልጻል
ኢየሱስ ሞቶ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ እንደ ረዳት ሆኖ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሰጣቸው ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል ቃል ገባ:- “ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ . . . የሚመጣውንም ይነግራችኋል።” — ዮሐንስ 14:16, 17፤ 15:26፤ 16:13
ከኢየሱስ ሞት በኋላ ይህ የተስፋ ቃል ተፈጽሟል። በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ አዳዲስ መሠረታዊ ትምህርቶች ለክርስቲያን ጉባኤ ይበልጥ እንደተብራሩለት ወይም እንደተገለጹለት መጽሐፍ ቅዱስ መዝግቧል። እነዚህ አዳዲስ ትምህርቶች በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ሁለተኛ ክፍል በሆኑት ማለትም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ወይም ‘በአዲስ ኪዳን” መጻሕፍት ውስጥ ተጽፈዋል። በዚህ አዲስ የዕውቀት ብርሃን ውስጥ ስለ ሥላሴ መኖር የተገለጠ ነገር ነበርን? አልነበረም። መንፈስ ቅዱስ ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ የገለጠው ከዚህ የተለየ ነገር ነበር።
ለምሳሌ ያህል በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ተሰብስበው በነበሩት ደቀ መዛሙርት ላይ መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ በውጭ ተሰብስበው ለነበሩት ሰዎች ስለ ኢየሱስ መሰከረላቸው። ታዲያ ስለ ሥላሴ ተናግሮ ነበርን? እስቲ የተናገራቸውን አንዳንድ ዓረፍተ ነገሮች ልብ በልና ራስህ ፍረድ:- “ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ።” “ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሳው ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን።” “ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም አደረገው።” (ሥራ 2:22, 32, 36) እነዚህ ቃሎች ሥላሴን ከማስተማር ይልቅ ኢየሱስ ለአባቱ ያለውን ተገዢነት ይኸውም የአምላክን ፈቃድ ለማስፈጸም እንደ መሳሪያ ሆኖ ማገልገሉን የሚያጎሉ ናቸው።
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አንድ ሌላ ታማኝ ክርስቲያን ስለ ኢየሱስ ተናግሯል። እስጢፋኖስ ለቀረበበት ክስ መልስ እንዲሰጥ ወደ ሳንሀድሪን ሸንጎ አምጥተውት ነበር። በዚያ ፋንታ እስጢፋኖስ የሁኔታውን አቅጣጫ በመቀየር የእርሱ ከሳሾች እንደ አባቶቻቸው ዓመፀኞች እንደሆኑ ተናገረ። በመጨረሻም የተመዘገበው ታሪክ እንዲህ ይላል:- “መንፈስ ቅዱስም ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኩር ብሎ ሲመለከት የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም በይሖዋ ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ።” (ሥራ 7:55, 56) መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን ከአብ ጋር እኩል እንደሆነ ሦስት ራስ ያለው ሥላሴ ክፍል አድርጎ ሳይሆን በአምላክ ቀኝ እንደቆመ “የሰው ልጅ” አድርጎ የገለጸው ለምንድን ነው? በግልጽ እንደሚታየው እስጢፋኖስ የሥላሴ ሐሳቡም እንኳ አልነበረውም።
ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች ወደ ቆርኔሌዎስ ይዞ በሄደ ጊዜ ስለ ሥላሴ መሠረተ ትምህርት ለመግለጽ ሌላ ተጨማሪ አጋጣሚ ነበር። ታዲያ ምን ሆነ? ኢየሱስ “የሁሉ ጌታ” መሆኑን ጴጥሮስ ገለጸ። ነገር ግን ይህ ጌትነት የተገኘው ከሌላ ምንጭ መሆኑን በማብራራት ቀጠለ። ኢየሱስ “በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ” ነበር። ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ አባቱ ለተከታዮቹ ‘ይገለጥ ዘንድ ሰጠው [ፈቀደለት]’። መንፈስ ቅዱስስ ምን አደረገ? በዚህ ውይይት ውስጥ መንፈስ ቅዱስም ተጠቅሷል፤ ነገር ግን እንደ ሦስተኛ የሥላሴ አካል ተደርጎ አይደለም። ከዚህ ይልቅ “እግዚአብሔር [ኢየሱስን] በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው።” እንግዲያው መንፈስ ቅዱስ አካል ሳይሆን በጥቅሱ ላይ እንደተጠቀሰው “ኃይል”፣ አካል የሌለው ነገር መሆኑ ታይቷል። (ሥራ 10:36, 38, 40, 42) መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ብትመረምር መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ አካል ያለው ሳይሆን ሰዎችን ሊሞላ የሚችል፣ የሚገፋፋቸውና ፊታቸው በደስታ እንዲበራ የሚያደርግ አንቀሳቃሽ ኃይል ለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃዎች ታገኛለህ።
በመጨረሻም የሥላሴ ትምህርት የእውነት መሠረተ ትምህርት ቢሆን ኖሮ ሐዋርያው ጳውሎስ ለአቴናውያን በሚሰብክበት ጊዜ ስለዚሁ ለማስተማር ጥሩ አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። በንግግሩ ‘ለማይታወቅ አምላክ” ብለው ካዘጋጁት መሠዊያ ጋር አያይዞ እንዲህ አለ:- “እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ።” ስለ ሥላሴ ነገራቸውን? በፍጹም። “ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነው” በማለት ገለጸላቸው። ስለ ኢየሱስስ ምን አላቸው? “[አምላክ] ቀን ቀጥሮአልና፣ ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በፅድቅ ሊፈርድ አለው።” (ሥራ 17:23, 24, 31) እዚህ ላይ ስለ ሥላሴ የተሰጠ ምንም ፍንጭ የለም።
እንዲያውም ጳውሎስ ኢየሱስና አባቱ እኩል የሥላሴ ክፍል ሊሆኑ እንደማይችሉ የሚያስረዳ ስለ አምላክ ዓላማ የገለጸው አንድ ነገር ነበር። እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና፤ ነገር ግን:- ሁሉ ተገዝቶአል ሲል፣ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።” (1 ቆሮንቶስ 15:27, 28) እንግዲያው አምላክ አሁንም ኢየሱስን ጨምሮ ከሁሉም በላይ ነው ማለት ነው?
ታዲያ ሥላሴ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነውን? አይደለም። ጆን ሮቢንሰን ትክክል ነበሩ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። እንዲሁም “የክርስቲያን አስተሳሰብ” ክፍልም አይደለም። ይህንን ለአምልኮህ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አድርገህ ትመለከተዋለህን? ልትመለከተው ይገባሃል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “የዘላለም ሕይወትም ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ነው።” (ዮሐንስ 17:3 የ1980 ትርጉም ) ለአምላክ የምንሰጠውን አምልኮ በቁም ነገር ከያዝነው እሱን ራሱን በገለጠልን መንገድ እንደ እሱነቱ ማወቃችን ለሕይወታችን አስፈላጊ ነው። ይሖዋን ‘በእውነትና በመንፈስ’ ከሚያመልኩት እውነተኛ አምላኪዎች መካከል ነን ለማለት የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። — ዮሐንስ 4:23
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በ1907 በታተመው ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ ጥራዝ 2 ገጽ 33 መሠረት
b ኖቫሽያን እዚህ ለማለት የፈለገው “አንድ” ለሚለው ቃል የገባው ቃል ግዑዝ ፆታ መሆኑን ነው። ስለዚህ ትክክለኛ ትርጉሙ “አንድ ነገር” የሚል ነው። “አንድ” የሚለው ግሪክኛ ቃል ልክ በዚሁ መንገድ ከገባበት ከዮሐንስ 17:21 ጋር አወዳድር። አዲሱ የካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ (የ1967 እትም) ኖቫሽያን የጻፈውን ደ ትሪኒታተ የተባለውን ጽሑፍ ጠቅለል ባለ መልኩ ይቀበለዋል። እርግጥ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ እንደ መለኰታዊ አካል ተደርጎ ያልቀረበ መሆኑን ጭምር ጠቅሷል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቅዱሳን ጽሑፎች ግልጽ ሐሳብ ኢየሱስና አባቱ አንድ አምላክ ያለመሆናቸውን በግልጽ ያሳያል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደነበረ መንፈስ ቅዱስ ያልገለጸው ለምን ነበር?