የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 11/15 ገጽ 4-7
  • “የመጨረሻው ጠላት” ድል ይደረጋል!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “የመጨረሻው ጠላት” ድል ይደረጋል!
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጠላትህን እወቅ
  • የምታፈቅረው ሰው ሲሞት የሚገጥምህን ኀዘን መቋቋም
  • በሞት ላይ ድል ማግኘት
  • የሞት መውጊያ ይወገዳል
    ንቁ!—1993
  • “ሞት በድል ተዋጠ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ጠላታችን ሞት የሚጠፋው እንዴት ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2019
  • የትዳር ጓደኛ ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 11/15 ገጽ 4-7

“የመጨረሻው ጠላት” ድል ይደረጋል!

ትንሽ ልጅ በነበርክበት ጊዜ ጨለማን ፈርተህ ይሆናል። ፍርሃት የሚለቅቁ ተረቶችና አንዳንድ አስፈሪ ነገሮችን ስላደረጉ ሰዎች ስትሰማ በጭንቀት ተሞልተህ ሊሆን ይችላል። እንቅልፍ እስኪወስድህ ድረስ እናትህ ወይም አባትህ መብራት አብርተው ሲተዉልህ መንፈስህ ምን ያህል ይረጋጋ ነበር!

በተመሳሳይም ሞት ብዙዎችን ያስፈራቸዋል። ሆኖም አስፈሪ ሊሆንባቸው አይገባም። ለምን? ሞት ራሱ ምን እንደሆነ ማወቃችን እንዳንፈራ ሊያደርገን ይገባል።

ጠላትህን እወቅ

የጥንቷ እስራኤል ጥበበኛ ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም” በማለት አስታውቋል። (መክብብ 9:​5) በራስህ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው በዚህ በመለኮት አነሣሽነት የተነገረ ቃል መሠረት ሞት በቀላል አነጋገር የሕይወት ተቃራኒ ነው። ሙታን ምንም የሚያውቁት ነገር የለም።

ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ስለ ሞት ሲናገር ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ “ሞት ሆይ፣ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፣ ድል መንሣትህ የት አለ?” በማለት ጻፈ። ሞትን የሚያስከትለው መውጊያ ምንድን ነው? ጳውሎስ “የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው” በማለት መልሱን ይሰጣል። (1 ቆሮንቶስ 15:​55, 56፤ ሆሴዕ 13:​14) ይህ የሚገድል መውጊያ ምንጩ ምንድን ነው? በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ ሌላ ቦታ ላይ ጳውሎስ “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ” በማለት ገልጿል። (ሮሜ 5:​12) ሐዋርያው “ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ” ባለ ጊዜ ስለዚያ “አንድ ሰው” ማንነት በግልጽ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 15:​22) በመጀመሪያው ቅድመ አያታችን በአዳም ዓመፅ ምክንያት ሁላችንም ለሞት መውጊያ የተጋለጥን ሆንን። — ዘፍጥረት 3:​1–19

ጥሩ ጤንነትና ፍቅር የሞላበት ቤተሰብ ይዘን አስደሳች በሆነ ስፍራ ብንኖር ማንኛችንም ለመሞት አንመርጥም ነበር። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው ‘ጊዜና አጋጣሚ’ ሕይወታችንን ሊያሳጣን ይችላል። (መክብብ 9:​11) እንዲያውም በሕይወታችን ላይ ነገ ምን እንደሚያጋጥመን አናውቅም። (ያዕቆብ 4:​14) እርግጠኛ የሆነ አንድ ነገር ቢኖር ሁላችንም ኃጢአትንና ሞትን መውረሳችን ነው። ስለዚህ ሞት ጠላታችን ሆኖ ያሳድደናል፤ በኋላም ያጠቃ⁠ናል።

የምታፈቅረው ሰው ሲሞት የሚገጥምህን ኀዘን መቋቋም

ሞት የምናፈቅረውን ሰው ሲነጥቅብን ጠላት መሆኑ ይበልጥ ይሰማናል። አንዲት ለመሞት ስታጣጥር የነበረች ሚስት “ለአንተ ይብስብሃል” በማለት ለባሏ ተናገረች። እንደዚህ ብላ ለመናገር የቻለችው ለምን ነበር? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ” ስለሚል ነው። (መክብብ 9:​10) ሙታን ምንም ዓይነት ሥቃይ አይደርስባቸውም። የኀዘኑ ጫና የሚወድቀው ግን በቀሪዎቹ ዘመዶችና ጓደኞች ላይ ነው። እንደዚህ የመሰለው ኀዘን ሲያጋጥም ማድረግ የምንችለው ነገር ይኖራልን?

የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ የሚያጽናኑ ቃሎችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል የመጽናናት ምንጭ ሊሆኑ ከሚችሉት መካከል አንዱ የመዝሙር መጽሐፍን ማንበብና በተነበበው ላይ ማሰላሰል ነው። “የመዳናችን እውነተኛ አምላክ፣ ሸክማችንን በየቀኑ የሚሸከምልን ይሖዋ የተባረከ ይሁን” እንደሚሉት ያሉት ቃላት በጣም ያጽናናሉ። — መዝሙር 68:​19 አዓት

ሌላው የመጽናናት ምንጭ የክርስቲያን ጉባኤ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ጻፈ:- “በእውነት ባልቴቶች የሆኑትን ባልቴቶች አክብር። ማንም ባልቴት ግን [በቁሳዊ መንገድ ሊረዷት የሚችሉ] ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፣ እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፣ ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና። ባልቴት በመዝገብ ብትጻፍ ዕድሜዋ ከስድሳ ዓመት እንዳያንስ፣ የአንድም ባል ሚስት የነበረች እንድትሆን ያስፈልጋል፤ ልጆችን በማሳደግ እንግዶችንም በመቀበል፣ የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፣ የተጨነቁትንም በመርዳት በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፣ ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል።” (1 ጢሞቴዎስ 5:​3, 4, 9, 10) ዛሬም በተመሳሳይ የይሖዋ ምስክሮች እንደዚህ ያሉትን አማኞች ይረዳሉ ያጽናናሉም።

አብዛኛውን ጊዜ በኀዘን የተጠቃው ሰው ስሜታዊ ማስተካከያ ማድረግ ይከብደዋል። ሚስቱ ሁለት ዓመት ቀድማው የሞተችበት አንድ ሰው “ሚስቴን በጣም እወዳት ነበር። በሕይወቴ ውስጥ እንደዚህ ያዘንኩበት ወቅት የለም፤ ይህን ኀዘን መቋቋም በጣም አስቸግሮኛል” በማለት ጽፎ ነበር። ለተወሰነ ጊዜ አግብቶ የቆየ አንድ ሰው ካሉት ሰብአዊ ዝምድናዎች ሁሉ የሚበልጥ ቅርበት ባለው በዚህ ዝምድና ከእሱ (ወይም ከእርሷ) ጋር ኑሮን ተካፍሏል። የትዳር ጓደኛ ሲሞት በሕይወት የቀረው ጓደኛ ታላቅ ኀዘን ይሰማዋል። እንደዚህ ያለው ሰው ለእርዳታ ወደ ማን ዘወር ማለት ይችላል?

እንደዚህ ባሉት ሁኔታዎች ውስጥ ጥሩ ክርስቲያናዊ ጓደኞች የሚገነቡ ሊሆኑ ይችላሉ። “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል” በማለት ጥበብ የተሞላበት ምሳሌ ይናገራል። (ምሳሌ 17:​17) ባሏ የሞተባት ሴት ወይም ሚስቱ የሞተችበት ሰው ጥሩ ድጋፍ የሚሰጡ ባልንጀሮችና ረዳቶች ያስፈልጓቸዋል። እንደዚያ ማድረጉ ሊያስለቅሰው ቢችልም ጥበበኛ ጓደኞች ኀዘንተኛውን እንዲያወራ ያበረታቱታል። ምናልባትም የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣት ምን ያህል አሳዛኝና አስከፊ እንደሆነ ተሞክሮ ያለው ሰው ደግነት የተሞላበት እርዳታ ሊሰጥ ይችላል። “የተጨነቁትን ነፍሳት በሚያጽናና ቃል ተናገሯቸው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይመክራል። (1 ተሰሎንቄ 5:​14 አዓት) ባሏ የሞተባት ሴትና ሚስቱ የሞተችበት ሰው የትዳር ጓደኛቸውን ሲያስታውሱ ሆዳቸው እንደሚባባ አስታውስ። ስለዚህ ኀዘንተኛው ወደ ሌሎች በጣም መጠጋት ያለበት ሁሉም ንጹሕ ጠባይን ማሳየት በሚችሉበት ሁኔታ መሆን ይገባዋል። — 1 ጴጥሮስ 2:​12

እርዳታ የሚያስፈልገኝ እኔ ነኝ ብለው ለሚያስቡ ቀላል ሥራ ባይሆንም ሌሎችን ለመርዳት ራስን ማስጠመድ ሞት ላስከተለው ሥቃይ ፍቱን መድኃኒት ነው። እዚህ ላይ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ትልቅ ድርሻ አለው። ሳይቆጥቡ ለሌሎች አንዳንድ ነገሮችን መሥራት ኀዘንና ትካዜን ለማራቅ ይረዳል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [ደስተኛ አዓት] ነው” ብሏል። — ሥራ 20:​35

በሞት ላይ ድል ማግኘት

ንብ ከነደፈ በጣም ያሳምማል፣ ሊገድልም ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን ቆዳህ ውስጥ ጠልቆ የገባውን ሰንኮፍ ነቅሎ ማውጣት ፋታ ለማግኘት ይረዳል። ነገር ግን ሞትን ከሚያስከትለው መውጊያ ለመላቀቅ ምን ተስፋ አለ?

ኃጢአት ሞትን የሚያስከትል መውጊያ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ ጳውሎስ “ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 15:​57) በሞት ላይ የሚገኘው ድል ከክርስቶስ ጋር የተዛመደው እንዴት ነው? ኢየሱስ ስለ ራሱ “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ባለ ጊዜ ከሞት መዳን የሚቻለው በእርሱ አማካኝነት እንደሆነ ማመልከቱ ነበር። (ማቴዎስ 20:​28) አዎን፣ በአምላክ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስና ይሖዋ በእርሱ በኩል ባዘጋጀው የቤዛ ዝግጅት ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ሁሉ ከአዳም የተወረሰው ሞት ለሁልጊዜው አንቀላፍተው እንዲቀጥሉ አይተዋቸውም። — ዮሐንስ 3:⁠16

“በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ” በማለት ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ልብን በደስታ ሞቅ ያደርጋሉ። — ዮሐንስ 5:​28, 29

የአምላክ ነቢይ የነበረው ኢሳይያስ ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት “ሞትን [ይሖዋ አምላክ] ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል” በማለት ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 25:​8) እንደገናም በራእይ 21:​4 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ “[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” በማለት ይህንን አስደሳች የወደፊት ጊዜ ይገልጸዋል። በሞት ላንቀላፉት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው በዚህ ተስፋ በመጠናከር ኀዘን የደረሰባቸው ሰዎች “ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ” ማዘን አያስፈልጋቸውም። — 1 ተሰሎንቄ 4:​13

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጸው አምላክ ለሰው ዘሮች ያዘጋጀላቸውን የወደፊት ጊዜ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። በቅርብ የሚመጣው “ታላቁ መከራ” አሁን ያለውን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ያጠፋል። (ራእይ 7:​14) የሐሰት ሃይማኖትን የሚከተሉ ይጠፋሉ። ለረሀብና ለጦርነት አስተዋጽኦ ያደረጉት ስግብግብ የፖለቲካና የንግድ ድርጅቶች ከእንግዲህ ወዲያ አይኖሩም። ቀጥሎ ኢየሱስ ክርስቶስ ለብዙ ሰዎች መሞት ምክንያት የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስን ያስረዋል። ከዚያም ክርስቶስ ለሰው ዘሮች የከፈለውን ቤዛ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግበት የሺህ ዓመት ግዛቱን ይጀምራል። በተስፋ ሲጠበቅ በነበረው ትንሣኤ አማካኝነት ሙታን እንደገና በሕይወት ለመኖር ተመልሰው ይመጣሉ። እንዲሁም ከአምላክ ቃል የሚመጣው ብርሃን ደምቆ ስለሚበራ የሰው ልጆች ጠላት ስለሆነው ሞት የነበሩት አጉል ልማዶች ሁሉ ይጠፋሉ። በሕይወት ያሉት ሁሉ የአምላክን መንገዶች ለመማርና ከእርሱ የጽድቅ ደረጃዎች ጋር ለመስማማት አጋጣሚው ይከፈትላቸዋል።⁠— ምሳሌ 4:​18፤ ሥራ 24:​15፤ ዕብራውያን 2:​14, 15፤ ራእይ 18:​4–8፤ 19:​19–21፤ 20:​1–3

ጳውሎስ “በኋላም፣ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ፣ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው” በማለት ተናገረ። (1 ቆሮንቶስ 15:​24–26) በአዳም ኃጢአት የመጣ ማንኛውም የአካል ጉድለት ይወገዳል። የመጨረሻ ፈተና ሲመጣ አምላክን የሚያፈቅሩ ሁሉ የታመኑ በመሆን ድል ይነሣሉ። (ራእይ 20:​4–10) ፍጹም እንዲሆኑ ስለሚደረጉ እነዚህ ታዛዥ ሰዎች ለሰባ ወይም ለአንድ መቶ አሥር ዓመታት ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ይኖራሉ። በሚያፈቅረው ልጁ በኩል ከአምላክ የተሰጠ እንዴት ያለ ሥጦታ ነው! — ሮሜ 6:​23

ነገሩ እንዲህ ከሆነ ለምን ያህል ጊዜ መኖር ትችላለህ? ሕይወትህ ለዘላለም ሊራዘም ይችላል። በዚህ ዓለም “የፍጻሜ ዘመን” እንደምትኖረው ሳይሆን ፈጽሞ ላትሞት ትችላለህ። (ዳንኤል 12:​4፤ ዮሐንስ 11:​25, 26፤ 17:​3) መለኮታዊውን ፈቃድ ካደረግህ ተስፋ በተገባልን የአምላክ አዲስ ዓለም ልትኖር ትችላለህ። — 2 ጴጥሮስ 3:​13

ይሁን እንጂ በዕድሜ የገፋህ ከሆንክ ልትሞት እንደምትችል ያለውን እውነተኛ ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልግሃል። የትንሣኤ ተስፋ ደስታ እንደሚያመጣልህ ምንም አያጠራጥርም። ነገር ግን በዚያ አዲስ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ይሖዋ ስለ ቤተሰብ ዝግጅት ምን ዓላማ ሊኖረው እንደሚችል ያሳስብህ ይሆናል። እንደዚህ ያለው ነገር እንዲያስጨንቅህ አትፍቀድ። ይሖዋ ለዘላለም ለእርሱ ታማኝ ስለሚሆኑለት ሰዎች ዘላቂ ደስታ ያስባል።

አስጨናቂ የሆኑት እነዚህ የሰይጣን ክፉ የነገሮች ሥርዓት “የመጨረሻ ቀኖች” ወደማለቂያቸው እየተቃረቡ ሲሄዱ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን በማገልገል የሚገኘውን ደስታ የሞት ፍርሃት እንዲያጠፋብህ አትፍቀድ። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) የምታፈቅረውን ሰው በሞት አጥተህ ከሆነ ሞት ጊዜያዊ መሆኑን በአእምሮህ ያዝና በዚህ እውቀት ተጽናና። (ራእይ 20:​13, 14) በትንሣኤ ተስፋ ተማመን። ከዚያም ታላቁን መከራ በሕይወት በማለፍም ይሁን በትንሣኤ አማካኝነት ወደ አዲሱ ዓለም ከገባህ የመጨረሻው ጠላት የሚሻረው ሞት እንደሆነ በተሰጠው ዋስትና እርግጠኛ ሁን። — ራእይ 7:​9, 14

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መልካም ክርስቲያናዊ ባልንጀሮች ያዘነውን ሰው በመንፈሳዊ ሊገነቡት ይችላሉ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በምናፈቅረው ሰው ሞት ምክንያት የደረሰብን ኀዘን ራስን ሌሎችን በመርዳቱ ሥራ በማስጠመድ ሊቃለል ይችላል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ