የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 11/15 ገጽ 8-11
  • ከአቋማቸው ፍንክች የማለት ሐሳብ አልነበራቸውም!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከአቋማቸው ፍንክች የማለት ሐሳብ አልነበራቸውም!
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ያለ ምክንያት ተጠሉ
  • የሮም መንግሥት ስደቱን አፋፋመው
  • በግልጽ የሚታይ ንጽጽር
  • ምስክርነት መስጠቱ ያስከፈለው ዋጋ
  • በቁጥር መጨመራቸው የስደቱን መጠን ከፍ አደረገው
  • ሽልማቱ
  • የጥንቱ ክርስትናና ፖለቲካዊ መንግሥት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖችና ዓለም
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • በእምነታቸው የተጠሉ ሰዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • መጽሐፍ ቅዱስ—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ፣ ክፍል 5
    ንቁ!—2012
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 11/15 ገጽ 8-11

ከአቋማቸው ፍንክች የማለት ሐሳብ አልነበራቸውም!

የይሖዋ እጅ ከመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ጋር ነበረ። (ሥራ 11:​21) በአምላክ እርዳታ ከአቋማቸው ፍንክች ሳይሉ ትክክለኛውን መንገድ ተከትለዋል። በተጨማሪም የከረረ ጥላቻ ይባስ ብሎም የመረረ ስደት የደረሰባቸው መሆኑ የታወቀ ታሪካዊ ሐቅ ነው።

የመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ታማኝ ተከታዮች ንጹሕ አቋም ማንም የሚያውቀው ነው። ሕይወታቸውን ቢያሳጣቸውም እንኳ ከእምነታቸው አልወላወሉም። ነገር ግን እንደዚህ ያለ ጭካኔ የደረሰባቸው ለምንድን ነው?

ያለ ምክንያት ተጠሉ

ኢየሱስን በመምሰል እውነተኛ ክርስቲያኖችም ይህ ዓለም ባለው ምኞትና እምነት አልተካፈሉም። (1 ዮሐንስ 4:​4–6) ከዚህም በላይ የክርስትና እድገት “በጣም ፈጣንና ውጤታማነቱም በግልጽ የሚታይ ስለነበር [ከሮም ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት] ጋር መጋጨታቸው የማይቀር ነገር ነበር” በማለት ታሪክ ጸሐፊው ኤድሞን ዲ ፕረሳንሰ ጠቅሰዋል።

ኢየሱስ በአንድ ወቅት “በከንቱ ጠሉኝ” ተብሎ የተነገረውን ትንቢታዊ መዝሙር ለራሱ እንደሚሠራ አድርጎ ተጠቅሞበታል። (ዮሐንስ 15:​25፤ መዝሙር 69:​4) ይህንን ለደቀ መዛሙርቱ ከመንገሩ በፊት “ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዷችኋል” በማለት አስጠንቅቋቸው ነበር። (ዮሐንስ 15:​20) የኢየሱስን ፈለግ መከተሉ ቀላል ላይሆን ይችላል። በአንድ በኩል በአይሁዳውያን መካከል ያሉት የሃይማኖት መሪዎች አይሁዳውያን የሆኑትን የኢየሱስ ተከታዮች ከአይሁድ እምነት የተገነጠሉ ከሀዲዎች አድርገው ሊመለከቷቸው ነው። የኢየሱስ ተከታዮች ስለ እርሱ ፈጽሞ እንዳይናገሩ በተከለከሉ ጊዜ ግን ትእዛዙን ለመቀበልና በዚህም ምክንያት ከእምነታቸው ለመወላወል እምቢ ብለዋል። — ሥራ 4:​17–20፤ 5:​27–32

ከ33 እዘአ ትንሽ ዘግየት ብሎ ለአይሁድ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በተሰጠው ምስክርነት ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ “በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል” የሚል ክስ ቀረበበት። ክሱ ሁሉ መሠረተ ቢስ ቢሆንም በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት ተፈረደበት። ከዚህም የተነሣ “በኢየሩሳሌም ባለች ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ፤ ሁሉም ከሐዋርያትም በቀር ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ አገሮች ተበተኑ።” (ሥራ 6:​11, 13፤ 8:​1) ብዙዎች ታሠሩ።

አይሁዳውያኑ የኢየሱስን ተከታዮች “በቃላት ሊገለጽ በማይችል ጥላቻ” ያሳድዷቸው ነበር በማለት ክርስቲያኒቲ ኤንድ ዘ ሮማን ኤምፓየር (ክርስትና እና የሮማ ግዛት) የተባለው መጽሐፍ ተናግሯል። የሮማ መንግሥት ክርስቲያኖችን ለመጠበቅ ሲባል እርምጃ ለመውሰድ ተገዶ ነበር። ለምሳሌ የሮማ ወታደሮች ሐዋርያው ጳውሎስን አይሁዳውያን ሊገድሉት ሲሉ አስጥለውታል። (ሥራ 21:​26–36) ሆኖም በክርስቲያኖችና በሮማ መንግሥት መካከል የነበረው ግንኙነት ከችግር ነፃ አልነበረም።

የሮም መንግሥት ስደቱን አፋፋመው

እስጢፋኖስ ከሞተ ዘጠኝ ዓመት ገደማ ቆይቶ የሮማው ገዥ ሄሮድስ አግሪጳ ቀዳማዊ አይሁዶችን ደስ ለማሰኘት ፈልጎ ያዕቆብን ገደለው። (ሥራ 12:​1–3) በዚያ ወቅት በክርስቶስ ማመን እስከ ሮም ድረስ ተስፋፍቶ ነበር። (ሥራ 2:​10) በ64 እዘአ የዚያች ከተማ አብዛኛው ክፍል በእሳት ተቃጠለ። ወዲያውኑ ለከተማይቱ መቃጠል ተጠያቂው ኔሮ ነው እየተባለ የሚናፈሰውን ወሬ ለማፈን በማሰብ ለከተማይቱ ጥፋት ተጠያቂዎቹ ክርስቲያኖች ናቸው በማለት አሠቃቂ ስደት አደረሰባቸው። ከተማይቱን ያቃጠላት ይበልጥ ክብራማ በሆነ መንገድ እንደገና ሊሠራት በማሰብና በኋላም በስሙ ኔሮፖሊስ ብሎ ሊሰይማት ስለፈለገ ይሆንን? ወይስ ለክርስቲያኖች ባላት ጥላቻ የታወቀችው ወደ ይሁዲነት የተለወጠችው ሚስቱ ንግሥት ፖፓይ እነሱን እንዲከስ ስለገፋፋችው ነው? ተመራማሪዎች እርግጠኞች ባይሆኑም ያስከተለው ጉዳት ግን በጣም አስፈሪ ነበር።

ሮማዊው ታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ ሲጽፍ “በግድያቸው ላይ ይቀለድ ነበር። የአራዊት ቆዳ ካለበሷቸው በኋላ [ክርስቲያኖቹ] በውሾች ተቦጫጭቀው እንዲሞቱ ይደረጉ ነበር። በመስቀል ላይ ይቸነክሯቸው ነበር። ቀኑ ሲያልፍ እንደ መብራት እንዲያገለግሉ ነዳጅ ይለቀቅባቸውና በእሳት ይቃጠሉ ነበር” ብሏል። የንጉሠ ነገሥቱ የአትክልት ቦታ ብርሃን እንዲያገኝ ሰብአዊ ችቦዎች ተቀጣጥለው ነደዱ። የክርስቲያኖች ወዳጅ ያልነበረው ታሲተስ ጨምሮ “ለሕዝቡ ጥቅም ሳይሆን ከአንድ ሰው [ማለትም ከኔሮ] ጭካኔ የተነሣ እንዲጠፉ ሲደረጉና ወንጀለኞች ናችሁ ተብለው መቀጣጫ እንዲሆኑ ሲፈረድባቸው የሰዉን ኀዘኔታና ርኅራኄ ቀሰቀሰው” በማለት ጻፈ።

በግልጽ የሚታይ ንጽጽር

ለሮም መጥፋት ተጠያቂዎች ናችሁ ብሎ ክርስቲያኖችን መክሰስ ለኔሮ ዓላማ ቢስማማም የሥራ እንቅስቃሴያቸውን ግን አላገደውም ወይም በአገሪቱ ውስጥ የክርስትናን ሃይማኖት አልከለከለም። ታዲያ ሮማውያን የክርስቲያኖችን መሰደድ የሚደግፉት ለምንድን ነው? ምክንያቱም “ትንሹ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ለአምልኮቱ ባለው ቅንዓትና በጨዋነቱ ተድላ ወዳድ የነበረውን አረመኔ ዓለም በአቋሙ ኮንኖት ስለነበረ ነው” በማለት ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት ተናግረዋል። በክርስትናና በሮማ ግላዲያቶሪያል ትርኢት ላይ በሚቀርበው ደም አፍሳሽነት መካከል ያለው ንጽጽር በጣም ከፍተኛ ነው። ሮማውያን ክርስቲያኖችን ዳግመኛ ላለማየትና ከሕሊና ሥቃይ ለማረፍ የሚያስችል ሊታለፍ የማይገባ አጋጣሚ መጣላቸው።

የዓለም ኃያል እንደመሆኑ መጠን የሮም መንግሥት ለምንም ኃይል የማይበገር ይመስል ነበር። ሮማውያን ወታደራዊ ልዕልናቸውን የተቀዳጁበት አንዱ ምክንያት ሁሉንም አማልክት በማምለካቸው እንደሆነ አድርገው ያምኑ ነበር። ስለዚህ ክርስቲያኖች በአንድ አምላክ ብቻ ጥብቅ እምነት መያዛቸውና ሌሎች አማልክትን፣ የንጉሠ ነገሥቱን አምልኮ ጭምር መቃወማቸውን ሊረዱት አልቻሉም ነበር። የሮም መንግሥት ክርስትናን የንጉሠ ነገሥቱ ግዛት የተመሠረተበትን ዋና መሠረት እንዲናቅ የሚያደርግ ኃይል እንደሆነ አድርጎ ቢመለከተው ሊያስደንቀን አይገባም።

ምስክርነት መስጠቱ ያስከፈለው ዋጋ

ወደ አንደኛው መቶ ዘመን እዘአ ማለቂያ አካባቢ ሐዋርያው ዮሐንስ “ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር” በመሆኑ ፍጥሞ በምትባል ደሴት ግዞተኛ ሆኖ ነበር። (ራእይ 1:​9) ይህን እንዳደረገ የሚታመነው የሮም ንጉሠ ነገሥት የነበረው ዶሚሺያን ነው። በኢየሱስ ተከታዮች ላይ እንዲህ ያለ ተጽእኖ ቢደርስም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሲጠናቀቅ ክርስትና በሮማ ግዛት በጠቅላላ ተስፋፍቶ ነበር። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነበር? ኤ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ኧርሊ ቸርች (የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ) የተባለው መጽሐፍ ክርስትና “የቆመችው በምታከናውነው አገልግሎቷ ነበር” በማለት ይናገራል። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ቢሰደዱም ዮሐንስ እንዳደረገው ከእምነታቸው የማይወላውሉና ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ በቅንዓት መመስከራቸውን ይገፉበት ነበር። — ሥራ 20:​20, 21፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:​2

በ112 እዘአ ንጉሠ ነገሥት ትራጃን ፕሊኒን በቢቲኒያ ላይ (ከዛሬዋ ቱርክ ሰሜናዊ ምዕራብ ላይ በምትገኘው) ገዥ አድርጎ ከሾመው ከሁለት ዓመት በኋላ በክርስቲያኖች ላይ ይደርስ የነበረው ስደት አዲስ መልክ ያዘ። ከዚያ በፊት የነበረው አስተዳደር ልል ስለነበረ ሥርዓት እንዲበላሽ አድርጎ ነበር። ቤተ መቅደሶች ተትተውና ለመሥዋዕት ይቀርቡ ለነበሩት እንስሳት ምግብ የሚሆን ገፈራ ዋጋው በጣም ቀንሶ ነበር። መሥዋዕትና ጣዖት አልባ የሆነውን የክርስትና አምልኮ ቀላልነት የችግራቸው ምንጭ እንደሆነ በማማረር ነጋዴዎች ይነቅፉ ነበር።

ፕሊኒ አረመኔያዊ አምልኮን እንደገና ለማቋቋም ሲጣጣር ክርስቲያኖች ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱ ሀውልት ፊት የወይንና የዕጣን መሥዋዕት አናቀርብም በማለት ሕይወታቸውን እስከ መክፈል ይደርሱ ነበር። ውሎ አድሮ ሮማውያን ባለ ሥልጣኖች ክርስቲያኖች “እጅግ የሚደነቅ ስነ ምግባር ቢኖራቸውም ለቀድሞዎቹ ሃይማኖታዊ ልማዶች ግን በቃላት ሊገለጽ የማይችል ጥላቻ አላቸው” ብለው ያምኑ እንደነበረ ፕሮፌሰር ሄንሪ ቻድዊክ ተናግረዋል። ክርስቲያን መሆን በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ተደርጎ መታየቱ ቢቀጥልም የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ከአቋማቸው ፍንክች የማለት ሐሳብ አልነበራቸውም።

ፕሮፌሰር ደብሊው ኤም ራምሴይ “የአንድ አረመኔ ቤተሰብ አባል የሆነ ግለሰብ ወደ ክርስትና በመለወጡ ምክንያት የሚፈጠረው ሁከት” ጥላቻን ያስከትል እንደነበረ ተናግረዋል። “አረመኔያዊ አማልክትን መቀበልን በሚያሳዩት በጣም በተለመዱት የማኅበረሰቡ ልማዶች አለመካፈሉን ጎረቤቶች ሊስማሙ በማይችሉበት አካባቢ አብሮ መኖር በጣም አስቸጋሪ ይሆናል” በማለት ዶክተር ጄ ደብሊው ሲ ዋንድ ገልጸዋል። ስለዚህ ብዙዎች የመጀመሪያዎቹን ክርስቲያኖች የሰውን ዘር የሚጠሉ ወይም አምላክ የለም የሚሉ ናቸው ብለው መጥራታቸው ሊያስደንቀን አይገባም።

በቁጥር መጨመራቸው የስደቱን መጠን ከፍ አደረገው

ሐዋርያው ዮሐንስ አስተምሮታል ተብሎ የሚነገርለት ፖሊካርፕ በሰምርኔስ (አሁን ኢዝሚር ትባላለች) ከተማ ውስጥ በጣም የተከበረ ሽማግሌ ሆነ። በእምነቱ ምክንያት በ155 እዘአ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዲቃጠል ተደረገ። የአንድ ክፍለ ሀገር ገዥ የነበረው ሮማዊው ስታቲየስ ኳድራቱስ ሕዝቡን ሰበሰበ። ስታዲየሙ የ86 ዓመት ዕድሜ ያለው ፖሊካርፕ የአማልክቶቻቸውን አምልኮ ባለመደገፉ በናቁትና በጠሉት አረመኔዎች ተሞልቶ ነበር። ወግ አጥባቂ አይሁዶች ሳይቀር ምንም እንኳ ዕለቱ ታላቅ ሰንበት ቢሆንም ፖሊካርፕ ተቃጥሎ የሚሞትበን እንጨት በፈቃዳቸው ሰብስበው አመጡ።

ከዚህ ቀጥሎ በሮማ ግዛት በሚኖሩ ክርስቲያኖች ሁሉ ላይ የስደት ማዕበል ተቀሰቀሰ። በንጉሠ ነገሥት ማርከስ አሬሊየስ ግዛት ሥር ብዙ ክርስቲያኖች ደማቸው እንደ ጎርፍ ፈሰሰ። የሮማ ዜግነት ያላቸው ከሆኑ በሰይፍ ይገደሉ ነበር። የሌላ አገር ዜጋ ከሆኑ ግን በቲያትር ማሳያ ስታዲየሞች ውስጥ በአራዊት እንዲገደሉ ይደረግ ነበር። ወንጀላቸው ምን ነበር? ከአቋማቸው ፍንክች የማይሉ ወይም እምነታቸውን ለመካድ እምቢ ያሉ ክርስቲያኖች ስለሆኑ ብቻ ነበር።

ዘመናዊዋ የፈረንሳይ ከተማ ልዮንስ የሮም ቅኝ ግዛት ሆና በሮም እና በራይን ወንዝ መካከል የምትገኝ ቁልፍ የአስተዳደርና የሮማ ጦር ሠራዊት የሠፈረባት ብቸኛ ቦታ ከነበረችው ከሉጁነም ተነሥታ ዛሬ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሳለች። በ177 እዘአ በዚህች ከተማ አረመኔው ሕዝብ በቁጣ የተነሣበት ጠንካራ የክርስቲያኖች ማኅበረሰብ ነበር። ይህ አድራጎት ክርስቲያኖች ከሕዝባዊ ቦታዎች እንዲገለሉ የተደረገበትን ጊዜ አስጀመረ። አድማው ዓመፅን በማነሣሳቱ ተከታትሎ የመጣው ስደት እየከፋ ስለሄደ ክርስቲያኖች ከቤታቸው ወጥቶ መሄድ አስፈሪ ሆኖባቸው ነበር። የሮም ገዥም ክርስቲያኖች በተገኙበት እንዲገደሉ ትእዛዝ አወጣ።

ሽልማቱ

የኢየሱስ ሐዋርያት መሞትና የተከላካይነት ተጽእኖአቸው አለመኖሩ ክርስቲያን ነን በሚሉት መካከል ክህደት እንዲነሣና እያደገ እንዲሄድ አደረገ። (2 ተሰሎንቄ 2:​7) በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጨረሻ ላይ ከሀዲው ክርስትና የመንግሥት ሃይማኖት ሆነ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ያላደረጉትን የሚያደርግ ከአቋሙ ለመወላወል ዝግጁ የሆነና ራሱን የዓለም ክፍል ያደረገ ከሀዲ ክርስትና ብቅ አለ። (ዮሐንስ 17:​16) ይሁን እንጂ ከዚህ ጊዜ በፊት ቀደም ብሎ የክርስትናን እምነት ታሪክ ጭምር የያዘ ጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ ተጠናቅቆ ነበር።

በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች የተቀበሉት ያ ሁሉ መከራና ሞት ከንቱ ነበርን? ከንቱ እንዳልሆነ ምንም አያጠራጥርም። ከእምነታቸው ፍንክች የማለት ሐሳብ ሳይኖራቸው ‘እስከ ሞት ድረስ የታመኑ ሆነው በመገኘታቸው የሕይወት አክሊል ተቀብለዋል።’ (ራእይ 2:​10) ዛሬም ቢሆን የይሖዋ አገልጋዮች ስደት ይደርስባቸዋል። ነገር ግን የመጀመሪያዎቹ የእምነት ጓደኞቻቸው እምነትና ንጹሕ አቋም ጠባቂነታቸው ለእነርሱ ትልቅ የብርታት ምንጭ ይሆንላቸዋል። ከዚህም የተነሣ የዘመናችን ክርስቲያኖችም ከአቋማቸው ፍንክች የማለት ሐሳብ የላቸውም።

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኔሮ

የሮም ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛት ሞዴል

ለቄሣር አምልኮ የተወሰነ መሠዊያ

[ምንጭ]

Nero: Courtesy of The British Museum

Museo della Civiltà Romana, Roma

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማርከስ አሬሊየስ

[ምንጭ]

The Bettmann Archive

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ