የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 12/1 ገጽ 8-13
  • በእምነታቸው የተጠሉ ሰዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በእምነታቸው የተጠሉ ሰዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ደቀ መዝሙር መሆን የሚጠይቀው “ዋጋ”
  • በጥላቻ የተሞሉና የተጠሉ
  • የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች የተጠሉት በእነማን ነበር?
  • የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች በሮማውያን ዓለም የተጠሉት ለምን ነበር?
  • ከአቋማቸው ፍንክች የማለት ሐሳብ አልነበራቸውም!
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ክርስቲያኖችና ዛሬ ያለው ሰብአዊ ኅብረተሰብ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ለእምነታችን መከላከያ ማቅረብ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖችና ዓለም
    መጠበቂያ ግንብ—1993
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 12/1 ገጽ 8-13

በእምነታቸው የተጠሉ ሰዎች

“በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።”​—⁠ማቴዎስ 10:​22

1, 2. የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ እምነታቸውን ተግባራዊ በማድረጋቸው ምክንያት ያጋጠሟቸውን አንዳንድ የሕይወት ተሞክሮዎች ልትናገር ትችላለህን?

በክሬት ደሴት የሚኖር በሥራው ሐቀኛ የሆነ አንድ ባለ ሱቅ በጣም ብዙ ጊዜ የታሰረ ሲሆን በተደጋጋሚ ደግሞ በግሪክ ፍርድ ቤቶች እንዲቀርብ ተደርጓል። ከሚስቱና ከአምስት ልጆቹ ተነጥሎ በአጠቃላይ ለስድስት ዓመታት ያህል በእስር ቤት አሳልፏል። በጃፓን የሚኖር ዕድሜው 17 ዓመት የሆነ አንድ ተማሪ ምንም እንኳ ጥሩ ጠባይ ያለውና በክፍሉ ከሚገኙት 42 ተማሪዎች በትምህርት ደረጃው አንደኛ ቢሆንም ከትምህርት ቤት እንዲባረር ተደርጓል። በፈረንሳይ የሚኖሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ትጉህና ጠንቃቃ ሠራተኞች መሆናቸው እየታወቀ ከሥራ ገበታቸው ባስቸኳይ እንዲሰናበቱ ተደርገዋል። እነዚህን የሕይወት ተሞክሮዎች የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?

2 እነዚህ ግለሰቦች በሙሉ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ለመሆኑ “ወንጀላቸው” ምንድን ነው? በመሠረቱ ሃይማኖታዊ እምነታቸውን ተግባራዊ ከማድረግ በስተቀር ምንም ወንጀል አልሠሩም። ባለ ሱቁ የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርቶች በመታዘዝ እምነቱን ለሌሎች ይናገር ነበር። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ጥፋተኛ ነህ ተብሎ የተከሰሰው በተለይ ሃይማኖትን ማስለወጥ ወንጀል አድርጎ በሚቆጥር በአንድ ያረጀ ያፈጀ የግሪክ ሕግ መሠረት ነው። ተማሪው የተባረረው ተማሪዎች የግድ ሊካፈሉበት በሚገባው የኪንዶ (የጃፓናውያን የሻሞላ ጨዋታ) ልምምድ ለመካፈል በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊናው ስላልፈቀደለት ነበር። (ኢሳይያስ 2:​4) በፈረንሳይ የነበሩት ደግሞ ከሥራ ገበታቸው ለመባረር ያበቃቸው ብቸኛው ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸው እንደሆነ ተነግሯቸዋል።

3. በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች በሌሎች ሰዎች እጅ ከባድ መከራ የሚደርስባቸው አልፎ አልፎ የሆነው ለምንድን ነው?

3 እነዚህን የመሳሰሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በአንዳንድ አገሮች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጽናት ለተቋቋሟቸው ችግሮች ዓይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው። ይሁን እንጂ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች በሌሎች ሰዎች እጅ ከባድ መከራ የሚደርስባቸው አልፎ አልፎ ነው። የይሖዋ ሕዝቦች በዓለም ዙሪያ በመልካም ጠባያቸው የታወቁ በመሆናቸው ማንም ሰው እነሱን ለመጉዳት የሚያነሳሳው በቂ ምክንያት ሊኖረው አይችልም። (1 ጴጥሮስ 2:​11, 12) የይሖዋ ምሥክሮች በማንም ላይ አያሴሩም ወይም ማንንም የሚጎዳ ተግባር አይፈጽሙም። (1 ጴጥሮስ 4:​15) ከዚህ ይልቅ በመጀመሪያ ለአምላክ ከዚያም ለመንግሥታት በመገዛት የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ለመከተል ይጥራሉ። በሕግ የሚፈለግባቸውን ቀረጥ ይከፍላሉ እንዲሁም ‘ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር’ ይጥራሉ። (ሮሜ 12:​18፤ 13:​6, 7፤ 1 ጴጥሮስ 2:​13–17) በሚያስተምሩት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት አማካኝነት ሰዎች ሕግን፣ የቤተሰብ መሠረታዊ ሥርዓትንና የሥነ ምግባር ሕግጋትን እንዲያከብሩ ያበረታታሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ሕግ አክባሪ ዜጎች በመሆናቸው ብዙ መንግሥታት ያመሰግኗቸዋል። (ሮሜ 13:​3) ሆኖም በመግቢያው ላይ ያለው አንቀጽ እንደሚያሳየው አንዳንድ ጊዜ የተቃውሞ ዒላማ ይሆናሉ፤ እንዲያውም በአንዳንድ አገሮች መንግሥታዊ እገዳ ተጥሎባቸዋል። ይህ ሊያስደንቀን ይገባልን?

ደቀ መዝሙር መሆን የሚጠይቀው “ዋጋ”

4. በኢየሱስ አባባል መሠረት አንድ ሰው የእሱ ደቀ መዝሙር በመሆኑ ምን ሊጠብቅ ይችላል?

4 ኢየሱስ ክርስቶስ የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን ምንን እንደሚያካትት በግልጽ ተናግሯል። ተከታዮቹን “ባርያ ከጌታው አይበልጥም” በማለት ነግሯቸዋል። “እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል።” ኢየሱስ የተጠላው “ያለ ምክንያት” ነበር። (ዮሐንስ 15:​18–20, 25፤ መዝሙር 69:​4 የ1980 ትርጉም፤ ሉቃስ 23:​22) ደቀ መዛሙርቱም ተመሳሳይ የሆነ መሠረተ ቢስ ተቃውሞ ሊጠብቁ ይችላሉ። “የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ሲል ከአንድ ጊዜ በላይ አስጠንቅቋቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 10:​22፤ 24:​9

5, 6. (ሀ) ኢየሱስ የእሱ ተከታዮች የሚሆኑ ሰዎች አስቀድመው ‘ኪሳራቸውን እንዲያሰሉ’ ያሳሰባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ታዲያ ተቃውሞ ሲያጋጥመን ግር ሊለን የማይገባው ለምንድን ነው?

5 በመሆኑም ኢየሱስ ተከታዮቹ የሚሆኑ ሰዎች አስቀድመው ‘ኪሳራቸውን እንዲያሰሉ’ አጥብቆ አሳስቧል። (ሉቃስ 14:​28) ለምን? የእሱ ተከታዮች ለመሆን ወይም ላለመሆን እንዲወስኑ ሳይሆን ደቀ መዝሙር መሆን የሚጠይቀውን ነገር ለመፈጸም ቆራጥ እንዲሆኑ ነው። ከመብቱ ጋር አብሮ የሚመጣውን ማንኛውንም ፈተና ወይም ችግር በጽናት ለመቋቋም ዝግጁ መሆን አለብን። (ሉቃስ 14:​27) የክርስቶስ ተከታይ በመሆን ይሖዋን እንድናገለግል ማንም ሰው አያስገድደንም። በቂ ግንዛቤ ኖሮን በፈቃዳችን የምናደርገው ውሳኔ ነው። ራሳችንን በመወሰን ከአምላክ ጋር ዝምድና በመመሥረታችን ከምናገኛቸው በረከቶች በተጨማሪ ‘የጥላቻ ዒላማ’ እንደምንሆን አስቀድመን እናውቃለን። ስለዚህ ተቃውሞ ሲያጋጥመን ግራ አንጋባም። ‘የሚጠይቀውን ዋጋ ስላሰላን’ ለመክፈል ሙሉ በሙሉ ዝግጁዎች ነን።​—⁠1 ጴጥሮስ 4:​12–14

6 የተወሰኑ የመንግሥት ባለ ሥልጣኖችን ጨምሮ አንዳንዶች እውነተኛ ክርስቲያኖችን የሚቃወሙት ለምንድን ነው? መልሱን ለማግኘት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የነበሩ ሁለት ሃይማኖታዊ ቡድኖችን መመልከቱ ጠቃሚ ነው። ሁለቱም ሃይማኖታዊ ቡድኖች ይጠሉ ነበር፤ ሆኖም ይጠሉ የነበሩባቸው ምክንያቶች ፍጹም የተለያዩ ናቸው።

በጥላቻ የተሞሉና የተጠሉ

7, 8. አሕዛብን በንቀት መመልከትን የሚያንጸባርቁ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው? ከዚህስ የተነሳ በአይሁዳውያን ዘንድ ምን ዓይነት አመለካከት ዳብሮ ነበር?

7 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ እስራኤል በሮማውያን አገዛዝ ሥር ነበረች፤ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሆነው የአይሁድ እምነት ደግሞ በአብዛኛው ጻፎችንና ፈሪሳውያንን በመሳሰሉ ጨቋኝ መሪዎች ቁጥጥር ሥር ነበር። (ማቴዎስ 23:​2–4) እነዚህ ወግ አጥባቂ መሪዎች ከአሕዛብ ስለ መለየት የሚናገረውን የሙሴን ሕግ መሠረታዊ ሐሳብ በማጣመም አይሁዳውያን ላልሆኑ ሰዎች ንቀት ለማሳየት ተጠቅመውበታል። ከጊዜ በኋላ ለአሕዛብ ጥላቻ ያለው በምላሹ ደግሞ በአሕዛብ የተጠላ ሃይማኖት አፈሩ።

8 በዚያን ጊዜ አይሁዳውያን አሕዛብን ርካሽ ሥነ ምግባር ያላቸው ፍጡራን አድርገው ይመለከቷቸው ስለነበር አይሁዳውያን አሕዛብን እንዲንቋቸው መስበክ ለአይሁድ መሪዎች አስቸጋሪ አልነበረም። እነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ አሕዛብ “በብልግና ድርጊት ስለሚጠረጠሩ” አንዲት አይሁዳዊት ሴት በፍጹም ለብቻዋ ከእነሱ ጋር መሆን የለባትም ብለው ያስተምሩ ነበር። ‘አሕዛብ በደም አፍሳሽነት ስለሚጠረጠሩ አንድ አይሁዳዊ ወንድ ብቻውን ከእነሱ ጋር መቀመጥ’ የለበትም። አንድ አይሁዳዊ ሲታለብ እስካላየ ድረስ አንድ አሕዛብ ያለበው ወተት ጥቅም ላይ ሊውል አይችልም። በመሪዎቻቸው ተጽእኖ የተነሣ አይሁዳውያን አሕዛብን የመራቅና ጨርሶ የማግለል አቋም ይዘው ነበር።​—⁠ከዮሐንስ 4:​9 ጋር አወዳድር።

9. የአይሁድ መሪዎች አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችን በተመለከተ የሚያስተምሩት ትምህርት ምን አስከትሏል?

9 አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችን በተመለከተ የሚሰጡ እንዲህ ዓይነት ትምህርቶች አይሁዳውያንና አሕዛብ ተስማምተው እንዳይኖሩ እንቅፋት ሆነዋል። አሕዛብ ደግሞ አይሁዳውያንን ለመላው የሰው ዘር ጥላቻ ያላቸው ሰዎች አድርገው ይመለከቷቸው ጀመር። ሮማዊው ታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ (በ56 እዘአ ገደማ የተወለደ) አይሁዳውያን “የተቀረውን የሰው ዘር የሚመለከቱት ልክ እንደ ጠላት ነበር” ብሏል። በተጨማሪም ታሲተስ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ አሕዛብ አገራቸውን እንዲክዱና ቤተሰባቸውንም ሆነ ወዳጆቻቸውን እርግፍ አድርገው እንዲተዉ ይማራሉ ብሏል። ሮማውያኑ ከቁጥራቸው መብዛት የተነሣ የማይበገሩ የሚመስሉትን አይሁዳውያን ታግሰዋቸዋል ለማለት ይቻላል። ሆኖም በ66 እዘአ የተነሣው የአይሁዳውያን ዓመፅ ሮማውያን ከባድ የአጸፋ እርምጃ እንዲወስዱ ከማነሳሳቱም በላይ በ70 እዘአ ለኢየሩሳሌም መጥፋት ምክንያት ሆኗል።

10, 11. (ሀ) የሙሴ ሕግ መጻተኞች ምን ዓይነት አያያዝ እንዲደረግላቸው ያዝዛል? (ለ) በአይሁድ እምነት ላይ ከደረሰው ነገር ምን እንማራለን?

10 ለመጻተኞች ይህን የመሰለ አመለካከት መያዛቸው በሙሴ ሕግ ላይ ከተጠቀሰው የአምልኮ ዓይነት ጋር የሚነጻጸረው እንዴት ነው? ሕጉ ከአሕዛብ መለየትን የሚያበረታታ ቢሆንም ምክንያቱ ግን እስራኤላውያንን በተለይም ንጹህ አምልኳቸውን ጠብቆ ለማቆየት ነበር። (ኢያሱ 23:​6–8) ያም ሆኖ ግን መጻተኞች የእስራኤልን ሕግ ሆን ብለው እስካልተቃወሙ ድረስ ፍትሐዊና ተገቢ በሆነ መንገድ እንዲያዙ እንዲሁም የእንግድነት አቀባበል እንዲደረግላቸው ሕጉ ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 24:​22) በኢየሱስ ዘመን የነበሩ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በሕጉ ላይ በግልጽ ከሚንጸባረቀው ምክንያታዊ መንፈስ በመራቅ ሌሎችን የሚጠላና ሌሎች ደግሞ በጥላቻ ዓይን የሚመለከቱት የአምልኮ ዓይነት አስገኙ። በመጨረሻም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የአይሁድ ብሔር የይሖዋን ሞገስ አጣ።​—⁠ማቴዎስ 23:​28

11 እኛ ከዚህ የምናገኘው ትምህርት አለን? አዎን፣ አለ። ሃይማኖታዊ እምነታችንን የማይጋሩንን ሰዎች በመናቅ ራስን የማመጻደቅና ከፍ ብሎ የመታየት ዝንባሌ የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ትክክለኛ ነጸብራቅ አይደለም፤ ይሖዋንም አያስደስተውም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን የታመኑ ክርስቲያኖች ተመልከቱ። ክርስቲያን ላልሆኑ ሰዎች ጥላቻ አልነበራቸውም፤ ወይም በሮም ላይ ዓምፀው አልተነሱም። ያም ሆኖ ግን ‘ይጠሉ’ ነበር። ለምን? ደግሞስ በእነማን?

የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች የተጠሉት በእነማን ነበር?

12. ኢየሱስ ተከታዮቹ ክርስቲያኖች ስላልሆኑ ሰዎች ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራቸው እንደሚፈልግ ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ ካስተማራቸው ነገሮች በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ደቀ መዛሙርቱ ክርስቲያን ላልሆኑ ሰዎች ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንዲኖራቸው ይፈልግ ነበር። በአንድ በኩል ተከታዮቹ ከዓለም የተለዩ እንደሚሆኑ ተናግሯል፤ ይህም የይሖዋን የጽድቅ መንገዶች ከሚጻረሩ አመለካከቶችና የአኗኗር መንገዶች መራቅ ማለት ነበር። ከጦርነትና ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኞች ይሆናሉ። (ዮሐንስ 17:​14, 16) በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ተከታዮቹ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎችን እንዲያንቋሽሿቸው ከማስተማር ይልቅ ‘ጠላቶቻቸውን እንዲወድዱ’ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 5:​44) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው” ሲል አጥብቆ አሳስቧል። (ሮሜ 12:​20) በተጨማሪም ‘ለሰው ሁሉ መልካም እንዲያደርጉ’ ነግሯቸዋል።​—⁠ገላትያ 6:​10

13. የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት በጣም ይቃወሟቸው የነበረው ለምንድን ነው?

13 ሆኖም ከጥቂት ጊዜ በኋላ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከሦስት አቅጣጫዎች ‘ጥላቻ’ ይሰነዘርባቸው ጀመር። የመጀመሪያዎቹ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ነበሩ። የእነዚህ መሪዎች ትኩረት ወዲያውኑ በክርስቲያኖች ላይ ማረፉ ብዙም አያስደንቅም! ክርስቲያኖች ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባርና የአቋም መመሪያዎች ነበሯቸው፤ እንዲሁም ተስፋን የሚያለመልመውን መልእክት በከፍተኛ ቅንዓት ያውጁ ነበር። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የአይሁድን እምነት ትተው ክርስትናን ተቀበሉ። (ሥራ 2:​41፤ 4:​4፤ 6:​7) የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች አይሁዳውያን የሆኑትን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደ ከሃዲዎች አድርገው ይመለከቷቸው ነበር! (ከሥራ 13:​45 ጋር አወዳድር።) እነዚህ የተናደዱ መሪዎች ክርስትና ባህላቸውን ዋጋ እንደሚያሳጣው ተሰምቷቸው ነበር። ሌላው ቀርቶ ለአሕዛብ ያላቸውን አመለካከት ይቃወም ነበር! ከ36 እዘአ አንስቶ አሕዛብ ክርስትናን በመቀበል ከአይሁድ ክርስቲያኖች ጋር ተመሳሳይ የሆነ እምነት ሊኖራቸውና ተመሳሳይ የሆኑ መብቶችን ሊጋሩ ችለዋል።​—⁠ሥራ 10:​34, 35

14, 15. (ሀ) ክርስቲያኖች በአረማውያን አምላኪዎች የተጠሉት ለምን ነበር? ምሳሌ ስጥ። (ለ) የቀድሞዎቹን ክርስቲያኖች በየትኛው ሦስተኛ ቡድን ‘ይጠሉ’ ነበር?

14 በሁለተኛ ደረጃ ክርስቲያኖች ይጠሉ የነበረው በአረማዊ አምላኪዎች ነበር። ለምሳሌ ያህል በጥንቷ ኤፌሶን ውስጥ እንስት አምላክ የሆነችውን የአርጤምስን የብር ምስሎች እየሠሩ መሸጥ አትራፊ የንግድ ሥራ ነበር። ሆኖም ጳውሎስ በዚያ በሰበከ ጊዜ ብዙ ቁጥር ያላቸው የኤፌሶን ሰዎች ምላሽ በመስጠት የአርጤምስን አምልኮ ተዉ። በዚህ ምክንያት የንግድ ሥራቸው አደጋ ላይ በመውደቁ አንጥረኞቹ ረብሻ ፈጠሩ። (ሥራ 19:​24–41) ክርስትና ወደ ቢታንያ (አሁን ሰሜን ምዕራብ ቱርክ) በተስፋፋ ጊዜ ተመሳሳይ የሆነ ነገር ተከስቶ ነበር። የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ተጽፈው ከተጠናቀቁ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የቢታንያ ገዥ የነበረው ወጣቱ ፕሊኒ አረማዊ ቤተ መቅደሶች እንደተተዉና ለመሥዋዕት ለሚቀርቡ እንስሳት የሚሆን መኖ ሽያጭ እጅግ መቀነሱን ተናግሮ ነበር። ክርስቲያኖች አምልኳቸው የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብንና የጣዖት አምልኮን ስለማይፈቅድ ለዚህ ነገር ተወቃሾቹ እነሱ ሆኑ፤ እንዲሠቃዩም ተደረጉ። (ዕብራውያን 10:​1–9፤ 1 ዮሐንስ 5:​21) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የክርስትና መስፋፋት ከአረማዊ አምልኮ ጋር የተያያዙ ጥቅማ ጥቅሞችን ይነካል፤ ንግዳቸውንም ሆነ ገንዘባቸውን ያጡ ደግሞ ለክርስትና ጥላቻ አድሮባቸዋል።

15 በሦስተኛ ደረጃ ክርስቲያኖች ‘የተጠሉት’ በብሔርተኞቹ ሮማውያን ነበር። መጀመሪያ ላይ ሮማውያን ክርስቲያኖችን እንደ አንድ አናሳ ምናልባትም አክራሪ የሆነ ሃይማኖታዊ ቡድን አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ክርስቲያን ነኝ ብሎ መናገር ብቻ እንኳ በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ሆነ። ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚመሩ ሐቀኛ ዜጎች ስደትና ሞት የሚገባቸው ተደርገው የታዩት ለምንድን ነው?

የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች በሮማውያን ዓለም የተጠሉት ለምን ነበር?

16. ክርስቲያኖች ከዓለም የተለዩ የሆኑት በምን መንገዶች ነበር? ይህስ በሮማውያን ዓለም እንዲጠሉ ያደረጋቸው ለምንድን ነው?

16 ክርስቲያኖች በሮማውያን ዓለም የተጠሉበት ዋናው ምክንያት ሃይማኖታዊ እምነታቸውን ተግባራዊ በማድረጋቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል ከዓለም የተለዩ ነበሩ። (ዮሐንስ 15:​19) ስለዚህ ፖለቲካዊ ሥልጣን አይዙም እንዲሁም ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠትም ፈቃደኞች አልነበሩም። በዚህ ምክንያት ታሪክ ጸሐፊው አውጉስቶስ ኔአንደር ክርስቲያኖች “ለዓለም በድን እንደሆኑና በሁሉም የኑሮ ዘርፎች እንደማይጠቅሙ ተደርገው ይታዩ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል። በተጨማሪም የዓለም ክፍል አለመሆን ማለት ከብልሹው የሮማውያን ዓለም ክፉ መንገዶች መራቅ ማለት ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ዊል ዱራንት “አነስተኛው የክርስትና ማኅበረሰብ በሃይማኖተኛነቱና በመልካም ምግባሩ ፈንጠዝያ የጠማውን አረማዊ ዓለም ሕሊና እየረበሸ ነበር” ሲሉ አብራርተዋል። (1 ጴጥሮስ 4:​3, 4) ክርስቲያኖችን በማሰቃየትና በመግደል ሮማውያን አስቸጋሪውን የሕሊና ድምፅ ዝም ለማሰኘት ሳይሞክሩ አልቀሩም።

17. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የስብከት ሥራ ውጤታማ እንደነበረ የሚያሳየው ምንድን ነው?

17 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማይቀዘቅዝ ቅንዓት ሰብከዋል። (ማቴዎስ 24:​14) በ60 እዘአ ገደማ ጳውሎስ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ [ተሰብኳል]” ለማለት ችሎ ነበር። (ቆላስይስ 1:​23) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ የኢየሱስ ተከታዮች በመላው የሮማ ግዛት ማለትም በእስያ፣ በአውሮፓና በአፍሪካ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ነበር! ሌላው ቀርቶ ‘ከቄሣር ቤተሰብ’ አባላት መካከል አንዳንዶች ክርስቲያኖች ሆነው ነበር።a (ፊልጵስዩስ 4:​22) ይህ ቅንዓት የተሞላበት ስብከት ጥላቻን አስነስቷል። ኔአንደር እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- “ክርስትና በሁሉም የኑሮ መስኮች በሚገኙ ሰዎች ዘንድ ያለማቋረጥ ተቀባይነት እያገኘ በመምጣቱ መንግሥታዊውን ሃይማኖት ስጋት ላይ ጥሎት ነበር።”

18. ክርስቲያኖች ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ አምልኮ መስጠታቸው ከሮም መንግሥት ጋር ያጋጫቸው እንዴት ነበር?

18 የኢየሱስ ተከታዮች ለይሖዋ ብቻ የተወሰነ አምልኮ ያቀርቡ ነበር። (ማቴዎስ 4:​8–10) ከሌላው ይልቅ ከሮም ጋር ቅራኔ ውስጥ የከተታቸው ምናልባትም ይህ የአምልኳቸው ገጽታ ሳይሆን አይቀርም። ደጋፊዎቻቸው በንጉሠ ነገሥት አምልኮ እስከተካፈሉ ድረስ ሮማውያን ሌሎች ሃይማኖቶችን አይቃወሙም ነበር። የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ግን በዚህ አምልኮ ሊካፈሉ አይችሉም ነበር። ራሳቸውን ከሮም መንግሥት ለሚበልጥ ባለ ሥልጣን ማለትም ለይሖዋ አምላክ ተጠያቂዎች እንደሆኑ አድርገው ይመለከቱ ነበር። (ሥራ 5:​29) በዚህም ምክንያት አንድ ክርስቲያን ዜጋ በሌሎች መስኮች ምንም ያህል አርአያ የሚሆን ተግባር ቢፈጽምም የመንግሥት ጠላት ተደርጎ ይቆጠር ነበር።

19, 20. (ሀ) በአብዛኛው በታመኑ ክርስቲያኖች ላይ ለሚሰነዘረው በተንኮል የተሞላ የሐሰት ክስ ቆስቋሾቹ እነማን ነበሩ? (ለ) በክርስቲያኖች ላይ ምን የሐሰት ክሶች ቀርበው ነበር?

19 የታመኑ ክርስቲያኖች በሮማውያን ዓለም ‘ይጠሉ’ የነበረበት ሌላም ምክንያት ነበረ። እነሱን በተመለከተ ይናፈሱ የነበሩ የሐሰት ወሬዎች በቀላሉ ተዓማኒነት ያገኙ ነበር። በተለይ ደግሞ በዚህ ነገር ግምባር ቀደም ቆስቋሾቹ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ነበሩ። (ሥራ 17:​5–8) በ60 ወይም በ61 እዘአ ጳውሎስ በሮም ከንጉሠ ነገሥት ኔሮ ፍርዱን ይጠባበቅ በነበረበት ጊዜ የአይሁድ መሪዎች ስለ ክርስቲያኖች እንዲህ ብለው ነበር:- “ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአልና።” (ሥራ 28:​22) ኔሮ ክርስቲያኖችን አስመልክቶ የሚናፈሱ የሐሰት ወሬዎችን ሳይሰማ እንደማይቀር የተረጋገጠ ነው። ኔሮ በ64 እዘአ ሮምን ላወደመው የእሳት ቃጠሎ በተወቀሰ ጊዜ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሲል በመጥፎ ስም ይጠቀሱ በነበሩት ክርስቲያኖች ላይ ለማላከክ እንደሞከረ ተዘግቧል። ይህ ክርስቲያኖችን ጠራርጎ ለማጥፋት ሲባል ከባድ የስደት ማዕበል እንዲነሳ ያደረገ ይመስላል።

20 ብዙውን ጊዜ በክርስቲያኖች ላይ የሐሰት ክስ ይሰነዘር የነበረው ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነገር በመናገርና እምነታቸውን አጣምሞ በመተርጎም ነው። በአንድ አምላክ ብቻ ያምኑ ስለነበረና በንጉሠ ነገሥቱ አምልኮ ስለማይካፈሉ አምላክን የካዱ የሚል ስያሜ ተሰጥቶአቸዋል። አንዳንድ ክርስቲያን ያልሆኑ የቤተሰብ አባላት ክርስቲያን ዘመዶቻቸውን ስለሚቃወሙ፣ ክርስቲያኖች ቤተሰብን የሚለያዩ ተብለው ተከስሰዋል። (ማቴዎስ 10:​21) የሰው ሥጋ ይበላሉ የሚል ስምም የተሰጣቸው ሲሆን ኢየሱስ በጌታ እራት ላይ የተናገራቸውን ቃላት በማጣመም የቀረበ ክስ ሊሆን እንደሚችል አንዳንድ ምንጮች ይናገራሉ።​—⁠ማቴዎስ 26:​26–28

21. ክርስቲያኖች ‘የተጠሉት’ በየትኞቹ ሁለት ምክንያቶች ነበር?

21 ስለዚህ ክርስቲያኖች በሮማውያን ‘ይጠሉ’ የነበሩት በሁለት ምክንያቶች ነበር:- (1) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተው እምነታቸውና ልማዶቻቸው፣ እንዲሁም (2) በሚቀርቡባቸው የሐሰት ክሶች። ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን የተቃዋሚዎቹ ዓላማ ክርስትናን ማጥፋት ነበር። እርግጥ በክርስቲያኖች ላይ ለሚደርሰው መከራ ቆስቋሾቹ ከሰው በላይ ኃይል ያላቸው ተቃዋሚዎች ማለትም የማይታዩ ክፉ መንፈሳዊ ኃይላት ናቸው።​—⁠ኤፌሶን 6:​12

22. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ‘ለሰው ሁሉ መልካም ለማድረግ’ እንደሚጥሩ የትኛው ምሳሌ ያሳያል? (በገጽ 11 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የምንመረምረው ምንድን ነው?

22 እንደ ቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም በተለያዩ አገሮች ‘ይጠላሉ።’ እነሱ ግን የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችን አይጠሉም፤ በመንግሥታት ላይ ሁከት ፈጥረው አያውቁም። ከዚህ ይልቅ የትኛውም የብሔር፣ የዘርና የጎሣ ድንበር የማይበግረው እውነተኛ ፍቅር በማሳየት ረገድ በዓለም ዙሪያ የታወቁ ናቸው። ታዲያ ስደት የሚደርስባቸው ለምንድን ነው? ለሚደርስባቸው ተቃውሞስ ምላሽ የሚሰጡት እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ‘ከቄሣር ቤተ ሰዎች’ የሚለው አገላለጽ በወቅቱ ነግሦ የነበረው የኔሮ የቅርብ ዘመድ የሆኑ የቤተሰብ አባላትን ብቻ የሚያመለክት ላይሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ ለንጉሣዊው ቤተሰብና ለአባላቱ ምግብ የሚያዘጋጁና ጽዳትን የመሳሰሉ የቤት ውስጥ ሥራዎች የሚያከናውኑ የቤት ሠራተኞችንና ዝቅተኛ ሹማምንቶችን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።

[ምን ብለህ ትመልሳለህ?]

◻ ኢየሱስ ተከታዮቹ የሚሆኑትን ሰዎች ደቀ መዝሙር መሆን የሚጠይቀውን ዋጋ እንዲያሰሉ ያሳሰባቸው ለምንድን ነው?

◻ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎችን በተመለከተ ሰፍኖ የነበረው አመለካከት በአይሁድ እምነት ላይ ምን ተጽእኖ አሳድሯል? ከዚህስ ምን እንማራለን?

◻ የቀድሞዎቹ የታመኑ ክርስቲያኖች የየትኞቹን ሦስት ቡድኖች ተቃውሞ ተጋፍጠዋል?

◻ የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች በሮማውያን ‘የተጠሉባቸው’ ዋነኞቹ ምክንያቶች የትኞቹ ነበሩ?

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘ለሰው ሁሉ መልካም ማድረግ’

የይሖዋ ምሥክሮች ‘ለሰው ሁሉ መልካም አድርጉ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ይጥራሉ። (ገላትያ 6:​10) ለጎረቤት ያላቸው ፍቅር ሃይማኖታዊ አመለካከቶቻቸውን የማይጋሯቸውን ሰዎች እንኳን በአስቸጋሪ ጊዜያት ለመርዳት ያነሳሳቸዋል። ለምሳሌ ያህል በ1994 በሩዋንዳ በደረሰው አስከፊ መከራ በአውሮፓ የሚገኙ ምሥክሮች የእርዳታ ሥራውን ለማገዝ ወደ አፍሪካ ለመሄድ ፈቃደኞች ሆኑ። እርዳታውን ለማዳረስ እንዲቻል በደንብ የተደራጁ መጠለያ ጣቢያዎችና የመስክ ሆስፒታሎች በአስቸኳይ ተቋቋሙ። ከፍተኛ መጠን ያላቸው ምግቦች፣ አልባሳትና ብርድ ልብሶች በአየር ተልከው ነበር። ከዚህ የእርዳታ አቅርቦት የተጠቀሙት ስደተኞች ቁጥር በአካባቢው ከሚገኙ ምሥክሮች ቁጥር በሦስት እጥፍ የሚበልጥ ነበር።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በማይቀዘቅዝ ቅንዓት ምሥራቹን ሰብከዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ