የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 12/1 ገጽ 4-10
  • ለተፈጥሮ አደጋዎች ተጠያቂው አምላክ ነውን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለተፈጥሮ አደጋዎች ተጠያቂው አምላክ ነውን?
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “የተፈጥሮ አደጋ” ምንድን ነው?
  • ተጠያቂው ማን ነው?
  • መፍትሄው ምንድን ነው?
  • አምላክ ወደፊት የሚፈጽማቸው ሥራዎች
  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተፈጥሮ አደጋዎች ምን ይላል?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • የተፈጥሮ አደጋዎች ይህን ያህል የበዙት ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • አምላክ በዛሬው ጊዜ ሰዎችን ለመቅጣት በተፈጥሮ አደጋዎች ይጠቀማል?
    ንቁ!—2012
  • የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 12/1 ገጽ 4-10

ለተፈጥሮ አደጋዎች ተጠያቂው አምላክ ነውን?

“አንተ አምላክ ምን አመጣህብን?”

ይህን እንደተናገሩ የተዘገቡት ኅዳር 13, 1985 በኮሎምቢያ ውስጥ ኔቫዶ ዴል ሩዝ በተባለው በበረዶ የተሸፈነ ተራራ ላይ ከተነሳው ፍንዳታ ከሞት የተረፉና የደረሰውን ጥፋት የተመለከቱ ሰው ናቸው። በፍንዳታው ምክንያት የተናደው በረዶ መላዋን የአርሜሮ ከተማ ከመቅበሩም በላይ በአንድ ሌሊት ከ20,000 በላይ ሕዝብ ገደለ።

ከላይ የተጠቀሱት ከአደጋው የተረፉ ሰው እንደዚህ ያሉበትን ምክንያት ለመረዳት አያስቸግርም። ሰዎች አስፈሪ የሆኑ የተፈጥሮ ኃይሎችን መቋቋም የማይችሉ መሆናቸው ስለሚሰማቸው እንዲህ ዓይነቶቹን መቅሠፍታዊ ሁኔታዎች የሚያመጣው አምላክ ነው ሲሉ ኖረዋል። ጥንታዊ ሕዝቦች የባሕር፣ የሰማይ፣ የምድር፣ የተራራ፣ የእሳተ ገሞራና የሌሎችም አደጋዎች ምንጭ የሆኑትን አማልክቶቻቸውን ለማስደሰት ስጦታና የሰው መሥዋዕት እንኳን ሳይቀር ያቀርቡ ነበር። በአሁኑ ጊዜም እንኳን በመቅሰፍታዊ የተፈጥሮ ሁኔታዎች የሚመጡትን መዘዞች እንደ እግዜር ፍርጃ ወይም ከአምላክ እንደተወሰነባቸው አድርገው የሚቀበሉ አንዳንድ ሰዎች አሉ።

ይሁንና በዓለም ዙሪያ በሰዎች ላይ ብዙ ስቃይና ጥፋት ለሚያስከትሉት አደጋዎች ተጠያቂው እውን አምላክ ነው? ተወቃሹስ እርሱ ነውን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልሱን ለማግኘት እንዲህ ባሉት አደጋዎች ውስጥ የሚካተቱትን ነገሮች ጠጋ ብለን መመርመር ያስፈልገናል። እንዲያውም ከታወቁት ማስረጃዎች ውስጥ አንዳንዶቹን እንደገና መመርመር ያስፈልገናል።

“የተፈጥሮ አደጋ” ምንድን ነው?

የቻይናዋ ታንግሻን በመሬት መናወጥ በተመታች ጊዜ፣ 242,000 ሰዎች እንደሞቱ ይፋ መግለጫዎች በተነገሩ ጊዜና ሀሪኬን አንድሩ የተባለ አውሎ ነፋስ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙትን ደቡብ ፍሎሪዳንና ሉዊዚያናን መትቷቸው በቢልዮን የሚቆጠር ዶላር ባጠፋ ጊዜ እንዲህ ዓይነቶቹ የተፈጥሮ አደጋዎች የዓለም አቀፉን የዜና ማሠራጫዎች ከፍተኛ ትኩረት ስበዋል። ሆኖም ያ የምድር መናወጥ ከታንግሻን በስተ ሰሜናዊ ምዕራብ 1,100 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘውና ሰው በማይኖርበት የጎቢ ምድረበዳ ላይ ደርሶ ቢሆን ኖሮ፣ ሀሪኬን አንድሩ የተባለው አውሎ ነፋስ ሌላ አቅጣጫ ይዞ በባሕር ላይ ቢያልፍና ጭራሹን ምድር ላይ ሳይደርስ ቢቀር ኖሮስ? እንዲህ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ሁኔታዎች አሁን ሊታወሱ አይችሉም ነበር።

እንግዲያውስ በግልጽ እንደሚታየው ስለ ተፈጥሮ አደጋዎች በምንናገርበት ጊዜ አስደናቂ ስለሆኑ የተፈጥሮ ኃይሎች ብቻ መናገራችን አይደለም። በያመቱ ለስታቲስቲክስ ያህል ብቻ የሚመዘገቡና ምንም ጉዳት ያላደረሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ትናንሽና ትላልቅ የመሬት ነውጦችና ብዙ ማዕበሎች፣ ውሽንፍሮችና ኃይለኛ አውሎ ነፋሶች፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎችና ሌሎች ኃይለኛ ክስተቶች አሉ። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቶቹ ሁኔታዎች የሕይወትና የንብረት ጥፋት በሚያስከትሉበትና የኑሮ መቃወስ በሚያደርሱበት ጊዜ አደጋዎች ይሆ⁠ናሉ።

ጥፋቱና የሚደርሰው ሞት ከተፈጥሮ ኃይሎቹ ጋር ሁልጊዜ ተመጣጣኝ እንደማይሆን ሊታወስ ይገባል። ከፍተኛ ጥፋት የሚደርሰው የሚከሰቱት የተፈጥሮ ኃይሎች በጣም ከባድ ስለሆኑ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል በ1971 መጠኑ በሬክተር መለኪያ 6.6 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ በዩናይትድ ስቴትስ ካሊፎርኒያ የምትገኘውን ፈርናንዶን በመምታቱ ምክንያት 65 ሰዎች ሞተዋል። አንድ ዓመት ቆይቶ በኒካራጉዋ በምትገኘው ማናጉዋ በሬክተር መለኪያ 6.2 የሆነ የመሬት መናወጥ በመድረሱ ምክንያት 5,000 ሰዎች ሞተዋል!

ስለዚህ የተፈጥሮ አደጋዎች አጥፊነት እየጨመረ መሄዱን በተመለከተ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ አለብን:- የተፈጥሮ ኃይሎቹ ከበፊቱ ይበልጥ ኃይለኞች ሆነዋልን? ለችግሩ መባባስ ምክንያት የሆኑት ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ናቸው?

ተጠያቂው ማን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አምላክ የዚህችን ምድር የተፈጥሮ ኃይሎች ጨምሮ የሁሉም ነገሮች ታላቅ ፈጣሪ መሆኑን ያረጋግጣል። (ዘፍጥረት 1:​1፤ ነህምያ 9:​6፤ ዕብራውያን 3:​4፤ ራእይ 4:​11) ይህ ማለት ግን እያንዳንዱን የነፋስ እንቅስቃሴ ወይም እያንዳንዱን የዝናብ ካፊያ የሚያመጣው እርሱ ነው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ምድርንና አካባቢዋን የሚቆጣጠሩ አንዳንድ ሕጎች ሥራ ላይ እንዲውሉ አድርጎአል። ለምሳሌ ያህል በመክብብ 1:​5–7 ላይ በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር ስላስቻሉት ሦስት መሠረታዊ እንቅስቃሴዎች ማለትም ስለ ፀሐይ በየቀኑ መውጣትና መጥለቅ፣ ስለ ነፋስ የማይለዋወጥ ሥርዓትና ስለ ውኃ ዑደት እናነባለን። የሰው ልጅ አወቀም አላወቀ እነዚህ የተፈጥሮ ሥርዓቶችና እነዚህን መሰል የአየር ጠባይን፣ ሥነ መሬትንና ሥነ ምሕዳርን የሚመለከቱ ሌሎች ሥርዓቶች በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ኖረዋል። እንዲያውም የመክብብ ጸሐፊ ይህን የጻፈው በማይለዋወጡትና ፍጻሜ በሌላቸው የፍጥረት መንገዶችና ኃላፊና ጊዜያዊ በሆነው የሰው ሕይወት ባሕሪ መካከል ያለውን ታላቅ ልዩነት ለማመልከት ነበር።

ይሖዋ የተፈጥሮ ኃይሎች ፈጣሪ ከመሆኑ በተጨማሪ እነርሱን ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል አለው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ ዓላማውን ለማከናወን እነዚህን ኃይሎች እንደተቆጣጠረ ወይም እንደፈለገ እንዳደረጋቸው የሚገልጹ ታሪኮችን እናገኛለን። እነዚህም ታሪኮች በሙሴ ዘመን ቀይ ባሕር እንዲከፈል ማድረጉን፣ በኢያሱ ዘመን ፀሐይና ጨረቃ ባሉበት ቀጥ ብለው እንዲቆሙ ማድረጉን ይጨምራሉ። (ዘጸአት 14:​21–28፤ ኢያሱ 10:​12, 13) የአምላክ ልጅና ቃል የተገባለት መሲሕ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም በገሊላ ባሕር ላይ የተነሳውን ማዕበል ጸጥ እንዲል ባደረገ ጊዜ በተፈጥሮ ኃይሎች ላይ ሥልጣን እንዳለው አሳይቷል። (ማርቆስ 4:​37–39) ይህን የመሰሉ ታሪኮች ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህች ምድር ላይ ያለውን ሕይወት የሚነኩ ነገሮችን ሁሉ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እንደሚችሉ ያረጋግጡልናል።  — 2 ዜና መዋዕል 20:​6፤ ኤርምያስ 32:​17፤ ማቴዎስ 19:​26

ይህም በመሆኑ በቅርብ ጊዜያት በእነዚህ የተፈጥሮ ኃይሎች ምክንያት እየጨመረ ለመጣው ጥፋትና ውድመት አምላክን በኃላፊነት ልንጠይቀው እንችላለንን? ይህን ጥያቄ ለመመለስ የተፈጥሮ ኃይሎቹ በቅርብ ጊዜ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ ይበልጥ ኃይለኛ መሆናቸውን፣ ምናልባትም ከቁጥጥር ውጭ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ መኖር አለመኖሩን በመጀመሪያ መመርመር አለብን።

በዚህ ረገድ ናቹራል ዲዛዝተርስ:- አክትስ ኦቭ ጎድ ኦር አክትስ ኦቭ ማን? የተሰኘው መጽሐፍ ምን እንደሚል ልብ በል:- “ከድርቅ፣ ከውኃ መጥለቅለቅና ከአውሎ ነፋስ ጋር የተያያዙት የአየር ጠባይ አሠራሮች እየተለወጡ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ የለም። የመሬት መንቀጥቀጥ፣ እሳተ ገሞራና የመሬት ነውጥ ሞገዶች ከበፊቱ ይበልጥ ኃይለኛ እየሆኑ ነው ብሎ የሚናገር የሥነ መሬት ተመራማሪ (ጂኦሎጂስት) የለም።” በተመሳሳይም ኧርዝ ሾክ የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚከተለው ብሏል:- “የእያንዳንዱ አህጉር አለቶች እያንዳንዳቸው በአሁኑ ጊዜ ቢደርሱ ኖሮ ለሰው ልጆች መቅሰፍታዊ ጥፋት ሊያስከትሉ ይችሉ የነበሩ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ትላልቅና ትናንሽ ሥነ መሬታዊ ሁኔታዎች ተከስተው እንደነበረ የሚያሳይ መዝገብ የያዙ ናቸው። እነዚህ ሁኔታዎች ለወደፊቱም በተደጋጋሚ እንደሚደርሱ በሳይንስ ተረጋግጧል።” በሌላ አነጋገር ምድርና በውስጧ ያሉ ከፍተኛ ኃይሎች ከሞላ ጎደል ሳይለወጡ ኖረዋል ማለት ነው። ስለዚህም አንዳንድ ስታቲስቲካዊ ዘገባዎች አንዳንድ ሥነ መሬታዊ ወይም ሌሎች እንቅስቃሴዎች እየጨመሩ መሆናቸውን ቢያመለክቱም ባያመለክቱም በቅርብ ጊዜ ምድር ከቁጥጥር ውጭ እስከመሆን ድረስ ሞገደኛ አልሆነችም።

ታዲያ ለምናነበው የተፈጥሮ አደጋዎች ተደጋጋሚነትና አጥፊነት መጨመር ምክንያቱ ምንድን ነው? ተወቃሾቹ የተፈጥሮ ኃይሎች ካልሆኑ ጥፋተኝነቱ የሚያነጣጥረው በሰዎች ላይ ነው። በእርግጥም ሰብዓዊ የሥራ እንቅስቃሴዎች አካባቢያችንን ለተፈጥሮ አደጋዎች ይበልጥ የተጋለጠና ሊጠቃ የሚችል እንዳደረጉት አዋቂዎች ተገንዝበዋል። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች እየጨመረ የሚሄደው የምግብ ፍላጎት ገበሬዎች ያላቸውን መሬት ከመጠን በላይ ደጋግመው እንዲያርሱት ወይም በጣም አስፈላጊ የሆነውን የደን ልባስ መንጥረው የተጋለጠ እንዲያደርጉት አስገድዷቸዋል። ይህም ከፍተኛ የመሬት መሸርሸርን አስከትሏል። እየሰፋ የሚሄደው የሕዝብ ብዛትም የደሳሳ ጎጆዎችንና በከተማ ውስጥ በአደገኛ ቦታዎች ላይ ያለ ዕቅድ የሚሠሩ ቆሻሻ ሠፈሮችን መስፋፋት አፋጥኗል። የተሻለ እድገት አላቸው በሚባሉ አገሮችም እንኳን ሳይቀር ብዙ ሰዎች በካሊፎርኒያው ሳን አንድሩዝ ደርማሳ ሥፍራ እንደሚኖሩት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ግልጽ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠዋል። እንደነዚህ ባሉት ሁኔታዎች አንድ ለየት ያለ አደጋ፣ ማለትም ማዕበል፣ የውኃ መጥለቅለቅ፣ ወይም የመሬት መናወጥ ቢነሳ የሚደርሰው ጥፋት “በተፈጥሮ” ምክንያት የመጣ ነው ሊባል ይችላልን?

ዓይነተኛ ምሳሌ የሚሆነን በአፍሪካዋ ሳህል አካባቢ የደረሰው ድርቅ ነው። በተለምዶ የምናስበው ረሀብና ሞት የሚያስከትለው ድርቅ የሚመጣው በውኃ ወይም በዝናብ እጦት ምክንያት እንደሆነ አድርገን ነው። ይሁን እንጂ በዚያ ስፍራ ረሀብና ችጋር ብዙ ጊዜ የተከሰተው በውኃ እጦት ብቻ ነውን? ኔቸር ኦን ዘ ራምፔጅ የተሰኘ መጽሐፍ “በሳይንስና በእርዳታ ድርጅቶች የተሰባሰቡ ማስረጃዎች በአሁኑ ጊዜ ረሀብ ሊወገድ ያልቻለው ከድርቅ ይልቅ ሰዎች ለረዥም ጊዜ በመሬትና በውኃ ያለአግባብ በመጠቀማቸው ምክንያት እንደሆነ ያመለክታሉ። . . . ሳህል ወደ በረሃነት የተለወጠው በአብዛኛው ሰው ሠራሽ በሆኑ ምክንያቶች ነው” በማለት ተናግሯል። የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ የሆነው ዘ ናታል ዊትነስ “ረሀብ የምግብ እጥረት ጉዳይ አይደለም፤ ወደ ምግብ ለመድረስ ያለመቻል ጉዳይ ነው። በሌላ አነጋገር ረሀብ የድህነት ጉዳይ ነው” በማለት ተናግሯል።

ከሌሎች አደጋዎች ስለሚመጣው ጥፋትም እንደዚሁ ማለት ይቻላል። በዓለም ውስጥ በሀብታም አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦች በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት እንደሚሞቱ የተደረጉት ጥናቶች ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ጥናት ባሳየው መሠረት ከ1960 እስከ 1981 ድረስ ጃፓን 43 የመሬት መንቀጥቀጥና ሌሎችም አደጋዎች የደረሱባት ሲሆን በዚሁ ምክንያት 2,700 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ይህም በእያንዳንዱ አደጋ 63 ሰዎች ሞተዋል ማለት ነው። በዚያው ወቅት ፔሩ ለ91,000 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆኑ 31 አደጋዎች የደረሱባት ሲሆን ይህም በእያንዳንዱ አደጋ 2,900 ሰዎች ሞተዋል ማለት ነው። ይህን ያህል ልዩነት የኖረው ለምንድን ነው? የአደጋው መንስኤዎች የተፈጥሮ ኃይሎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ በሚደርሰው የሕይወት ጥፋትና የንብረት ውድመት ላይ ግን ይህን ያህል ልዩነት ያመጣው ሰብአዊ ሥራ፣ ማለትም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ነው።

መፍትሄው ምንድን ነው?

የሳይንስ ሊቃውንትና ጠበብቶች የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቋቋም የሚችሉባቸውን መንገዶች ለመቀየስ ለብዙ ዓመታት ጥረው ነበር። ስለ መሬት መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራ አሠራሮች እውቀት ለማግኘት በመፈለግ ስለ መሬት ጥልቅ ምርምር አድርገዋል። የአውሎ ነፋሶችንና የውሽንፍሮችን አቅጣጫ ለመከታተል ወይም የውኃ መጥለቅለቅና ድርቅ የሚደርስበትን ጊዜ ለመተንበይ በህዋ ሳተላይቶች እየታገዙ የአየር ጠባዩን ሁኔታ ያጠናሉ። ይህ ሁሉ ጥናት የእነዚህን የተፈጥሮ ኃይሎች አደገኛነት ለመቀነስ ያስችለናል ብለው ተስፋ የሚያደርጉበትን መረጃ ሰጥቷቸዋል።

ታዲያ እንዲህ ዓይነቶቹ ጥረቶች ውጤት አስገኝተዋልን? እንዲህ ዓይነቱን ብዙ ወጪና ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ ጥረት በተመለከተ የተፈጥሮ አካባቢን የሚያጠና አንድ ድርጅት እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል:- “እነዚህ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠይቁ እርምጃዎች መጠነኛ ጥቅም አላቸው። ይሁን እንጂ ከሚያስገኙት ጥቅም ጋር የማይመጣጠን ከፍተኛ ገንዘብና ጥረት የሚፈጁ ከሆነ፣ ጭራሹንም በአደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸው ኅብረተሰቦች የሚኖሩበትን አደጋ የሚያባብስ ሁኔታ ችላ ለማለት ሰበብ የሚሆን ከሆነ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዘነ ይሆናል።” ለምሳሌ ያህል የባንግላዴሽ የባሕር ዳርቻ ደለልማ ሥፍራ በተደጋጋሚ የውኃ መጥለቅለቅና ማዕበል የሚያጠቃው ቢሆንም ይህን ማወቅ ብቻውን በሚልዮን የሚቆጠሩትን የባንግላዴሽ ነዋሪዎች እዚያው ከመኖር ሊያስቀራቸው አልቻለም። በዚህም ምክንያት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ያሳጣ ተደጋጋሚ አደጋ ደርሶአል።

በግልጽ እንደሚታየው ቴክኒካዊ መረጃ ማግኘት ጠቃሚ የሚሆነው እስከ ተወሰነ ደረጃ ድረስ ብቻ ነው። ሌላው አስፈላጊ ነገር ሕዝቦች ለአደጋ በተጋለጡ አካባቢዎች ወይም አካባቢውን በሚበክል መንገድ ከመኖር ሌላ አማራጭ እንዳይኖራቸው የሚያደርገውን ተጽእኖ ለማቃለል መቻል ነው። በሌላ አነጋገር በአደጋዎቹ የደረሰውን ጉዳት ለማቃለል የምንኖርበትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት በጥንቃቄ ማስተካከል ያስፈልጋል። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ተግባር ሊፈጽም የሚችል ማን ነው? ይህን ሊያደርግ የሚችለው ለተፈጥሮ አደጋ መንስኤ የሚሆኑትን ኃይሎች እንኳን ሊቆጣጠር የሚችለው አምላክ ብቻ ነው።

አምላክ ወደፊት የሚፈጽማቸው ሥራዎች

ይሖዋ አምላክ የሚያስወግደው የችግሩ ምልክቶች የሆኑትን ነገሮች ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለሰው ልጅ ችግር ሥረ መሠረት የሆኑትን ነገሮች ያስወግዳል። “ሰው ሰውን ለመጉዳት ገዢ” የሆነባቸውንና ስግብግብና ጨቋኝ የሆኑትን የፖለቲካ፣ የንግድና የሃይማኖት ሥርዓቶች ያጠፋል። (መክብብ 8:​9) ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚተዋወቅ ማንኛውም ሰው በገጾቹ ሁሉ ላይ አምላክ ምድርን ከክፋትና ከስቃይ አላቅቆ ሰላምና ጽድቅ የሚሰፍንባትን ምድራዊ ገነት እንደሚመልስ የሚያመለክቱ በርካታ ትንቢቶች እንዳሉ ሳይገነዘብ ሊያልፍ አይችልም። — መዝሙር 37:​9–11, 29፤ ኢሳይያስ 13:​9፤ 65:​17, 20–25፤ ኤርምያስ 25:​31–33፤ 2 ጴጥሮስ 3:​7፤ ራእይ 11:​18

ኢየሱስ ክርስቶስም ተከታዮቹ እንዲጸልዩ ያስተማራቸው ይህንኑ ነው፤ ይኸውም “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ ነገራቸው። (ማቴዎስ 6:​10) መሲሐዊቷ መንግሥት ነቢዩ ዳንኤል በትንቢት እንደተናገረው ፍጽምና የሌለውን ሰብአዊ አገዛዝ በሙሉ በማስወገድ በቦታቸው ትተካለች:- “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።” — ዳንኤል 2:​44

የአምላክ መንግሥት የምታከናውነውና በአሁኑ ጊዜ ያሉ መንግሥታት ግን ሊያከናውኑ ያልቻሉት ነገር ምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለመጪዎቹ ሁኔታዎች አስደናቂ ፍንጭ ይሰጠናል። በእነዚህ ገጾች ላይ እንደ ቀረቡት ሁኔታዎች ማለትም እንደ ረሀብና ድህነት በመሳሰሉት ችግሮች ፈንታ “በምድር ላይ ብዙ እህል ይኖራል፤ በተራሮችም ጫፍ ላይ ይትረፈረፋል። እንደዚሁም “የምድረ በዳም ዛፍ ፍሬውን ይሰጣል ምድርም ቡቃያዋን ትሰጣለች፣ በምድራቸውም ተዘልለው ይኖራሉ።” (መዝሙር 72:​16 አዓት ፤ ሕዝቅኤል 34:​27) የተፈጥሮ አካባቢን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ይነግረናል:- “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሃውም ሐሴት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል። . . . በምድረ በዳ ውኃ፣ በበረሃም ፈሳሽ ይፈልቃልና። ደረቂቱ ምድር ኩሬ፣ የጥማት መሬት የውኃ ምንጭ ትሆናለች።” (ኢሳይያስ 35:​1, 6, 7) ጦርነትም አይኖርም። — መዝሙር 49:​6

ይሖዋ አምላክ ይህን ሁሉ እንዴት እንደሚፈጽምና የተፈጥሮ ኃይሎች በሙሉ ጉዳት እንዳያደርሱ እንዴት እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ አይነግረንም። ይሁን እንጂ በጽድቅ መንግሥቱ ሥር ለሚኖሩ ሁሉ “እነርሱ ከነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ቡሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም” የሚለው ተስፋ እንደሚፈጸም የተረጋገጠ ነው። — ኢሳይያስ 65:​23

የይሖዋ ምስክሮች የአምላክ መንግሥት በ1914 በሰማይ መቋቋሟን በዚህ መጽሔትና በሌሎች የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል። በዚህች መንግሥት አመራር ለ80 ዓመታት ያህል ዓለም አቀፍ ምስክርነት ሲሰጥ የቆየ በመሆኑ ዛሬ ተስፋ በምናደርገው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” መግቢያ በር ላይ እንገኛለን። የሰው ልጅ ከተፈጥሮ አደጋዎች ብቻ ሳይሆን ላለፉት ስድስት ሺህ ዓመታት ወርሶት ከቆየው ከሕመምና ከስቃይ ነፃ ይሆናል። ስለዚያ ጊዜ በእርግጥ “የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” ሊባል ይችላል። — 2 ጴጥሮስ 3:​13፤ ራእይ 21:​4

አሁንስ? አምላክ በተፈጥሮ አደጋዎችም ሆነ በሌላ ምክንያት ለተጨነቁ ሰዎች የሚያደርግላቸው ነገር አለን? በእርግጥ አለ፤ ነገር ግን እርሱ የሚያደርገው አብዛኞቹ ሰዎች በጠበቁበት መንገድ ላይሆን ይችላል።

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰብአዊ የሥራ እንቅስቃሴዎች አካባቢያችንን ከፊት ይልቅ ለተፈጥሮ አደጋዎች የተጋለጠ እንዲሆን አድርገዋል

[ምንጭ]

Laif/Sipa Press

Chamussy/Sipa Press

Wesley Bocxe/Sipa Press

Jose Nicolas/Sipa Press

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ