የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ
በጋና አክራ፣ ሐምሌ 4, 1995፦ ላለፉት 60 ዓመታት ከታዩት ሁሉ የከፋ ኃይለኛ ዝናብ በመጣሉ ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ደርሷል። 200,000 የሚያክሉት ሰዎች ንብረታቸውን በሙሉ ያጡ ሲሆን 500,000 የሚያክሉት ከቤታቸው ተፈናቅለዋል እንዲሁም 22 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በዩ ኤስ ኤ፣ ቴክሳስ፣ ሳን አንጄሎ፣ ግንቦት 28, 1995፦ በረዶ የቀላቀለ ኃይለኛ ዓውሎ ነፋስ 90,000 ነዋሪዎች ያሏትን ይህችን ከተማ እንዳልነበረች ያደረጋት ሲሆን 120 ሚልዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገመት ንብረት አውድሟል።
በጃፓን ኮቤ፣ጥር 17, 1995፦ለ20 ሰከንዶች ብቻ የዘለቀው ርዕደ መሬት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ በአሥር ሺህ በሚቆጠሩት ላይ የመቁሰል አደጋ አድርሶባቸዋል፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ደግሞ ያለ መጠለያ ቀርተዋል።
ያለንበት ጊዜ አደጋዎች የሞሉበት ዘመን ነው ሊባል ይችላል። አንድ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት እንደጠቆመው ከ1963-92 ባሉት 30 ዓመታት ውስጥ በአደጋዎች ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡት፣ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ወይም ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር በየዓመቱ በአማካይ 6 በመቶ እየጨመረ መጥቷል። ይህን አስከፊ ሁኔታ በመመልከት የተባበሩት መንግሥታት የ1990ዎቹን አሥር ዓመታት “ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ አደጋዎች ቅነሣ ዓመታት” ብሎ ለመሰየም ተገዷል።
እርግጥ እንደ ዓውሎ ነፋስ፣ የእሳተ ጎሞራ ፍንዳታ ወይም ርዕደ መሬት ያሉት የተፈጥሮ ኃይሎች ሁልጊዜ ጥፋት ያደርሳሉ ማለት አይደለም። የተፈጥሮ ኃይሎች በሰው ልጆች ላይ አንዳችም ጉዳት ሳያደርሱ በየዓመቱ በመቶ ለሚቆጠሩ ጊዜያት ይከሰታሉ። ነገር ግን በሕይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጥፋት በሚያደርሱበት ጊዜ የተፈጥሮ አደጋዎች ተብለው መጠራታቸው ተገቢ ነው።
የተፈጥሮ አደጋዎች እየጨመሩ መሄዳቸው የማይቀር ነገር ይመስላል። ናቹራል ዲዛዝተርስ—አክትስ ኦቭ ጎድ ኦር አክትስ ኦቭ ማን? የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች አካባቢያቸውን ይበልጥ ለከባድ የተፈጥሮ አደጋ የተጋለጠ እንዲሆን በማድረግ በእነዚህ አደጋዎች ይበልጥ እንዲጠቁ አድርገዋል።” መጽሐፉ አንድ ምሳሌም ሰጥቷል፦ “ከትላልቅ የሸክላ ጡብ የተሠሩ ጥቅጥቅ ያሉ ቤቶች የሚገኙበት አንድ ገደል አፋፍ ላይ የተቆረቆረ መንደር አለ እንበል። ቀላል የሆነ ርዕደ መሬት እንኳ የሰው ሕይወት ሊያጠፋና ከፍተኛ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ አደጋ እንዲከሰት ይበልጥ ምክንያት የሆነው ርዕደ መሬቱ ነው ወይስ ሰዎች በዚህ አደገኛ መሬት ላይ እንደዚያ በመሰሉ አደገኛ ቤቶች ውስጥ መኖራቸው?”
ይሁንና የተፈጥሮ አደጋዎች እየጨመሩ መሄዳቸው ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንግዳ የማይሆንበት ሌላም ምክንያት አለ። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ‘በነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ላይ’ ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ “ራብና የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ሥፍራ” እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:3, 6-8 አዓት) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘በመጨረሻው ቀን’ ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው እና መልካም የሆነውን የማይወዱ እንደሚሆኑ ይናገራል።a (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ብዙውን ጊዜ እነዚህ ባሕርያት ሰው ተፈጥሮን የሚጻረር ነገር በመፈጸም የሰውን ልጅ ይበልጥ ለተፈጥሮ ኃይሎች እንዲጋለጥ ያደርጉታል። ሰው ሠራሽ አደጋዎችም አብዛኛዎቹ ሰዎች ሳይወዱ በግድ ከሚኖሩበት ፍቅር የሌለው ማኅበረሰብ መካከል የሚበቅሉ ፍሬዎች ናቸው።
የፕላኔታችን ነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ፣ የሰው ልጅ ባሕርይ የሰዎችን ሕይወት ይበልጥ አደጋ ላይ የሚጥል እየሆነና የምድር የተፈጥሮ ሃብት ከጊዜ ወደ ጊዜ አላግባብ እየባከነ ሲሄድ አደጋዎች በሰው ልጅ ላይ ከፍተኛ ችግር ማስከተላቸውን ይቀጥላሉ። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደሚብራራው በዚህ ወቅት የእርዳታ ቁሳቁሶችን ማቅረብ ራሱን የቻለ ፈታኝ ተግባር ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለ መጨረሻው ቀን ምልክቶች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ እና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 98-107 ተመልከት።
[ምንጭ]
ከላይ፦ Information Services Department, Ghana; በስተቀኝ፦ San Angelo Standard-Times
[ምንጭ]
COVER: Maxie Roberts/Courtesy of THE STATE