የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 12/15 ገጽ 3-7
  • ኢየሱስ የተወለደው በበረዶ ወራት ነበርን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ኢየሱስ የተወለደው በበረዶ ወራት ነበርን?
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምን ትርጉም አለው?
  • በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ስሌቶች
  • ታዲያ ከየት መጣ?
  • ምንም አይጎዳም?
  • ኢየሱስ የተወለደው መቼ ነበር?
    ንቁ!—2008
  • ኢየሱስ የተወለደው መቼ ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ገና በእርግጥ ክርስቲያናዊ በዓል ነውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • አንዳንዶች የገና በዓልን የማያከብሩት ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
ለተጨማሪ መረጃ
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 12/15 ገጽ 3-7

ኢየሱስ የተወለደው በበረዶ ወራት ነበርን?

“ከበረዶው ብዛት የተነሣ በኢየሩሳሌም ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ ቀጥ ብሏል።” እንዲሁም “የተራዘመው የበረዶ ዝናብ በሰሜኑ ክፍል የሚኖሩትን ግራ አጋብቷቸዋል።” ዘ ጀሩሳሌም ፖስት በተባለው ጋዜጣ ላይ ይወጡ የነበሩ እነዚህን የመሰሉ ርዕሶች በያዝነው መቶ ዘመን በእስራኤል ከነበሩት የክረምት ወራት ሁሉ አስከፊ በሆነው በ1992 ክረምት ለእስራኤላውያን አንባቢዎች መቅረባቸው የተለመደ ሆኖ ነበር።

በጥር ወር የአርሞንዔም ተራራ አናት ከ7 እስከ 12 ሜትር በሚደርስ የበረዶ ክምር ተሸፍኖ ነበር። ክረምቱ ግን ገና አላቆመም። ከጎላን ኮረብታዎችና ከላይኛው የገሊላ ክፍል አንሥቶ ኢየሩሳሌምንና አቅራቢያዋ የሆነችውን (በገጹ ሽፋን ላይ የምትታየውን) ቤተ ልሔምን ጨምሮ በደቡብ እስከሚገኘው እስከ ኔጌብ ድረስ ባለግርማና ለስላሳ ግን ኃይለኛ የሆነው በረዶአማ የአየር ጠባይ የእስራኤላውያንን ዕለታዊ እንቅሰቃሴ እየደጋገመ ያቋርጥ ነበር። አንድ የጀሩሳሌም ፖስት ርዕስ እንዲህ ብሏል:- “ባለፈው ሳምንት የተዥጎደጎዱት የካትዩሻ ሮኬቶች ሊያደርጉ ያልቻሉትን በትናንትናው ዕለት የጣለው ኃይለኛ በረዶ መንደሮችን ዘግቶ ነዋሪዎቹን ከቤታቸው እንዳይወጡ በመከልከል አላንቀሳቅስ ብሏቸው ነበር።”

ኃይለኛው ክረምት ጉዳት ያመጣው በከተማ ነዋሪዎች ላይ ብቻ አይደለም። ከየቦታው በመቶዎች የሚቆጠሩ ላሞችና ጥጃዎች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ዶሮዎች የሌሊቱ ቅዝቃዜ ከዜሮ በታች በጣም በመውረዱ ሳቢያ እንደሞቱ የሚገልጽ ሪፖርት መጥቷል። በረዶው በቂ ያልሆነ ይመስል ከባድና በጣም ቀዝቃዛ ዝናብም ከባድ ጉዳት አድርሷል። አንድ ቀን ሁለት እረኛ ልጆች ደራሽ ጎርፍ በርካታ በጎቻቸውን እንዳይወስድባቸው ለማዳን ሲሞክሩ እነርሱ ራሳቸው በጎርፉ ተወስደዋል።

እንዲህ ያለው ክረምት በመካከለኛው ምሥራቅ የተለመደ ባይሆንም በእስራኤል አገር የሚታተመው ኤሬጽ የተባለው መጽሔት እንደሚከተለው ብሏል:- “ባለፉት 130 ዓመታት በእስራኤል ምድር ላይ የተመዘገበው የሜትሮሎጂ መረጃ እንደሚያሳየው በኢየሩሳሌም ውስጥ በረዶ መዝነቡ የተለመደ ነገር ነው። . . . ከ1949 እስከ 1980 ድረስ የኢየሩሳሌም ከተማ ሃያ አራት በረዶአማ ክረምት አሳልፋለች።” ይሁን እንጂ ይህ ጉዳይ የሜትሮሎጂና የሰብአዊ ጉዳይ አጥኚዎች ብቻ የሚከታተሉት ጉዳይ ነው ወይስ ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም ልዩ ትርጉም አለው?

ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምን ትርጉም አለው?

ብዙ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ልደት ሲያስቡ የሚታያቸው በገና በዓል ወቅት በሚታየው ግርግም ውስጥ ያለ አንድ የሕፃን አልጋ ነው። ሕፃኑ ኢየሱስ በጨርቅ ተጠቅልሎና በእናቱ እቅፍ ውስጥ ሆኖ፣ የአካባቢውን ምድር ደግሞ በረዶ ሸፍኖት ይታያል። ብዙ ሰው የተቀበለው ይህ አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ታሪካዊ ወቅት ከሚሰጠው መግለጫ ጋር ይስማማልን?

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ልደት በጥንቃቄ የተጠናቀረ ዘገባ አቅርቦልናል:- “በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፣ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፣ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው:- እነሆ፣ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ [በቤተ ልሔም] መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ:- ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።” — ሉቃስ 2:​8–14

ይህንን ታሪክ ለአንድ እስራኤላዊ ብታነብለትና ከዓመቱ ውስጥ በየትኛው ጊዜ ላይ የተከናወነ ነገር ይመስልሃል ብለህ ብትጠይቀው “ከሚያዝያ እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ ነው” ብሎ ሊመልስልህ ይችላል። ለምን? መልሱ ቀላል ነው። በእስራኤል አገር ከኅዳር እስከ መጋቢት ድረስ ያለው ጊዜ፣ ታኅሣሥ 25ን ጨምሮ ቀዝቃዛና ዝናባማ የሆነ የክረምት ወቅት ስለሆነ ነው። በዚህ ወቅት እረኞች መንጋዎቻቸውን እየጠበቁ በሌሊት በሜዳ አያድሩም። ለምን እንደማያድሩ በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ የተጠቀሱትን ሪፖርቶች በመመልከት ልትረዳ ትችላለህ። ኢየሱስ የተወለደባት ቤተልሔም ከኢየሩሳሌም እምብዛም የማትርቅና ከፍ ባለ ቦታ ላይ የምትገኝ ከተማ ናት። የአየሩ ጠባይ ደህና ነው በሚባልበት ዓመት እንኳ በቤተ ልሔም በተለይ በክረምት ወራት ሌሊቱ በጣም ቀዝቃዛ ነው። — ሚክያስ 5:​2፤ ሉቃስ 2:​15

ኢየሱስ በረዶአማ በሆነው የታኅሣሥ ወር ሊወለድ እንደማይችል በዚያን ጊዜ የነበረው ታሪካዊ ሁኔታ ተጨማሪ ፍንጭ ይሰጠናል። የኢየሱስ እናት ማርያም መውለጃዋ የተቃረበ ቢሆንም ከመኖሪያ ቤቷ ከናዝሬት እስከ ቤተ ልሔም ድረስ መጓዝ ነበረባት። የሮም መሪ የነበረው አውግስጦስ ቄሣር ያወጣውን የሕዝብ ቆጠራ አዋጅ በመታዘዝ እሷና ዮሴፍ ለምዝገባ ሄደዋል። (ሉቃስ 2:​1–7) በዚህ ጊዜ የአይሁድ ሕዝብ የሮማ መንግሥት ቀረጥ አብዝቶባቸው ስለነበር የሮምን አገዛዝ በመጥላት ለማመፅ ተቃርቦ ነበር። ታዲያ የሮማ መንግሥት በጣም አስቸጋሪ በሆነውና በማያመቸው የክረምት ወራት ረጅም ርቀት ተጉዘው እንዲመዘገቡ በማዘዝ የማያስፈልግ ቁጣ ለምን ያነሣሳል? እንግዲያው አዋጁ ለጉዞ አመቺ በሆነው የመከር ወይም የበልግ ወራት ወጥቶ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰቡ የበለጠ ምክንያታዊ አይሆንምን?

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ስሌቶች

ታሪካዊውና መልክዓ ምድራዊው ማስረጃ ኢየሱስ በታኅሣሥም ይሁን በማንኛውም ሌላ የክረምት ወር አለመወለዱን ያረጋግጣል። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተወለደበትን ጊዜ በትንቢት አማካኝነት ይገልጥልናል። ይህን የሚናገረው የት ላይ ነው?

በዳንኤል መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ላይ መሲሑን ከሚመለከቱት አስደናቂ ትንቢቶች ውስጥ አንዱን እናገኛለን። ትንቢቱ ስለመምጣቱና ኃጢአትን ስለማስቀረቱ እንዲሁም ታዛዥ የሰው ልጆች “የዘላለምን ጽድቅ” እንዲያገኙ መሠረት ስለሆነው ስለመገደሉም ጭምር ይዘረዝራል። (ዳንኤል 9:​24–27፤ ከማቴዎስ 20:​28 ጋር አወዳድር።) በዚህ ትንቢት መሠረት እነዚህ ሁሉ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከወጣበት ከ455 ከዘአበ ጀምሮ በ70 የዓመታት ሳምንታት ውስጥ የሚከናወኑ ነገሮች ናቸው።a (ነህምያ 2:​1–11) በዚህ ትንቢት ውስጥ የተጠቀሱትን የጊዜ አመዳደቦች መሠረት አድርገን ስንነሣ መሲሑ በ70ኛው የዓመታት ሳምንት መጀመሪያ ላይ ይመጣል ማለት ነው። ይህም የሆነው ኢየሱስ ራሱን ለጥምቀት ባቀረበበትና በይፋ የመሲሕነት ሥራውን በጀመረበት በ29 እዘአ ነበር። “በሱባኤውም እኩሌታ” ወይም ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ መሲሑ ይገደላል፤ በዚህም በሙሴ ሕግ ሥር ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶች በሙሉ ያስገኙት የነበረው ጥቅም እንዲያበቃ ያደርጋል። — ዕብራውያን 9:​11–15፤ 10:​1–10

ይህ ትንቢት የኢየሱስ አገልግሎት ርዝማኔ ሦስት ዓመት ተኩል እንደነበረ ይገልጻል። ኢየሱስ በፀደይ ወራት ኒሳን 14 (በአይሁዶች አቆጣጠር) 33 እዘአ በዋለው የማለፍ በዓል ዕለት ሞተ። በዚያ ዓመት የማለፍ በዓል የዋለው ሚያዝያ 1 ቀን ይሆናል። (ማቴዎስ 26:​2) ከዚህ ተነሥተን ሦስት ዓመት ተኩል ወደ ኋላ ስንቆጥር የተጠመቀበት ጊዜ 29 እዘአ ጥቅምት መጀመሪያ ላይ ሆኖ እናገኘዋለን። ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ 30 ዓመት ሆኖት ነበር በማለት ሉቃስ ይነግረናል። (ሉቃስ 3:​21–23) ስለዚህ ኢየሱስ የተወለደው በጥቅምት ወር መጀመሪያ አካባቢ ላይ ነው ማለት ነው። በዚህ ወቅት ሉቃስ እንደዘገበው እረኞቹ “መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ” ሊያድሩ ይችላሉ። — ሉቃስ 2:​8

ታዲያ ከየት መጣ?

ኢየሱስ የተወለደው ጥቅምት መጀመሪያ ላይ መሆኑን ማስረጃዎቹ ካረጋገጡ ታዲያ ታኅሣሥ 25 የሚከበረው ለምንድን ነው? ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ ይህ በዓል መከበር የጀመረው ኢየሱስ ከተወለደ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ መሆኑን ሲናገር “በ4ኛው መቶ ዘመን ብዙዎቹ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያኖች የክርስቶስን የልደት በዓል ታኅሣሥ 25 ማክበር ጀመሩ። በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች የገናን በዓል ለረጅም ጊዜ ሲቃወሙ ቆይተው ነበር። ውሎ አድሮ ግን እነሱም ተስማሙበት” ይላል።

ልማዱ ክርስቶስ ከሞተ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ክርስቲያን ነን በሚሉት ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት ያገኘው ለምንድን ነው? ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ እውቀት ይሰጠናል:- “ከገና በዓል ጋር የተያያዙት ባሕላዊ ልማዶች ከተለያዩ ምንጮች የተገኙና የክርስቶስ ልደት በዓልና በክረምቱ አጋማሽ ላይ የሚከበሩት አረመኔያዊ የእርሻና የፀሐይ በዓሎች በመገጣጠማቸው ምክንያት የመጡ ናቸው። በሮማ ግዛት ሳተርናልያ (ታኅሣሥ 17) የፈንጠዝያና ስጦታ የሚሰጣጡበት ጊዜ ነበር። ታኅሣሥ 25ም ቢሆን የጽድቅ ፀሐይ ተብላ የምትጠራው የኢራንያን የምሥጢር አምላክ ሚትረ የተወለደችበት ቀን ነው ተብሎ ይታመን ነበር።”

ይህ ሁሉ እንዲሁ “በአጋጣሚ” የሆነ ነገር ነበርን? በአጋጣሚ ሊሆን አይችልም! የሮም መንግሥት በአራተኛው መቶ ዘመን በንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ዘመን ከክርስትና አሳዳጅነት ወደ “ክርስትና” ሞግዚትነት በአስደናቂ ሁኔታ ተቀይሮ በሕግ የታወቀ ሃይማኖት እንዳደረገው ታሪክ ያረጋግጥልናል። የክርስትናን መሠረታዊ ትርጉም ያልተረዱ አብዛኞቹ ሰዎች አዲሱን እምነት ተቀብለው የለመዷቸውን አረመኔያዊ በዓሎች “ክርስትና” የሚል ርዕስ በመስጠት ማክበር ጀመሩ። ስለዚህ የክርስቶስን ልደት ለማክበር አስቀድሞ “የጽድቅ ፀሐይ” ተብላ ለምትጠራው ጣዖት ከተወሰነው ከታኅሣሥ 25 ሌላ ተስማሚ የሆነ ምን ቀን ማግኘት ይችላሉ?

ምንም አይጎዳም?

በአይሁድ ሥርዓት ያደጉት የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን አለማክበራቸው ምንም አያጠራጥርም። ኢንሳይክሎፔዲያ ጁዳይካ “በአይሁዳውያን ባሕል የልደት ቀንን ማክበር ፈጽሞ የማይታወቅ ነገር ነበር” በማለት ይናገራል። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እንዲህ የመሰለውን በዓል እንዳላከበሩ ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ የተወለደበትን ቀን ከማክበር ይልቅ ራሱ በማያሻማ ሁኔታ ያዘዛቸውን ቀን ማለትም ኒሳን 14ን በሞቱ መታሰቢያነት ያከብራሉ። — ሉቃስ 22:​7, 15, 19, 20፤ 1 ቆሮንቶስ 11:​23–26

ከክርስቶስ ዘመን ብዙ መቶ ዘመን አስቀድሞ የአምላክ ሕዝቦች የነበሩት በባቢሎን የነበረው የግዞት ዘመናቸው ወደማለቁ ለተቃረበው አይሁዶች “እናንተ የእግዚአብሔር ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፣ እልፍ በሉ፣ እልፍ በሉ፣ ከዚያ ውጡ፣ ርኩስን ነገር አትንኩ፣ ከመካከልዋ ውጡ፣ ንጹሐንም ሁኑ” የሚል ማስጠንቀቂያ በትንቢት ተነግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 52:​11) እነዚህ ሰዎች የይሖዋን ንጹሕ አምልኮ እንደገና ለማቋቋም ወደ አገራቸው መመለስ ነበረባቸው። በባቢሎን አገር በነበሩበት ጊዜ ይከተሉት የነበረውን አምልኮና ርኩስ አረመኔያዊ ልማድ ይዞ መመለስ ሊያስቡት እንኳ የማይገባ ነገር ነበር።

ይኸው ተመሳሳይ ትእዛዝ ለክርስቲያኖችም በ2 ቆሮንቶስ 6:​14–18 ላይ በድጋሚ መሰጠቱ ሊያስደንቀን አይገባም። ክርስቶስን አንቀበልም ባሉት አይሁድ ምትክ የኢየሱስ ተከታዮች የእውነተኛ አምልኮ ወኪሎች ሆኑ። ሌሎች ሰዎች ከመንፈሳዊ ጨለማ ወጥተው ወደ እውነት ብርሃን እንዲመጡ የመርዳት ኃላፊነት ተቀበሉ። (1 ጴጥሮስ 2:​9, 10) የክርስቶስን ትምህርቶች ከአረመኔ ልማዶችና በዓሎች ጋር ከቀላቀሉ እንዴት ይህን ዓይነት እርዳታ ሊሰጡ ይችላሉ?

“በረዶ የፈነጠቀበትን የገና በዓል” ማክበር ለብዙዎች ደስ የሚያሰኝ ቢሆንም ‘ርኩስን እንደመንካት’ ይቆጠራል። (2 ቆሮንቶስ 6:​17) አምላክንና ክርስቶስን በእውነት የሚወድ ሰው ከዚህ በዓል ይርቃል።

የገና በዓል ከአረመኔዎች የመጣ ከመሆኑም በላይ ኢየሱስ የተወለደው በጥቅምት ስለሆነ እውነትን ሊወክል የሚችል በዓል አለመሆኑን ተመልክተናል። አዎን፣ አንድ ሰው በአእምሮው ውስጥ የሚስለው ትዕይንት ምንም ዓይነት ቢሆን ኢየሱስ የተወለደው በበረዶ ወራት አልነበረም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይህ ትንቢት ሙሉ በሙሉ የተብራራበትን ጦርነት የሌለበት ዓለም ይመጣ ይሆንን? የሚለውን በኒው ዮርኩ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የእንግሊዝኛ ብሮሹር ገጽ 26 ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በበረዶ የተሸፈነችው ኢየሩሳሌም ከምሥራቅ በኩል ስትታይ

[ምንጭ]

Garo Nalbandian

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኢየሩሳሌም ግንቦች ዙሪያ የሚገኝ በረዶ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከዚህ በታች እንደሚታየው እረኞች በድንጋያማዎቹ የኮረብታ ጥጎች በሌሊት ማደር የሚችሉት በሞቃታማ ወራት ብቻ ነው

[ምንጭ]

Garo Nalbandian

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ