ገና በእርግጥ ክርስቲያናዊ በዓል ነውን?
ዘወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚናገረው “ገና ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት የሚያከብሩበት ቀን ነው።” ያም ሆነ ይህ ኢንሳይክሎፔድያው በማከል፦ “የጥንቶቹ ክርስቲያኖች [የኢየሱስን] ልደት አላከበሩም ምክንያቱም የማንኛውንም ሰው የልደት በዓልን ማክበርን አረማዊ ልማድ አድርገው ይመለከቱት ነበር” ብሏል።
በጎልቢ እና ፐርዱ የተዘጋጀው ዘ ሜኪንግ ኦቭ ዘ ሞደርን ክሪስማስ የተባለ መጽሐፍ “የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ልደት አላከበሩም። ራሳቸው የልደት ቀናት ከአረማዊ ተግባራት ጋር የተቆራኙ ሲሆን ወንጌሎች የክርስቶስን ልደት በተመለከተ ይህ ነው ብለው የተወሰነ ቀን አይጠቅሱም” ብሏል።
የልደት ቀን ክብረ በዓል ክርስቲያናዊ ሥረ መሠረት ሳይኖረው እንዲህ ያለ ታላቅ “ክርስቲያናዊ” በዓል የሆነው እንዴት ነው?
“የገና በዓል” አረመኔያዊ መሠረት
“ለሁሉም ሰው ሠርግና ምላሽ ሆኗል፤ ሁሉም ይደሰታል፣ ሥራ እና ንግድ ለጊዜው ጋብ ብሏል፣ ቤቶች ከዓመት እስከ ዓመት ለምለም በሆነው ጥድ አጊጠዋል። ባልንጀሮች እርስ በእርስ ይጠያየቃሉ፤ እንዲሁም ስጦታ ይለዋወጣሉ። በተጨማሪም አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች ለደንበኞቻቸው ስጦታ ያበረክታሉ። መላው ጊዜ የመደሰቻና ሰው ሁሉ በጎ ለማድረግ ፈቃደኛ የሚሆንበት ጊዜ ነበር። በተጨማሪም ሕዝቡ የሚፈነጥዙበት ጊዜ ነበር።”—ፓጋኒዝም ኢን ክሪስቸን ፌስቲቫልስ (አረማዊነት በክርስቲያናዊ በዓላት ውስጥ) በ ጄ ኤም ዊለር።
ይህ መግለጫ ከምታውቁት የገና በዓል ጋር አልተመሳሰለባችሁም? የሚገርመው ግን ይህ የገና በዓል አልነበረም! ከዚህ ይልቅ የሳምንት ዕድሜ ያለውና ከክረምት በዓል ጋር የተያያዘውን የአረመኔያዊ ሮማውያን በዓል ስለሆነው ሳተርናሊያ የተሰጠ መግለጫ ነው። (በስተ ጀርባ ባለው ገጽ ላይ በሥዕል ተገልጿል።) በሮሙ ሚትሬይክ ሃይማኖት የግብዣ ቀን መሠረት የማትረታው ፀሐይ ልደት ታኅሣሥ 25 ቀን ይከበር ነበር። በሮማውያኑ የሚትራ ሃይማኖት ዋነኛው የድግስ በዓል ይህ ነበር።
ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ብሏል፦ “ታኅሣሥ 25 የኢራንያን የብርሃን አምላክ የሆነው የሚትራ የልደት ቀን እና . . . ለማትበገረው ፀሐይ የተሰጠው ቀን እንዲሁም የሳተርናሊያ ማግስት በዓላቱ የሚያስከትሉትን ጠንቅ ለመከላከል የኢየሱስ ልደት ገና ተደርጎ በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት አገኘ።” ስለዚህ አረመኔያዊው የልደት ቀን ክብረ በዓል በሚትራ ፋንታ ክርስቶስን በመተካት ቀላል የስም ለውጥ ካደረገ በኋላ እስካሁን ቀጥሏል!
ቢሆንም የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ልደት ልዩ የሆነና ሊታወስ የሚገባው እንደሆነ ይሰማዎት ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረውን ብንመረምር እውነቱ ይከሰትልናል።
አስደሳች ቀን
የሉቃስ ወንጌል ሁለተኛ ምዕራፍ የተፈጸመውን ትዕይንት ይተርክልናል። ሉቃስ የሰማይ መላእክት፣ ተራ እረኞች፣ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችና ማርያም ራሷ ለዚህ አስደናቂ ክንዋኔ እንዴት ያለ ምላሽ እንደሰጡ ይነግረናል።
በመጀመሪያ “መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች” በቀዝቃዛው የክረምት አጋማሽ ላይ ይህንን ሊያደርጉ እንደማይችሉ አንዘንጋ። “የጌታ መልአክ” በተገለጠና የአምላክ ክብር በዙሪያቸው ባበራ ጊዜ እረኞቹ መጀመሪያ ፈርተው ነበር። መልአኩ “እነሆ፣ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” ብሎ ሲነግራቸው ተረጋጉ። “ብዙ የሰማይ ሠራዊት” መላእክት ድንገት ሲታዩ እረኞቹ ይህ ልደት ከሌላው ለየት ያለ እንደሆነ አወቁ። የሚያስደንቀው ግን መላእክቱ አዲስ ለተወለደው ሕፃን ስጦታዎች አላመጡም። ከዚህ ይልቅ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” በማለት መላእክቱ ይሖዋን አመሰገኑ።—ሉቃስ 2:8–14
ይሖዋ ይህንን አስደሳች ልደት አስታውቋቸው ስለነበር ሁላችንንም እንደሚሰማን እረኞቹም ሕፃኑን በገዛ ዓይናቸው ለማየት ፈለጉ። ሕፃኑ በግርግም ውስጥ ተኝቶ ሲያገኙት መላእክቱ የተናገሩትን ሁሉ ለወላጆቹ ነገሯቸው። ከዚያም እረኞቹ ሕፃኑን ሳይሆን “እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ።”—ሉቃስ 2:15–18, 20
የኢየሱስ እናት ማርያም የበኩር ልጅዋን በሰላም በመገላገሏ እንደተደሰተች አያጠራጥርም። ከዚህም በተጨማሪ “በልብዋ ይዛ ታሰላስለው ነበር።” ከዚያም የሙሴን ሕግ በመታዘዝ ከባሏ ዮሴፍ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች። ይህ የልደት ቀን ክብረ በዓል አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እንደዚህ “ያደረጉበት ምክንያት በእግዚአብሔር ሕግ ‘ወንድ የሆነ በኩር ልጅ ሁሉ ለእግዚአብሔር ተሰጥቶ የተቀደሰ ይሆናል’ የሚል ትእዛዝ ተጽፎ ስለነበር” ሕፃኑን ወደ አምላክ ለማቅረብ ነው።—ሉቃስ 2:19, 22–24 የ1980 ትርጉም
ማርያምና ዮሴፍ “እርሱም ሕይወቱን ለእግዚአብሔር የሰጠ ጻድቅ ሰው ነበር፤ የእስራኤልን የመዳን ተስፋ ይጠባበቅ ነበር” (እንደ 1980 ትርጉም) ብሎ ሉቃስ ከገለጸው ስምዖን ጋር በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ተገናኙ። “በጌታም የተቀባውን ሳያይ እንደማይሞት በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር።” ቀጥሎ የሆነውም ነገር ‘በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተፈጸመ’ ነበር። ስምዖን ሕፃኑን አቀፈው፤ ይህንንም ያደረገው ስጦታ ለመስጠት ሳይሆን “ጌታ ሆይ፣ አሁን እንደ ቃልህ ባርያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው” ብሎ አምላክን ለማመስገን ነበር።—ሉቃስ 2:25–32
ቀጥሎም በዕድሜ የገፋችው ነቢይቷ ሐና መጣች። እርሷም “እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር።”—ሉቃስ 2:36–38
ማርያም፣ ስምዖን፣ ሐና፣ እረኞቹ፣ የሰማይ መላእክትም ጭምር በኢየሱስ መወለድ ሁሉም ተደስተዋል። ይሁን እንጂ በልደት ቀን ለፈንጠዝያም ሆነ ስጦታ በመለዋወጥ እንዳልተካፈሉ ልብ በሉ። ከዚህ ይልቅ የመዳናቸው ሰማያዊ አዘጋጅ የሆነውን ይሖዋን ከፍ ከፍ አድርገዋል።
አንዳንዶች አሁንም ‘“ሦስቱ ጠቢባን ሰዎች” ስጦታ በመስጠት ኢየሱስን ካከበሩት የገና ስጦታ ማበርከት እንዴት ስሕተት ሊሆን ይችላል?’ የሚል ምክንያት ያቀርቡ ይሆናል።
የገና ስጦታዎች
እንደገና የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ እንመርምር። በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ላይ ስለዚህ ጉዳይ ተጽፎ ታገኛላችሁ። ምንም ዓይነት የልደት አክብሮትም ሆነ የተወሰነ ቀን ከመጥቀስ ይልቅ እዚህ ላይ የሚናገረው ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ስለተፈጸመ ነገር ነው። በቁጥር 1 ላይ ማቴዎስ እንግዶቹን “ከምሥራቃዊው ክፍል የመጡ ኮከብ ቆጣሪዎች [በግሪክኛ ማጂ]” [አዓት] ብሎ የጠራቸው ስለ ይሖዋ አምላክ ምንም ዓይነት እውቀት ያልነበራቸው አረማውያን ናቸው። እነዚህ ሰዎች የሚከተሉት ኮከብ የመራቸው በቀጥታ ኢየሱስ ወደ ተወለደበት ወደ ቤተ ልሔም ሳይሆን ንጉሥ ሄሮድስ ይገዛ ወደ ነበረበት ወደ ኢየሩሳሌም ነው።
ይህ ክፉ ገዢ ስለ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ” በሰማ ጊዜ ልጁን መግደል እንዲችል “ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ” ካህናቱን አማከራቸው። ካህናቱ የመሲሑ የትውልድ ስፍራ ቤተ ልሔም እንደሆነ የሚጠቁመውን የሚክያስ ትንቢት ጠቅሰው መለሱለት። (ሚክያስ 5:2) ሄሮድስ በግብዝነት “ሂዱ፣ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ” ብሎ በግብዝነት እንግዶቹን አዘዛቸው። ኮከብ ቆጣሪዎቹ መንገዳቸውን ሲያቀኑ ኮከቡም “ሕፃኑ [ትንሹ ልጅ አዓት] ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር።” አስታውሱ እዚህ ላይ ኢየሱስ የተገለጸው እንደ ጨቅላ ሕፃን ሳይሆን “ትንሽ ልጅ” ተብሎ ነው።—ማቴዎስ 2:1–10
ነገሥታትን ከሚጎበኝ ጥሩ ቦታ ያለው የምሥራቅ ሰው ጋር በሚስማማ ሁኔታ አረማውያኑ ኮከብ ቆጣሪዎች ወድቀው ከሰገዱለት በኋላ “[ለትንሹ ልጅ] እጅ መንሻ ወርቅና እጣን ከረቤም አቀረቡለት።” ማቴዎስ በመቀጠል አንዲህ አለ፦ “ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ” ይላል።—ማቴዎስ 2:11, 12
ከዚህ አጭር የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በመነሣት አንዳንዶች ለገና ስጦታ ልማድ ድጋፍ ለማግኘት ሙከራ አድርገዋል። የሆነ ሆኖ ዲስከቨሪንግ ክሪስማስ ካስተምስ ኤንድ ፎልክሎር የተባለው መጽሐፍ ሲያብራራ አሁን ያለው የስጦታ ልውውጥ ሮማውያኑ ድሀ ጎረቤቶቻቸውን ከሚረዱበት የሳተርናሊያው ስጦታዎች የመጣ ነው “የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን . . . የማጂዎች ስጦታ መታሰቢያ ያለውን ትርጉም በብልሃት አስተላልፋለች” ብሏል። ይህ በኢየሱስ መወለድ እግዚአብሔርን ካወደሱት እንደ ተራዎቹ እረኞች ከመሳሰሉት እውነተኛ አምላኪዎች ምንኛ የተለየ አድራጎት ነው!
ክርስቶስን እንደ ንጉሥ አድርጋችሁ አክብሩት!
ዛሬ ኢየሱስ ገና ሕፃን አይደለም። ኃያል ገዢ፣ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ነው። እንዲህም ተደርጎ ሊከበር ይገባዋል።—1 ጢሞቴዎስ 6:15, 16
አዋቂ ከሆንክ አንተ ባለህበት ሰዎች የልጅነት ፎቶግራፍህን ሲያዩ እፍረት ተሰምቶህ ያውቅ ይሆን? እውነት ነው እንዲህ ያሉ ምስሎች ወላጆችህ አንተ ስትወለድ ያገኙትን ደስታ ያስታውሳቸዋል። ነገር ግን አሁን ራስህን የቻልህ ትልቅ ሰው ሆነሃል። ታዲያ ሰዎች ሁልጊዜ አሁን ያለህን ማንነት እንዲያዩልህ አትመርጥምን? በተመሳሳይም አረመኔያዊ ልማድ በሆነው ገና እና ኢየሱስን እንደ ንጉሥ አድርገው ከማክበር ወደ ኋላ በሚጎትታቸው የሕፃን አክብሮት በየዓመቱ ተከታዮቹ ነን የሚሉ መማረካቸው ምን ያህል በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ማላገጥ እንደሆነ አስብ። ሌላው ቀርቶ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጭምር ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ አሁን በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳለ ማለትም በሰማይ ያለ ንጉሥ እንደሆነ ማስረዳት አስፈልጎት ነበር። “ክርስቶስንም በሥጋ እንደሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፣ አሁን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም” በማለት ጳውሎስ ጽፏል።—2 ቆሮንቶስ 5:16
ክርስቶስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ በመሆን በቅርቡ ሥቃይን፣ መከራን፣ በሽታን እና ሞትን በማስወገድ ትንቢታዊ ተስፋዎችን ይፈጽምልናል። በገነታዊ ሁኔታዎች ሥር እዚሁ ምድር ላይ ለሁሉም የተንጣለለ ቤትና በውጤቱ የሚያረካ ሥራ እንዲኖራቸው የሚያደርግ እሱ ነው። (ኢሳይያስ 65:21–23፤ ሉቃስ 23:43፤ 2 ቆሮንቶስ 1:20፤ ራእይ 21:3, 4) እነዚህ ኢየሱስን የማያስከብር ነገር ከመፈጸም የሚቆጥቡን በቂ ምክንያቶች ናቸው።
የራሱን የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል እውነተኛ ክርስቲያኖች ከስጦታዎች ሁሉ የላቀውን ማለትም ወደ ዘላለም ሕይወት ሊመራ የሚችለውን ስለ አምላክ ዓላማ የሚናገረውን እውቀት ለመስጠት ይጥራሉ። (ዮሐንስ 17:3) ይህን የመሰለው ሰጪነት ላቅ ያለ ደስታ ያመጣል። ኢየሱስ እንዳለው “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [ደስተኛ አዓት] ነው።”—ሥራ 20:35፤ ሉቃስ 11:27, 28
አንዳቸው ለሌላው ልባዊ አሳቢነት ያላቸው ክርስቲያኖች ከዓመቱ በየትኛውም ቀን ሳይጠበቅ ስጦታ በመስጠት ፍቅራቸውን ከመግለጽ አንዳችም የሚያግዳቸው ነገር የለም። (ፊልጵስዩስ 2:3, 4) አንድ ቀላል ምሳሌ ብንወስድ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሩን ካዳመጠ በኋላ ያለውን ምስጋና ለመግለጽ ከፈለገ ልጅ አንድ ሥዕል በስጦታነት መቀበሉ እንዴት ልብን በደስታ ሞቅ የሚያደርግ ነው! ከቤተ ዘመድም ያላቸውን ፍቅር የሚገልጽ ያልተጠበቀ ስጦታ ሲቀርብ የሚያበረታታ ነው። በተመሳሳይም ወላጆች ለልጆቻቸው ስጦታ ለመስጠት በዓመቱ ውስጥ ተስማሚ አጋጣሚዎችን ቢመርጡ ከፍ ያለ ደስታ ሊያገኙ ይችላሉ። ይህ ዓይነቱ ክርስቲያናዊ ለጋስነት በበዓል ቀናት አስገዳጅነትም ሆነ በአረመኔያዊ ልማዶች ያልጎደፈ ነው።
በዚህም ምክንያት ዛሬ ከተለያዩ ብሔራት የተውጣጡ ከአራት ሚልዮን ተኩል በላይ የሆኑ ክርስቲያኖች ገናን አያከብሩም። እነዚህ በመደበኛነት ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች ለጎረቤቶቻቸው ምሥክርነት በመስጠት የሚጣደፉት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። (ማቴዎስ 24:14) ምናልባት በቅርቡ እርስዎን ለማነጋገር ወደ ቤትዎ መጥተው ትገናኙ ይሆናል። ይሖዋ አምላክን ከዓመት እስከ ዓመት በየቀኑ ሳያሰልሱ ስለማወደስ ያመጡላችሁን መልእክት በጉጉት መቀበላችሁ ቤተሰባችሁን ወደ ታላቅ ደስታ የሚመራ ያድርገው።—መዝሙር 145:1, 2
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች ከስጦታዎች ሁሉ የላቀውን ማለትም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራውንና ስለ አምላክ ዓላማ የሚናገረውን እውቀት ለጎረቤቶቻቸው ያበረክታሉ
[ምንጭ]
Culver Pictures