በምሥራቅም ሆነ በምዕራብ ይሖዋ ለሕዝቡ ኃይል ይሰጣል
የምስክርነቱ ሥራ በታገደባቸው ክልሎች፣ በብጥብጥ በተከፋፈሉና በቅርብ ጊዜ እገዳ በተነሳላቸው አገሮች ባጠቃላይ በመላው ዓለም አቀፍ መስክ ይሖዋ ለምስክሮቹ “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” መስጠቱን ቀጥሏል።—2 ቆሮንቶስ 4:7 አዓት
በእገዳ ሥር የተገኘ ብልጽግና
በሩቅ ምሥራቅ በሚገኙ ተጎራባች ደሴቶች የስብከቱ ሥራ ከታገደ 17 ዓመት ሆኖታል። በነዚህ ደሴቶች የሚገኙ ምስክሮች ያጋጠማቸው ሁኔታ ተስፋ አስቆርጧቸዋልን? አላስቆረጣቸውም። በዚህ ባለፈው ግንቦት 10,756 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ላይ ደርሰዋል። ከእነዚህም መካከል 1,297 የሚሆኑት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተሠማሩ ናቸው። የዓለም ሁኔታ እየተበላሸ በሄደ መጠን በደሴቶቹ ላይ የሚኖሩት ሰዎች ከምንጊዜም የበለጠ እውነትን የመስማት ፍላጎት እያደረባቸው ነው። ስለዚህ አስፋፊዎቹ 15,654 የሚያክሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ፍላጎት ባላቸው ሰዎች ቤት እንደመሩ ሪፖርት አድርገዋል። ቀደም ብሎ የኢየሱስን ሞት ለማሰብ በጥበብ በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ 25,397 ሰዎች ተገኝተዋል።
“መለኮታዊ ትምህርት” የወረዳ ስብሰባ የአገሩ ሁኔታ በሚፈቅደው መሠረት በጥበብ በተደረገ ጊዜ ወንድሞች በዩናይትድ ስቴትስ ታትመው የወጡትን አዳዲስ ጽሑፎች በራሳቸው ቋንቋ በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል። ተርጓሚዎች፣ አራሚዎችና ሌሎች ሠራተኞች በመቶ የሚቆጠሩ ገጾች ያሉትን አዲስ መጽሐፍ በወቅቱ ለማድረስ ሲሉ ተጨማሪ ሰዓት ለመሥራት ፈቃደኞች ሆነዋል። እንዲሁም አንድ የዓለማውያን የማተሚያ ድርጅት የማተሙንና የመጠረዙን ሥራ በመሥራት ተባብሯል። በስብሰባው ላይ የተገኙ ሰዎች ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ በቀለም ያሸበረቁ ሥዕሎች ያሉትን ይህን መጽሐፍ በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል። ብዙ የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ለየይሖዋ ምስክሮች አክብሮት አላቸው። አብዛኛውን ጊዜ ተቃውሞ የሚመጣው ከሕዝበ ክርስትና ቄሶች ነው። በቅርቡ እገዳው እንደሚነሳ ተስፋ ይደረጋል።
በአሜሪካ አገሮችስ ሁኔታው እንዴት ነው?
በምዕራብ አገሮች የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች ችግሮቻቸውን ሁሉ በድፍረት በማሸነፍ በምሥራቅ ከሚገኙት ወንድሞቻቸው ጋር ተገናኝተዋል። የይሖዋም መንፈስ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ታግለው እንዲያሸንፉ ይረዳቸዋል። ለምሳሌ ያህል ሕገ ወጥ የዕፅ ምርትና ሽያጭ የሚቆጣጠሩ ቡድኖች በጫካ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱባት ከአንዲት የላቲን አሜሪካ አገር የመጣውን የሚከተለውን ሪፖርት እንውሰድ።
አንድ የምስክሮች ቡድን አንድ አውቶብስ ይዞ ወደ አንድ ገለልተኛ ክልል ይሄዳል። ከአውቶብሱ ሲወርዱ ከመንደሩ የምታስወጣ አንዲት ቀጭን መንገድ ተመለከቱ። ስለዚህ አምስቱ ወንድሞች እኅቶችንና ልጆችን በመንደሩ ውስጥ እንዲሠሩ ከመደቡ በኋላ ይህች ቀጭን መንገድ ወዴት እንደምትወስድ ለማየት ሄዱ። ከወንድሞች አንዱ እንዲህ በማለት ያጋጠማቸውን ይናገራል፦
“መንገዱን ይዘን ሁለት ሰዓት ሙሉ በእግር ስንጓዝ ያገኘነው በጣም ጥቂት ቤቶችን ነበር። ከዚያም በራሳቸው ላይ ቆብ ያጠለቁና የጦር መሣሪያ የታጠቁ ስምንት ሰዎች በድንገት ከጫካው ውስጥ ብቅ አሉ። አንዳንዶቹ መትረየስ ታጥቀዋል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ገጀራ ይዘዋል። ሳናውቀው ምን ውስጥ ገባን ይሆን? ሰዎቹ ምን እንደሚፈልጉ ጠየቅናቸው፤ ነገር ግን ጸጥ ብለን ምንም ሳንናገር ወደፊት እንድንሄድ ተነገረን። እንደተባልነው አደረግን! ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ውስጥ ሌላ ሁለት ሰዓት በእግራችን ከተጓዝን በኋላ ወደ አንድ የተመነጠረ ቦታ ደረስን። መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ያሉበት ካምፕ እንደሆ ግልጽ ነው። ጠመንጃ የታጠቁ ጠባቂዎች ዙሪያውን አሉ። በካምፑ መሀል አንድ በጥሩ ሁኔታ የተሠራ ቤት አለ። ወደዚህ ቤት እንድንሄድ ተደረግን።
“ቁጭ እንዳልን አንድ ሰው፣ (የካምፑ መሪ ይመስላል) አነጋገረን። ሰውዬው ንጹህ ልብስ የለበሰ፣ በጣም የተማረና የሚያስከብር ጠባይ ያለው ነው። ከወንድሞቻችን ወደ አንዱ በማመልከት ተነስ አለው። ከዚያም ‘ስለ ቡድናችን ምን ሐሳብ ትሰጣለህ?’ ሲል ጠየቀው። ወንድምም የት እንዳለን በሚገባ ስለተገነዘበ እንዲህ በማለት መለሰለት፦ ‘እርግጥ ስለናንተ ቡድን እናውቃለን፤ ይሁን እንጂ እኛ ለቡድናችሁም ይሁን ለማንኛውም ሌላ የፖለቲካ ድርጅት ምንም ዓይነት ዝንባሌ የለንም። እኛ እዚህ የመጣንበት ምክንያት በክርስቶስ ኢየሱስ ስለምተመራው የይሖዋ አምላክ መንግሥት ለመስበክ ብቻ ነው። ይህች መንግሥት በቅርቡ የዚህን የነገሮች ሥርዓት የፖለቲካ መንግሥታት በሙሉ ታጠፋለች። በዚህች ምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎችም በገነታዊ ሁኔታዎች ሥር አስደናቂ በረከቶችን ታመጣለች። ይህም ማንኛውም ሰው ወይም የሰዎች ቡድን ማድረግ የማይችለው ነገር ነው።’
“ሰውዬው አመለካከቱ ተለወጠ። ከዚያም ጥያቄዎችን ይጠይቅ ጀመረ። ‘ይህን ሁሉ የተማራችሁት ከየት ነው? እንደዚህ ለመናገር የተዘጋጃችሁት እንዴት ነው?’ ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ስለ ዓለም ሁኔታዎች ጥሩ ምስክርነት ለመስጠትና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ዘሮች ብቸኛ ተስፋ ለይቶ እንደሚናገር ለማስረዳት ቻልን። በተጨማሪም በሥልጣን ላይ የሚገኙትን ባለ ሥልጣኖች እንደምንታዘዝ ነገር ግን የእነሱ ትዕዛዝ ከይሖዋ ቃል ጋር የሚጋጭ ከሆነ በቅድሚያ አምላካችንን ይሖዋን እንደምንታዘዝ በመናገር ሮሜ ምዕራፍ 13ን አብራራን። በመጨረሻም የያዝናቸውን መጽሐፎች አበረከትንለት። ሦስት መጽሐፎችና አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ከወሰደ በኋላ እንዲያውም ይግረማችሁ ብሎ ለመጽሐፎቹ ገንዘብ ሰጠን። መጽሐፎቹን እንደሚያነባቸው ነገረን።
“ቀጥሎም መሪው ከጠባቂዎቹ ለአንዱ ከካምፑ እንዲያስወጣን ምልክት ሰጠው። በሌላ የምስክርነት መስክ ላገኘነው ድል ይሖዋን እያመሰገንን ወዲያው ወደመጣንበት ጉዟችንን ቀጠልን።”
ብጥብጥ በቦጫጨቃት አፍሪካ
በሩቅ ምሥራቅና በሩቅ ምዕራብ አጋማሽ ላይ የአፍሪካ አህጉር ትገኛለች። የጎሳ ውጊያ በዚያ የሚገኙትን አንዳንድ አገሮች ከባድ የብጥብጥ ማዕበል እንዲያናውጣቸው አድርጓል። በላይቤሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምስክሮች አሁንም በእርስ በርስ ጦርነቱ እየተነኩ ናቸው። ቀደም ሲል በጥቅምትና በኅዳር ወራት ውጊያ የሚደረገው በዋና ከተማዋና በአካባቢዋ ነበር። ከዚያም ውጊያው መላ አገሪቱን ስላዳረሰና ወንድሞች ከሌላው ሕዝብ ጋር ወደ ጫካ ስለሸሹ ጉባኤዎች በጠቅላላ ተበተኑ። ይሁን እንጂ ወንድሞች ቅንዓታቸው አልቀነሰም። በሚሸሹበት ጊዜ በደረሱበት ሁሉ ይሰብካሉ። ይህም በጣም ሩቅ በሆኑት የአገሪቱ ክፍሎች ትልቅ ምስክርነት እንዲሰጥ አስችሏል።
ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ወንድሞችን ያቀፈ አንድ ጉባኤ በአንድ የጎማ ተክል ማሳ ውስጥ ጊዜያዊ የመንግሥት አዳራሽ ሠራ። ውጊያው በሚካሄድበት አካባቢ በምትገኘው ከተማ ውስጥ የሚኖረው ሲቪል ሕዝብ በአየር ከሚደረገው የቦምብ ድብደባ ለማምለጥ ሲል ቀን ቀን በዙሪያው ወደሚገኘው ጎማ ለማምረት የሚያገለግል ሙጫ የሚሰጡ ዛፎች ወዳሉበት እርሻ ይሸሻል። በአካባቢው የሚገኙት ወንድሞች (ከዋና ከተማዋ ከሞንሮቪያ የተፈናቀሉትን አስፋፊዎች ጨምሮ) የመስክ አገልግሎት በማደራጀት የጎማ ሙጫ አምራች ዛፎች ሥር ተከልለው ለሚገኙት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ዘወትር ሲሰብኩ ይታያል። ወንድሞችና እኅቶች የአውሮፕላን ድምፅ በሚሰሙበት ጊዜ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ጉድጓድ ውስጥ ዘለው ይገባሉ። ከዚያ አደገኛው ሁኔታ ሲያልፍ ምስክርነታቸውን ይቀጥላሉ።
በጣም የሚያስገርመው ምንም እንኳን ይህ የእርስ በርስ ውጊያ ቢኖርም ወደ ማኅበሩ ሪፖርት የላኩት በሺህ የሚቆጠሩ የጉባኤው አስፋፊዎች በመስክ አገልግሎት ያሳለፉት አማካኝ ሰዓት 18.1 ሲሆን በየወሩ 3,111 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም ተመርተዋል።
በአፍሪካ ባለፉት አራት ዓመታት በ18 አገሮች በይሖዋ ምስክሮች ሥራ ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነስቷል። ደግሞም እጅግ በጣም የሚያስደስት ነገር ተፈጽሟል! በማላዊ በሚገኙት ምስክሮች ላይ በጥቅምት ወር 1967 ተጥሎ የነበረው እገዳ ነሐሴ 12 ቀን ተነስቷል። በሕቡዕ ይካሄድ የነበረው የምስክሮቹ ስብከት ምን ጊዜም ጥሩ ውጤት ያስገኝ ነበር። አሁን ግን ምስክሮቹ ነፃነት ስላገኙ እንደልብ ሊሠሩ ይችላሉ። እርግጥ በጨቋኞች በግፍ የተገደሉትን ብዙ ውድ ጓደኞቻቸውን ለማየት ትንሣኤን መጠበቅ አለባቸው።
በሞዛምቢክ የተደረገው የሰላም ስምምነት ከጥቅምት 4, 1992 ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል። ላለፉት 16 ዓመታት ሲካሄድ በነበረው አስከፊ ጦርነት ምክንያት ቀድሞ የማይደረስባቸው የነበሩ የአገልግሎት ክልሎች አሁን እየተሰበከባቸው ነው። በካሪይኮ አካባቢ ላለፉት ሰባት ዓመታት ከድርጅቱ ጋር የነበራቸው ማንኛውም ዓይነት ግንኙነት ተቋርጦባቸው ከነበረው ከ375 ወንድሞችና እኅቶች ጋር ግንኙነቱ እንደገና እንዲቀጥል ማድረግ ተችሏል። የአውራጃው ዋና ከተማ በሆነችው ቀድሞ አንድ ማጎሪያ ካምፕ በሚገኝባትና የይሖዋ ምስክሮችን አቋም ለማስለወጥ “የመልሶ ማስተማሪያ” ማዕከል በነበረችው በሚላንጌ የልዩ ስበሰባ ቀን ተደርጓል። አብዛኞቹ የይሖዋ ምስክሮች ከማላዊ የመጡ ስደተኞች ነበሩ። በሚላንጌ ለይሖዋ ምስክሮች ጥሩ አቀባበል ያደረገውን የከተማውን አስተዳዳሪ ጨምሮ አስገራሚ ብዛት ያላቸው 2,915 ሰዎች በስብሰባው ላይ ተገኙ። ስለዚህ የቀድሞው “የመልሶ ማስተማሪያ” ማዕከል አሁን ለአንድ ቀን የመለኮታዊ ትምህርት ማስተማሪያ ማዕከል ሆኖ ዋለ።
አንድ ሚሲዮናዊ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “በተቴ አውራጃ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የሚገኙትን ወንድሞቻችንን በተመለከተ አንድ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ተወካይ አንድ አስደሳች የሆነ አስተያየት ሰንዝረዋል። የይሖዋ ምስክሮች ከሌሎቹ ቡድኖች ተለይተው የራሳቸውን ካምፕ እንዳደራጁ ተናግረዋል። እሳቸውም ‘በሚገባ የተያዘ ካምፕ የእነሱ ብቻ ነው’ በማለት ከተናገሩ በኋላ ‘የይሖዋ ምስክሮች ንጹሆች፣ የተደራጁና የተማሩ ናቸው’ ሲሉም አክለው ተናግረዋል። ከዚያም እኔ ራሴ ተዘዋውሬ ለመመልከት እንድችል በአውሮፕላን ይዘውኝ ለመሄድ ግብዣ አቀረቡልኝ። በአየር ላይ እንዳለን አውሮፕላን አብራሪው ሁለት ካምፖችን አመለከተኝ። አንደኛው ያረጀና ቆሻሻ እንዲሁም ያለምንም ፕላን እርስ በርሳቸው በጣም ተጠጋግተው የተሠሩ የጭቃ ቤቶች ያሉበት ነው። ሌላው ካምፕ ደግሞ በመካከላቸው ባለው መንገድ በመስመር ተከፋፍለው በጥሩ ፕላን የተሠሩ ቤቶች ያሉበት ነው። ቤቶቹ ግቢያቸው ተጠርጎ ንጹህ ሆነው ይታያሉ። እንዲያውም አንዳንዶቹ እቤት በተሠሩ ቀለሞች የተጌጡ ናቸው። አውሮፕላን አብራሪው ‘ገምት የእናንተ ሰዎች የሚኖሩበት የትኛው ይመስልሃል?’ አለ። ለእኔ በዚህ ካምፕ ያሉትን ወንድሞች ማግኘቱ በጣም የሚያስደስት ነበር። በአሁኑ ጊዜ በዚህ የምስክሮቹ መንደር ውስጥ ስምንት ጉባኤዎች ይገኛሉ።”
“በንስር አገር” ውስጥ
ይህ የአሜሪካ አርማ ሆኖ የሚያገለግለው ንስር አይደም። በምሥራቁና በምዕራቡ ዓለም መካከል አንዷ የአውሮፓ አገር አልባኒያ ትገኛለች። በአገሩ ቋንቋ ስሟ ሺኪፔሪያ ሲሆን ትርጉሙም “የንስር አገር” ማለት ነው። በዚህ አገር በይሖዋ ምስክሮች ላይ ተጥሎ የነበረው ጭካኔ ያለበት የ50 ዓመት እገዳ በቅርቡ ተነስቶላቸዋል። በዚህ አገር የሚገኙት የይሖዋ ምስክሮችም ባገኙት የአምልኮ ነፃነት አማካኝነት በምሥራቅና በምዕራብ ካሉት ወንድሞቻቸው ጋር ለመገናኘት ችለዋል። በዚህ አገር የሚገኙ ወንድሞች በእርግጥም ‘ዘመኑን እየዋጁ’ ነው። (ኤፌሶን 5:16) በዋና ከተማዋ በቲራና በአልባኒያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነው ትልቅ ስብሰባ መጋቢት 21 እሁድ በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ ተደረገ። ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ 75 ፈቃደኛ ምስክሮች በጣም ቆሽሾ የነበረውን አዳራሽ በማጽዳት ብሩህና ንጹህ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አደረጉት። የቲያትር ቤቱ አስተዳደር በጣም ተገረመ። አዳራሹን ካጸዱት 75 ፈቃደኛ ሠራተኞች መካከል የተጠመቁት 20 የሚሆኑት ብቻ ናቸው።
የአየሩ ጠባይ በጣም ተስማሚ ነበር። የውጭ አገር ልዑካን ሲመጡ እየተጨባበጡና እየተቃቀፉ ሰላምታ መለዋወጡ የልዩ ስብሰባውን ቀን በጣም ልዩ አደረገው። ወንድም ናሾ ዶሪ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ የመክፈቻውን ጸሎት አቀረበ። ወንድም ናሾ የተጠመቀው በ1930 ሲሆን አሁን ዓይኑ በደንብ አያይለትም። ፕሮግራሙ የቀረበው በአልባኒያ ቋንቋ ሲሆን አብዛኛው የፕሮግራሙ ክፍል የቀረበው በውጭ አገር ልዩ አቅኚዎች ነው። ጎብኚ የሆኑት የግሪክ ወንድሞች በአዳራሹ ውስጥ ወዳሠሩት ትልቅ ገንዳ 41 አዲስ ወንድሞችና እኅቶች እየሄዱ ሳሉ ለስብሰባው ሲባል ወደ አልባኒያ ቋንቋ ከተተረጎሙት ስድስት መዝሙሮች መካከል “ራስን ለአምላክ መወሰን” የተባለው መዝሙር በ585 ተሰብሳቢዎች ተዘመረ። እንዴት ያለ ትልቅ ለውጥ ነው! ቀደም ባለው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ መገኘት ማለት ከባድ ሥራ ወዳለበት ካምፕ የሚያስወስድ ነበር። በስብሰባዎች መገኘት የሚችሉት ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ብቻ ነበሩ።
ስብሰባው በተደረገ ማግስት የመጠበቂያ ግንብ ቢሮ ከቲያትር ቤቱ አስተዳዳሪ አንድ የስልክ ጥሪ ደረሰው። ይህ አስተዳዳሪ ብዙውን ጊዜ ቲያትር ቤቱን እነማን እየተጠቀሙበት እንዳሉ ለማወቅ አይከታተልም። ይህ የምክትል አስተዳዳሪው ሥራ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ አለ፦ “የደወልኩት ላመሰግናችሁ ነው። ይህ ቦታ እንዲህ ንጹህ ሆኖ አይቼው አላውቅም። እንዴት ንጹህ እንደሆነ መግለጽ ያስቸግረኛል። ትናንትና በቲያትር ቤታችን ላይ ንፋስ ከሰማይ ወርዶ ሙልጭ አድርጎ ያጸዳው ነው የሚመስለው። በቲያትር ቤቱ አዳራሽ ለመጠቀም ከፈለጋችሁ እባካችሁ በማንኛውም ጊዜ ተመልሳችሁ ኑ። ለእናንተ ቅድሚያ እንሰጣችኋለን። ምነው በየሦስት ወሩ እየመጣችሁ ያለምንም ኪራይ በነፃ በተጠቀማችሁበት!”
ምስክሮቹ በሚገባ ተጠናክረው ይሖዋን እያመሰገኑ ወደየከተሞቻቸው ተመለሱ። ከዚያም ለኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ። ከ15 ቀን በኋላ ሐሙስ ሚያዝያ 6 በሰባት ቦታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የመታሰቢያው በዓል በግልጽ ተደረገ።
ቤራት በተባለች ከተማ የተሰብሳቢዎች ብዛት ወደ 170 ደርሶ ነበር። ይህም የአካባቢውን ቄስ በኃይል አስቆጣው። በቤራት ከሚገኙት 33 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ውስጥ 21 በልዩ ስብሰባው ላይ የተጠመቁ ናቸው። በቤራት ከተማ በመታሰቢያው በዓል ላይ 472 ተሰብሳቢዎች እንደተገኙ ሪፖርት ተደርጎልናል። የሌሎች ከተሞች የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች ቁጥርም ከፍተኛ ነበር። ይህ ውጤት በአብዛኛው የተገኘው ልዩ አቅኚዎች በሚሰጡት ጥሩ አመራር ምክንያት ነው።
አንድ ትልቅ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሚገኝባትና ከአልባኒያ ከተሞች ሁሉ በጣም ብዙ ካቶሊኮች በሚኖሩባት በሽኮደር ከተማ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አንድ ወርሃዊ መግለጫ እያተመ ማውጣት ጀመረ። እያንዳንዱ እትም “የይሖዋ ምስክሮችን እንዴት መሸሽ እንደሚቻል” ይናገራል። የመጨረሻው እትም “የይሖዋ ምስክሮች ሽኮደርን ወርረዋታል!” ይላል። በዚያ የሚገኘው የሁለት ምስክሮች ታላቅ ሠራዊት ሥርዓታማና ቁምነገረኛ የሆኑ 74 ሰዎችን ወደ መታሰቢያው በዓል እንዲመጡ አድርጓል። የመታሰቢያውን በዓል ንግግር ከሰሙ በኋላ 15 ቤተሰቦች የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። አራት የምስክሮች ሠራዊት በሚገኝባት በሌላዋ ከተማ በዱረስ 79 ሰዎች ተሰብስበዋል። ይህም በጣም የሚያስደንቅ ቁጥር ነው።
ምስክሮቹን በድንጋይ ደብድበው ለማባረር በዛቱት የካቶሊክ ወጣቶች ተቃውሞ ምክንያት ተራራ ላይ በምትገኘው በካልሜቲ አይ ፎገል መንደር የሚደረገው የመታሰቢያው በዓል ስብሰባ በአካባቢው በሚገኝ በአንድ ወንድም ቤት ተደረገ። በዚያም 22 ሰዎች ስብሰባውን በሰላም ተከታትለዋል። በዚህ ቡድን ውስጥ አምስት አስፋፊዎች ሲኖሩ ሦስቱ ቀደም ሲል በተደረገው ስብሰባ ላይ የተጠመቁ ናቸው።
በቨሎር ከተማ ሁለት ወጣቶች አንድ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂ አግኝተው ካነበቡ በኋላ “በመጠበቂያ ግንቡ ውስጥ በተማርነው እውነት መሠረት አሁን ራሳችንን እንደ ይሖዋ ምስክሮች አድርገን እንቆጥራለን። እባካችሁ የሚረዳን ሰው ላኩልን!” ሲሉ ጽፈው ነበር። ሁለት ልዩ አቅኚዎች እዚያ እንዲያገለግሉ ተመደቡ። ደብዳቤውን ከጻፉት ወጣቶች አንዱ ወዲያው አስፋፊ ሆነ። ይህም ወጣት በቨሎር ከተማ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከተገኙት 64 ተሰብሳቢዎች መካከል በመሆኑ ተደስቷል።
በዩናይትድ ስቴትስ እውነትን የሰማ የአልባንያ ተወላጅ የሆነ አንድ ወንድም በ1950ዎቹ ዓመታት ወደ ትውልድ ከተማው ወደ ግሬካስተር ተመለሰ። በዚያም እስከሞተበት ጊዜ ድረስ የተቻለውን ያህል አገልግሏል። የእውነትን ዘር በልጁ ልብ ውስጥ ዘራ። እገዳው ሲነሳ ይህ ልጅ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሚረዳው ሰው እንዲልክለት ጠየቀ። በስተሰሜን በኩል በአንድ መንደር ውስጥ የሚኖር ሌላ ፍላጎት ያለው ሰውም የሚረዳው ሰው እንዲላክለት ጠየቀ። ስለዚህ አራት ልዩ አቅኚዎች ወደዚያው ተላኩ። በመታሰቢያው በዓል ማግስት ረቡዕ ጠዋት ከአራቱ ልዩ አቅኚዎች አንዱ በቲራና ወደሚገኘው የማኅበሩ ጽፈት ቤት ስልክ ደውሎ እንዲህ አለ፦ “የይሖዋ መንፈስ እንዴት እየሠራ እንዳለ ሳልነግራችሁ ዝም ማለት አልቻልኩም። በጣም ተደስተናል። የመታሰቢያው በዓልም የተሳካ ነበር!” ሰባቱን የመንግሥቱ አስፋፊዎች የያዘውን ቡድን ጨምሮ የተሰብሳቢዎች ቁጥር 106 ነበር።
በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙት ጠቅላላ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ስንት ነበር? 30 አስፋፊዎች በነበሩበት በ1992 የተሰብሳቢዎች ቁጥር 325 ነበር። አሁን በ1993 131ቹ አስፋፊዎች 1,318 ተሰብሳቢዎች ነበሯቸው። በሁለቱም ዓመታት የተሰብሳቢዎች ቁጥር የአስፋፊዎችን ቁጥር አሥር እጥፍ ያህል ነበር። እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ‘ታናሹ ሺህ’ ሲሆን ማየት እንዴት ያስደስታል!—ኢሳይያስ 60:22
“አውታሮችሽን አስረዝሚ”
የይሖዋ ምስክሮች የስብከት ሥራ በሁሉም የምድር ማዕዘናት እየሰፋ በሄደ መጠን የሚከተለው ጥሪ ያስተጋባል፦ “የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፣ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቆጥቢ፤ አውታሮችሽን አስረዝሚ ካስሞችሽንም አጽኚ። በቀኝና በግራ ትሰፋፊያለሽና።” (ኢሳይያስ 54:2, 3) ይህ በአምላክ “ታላቅ የመገናኛ ድንኳን” ላይ የሚደረግ መስፋፋት በአምላኪዎቹ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተመስሏል። ይህም በእርግጥ በምሥራቅ አውሮፓ በተለይም በቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት ውስጥ ባሉ አገሮች በግልጽ ሲፈጸም ይታያል። ይሖዋ አገልጋዮቹ ይጨቆኑ በነበሩባቸው አሥርተ ዓመታት ወቅት ደግፎ ካቆያቸው በኋላ አሁን ድርጅቱን ለማስፋትና ለማጠናከር ለምስክሮቹ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ኃይል እየሰጣቸው ነው።
በሩስያ ሞስኮ በሚገኘው የሎኮሞቲቭ ስታዲየም ከሐምሌ 22–25 በተደረገው ስብሰባ የተሰብሳቢዎች ከፍተኛ ቁጥር 23,743 ደርሶ ነበር። ይህም ባለፈው ዓመት ከተደረጉት “መለኮታዊ ትምህርት” ብሔራት አቀፍ ተከታታይ ስብሰባዎች ጎላ ብሎ የሚታይ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት እንኳ ይህ ይቻላል ብሎ ያሰበ ማን ነበር? አሁን ግን ይህ እውን ሆኖአል! ከጃፓንና ከኮሪያ ከ1,000 በላይ ወንድሞችና እኅቶች መጥተዋል። ወደ 4,000 የሚጠጉት ደግሞ ከዩናይትድ ስቴትስና ከካናዳ እንዲሁም ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ደግሞ በደቡብ ፓሲፊክ፣ በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በሌሎች አካባቢዎች ከሚገኙ ከ30 በላይ ከሚሆኑ አገሮች የመጡ ናቸው። በእርግጥም ምሥራቅና ምዕራብ እየተገናኙ ነው። እነዚህ ሁሉ ከ15,000 በላይ ከሚሆኑት የሩስያ ወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸው ጋር በነፃነት መቀላቀላቸው እንዴት የሚያበረታታ ነው! ደስታቸው ከልክ ያለፈ ነበር።
የሚያስገርም ብዛት ያላቸው 1,489 አዲስ ምስክሮች ተጠመቁ። ጥምቀቱ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ በመጀመሪያ ገጹ ላይ ይዞ የወጣውን ግሩም ፎቶ ግራፍ ጨምሮ በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በዓለም ዙሪያ ተላልፏል። ምንም እንኳን በጥምቀቱ ጊዜ እንደ ነጎድጓድ የሚያስተጋባ ጭብጨባ ቢደረግም ተናጋሪው ስብሰባው እንዲህ እንዲሳካ የረዱትን 4,752 ፈቃደኛ ሠራተኞችና የመንግሥት ባለ ሥልጣኖች ካመሰገነ በኋላ “ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋን እናመሰግናለን” ብሎ በተናገረበት የመጨረሻ ንግግር ወቅት የተሰማው ጭብጨባ ከዚያ የበለጠ ደማቅ ነበር። አዎን፣ ከኦርቶዶክስ ሃይማኖተኞች የተቃጣውን ጠንካራ ተቃውሞ ይሖዋ ገቶታል። እንዲሁም ስብሰባውን አስደሳች ለማድረግ የሚያስችለውን አስፈላጊውን ኃይል ሰጥቷል።
ይሁን እንጂ የዩክሬይን ከተማ በሆነችው በኪየቭ ከነሐሴ 5–8 ከዚህ የበለጠ ነገር ተከናውኗል። አሁንም ፈቃደኛ ሠራተኞች ስታዲየሙን ሙሉ በሙሉ አጸዱት። ይህ እጅግ በጣም ሰፊ የሆነ የመንግሥት አዳራሽ 64,714 የደረሰ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎችን ቁጥር ይዞ ነበር። አሁንም ምስክሮቹ ከምሥራቅም ከምዕራብም እንዲሁም በሁለቱ መሐል ካሉት ከሁሉም የዓለም ክፍሎች መጡ። ዋና ዋና ንግግሮች ወደ 12 ቋንቋዎች ተተረጎሙ። በአውሮፕላን፣ በባቡርና በአውቶቡስ የመጡትን 53,000 የሚሆኑ ልዑካን ከባቡር ጣቢያና ከአውሮፕላን ማረፊያ መቀበልና ወደሚያርፉባቸው ሆቴሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የግል መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ወደ ጀልባዎች መወሰድ ነበረባቸው። ሁሉም ነገር የተከናወነው በአነስተኛ ወጪ በተሳካና ቅልጥፍና በተሞላበት ቅንጅት ነው። ይህም ከከተማው ፖሊስ አድናቆትንና ምስጋናን አትርፏል።
አስደሳች ከሆነው የስብሰባው ፕሮግራም ሁሉ ከፍተኛውን ደረጃ የያዘው በአጠቃላይ ሁለት ሰዓት ተኩል የፈጀው የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ነው። 7,402 አዲስ ወንድሞችና እኅቶች ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በጥምቀት አሳዩ። በዚህ ጊዜ ጭብጨባው በሰፊው ስታዲየም ዙሪያ አስተጋባ። ይህም በ1958 በኒው ዮርክ ከተማ 253,922 ሰዎች በተሰበሰቡ ጊዜ ከተመዘገበው 7,136 ከፍተኛ የተጠማቂዎች ቁጥር የሚበልጥ ነው።
ይህ የፍርድ ዘመን ወደ ፍጻሜው እየገሰገሰ በሄደ መጠን በግ መሰል ሰዎች ከምሥራቅ፣ ከምዕራብ እንዲሁም ‘በጣም ሩቅ ከሆነው የምድር ዳር’ እንኳ ሳይቀር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ በአንድነት እየተሰበሰቡ ነው። በእርግጥም ‘ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም’ የተውጣጡ ሰዎች የይሖዋን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በመከናወን ላሉት ነገሮች ሁሉ መሠረት በሆነው በክቡር የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ያላቸውን እምነት በማወጅ ከመንፈሳዊ የአምላክ እስራኤል ጋር እየተባበሩ ናቸው።—ሥራ 1:8፤ ራእይ 7:4, 9, 10
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በሞስኮ እና በኪየቭ ምሥራቅ ከምዕራብ ጋር ሲገናኝ